በላ ልበልሃ

ማንነት፣ ዘር እና ዘረኝነት

“ዘር” እና “ማንነት” እንደ አገባቡ መጠነኛ ተዛምዶ ሊኖራቸው ቢችልም በሁለቱ ፅንሰ-ሃሳቦች መካከል መሠረታዊ ልዩነት አለ:: “ዘር፣አብረው የሚወለዱ የቆዳ ቀለማትንና አካላዊ ቅርጾችን የመሳሰሉ ተፈጥሯዊ ባሕርያትን የሚያካትት ፅንሰ-ሃሳብ ነው:: ማንነት ግን ከመወለድ በኋላ በባህል የሚገኙና በማህበረሰብ የሚተላለፉ እንደ የአኗኗር ስልት፣ የጋብቻ ደንብ፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት፣ እና የመሳሰሉትን ትውፊታዊ የማንነት መገለጫዎችን ሚያካትት ነው::” ይህ ሆኖ ሳለ በተለይም አሁኑ ጊዜ በሀገራችን የፖለቲካ አውድ ውስጥ በተለያዩ መገናኛ ብዙሀን መድረኮችም ሆነ በዘወትሯዊ ማህበራዊ ሕይወት የግንኙነት ተግባቦቶች አንዱ ቃል የሌላው መገለጫ ሆኖ የሚያገለግል ይመስል ተጣርሰው ሲቀርቡ ይስተዋላል:: ይህ ሁኔታ ደግሞ “ችግሩ የግንዛቤ ጉድለት ነው ወይስ በኢትዮጵያ አውድ በአሁኑ ወቅት ለዚህ የሚያበቃ የዘረኝነት ፖለቲካ በእውን እየተካሄደ ይገኛል ለማለት ተፈልጎ ነው?” የሚል ጥያቄ እንዲነሳ ያስገድዳል:: እንዲህ ያሉትን ስሜት ገብ ቃላት ከመሪ እስከ ከልሂቃን፣ ከፖለቲከኛ እስከ ጋዜጠኛ፣ ወዘተ.፣ ለጉንጭ አልፋ ፍጆታነት በዋሉ ቁጥር “ሞኝና ወረቀት የያዙትን አይለቁም” እንደሚባለው በተደራሹ፣ በተለይም በወጣቱ ትውልድ ላይ ውሎ አድሮ የሚያስከትለው አፍራሽ ውጤት በቀላሉ የሚፀዳ አይደለም:: በተለይ በሚዲያ አጠቃቀም በኩል ጥንቃቄ የሚያሻው ይመስለኛል:: ኚዮንግ ፎንግ ማይ እንዲህ ያሉ የግንዛቤ ጉድለቶች “በሚዲያና በማህበራዊ ግንኙነት መረቦች በኩል ባልተሟላ መረጃ ተጋነው ስለሚቀርቡ በብዙ ሀገሮች ያልተጠበቀ አደጋን አስከትለዋል” በማለት ገልጾታል:: ለምሳሌ በቦዝኒያ ሄርዞጎቢና የተፈፀመውን ኢሰብአዊ ድርጊት በአብዛኛው በሚዲያ ፕሮፖጋንዳ የታገዘ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው::

 የዚህ አጭር ጽሑፍ ዓላማም በፅንሰ-ሀሳቦቹ መሀል ያሉትን መሠረታዊ ልዩነቶች ለመጠቆምና በዘረኝነት አስተሳሰብ ላይ የተመሠረቱ አንዳንድ የዘር ምድቦችን ከእነ ትርጉማቸው ለግንዛቤ ያህል ማመልከት ነው:: በእርግጥ ርዕሰ-ጉዳዩ ሰፊና ጥልቅ በመሆኑ በዚህ አጭር ፅሑፍ ፅንሰ-ሀሳቦቹ የሚያካትቷቸውን ሁሉንም ገጽታዎች አሟልቶ ለማቅረብ አይቻልም:: ስለዚህ ቀጥሎ እንደቀረበው የጽሑፉ ትኩረት በፅንሰ-ሀሳቦቹ ምንነትና የአጠቃቀም ልዩነቶች ላይ ያተኩራል::

w“ዘር” የሚለው ቃል የሰው ልጆችን በአካላዊ ቅርጽና በቆዳ ቀለም ላይ የተመሠረቱ ባሕርያትን የሚገልጹ በርካታ ብያኔዎች ሲሰጡት ቆይቷል:: በመሆኑም በፅንሰ-ሀሳብ ደረጃ በዋነኛነት በሰው ልጆች መካከል በሚኖሩ አካለዊ የተፈጥሮ ቅርፆችና የቆዳ ቀለማት (‘phenotypes’) ልዩነቶች ላይ መሠረት በማድረግ ለብዙ ዘመናት ብያኔ ሲሰጠውና ሲሠራበት የቆየ ክስተት ነው:: ‘ከዘር’ ጋር ተዛምደው የሚጠቀሱ ባሕርያትና ቅርፆችም በደምና በአጥንት የሚወረሱ ወይም በመወለድ የሚገኙ ተደርገው ነው የሚታዩት:: ለምሳሌ፣ በቆዳ ቀለም፡- ነጭ፣ ጥቁር፣ ቢጫ፣ ቀይ፤ በፀጉር ዓይነት፣ ከርዳዳ፣ ግልስልስ፣ ልሁጫ፤ በዓይን ቀለም ፡-ሰማያዊ፣ ጥቁር፤ በአካለዊ ቅርፅና፤ ቁመና፡- ወፍራም፣ ቀጭን፣ አጭር፣ ድንክ፣ ረዥም፤ አጥንተ ሰፊ፣ አጥንተ ጠባብ፣ የከንፈር ስስነትና ድጉሰት፣ ድፍጥጥና ሰልካካ አፍንጫ፣ ወዘተ.፣ እና በመሳሰሉ በሰው ልጆች መካከል ያለ ተመሳሳይነትንና ልዩነትን በመግለፅና በመመደብ አንዱን ወገን ከሌላው ወገን ለመለየት ሲያገለግል የቆየ የማንነት መመዘኛ ነው::

በቀላሉ መረዳት እንደሚቻለው ይህ ዓይነቱ አስተሳሰብ የሚወሰነው ከሥነ-ሕያወት አፈጣጠር፣ ከተፈጥሮ፣ ጋር ተቆራኝቶ እንጂ የባህል ውጤት ተደርጎ አይደለም::

በመሆኑም በጊዜና በቦታ በባህልና በማህበረሰብ ከተገነቡ መመዘኛ መገለጫ ባሕርያት ውጭ በዘር ላይ የሚያተኩር ኢሳይንሳዊ አስተሳሰብ በመሆኑ በምሁራን ዘንድ ከፍተኛ ነቀፌታና ውግዘት ገጥሞታል:: የግለሰቦችንና ቡድኖችን ማንነት በዘር መገለጫዎች ለመለየት ቢፈለግ አንድ ግለሰብ ወይም አንድ ማህበራዊ ቡድን በታሪክ ከስንት የተለያዩ ዘሮች ጋር እንደተቀየጠ ለማወቅ እጅግ አስቸጋሪ ይሆናል:: ከዚህ የተነሳም ሞንታግ “ዘር የሚለው ቃል ሳይንሳዊ መሠረት የለውም፤ እውነቱን ለመናገር በገሀዱ ዓለም ውስጥ ሊሠራ የሚችል መመዘኛ ሊሆን አይችልም:: በአሁኑ ጊዜ በሳይንቲስቶች ዘንድ ሙሉ በሙሉ የታመነበት ጉዳይ ዘር የሚለው ቃል በዘፈቀደ ብያኔ ሲሰጠው ቆይቷል” ይለናል::

በተለይም ከ20ኛው ምዕተ-ዓመት የመጀመሪያ አጋማሽ ሩብ ዓመታት ወዲህ ሥር-ነቀል የንድፈ-ሃሳብና የአሠራር ለውጦች ተከትለዋል:: ለውጦችም ህብረተሰቦችን በተመሳሳይነትም ሆነ በልዩነት ለይቶ ለመመደብ ባህላዊ የንፅፅር መገለጫ ባሕርያት እንጂ ተፈጥሯዊ የሰው ልጅ ባሕርያትና ቅርፆች ሊሆኑ እንደማይችሉ መረጋገጣቸው ነው:: በመሆኑም ከ’ድኅረ-ዘመናዊነት’ ዘመን (በተለይም ከ1960ዎቹ) ወዲህ በ’ዘር’ ላይ ተመሥርቶ በስፋት ሲገለፅና ሲሠራበት የነበረው ኢሳይንሳዊ አስተሳሰብና መሥፈርት ውድቅ እየሆነ በ’ባህላዊ የጋራ የማንነት መለያ ባሕርያት’ ተካትቶ ወይም ተተክቶ በተግባር ላይ ሊውል ችሏል::

 ማንነት፡- “ማንነት” የሚለው ጽንሰ-ሃሰብ የሚገልፀው ከባህላዊ ባሕርያት ጋር የተያያዙ መገለጫዎችን፡- ለምሳሌ፣ ከዜግነት፣ ከልማድ፣ ከባህል ቅርሶች፣ አኗኗር ስልትና መሠረት፣ ከየት-መጥ እና ከትውልድ ሐረግ ታሪክ፣ ከቋንቋ፣ ከእምነት፣ ወዘተ.፣ ጋር ከተያያዙ የባህል ባሕርያት ነው:: ስለሆነም የሚወሰነው በባህል እንጂ በተፈጥሮ (በዘር) አይደለም:: ለምሳሌ በአፍሪካ የጥቁር “ዘር” የሚባል ህዝብ ሊኖር ቢችልም በዚህ ዝርያ ውስጥ ከሺህ በላይ የተለያዩ የብሔረሰብ ማንነቶች ይገኛሉ:: በዘር ቢወሰን ኖሮ የሚኖረው ማንነት አንድ ብቻ በሆነ ነበር:: ነገር ግን ማንነት የባህል ጉዳይ በመሆኑ እና ባህል ከህብረተሰብ ህብረተሰብ ስለሚለያይ የተለያዩ የብሔረሰብ ማንነቶች እንዲኖሩ አስችሏል ማለት ነው:: የአንዱ ማንነት ከሌላው ማንነት የሚለይባቸው መገለጫ ባሕርያትም የባህል ውጤቶች ናቸው:: እንዚህን ባሕርያትም እጅግ በርካታ በሆኑ ምሁራን “ዘር” ከሚለው የአመዳደብ ዘዴ በተለየ መንገድ ገልፀዋቸዋል:: ከእነዚህ መካከልም

 በመምሁራን ዘንድ በሰፊው የሚጠቀሰው የስሚዝንና የሀችንሰንን ሥራ አንዱን ከሌላው ማህበረሰብ ለመለየትና ለመግለፅ የሚያስችሉ ሰባት ዋና ዋና የማንነት መገለጫ ባህላዊ ምድቦችን እንደ ምሳሌ መጥቀስ ጠቃሚ ይሆናል:: እነዚህም፡-

“በአውሮፓ የዘረኝነትን አስተሳሰብ በመከተል የዓለማችንን የሰው ዘር የበላይነትና የበታችነት የደረጃ ተዋረድ ሥርዓት ለመስጠት እንደ አንድ ‹የሳይንስ መስክ› ተወስዶ አከፋፈሉና አመክንዮ-ሀሳቡ በሰፊው ይጠናና በገቢር ሲተረጎም ቆይቷል”

1ኛ) አንድ የወል ተፀውኦ ስም፤

2ኛ/ የጋራ ጥንታዊ ሥነ ታሪክ (ሚት)፡-

3ኛ/ የጋራ ታሪክ ትውስታዎች፣

4ኛ/ አንድ ወይም ከአንድ በላይ የሆኑ የጋራ የባህል ገፅታዎች፣ ለምሳሌ፡- ቋንቋ፣ ልማዳዊ እምነትና አሠራሮች፣ የአኗኗር ስልት፣ ጋብቻ፣ ሃይማኖት፣ ወዘተ.

5ኛ/ በአካል መኖር የግድ የማይጠይቅ ከትውልድ ሀገር ጋር የሚኖሩ አባላት የጥንታዊ አባት/እናት ሀገር ትዕምርታዊ ዝምድና ወይም ትስስር፤

 6ኛ/ በብሔረሰቡ ህዝብ ወይም ቢያንስ በተወሰኑ የማህበረሰቡ ክፍሎች በጋራ የሚንፀባረቅ የአንድነት ስሜት፤

7ኛ/ የጋራ መልክዓ-ምድራዊ ሥፍራ ናቸው:: በዚህ መልክ አንትሮፖሎጂስቶች በተለይም ኢትኖሎጂስቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻሉ የመጡ ወደ 200 በሚሆኑ ባህላዊ አምዶች ሥር ከ2000 በላይ የማንነት መገለጫ ንፅፅራዊ ባሕርያትን አውጥተዋል:: በመሆኑም በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ሀገሮች እነዚህን የማንነት ባህላዊ ባሕርያት እንደ መሥፈርት እየተጠቀሙባቸው ይገኛሉ:: ስለሆነም እነዚህ የማንነት መገለጫ መመዘኛ ባሕርያት የሚወሰኑት በባህል እንጂ በዘር ገጽታዎች ላይ አለመሆኑን መረዳት ያስፈልጋል::

ዘረኝነት፡- ዘረኝነት ሲባል ምን ማለት ነው? የፅንሰ ሀሳቡ ፍች ሰፊና ጥልቅ ነው:: ሆኖም ለዚህ ጽሑፍ የሮጀር ባላድን ብያኔ እንመልከት:: ይኸውም፡- “ዘረኝነት አንድ የህዝብ ቡድን ከሌላው ህዝብ ቡድን ማንነት የሚለየው ‹በዘር› ነው በሚል አስተሳሰብና በዚህ የሚያምን ዘረኛ ቡድን ራሱን ከሌላው ቡድን የበላይ አድርጎ የሚያይበት አመለካከትና ይህን አመለካከቱን በገቢር የሚያውልበት መንገድ ነው” የሚል ነው::

ከዚህ ተነስተን ስንመለከት የዘረኝነት አስተሳሰብ ዋና መሠረት የሰውን ልጆች በይበልጥ በደምና በአጥንት በተወረሰ አካላዊ ቅርጽና የቆዳ ቀለም ያላቸውን ልዩነቶች በመጠቀም በበላይነትና ዝቅተኝነት የደረጃ ተዋረድ ሥርዓት ለማበጀት ይደረግ ከነበረ በዘር የተመሠረተ የምደባ ተግባር የመነጨ አስተሳሰብና እምነት ነው:: ይህንም ኋይት “ከዘር እሳቤ ላይ ተመሥርቶ የሰው

ልጆች በተፈጥሮ፣ በመወለድ፣ በደም በአጥንት፣ የሚያገኙት አካላዊ ቅርፅና ይዘት የቆዳ ቀለም ስብዕናቸውን፣ እውቀታቸውን፣ የማሰብ ችሎታቸውን በአጠቃላይም ባህላቸውን ይወስነዋል” ከሚል የቲዮሪ አመለካከት የመነጨ ነው:: በተጨማሪም ብርያነ አለየን “ሆኖ ግን በሥነ-ሕይወት አፈጣጣር በደም የሚወረስ በሰዎች መካከል የሚያለያይ ምንም ዓይነት ገደብ በእርግጥ አይገኝም” ይላል:: ይህን ካልን የዘር አከፋፈል በምን መልክ፣ መንገድና መመዘኛ ነው የሰው ልጆችን ይመድብና ይገልፅ የነበረው? የሚለውን መመልከት ስለ እሳቤው ይበልጥ ለመረዳት ስለሚረዳ እንደሚከተለው በአጭሩ ለመጠቆም ሞክሬያለሁ::

 ዘረኝነት ያቆጠቆጠው ከባሪያ ንግድና ከአይሁዳውያን የንግድ ሥራ ብልጫ ጋር በተያያዘ መልክ በ16ኛው ምዕተ ዓመት መቋጫ በአውሮፓ በተለይም በእንግሊዝ አገር እንደ ነበር የታሪክ መረጃዎች ያወሳሉ:: ለምሳሌ “በዘር የተመሠረተ የተለያዩ ህዝቦች የሚኖሩበት አዲስ የመሬት አከፋፈል” በሚል ርዕስ በፍራንሲዮስ በርኒየር (እ.ኤአ) በ1684 ዓ.ም. የተፃፈና የመጀመሪያው ተጠቃሽ ሥራ እንደሆነ የሚጠቁሙ መረጃዎች ይገኛሉ:: ከዚያም ዘረኝነት ሥር እየሰደደ የመጣው በተለይም በአንግሎ- ሳክሶን የዘር ትርክት (ሚት) ተመሥርቶና ተመርቶ “የበላይነት የተሰጠው፣ አይበገሬ፣ ነፃ ፍጡርና ንፁህ ዘር” በሚል አመለካከት አውሮፓውያን ዓለምን በቅኝ ግዛት ሲቀራመቱ በነበሩበት ታሪካዊ ዘመን፣ በ18ኛው ምዕተ ዓመት (በዘመነ-አብርኆት (በዘመነ-ኢላይተንመንት)) አጋማሽ ጀምሮ በመስፋፋት ከ”ጥቁሩ ዓለም” የተለያዩ ህዝቦችና ባህሎች ጋር መገናኜት በጀመሩበት ጊዜ ነበር::

 በአውሮፓ የዘረኝነትን አስተሳሰብ በመከተል የዓለማችንን የሰው ዘር የበላይነትና የበታችነት የደረጃ ተዋረድ ሥርዓት ለመስጠት እንደ አንድ ‹የሳይንስ መስክ› ተወስዶ አከፋፈሉና አመክንዮ-ሀሳቡ በሰፊው ይጠናና በገቢር ሲተረጎም ቆይቷል::

በመሆኑም የሰውን ልጆች ‹ዘመናዊ› የዘር አከፋፈል በግንባር ቀደምትነት መሠረት እንደጣለ በብዙዎች ዘንድ የሚጠቀሰው ካሮለስ ሊኒየስ የተባለው ጀርመናዊ ታክሶኖሚስት ነው:: ይህንም ኋይት እና መንቻካ “ካርሎስ ሊኒየስ የሰው ልጆችን የዘር አመዳደብ መሠረት የጣለ ታክሶኖሚስት ነው” በማለት ይገልፃሉ:: ካርሎስ ሊኒየስ በ1758 ዓ.ም. የዘረኝነት የበላይነትና የበታችነት የደረጃ ተዋረድ ቀመር በማብጀት የዓለማችንን የሰው ዘር በአራት ምድቦች ነበር የከፈለው:: የአመዳደቡ መመዘኛ ቀጥሎ እንደቀረበው ዘር በንፍቀ-ዓለም (በቦታ)፣ ዘር በቆዳ ቀለም የተመሠረተ ሲሆን በበላይነትና በበታችነት የተዋረድ ደረጃ በትይዩ ይገልፃል:: ይህም የሚከተለውን ይመስላል::

ካርሎስ ሊኒየስ ከአመዳደቡ ጋር የእያንዳንዱን የሰው ዝርያ የባሕርይ መገለጫዎችን ጨምሮ በመግለጽ ነበር ያስቀመጠው:: ይኸውም፡-

ዘር በመልክአ-ምድር የቆዳ ቀለም የበላይነት እና የበታችነት የደረጃ ተዋረድ
አውሮፓዊ የሰው ዘር ነጭ ነጭ አንደኛ ደረጃ የበላይ ቁንጮ
ኤስያዊ የሰው ዝርያ ብጫ ብጫ ዘር ሁለተኛ ደረጃ
አሜሪካዊ የሰው ዝርያ ቀይ ቀይ ዘር በሦስተኛ ደረጃ
አፍሪካዊ የሰው ዝርያ ጥቁር ጥቁር ዘር የበመጨረሻ ደረጃ

1. አሜሪካዊ የሰው ዝርያ (ቀይ) (ሆሞ ሳፒያን አሜሪካነስ፣ የቆዳ ቀለሙ ቀይ፣ በባሕርይው ጠባየ ብልሹ፣ በቀላሉ ተንበርካኪ)::

 2. አውሮፓዊ የሰው ዘር (ነጭ) (ኢሮፒየስ፣ የቆዳ ቀለሙ ነጭ፣ በባሕርይው የማይበገር፣ ጠንካራ)::

 3. እስያዊ የሰው ዘር (ብጫ) (ሆሞ ሳፒያን ኤሺያቲክ፡ የቆዳ ቀለሙ ብጫ፣ በጠባዩ ስስታም፣ ቆዘምተኛ)::

 4. አፍሪካዊ የሰው ዘር (አፈር) (አፍሪካን ሆሞ ሳፒያንስ፡-የቆዳ  ቀለሙ አፈር-ጥቁር፣ በባሕርይው እርባና-ቢስ፣ ደካማ፣ ሰነፍ)::

ካርሎስ ሊኒየስ ከእነዚህ ከአራቱ የዘር ምድቦች ውጭ “ሞንስተር” የሰው ዘር በሚል የሚገኝበትን መልክዓ-ምድር ሳይጠቅስ በአምስተኛ የሰው ዘር ምድብ ጨምሮ የሚያስቀምጠው ክፍልም ይገኛል:: ሲጠቅሰውም የተለያዩ የዘር ምድቦችን የያዘ መሆኑንና ለዚህም እንደ ምሳሌ ያነሳቸው “የደቡብ አሜሪካ ፓታጎኒያን፣ የካናዳ ጥፍጥፍ ራሶችን እና ከአራቱ ዋና ምድቦች የሰው ዝርያዎች ጋር ምንም አምሳያነት የሌላቸው ሌላ ዓይነት ዝርያ” አድርጎ በመሳል ነበር::

ከዚህ ቀጥሎ የሚጠቀሰው የሊኒየስ ደቀ-መዝሙር የጀ.ኤፍ. ብሉሜንባኽ አመዳደብ ነው:: ብሉሜንባኽ በ1775 ዓ.ም. የሰው ልጆችን በአራት ምድቦች ነበር የከፈላቸው:: እነዚህም፡-

 1. አውሮፓውያን፣ ምሥራቅ እስያ እና ከፊል ሰሜን አሜሪካ፣

2. አውስትራሊያውያን፣

3. አፍሪካውያን፣

4. ቀሪው የዲሱ ዓለም ሰዎች፣ በሚል ሲሆን በመቀጠል በ1795 ዓ.ም. ባቀረበው ጥናት ከላይ ከተተቀሱት በተጨማሪ አምስት የተለያዩ ዘሮችን አመልክቷል:: እነርሱም፡-

 1. ኢትዮጵውያን፣

 2. ካውካሲያኖች፣

 3. ሞንጎሊያውያን፣

 4. አሜሪካን እና፣

5. ማላያውያን፣ የሚል ተጠቅሰው ይገኛሉ:: ከእነዚህ ሌላ ኤስኪሞዎችን ከምሥራቅ እስያ ዝርያ ጋር ወግኗቸዋል::

 ይህን አመዳደብ ተከትሎ በ18ኛው ምዕተ-ዓመት ገደማ ዶ/ር ሳሙኤል ሞርቶን በዘር ምድቦቹ መካከል ያሉትን የበላይነትና የበታችነት ተዋረረዶች በሥነ-ሕይወት (በባዮሎጂ) ጥናት በተለይም በጭንቅላት መጠን ምርምር በማድረግ የማሰብ ችሎታ ልዩነቶችን በመለየት ማረጋገጥ ያስፈልጋል የሚል መከራከሪያ ሀሳብ አራመደ:: በኋላም የሞርቶን ተከታይ የነበረ ሉዊስ አጋሲዝ የተባለ ምሁር “የጥቁር ዘር መናኛ ብቻ ሳይሆን ከቀሩት የሰው ዘሮችም የተለየ ፍጡር ነው” ከሚል ድምዳሜ ላይ ደረሰ::

ማርቪን ሀሪስ ሁለት የተለያዩ ዘሮችን ለመከፋፈል ጠቃሚ የሆነ የቅይጥነት (ሀይፖደሰንስ) ቲዮሪ በሚል አንድ ንድፈ ሀሳብ በ1916 ዓ.ም. አቅ ርቦ ነበር:: በንድፈ-ሀሳቡ መሠረት ከየሁለቱ የተለያዩ ዘሮች ተዳቅሎ የተወለደ ሰው በሥነ-ሕይወት ሳይንስም ሆነ በማህበረሰብ ‹ርካሽ› ዝርያ ተደርጎ መወሰድ እንዳለበት ከሚያውጅ ድምዳሜ ላይ ደርሷል:: ይኸውም፡- “የነጭና የኢንዲያን ድቅያ ኢንዲያን ነው:: የነጭና የጥቁር ውላጅ ጥቁር ነው:: የነጭና የሂንዱ ዲቃላ ሂንዱ ነው:: የአውሮፓና የአይሁዳዊ ውላጅ አይሁዳዊ ነው” የሚል ነበር:: ይህም በአንዳንድ ሀገሮች በሕግ ፀድቆ 1/8ኛ ወጥም 1/16ኛ የቅይጥ የሆኑ ሰዎች (‹ዜጎች›) የዘር ማንነት በዚሁ መሠረት በህዝብ ቆጠራ ተሠርቶበታል:: በሕጉ መሠረት አንድ ነጭ ግለሰብ 1/8ኛ ወይንም 1/16ኛ የሚሆን የጥቁር ዘር ጥንቅር ካለበት ግለሰቡ ወይም ‹ዜጋው› ጥቁር ዘር ተብሎ እንዲመደብና እንዲታወቅ ተደርጓል::

 በአጠቃላይ በእነዚህ አመዳደቦች መሠረት ዘረኝነት በሰው ልጅ ላይ ያደረሰው ግፍና ሰቆቃ ተዘርዝሮ አያልቅም:: በጀርመኑ ናዚ – በአዶልፍ ሂትለር – የተመራው ፋሽዝም ያደረሰው የሰው ልጅ እልቂት መሠረቱ ዘረኝነት መሆኑን ልብ ይሏል:: ዘረኝነት ከቅኝ ግዛት ፖለቲካ ጋር እጅና ጓንት በመሆን ከሁለት ምዕተ-ዓመታት በላይ በአህጉረ-አፍሪካ የሰውን ልጅ ከሰው ልጅ ተራ በሚያወጣ ደረጃ ለተከናወነው ዘግናኝ ድርጊት ሁሉ ታሪክ የቅርብ ጊዜ ምስክር ነው:: ከዚህ የተነሳ ነው ሮጀር ባላድ በአሁኑ ጊዜ “ዘረኝነት … እንደ ትልቅ የሰው ልጅ የሞራል ዝቅጠትና እንደ እርጉም አስተሳሰብና ምግባር ተደርጎ ይታያል:: በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የሰውን ልጆች በዘር ማንነት አንዱን ከፍ ሌላውን ዝቅ በማድረግ እጅግ ዘግናኝ ድርጊት የፈፀመ ክፉ ምግባር ነው::… በዚህ ምክንያትም በዘመናችን ‹ዘረኛ› የሚለው ቃል እጅግ በጣም አሳፋሪ ስድብ ሆኖ ይገኛል::” ሲል የገለጸው::

 የዘረኝነት መሠረተ-ቢስነት፡- በአሁኑ ጊዜ ሳይንቲስቶች በጥናት ላይ ተመሥርተው እንደሚገልጹት የሰው ልጆች ሐብለ-ዘር እጅግ በጣም ተመሳሳይነት ያለው መሆኑን በማረጋገጥ ላይ ናቸው:: “ሁሉም የሰው ልጆች ከአንድ ዘር የተገኙ ናቸው:: የምንጋራው የሀብለ-ዘር ዓይነት ብዛት ከምንለያይበት መጠን በእጅጉ ይልቃል::” በአሁኑ ጊዜ ሳይንቲስቶች በቅርቡ ባደረጉት በዓለማችን ከቁጥር የማይገቡ የሀብለዘር ልዩነቶችን በጥናት በመለየት የሰው ልጆች ምን ያክል አንድ እንደሆኑና እንዴት በዓለማችን እንደተሠረጩ ግልጽ የሆነ መረጃ እያቀረቡልን ይገኛሉ:: በተደረሰበት ውጤት መሠረት “የሰው ልጅ ጀኖም (ሐብለ- ዘር) በቁጥር 25000 ሺህ በሚሆኑ ጂኖች የተጠናቀረ ነው:: እንደ ቆዳ ቀለም፣ እንደ ፀጉር ዓይነቶች፣ እንደ አፍንጫ ቅርፆች፣ ወዘተ.፣ የመሳሰሉ ውጫዊ ልዩነቶች የሚወሰኑት እጅግ በጣም ጥቂት በሆኑ ጂኖች ነው:: በአንድ ጥቁር አፍሪካዊና በአንድ ነጭ ኖርዲክ መካከል ያለው የሰው ልጅ ጂን ልዩነት (ልዩነት ከተባለ) 0.0005 ብቻ ነው:: በአንትሮፖሎጂስቶችና በሰው ልጅ ሀብለዘር ሳይንቲስቶች መካከል ከሥነ-ሕይወት የቲዮሪ ዕይታና አቋም አንፃር የተደረሰበት በሰፊው የታመነበትና የተደረሰበት ስምምነት ወይም ድምዳሜ እንዲያውም በእውነተኛው አገላለጽ የሰው ልጅ ‹ዘሮች› የሚባል ነገር ጨርሶ የለም:: የሚል ነው:: የዘር አስተሳሰብ (ዘረኝነት) ሳይንሳዊ አይደለም:: ‹መሠረተ-ቢስ› ነው የሚባለውም ለዚህ ነው::

 ለማጠቃለል ያህል ከዘረኝነት አስተሳሰብ አንፃር ሲታይ የግለሰብም ሆነ የብሔረሰብ ማንነት ከግለሰብ ወይም ከብሔረሰብ ማንነት የሚለይበት መንገድ ከቆዳ ቀለማትና ከአካለዊ ቅርፅ አኳያ መሆኑንና በባህል የማንነት ገጽታዎች ላይ አለመሆኑን፣ የዘረኝነት ዋነኛ መሠረት ሀሳብ ሆኖ ማገልገሉንና በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ በደም የጨቀየ፣ እጅግ አስከፊና ዘግናኝ ውጤት እንዳለውም ለመግለጽ ተሞክሯል::

በመነሻው ላይ እንደተጠቆመው ዋናው ቁምነገር ከተገለፁት ባሕርያቱ አኳያ ሲታይ ዘረኝነት በሀገራችን አውድ ውስጥ እውን ‹ተከስቷል› ተብሎ ሊነገር ይቻላል ወይ? የሚለው ይሆናል:: በሚዲያም ሆነ በተለያዩ መድረኮች እና በዕለት ተዕለት ማህበራዊ ሕይወት ‹የዘረኝነት ፖለቲካ›፣ ‹ዘረኞች›፣ ‹የዘር ፍልስፍና›፣ ወዘተ.፣ እየተባለ በጭፍን ሲነገር፣ ሲደመጥና ሲነበብ ምን ለማለት ተፈልጎ ይሆን ማሰኜቱ ብቻ ሳይሆን “ቆቅ በራሷ ላይ መዐት ታወርዳለች” እንዲሉ ሊያስከትለው የሚችለውን ጦስ ጭምር ማጤን ተገቢ ይሆናል:: በእኔ በኩል በቀለም ወይም በአካላዊ ቅርጽ ላይ የተመሠረተ የዘረኝነት ፖለቲካ በሀገራችን አውድ ውስጥ እየተካሄደ አይገኝም:: የህን ያልኩበት ምክንያትም ግልፅ ነው:: ይህም በሀገራችን አውድ በቆዳ ቀለም፡- ነጭ፣ ጥቁር፣ ቢጫ፣ ቀይ ቀለም፤ በአካላዊ ቅርፅ በቁመት፣ በአጥንት ስፋት፣ በውፍረት፣ በቀጭን፣ በአጭር፣ በድንክ፣ በረዥም፤ በአጥንት ስፋትና ጥበት፣ በከንፈር ስስነትና ድጉሰት፣ ድፍጥጥና በሰልካካ አፍንጫ፣ ወዘተ.፣ በፀጉር ዓይነት፡ – በከርዳዳና በልሁጫ፤ በዓይን ቀለም፡- በሰማያዊ፣ በጥቁር፤ ወዘተ.፣ በአጠቃላይም በዘር የማንነት ባሕርያት ላይ ተመርኩዞ የሚካሄድ እንቅስቃሰሴ ባለመኖሩ ነው:: በሀገራችን እየተካሄደ ያለው የዘረኝነት ፖለቲካ ወይም የብሔረሰብ የፖለቲካ ሳይሆን ለቁሳዊ ጥቅምንና ሥልጣንን ኢላማ ያደረገ የብሔረሰብ መለዮ/አርማ ከደረታቸው በለጠፉ የብሔረሰብ ‹ልሂቃን› የሚከናወን ‹የፖለቲካ ብሔረሰብ› ነው ቢባል ከውእነት የራቀ አይሆንም::


አብርሃም ሊንከን

ሊንከን “እንደ ሀገር ‹ሁሉም የሰው ልጆች በአፈጣጠር እኩል ናቸው› ብለን በማወጅ እንጀምራለን:: አሁን በተግባር የተረዳነው ግን ‹ከጥቁሮች (ከኔግሮስ) በስተቀር ሁሉም ሰው ልጆች የተፈጠሩት በእኩልነት ነው›:: ምንም የማያውቁ ሰዎች የሥልጣ ኃላፊነት ሲያገኙ ግልፅ ሆኖ የሚረዱት ነገር፡- ‹ከጥቁሮች (ከኔግሮስ)፣ ከባዕዳን፣ ከካቶሊኮች በስተቀር ሁሉም የሰው ልጆች በእኩልነት የተፈጠሩ መሆናቸውን ነው›::” – ሲል በደብዳቤው ፅፏል::


ማርቲን ሎተር ኪንግ

ማርቲን ሉተር ኪንግ – ህልም አለኝ በሚለው ፅሁፉ ደግሞ “ጥቁር ሕፃናት የነጭ ሕፃናትን እጆች ጨብጠው ሰላም የሚሉበት አንድ ቀን ይመጣል ብየ ተስፋ አርጋለሁ::” ብሏል::  

“አንድን ዘር የበላይ ሌላውን የበታች ያደረገው ፍልሥፍና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ውድቅ እስካልተደረገና እስካልተወገዘ ድረስ ሁሉም ነገር ጦርነት ነው እላለሁ:: በማንኛውም ሀገር በዜጎቿ አንደኞቹ መካከል ሁለተኛ ደረጃ ዜግነት ከፍሎ በሥራ መዋሉን እስካላቆመ ድረስ እና የሰው ልጅ የቆዳ ቀለም ልዩነት ዋጋ ቢስ መሆኑ እስካልተረጋገጠ ድረስ ጦርነት አለ እላለሁ:: በዘር ያልተመሠረተ የሰው ልጆች መሠረታዊ ሰብአዊ መብቶች በእኩልነት መከበራው እስካለተረጋገጠ ድረስ ምንጊዜም ጦርነት ይኖራል ብየ አምናለሁ::” ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ -ነጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ


ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ንጉሠ-ነገሥት ዘ-ኢትዮጵያ
Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top