አድባራተ ጥበብ

በሥነ- ተረት ውስጥ የሕይወት አንድምታ

የቀድሞው ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት በ1978 ዓ.ም ያሳተመው የማርክሲዝም ሌኒኒዝም መዝገበ ቃላት ሥነ- ተረትን (mythology) እንዲህ ይፈታዋል።

 “ነገሮችን በማጋነን ወይም አስደናቂ ፍጡሮችን በመፍጠር ወይም ደግሞ አስገራሚ ተረቶችን በማውሳት የተፈጥሮ እና የሕብረተሰብ ሁኔታ በምሳሌ የሚገለጽበት ዘዴ ሥነ- ተረት ይባላል።” ወረድ ብሎም ”…ሥነ-ተረት ከሚቀሰቅሳቸው ሥነ-ውበታዊ ስሜቶችና ከሚጠቀምበት ምናባዊ ፈጠራ አንጻር ንቁ ያልሆነ የእውነታ ስነ-ጥበባዊ አመለካከት ነው።”

ቴዎድሮስ ገብሬ ደግሞ “በይነ ዲሲፕሊናዊ የሥነ ጽሁፍ ንባብ” በሚለው መጽሐፉ ውስጥ የሥነ-ተረትን ትርጉም (mythology) በዚህ መልኩ ተመልክቶታል። ‹‹ሚት የሰው ልጅ የነገረ ፍጥረት እና የነገረ ሕላዊ እንቆቅልሾችን ለመመለስ የሞከረበት፣ እየተመሰቃቀለ ለሚያስቸግረው ዓለም ህልው ሥርዓት (cosmic order) ለማበጀት የባተለበት እምነታዊና ፍልስፍናዊ ጥበብ ነው።” በማለት።

ሥነ-ተረት ንቁ ባልሆነው የሰው ልጅ አመለካከት ውስጥ ተፈጥሮም ሆነ ስለሕብረተሰቡ ምንነት የተሰጠ ጥበባዊ ገለጻ ከሆነ በነቃው ህሊና ደግሞ ሲታይና ሲተነተን የሕይወት አንድምታው ምን ሊመስል ይችላል? ከተረትነት አልፎ ዛሬም ድረስ በሰው ልጆች ኑሮና ሕይወት ውስጥ የያዘው ቦታና ትርጉም እንዴት ይታያል? የሚለው ጥያቄ ይህንን ጽሑፍ ለማዘጋጀት ቆስቋሽ መንፈስ ሆኖኛል። በጣም በጥቂቱ የተመረጡትን ሥነ- ተረቶች እያነሳሁ ሕይወትና ኑሮን ከዛሬው ዘመን ሰው እውነታ ጋር እያስማማሁ የሚቀጥለውን ብያለሁ::

 የአማልክቱ ጉባዔ እና የሚቲንከስ ሴራ

 እንደጥንታዊው የግሪኮች ተረት ከሆነ በጥንት ጊዜ ይኖር የነበረው የሰው ልጅ አፈጣጠር አሁን ከሚታወቀው ሰው የተለየ ነበር። የዚያን ዘመኑ ሰው ያለው አራት እግር፣ ሁለት ጭንቅላት፣ ሁለት ፊት፣ አራት ዓይኖችና አራት እጆች የነበሩት ግዙፍ ሰው ነበር። በዚህም አፈጣጠሩ ሰው በመታበዩ የአማልክቱን መንደር ማሸበርና መበጥበጥ የዘወትር ስራው ሆነ።

በዚህ ዓይነቱ የሰው ድርጊት የተደናገጡት አማልክት ሰውን ይፈሩት ጀመር። አንድ ቀን ግን የአማልክቶች ሁሉ አምላክ የሆነው ዜሁስ ይህንን የሰው ልጅ ትዕቢት ልክ ለማስያዝ ስለፈለገ አማልክቱን በሙሉ ጠርቶ ታላቅ የምክክር ጉባዔ አደረገ። “ይህን መንደራችንን እየበጠበጠ ሰላምና ክብር የነሳንን ሰው ምን እናድርገው? ልኩን የምናሳየውስ በምን ጥበብ ነው? እስቲ መላምቱ?” ሲል ጉባዔውን ጠየቀ። ጥበበኛው የምክርና የዘዴ አምላክ የሆነው፣ ሚቲንከስ ከዜሁስ ፊት ቆሞ እንዲህ አለ፡-

 “ሰው ለአማላክቱ የስጋት የፍርሃት ምንጭ እንዳይሆን ከፈለጋችሁ ተፈጥሮውን ከአራትነት ወደ ሁለትነት መሰንጠቅና መክፈል ነው። በዚህም ሙሉነቱንና አንድነቱን ያጣል፣ ግማሽ ይሆናል። በአራት እጁ መስራት አቁም በሁለት እጁ ብቻ ይሰራል። በአራት ዓይኑ ማየት አቁሞ በሁለት አይኑ ብቻ ይመለከታል። አስተሳሰቡም ራሱ ከሁለት በመከፈሉ ምክንያት ደካማ ይሆናል። ለሁለት ተከፍሎም አላርፍ ካለ እንደገና መሰንጠቅ ነው። አንድ ዓይን፣ አንድ እግር፣ ግማሽ ጭንቅላትና አንድ እግር ብቻ እንዲኖረው ማድረግ ነው። የሰውን ተፈጥሮ በዚህ መልኩ በከፋፈልነው ቁጥር ሰው ለአማልክቱ የስጋት ምንጭ መሆኑ ያበቃል። የእኛ ባሪያ ሆኖ ተንበርክኮ እየሰገደ በፍርሃት ይኖራል። የአማልክቱ መከበርና መፈራት ዋስትናው የሰው ተፈጥሮ መከፋፈልና መሰነጣጠቅ ብቻ ነው“ ይለዋል። ዜሁስ በሚቲንከስ ምክር ስለተደሰተ ምክሩን ለመፈጸም አላቅማማም። ወዲያውኑ ሰው ላይ ፈረደበት። ሰው ከአራትነት ወደ ሁለትነት አነሰ። ተከፈለ። በዚህ ፍርድ ሰው በማንነቱ ውስጥ አስተናግዶት የማያውቀውን የፍርሃት ስሜት ተማረ። ፍርሃት ለአማልክቱ እንዲንበረከክ አደረገው ይለናል ሥነ-ተረቱ።

አንድምታው (Implication) ምንድነው? ሰው አዳም ተብሎ በሚታወቅበት ስሙ በገነት ሳለ ጉልበታም ነበር። በፍጥረታት ሁሉ ላይ ሥልጣን ስለተሰጠውም የሚፈራና የሚከበር ነበር። አንድ ቀን በፈጣሪው ፈቃድ አንቀላፍቶ የማያውቀው አዳም እንዲያንቀላፋ ተደረገ። ለምን ይሆን እንዲያንቀላፋ የተወሰነበት? ከእንቅልፉ ሲነቃ ከአዳም ሙሉ አካል ተከፍላ የተሰራች የኑሮ ጓደኛውን ሴት አገኘ። ትኩር ብሎ ካያት በኋላ ይህቺ ከስጋዬ የተገኘች ሥጋ፣ ከአጥንቴ የተገኘት አጥንት ስለሆነች ሴት ትባል ብሎ ጠራት። ቆይቶ ደግሞ ሄዋን ሲል ክፋዩን ሰየማት።

 ከዚህ በኋላ አዳም ደካማ ሆነ። ክፋዩን መከተል፣ እሷን መስማት፣ እሷን ማድንቅ ስራው ሆነ። አምላኩ የነገረውን ትእዛዝ እንኳን ማስታወስ ተሳነው። አዳም ሲከፈል ማስተዋሉን አጣ፣ የአካሉን ክፋይ ምክር ሰምቶ፣ አትብላ የተባለውን ፍሬ በልቶ፣ ከሞቀውና ካማረው መኖሪያው ከገነት ወደ ምድረ ፋይድ ተሰደደ።

 አዳም ደካማ ሆነ። የተፈጥሮ ገዢ የነበረው ከተፈጥሮ በታች ወደቀ። ለፀሐይና ለተራራው፣ ለባህሩና ለምድሩ ሁሉ እንግዳ ባይተዋር ሆነ።

አዳም ሙሉነቱ ሲከፈል ፈሪ ሆነ፣ እሱም በተራው መውለድ በሚሉት የሕይወት ህግ ስር ወድቆ እራሱን መከፋፈል ጀመረ። አቤልና ቃየል የሚባሉ ልጆች አካሉን ከፍሎ ወለደ። አንደኛው በሌላኛው ላይ ድንጋይ አነሳ። በአዳም መከፋፈል ሞት መልኩን ለአዳም ገለጠ። ለዘመናት ሲያለቅስ ኖረ። ደስታው፣ ነጻነቱ፣ ክብሩ ሁሉ ጠፋ። አዳም ከዚህ መዓት ያድነው ዘንድ በምድረ ፋይድ ተጥሎ ለአምላኩ ተንበረከከ። አዳም ማንነቱ ሁለት መሆን ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ሕይወቱ በስቃይና ፍርሃት ብቻ ሆነ። የልጅ ልጆቹ ልክ እንደዚህ ሲከፋፈሉ በጎሳ፣ በነገድ፣ በቋንቋ፣ በሀገር፣ በሐይማኖት ተለያይተው መጠፋፋት የማንነታቸው መገለጫ ሆነ። ይኸው የሚቲንከስ ሴራ ዛሬም በእኛ ዘመን እውነት ሆኖ እያየነው ነው። የፖለቲካውን ስልጣን የጨበጡት የእኛ ምድር አማልክቶች በሚቲንከስ ጥበብ የሰው ልጅን ብዙ ቦታ እየከፋፈሉት በፍርሃትና በባርነት ሲገዙት እያየን ነው። አንድነት ኃይል ነው የሚሉት በአንደበታቸው ብቻ ነው። በልባቸው ውስጥ ያሸመቀው ድብቁ እውነት ግን “ልዩነት ኃይል ነው!” ይለናል። ሕዝቡን በከፋፈሉት ቁጥር እነሱ ይፈራሉ። ሥጋት የሚሆንባቸውን ሁሉ በፍርሃት ሰንሰለት አስረው በባርነት ቀንበር ይገዙታል። ማንም ሰው ወደ ስልጣናቸው መንበር እንዳይጠጋና ሰላም እንዳይነሳቸው አንድ የሆነውን የሰው ማንነት ሲከፋፍሉት ይታያሉ። የኢኮኖሚውንም ስልጣን የጨበጡት የምድራችን አማልክቶች ለሀብታቸው መብዛት ሲሉ ይህንኑ የሚቲንከስን ጥበብ ይሰሩበታል። በዚህም ክፍልፍሎሽ ቢሊዮኖች ድሃ ሆነው በፍርሃት በባርነት ስቃይ ውስጥ ወድቀው ይኖራሉ። ጥቂት ሃብታም የምድራችን አማልክቶች ደግሞ እየተዘመረላቸውና እየተሰገደላቸው በመንበረ ግዛታቸው ተፈርተው ይኖራሉ። ሰው በተከፋፈለ ቁጥር እያነሰ ይመጣል። ሰው ዛሬ በሙሉ አቅሙ አይደለም ያለው። በአራት ዓይኑ አያይም፣ በአራት እጁ አይሰራም፣ በአራት እግሩ አይሮጥም፣ በሚቲንከስ ሴራ ተሰነጣጥቆ ደካማ ሆኗል። ይህንኑ እውነት በሃይማኖት በኩል ብንመረምረውም ሰው እንደዚሁ አንድ አምላክ አለ እያለ ግን በብዙ ሺ የሐይማኖት ድርጅቶች ተከፋፍሎና እውነቱን ማየት ተስኖት በፍርሃት ተንበርክኮ ይታያል። የሰው ልጅ በዚህ ስነ-ተረት ውስጥ ያልነቃውን ምናቡን ቀስቅሶ ቢመረምረው የሕይወቱን አንድምታ በብዙ መልኩ እየተነተነ ሊረዳው ይችላል። የራሱንም የሕይወት ፍልስፍና ወይም እምነት ሊመሰርት ይችላል። ተረቱ ተረት ብቻ አይደለም፣ መራርም እውነት ነው።

 የፓንዶራ ሳጥን

አንድ ቀን ፕሪማቲዎስ የተባለ የአማልክት ወገን ነበር። እሳትን ከዜሁስ ጓዳ ውስጥ ሰርቆ ለሰው ልጅ ይሰጣል። ሰው እሳትን በወዳጅ በፕሪማቲዎስ በኩል ከማግኘቱ በፊት ኑሮው በጣም አስቸጋሪና ቀዝቃዛ ነበር። የሰው ኑሮ በምድር ላይ የሞቀውና የደመቀው በእሳት ምክንያት ነበር። ዜሁስ የሰው ልጅ ኑሮ በእሳት መገኘት ምክንያት መሞቁና መድመቁ ያስቆጣዋል። ተቆጥቶም ዝም አላለም፣ አንድ መላ ዘየደ። በዚያን ጊዜ በምድር ላይ የሚኖሩት ወንዶች ብቻ ነበሩ። ሴት ገና አልተፈጠረችም ነበር። ዜሁስ ፓንዶራን ሴት አድርጎ ከሰራት በኋላ ለሰው ልጅ የበቀል ዱላ ትሆነው ዘንድ አንድ ሳጥን አዘጋጅቶ ከነ ቁልፉ ይሰጣታል።

በዚያ ሳጥን ውስጥ ክፉ ነገሮች በሙሉ ሞት፣ ስቃይ፣ ሕመም፣ እርጅና፣. ድህነት ወዘተ. ታጭቀው ታሽገውባቸው ነበር። ዜሁስ ለፓንዶራ እንዲህ ይላታል፣ “አሁን ወደ ምድር እልክሻለሁ። እዚያ ስትደርሽ ባል ታገቢያለሽ። ይህንን ሳጥንም ከነቁልፉ ትሰጪዋለሽ። ግን ሳጥኑን በፍጹም እንዳትከፍቺው” ይላታል። ፓንዶራ የዜሁስን ትእዛዝ ተቀብላ ከነ ሳጥኑ ወደ ምድር ትወርዳለች። በፓንዶራ ውበት የተደነቀው ወንዱ አፒመትየስ በፍቅር ይንበረከክላታል። ወዲያውኑም ያገባታል። ከዜሁስ የተላከለትን ሳጥንም ከነቁልፉ ለአፒመንትየስ ትሰጠዋለች። ከዚያን ቀን ጀምሮ ግን ፓንዶራ ይህንን ሳጥን ትረሳዋለች። ከጋብቻው ቀን በኋላ ደግሞ ባሏ ፓንዶራን ይረሳታል። ትኩረቱ ሁሉ መሬት በማረስና በመቆፈር፣ የደረሰውን ፍሬ በመሰብሰብ፣ ወደ ቤቱ ሲመለስም እራቱን በልቶ በማንቀላፋት ብቻ ይሆናል።

 ፓንዶራ ብቸኝነት ያሰቃያት ጀመረ። አንድ ቀን ግን ይህንን ብቸኝነት ለማሸነፍ ስትል የረሳቸውን ሳጥን አስታወሰች። እንዳትከፍተው የተሰጣትን ትእዛዝ ጥሳ ሳጥኑን ከፈተችው። እነዚያ ታፍነውና ታሽጎባቸው በሳጥኑ ውስጥ ይኖሩ የነበሩት የመከራና የስቃይ ዘሮች ከተከፈተው ሳጥን ውስጥ እየወጡ ቤቱንና ውጩንም ሞሉት። ምድር አይታ የማታውቀውን መከራና ስቃይ አስተናጋደች። ፓንዶራ መልሳ ሳጥኑን ዘጋችው። ተስፋ ብቻ ከሳጥኑ ውስጥ ሳይወጣ ቀረ። ፓንዶራ በሰራችው ስህተት አዝና ብትጸጸትም በሳጥኑ ውስጥ የቀረው ተስፋ ግን ያጽናናት ጀመር። ፓንዶራ በተስፋ ምክንያት ሕይወትን በዚች

“የሞላውና ያማረ የሚመስለው የኑሯችን ሞሰብ በዚያ ልንቆጣጠረው በማንችለው የአሞራው መንቆር ሲተፈተፍ በጣም ያመናል። ስቃይ ጓደኛችን ይሆናል”

ምድር ላይ ቀጠለች ይላል ሥነ-ተረቱ።

 አንድምታው

ሰው ልክ እንደፓንዶራ ብቸኝነቱን ይፈራዋል። ተፈጥሮው ማህበራዊ ነው። ፓንዶራ በባሏ ስትረሳና ብቸኝነት ሲከባት የረሳችውን ሳጥን እንድታስታውስ ሆነች። ሰው ሲረሳና ብቻውን ሲሆን በተቃራኒው ረስቶ የነበረውን የነገር ሳጥን ከአእምሮው ጓዳ ውስጥ መፈለግ ይጀምራል። ከብቸኝነቱ ለመሸሽ የሚመርጠው መንገድ ይህንኑ ነው። ይህንን አደገኛ ሳጥን መክፈት ሲጀምር ከብቸኝነቱ ማምለጫ አድርጎ የመረጠው ተግባር ያልጠበቀውን መከራና ስቃይ በኑሮው ውስጥ ያመጣበታል።

 በብዙዎቻችን የትዳር ጎጆ ውስጥ የተቀመጠ እና የተረሳ የፓንዶራ ሳጥን መኖሩን መርሳት የለብንም። በጋብቻው ግንኙነት ውስጥ የተረሳው አንደኛው ወገን ይህንኑ የተረሳውን ሳጥን ሲያስታውስ ይከፍተዋል። ከዚህ ሳጥን ውስጥ በሚወጣ መከራና ስቃይ የተነሳ የብዙ ሰው ትዳር ፈርሷል። በባሎቻቸው የተረሱ ብዙ ሚስቶች በከፈቱት የፓንዶራ ሳጥን ቂምና በቀልን ተምረዋል። የማያውቁትን ቅናት አውቀውታል። በዚህም ምክንያት የብዙ ሰው ትዳር ታሟል፣ ሞቷል።

 በፓንዶራ ጎጆ ውስጥ ይህ ሳጥን እንዲቀመጥ ሴራውን የጠነሰሰው ዜሁስ ነው። ልክ እንደዚሁ በእያንዳንዳችን የትዳር ጎጆ ውስጥ ይህንን የተንኮል ሳጥን ያስቀመጡና ጊዜውን ጠብቆ እንዲፈነዳ የሚሰሩ ከእኛ ውጭ የሆኑ ጠላቶች እንዳሉን መርሳት የለብንም። አንደኛው ወገን ይህንን ሳጥን ረስቶት ቆይቶ ሊሆን ይችላል። ከዘመናት በፊት አንድ ሰው ስለትዳራችን አጋር መጥፎ ነገር ነገሮን እኛ ግን ረስተነው ቆይተን ይሆናል። ይህ ሁሉ ትዝ የሚለን ግን ብቻችንን ስንሆንና ስንረሳ ነው። ከተደበቀው የአእምሮ ጓዳችን ውስጥ እየቆፈርን የምናወጣው ልክ እንደፓንዶራ አንዱ በሌላው አካል ሲረሳ ነው። በጋብቻው ሂደት ውስጥ አንድ አካልና አንድ አምሳልነት እውን ሆኖ ማየት የተሳነን ለዚህ ነው።

 የሰው ልጅ በሕልውና ውስጥ ብዙ ክፍት ቦታዎች አሉት። ክፍተቱን ካልሞላውና ከራሱ ጋር ካላዋሃደው ብቸኝነቱ የስቃይ ምንጭ ይሆንበታል። በሥጋውና በመንፈስ መካከል ያለውን ክፍት ቦታ በነቃውና ባልነቃው አእምሮ መካከል ያለውን ክፍት ቦታ፣ በወንድና በሴት፣ በባልና በሚስት፣ መካከል ያለውን ክፍት ቦታ በተዋህዶ መሙላት እና አንድ ማድረግ ካልቻለ ምንጊዜም ቢሆን የትም ቦታ ብንኖር የፓንዶራ ሳጥን በሁላችንም ሕይወትና ኑሮ ውስጥ ቦታ ይዞ ይኖራል። ከብቸኝነት ለማምለጥ ስንል ከዚሁ የክፋት ሳጥን ጋር ጓደኝነት እንጀምራለን። ብዙ ባሎች በሚስቶቻቸው በመረሳታቸው ምክንያት ልክ እንደፓንዶራ ሳጥን አልኮል መጠጣትን ጓደኝነት አድርገውታል። ውጤቱ ግን ሁለቱንም ነው የሚጎዳው። ፓንዶራ በከፈተችው ሳጥን ምክንያት ባሏ ኢፒመትየስ የማያውቀውን ሞትና፣ መከራ በምድር ላይ አይቷል። መረሳት መጥፎ ነው፣ ጉዳቱ በአንደኛው ወገን ላይ ብቻ አያበቃም። በባልና ሚስት መለያየት ምክንያት መከራው ለልጆችም ይተርፋል። ለአገርም ይደርሳል።

የፓንዶራ ሳጥን አንድምታው ብዙ ነው። ወደ ሌላው ልቀጥል።

 የፕሪማቲዎስ ጉበት

 ሰውን የሚወድ፣ በግማሽ አካሉ የሰው ባህሪ፣ በግማሽ አካሉ ደግሞ የአምላክነት ባህሪይ ያለው ፕሪማቲዎስ የሚባል የአማልክትም የሰውም ወገን የሆነ ፍጡር ነበር። ዜሁስ እሳትን ከፈጠረ በኋላ ከሰው ደብቆና ከልክሎ ብቻውን ይጠቀምበት ነበር። የጎጆውን ጨለማ የሚያባርርበት፣ የኑሮውን ቆፈን የሚያሞቅበትን እሳት ዜሁስ ለሰው ከለከለው። ፕሪማቲዎስ በዜሁስ ነገር ስለተበሳጨ እሳትን ከዜሁስ ጓዳ ሰርቆ ለሰው ልጆች ይሰጣቸዋል። ሰው ባገኘው እሳት ምክንያት ኑሮውም ሕይወቱም አስተሳሰቡም ሳይቀር በፍጥነት ተለወጠ።

ዜሁስ ባየውና ፕሪማቲዎስ ባደረገው ነገር ተቆጣ። እናም በምስኪኑ ፕሪማቲዎስ ላይ ለዘላለም የሚፈጸም ቅጣት በጉበቱ ላይ ፈረደበት። በኦሎምፐስ ተራራ ላይ እንደ ቆዳ ተወጥሮ እንዲታሰር ካደረገ በኋላ ጉበቱን የሚበላ ባለመንቆራም አሞራ ላከበት። አሞራው በዚያ ሹል መንቆሩ የፕሪማቲዎስን ጉበት ይተፈትፈዋል። ሲያልቅ ጥሎት ይሄዳል። ጉበቱ መልሶ ሲሞላ እና ሲያድግ ደግሞ የጠፋው አሞራ በሮ ከች ይላል። የተለመደ ተግባሩን በፕሪማቲዎስ ቅጣተኛ ጉበት ላይ ይፈጽማል። ለፕሪማቲዎስ ይህ አይነቱ ቅጣት ለዘላለም እንዲፈጸምበት ተፈረደበት። አሞራው ትቶት ሲሄድ እና የተበላው ጉበቱ እንደገና መሙላት ሲጀምር ደስ ይለዋል። ይህንኑ አይቶ ጉበቱን ለመብላት አሞራው ወደ እሱ ሲመጣ ደግሞ ደስታው ጠፍቶ ስቃዩ ቦታውን ይይዛል። አሳዛኝ ፍጡር!

አንድምታው

የማያቋርጥ ስቃይና ደስታ በሚያቋርጠው እድገታችን ወይም ለውጣችን ውስጥ ተደብቆ ይከተለናል የሚል ፍልስፍናዊ ትርጉም ይሰጠናል። ሰው በህይወቱ እና በኑሮ የፕሪማቲዎስን ጉበት ይመስላል። እሳት የስልጣኔ መሰረት ነው ይባላል። የሰው ልጅ በፈጠረው ስልጣኔ ውስጥ በኑሮና በሕይወቱ ውስጥ ለውጥ ቢፈጥርም ከለውጡ ጋር አብሮ የሚመጣው ደስታ ብቻ ሳይሆን ሀዘንም ጭምር ነው።

 የሞላውና ያማረ የሚመስለው የኑሯችን ሞሰብ በዚያ ልንቆጣጠረው በማንችለው የአሞራው መንቆር ሲተፈተፍ በጣም ያመናል። ስቃይ ጓደኛችን ይሆናል። አሞራው ትቶን ሲሄድ እና የተበላው ጉበት መሙላት ሲጀምር ደግሞ ደስታ ጓደኛችን ይሆናል። ግን ብዙ አይዘልቅም። ያ መከረኛ አሞራ በኑሮ ሰንሰለት ተወጥረን ወደ ታሰርንበት የእንያዳንዳችን የሕይወት ጎጆ ውስጥ በርሮ ይመጣል። ይህን ጊዜ ደስታ ይጠፋል፣ ስቃይ ቦታውን ይይዛል። ዓለም ዘጠኝ ነች ሞልታ አታውቅም የሚለውን ብሒል የተማርነው ከዚህ የፕሪማቲዎስ ስቃይ ይመስለኛል።

 አንቷን ቼሆብ “ሁላችንም የተገኘነው ከጎጎል ካፖርት ውስጥ ነው” ብሎ ነበር። እኔ ደግሞ እንዲህ እላለሁ፣ “ሁላችንም የምንኖረው ልክ እንደ ፕሪማቲዎስ ጉበት ነው።” አበቃሁ፣ በሌላ ጊዜ በሌላ ጉዳይ እስከምንገናኝ ደህና ቆዩ።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top