ቀዳሚ ቃል

በፖለቲካ ባህላችን ላይ ብንወያይስ?

የሀገራችን ፖለቲካ ባህል ኋላ ቀርና ጠባብ (parochial) ሆኖ ቆይቷል፡፡ አላዳብነውም፡፡ አልተነጋገርንበትም፡፡ ታዛ መፅሄት ገና ከመጀመሪያ ዕትምዋ ጀምሮ በፖለቲካ ባህላችን ዙሪያ የሃሳብ ልውውጥ እንዲፈጠር የበኩልዋን ጥረት ስታደርግ ቆይታለች፡፡ የሃሳብ ፍßት ግን አሁንም ቢሆን ጎልቶ አልወጣም፡፡ ጎልቶ እንዲወጣ እንጥራለን፡፡

 በአገራችን የፖለቲካ ባህል ታሪክ ውስጥ የልዩነቶቻችን ምንጮች የሆኑት አመለካከቶች ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ተንትነው አልቀረቡም፡፡ ከዚያ ይልቅ ሃሳቦችን እያድበሰበሱ ቃላቶችን እየሰነጠቁ ማብጠልጠል ብቻ ከሆነ ረዥም ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡

 በእኛ ዘመን በተለይም ዛሬ፣ ገኖ የወጣው የልዩነትም ሆነ የፖለቲካ ሃሳብ ማዘዋወሪያ ቋንቋ ቀድሞም የነበረ ነው፡፡ በተለይም በአሁኑ ወቅት ፋሽን ሆኖ ሁሉም ዓይነት የህብረተሰብ ክፍሎች ማለትም ከሀገር መሪ እስከ ከፍተኛ ምሁራንና የፖለቲካ ተንታኞች ድረስ የሚያወሩት፣ የሚወያዩበት፣ የሚስማሙበት እና የሚለያዩበት መነሻ ምክንያት ሆኖ የምናገኘው ቋንቋና ሃሳብ፤ ማንነት፣ ዘርና ዘረኝነት የሚሉ እሳቤዎች ናቸው፡፡

 ይህ ዓይነት እንደወረደ የሚናገር ባህል ብዙ ዋጋ አስከፍሎናል፡፡ በዚህ መንገድ ከገፋንበትም ገና ብዙ ዋጋ ማስከፈሉ አይቀርም፡፡ ስለዚህ ብዙ መነጋገርና መወያየት ይኖርብናል እንላለን፡፡ በዚህ በሃያኛው ዕትማችን በኢትዮጵያ ባህል ላይ ከፍተኛ ምርምር እና እውቀት ያካበተው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው መምህር ዶ/ር ባይለየኝ ጣሰው “ማንነት፣ ዘርና ዘረኝነት” በሚል ርዕስ መጣጥፍ ይዞልን ቀርቧል፡፡

 ይህ ጽሑፍ እንደ መነሻ ወስደን ብንወያይበት፣ሌሎች ጸሐፊዎችም የበኩላቸውን ቢያክሉበት የፖለቲካ ባህላችንን ዘመናዊ እና ሳይንሳዊ በማድረግ ሂደት ላይ መልካም አስተዋጽዎ ይኖረዋል፡፡ ለዚህም የተጻፈውን አንብቡ፤ እናንተም ጻፉ፡፡ ነፃ ሃሳብ ይንሸራሸር፡፡

 መልካም ንባብ !

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top