አድባራተ ጥበብ

ሐጅ አብደላ ሙሐመድና – በቀን የአንድ ቡና ወይም ማኪያቶ ግብዣ

በ2004 በአገራችን በተለይም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፎክሎር ጥናት የዱክትርና ትምህርት ፕሮግራም ሲከፈት ከመጀመሪያዎቹ ተማሪዎች አንዱ ነበርኩ። መስኩ አዲስ ስለነበር ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓና ከኤዥያ በመጡ መምህራን ትምህርት ይሰጥ ነበር። ከኮርሶቹም መካከል ‹‹የቃል ታሪክ/ Oral History, Oral Tradition›› የሚባለው አንደኛው ነበር። የኮርሱን ዝርዝር ይዘት በዚህ የተወሰነ አምድ መግለጹ አዳጋች ቢሆንም ከዚህ መጣጥፍ ጋር የተያያዘውን ጉዳይ ከይዘቱ ጋር አሰናስኜ በአጭሩ ለማቅረብ እሞክራለሁ።

 የቃል ታሪክ ከተለመደው የነገስታት፣ የሃይማኖት ተቋማትና መሪዎች ወይም የኢሊቶች የመረጃ አሰባሰብና የታሪክ አጻጻፍ በፊት፣ ጎንና ኋላ የነበረንና ያለን ግለሰብ ወይም ቡድን ገጠመኝ መረጃ እንደ ዋና የታሪክ ምንጭና ታሪክ፣ ወይም ለተመዘገበ የመረጃ ሰነድ ለማሟያ ወይም ለማጠናከሪያ ወይም ለማመሳከሪያ ወዘተ. የሚያገለግል የግለሰቦችና ቡድኖች ሁነቶችን መረጃና ታሪክ የሚመለከት ነው። በድምሩ ተጽእኖ ፈጣሪ የሆኑ የድምጽ አልባ ሁነቶች፣ ግለሰቦችና ቡድኖችን ታሪክ መረጃ በመሰብሰብና በማደራጀት የተሻለ ታሪክ ለመጻፍ አይን የሚከፍት በቅርብ ጊዜ የተጀመረ የትምህርት አይነት ነው። በዚሁ መሰረት ኮርሱ ከሚሸፍናቸው ስራዎች መካከል አንጻራዊ በሆነ መልኩ የአንድ ተጽእኖ ፈጣሪ ሁነት፣ ግለሰብ ወይም ቡድን ታሪክ ማዘጋጀት የሚጠይቅ ስለነበር፣ ይኸ ሁኔታ ቀጥሎ ከሚቀርበው ባለ ታሪክ ጋር አገናኘኝ።

 የዚህ የቃል ታሪክ ባለቤት ‹‹አብደላ ሙሐመድ›› ይባላል። የቃል ታሪኩን ካዘጋጀሁ በኋላ ‹‹ሐጅ›› ማድረጉን በማወቄ ከዚህ በኋላ ‹‹ሐጅ አብደላ ሙሐመድ›› ብዬ መጥራቱን መርጫለሁ። ሐጅ አብደላ የቃል ታሪኩን ሳዘጋጅ ጡረተኛ ነበር። የቀደመ ስራው በእርዳታ ድርጅት ውስጥ ይሰራ ስለነበር፣ ጡረታ ከወጣም በኋላ በዚሁ የሰብአዊ አገልግሎቱ ቀጠለበት። በተለይም በ‹‹አወልያ የሚሲዮን ድርጅት›› ስር በሚተዳደረው የአወልያ ሚሲዮን ትምህርት ቤት ወላጆችን በመወከል የሚሲዮን ትምህርት ቤቱ የቦርድ አባል ሆኖ በነጻ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።

የአወልያ ሚሲዮን ትምህርት ቤት ሲጀመር ነጻ የትምህርት አገልግሎት የሚሰጥበት የህዝብ የሚሲዮን ተቋም ነበረ። ቆይቶ የ‹‹ሰው›› አይን በዛበትና በነጻ ትምህርት የሚሰጥበት አቅሙ እንዲዳከም ተደረገና አነስተኛ ክፍያ እያስከፈለ፣ ለተወሰኑ ችግረኞች ደግሞ የነጻ እድል እየሰጠ የትምህርት አገልግሎት ወደ መስጠት ተሸጋገረ። ሐጅ አብደላ ሙሐመድ ወላጆችን ወክሎ የትምህርት ቤቱ የቦርድ አባል የሆነው በዚህ ወቅት ነበር። ሐጅ አብደላ ሙሐመድ በዚህ የትምህርት ቤት የቦርድ አባልነት ዘመኑ በርካታ በውጣ ውረድ የተሞሉ ገጠመኞች አሉት። ከብዙዎቹ ገጠመኞቹ መካከል በአንድ ወቅት የገጠመውና የሰብአዊ አገልግሎቱ ወደ ሞዴልነት እንዲቀየር የሆነው ቃል ታሪኩ እንዲህ ቀርቧል።

 የአወልያ ሚሲዮን ትምህርት ቤት ቦርድ ተሰብስቦ በዚህ አመት ለአምስት መቶ ችግረኛ ተማሪዎች የነጻ ትምህርት እድል እንዲሰጣቸው ይወስናል። በዚሁ መሰረት የአመልካቾችን ማመልከቻ ዝርዝር እየመረመርንና እያጣራን ነጻ የትምህርት እድል ለማግኘት የሚያስችላቸውን ስንለይ ቆይተን አምስት መቶ ስንደርስ አቆምን። የነጻ እድል ፈላጊዎቹን ማመልከቻ አይተን ሳንጨርስ፣ የአመቱ ኮታ ስለሞላ ከዚህ በላይ መልፋት አልነበረብንምና ዘጋን። የቦርዱ አባሎች ስራችንን ጨርሰን ከአዳራሽ ስንወጣ በር ላይ ሶስት የሚሆኑ እናቶች ከዘበኛ ጋር ድብድብ ቀረሽ ግብግብ ገጥመዋል። ፈጥኜ መካከል ገባሁና በእጆቼ እየገላገልሁ፣ በአፌ እየተቆጣሁ ነገሩን ለማብረድ ሞከርኩ።

ሁሉም ወገኖች የእኔን መቆጣት እንደተረዱ ሁሉ አደብ ገዙ። በዚሁ መካከል ‹‹ጋሸ አብደላ … ለአላህ ብለው የዛሬን … ›› የሚል ድምጽ ሰማሁ። የግጭቱ መነሻ የዚህ የነጻ እድል ጉዳይ እንደሆነና የተጨረሰ እንደሆነ ባውቅም፣ የወላጆች ወኪል ነኝና ወላጆች የሚሉትን መስማት፣ ከዚያም ያለውን ሁኔታ ማስረዳት ነበረብኝ።

‹‹እናቴ የሚሉት ይገባኛል። ሁሉም ልጆች በነጻ ቢማሩ የሁሉም የኮሚቴ አባል ደስታ ነበር። ነገር ግን አወልያ እንደ ድሮው አይደለም። አሁን አቅሙ ተዳክሟል። አምስት መቶ ተማሪዎች ነጻ የትምህርት እድል እንዲያገኙ የሆነውም ገንዘብ ኖሮት አይደለም። ለስንት አመት ከፍተኛ እርዳታ ሲሰጥ የነበረ ስመ ጥሩው ትምህርት ቤት በእኛ ዘመን ሊዘጋ አይገባም በሚል ቁጭት የተደረገ ነው። ትምህርት ቤቱ አቅም ኖሮት፣ እኛም ለክፋት ያደረግነው አይደለም›› እያልኩ ብዙ ለፈለፍኩ። የምናገረው እ ን ዳ ል ገ ባ ቸ ው ከፊታቸው ገጽታ በውል ያስታውቃል። የቆሙት ይኸን ለመስማት አልነበረም።

 ‹‹ጋሼ አብደላ … አማራጭ የለንም። እኛም ባይቸግረን ኖሮ በልመና የሰው ፊት አይገርፈንም ነበር። አወልያ የልጆቻችን ተስፋ ነው ብለን ብንመጣ ጨለማ ተቀበለን። የኛስ ይሁን አላህ በቃችሁ ብሎ ምህረቱን እስኪሰጠን እንኖራለን። አሁን የቸገረን የልጆቻችን መጨረሻ ነው። ተምረው ሰው ይሆናሉ ብለን ነበር። እሱም አልሆን አለ።››

የሚናገሩት የተቆራረጠ ሀሳብና ሀሳባቸው የተገለጸበት ድምጽ በራሱ ስሜት የሚነካ ነበር። የውስጣቸው ስሜት ደግሞ ሊገልጹት የሚችሉት አይነት አልነበረም። የአንዷ እናት ፊት ከፍቶት አይተህ ወደ ሌላዋ ዘወር ስትል በእንባ የታፈነ ፊት ታያለህ። ይኸን ማየት ፈርተህ ወደ ሌላዋ ዘወር ስትል፣ እድሜና ችጋር የጠበሰው፣ በዚያ ላይ ተስፋ የቆረጠ እናት ፊት ታያለህ። … መግለጽ ከባድ ነው።

 ‹‹ችግራችሁ ሳይገባን ቀርቶ አይደለም። የምንችለውን ሁሉ አድርገን ለአምስት መቶ የኔ ቢጤዎች የነጻ እድል እንዲያገኙ አደረግን …›› አልኩና እንኳን ለእነሱ ለእኔም የማያሳምን ሀሳብ ተነፈስኩ። አይናቸውን ማየት፣ ከፊታቸው ገጽታ ጋር ፊት ለፊት መጋፈጥ … ።

‹‹አሁን የቀረነው ሶስት ብንሆን ነው። ምርጫ ባይኖረን፣ ሰማይ መሬቱ ባይደፋብን፣ ልጆቻችን በራሳቸው ላይ አደጋ ይፈጥራሉ ብለን ባንሰጋ እዚህ አንቆይም ነበር። ለአላህ ብላችሁ እርዱን፣ ከቅሌት አውጡን››

 የማየውንም ሆነ የምሰማውን መቋቋም አልቻልኩም። ውስጤ ተነካና እኔም ስሜታዊ ሆንኩ። ሆድ ባሰኝ። ልቤ ታፈነ። የመጨረሻውን ባላውቅም በእኔ ወጭ የእነዚህ ሶስት እናቶች ልጆች እንዲመዘገቡ ወሰንኩ። የእናቶች ምርቃን ምን ሊሆን እንደሚችል ለማንም ግልጽ ነው።

 ከዚህ በኋላ ጋሽ አብዳላ ሙሐመድ ችግረኛ ተማሪዎችን ከፍሎ አስመዘገበ የሚለው ዜና ተዛመተ፤ ብዙ ቤተሰቦችም ዘንድ ተዳረሰ። በማላውቃቸው የስልክ ቁጥሮች መጨናነቅ ጀመርኩ። የሁሉም ስልክ ደዋዮች ፍላጎትና ጥያቄ አንድ ነው። ‹‹የችግረኛ አባት መሆንዎትን ሰምተናል። አላህ ጀዛውን በምድርም በሰማይም ይክፈልዎት። … እንደሚከብድዎት እናውቃለን፣ ቢሆንም ልጄ ትምህርት አጥቶ ወደ ክፉ ነገር ከመግባቱና ከመበላሸቱ በፊት ድረሱልኝ›› የሚል ነው። አሁን ሌላ ችግር ተፈጠረ። አቅም እንደሌለኝ በፈጣሪ ስም እየማልኩ ለማስረዳት ብለፋም የሚሰማኝ ጠፋ። ሁሉም ‹‹ከኔ አንተ ትሻላለህ›› ባይ ሆነ። ጭንቀት ውስጥ ከተተኝ።

 ይኸንኑ ጭንቀቴን እንደ ዋዛ ለአንድ የቅርብ ወዳጄ አጫወትኩት። ከልቡ በተመስጦ ሲያዳምጠኝ ቆይቶ ‹‹ከባድ ሁኔታ ውስጥ ነው የገባኸው። ሁሉም የራሱን ብቻ እያስቀደመ ‹እኔን ብቻ› ስለሚል … አላህ ይርዳህ። ለማንኛውም እኔ ለሁለት ተማሪዎች የዚህን አመት የትምህርት ቤት ክፍያ ልክፈልልህ›› የሚል መፍትሄ አመጣ። የዛን ጊዜ የነበረኝን ደስታ አሁን ልገልጽልህ አልችልም። … ባይገርምህ የዚህ ወዳጄ እርዳታ ሌላ መፍትሄ ይዞልኝ ብቅ አለ። ወዳጆቼን ማስቸገር። በኔ አማካኝነት ችግረኛ ተማሪዎች መግባታቸው ሲሰማ ፈላጊዬም በረከተ። እኔም እንቢ ማለቱን ወደ ጎን አስቀምጨ ፊቴን ወደ ጓደኞቼ አዞርኩ። ብዙዎቹ አላሳፈሩኝም። ቢያምኑበትም ባያምኑበትም ሳልከብዳቸው አልቀረሁም መሰል አንድም ሁለትም ችግረኛ ልጆች ይቀበሉኛል። እኔም ተረጅና እረጅን በአካል አገናኛለሁ እንጂ መካከል ጣልቃ አልገባም። በዚህ ሁኔታ፣ ግማሹ ለአንድ አመት፣ ሌላው ለሁለት አመት እየረዳ በሁለት አመት ውስጥ ከአርባ በላይ የሚሆኑ ተረጂ ተማሪዎች በእኔ ስር ገቡ።

 በዚሁ መካከል ጀርመን አገር የምትኖር ልጄ የመጀመሪያ ልጇን ትወልድና ለመጠየቅ ወደ ጀርመን አገር እሄዳለሁ። ለአገሩ ጥቁር እንግዳ ስለነበርኩ፣ ከቀናት በኋላ የልጄ ጓደኞች እኔን አባቷን ለመቀበል የሆነ የግብዣ ፕሮግራም ያዘጋጃሉ። እንዳልኩት ተጋባዡ እኔው ስለነበርኩ የተዘጋጀውን ኬክ እንድቆርስና ዱኣም እንዳደርግ ተጠየኩ። ኬኩ አጠገብ ቆሜ ጋባዦቼን ከፊት ለፊት አየኋቸው። ብዙዎቹ በባህል ልብስ የደመቁ ሐበሾች ናቸው። በጣም ያምራሉ። ለልጄ ያላቸውን ፍቅር በእኔ ስም ለመግለጽ እንደመጡ ተሰማኝ። ለተወሰኑ ደቂቃዎች ጥሞና ውስጥ ገብቼ ስመለስ ልቤ ደረቴ ውስጥ ስትዘል አገኘኋት።

 ‹‹መቼም በመንፈስ ብቻ ሳይሆን በእድሜም ቢሆን አባታችሁ ሳልሆን አልቀርም። የአገራችን ባህል በሚፈቅደው መሰረት እዚህ አገር በምቆይበት አንድ ወር ውስጥ በቀን አንድ ስኒ ማኪያቶ ወይም ቡና የምትነፍጉኝ አይመስለኝም። ይህን ግብዣችሁን ሳስብ ቸግሮኝ የነበረ ጉዳይ ታወሰኝና ላካፍላችሁ ወደድኩ።›› አልኩና የአወልያ ትምህርት ቤት ገጠመኜንና በዚያው ምክንያት ሰዎች እያስቸገርኩ ከአርባ በላይ ችግረኛ ተማሪዎች እየተረዱ እንደሆነ፣ ባንድ በኩል የእርዳታ ፈላጊ ተማሪዎች ቁጥር እየጨመረ፣ በሌላ በኩል ይረዱኝ የነበሩ ወዳጆቼ እጃቸው እያጠረ በመሀል ማቋረጥ እንደጀመሩ ገለጽኩ። በመጨረሻም በቀን የሚጋብዙኝን አንድ ሲኒ ቡና ወይም ማኪያቶ በጥሬ ገንዘብ ቢሰጡኝ ለችግረኛ ተማሪዎች ድጋፍ እንደሚሆነኝ በሰፊው አስረዳኋቸው። እነሱም ፈዝዘው ነበር የሚያዳምጡኝ።

 በገጠመኜ ትረካ ሁሉም ስሜታቸው ተነክቶ ነበር። ይህንንም በተግባር ገለጹልኝ። አንዱ ተነስቶ ለሶስት ተማሪ ድጋፍ አደርጋለሁ፣ ሌላኛው ለአምስት፣ አንዱ ለአራት፣ ስድስት … እያለ ድጋፍ የማድረጉ ቃል መግባት ተጧጧፈ። በዚህ በልጄ አማካኝነት በተደረገልኝ የመስተንግዶ ግብዣ ባቀረብኩት የአንድ ሲኒ ቡና ወይም ማኪያቶ ግብዣ ከስድሳ በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች ድጋፍ ለማግኘት በቃሁ። … በአሁኑ ጊዜ በዚህ በጀመርኩት መንገድ ከመቶ ሀያ በላይ እርዳታ የሚያገኙ ልጆች አሉ።

 አሁን አሁን የተረጂ ልጆች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ መሄድ በራሱ ችግር እየሆነብኝ ነው። በሌላ በኩል ከሚረዱኝ ሰዎች መካከል ከፊሎቹ እኔን ላለማስቀየም ብለው እንደሆነ ይገባኛል። አንዳንዶቹ ደግሞ ለአንድ አመት ይረዱና ለቀጣዩ አመት ያቋርጣሉ። ይኸን መሸፈኑም ሌላ ጣጣ ነው። እኔም በየቤቱ መዞሩ ከእድሜዬ ጋር አልሆንልህ እያለኝ ነው። ይህን ሁሉ የታዘቡ አንዳንድ ወዳጆቼ ለምን NGO አቋቁመህ አታርፍም። በዚያም ላይ ለብዙ የሚረዱ ተማሪዎች ተደራሽ ይሆናል ይሉኛል። ሃሳቡን እንዲሁ ስታስበው እውነትነት አለው። መሬት ላይ ያለው ደግሞ ሌላ ነው። እውነት ቢኖር ከንጉሱ ጀምሮ የተቋቋመው የአወልያ ሚሲዮን ድርጅት ይህን ማድረግ ይችል ነበር። ነገር ግን በመንግስት ቀጥተኛና ስውር ግፊት ወደ ጠርዝ እየተገፋ፣ አቅሙ እንዲዳከም እየተደረገ፣ አብደላ ሙሐመድ የሚባል ሰው NGO ለማቋቋም ማሰቡ የማይቻል ከንቱ ልፋት ይሆንብኛል። በዚያ ላይ NGO ወጩ፣ ፈላጊው፣ ውጣውረዱ የትየለሌ ነው።

ከዚህ በላይ በአጭሩ የተረኩትን የቃል ታሪክ፣ የክፍል ጓደኞቼ በተገኙበት፣ እኔ እንደ የቃል ታሪክ አቀናባሪ ሐጅ አብደላ የቃል ታሪክ ተራኪ ሆነን ለኮርሱ መምህርት ለፕሮፌሰር ሉዊዛ ዴል ጉይዲስ (Luisa Del Giudice) ቀረበ። የሐጅ አብደላ የአወልያ ትምህርት ቤት ገጠመኝ ትረካው ብቻ ሳይሆን በእያንዳንዱ ሁነት የሚታየው አካላዊ እንቅስቃሴው፣ የድምጽ ቃናው አስደማሚ፣ አስገራሚ፣ መሳጭና ስሜት ነኪም ነበር። በተለይ አወልያን ሲያነሳ፣ ውስጣዊ ስሜቱ እጅጉን መጎዳቱ ያስታውቅበት ነበር። ለማንኛውም የምንወስደው ኮርስ ጊዜው አለቀና ከፕሮፌሰር ሉዊዛ ጋር የመሰናበቻ ጊዜያችን ደረሰ። ፕሮፌሰሯ ተግባቢ፣ ፈጣንና አትጊ ነበረች። ወደ አፍሪካ አህጉር ስትመጣ የመጀመሪያዋ ነበር። ስለ ኢትዮጵያ ደግሞ የሚመች ነገር አልሰማችም ነበር። ሌባ የበዛባት አገር ናት ብለዋት የበር መቆለፊያ ቁልፍ፣ መብራት የለም ብለዋት የእጅ ባትሪ፣ መድሃኒት የለም ብለዋት ለድንገተኛ ደራሽ አገልግሎት የሚውል መድሃኒት፣ የረባ ልብስ የለም ብለዋት መጠነኛ ልብስ፣ ወዘተ ይዛ መጥታ ነበር። እዚህ አዲስ አበባ ኑራ፣ ላሊበላና አክሱም ደርሳ ኢትዮጵያን ስትረዳ፣ ቀድማ በነበራት ስጋት ፋንታ ከአዲስ አበባ ጋር ፍቅር በፍቅር ሆነች። ያው እኛ ደግሞ የአዲስ አበባና የኢትዮጵያ ወኪል ሆንንና አብረናት መልካም የትምህርት ጊዜ አሳለፍን። በመጨረሻ በአንድ የባህል አዳራሽ ውስጥ የመሰናበቻ ፕሮግራም አዘጋጀን። በምንችለው አቅም እንደ ቀሚስና ነጠላ፣ የአንገት ፎጣና ጌጣጌጥ የመሳሰሉ ልዩ ልዩ ባህላዊ የመታሰቢያ ስጦታ አበረከትን።

ፕሮፌሰር ሉዊዛ በፈንታዋ የተማሪዎቿን ስም እየጠቀሰች፣ ስጦታዋን ከተረዳችላው ባህሪያቸው ጋር ለማዛመድ እየሞከረች፣ በዚህም ፈገግታን እያነገሰች ይዛቸው የመጣቻቻቸውን እቃዎች መታሰቢያ አደረገች። በዚያን ጊዜ ከሆነው፣ ከመካከላችን ጆሮዎቹን በጥጥ የሚሸፍን ነበረ፤ ለዚህ ተማሪ መድሃኒት ተበረከተለት። ከመካከላችን የመስክ ተሞክሮውን የሚደጋግም ነበረ፤ ለሱ የበር ቁልፍ ተሰጠው። ለሴቶቹም እንዲሁ እንደ ባህሪያቸውና ሰውነታቸው የሚመጥኑ ልብሶች ለዛ በታጀበ ጨዋታ ተሰጠ። በዚህ መልኩ ለኔ የሚበከረትልኝ የስጦታ ጊዜ

“አዲስ አበባ ኑራ፣ ላሊበላና አክሱም ደርሳ ኢትዮጵያን ስትረዳ፣ ቀድማ በነበራት ስጋት ፋንታ ከአዲስ አበባ ጋር ፍቅር በፍቅር ሆነች። ያው እኛ ደግሞ የአዲስ አበባና የኢትዮጵያ ወኪል ሆንንና አብረናት መልካም የትምህርት ጊዜ አሳለፍን”

ደረሰና ‹‹ኦ! ሙሐመድ›› አለችና ፈገግታ በፈገግታ ሆና (ወይም መስሎኝ) አንድ የተጠቀለለ እቃ የያዘ እጇን ዘረጋችልኝ። ስጦታዬን በስስትና በጉጉት ተቀበልኩ። እሽጉ ውስጥ ያለው ነገር ምን ይሆን? አይኖቼ እሽጉን ዘልቀው ወደ ውስጥ መዝለቅ ቃጣቸው። በዚሁ መካከል ስጦታው የታሸገበት መጠቅለያ ላይ በደማቁ የተጻፈ መልእክት አገኙ፤ ‹‹Mohammed ILLUMINATION!››

 የስንብት ግብዣው በዚህ መልኩ ቆየና ከፕሮፌሰር ሉዊዛ ጋር በአካል ለመለያየት እኛ ባለንበት መቆም፣ እሷ ወደ መኪና መግባቷ ግድ ሆነ። በዚሁ መካከል ፕሮፌሰር ሉዊዛ መኪና ውስጥ እንዳለች ‹‹ሞሀመድ›› ስትል ጠራችኝ። ‹‹አቤት ፕሮፌሰር›› አልኳት በፍጥነት፣ ምን ተፈጠረ ብዬ። ‹‹በነገራችን ላይ በቀን የአንድ ስኒ ቡና ግብዣውን አልረሳውም – ILLUMINATION ›› ተሳሳቅን።

 ከወራት በኋላ፣ በትምህርት ፕሮግራሙ አስተባባሪ በዶ/ር ፈቃደ አዘዘ በኩል አንድ መልእክት እንዳለኝ ተነገረኝ። ዶ/ር ፈቃደ አሜሪካ መሄዱን አውቅ ስለነበር፣ እዚያ ከሚኖሩ ወዳጆቼ የሆነ መጽሐፍ ሳይላክልኝ እንዳልቀረ ግምቱ ነበረኝ። ከዚያ በዘለለ ዶ/ር ፈቃደን ከማን፣ ምን እንደተላከልኝ ጠይቆ ለመረዳት የሚያስችል ቅርበት አልነበረኝም። መልእክቱ ደርሶኝ የሆነውን እስከምረዳ መጠበቅ ነበረብኝ።

 ዶ/ር ፈቃደ በቀጠረኝ እለት አንድ የታሸገ ፖስታ ሰጠኝ። ከፕሮፌሰር ሉዊዛ የተላከ ነበር። ፖስታው ቀለል ያለ መጠንና ክብደት ነበረው። በብርሃን ፍጥነት በሚሉት ሩጫ ፖስታውን ከፈትኩት። አንድ ለሁለት የተጣጠፈ ወረቀት መዘዝኩ። ያው በእንግሊዝኛ የተጻፈ አጠር ያለ ጽሁፍ ማንበብ ጀመርኩ።

 ‹‹ስንተዋወቅ አፍሪካ ብሎም ኢትዮጵያ የመጀመሪያዬ እንደነበር እንደነገርኳችሁ የምታስታውስ ይመስለኛል። በዚያ ላይ ስለ ኢትዮጵያ መልካም መረጃ ስላልነበረን፣ በተለይ ቤተሰቦቼ ጭንቀት ውስጥ ነበሩ። በዚህ የተነሳ ይመስለኛል፣ በደህና ወደ አገሬ በመመለሴና በሰላም ከቤተሰቤ ጋር በመቀላቀሌ፣ ቤተሰቦቼ ‹የእንኳን ደህና ተመለሽ› የአቀባበል አጠር ያለ ግብዣ አደረጉልኝ። በደንቡ መሰረት ኬክ እንድቆርስ ጋበዙኝ። በዚህ ቅጽበት የሐጅ ሙሐመድ (አብደላ ሙሐመድ) በቀን የአንድ ቡና/ማኪያቶ ግብዣ ታሪክ ታወሰኝና የቀረበልኝን ኬክ ከመቁረሴ በፊት ለቤተሰቦቼ የሆነውን ተረኩላቸው። ሁሉም የቤተሰቤ አባሎች ከልባቸው ተመስጠው የገጠመኜን ተረክ ይከታተሉ ነበር። ከዚህ ሁሉ በኋላ አንድ ሀሳብ ቀረበ። ሁሉም ለሐጅ ሙሐመድ የአንድ ቀን ቡና ዋጋ ሊጋብዙት ወሰኑ። ከዚህ ፖስታ ውስጥ የምታገኘው ሀምሳ ዶላር በዚህ እለት ለሐጅ አብደላ ልጆች የተሰባሰበ የአንድ ቀን የቡና ግብዣ ነው። በእኛ ስም አድርስልን – Mohammed ILLUMINATION!››

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top