አድባራተ ጥበብ

ታደሰ ወርቁ፣ ብዙ የማያወራ ግን ብዙ የሠራ ጠቢብ

 “ታደሰ ወርቁ ቂም የማይዝ፣ ማንም ሰው በእሱ ፊት ስለሌላ ሰው አንስቶ እንዲያወራ የማይፈቅድ ንፁህ ሰው ነው:: በኪነጥበቡ ዓለም ከሠራቸው ሥራዎች የበለጠ የምኮራበት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብም የሚኮራበት ሥራ “ሕዝብ ለሕዝብ” ነው:: ያን በመሰለ ሁኔታ አዘጋጅቶ፣ ያን የመሰለ የጥበብ ሥራ አደራጅቶ፣ ያን ሁሉ ሰው ሰብስቦ፣ ለዚያ ሁሉ ሰው የሚሆን እንቅስቃሴ ፈጥሮ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ስጦታ ያበረከተ ሰው ነው::” አበው ከያኒ ደበበ እሸቱ::

“ታደሰ የፍቅር ሰው ነው፣ ሥራዎቹም ከዚህ ይመነጫሉ:: ሙያውን በጣም ይወዳል:: ታዴ ባለበት ቦታ ሁሉ ሳቅና ደስታ አለ:: ታደሰ የደግነት ምሳሌ ነው:: ደግነት ቁሞ ሲሄድ ማየት ከፈለግክ ታዴን ማየት ብቻ ነው:: ፍቅር ቆሞ ሲሄድ ማየት ከፈለግክ ታደሰን ማየት ነው::” አበው ከያኒ ተክሌ ደስታ::

ታደሰ ወርቁ ሲሠራ እንጂ ሲያወራ የማይታይ አመለ ሸጋ ባለሙያ ነው:: ትንሽ ነገር ሠርተው ወደሚዲያ የሚሮጡ፣ ወይም ባልሠሩት ሥራ የሚያጌጡ፣ የሌሎችን ሥራ እየሠረቁም እየነጠቁም ያለሃፍረት የሚኖሩ ብልጣ ብልጦች ባሉባት ሃገራችን ታደሰ ብዙዎች እንደሚመሰክሩለት ለሥራው እንጂ ለስሙ ተጨንቆ አያውቅም:: ይህን ቃለመጠይቅ ለማድረግ እንኳ የወሰደብኝን ጊዜ የማውቀው እኔ ነኝ:: በመጨረሻ የተስማማነውም የእሱን አይነት ባለሙያዎች ያለፉበትን የጥበብ ሕይወት ቢያጋሩ አዲሱ ትውልድ ይጠቀማል በሚል ነው:: በዚህ አጋጣሚ አበው ከያኒ ደበበ እሸቱ ከፍ ብሎ የጠቀሰው የሕዝብ ለሕዝብ ኢትዮጵያ -አደይ አበባ የባህል ትርኢትን- በተመለከተ በድርሰቱ ባለቤትነት ዙሪያ ስለሚነሳው ጉዳይ ታደሰ ለመጀመሪያ ጊዜ መልስ ሰጥቶበታል::

ታደሰ ጥር 27 ቀን 1941 ዓ.ም፣ ሚዛን ተፈሪ ነው የተወለደው:: ያደገው ደግሞ አዲስ አበባ ውስጥ ነው:: ገና በልጅነቱ እናቱ ወ/ሮ የሸዋሀረግ ወ/ አረጋይና አባቱ አቶ ወርቁ ባልቻ በመለያየታቸው እህቱና እሱ ከክርስትና አባቱ ጋር መኖር ጀመሩ:: የክርስትና አባቱ ፊታውራሪ ዓለማየሁ ፍላቴ በወቅቱ የሚዛን ተፈሪ ገዥ ስለነበሩ አስተማሪ ተቀጥሮላቸው ቤት ውስጥ ይማሩ ነበር:: ዘመናዊ ትምህርት ቤት ገብተውም ለአንድ ዓመት ያህል ተምረዋል:: ሆኖም የእናታቸው ናፍቆት በጣም ያስቸግራቸው ነበር:: አንድ ጊዜ የክርስትና አባቱ ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ ይዘዋቸው መጡና ከእናታቸው ጋር የሚገናኙበት አጋጣሚ ተፈጠረ:: በዚያውም ቀሩ:: ከእናቱ ጋር ሆኖ መሳለሚያ አካባቢ በሚገኘው ልዑል ወሰን ሰገድ ት/ቤት እስከ ስድስተኛ ክፍል ተማረ:: ከዚያ የ1953ቱ የታህሳስ ግርግር መጣ:: ትምህርት ቤቶች ተዘጉ:: ቤተሰቦቹም ከቤት እንዳይወጣ ፈለጉ:: ታደሰም ትዕዛዛቸውን ማክበር ነበረበት:: በአጋጣሚ የነሱን ቤት ተከራይቶ የሚኖር የአስር አለቃ ታምሩ የሚባል ወጣት መርማሪ ፖሊስ ነበር:: ታዲያ አንድ ቀን ለራሱ ጉዳይ ወደ ኮልፌ ሙዚቃ ክፍል ሲሄድ ታደሰን ይዞት ይሄዳል:: እዚያ ሙዚቀኞቹን ይመለከታል፤ የፋንፋር ባንድ አለው፣ ኦርኬስትራው ዘመናዊና የተሟላ ነው:: የቴያትር ክፍልም አለው:: አቶ ተስፋዬ አበበ የግጥምና ዜማ ደራሲ ነው፣ የቴያትር ክፍሉም ኃላፊ ነበር:: ከዚያች ዕለት ጀምሮ የታደሰ ልብ ወደ ሙዚቃው አዘነበለ:: እንደአጋጣሚም ሆኖ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ወጣቶችን ለመቅጠር ማሰባቸውን ይሰማል:: ከዚያ ቤተሰቡን ሳያማክር ይሄድና ይመዘገባል:: ተቀበሉት:: እዚያው ካምፕ ውስጥ ሆኖም መሰልጠን ጀመረ:: መጀመሪያ ወታደራዊ ስልጠና ወሰደ:: ቀጥሎ የክላርኔት አጨዋወትን ተማረ:: መምህሩ ሚስተር ሃጎፕ የሚባሉ ሲሆኑ ነርሲስ ናልቫንዲያንም የኦርኬስትራው መሪ ነበሩ::

 ታዛ:- ከዚያስ? ቀሪውን ታሪክ ከታደሰ ወርቁ ጋር ቨርጂኒያ በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ካደረግነው ቃለ መጠይቅ ትረዳላችሁ ብለን ተስፋ እናደርጋለን::

ታደሰ፡- ከዚያ የኦርኬስትራው ቡድን ለምን አይጠናከርም?  የሚል ነገር ይነሳል:: ስለዚህ የዳንስ ስልጠናም ይሰጠን ጀመር:: አሰልጣኛችን ኮሎኔል ሺፈራው ከበደ የሚባል መኮንን ነበር:: ሌላም አቶ ከበደ ተካ የሚባል አሰልጣኝ ነበረን:: ሌሎችም እንዲሁ:: ብዙም ሳይቆይ ሴቶችም በዳንስ መሰልጠን አለባቸው ተባለና መጡ:: የስድስት ወር ስልጠናቸውን ሲጨርሱ አብረን መድረክ ላይ መሥራት ጀመርን:: ያን ጊዜ ትርኢቶች በአብዛኛው የሚቀርቡት በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የልደት አዳራሽ ነበር:: የፖሊስ ኦርኬስትራ፣ የጦር ሠራዊት ኦርኬስትራ፣ የክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራና አንዳንዴም ኦርኬስትራ ኢትዮጵያ ሥራቸውን ያቀርቡ ነበር:: በዚህ መልኩ ለሁለት ዓመት ያህል ከሠራሁ በኋላ የወታደራዊው ዲስፕሊን ጥብቅነት ስላስጠላኝ ወደ ቤተሰቦቼ ሄድኩና በዚያው ቀረሁ:: ታዲያ ይህን ያወቀው አበራ ፈይሳ የሚባል ባለሙያ፣ በወቅቱ በብሔራዊ ቴያትር የ”ለ” ቡድን ኦርኬስትራ ተጫዋች የነበረ፣ አሁን እዚህ አገር ያለ፣ ቤቴ ድረስ ይመጣና “እኛ ጋ እኮ በጣም በጣም ትፈለጋለህ፣ አናግረው ብለውኝ ነው የመጣሁት:: ለምን አብረን ሄደን አታነጋግራቸውም?” ይለኛል:: ያኔ የ”ለ” ቡድን ኦርኬስትራ ኃላፊ ደግሞ ሟቹ አቶ ፀጋዬ ደባልቄ ነበር::

ከእናቱ ወ/ሮ የሸዋሀረግ ወ/አረጋይ ጋር

ታዛ:- መቼ ነው ዘመኑ? ከአብዮቱ በፊት ነው?

ታደሰ፡- አዎ! በሃምሳ ስምንት ዓ.ም አካባቢ ይመስለኛል::

ታዛ:- ስለዚህ በፖሊስ ኦርኬስትራ ውስጥ ለአምስት ዓመት ያህል ቆይተሃል ማለት ነው?

ታደሰ፡– ለአራት ዓመት፣ ምክንያቱም ሥልጠናውን ጨርሼ በሃምሳ አራት ዓ.ም ነው የጀመርኩት:: ብሔራዊ ቴያትር ተቀበሉኝና “የ “ሀ” ቡድን ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ሣህሉ ነው:: አንተ ደግሞ የ “ለ” ቡድን ኃላፊ ሁን” ብሎ አቶ ፀጋዬ ደባልቄ አናገረኝ:: አበራ አቅርቦኝ ማለት ነው:: እኔም ምንም ችግር የለውም ብዬ ተስማምቼ ስወጣ አቶ ተስፋዬ ሣህሉ ከማዶ እየመጣ፣ “በእኔ ሥራ፣ በእኔ እንጀራ ልትገባ፣ ምን አደረግሁህ?” ሲለኝ ደነገጥኩ:: እኔ ምንም የማውቀው ነገር የለም::

ታዛ:- ትተዋወቁ ነበር ከዚያ በፊት?

ታደሰ፡- ኧረ በፍፁም! ብቻ ጨለም ያለ ቦታ ሲሆን ከመድረኩ አካባቢ ነው:: አቶ ፀጋዬ ደባልቄ ያው የተከበረ ሰው ነው፣ ይፈሩታልም:: እና “ሰሞኑን ናና ሥራህን ጀምር” ብሎ ተሰናብቶኝ ገና ከመውጣቱ ነው:: እና አቶ ተስፋዬን ስሰማ በቃ ቀፈፈኝ:: ወጥቼ ሄድኩ:: ከዚያ እነጥላዬ ገብሬና ሌሎች የ”ለ” ቡድን የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋቾች ተከተሉኝና “እንዳትሰማው፣ መምጣትና መሥራት አለብህ” አሉኝ:: እኔ ግን ስለደበረኝ ቤቴ ሄጄ አልተመለስኩም:: ከዚያ እንደገና አፈላልገው፣ እላይ ፊት በር ከእናቴ ጋር ነበርኩ፣ እዚያ ድረስ አጠያይቀው መጥተው “ምነው? ምነው? እንዴት እንዲህ ታደርገናለህ? እኛም እኮ ጊዜ እየሄደብን ነው” ብለው አናገሩኝ:: እሽ ብዬ ሄድኩ:: ሆኖም ጭቅጭቁን ፈሩ መሰል “ግድየለም አንተ ተወዛዋዥ ሆነህ ሥራ ጀምር” አሉኝ:: ያኔ ደግሞ እነ መኮንን አመና፣ እነ ኃይሉ፣ እነ አስናቀች ወርቁ፣ እነ ጠለላ ከበደ፣ እነ አየለች ይርዳው፣ እነ በለጡ አጥናፉና ብዙ ነባር ባለሙያዎች እየሠሩ ነበር:: የሚያስጠኑኝ ሁለት ሰዎች ተመደቡልኝ:: ልምዱ ስለነበረኝ ብዙ ጊዜ አልወሰደብኝም:: በዚያው ሳምንት ውስጥ ዜማዎች ሲመጡ የሚያዘጋጅ ሰው ጠፋ መሰለኝ “አንተ ለምን አትሠራልንም” አሉኝ:: እሺ ብዬ አንድ ሁለት ሙዚቃዎችን አቀነባበርኩላቸው:: ከዚያ በክፍል ኃላፊው ስም ተላለፈ:: እንግዲህ መሰረቅ፣ ክሬዲትህን ማስወሰድ ከዚያ ይጀምራል:: እኔ ግድ ስለሌለኝ ስሜትም አልሰጠኝ:: ቀስ በቀስ ሥራዬን እያዩ ሲሄዱ አቶ ተስፋዬን ተው አሉትና ከጥቂት ጊዜ በኋላ ቦታው ሙሉ በሙሉ ለእኔ ተሰጠኝ:: ሰዎችን እንድቀጥርም ተደረገ:: ነፍሱን ይማረውና አንዋር የሻነህ፣ ጌታነህ ኃይሌ፣ ይፍሩ ጎበና፣ እድሪስ አህመድና የመሳሰሉት በእኔ የኃላፊነት ዘመን የተቀጠሩና ያሰለጠንኳቸው ናቸው:: በዚያን ጊዜ ጀምበሬ በላይም ከእኔ ጋር ነበር:: ሥልጠናቸውን እንደጨረሱ ፕሮግራም ሰራንና ትርኢት አቀረብን:: ታዲያ ያኔ “ለ” ቡድኖች ተነሱና “እኛም የራሳችን የዳንስ ቡድን እንዲኖረን እንጂ ከሌላ ክፍል እየተዋስን ለመሥራት አንፈልግም፣ ይቀጠርልን” አሉ:: ተቀጠረላቸው:: የማዘጋጀቱን ሥራ እኔ መሥራት ጀመርኩ:: ከአንድ ሁለት ዓመት በኋላ ግን በበጀት እጥረት ይሁን በምን የውዝዋዜው ክፍል አንድ ላይ ይሁንና ለሁለቱም ክፍሎች ይሥራ ተባለ:: የተወሰኑ ባለሙያዎች ተቀነሱና አንድ ቡድን ሆነ:: እኔም ሙሉ ኃላፊነቱን ወስጄ መሥራት ቀጠልኩ::

ከልጁ ከትውልድ ጋር

 ታዛ:- ወደ ብሔራዊ ቴያትር መምጣትህ ምን ጨመረልህ?

ታደሰ፡- ወደ ብሔራዊ ቴያትር መምጣቴ በብዙ የውጪ ዝግጅቶች ለመሳተፍና አዳዲስ ሃሳቦችን ለማግኘት እንዲሁም ዓለማቀፍ ደረጃ ያላቸውን ሥራዎች ለመሥራት አስችሎኛል:: የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴያትር ከውጭ ትርኢት ይዘው የሚመጡ ቡድኖችንም ያስተናግዳል:: እነዚህ ቡድኖች የሚያቀርቡትን ትርኢት ስመለከት ውስጤ ልዩ ስሜት ይሰማኝ ጀመር:: በተለይም ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳደረብኝ ጆሊባ የሚባል ከጊኒ የመጣ ቡድን ነበር:: እንደውም ጃንሆይ ለእያንዳንዳቸው ወርቅ ነው የሸለሟቸው:: በእውነቱ የነሱ ትርኢት ነው ጭንቅላቴን የከፈተው:: በጣም አስደናቂ ነበር::

ታዛ:- ያልከው ትርኢት ባህላዊ ነው ዘመናዊ?

 ታደሰ፡- ባህላዊ ሆኖ በታሪክ ላይ የተመሠረተ ነው:: ዘመናዊ አቀራረብም ተደርጎበታል:: አያያዥ ተሠርቶለታል:: ወጥ የሆነ፣ ያለ ቋንቋ በእንቅስቃሴ ብቻ የተዘጋጀ ድርሰት ነበር:: እና ከኛ ሃገር ጋራ እያገናዘብኩ እንዳስብ አደረገኝ:: እነሱ ከሄዱ በኋላ የባህል ቡድናችን ይዘን ለመላው አፍሪካ ዝግጅት ወደአልጄሪያ ሄደን ነበር:: እነ አቶ ፀጋዬ ገ/መድኅን፣ ፀጋዬ ደባልቄ፣ ሳሙኤል ፈረንጅ፣ ሙላቱ አስታጥቄ፣ ከቴያትር እነ ሐይማኖት ዓለሙ፣ ወጋየሁ ንጋቱ፣ ደበበ እሸቱ ሁሉ ነበሩበት:: እዚያም ተካፈልንና ተጨማሪ ሃሳቦችን አገኘሁ:: በነገርህ ላይ ከሃገራችን ባለሙያዎች በጣም በጣም የማከብረውና የማደንቀው አቶ አውላቸው ደጀኔን ነው:: በጣም ብዙ የሠራ ሰው ነው:: እስካሁንም ድረስ ሥራዎቹ አሉ:: በዚያን ጊዜ ቪዲዮ አልነበረም:: ቴፕ ይዞ ወደገጠር እየሄደ፣ ትርኢቱን ተመልክቶና ሙዚቃውን ቀርፆ እያመጣ የሠራውን ሥራ ሳስበው በጣም የሚያስከብረው ነው:: ጋሼ አውላቸው በቴያትሩም ቢሆን እንደምታውቀው ብዙ የሠራ ታላቅ ባለሙያ ነበር::

ታዛ:- የስልጠና ዕድልስ አግኝተህ ታውቃለህ?

ታደሰ፡- አዎ፣ በ1961 ዓ.ም ሚስዝ አና ሜሪዳና ካርሎስ የሚባሉ እጅግ የታወቁ ባለሙያዎች ከሜክሲኮ መጥተው የሦስት ወር ሥልጠና ሰጥተውናል:: በወቅቱ እኔን ጨምሮ፣ አስናቀች ወርቁ፣ ጠለላ ከበደ፣ አልጋነሽ ታሪኩ፣ አሰለፈች በቀለ፣ አልማዝ ኃይሌ፣ ጀምበሬ በላይ፣ ሠይፈ አርኣያ፣ አበበች ገ/ሚካኤል፣ ኃይሉና ሺፈራው ወ/ ማርያም መሳተፋቸውን አስታውሳለሁ:: ከዚያም ወደሜክሲኮ ሄደን ትርኢታችንን አቅርበናል:: ከተለያዩ ባለሙያዎች ጋር በመላው ዓለም የኪነጥበብ ፌስቲቫል ላይ ተካፍለንም ጥሩ ተቀባይነት አግኝተናል:: በግሌ በሥልጠናውና በፌስቲቫሉ መሳተፌ ለበለጠ ሥራ እንድነሳሳ አድርጎኛል፤ አዲስ አቅጣጫ አመላክቶኛል:: አንዳንድ አሰልቺ የነበሩ ንቅናቄዎችን ለመለወጥም ረድቶኛል ማለት እችላለሁ::

ታዛ:- እስኪ አሁን ደግሞ ስለሠራሃቸው ሙዚቃዊ ድራማዎች እናውጋ:: “ትግላችን” ነው “ደማችን” የሚቀድመው?

ታደሰ፡- “ትግላችን” ነው የሚቀድመው:: ያው የጋሽ ጸጋዬ ገ/መድኅን ድርሰት ነው:: የቴያትሩ ርዕስ “ትንሣኤ ሠንደቅ ዓላማ” ነበር:: እንደ ማይም ዳንስ ድራማ ሆኖ ከሌሎች የቴያትር ሥራዎቹ ጋር የተቀናጀ ነበር:: በመጀመሪያ ኃላፊና አዘጋጅ ሆኖ የተመደበው ሐይማኖት ዓለሙ ነበር:: ሆኖም ብቻውን ሊሠራ ስላልቻለ እኔ ተጨመርኩና አብረን ማዘጋጀትና እንደ ተዋናይም ሆነን መሥራት ጀመርን:: ተፈራ አቡነወልድ፣ ሙላቱ አስታጥቄ፣ ነርሲስ ናልቫንዲያንና ዳዊት ይፍሩ በዝግጅቱ ላይ ተካፍለዋል:: ዓለም፣ (ዓለምፀሃይ ወዳጆ)፣ ወጋየሁ ንጋቱና ደበበ እሸቱም ነበሩበት:: የባህል ቡድኑ ደግሞ ሁለት መቶ የሚሆኑ ከአሶሳ፣ ከጋምቤላና ከሌሎችም አካባቢዎች የመጡ ተሳታፊዎችን ይዞ በጌታቸው አብዲና በአባተ መኩሪያ ተዘጋጀና ለመላው ዓለም ጥቁር ሕዝቦች ፌስቲቫል ወደ ናይጄሪያ አብረን ተጓዝን:: የሚገርምህ ከአዲስ አበባ ከመነሳታችን በፊት የሸኙን ጄኔራል ተፈሪ ባንቲ የደርጉ ሊቀመንበር ነበሩ:: “እንግዲህ እናንተ ሃገራችሁን ወክላችሁ ስለምትሄዱ የኢትዮጵያ ሙሉ አምባሳደሮች ናችሁ:: በአለባበሳችሁ፣ በአቀራረባችሁና በየዕለት ውሏችሁ ሃገራችሁን እንዳትረሱ” የሚል ምክር ሰጡን:: ልንመለስ ስንዘጋጅ ደግሞ መገደላቸውን ሰማንና አዘን:: እንግዲህ ከትርኢቱ ሌላ ሙሉ የኦርኬስትራ ባንድ ነበር የወሰድነው:: እና ከመደበኛው ትርኢት ባሻገር እንደ ጥላሁን ገሠሠና ሙሉቀን መለሰ ያሉ ታዋቂ ሙያተኞች የሚጫወቱበት መድረክም ነበረን:: በዚያ ላይ ኢትዮጵያ እንደመሪ አገር ሆና ልዩ ቦታ ነበር የተሰጣት:: በአቶ ማሞ ተሰማ አስተባባሪነት የተዘጋጀ ትልቅ ኤግዚቪሽንም ቀርቦ ኢትዮጵያን በሚገባ አስተዋውቋል::

ታደሰ በወጣትነት

ታዛ:- የተመልካቹን አቀባበልስ እንዴት አገኛችሁት?

ታደሰ፡- በጣም ጥሩ አቀባበል ነው ያገኘነው:: ከጠበቅነው በላይ ነበር ማለት ትችላለህ::

ታዛ:- አገር ቤት ተመልሳችሁስ አሳያችሁት?

ታደሰ፡- እንደውም:: ታስቦ ነበር፤ ሆኖም ነገ ዛሬ ሲባል ቆየና በዚያው ቀረ:: ባይሆን ኩባ ውስጥ የተዘጋጀ የወጣቶች ፌስቲቫል ነበር:: ሐይማኖት አንዳንድ ለውጦችን አደረገበትና እዚያ ሄዶ ታዬ:: የሆነ ሌላ ሃገርም የታዬ ይመስለኛል::

ታዛ:- እስኪ ስለደማችን ደግሞ ንገረን::

ታደሰ፡– ለአራተኛው የአብዮት በዓል መሰለኝ:: መቶ አለቃ ግርማ ነዋይ (ኋላ ብርጋዴር ጄኔራልና የፖሊስ ሠራዊት አዛዥ)፣ ያን ጊዜ በደርግ ጽ/ቤት ኃላፊነት ነበረው:: ሌላም አበበ በየነ የሚባል ሰው ነበር:: ሁለቱ ነበሩ አመራር የሚሰጡን:: እኔ በአዘጋጅነት ተመደብኩ እንደጀርመኑ መሪ ኤሪክ ሆኔከርና የኩባው ፊደል ካስትሮ ያሉ እንግዶች ከውጪ ስለሚመጡ ዝግጅቱ እንደማይም ዳንስ ድራማ አይነት እንዲሆን ነው የተፈለገው:: ያኔ ቁጭ ብለን ተነጋገርንና ዓለም (ዓለምፀሃይ ወዳጆ) ድርሰቱን እንድትሠራ አደረግን:: በለውጡ ሂደት የታዩ ጥሩም ሆኑ ክፉ ነገሮችን እየተመካከርን እንዲገቡበት ለማድረግ ሞከርን:: ግጥሙንም ታሪኩንም ጥሩ አድርጋ ሠራችው:: ከተለያዩ ቴያትር ቤቶችም ተጨማሪ ባለሙያዎች እንዲመጡ ተደረገ:: ሙዚቃውን አማኒ ኢብራሂም፣ ሰለሞን ሉሉና የፖሊሱ ኮሎኔል አያሌው አበበ ሆነው ሠሩት:: ከአማኒ ጋር በተለይ እያመሸን ቁጭ ብለን ነው የሠራነው:: “እዚህ ላይ ብስጭቱን የሚገልጽ አድርግልኝ፣ እዚህ ላይ ደግሞ ደስታውን፣ ወይ ቁጣውን”፣ እንደዚህ እያልኩ አማኒ ፒያኖ ይዞ በርከት ያሉ ዜማዎችን በማውጣትና ሙዚቃውን በመጻፍ ጉልህ አስተዋጽኦ አድርጓል:: ከዚያ ሠራን፣ መቼም ሩጫ ነው:: በመካከሉ ለበዓሉ አንድ አምስት ቀን ሲቀሩት የደርግ ባለሥልጣናት ዝግጅቱን ሊገመግሙ መጡ:: አይተው ሲጨርሱ አበዱ:: “የደርግ ሥራና ያስገኘው ውጤት የት አለ? እዚህ ውስጥ ለውጡን ሕዝቡ በትግሉ፣ በራሱ ጥረት እንዳመጣው አድርጋችሁ ያቀረባችሁት ልክ አይደለም:: ንጉሡን ማነው የጣለው? ደርግ አይደለም ወይ?” ብለው አበዱ:: እኔ፣ ደበበ እሸቱ፣ አበበ በየነ ሆነን ለመከራከር ብንሞክርም የሚሰማን አጣን::

ታዛ:- ያኔ ከመጡት የደርግ አባላት ውስጥ እነማንን ታስታውሳለህ?

ታደሰ፡- ዋናው የኮሚቴ ሰብሳቢ ኮሎኔል ፍስሐ ደስታ ነው:: ከእሱ በታች ያው ግርማ ነዋይ አለ:: ከዚያ አበበ በየነ አለ፣ በጣም ጥሩ ሰው ነው:: ጎበዝ ሰው:: አሁንም በሕይወት አለ:: በማግስቱ እዚያ መስቀል አደባባይ ወዳለ ቢሮ እኔ፣ ደበበ እሸቱና አበበ በየነ ተጠራንና ሄድን:: በቃ ጨፈጨፉን:: “ተማሪው ንጉሡን ጎትቶ ሲጥል ያሳያችሁት የደርግ አስተዋጽኦ የለም ወይ? የወታደሩን ውለታ የማታሳዩ ከሆነ ትርኢቱ ይቅር” አሉን:: ያን ሁሉ ጊዜ ለፍተን:: “አሻሽላችሁ የምትመጡ ከሆነ ፕሮግራም ይያዝላችኋል:: አለዚያ ይቀራል” አሉን:: አበበ በየነ ከእኛ ጎን ሆኖ ለመከራከር ሞክሮ ነበር:: አልሆነም:: በኋላ ግርማም፣ አበበም፣ ሌሎችም ይመክሩን ጀመር:: “በቃ ምንም መልስ አትስጡ፣ አይሆንም አትበሉ:: ዝም ብላችሁ እሺ እሺ በሉ” አሉን:: ሃሳባቸውን ተቀበልንና የተወሰነ ለውጥ አደረግን:: በፊት ተማሪው ነበር ከፊት የሚሰለፈው:: ከዚያ ወታደሩን ወደፊት አመጣንና ከኋላ የሚገፋው ግን የተማረው ወገንና ሕዝቡ እንዲሆን አደረግን:: ከዚያ የዘማቹን ሕዝብ ተሳትፎ፣ የወጣቱን እልቂት፣ በወቅቱ ተወዳጅ ከነበሩ ዜማዎች ጋር በማዋሃድ አቀረብነውና የተዋጣ ሥራ ሆነ:: ተወዳጅነትን አገኘ:: መሪዎቹም ወደ ብሔራዊ ቴያትር መጥተው አዩት:: በነገርህ ላይ ቅድም ዘንግቼ ያልነገርኩህ “ትግል ነው መፍትሄው” የሚል ዓለም የፃፈችው ድርሰትም ነበር:: በሴቶች የእኩልነት ጥያቄ ላይ ያተኮረ ነው:: አጠር ያለ ነው፣ ግን በጣም ውጤታማ ሥራ ነበር:: እና ጥሩ አድርገን በመድረክ ሠራነው:: እሱም በብሔራዊ ቴያትር ነው የቀረበው::

ታዛ:- አመሰግናለሁ ታዴ! እስኪ አሁን ደግሞ ስለ ሕዝብ ለሕዝብ ዝግጅት አጫውተን:: ሃሳቡ እንዴት ተፀነሰ? ዝግጅቱስ እንዴት ተከናወነ?

ታደሰ፡- የባህልና ስፖርት ጉዳይ ሚኒስትር ቋሚ ተጠሪ የነበሩት አቶ ዘውዴ ጉርሙ ቢሯቸው አስጠሩኝና እኔ በጀት አለኝ:: እስከ አሥር ሺህ ብር ልመድብልህ እችላለሁ:: እስኪ እባክህ አንድ ሁነኛ ነገር ሥራ:: መንግስት በጣም ይፈልግሃል፤ እስኪ ተዘጋጅበትና ንገረኝ ይሉኛል::

 ታዛ:- እንዲሁ በጥቅሉ?

ታደሰ፡- አዎ፣ እኔም እስኪ ላስብበት አልኳቸውና ተለያየን:: ነገ ዛሬ እያልኩ ጊዜው እየረዘመ ሲሄድ በመሃል የሕዝብ ለሕዝብ ሃሳብ ከአቶ ሺመልስ ማዘንጊያ (በወቅቱ የኢሠፓ የርዕዮተ ዓለም መምሪያ ኃላፊ) ቢሮ ይመጣል:: ከዚያ በአቶ አያልነህ ሙላት ኃላፊነት እኔ፣ ሙላቱ አስታጥቄና ተስፋዬ ለማ መሰብሰብ ጀመርን:: ሙዚቀኞችን፣ ዘፋኞችንና ተወዛዋዦችን መምረጥ ነበር የመጀመሪያ ሥራችን:: በመሠረቱ ለእንደዚህ አይነቱ የማይም ዳንስ ድራማ ሃገሪቱ ያዘጋጀቻቸው ባለሙያዎች ነበሩ ማለት ያስቸግራል:: ሰውነታቸውን እንደልባቸው እንዲያዙት (flexible) ሆነው በሚገባ የሠለጠኑ የሉንም:: እንደምንም በቴክኒክ እየተደገፍን ለማዘጋጀት ነው የሞከርነው:: ምርጫው ካለቀ በኋላ በጀቱ ምኑ ተወስኖ ሥራው እንዲጀመር ተደረገ:: ከዚያ በፊት ግን ቋሚ ተጠሪው በፈቀዱልኝ ገንዘብ አንድ ላንድሮቨር መኪና፣ አንድ ሾፌር፣ ሁለት የካሜራ ባለሙያዎችን፣ የሙዚቃ ባለሙያውን ኩት ኡጅሉን፣ አቶ ላቀው የሚባሉትን ፎቶ አንሺና ሠዓሊ ታደሰ መስፍንን ይዤ ወደክፍለ ሃገር ወጣሁ:: በተለያዩ ክፍላተ ሃገር፣ በበርካታ ቦታዎች እየተዘዋወርን ከቀረፅንና መረጃዎችን ካሰባሰብን በኋላ ወደ አዲስ አበባ ተመለስን::

ታዛ:- የጉዟችሁ ዋና ዓላማ ምንድን ነበር? በትርኢቱ ውስጥ የሚካተቱትን አይነት ጨዋታዎች ለመምረጥ ነው ወይንስ ተሳታፊዎችን ለመመልመል?

ታደሰ፡- በቂ በጀት ቢኖረን ኖሮ ከጎበኘናቸው አካባቢዎች መምጣት የሚገባቸው ብዙ ጠቃሚ ሰዎች ነበሩ:: ለምሣሌ የወላይታው ካሣ አላሮን ከዚያ ነው ያስመጣነው:: እሱን መተካት አይቻልም ነበር:: ሌሎችንም ማምጣት ይገባ ነበር:: ያው የአቅም ጉዳይ ነው:: እንደዛ ሆኖ ሥራዎቹ በፊልም ተቀርፀው፣ የአለባበሳቸውን ዲዛይን ታደሰ መስፍን በሥዕል ንድፍ እየሠራ፣ ምን ልበልህ በጣም የተሟላና ሰላማዊ ቡድን ነበር:: ከዚያ የመረጥናቸውን ዜማዎች ይዘን ሙላቱ አስታጥቄ ሙዚቃውን፣ እኔ ንቅናቄውንና ዝግጅቱን፣ ተስፋዬ ለማ አስተዳደሩን፣ በበላይነት ደግሞ ከሺመልስ በታች አያልነህ ሙላት አለ:: ሰዎቹን አሰባሰብንና ሥራው ተጀመረ:: አንድ ቀን እየተለማመድን እያለን አያልነህ መጣ:: ባይለየኝ ጣሰውም (ዛሬ ዶ/ር) አብሮት ነበር:: ባይለየኝ የማደንቀውና በጣም ቁምነገረኛ ሰው ነው:: ሠራተኛው ሁሉ ይወደው ነበር ደሞ የሚገርምህ:: አያልነህ ተስፋዬን፣ ሙላቱን፣ እኔንና ባይለየኝን ሰበሰበንና “ምንድነው የምታቀርቡት?” ይለናል:: “ተነጋግረን የለም ወይ?” እንለዋለን:: “አይ አሁን ባይለየኝ እየጻፈ አንተ የምትሠራውን ሥራ ተርክልን፣ ድርሰቱን እንደ ቃለጉባኤ አድርጎ ይጻፈው” አለ:: እሺ ብዬ “እንዲህ ይሆናል፣ እንዲህ ይደረጋል፣ የአንዱ ገጠር የአንዱ መንደር ልጅ ከአንዱ መንደር ጋር … እንዲህ እያልኩ ሃሳቡን … ጎጃምኛው ለጎንደርኛው፣ ጎንደርኛው ለጎጃምኛው ምንድነው? የኦሮምኛው አጨፋፈር እንዴት ነው?” … እያልኩ ይሄን ታሪክ የተያያዘ ሃሳብ አድርጌ አቀረብኩት:: ከዚያ በሁለት በኩል የሚሰለፉ ተፋላሚዎች አሉ አይደል? አንዱን “እከሌ በለው” አለና ስም ሰጠው::

ታዛ:- ማን? ጋሼ አያልነህ?

ታደሰ፡- አዎ! ከዚያ ያው ተረቀቀና በማግስቱ ሺመልስ ቢሮ ተሰብስበን የተጻፈው ነገር ተነበበ:: ሲነበብ የኮሚቴ አባላቱ፣ ዝግጅቱን በገንዘብ የደገፉትን ጨምሮ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የቱሪዝም ኮሚሽንና ቀይ መስቀል ተጠርተዋል:: በተጨማሪ ጸጋዬ ገ/መድኅን፣ ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌና ጸጋዬ ደባልቄም ተገኝተዋል:: እኔ ስናገር እንግዲህ “ሻቦላ” የሚል ቃል ተጠቅሜ ስለነበር አፈወርቅ ማረሚያ ሰጡ:: “ጎራዴ” ተብሎ ተስተካከለና ያው ድርሰት ጸደቀ:: ያንኑ ሥራ ከሙላቱ ጋር እየተነጋገርን “ይኼ እንዲህ ቢሆን፣ ይኼኛው ሙዚቃ ደግሞ በዚህ መልክ ቢሆን” እያልን እየተመካከርን ሠርተን ጨረስን:: ከዚያ አልባሳቱ ከተዘጋጁና መጽሔቱ ከታተመ በኋላ ሶስት የመብራት፣ የድምጽና የኮሪዮግራፊ ኤክስፐርቶች ከጀርመን ሃገር መጡልን:: ትርኢቱን አዩ:: ከዚያ እኛ ኃላፊ የተባልነው፣ እነ ካሳ ከበደና ሌሎቹ ባለሥልጣናትም ባሉበት ከኛ ጋር ተሰበሰቡና ዝግጅታችንን በጣም አድንቀውና አመስግነው ተናገሩ:: “በጣም ግሩም የሆነ ወጥ ሥራ ነው፣ ከመብራትና ከድምጽ ውጪ ምንም የሚስተካከል ነገር አይታየንም:: ይህም በእኛ ባለሙያዎች ድጋፍ ይስተካከላል” አሉን:: ከዚህ በኋላ የጉዞው ነገር ተወሰነ:: ሆኖም ከባለሙያዎቹ ባልተናነሰ ሁኔታ አብረው የሚሄዱ የሴኩሪቲና የአስተዳደር ሰዎች፣ ሃኪምና የመሳሰሉት ተጨማመሩበት:: አስፈላጊ ያልሆኑት ሁሉ:: እኔ ባለሙያ አነሰኝ እያልኩ ነው ይኼ ሁሉ የሆነው:: ባይለየኝም አልተጨመረም:: … በመጨረሻ “አያልነህም አይሄድም” ሲባል ሰማን:: እኔ እንጃ ከየት እንዳመጡት:: እኔ፣ ሙላቱና ተስፋዬ ሆነን ኦርማ ጋራዥ ጀርባ አልባሳቱ ከተሰፉበት ቦታ ደርሰን ስንመለስ “አንድ ነገር ላናግራችሁ እፈልጋለሁ” አለን ተስፋዬ:: “ሙሌ ያው አንተ ታውቃለህ፣ ሙዚቃውን ሠርተሃል:: ታዴ ደግሞ አንተ ኮሪዮግራፈርም ነህ፣ እንደገና ደራሲም ነህ፣ ሁለት ነገር ይዘሃል:: እኔ ያው ለእናንተ አገልግሎት ሰጪ ነኝ እንጂ ምኑም ውስጥ የለሁበትም:: እና ላልሄድም እችላለሁ:: ይሄ ሰውዬ ግን ለእኛ ደክሟል::” እንግዲህ በል ተብሎ ነው::

 ታዛ:- ማንን ነው ደክሟል ያለው?

 ታደሰ፡- አያልነህን

ታዛ:- እሺ?

 ታደሰ፡- “ለእኛ ደክሟል፣ የምታዩት ነው:: ላይ ታች እያለ እየተሯሯጠ ነው አንዳንንድ ነገር ሲያስፈቅድልን የነበረው:: እና ይቅርታ አድርግልኝና ታዴ ድርሰቱ ባንተ ስም ነው፣ ኮሪዮግራፈሩም አንተ ነህ:: እንዲያው ድርሰቱን ብትሰጠውና ቢሄድ ምን ይመስልሃል?” አለኝ:: ችግር የለውም:: በዚህ ከሆነ የሚሄደው አትጨነቅ አልኩት::

ታዛ:- ስሙ እንደ ደራሲ እንዲጠቀስ ነው?

ታደሰ፡- አዎ፣ አስተዋጽኦ ያደረጉት ሰዎች ብቻ እንዲሄዱ ተብሏል መሰለኝ:: አላውቅም:: እና ስሙ ለእሱ ተሰጠ:: ያው በዚያ ምክንያት ሄደ ማለት ነው::

ታዛ:- ሄዶ እስከመጨረሻው ነበር ወይስ በአጭር ጊዜ ነው የተመለሰው?

ታደሰ:- የለም፣ ግሪክ ላይ ነው የት አገር ስንደርስ፣ ዞረን ከጨረስን በኋላ፣ አንድ አገር ነው እንደዚህ ሲቀረን እንዲመለስ ተደረገ:: ከዚያ አገር ቤት ከገባን በኋላ የሚሰጠውን አስተያየት ስሰማ፣ አሁንም እዚህ ሆኜ ስሰማ ድፍረቱ ይገርመኛል:: እንዲህ ማለቱ ራሱ … እኔ ብሆን እሳቀቃለሁ:: መጀመሪያ ለመሄጃ ከተጠቀምኩበት ስመጣ እኔ እንዲህ ነኝ ብዬ መናገር የለብኝም:: ከዚያ በኋላ በተለያየ አጋጣሚ ስሰማ “ይህን አርጌ፣ እንዲህ አርጌ ሠርቼ፣ እከሌና እከሌ ሆነው” … ድርሰቱን ለውጦት በቃ የራሱ አድርጎት ድፍን አድርጎ ያወራል:: እኔ ደግሞ ክሬዲቱን አገኘሁ አላገኘሁ ግድ የለኝም:: የእሱ እንደዚህ ርካሽ መሆን እና ራሱን ዝቅ ያደረገ ሰው መሆኑን በአሠራሩ ታዘብኩት እንጂ:: ለነገሩ የእኛ ሕዝብ ለዘፈንና ለሌላ ነገር ካልሆነ በስተቀር ለዚህ አይነት ሥራ ቦታ የሚሰጥም አይደለም:: እኔም ለዛ አልጨነቅም ብዬ ነው የተውኩት:: እዚያም ደግሞ በእውነት በቁጥር እንነስ እንጂ … ባይለየኝ ራሱ የሚታዘበው ይመስለኛል:: ሙላቱም የሚታዘበው ይመስለኛል:: ሙላቱ እንግዲህ ከሰው ጋር መጋጨት አይፈልግም:: ራሱን ገለል ማድረግ የሚፈልግ ሰው ነው:: ግን ይታዘባል:: እኔም በቃ ጥቅም ለሌለው ነገር ምን አጨቃጨቀኝ ብዬ እንጂ … ባለሙያው ራሱ ያውቃል:: እንደውም ሃሳቡን ስሠራው ከድሮ ጀምሮ ዓለምም ታውቃለች:: የማያውቅ ሰው አለ ብዬ አላምንም:: ከዚህ ባሻገር ሕዝብ ለሕዝብ ውጤቱ ጥሩ ነው:: ከሕዝብ ያገኘው ተቀባይነትም ጥሩ ነበር::

ታዛ:- መቼም በበርካታ ሀገሮች በተከታታይ የቀረበና በብዛት የታየ ትርኢት ቢኖር የሕዝብ ለሕዝብ ያቀረበው መሆን አለበት:: ስለሥራችሁ ስታስብ ይህ ቢሆን ወይም ቢደረግ ኖሮ የምትለው ጉዳይ አለ?

ታደሰ፡- በተለይ ነፃነት ቢኖርህ፣ ባይገቡብህ፣ ይሄ ለምን ሆነ? እያሉ ባይጨቀጭቁህ፣ ሠርተህ ከጨረስክ በኋላ መጥተው ቢያርሙልህ ጥሩ ነው:: እየሠራህ ግን ይኼ እንዳይገባ፣ ይኼ ለምን ገባ? ይኼ ለምን ወጣ? ሲሉህ ድርሰትህ መላ ያጣል:: ያ ነው ያገራችን ችግር::

ታዛ:- በቡድኑ ውስጥ ጋሼ ታደለ ታምራትም ነበሩበት:: የእሳቸው ድርሻ ምን ነበር?

ታደሰ፡- ታደለ ከአበበ ከበደ ጋር ሆኖ በአልባሳትና ቁሳቁስ በጠቅላላ (እንደ ጎራዴ፣ ዱላ፣ ሰፌድና ሌሎችም)፣ ላይ ነበር የሚሠራው:: አሰገደች ሃብቴ ሜክ አፕ ላይ ነበረች::

ታዛ:- እንደ አምታታው በከተማ ባሉ ሙዚቃዊ ድራማዎችና በልዩ ትዕይንተ ጥበባት ፕሮግራምም ላይ ትሠራ ነበር:: አንድ የዌይተር ዳንስ ነው እንደዚህ የሚባል ልዩ ሥራ መሥራትህንም አስታውሳለሁ:: እስኪ ስለነዚህ ሥራዎችህ አጫውተኝ::

ታደሰ፡- የትሪ ዳንስ ነው:: ስብሃት ተሰማ አንድ ድርሰት ነበረው:: እና ሊያዘጋጀው ፈለገና “እስኪ ከዚህ እስከዚህ ያለውን ክፍል በዳንስ ግለጽልኝ:: ይቺን ክፍል እርዳኝ” አለ:: እና እሺ ብዬ፣ ተዘጋጅቼ ልሠራ ስል የእሱ ቴያትር ቀረ:: ጥሩ ድርሰት ነበረ:: ስብሃት ጎበዝ ሰው ነበር:: በዚያ ምክንያት ሃሳቡ ውስጤ ስለነበረ አንድ ቀን ለምን አልሠራውም አልኩና ሃሳቡን ለተሾመ ሲሳይ ነገርኩት:: ምን እንደምፈልግም በዝርዝር አስረዳሁት:: በእውነቱ ሙዚቃውን ጥሩ አድርጎ ሠራው እንዳየኸው:: ለጆኒም፣ በእንግሊዝኛ ለሚጫወተው፣ እንዲሁ አንድ ጥሩ ሥራ ሠርቼለት ነበር:: ትዝ ይለኛል በመብራትም፣ በንቅናቄም፣ በሌላውም የተሳካ ስለነበር በየሳምንቱ ከፍተኛ አድናቆት ያገኝ ነበር:: የመጀመሪያው የትዕይንተ ጥበባት ሥራም የእኔ ነበር:: ከዚያ በኋላ ሌሎቹ እየተረከቡ ሄዱ:: ጥላሁን ታሞ ከተነሳ በኋላ ብሔራዊ ቴያትር ሲመደብ ለመጀመሪያ ጊዜ መድረክ ላይ የወጣውም ያኔ ነበር:: ከላይ ከጣራው ነበር የምናወርደው::

ታዛ:- “እናት ዓለም ጠኑ” ላይ በላይ ዘለቀን ሆነህ ተውነሃል:: በመድረክም ላይ ተሰቅለህ፣ ትንፋሽህን ውጠህ ለረጅም ጊዜ ትቆያለህ:: ታች ደግሞ እትዬ አስናቀች ክራር እየመታች ታንጎራጉራለች:: እሱ ነገር ፈታኝ አልነበረም? እንዴት ተጫወትከው?

ታደሰ፡- ጋሽ ጸጋዬ ነው የመደበኝ:: ከ”ትንሳኤ ሠንደቅ ዓላማ” ጀምሮ በቅርብ ይከታተለኝ ነበር:: እንዳልከው የኔ ድርሻ በጣም ከባድ ነበር:: አንገቴን ወዳንድ አቅጣጫ ዘምበል አድርጌ ለረዥም ጊዜ ስለምቆይ የህመም ስሜት ነበረው:: ከጫማዬ ሥር ድጋፍ እንዲሆነኝ ተብሎ የታሰረው ገመድም ይመረምረኝ ነበር::

ታዛ:- እንደውም የሰማሁት ነገር አለ:: አንዴ እንደተሰቀልክ አመመህ አሉ:: ታስታውሰዋለህ? ታደሰ፡- አዎ አሞኝ ነበር:: ታውቃለህ ረስቼው ነበር:: አስመለሰኝ ልበል? ፀሐይ እንዳለ እንደረዳችኝ ትዝ ይለኛል::

ታዛ:- የመድረክ ባለሙያዎቹ በሚያስደንቅ ቅልጥፍና መብራት አጥፍተው፣ ተመልካቹ ሳያውቅ ካወረዱህና ፋታ ከወሰድክ በኋላ መልሰው እንደሰቀሉህ ጋሽ ተክሌ ደስታ አጫውቶኛል::

ታደሰ፡- እውነት ነው:: ታምሜ ነበር:: እነጋሼ አብርሃም ሲያወርዱኝ አጠገቤ ፀሐይ እንዳለ ነበረች::

ታዛ:- በዝግጅት ረገድ ከሠራሃቸው ተውኔቶች የተክሌ ደስታ “ፍልሚያ” አንዱ ነው፣ እስኪ ሌሎቹን ደሞ ንገረን::

ታደሰ፡- “ፍልሚያ” በጣም ደስ ብሎኝ የሠራሁት ነበር:: አቤት አቤት ሕዝቡ መቼም በጣም ነበር የወደደው:: ከባለሙያ ጋር ስትሆን በጣም ይጠቅምሃል:: ተክሌ አብሮኝ ስለነበር እየተነጋገርን፣ በገንዘብ አወጣጥም በምንም ሳንጨነቅ በጣም ጥሩ ሆኖ ነበር የተሠራው:: ደቤ (ደበበ እሸቱ) ነበር፣ ሲራክ ታደሰ፣ ዓይናለም ተስፋዬ፣ ሃምዛ አብዶና ኃይሉ ብሩም ነበሩበት:: ተስፋዬ ሸዋዬ (በወቅቱ የባህል ሚኒስትር የነበሩ) ናቸው ያስቆሙት:: ቴያትሩን ካዩ በኋላ ተክሌን አስጠርተው አነጋግረውት ነበር:: ለውጥ ያሉትን አልለውጥም አላቸው መሰለኝ እንዲቆም ተደረገ:: ሌላው ያዘጋጀሁት “በር” ነው::

ታዛ:- ራስ ቴያትር የታየውን የዓለምፀሃይ ወዳጆ ተውኔት ማለትህ ነው?

ታደሰ፡- አዎ፣ ከሙዚቃዊ ድራማዎች “ትግል ነው መፍትሄው”፣ እና “ደማችን” እነዚህም የዓለምፀሃይ ድርሰቶች ናቸው::

ታዛ:- ታደሰ ወርቁን ብዙዎች ይወዱታል:: ብሔራዊ ቴያትር ያነጋገርኳቸው ባለሙያዎች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በፍቅር ነው የሚያነሱህ:: ሥራ ላይ ኮስታራ እንደሆንክ ነው የሰማሁት:: የመወደድህ ምስጢር ምን ይመስልሃል?

 ታደሰ፡- እግዚአብሔር ይመስገን! የእሱ ጉዳይ ነው:: እኔ በባህሪዬ አንደኛ ሰው እወዳለሁ፤ ጨዋታ እወዳለሁ:: ሁለተኛ ሥራ ስሠራ አላዳላም:: እከሌ ቅርቤ ነው ወይም ጓደኛዬ ነው፣ እከሊት እንዲህ ነች ብዬ አላበላልጥም:: የእውነት ነው የማደርገው:: ደስ አይለኝም እንደዚያ አይነት ነገር:: እና ይህን ስለሚያዩ ይመስለኛል:: ሰው ስትወድ ለሰው ቅርብ ትሆናለህ፣ በቃ ከዚህ የተለየ ነገር የለኝም::

ታዛ:- በጠቅላላው ብሔራዊ ቴያትር ለምን ያህል ጊዜ ሠራህ?

ታደሰ፡- ወደ ሃያ ሶስት፣ ሃያ አራት ዓመት ይመስለኛል::

ታዛ:- ወደዚህ (ወደ አሜሪካ) እንደመጣህ ሙዚቃዊ ሥራዎችን ለመሥራት ትንቀሳቀስ እንደነበር ሰምቻለሁ::

ታደሰ፡- እውነት ነው:: በፈረንጆች ማርች 1989 ነው ወደዚህ የመጣሁት:: በ”ሕዝብ ለሕዝብ” ሥራ የመጣሁ ጊዜ አንዲት ኒውዮርክ ውስጥ የዳንስ ኩባንያ ያላት አሜሪካዊት በጓሮ በር አስጠራችኝ:: እንግዲህ “ማነው አዘጋጁ?” ብላ ጠይቃ ነው:: ከዚያ ጋሽ ማዕረጉ በዛብህ እያስተረጎመ ስናወራ፣ “እንዴት ሠራኸው? እዚህስ ያለውን ሁኔታ እንዴት አገኘኸው? አንተ እዚህ መጥተህ ልምድ ብንለዋወጥስ ምን ይመስልሃል? ለተወሰነ ጊዜ እኛ ጋር ብትሆን፣ ዕድሉ ከተገኘ ደግሞ እኛ ወደ ኢትዮጵያ ብንሄድ” ብላ ብዙ አውርተን ነበር:: እና ተመልሼ ከመጣሁ ከዓመታት በኋላ በሰው በሰው ላፈላልጋት ሞከርኩ:: ሆኖም በሕይወት የለችም አሉኝ፣ እሱ ቀረ:: ከዚያ በኋላ በሌላ የሥራ መስክ ተሠማርቼ ቆይቼ ዶ/ር ዮናስና ዓለማየሁ የሚባሉ ሰዎች አገኙኝና ሙዚቃ እንዳዘጋጅላቸው ጠየቁኝ:: ከዚያ ሰፋ ያለ ጊዜ ወስደን እንድንወያይበት ወደ ፊላደልፊያ ወሰዱኝ:: አንድ አራት የኪነጥበብ ሰዎች ባሉበት ራት እየበላን ትልቅና ደረጃውን የጠበቀ የሙዚቃ ዝግጅት ለማቅረብ እንደሚፈልጉ አጫወቱኝ:: ዓላማውም ለበጎ አድራጎት ተግባር መሆኑን፣ ይኸውም በእሥራኤል የሚገኙ የኢትዮጵያ ቅርሶችና ይዞታዎች ለሌሎች ሃገሮች እየተሰጡባት ስለሆነ ከሙዚቃው በሚገኘው ገቢ ጠበቃ ቀጥረን ለመከራከር እንሻለን:: ዝግጅቱም በመላው ዓለም በሚገኙ ሚዲያዎች እንዲታይ ስለምንፈልግ ያን ደረጃ የሚመጥን ሥራ እንዲሠራ ነው አሉኝ:: ለሃገራችን ታሪክና ቅርስ ከሆነማ እኔም በነፃ ነው የምሠራው፣ ገንዘብ አላስከፍላችሁም አልኳቸው:: ደስ አላቸው:: ሆኖም ምኞታቸውና ገንዘብ የማውጣት ፍላጎታቸው የሚጣጣም አልሆነም:: ለምሳሌ ለአልባሳት የሚሆን በጀት በበቂ ለመያዝ ሲሰስቱ አየን:: ከዚያ እዚህ አገር በተለያዩ ክፍለ ግዛቶች ያሉ ባለሙያዎችን መምረጥ ጀመርን:: ከኢትዮጵያ ማስመጣት አልቻልንም:: ስለዚህ ኒውዮርክ፣ ዋሺንግተን፣ ካሊፎርኒያና ከየቦታው ያሉ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችን ተሰባስበው እዚህ ሊመጡና የተወሰነ ገንዘብም ሊከፈላቸው ይገባል ብለን ነገርናቸው:: ተስማሙ:: ልጆቹ መጡ:: እነማንጠግቦሽ ጦይብ፣ እታገኝ ሙላው፣ አልማዝ ፈጠነ፣ ሣራ ተክሌ፣ ሚኒያ እስጢፋኖስ፣ ፋንትሽ በቀለ፣ ብሩክ አሰፋ፣ የሺዋስ አንዳርጌ፣ አሸናፊ ምትኩ፣ ወሮታው ውበት፣ አሰፉ ደባልቄ፣ ደረጀ ደገፋው፣ ኤልያስ አረጋ፣ ተካ ጉልማ፣ እንዲሁም ዓለምጠሃይ ወዳጆ፣ ዓይናለም ተስፋየ፣ አሰገደች ሃብቴና ፈለቀ አርምዴን ያዝኩና ልምምዳችንን ቀጠልን:: የትርኢቱ ጊዜ ሲቃረብ እርዳታ የሚሰጡን ትልልቅ ሰዎች ይመጣሉና ወደ ፊላደልፊያ መጥታችሁ ለምን ልምምዳችሁን አታሳዩዋቸውም አሉን:: እሺ ብለን ሄድን:: ከዚያ ሜዳ ላይ እየተለማመድን የገንዘብ ርዳታ ያደርጋሉ የተባሉት አይሁዶችና ሌሎችም ቁጭ ብለው ተመለከቱ:: ከዚያ ከተመለስን በኋላ ዲሲ ውስጥ በሊንከን ቴያትር ለሶስት ቀናት ታየ:: ቺካጎም ሁለት ቀን ሠራን:: ከዚያ የፈለጉትን ያህል ገንዘብ ስላላገኙ ይሁን አላውቅም፣ ለልጆቹ አልከፈሉም:: በዚህ ምክንያት ቆመ::

 ታዛ:- ለቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ደግሞ ዲቪዲ ሠርታችኋል::

 ታደሰ፡- አዎ፣ መንፈሳዊ መዝሙሮች ናቸው:: ያው የምታውቀው ነው:: ዋናው እዚህ አገር እኮ ለመሥራት የሚያስቸግርህ ሰዉ ቢፈልግም ኑሮው አያሠራህም:: ስትቀጥረው እሺ ይልና ይቀራል:: ለምንድነው ስትለው ፈቃድ ከለከሉኝ ይልሃል:: ወይ እንዲህ ሆንኩ ይልሃል:: እኔ ከሰዓት ነው ሺፍቴ ይልሃል:: ሌላው ጠዋት ነኝ ይላል:: እና በሩጫ በሩጫ የተሠራ ነው እሱ ራሱ:: እንጂ እኔ በቤተክህነት ሥራ ብዙ ብዙ የቆየ ሃሳብ ነበረኝ::

ታዛ:- የኢትዮጵያ ሙዚቃ ሲታሰብ ብዙ የሰጡን እኛ ግን በቂ ዕውቅና፣ ክብርና ሞገስ ያልሰጠናቸው የምትላቸው ካሉ ብናነሳቸው::

ታደሰ፡- በባህል ሙዚቃ፣ ዋናውና ደጋግሜ የማነሳው ጋሼ አውላቸው ነው:: ሌላው ትልቅ አስተዋጽዎ ያደረገው ጋሽ ኢዩኤል ዮሐንስ ነው:: እንደውም ትዝ ይለኛል ለንደን ላይ አግኝቼው “የልጃገረዶች ሳሎን” የሚለውን ጨዋታ እባክህን አደራ ልስጥህ፣ እሱን ነገር መልሰህ አስተካክለህ ሥራው” ብሎኝ ነበር:: በጣም አስቂኝ የሆነ እንደ ድራማም፣ እንደ ማይም ዳንስ ድራማም አይነት ነው:: እና እመኘዋለሁ፣ ደስ ይለኛል:: ግን በየትኛው ጊዜ፣ በምን በጀት ልሥራው? ታደለ ታምራት ደግሞ ጋሼ አውላቸው ከለቀቀ በኋላ ለረዥም ጊዜ በባህል ክፍል ኃላፊነት የሠራ ትጉህ ሰው ነው:: ወደ ሙዚቃው ስንመጣ ጋሽ መርዓዊ ስጦት እንደዚሁ የማይታክት ጠንካራ ባለሙያ ነው:: ተሾመ ሲሳይም ሌላው የሃገር ባለውለታ ነው:: እንግዲህ ሌላውና ትልቅ ዋጋ የምሰጠው ሙላቱ አስታጥቄ ነው:: ብዙ ሥራ የሠራ ሰው ነው:: ከእሱ ጋር በሙያህ በጣም ተግባብተህ መሥራት ትችላለህ:: ሌላው ታላቅ ባለሙያ አማኒ ኢብራሂም ነው:: ከእሱ ጋር ስትሠራ ብዙ ትማራለህ፣ ትደሰትማለህ:: ሌላ እንዲሁ ያለቦታው ገብቶ ቀረ እንጂ ኤልያስ አረጋም በጣም ጎበዝ ባለሙያ ነበር:: የክራር ችሎታው መቼም ግሩም ነው:: ከእሱ ጋር በቀላሉ መግባባት ይቻላል:: ባለ ትልቅ ተሰጥኦም ነው:: በሕዝብ ለሕዝብ ጊዜ ሙላቱን ይረዳ የነበረም ነው::

ታዛ:- ታዴ፣ ለነበረን ቆይታ እጅግ በጣም አድርጌ አመሰግንሃለሁ::

 ታደሰ፡- እኔም አመሰግናለሁ!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top