የታዛ ድምፆች

ዳ ይ ስ ሌ ክ ሲያ

‹‹ ….. በየሀገሩ፣ በየአህጉሩ ካሉት ተማሪዎች ውስጥ ከአምስት እስከ ሰባት በመቶ የሚሆኑት በዳይስሌክሲያ ይሰቃያሉ›› ይላል አንድ አደባባይ የዋለ ጥናታዊ ሰነድ። በሰነዱ እንደተመለከተው ‹‹በልዩ ዕውቀት፣ በልዩ ጥበብ የተካኑ፣ የሠለጠኑ መምህራን ረድኤት ካልታከለበት በቀር የዳይስሌክሲያ ተማሪዎች ችግር በመጠኑም ቢሆን ሊቃለል አይችልም። ፈጽሞ ይወገዳል ማለትማ እስከአሁን አልተቻለም።››

ለመሆኑ ‹‹ዳይስሌክሲያ›› ምንድን ነው? ሰላሣ ዓመት በፈጀ ጥልቅ ምርምር የተሳተፉ ጠቢባንና ጠባባት የደረሱበትን ‹‹አጠቃላይ ስምምነት›› መሠረት በማድረግ አንድ ድርሳን እንዳሰፈረው ‹‹ዳይስሌክሲያ ንባብን፣ እንዲያ ሲልም ጽሕፈትን በመማር ረገድ የሚፈጠር ልዩ ችግር ነው።››

ምስኪን አነባበብን የሚመለከተውን ደግሞ ለብቻው በመሰንጠር ‹‹ሊጋስቴኒያ›› (ሕፀፀ- ምንባብ) ብለው የሠየሙት እንደ ጎርጎርዮሳዊው ቀመር በ1916 ዓ.ም ጀርመናዊው ማዕምረ ሥነ ልቡና ፖል ራንሸቡርግ መሆናቸውን ድርሳናት ያወሳሉ። ይሁንና በሌጋስቴኒያም ሆነ በዳይስሌክሲያ ታሥረው መከራ የሚቆጥሩት ጉብሎች ከዚያ ችግራቸው የሚገላገሉበትን ብልኃት ከማውጣትና ከማውረድ በቀር እስከ አሁን አንዳች ዘላቂ መፍትሔ አለመገኘቱን የሚጠቁሙ ዘገባዎች አልታጡም። ጥናቱና ምርምሩ ግን እንደቀጠለ ነው።

 በተለይም ካለፉት ሦስት አስርት ጀምሮ በስፋትና በጥልቀት ምርምር የሚያካሂዱ አያሌ የሕክምና ሊቃውንትና የሥነ ልቡና ጠበብት፣ መምህራንና ርዕሳነ መምህራን መኖራቸው ተረጋግጧል። መንስኤውንም ሆነ መፍትሔውን ለማግኘት ግን አልበቁም። በሌላ በኩል ደግሞ ለዚህ መፍትሔ ላጣ ብርቱ ችግር ወላጆችን፣ ትምህርት ቤቶችንና አካባቢዎችን ተጠያቂ ሊያደርጉ የሞከሩ በሰሎች መኖራቸውን የሚጠቁሙ ዘገባዎች የዓይን ምስክርነት አልተነፈጋቸውም። ‹‹በአዕምሮ የተግባር እንቅስቃሴ ስንፈት ሳቢያ ብቻ የሚከሰት እንጂ በሌላ ምክንያት የሚሰርፅ አይደለም›› ሲሉ አስተያየት የሰነዘሩ ሐኪሞችም ተደምጠዋል። የዶክተሮቹ ውጤት በመጠኑ ትክክል ነው። የቀሩት አባባሎች ግን እንዲያው ‹‹አስተያየት›› ከመሰኘት አልፈው በሊቃውንት በረከተ ጽድቅ የተቸራቸው አልሆኑም።

ሊቃውንት እንዳሰመሩበት በዳይስሌክሲያ በተጨመደዱ ሰዎች ዘንድ ግድፈተ ፊደል ውልጠተ ፊደል ይስተዋላል። ለምሳሌም ተቀራራቢ ድምፅ ያላቸውን “ደ” ን ከ “ተ” ለመለየት በብርቱ ይሳናቸዋል። እንዲሁም በ”ገ” እና በ“ከ” መካከል ያለውን ልዩነት ለማወቅ ፍጹም ያቅታቸዋል። ለዚህም ነው የአንጎል ድክመት መኖሩ ሊታመን የቻለውና ከላይ እንደተጠቀሰው የዶክተሮች ጥናት ግኝት በመጠኑ ትክክል መሆኑ የተመሰከረለት። በመጠኑ የተባለውም ሙሉ በሙሉ በእርሱ ምክንያት ብቻ ነው የሚከሰተው በማለት ከእንዲህ ዓይነቱ መደምደሚያ ለመድረስ ስለማይቻል መሆኑን ሰነዱ ስለሚያረጋግጥ ሳይሆን አልቀረም። ስለምን? ለድክመቱ አስተዋፅኦ ያደረገ ሌላ ድክመት ሳይኖር እንደማይቀር ይገመታልና! ወረደም ወጣ፣ በዚህም መጣ በዚያ፣ ሌላ ተደራቢ ሚና ይኑረውም አይኑረውም ዞሮ ዞሮ ያው የአእምሮ ስንፈት የአንጎል ድክመት መኖሩን በስንፈቱ፣ በድክመቱ አስባቢያም ግድፈቱ መከሰቱን ለማስተባበል የቃጡ ተጠባቢዎች አልተገኙም። ይህን አስመልክተውም እንዲህ ይላሉ።

በድምጽ ተቀራራቢነት ያላቸውን ፊደላት ማለትም “ደ” ን እና “ተ” ን “ገ” ን እና “ከ” ን አድምጠው ልዩነታቸውን ለመረዳትና በትክክል በወረቀት ለማስፈር የማይችሉት በአዕምሮ ስንፈት፣ ድክመት፣ ጉድለት ሳቢያ መሆኑን አረጋግጠዋል። ለምን አንጎላቸው ደከመ? የተሰኘው ጥያቄ ደግሞ አንድ ራሱን የቻለ ጉዳይ ነው። ለዳይስሌክሲያ ወይም ለሊጋስቴኒያ መንስኤ ምክንያት የሆነ ሌላ ተደራቢ ሰበብ ሊኖርም ይችላል። በተጨማሪም እነዚያው አበሰኞች ሆሄን በትክክለኛ ስያሜው ሳያምታቱ ለመጥራት፣ ለመረዳትና ያን የተረዱትን ሳያዛንፉ ለመጻፍ ካለባቸው መከራ ሌላ የሆሄውን አቅጣጫ ለመለየት በሲራዊ (ኦፕቲካል) ግንዛቤ ለማግኘት መጠነኛ ችግር እንደሚገጥማቸው እናያለን። ይህም በማያወላውል ሁኔታ የአዕምሮ ተግባር ጉድለትን ያመለክተናል። በዳይስሌክሲያ ተተብትበው ፊደል ሲገድፉ አዛብተው ሲጽፉ የሚገኙት ሰዎችም እንዴትና የት እንደ ጎደለ ለማወቅ አቅም ያንሳቸዋል።

 ትምህርተ ቤት ገብቶ ገና “ሀ” ብሎ ከጀመረበት ጊዜ አንሥቶ ዳይስሌክቲክ ወይም ዳይስሌክኛ መሆኑ የተነገረለት አንድ የአሥራ ስድስት ዓመት ጉብል “ቀስ በቀስ የጅልነት ስሜት እየሰረጸብኝ መሄዱን ብቻ ነው ልገነዘብ የበቃሁት። በአጠገቤ የተቀመጡት ተማሪዎች መምህሩ በቃል የሚያስተላልፈውን እያደመጡ ሲጫጭሩ እኔ ግን እንዴት ሆሄያቱን አቀናጅቼ፣ አንዱን ከሌላው ለይቼና ተረድቼ እንደምጽፍ እቸገራለሁ፣ እጨነቃለሁ። ራሴን በጅልነት ኮንኜ እነርሱን ትጉሃኑን አደንቃለሁ” ሲል ነው ብሶቱን ያስተጋባው።

ጠበብት እንዳረጋገጡት ብዙውን ጊዜ ችግሩ ይበልጥ እየጎላ መታየት የሚጀምረው በ3ኛው የትምህርት ዓመት ላይ ነው። ወይም መምህሩ ትምህርቱን በቃል እየሰጠ ተማሪዎቹ እያደመጡ እንዲጽፋ ማለማመድ በሚጀምርበት ወቅት ነው። ስንፈቱ፣ ጉድለቱ ጉልህ የሚሆነው ያኔ ነው። እስከዚያ ድረስ ግን ሕፃናቱ በአመዛኙ ድክመታቸውን ሸፍነው ይገኛሉ።

ለምሳሌ ከላይ የተገለጸው ያ የአሥራ ስድስት ዓመት ጉብል አበሰኛ 1ኛ ና 2ኛ ክፍል በሚማርበት ወቅት “አውቃለሁ” ከማለት በቀር “አይገባኝም” ሲል እንዳልተናገረ ራሱ መስክሯል። መምህሩ አንዳንድ ነገር በቃል ሲያስረዳ ግን ያችን ከአስተማሪው አንደበት የፈለቀች ፊደል በትክክል አይጠራትም። ድክመቱንም እንደምንም ሸፍኖ ፈተናውን በትግል ያልፋል። ወደ 3ኛ ክፍል በተሻገረበት ወቅት ግን ቀስ በቀስ ተጋልጧል።

መቼም አንድ ሥነ ሕይወታዊ፣ ሥነ ልቦናዊ፣ ሥነ አዕምሮአዊ ወይም ማኅበራዊ ችግር ሲከሰት ያን ውጥንቅር ለመፍታት ይቻል ዘንድ እውቅ ሊቃውንት፣ በሳል መማክርት የሚወያዩበት መድረክ መቆርቆሩ በባሕር ማዶው አህጉር የተለመደ ነውና በኮሎኝ፣ ፌደራላዊት ጀርመን የተቋቋመ አንድ ተቋም ሕልውናውን ካስመሰከረ ቆየትየት ማለቱ ታውቋል።

ለአያሌ ዓመታት ሲመረምሩና ሲያጠኑ ጊዜ ያሸመገሉት እነዚያው ጀርመናውያን ተጠባቢዎች ተቋሙን በውይይትና በጥናት መድረክነት ብቻ አይደለም የተጠቀሙበት። ‹‹የሌጋስቴኒያ ሕክምና›› ሊሰጥ እንደሚችልም ተዘግቧል። የተቋሙን መርሐ ግብር አንድ በአንድ መዘርዘሩን ለጊዜው እናቆየውና ሚካኤል ፕራስ በመሰኘት የታወቁት የዳይስሌክሲያ ማእምር ያሠፈሩትን እንመልከት።

‹‹ዳይስሌክሲያ›› ይላሉ ሚካኤል ፕራስ ‹‹በአጭሩ የሚገላገሉት አይደለም። ይበልጡንም ትምህርቱ በልዩ መምህራን ካልተሰጠ በቀር ከዓመት ዓመት ችግሩ እየበረታ ይሄዳል። ዳይስሌክሲያ የሚቆልለውን ሥነ ልቡናዊ፣ ሥነ አዕምሯዊ ጫና አስመልክተው የተናገሩት ሐራልድ ኩቢሽ በወገናቸው ደግሞ እንዲህ ነው የሚሉት፣ ‹‹በጊዜ ብዛት የሕፃናቱ ሞራል ክፉኛ ይነካል። ወደ ትምህርት ቤት ለመሔድም ፍላጎታቸው የነቃ አይሆንም።›› በዚህም ብቻ አይደመደምም። ዳይስሌክሲያ በብርቱ ነው የሚያዳሽቀው። በዚህ ረገድ አንድ ድርሳን አቅራቢ ያሠፈሩትን ስንመለከት እንዲህ የሚነበብ ሆኖ እናገኘዋለን።

‹‹… የኤ-ቢ-ሲ-ዲ- ትግሏ ፍሬ አልባ መሆኑን ከተረዳች ሰንብታለች። አንድ ኮረዳ! በአሁኑ ጊዜ ጋዜጣ ሲንኮሻኮሽ ስትሰማ እንኳ እንደ እብድ ያደርጋታል። ወረቀት ሲዘረጋጋ ወይም ሲተጣጠፍ ድምጹ ወደ ጆሮዋ የገባ እንደሆነ ታለቅሳለች።››

“ዱላ ይበልጥ ያደድባል፣ በትር ይበልጥ እልኸኛ ያደርጋል፣ ጋግርታም ያደርጋል እንጅ አያተጋም። ደግ አያስመለክትም፣ የጥበብ ጎዳና አይከፍትም። አዕምሮን ብሩኅ አያደርግም። መጠላትን እንጂ መወደድንም አያስገኝም”

ሌላው ‹‹አሳሳቢ›› ሲሉ ፈታሾች ያሰመሩበት ነጥብ አለ። ይኸውም የመምህራንና የወላጆችን ስልቹነት ነው። ለዚህም እንደ ምሳሌ አድርገው ካቀረቧቸው ውስጥ “በሁለት ሰዓት ውስጥ ሦስት መስመር ብቻ ከሚጽፍ ልጅ አጠገብ መቀመጡ ራሱ አዕምሮ ማጉበጥ ነው።” ሲሉ ያማረሩ አንድ እናት ተጠቅሰዋል። የመምህራን ስሞታም ከዚህ ይበልጥ የጎፈነነ ነው። ‹‹የዳይስሌክሲያ ጣጠኞችን ለማስተማር በልዩ ጥበብ የተካኑ፣ በተለይ የሠለጠኑ መምህራን መሆን ይገባቸዋል›› የተባለውም ለዚህ ሳይሆን አልቀረም። ከዚህ ግንዛቤ በመነሣትም ነው ዛሬ በርከትከት ያሉ ‹‹ልዩ መምህራን›› በአንዳንድ የአውሮፓ ት/ቤቶች ሊገኙ የበቁት።

 የማኀበራዊ ጉዳይ ተመልካቾች እንደዘገቡት ደግሞ በተለይ ስልቹና ብስጩ ወላጆች ልጆቻቸውን ይበልጥ ችግር ላይ ከመጣል የተመለሱ አልሆኑም። ለምሳሌ ከላይ የተጠቀሱት እኒያ ‹‹ከእርሱ ጋር ተጎልቶ መዋል አንጎል ማጉበጥ ነው›› ያሉት እናት በልጃቸው እንደተወደዱ አልዘለቁም። ‹‹ተማር! አንተ ጅል!›› እያሉ በልጅነቱ ይሰድቡት፣ አንዳንዴም በንዴት ይኮረኩሙት ነበረ። እርሱ ግን በቁጣና ቁንጢጥ ከዳይስሌክሲያው ሊገላገል አልቻልም። ይበልጥ በግድፈቱ፣ በውልጠቱ፤ በድክመቱ እንደደነደነ ቀረ። ከዚህም ባሻገር እናቱን ዓይንሽን ለአፈር ይላቸው ገባ። አድጎ ትልቅ ከሆነ በኋላም ዘወር ብሎ አላያቸውም።

እዚህ በሀገራችንም ‹ዳይስሌክሲያ፣ ሊጋስቴኒያ› ተብሎ አይታወቅ ወይም አይነገር እንጅ በእንዲህ ዓይነቱ ችግር ተይዘው የሚማቅቁ፣ አበሳ የሚቆጥሩ መኖራቸውን እናውቃለን። “ይሄ ደደብ ትምህርት አይገባው ገና የፊደል ዘር እንኳን መለየት አልቻለም …. በአሥር ዓመቱ ‹‹ሀ››ን እንኳ ከ‹‹አ›› አይለይም። ወዘተ…. ወዘተ…” ሲባል እንሰማለን። ችግሩን ጠለቅ ብሎ የመረዳቱ ነገር እጅግም የለምና!። በዚህ አጋጣሚ የሀገራችን ወላጆች እንዲገነዘቡ ማድረግ ተገቢ ይመስለኛል። ዱላ ይበልጥ ያደድባል፣ በትር ይበልጥ እልኸኛ ያደርጋል፣ ጋግርታም ያደርጋል እንጅ አያተጋም። ደግ አያስመለክትም፣ የጥበብ ጎዳና አይከፍትም። አዕምሮን ብሩኅ አያደርግም። መጠላትን እንጂ መወደድንም አያስገኝም።

ስድብም ከዱላ ያላነሰ የውድመት ተልዕኮ አለው። ከፍ ሲል ገልጸነዋል። ይህን ቁም ነገር ኀብረተሰባችን እንዲረዳው ያሻል። የአያሌዎች አጉል ጠባይ የልጅን ቅስም መስበር በአጓጉል ቁርፍድፍድ ቋንቋ ማቁሰል፣ ማጎሳቆል፣ መደብደብ መሆኑን የዚህ ጸሑፍ አቅራቢ በሚገባ ያውቃል። ከዚህ ክፉ ልማድ መላቀቅ ይገባል።

 ምሁራን እንደሚያስገነዝቡት ‹‹ልዩ መምህራን›› በማይገኙበት ሥፍራ ወላጆች ዳይስሌከኛ ልጆቻቸውን በከፍተኛ ትዕግሥት ለማስጠናት መጣር አለባቸው። ‹‹አንተ አይገባህም፣ አትረባም፣ ደደብ…..›› ማለት ፈጽሞ አይኖርባቸውም። ችግሩን ራሱ ልጁ ሆን ብሎ የፈጠረው አለመሆኑን መረዳት ይገባቸዋል።

 በተረፈ ግን የዳይስሌክሲያ ምርምር በስፋት በዓለም እንደቀጠለ ነው። “ጠቢባዊ በረከት ያልተነፈገው ጥናት ለብዙዎቹ አበሰኞች የተስፋ ጭላንጭል ያሳያል” ሲሉ ነው ብዙዎቹ የሚተማመኑት።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top