ከቀንዱም ከሸሆናውም

የፕላኔታችን ምስጢራዊ ኪነ-ሕንፃ በኢትዮጵያ

የታነፀው የዛሬ 950 አመት ግድም ነው። የሚገኘውም ከላሊበላ ከተማ 42 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው። ይምርሃነክርስቶስ ቤተ-ክርስትያን ይባላል:: ወደ ይምርሃነ ክርስቶስ ቤተ-ክርስቲያን ሲኬድ መንገዱ ምቹ አይደለም። በዚህ ጠመዝማዛና ወጣ ገባ መንገድ ላይ ለመኪናውም ሆነ ለአሽከርካሪው እንዲሁም ለተጓዡ የምቾት ነገር የማይታሰብ ነው። ነገር ግን ጉዞው እንደተጠናቀቀ ከፊት ለፊታችን የቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስን የዋሻ ውስጥ ቤተ-ክርስትያንን እናገኛለን። ገና    ውጭያዊ ገፅታውን ስንመለከተው እንኳንስ የዛሬ 950 አመታት የተሰራ ነው ብሎ መቀበል ይቅርና በቅርቡ ተሰርቶ የተጠናቀቀ ውበትን ከግርማ ሞገስ ጋር የተጐናፀፈ ኪነ-ህንፃ እንደሆነ እንገምታለን። እውነቱን ስናውቅና ውስጡን መጐብኝት ስንጀምር ደግሞ እጅግ የሚያስገርሙ ምስጢራትን እናገኛለን።

 የዚህን ቤተ-ክርስትያን የኪነ-ህንፃ አሰራር በተመለከተ የዛሬ አስራ አራት አመት ግድም አንድ ዶክመንተሪ ፊልም ለመስራት እኔና የስራ ባልደረቦቼ ወደ ስፍራው ተጉዘን ነበር። ከዚያም ተአምራዊውን ቤተ-ክርስትያንና ዙሪያ ገባውን ስንቀርፅ ቆየን። ቀጥሎም ስለዚሁ ቤተ-ክርስትያን አሰራር ለመናገር አቅማችን አልፈቀደም። ከዚያም አለፍ ሲል ደግሞ ይህን ቤተ-ክርስትያን በተመለከተ ጥናት ተደርጐ የተፃፉ መረጃዎች እምብዛም ስለሌሉ ያቀድነው ሁሉ ሳይሳካልን ቀርቶ እስካሁን ድረስ አለ።

በአንድ ወቅት ደግሞ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስትያን ስር የሚገኘው የማህበረ ቅዱሳን የጥናትና ምርምር ማዕከል ጥሪ አደረገ። የጥሪው መሰረትም ሦስተኛውን አመታዊ የጥናትና የምርምር ጉባኤ በብሔራዊ ሙዚየም አዳራሽ እንደሚያደርግ እና በዚያ ላይ ታዳሚ እንድንሆን ነው። ጉባኤው ለሁለት ቀናት የተካሄደ ሲሆን በዚህም ቤተ-ክርስትያኒቱን በተመለከተ አራት ሰፋፊ የጥናትና ምርምር ውጤቶች ቀርበዋል። ከነዚህ መካከል ደግሞ ዛሬ ርዕሰ ጉዳያችን ያደረግነው የቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ የዋሻ ውስጥ ቤተ-ክርስትያን ታሪክ አንዱ ነው።

 በዚህ ቤተ-ክርስትያን ላይ የመነሻ ጥናት ያቀረበው ደግሞ ዲያቆን ዶ/ር መንግስቱ ጐበዜ ነበር። ዶ/ር መንግስቱ ጐበዜ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የአርኪዮሎጂ ዲፓርትመንት መምህር ነው። የማህበረ ቅዱሳን የጥናትና ምርምር ክፍል ውስጥም ኃላፊ ነበር። ከዚህ በፊት ሁለት መፃህፍትን ለአንባቢያን ያደረሰ ተመራማሪ ነው። እ.ኤ.አ በ2004 ዓ.ም በእንግሊዝኛ ቋንቋ ‘‘Lalibela and Yimrehanekirstos; the Living Witnesses of Zagwe Dynasty’’ /ላሊበላ እና ይመርሃነክርስቶስ፣ የዛጉዌ ሥርወ መንግስት ህያው ምስክሮች/ በሚል በአማርኛ ልንተረጉመው የምንችለውን ጥናት አሳትሟል። ከዚያም እ.ኤ.አ በ2008 ዓ.ም ‘‘HERITAGE TOURISM IN ETHIOPIA’’ የተሰኘ ሌላ መፅሀፍ በእንግሊዝኛ ቋንቋ አሳትሟል። በአማርኛ ‘የቅርስ ቱሪዝም በኢትዮጵያ’ ልንለው የምንችለው መጽሐፍ ነው። አሁን ደግሞ Yemirehanekirestose A bridge between Axum and Lalibela Civilization የሚል መጽሀፍ አሳትሟል:: ስለዚህ መንግስቱ ጐበዜ የይምርሃነክርስቶስ ቤተ-ክርስትያንን ጉዳይ ይዞ ሲቀርብልን ምስጢራዊውን ኪነ- ህንፃ ለማስተዋወቅ በአደባባይ ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኘነው እሱን መሆኑንም ልብ ማለት አለብን። ምክንያቱም የይምርሃነክርስቶስ ኪነ- ህንፃ ከጠቢባን ብዕርና ውይይት ተሸሽጐ የኖረ ተአምራዊ ቤተ-ክርስትያን ነው። እርግጥ ነው ስለ ይምርሃነክርስቶስ ማንነትና ስብዕና የፃፉ የሉም ማለት ግን አይደለም።

 ዲያቆን መንግስቱ ጐበዜ ገና በመግቢያ ንግግሩ ላይ ሲገልፅ፣ ዛሬ የምናደርገው በይምርሃነክርስቶስ ቤተ-ክርስትያን ውስጥ ጉብኝት ነው። ከተሳካልኝ አስጐበኛችኋለሁ በማለት ጀመረ። በፎቶ ግራፍ መግለጫዎች በታጀበው ማብራሪያው ማስቃኘት ጀመረ።

በዋሻ ውስጥ ሁለት ኪነ-ህንፃዎች አሉ። አንደኛው የይምርሃነክርስቶስ ቤተ-መንግስት ነው። ይምርሃነክርስቶስ ከኢትዮጵያ ነገስታት ውስጥ አንዱ ስለነበር ለአርባ ዓመታት ሀገሪቱን አስተዳድሯታል። ዘመኑም ከ1053 እስከ 1093 ዓ.ም እንደነበር ተክለፃዲቅ መኩሪያ በታሪክ መጽሐፋቸው ውስጥ ጠቅሰውታል። ይህ የአገዛዝ ዓመተ ምህረት በተለያዩ ፀሐፊዎች የተለያየ ዘመን ተፅፎበታል። ለምሳሌ ኀሩይ ወ/ስላሴ ከ1077-1117 ዓ.ም ብለው ጽፈዋል።

የሆነ ሆኖ ሁሉም ፀሐፊዎች የሚስማሙበት ቅዱስ ይምርሃነክርስቶስ ኢትዮጵያን በአስራ አንደኛው ዘመነ መንግስት ላይ፣ የዛጉዌን ስርወ መንግስት ወክሎ ለአርባ አመታት እንደመራት ነው። በዚህ ዘመኑም በርካታ ምድራዊና መንፈሳዊ ተግባራትን አከናውኖ አልፏል። ከነዚህም ውስጥ ቀደም ብለን በመግቢያችን ላይ የገለፅነው ቤተ- መንግስቱንና ቤተ-ክርስትያንን በዋሻ ውስጥ ሰርቶ አልፏል። እነዚህ ኪነ-ህንፃዎች የዛሬ የትኩረት አቅጣጫዎቻችን ናቸው።

 ይህ ዋሻ ውስጥ ያለው የቅዱስ ይምርሃነክርስቶስ ቤተ-ክርስትያን የተሰራው ውሃ ላይ ነው ይባላል። ከስሩ ውሃ መኖሩ ይነገራል። ከዚህ በተጨማሪም ውሃ ላይ እንደቆመ ለማሳየት ቀሳውስቱ ረጅም እንጨት ወደ መሬት ውስጥ እየከተቱ ያሳያሉ። ‘ማየት ማመን ነውና’ የቤተ-ክርስትያኑ መሠረት ስሩ ውሃ መሆኑን እንመለከታለን። ይሄ አንድ ትንግርት ካልሆነ በስተቀር እንዴት ያንን የሚያክል ቤተ-ክርስትያንና ቤተ-መንግስት ውሃ ላይ ለ950 ዓመታት ቆሙ ብሎ ማሰብ ግዴታ ነው። ምስጢራዊው የይምርሃነክርስቶስ ኪነ- ህንፃ የተቀመጠበት ውሃ ምንድን ነው? ይሄስ እንዴት ሊሆን ቻለ? እውነትስ ውሃ ላይ ነው እንዴ ያለው? የሚሉትን ጥያቄዎች በዘርፉ ባለሙያዎች የሆኑ የውሃ ጠበብቶች (Hydrologists) ምርምር ማድረግ እንደሚገባቸው ጥናት አቅራቢው ዲያቆን መንግስቱ ጐበዜ አሳስቧል። በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ግን የቤተክርስትያኑ መሰረት ውሀ መሆኑን መናገር ይቻላል::

 ሁለተኛው ትንግርታዊ ጉዳይ ይህ ቤተ-ክርስትያን የተገነባበት ሂደት ፍፁም ምስጢራዊ መሆኑ ነው። ለምሳሌ መሠረቱ ድንጋይ ነው። ቋሚዎቹም በከበረ ድንጋይ የቆሙ ይመስለናል። እንደገና ደግሞ ድንጋዩ ላይ ፍፁም አንድ ላይ ተጣብቀው የተፈጠሩ የሚመስሉ እንጨቶች ውበትን ተጐናፅፈው የቤቱ ቋሚዎች ሆነዋል። ድንጋይ እና የእንጨት ቅርፆች አንድ ላይ የተዋሃዱበት ምስጢር እንዴት እንደሆነ አይታወቅም። በአጠቃላይ አሰራሩ ድንጋይ እና እንጨት ያሉበት ቢሆንም፣ እንዴት እንደተጣበቁ፣ ምንስ እንዳያያዛቸው የሚታወቅ ነገር የለም። በምስማርም ሆነ በጀሶ መያያዛቸውን የሚያውቅ የለም። ነገር ግን እስከ አሁን ድረስ ውበትን ከግርማ ሞገስ ጋር ተጐናፅፈው ለ950 ዓመታት ድረስ ቆይተዋል። ስለዚህ የኪነ-ህንፃ ጠበብቶች የትኩረት አቅጣጫ አድርገውት ይህን ምስጢር እንዲፈቱት መንግስቱ ጐበዜ ይጠቁማል።

 ሦስተኛው አስገራሚ ጉዳይ የሥነ-ጥበብ ውጤቶች የሆኑት የግድግዳ እና የጣሪያ ላይ ስዕሎች ናቸው። የይምርሃነክርስቶስ ቤተ-ክርስትያን በልዩ ልዩ ማራኪ ስዕሎች ያሸበረቀ ነው። ስዕሎቹ ደግሞ ከወትሮው ከምናውቃቸው የእምነት ስዕሎች ወጣ ያሉ ናቸው። ለምሳሌ ሁለት አፍ ያለው አሞራ፣ ውሻ፣ እንደገና ደግሞ ከውሻው ጭራ ላይ የሚቀጠል ሌላ እንስሳ፣ አሳዎች እና ሌሎችም ስዕሎች የጣሪያውን ገፅታ በቀለማት አሸብርቀውታል።

ከዚህ በተጨማሪም የሂሳብ ምስሎችን (Geometric Figures) የያዙ ስዕሎች አሉ። (Triangle) ሶስት ጐን፣ (Rectangle) አራት ጐን፣ (Square)፣ ክብ (Circle) ስድስት ጐን (Hexagon) እያለ በርካታ የሂሳብ አስተሳሰቦችን የያዙ ምስሎች የይምርሃነክርስቶስን ቤተ-ክርስትያን ጣሪያ የዛሬ 950 ዓመታት አሸብርቀውታል። ቤተ-ክርስትያኑ የሊቃውንት ብሩሾች ያረፉበት የስልጣኔ ማሳያ እንደሆነ ተመራማሪው መንግስቱ ጐበዜ ይጠቁማል።

ምክንያቱም በጣሪያው ላይ የሚታዩት የቀለማት ውህደት እና ህብር ምንም ሳይደበዝዝ እስከ ዛሬ ድረስ አለ። በዚያ ላይ ደግሞ በነዚህ ቀለማት የተገለፁት ፍልስፍናዎች በርካታ ናቸው። ስለዚህ የሥነ-ጥበብ ባለሙያዎች ይህን ቤተ-ክርስትያን እንዲያጠኑት መንግስቱ ያሳስባል።

አራተኛው አስገራሚ ነገር ደግሞ ከአምስት ሺህ በላይ የሰው ልጅ አስከሬኖች በዋሻው ውስጥ ተነባብረው በግልፅ መታየታቸው ነው። ይሄ ብቻም አይደለም፤ እነዚህ አስከሬኖች አብዛኛዎቹ አልፈረሱም። ቆዳቸው፣ ፀጉራቸው፣ ሰውነታቸው ይታያል። ታዲያ እነዚህ ሁሉ አስከሬኖች እንዴት ላለፉት 950 ዓመታት ሳይፈርሱ ቆዩ? የማንስ አስከሬን ናቸው? ለምን እዚያ ቦታ ላይ ተቀመጡ የሚሉ አስተሳሰቦች ሊነሱ ይችላሉ።

እርግጥ ነው በአፈ ታሪክ እና በቤተ- ክርስትያኒቱ ቀሳውስት እንደሚነገረው ከሆነ እነዚህ የሙታን አፅሞች እዚያ ቦታ ላይ ያረፉት በተለይ ከውጭ ሀገር የቦታውን መንፈሳዊነትና ፀጋነት የሰሙ ምዕምናን እየመጡ ከዚህ አንሄድም እያሉ ሲሞቱም እዚያ ያረፉ ናቸው ይባላል። ይሄ ገለፃ በርካታ ጥያቄዎችን ሊያስነሳ እንደሚችል የቀድሞው የአዲስ አበባ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ኮሚሽነር ዶ/ር አያሌው ሲሳይ ይገልፃሉ። እንደ እርሳቸው አባባል ሰዎቹ የሞቱት ተራ በተራ ነው ወይስ አንድ ላይ? በማለት ይጠይቁና ራሳቸው መልስ ይሰጣሉ። ዶክተር አያሌው ሲያስረዱ የአካባቢው ሰው አስከሬኖችን ከዋሻ ውስጥና ከአብያተ-ክርስትያናት ጐን የማስቀመጥ የቆየ ባህል ስላለው አፅሞቹ የፈረንጆች ሳይሆኑ የኢትዮጵያዊያን እንደሆኑ ይጠቁማሉ። ግን ጥናት መደረግ እንዳለበትም ያሳስባሉ።

 ግርሃም ሐንኩክ የተባለው ፀሐፊ እና ሌሎች የውጭ ሀገር ሰዎች አልፎ አልፎ እንደሚጠቀሙት፣ የላሊበላን አብያተ- ክርስትያናት የሰሩት ሰዎች ከውጭ ሀገር የመጡ የኪነ-ህንፃ ባለሙያዎች ናቸው እና እነዚህ ሰዎች ህንፃውን ሰርተው ከጨረሱ በኋላ እዛው ኢትዮጵያ ውስጥ ተገድለዋል የሚል ማረጋገጫ የሌለው ፅሁፍ ከዚህ በፊት አሰራጭተዋል። የነ ግርሃም ሀንኩክ መላ ምት እነዚያ የተገደሉት የውጭ ሀገር ሰዎች አፅም፣ የነዚህ የአምስት ሺ ሰዎች በይምርሃነክርስቶስ ውስጥ የሚገኘው እንደሆነ ሊጠቁሙ ይፈልጋሉ። እርግጥ ነው ይህ አባባል በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት የለውም። ምክንያቱም አፅሞቹ የህፃናት ጭምር ሁሉ አላቸው። ከዚህ በላይ ግን ይህን ሁሉ ሰው መግደል ወይም በግፍ ማለቅ በራሱ በታሪክ ውስጥ ተመዝግቦ መቀመጥ ነበረበት። በመሆኑም በየትኛውም የታሪክ መዝገብ ውስጥ ባለመፃፉ የግርሃም ሐንኩክ እና የመሰሎቹ አባባል ተቀባይነት እንደሌለው ዶ/ር አያሌው ሲሳይ ተናግረዋል።

 የሆኖ ሆኖ ግን፤ በጣም የሚያስገርመው አስከሬኖቹ አለመፍረስ እና የነማንስ እንደሆነ እስከ አሁን ድረስ አለመጠናቱ እንደሆነ ጥናት አቅራቢው መንግስቱ ጐበዜም ይገልፃል። ስለዚህ ወደፊት ፓላታላጂስቶች እና አርኪዮሎጂስቶች የዚህን አፅሞች ምስጢር እንዲመራመሩበት ጥሪ ቀርቧል።

ይህን የይምርሃነክርስቶስ ቤተ-ክርስትያን ቀደም ባለው ዘመን መጥተው ካዩት የውጭ ሀገር ሰዎች መካከል ፖርቹጋላዊው ፍራንሴስኮ አልቫሬዝ ቀዳሚ ነው። አልቫሬዝ እ.ኤ.አ በ1520 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ እስከ 1526 ዓ.ም ድረስ ለስድስት ዓመታት ኢትዮጵያን እየተዘዋወረ ከጐበኘ በኋላ የፃፈው መፅሀፍ ‘‘Narrative of the Portuguese Embassy to Abyssinia during the year 1520-1527’’ በሚል ርዕስ ታትሟል።

በዚህ መፅሀፍ ውስጥ አልቫሬዝ ስለ ቅዱስ ይምርሃነክርስቶስ ቤተ-ክርስትያን ተናግሯል። እርሱ የገለፃቸው ጉዳዮች ከአንድ ነገር በስተቀር ሁሉም እስከ አሁን ድረስ ከሞላ ጐደል እንደሚገኙ ጥናት አቅራቢው መንግስቱ ጐበዜ ተናግሯል። አልቫሬዝ ከገለፃቸው ጉዳዮችና ዛሬ ግን የለም የተባለው ትልቁ የብራና መጽሐፍ ነው። የብራናው መጽሐፍ ቄሶቹ የሚያነቡት ሲሆን ንጉሱ ይምርሃነክርስቶስ ራሱ ሲቀድስ የሚታይበት ስዕል እንዳለው አልቫሬዝ ገልጿል። መንግስቱ ጐበዜ ደግሞ ይህ የብራና መጽሐፍ ዛሬ በዚያ አካባቢ እንደሌለ ገልጿል። አንዳንድ ሰዎች ግን ይህ ገድለ ይምርሃነክርስቶስ በላሊበላ ከአስሩ አብያተ-ክርስትያና በአንደኛው ውስጥ እንደሚገኝ ይገናገራሉ።

 የቅዱስ ይምርሃነክርስቶስ የዋሻ ውስጥ ቤተ-ክርስትያንና ቤተ-መንግስት ልዩ ከሚያደርጉት ጉዳዮች አንዱ አካባቢው እጅግ ጥቅጥቅ ባሉ ደኖች መሸፈኑ ነው። ከ161 ሄክታር በላይ ደን ያለው ይህ ስፍራ ለሰው ልጅ ሁሉ ማራኪ አካባቢ እንደሆነ ተወስቷል።

 ከዚህ ሁሉ አስገራሚ ነገር ውስጥ ግን የሚደንቀው ይህ ቤተ-ክርስትያን በዩኔስኮ መዝገብ ውስጥ እስከ አሁን ድረስ አልሰፈረም። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ የኪነ- ህንፃ ታሪኩና ውበቱ በፀሐፊያን ባለመወሳቱ ነው። ይምርሃነክርስቶስ ዩኔስኮ በቅርስነት ለመመዝገብ ካስቀመጣቸው አስር መስፈርቶች ውስጥ አብዛኛዎቹን የሚያሟላ እንደሆነ መንግስቱ ጐበዜ ይገልፃል። ላለፉት 950 ዓመታት በውበትና በምስጢር አሸብርቆ እያገለገለ ያለው ይህ የእምነትና የስልጣኔ ቦታ የተሸሸገው የፕላኔታን ትንግርት ነው። ከዚህ ሌላ ንጉሱ ይምርሃነክርስቶስ ራሱ አስገራሚ መሪ ነበር። ትዳር አልመሰረተም፤ ልጅ የለውም፤ ህይወቱን በብህትውና ያሳለፈ ቅዱስ መሪ ነበር። ጥበብን፣ ባህልን፣ እምነትን፣ ህግን አጥብቆ የያዘ አስገራሚ ሰው ነው። እናም የዚህን ድንቅዬ የኢትዮጵያ መሪ ታሪክ ቀጥሎ በአጭሩ እናየዋለን::

አርክቴክት እና ቅዱስ የሆነው ጥበበኛው የእትዮጵያ መሪ

በኢትዮጵያ ውስጥ “ቅዱስ” በሚል መጠሪያ የሚታወቁ መሪዎች አሉ። መሪዎቹ ቅዱስ መባላቸው ብቻ አይደለም የሚደንቀው፤ በተለይም በስማቸው አብያተ-ክርስትያናት ተገንብተዋል። በየዓመቱም የነዚህ መሪዎች ልደት እና ክብረ በዓልን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማንያን እጅግ በደመቀ ሁኔታ ያከብሩላቸዋል። እነዚህ የኢትዮጵያ ቅዱሳን መሪዎች በስማቸው ይፀለያል፤ ይቀደሳል። በስማቸው አጋንንት ይወጣል፤ በስማቸው ሰው ይፈወሳል፤ በስማቸው ኢትዮጵያ እንድትባረክ፣ ዓለም እንዲባረክ ፈጣሪ ይለመናል። የሰሩት የፅድቅ ተግባርም ይተረካል። ያነጿቸውን አብያተ-ክርስትያናትም ለመሳለም አያሌ ምዕመናን ባህር አቋርጠው ሁሉ በመምጣት ይታደሙባቸዋል። እነዚህ ስመ ገናና መሪዎች የኖሩት ደግሞ በ11ኛውና በ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ነው። ከእነርሱ በኋላ ቅዱስ ተብሎ የተጠራ የኢትዮጵያ መሪ እስከዛሬ ድረስ የለም። ለመሆኑ እነዚህ ቅዱሳን መሪዎች እነማን ናቸው?

ኢትዮጵያን ከ1077 እስከ 1117 ዓ.ም ለ40 ዓመታት የመራት ንጉስ ይምርሃነክርስቶስን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስትያን “ቅዱስ” በማለት ትጠራዋለች። ቀጥሎም ወደ ዙፋን የወጣው ንጉስ ሀርቤይ ወይም ስመ-መንግስቱ ገብረማርያም የሚሰኘው ማለት ነው፤ እሱም ኢትዮጵያን ከ1117 እስከ 1157 ድረስ መርቷታል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስትያን ይህንንም መሪ “ቅዱስ” ብላዋለች። ሦስተኛውና በምድራችን ላይ ገናና ስምና ዝና ያለው ደግሞ ላሊበላ ነው። ንጉስ ላሊበላ ኢትዮጵያን ከ1157 እስከ 1197 ዓ.ም ለ40 ዓመታት መርቷታል። ቤተ- ክርስትያኒቱም ይህን መሪ “ቅዱስ” የሚሰኝ መጠሪያ ሰጥታዋለች። አራተኛው ደግሞ ንጉስ ነአኩቶለአብ ነው። ይህ ንጉስ ኢትዮጵያን ከ1197 እስከ 1237 ለአርባ ዓመታት መርቷታል። እርሱንም እንዲሁ “ቅዱስ” በማለት ቤተ-ክርስትያኒቱ ትጠራዋለች። የነዚህ መሪዎች ቅድስና ምንድን ነው? ለምንስ ቅዱስ ተባሉ? የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም።

 እነዚህ መሪዎች “ቅዱስ” የሚለውን መጠሪያ ያገኙት በዘመነ ስልጣናቸው ባከናወኗቸው መንፈሳዊና ሥጋዊ ተግባራት ነው። በህዝብ አመራር ረገድ የዜጐቻቸውን መብትና ጥቅም ከማስከበራቸው በተጨማሪ ዘመናቸው የሰላምና የመረጋጋት ስለነበር በርካታ ግብረሰናይ ድርጊቶችን አከናውነዋል። የሄ ብቻም አልነበረም፤ መሪዎቹ ራሳቸው ቅስናን የተቀበሉ “ቄስ ወ ንጉስ” (ቄስና ንጉስ) ነበሩ። ይቀድሳሉ፣ ይዘምራሉ፣ ፀሎት ይመራሉ፣ ያስተምራሉ፣ መፃሕፍት ያዘጋጃሉ፣ ኪነ-ህንፃ ያስገነባሉ፣ አብያተ- ክርስትያናትን ያቋቁማሉ፣ እንደ ሀገር መሪ ደግሞ ኢትዮጵያን ያስተዳድራሉ። አስገራሚ መሪዎች ነበሩ። እነዚህ ቅዱሳን መሪዎች ሁሉም ማለት የቻላል የኪነ-ህንጻ ባለሙያዎች ነበሩ::

ኢትዮጵያ በታሪኳ ሌላም አንድ አስገራሚ መሪ አይታለች። እንደውም ይህ መሪ ለነ ላሊበላ ሁሉ አርአያ የሆነ እጅግ አጥባቂ የመንፈስ ሰው ነበር። ይምርሃነክርስቶስ ይባላል። ከላሊበላ ቀድሞ ኢትዮጵያን የመራ የዛጉዌ ሥርወ-መንግስት ገናና መሪ ነው።

 ይምርሃነክርስቶስ ባህታዊው የኢትዮጵያ መሪ ሊባል የሚችል ነው። በዘመነ ስልጣኑ /ከ1077 እስከ 1117 ዓ.ም/ ድረስ በቆየበት ጊዜ ልዩ ልዩ ሕጐችን እና ደንቦችን አውጥቶ ነበር። ለምሳሌ አንድ ወንድ በአንዲት ሴት፣ አንዲት ሴት በአንድ ወንድ እንዲፀኑ የሚለውን የሐዲስ ኪዳን ሕግ እና ትዕዛዝ በማጠናከር፣ ብዙ ሚስቶችን የማግባቱን ልማድ አስቀርቷል በማለት ዶ/ር አያሌው ሲሳይ “የአገው ህዝቦችና የዛጉዌ ሥርወ-መንግስት” በሚለው መጽሐፋቸው ላይ ገልፀዋል። ከዚህ ሌላ ንጉሱ ይምርሃነክርስቶስ ራሱ ንጽህናውን ጠብቆ፣ ከሴት ርቆ፣ “ካህን ወ ንጉስ” / ካህንና ንጉስ/ በሚል ማዕረግ የመጀመሪያው ክህነትንና ሥልጣነ መንግስትን አጣምሮ የያዘና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ- ክርስትያን ከላስታ ዋግ /ዛጉዌ/ ነገስታት መካከል በግንባር ቀደምትነት “ቅዱስ” የሚል የክብር ቅጽል የተሰጠው ንጉስ እንደሆነ የዶ/ር አያሌው መጽሐፍ ያብራራል።

ቅዱስ ይምርሃነክርስቶስ በወቅቱ የአረማውያን ተግባር የሚባለውን በጥንቆላ፣ በአስማት፣ በመተትና በሟርተኛነት ሥራ የተሰማሩትን ግለሰቦችና ወደ እነሱም ለማስጠንቆል የሚሄደውን ማንኛውንም ግለሰብ በአዋጅ እንዲታገድ አድርጓል።

ከእነዚህ ሌላም በዘመነ ስልጣኑ አስገራሚ ሕጐችን አውጥቶ ነበር። እነዚህም እንዲህ የሚሉ ነበሩ፤ “ከአንድ አባትና እናት የተወለዱ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ወንድማማቾች ቢኖሩ እና አንደኛው ሀብታም ሌላው ድሃ ቢሆኑ ድሃው የሃብታሙን ወንድሙን ንብረት ይካፈላል፤ ሁለቱም የአንድ ማህፀን ፍሬዎች ናቸውና” ይላል።

ሌላው የቅዱስ ይምርሃነክርስቶስ ሕግ / አዋጅ/ የሚከተለው ነው። በርስት የተነሳ በጣም የተጣሉ ሁለት ወንድማማቾች ጉዳይ ለቅዱስ ይምርሃነክርስቶስ ቀረበለት። ሁለቱንም ከርሱ ፊት አስቀርቦ ለፍርድ በመቀመጥ በሚከተለው ደንብ አስማምቷቸዋል፤ ሁለታችሁም ንብረታችሁን ለአምስት ክፈሉት፣ ሁለቱ እጅ ለትልቁ ልጅ፣ ቀሪው ደግሞ ለትንሹ ይሁን፤ እንዲሁም የሞቱት ወላጆቻችሁ መኖሪያ ቤት ለትንሹ ልጅ ይሰጥ” የሚል እንደነበር ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት (Church and Stat in Ethiopia) በተሰኘው መጽሐፋቸው ገልፀዋል።

 አፄ ይምርሃነክርስቶስ ትሁት፣ ቅንና ትክክለኛ ሰው፣ ስልጣኑንም መከታ በማድረግ በማንም ላይ በደል ወይም ግፍ ያልፈፀመ፣ ቀና፣ ፍትህና ርዕትእን ያራመደ ንጉስ እንደነበር ገድሉ በስፋት ያስረዳል። የይምርሃነክርስቶስ የገድል መጽሐፍም የሚገኘው ላሊበላ ከተማ፣ ከአስራ አንዱ ፍልፍል አብያተ-ክርስትያናት መካከል በቤተ-መድሐኒዓለም ውስጥ ነው።

አፄ ይምርሃነክርስቶስ፣ ከቤተ-መንግስቱ ከዛዚያ በመመላለስ ወግረ ስሂን በተባለ ስፍራ ከትልቅ ዋሻ ውስጥ አንድ እጅግ ድንቅ የሚባል ትንግርታዊ ቤተ-ክርስትያን አሳንጿል። ቤተ-ክርስትያኑ የተገነባው በውሃ ላይ ነው ይባላል። የቤተ-ክርስትያኑ መሠረት /ስሩ/ ውሃ እንደሆነ ቀሳውስቱ ለሚመጣው ምዕመን ሁሉ ያስረዳሉ።

ይህንን ቤተ-ክርስትያን ለማሳነፅ ባቀደ ጊዜም፣ ስራውን ከማስጀመሩ በፊት ህንፃው ለሚቀመጥበት ቦታ ባለርስቶች ለነበሩ ሰዎች የመሬቱን ዋጋ እንደከፈላቸው ይነገራል።

 አፄ ይምርሃነክርስቶስ ቤተ-መንግስቱንና ቤተ-ክርስትያኑን በዋሻ ውስጥ ያነፀ ሲሆን፤ እንጨትንና አለትን አጣምሮ የሰራው ነው። እስከ ዛሬ ድረስ ግን እነዚህ እንጨቶችና አለቶች እንዴት ተጣምረው ኪነ-ህንፃዎቹን እንዳቆሟቸው የሚታወቅ ነገር የለም።

በዚህ በቅዱስ ይምርሃነክርስቶስ ቤተ- ክርስትያን አፀድ ውስጥ የራሱ የቅዱስ ይምርሃነክርስቶስ መቃብር ይገኛል። መቃብሩ ደግሞ የቤተ-ክርስትያን ልብስ ለብሶ ላለፉት 900 ዓመታት ቆይቷል። እስከ አሁንም ድረስ አለ። ከርሱ ጐን ደግሞ የአገልጋዩ መቃብር ተብሎ የሚነገር ሌላ የቀብር ቦታ አለ።

 ይምርሃነክርስቶስ “ቀሲስ ወ ንጉስ” የሚል ማዕረግ የነበረውና እንደ ንጉስ ፈራጅ እንደ ካህን ናዛዥ ስለሆነ ይህንን ተገን በማድረግ ዛሬም ጭምር ወደ እሱ ቤተ-ክርስትያን ተጉዘው የሚደርሱ ምዕመናን ከዋሻው ውስጥ ከቤተ-መቅደሱ በስተኋላ በኩል የአገልጋዩ ይሆናል ተብሎ ከሚገመተው ሌላ መቃብር አጠገብ ለብዙ ዘመናት በግምጃ ጨርቅ ተሸፍኖ እና ተከብሮ ለምዕመናንና ለጐብኚዎች መታሰቢያነት የሚገኘውን መቃብሩን በመዞር ፍታኝ ይምርሃነክርስቶስ የሚሉትን መስማት የተለመደ ነው በማለት ዶ/ር አያሌው ሲሳይ ይገልፃሉ።

እንግዲህ ኢትዮጵያ ኖሮ ብቻ ሳይሆን ሞቶም ቢሆን የሚታመንበት፣ በስሙ የሚፀለይበት፣ መንፈሱ ችግርና ከመከራም የሚያወጣ ተወዳጅ አርክቴክትና መሪ ነበራት። ቅዱስ ይምርሃነክርስቶስ ከሀገር መሪነት አልፎ የኢትዮጵያ የመንፈስ መሪ ነው። በትውልዶች ውስጥ የዘመናትን ኬላ እየሰበረ ዝንት ዓለም ገና ይኖራል። እንዲህ አይነቱን መሪ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ- ክርስትያን “ቅዱስ” ብላ ነው የምትጠራው። ቅዱሳን መሪዎች የነበሩባት ሀገር ነች! ከነ ይምርሃነክርስቶስ፣ ከነ ሃርቤይ፣ ከነ ላሊበላ፣ ከነ ነአኩተለአብ በኋላ ኢትዮጵያ እንዴት ቅዱስ መሪ ማፍራት አልቻለችም? ይህን ትውልድ ሁሌም ሊጠይቀው የሚገባ ይመስለኛል። የመንፈስ ቅዱሳን መሪዎች እንዴት ጠፉ?

 ቅዱስ ይምርሃነክርስቶስ በሀገር መሪነቱም የእስከ ዛሬ ድረስ መነጋገሪያ የሆነውን የአባይ ወንዝን ለመገደብ እና ኢትዮጵያን ለማልማት ትልቅ አላማ ነበረው። ታሪክ ፀሐፊው አቶ ተክለፃዲቅ መኩሪያ ሲገልፁ፤ ቅዱስ ይምርሃነክርስቶስ በዘመነ መንግስቱ ከአከናወናቸው ዋና ዋና ተግባራት መካከልም የአባይ ውሃ ወደ ምድረ ግብፅ እንዳይወርድ ለመገደብ ያደረገው ሙከራ ነው። ይህ ተግባሩ እንዲህ ቀርቧል።

“የአባይ ውሃ በግብፅ እያነሰ በመሄዱ እና ባገሪቱም የውሃ ችግር ስለተፈጠረ መሪዎቹ ተደናግጠው የኢትዮጵያ ንጉስ እንዳይፈስ ገድቦት ነውና አማላጅ ሆነው ሄደው ተነጋግረው ያስለቅቁ ብሎ፣ ቪዘር አልአፍዳል የእስክንድሪያውን ሊቀ ጳጳሳት ሚካኤልን ወደ ኢትዮጵያ ላካቸው። እሳቸውም መጥተው የአባይ ውሃ ቢቆም በጥም የሚያልቁት ክርስትያኖቹ ወንድሞቻችሁ ጭምር እንጂ ሙስሊሞቹ ብቻ አይደሉም፤ አሁንም ከግብፅ ተልኬ የመጣሁት ይህንኑ ለእናንተ ለልጆቼ ለመግለፅ ነው ብለው ለንጉሱ ለይምርሃነክርስቶስ እና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች ልመናውን አቀረቡ። በዚህ ጊዜም፣ ውሃው ተለቀቀ፣ ሊቀጳጳሳቱም ደስ ብሏቸው ወደአገራቸው ተመለሱ” በማለት ጽፈዋል።

ቅዱስ ይምርሃነክርስቶስ ላይ ብዙም ባይሆኑ የተለያዩ ፀሐፊያን የደረሱበትን የጥናትና ምርምር ጽሁፎቻቸውን መፃህፍቶቻቸውን አስነብበዋል። በመጀመሪያ የሚጠቀሰው መጽሐፍ “ገድለ ይምርሃነ ክርስቶስ” የተሰኘው ነው። ይህ መፃህፍ ከተዘጋጀ ረጅም አመታትን አስቆጥሯል። አንዳንድ ፀሐፊያን በዘመነ ይምርሃነክርስቶስ የተዘጋጀ ነው፤ እድሜውም ከ950 ዓመት በላይ ነው ይላሉ። ሌሎች ደግሞ ገድል በብዛት የተፃፈው በ14ኛውና በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሸዋ ነገስታት አማካይነት ነው በማለት ቀረብ ያደርጉታል። የዛጉዌን ነገስታት ገድል የፃፉት ሸዋዎች ናቸው ይባላል። ይህ ሆኖ ግን ገድለ ይምርሃነክርስቶስ የመጀመሪያው መጽሐፍ ነው።

 በሁለተኛነት የሚጠቀሰው ፖርቹጋላዊው ቄስ ፍራንሲስኰ አልቫሬዝ እ.ኤ.አ በ1520 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ለስድስት ዓመታት ሀገሪቱን ከጐበኘ በኋላ የፃፈው ያዘጋጀው የታሪክ መጽሐፍ ነው። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የተለየው ነገር ቢኖር፣ በይምርሃነክርስቶስ ቤተ-ክርስትያን ውስጥ ስላሉት ሁለት የመቃብር ስፍራዎች ሁኔታ የፃፈው ነው። ምእምናን እጅግ የሚያከብሯቸው የመቃብር ቦታዎች በተለይም የቤተ-ክርስትያን ግምጃ ለብሰው የሚታዩት የቅዱስ ይምርሃነክርስቶስ እና አንደኛው ደግሞ የራሱ የንጉሱ አገልጋይ መቃብር ነው ተብሎ የሚታሰበውን ታሪክ ለወጥ አድርጐታል። እንደ አልቫሬዝ አፃፃፍ አንደኛው መቃብር የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ የይምርሃነክርስቶስን ቅድስና በመስማት ለጉብኝት ከመጡ በኋላ ከዚሁ አርፈው መቀበራቸውን ቄሶች ነገሩኝ ብሎ ጽፏል።

 ከዚህ በተረፈ ተክለፃዲቅ መኩሪያ፣ ኅሩይ ወልደስላሴ፣ ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት፣ ዶ/ር ስርግው ኃብለስላሴ፣ ዶ/ር አባ አየለ ተክለሃይማኖት፣ ሲልቪያ ፓንክረስት፣ ፕ/ር ሪቻርድ ፓንክረስት፣ ግርሃም ሀንኩክ እና በዘመናዊ ጥናቶቻቸው ደግሞ ዲያቆን መንግስቱ ጐበዜ (Lalibela and Yemerehanekiristos the living witnesses of zaguwea Dynasity) በሚሰኘው መጽሐፉ እና ዶ/ር አያሌው ሲሳይ ደግሞ (የአገው ሕዝቦችና የዛጉዌ ሥርወ መንግስት) በተሰኙት መጽሐፍቶቻቸው ብዙ መረጃዎች ለዚህ ትውልድ ካደረሱ ፀሐፊያን መካከል ይጠቀሳሉ። ሌሎችም አሉ።

በመጣጥፎች ደግሞ ጆን ግርሃም እና ሰለሞን አበበ ቸኰል ስለ ይምርሃነክርስቶስ ታሪክ አስነብበውናል። የዛሬ 10 ዓመት ግድም ጥቅምት 17 ቀን 1994 ዓ.ም ሰለሞን ባቀረበው መጣጥፍ “የቡግናው ይምርሃነክርስቶስ በ90 ዓመቱ ታሪክ የሰራ መሪ” በሚል ርዕስ ማለፊያ ጽሁፍ አቅርቧል። ሰለሞን የቅዱስ ይምርሃነክርስቶስን ውልደትና እድገት በሚከተለው መልኩም አስተዋውቆናል።

 ከይምርሃነክርስቶስ ቀደም ሲል ኢትዮጵያን ይመራ የነበረው ጠጠውድም የሚባል ንጉስ ነበር። እርሱ ደግሞ አንድ ቀን በሃገሪቱ የሚገኙ ኰከብ ቆጣሪዎችን እና አዋቂ የሚባሉትን ሁሉ ሰብስቦ እኔን የሚተካኝ መሪ ማነው? ብሎ ይጠይቃቸዋል።

 “የወንድምህ የግርማ ስዩም ልጅ ይምርሃነክርስቶስ የሚባል ይወርስሃል” አሉት …። ጠጠውድምም ወይም በስመመንግስቱ አፄ ሰለሞን፣ ይሄ ልጅ ከዚህች ምድር መጥፋት አለበት ብሎ አስቦ ለእናቱ እንዲህ ሲል ላከላት።

 “ልጅሽ የወንድሜ ልጅ ስለሆነ… ፈረስ ግልቢያ፣ ጦር ውርወራ፣ ውሃ ዋና፣ እየተማረና የቤተ-መንግስት ሥነ ሥርዓትን እየተከታተለ እንዲያድግ ወደ እኔ ላኪው” አላት። እርሷ ደግሞ ገዳማውያንን አማከረች፣ ወደ ፊት ንጉሥ የሚሆነውን ልጇን የሚወስዱ ወታደሮች ሲመጡ፣ ልጇ ጠፍቶባት እሪ ስትል አገኟት። “ልጄ ጠፋ! ሞተ! ልጄ ሞተ” እያለች የምታወርደውን እንባዋን አይተው አዝነው ተመለሱ። እነሱ ሲሄዱላት ቶሎ ብላ ልጇን ከደበቀችበት ቦታ አስወጣችውና ወደ ሩቅ አገር ሄዶ እነዲያድግ አደረገች። በሄደበትም መንፈሳዊ ትመህርትን እየተማረ አደገ። 17 ዓመት ሲሞላው ጠጠውድም ልጁ በህይወት መኖሩን ስለሰማባት ከአገር ውጭ ወደ ግሪክ እንዲሰደድ አደረገችው። በስደት ኑሮውም ከፍተኛ ትምህርትን ተምሯል። ሥነ-ህንፃ፣ ግብረ ህንፃ፣ ሥነ ቅርፃ ቅርፅ ብሉያትንና ሐዲሳትን እንደተማረ ገድሉ ይጠቁማል….። በስደት በቆየባቸው 40 ዘመናት መጨረሻ ላይ በሮማ፣ በእየሩሳሌም የሚገኙትን ገዳማት በመዞር ጐብኝቷል። ይምርሃነክርስቶስ ጐረምሳ ሳለ በ17 ዓመቱ ወጥቶ ከ40 ዓመታት የስደት ኑሮ በኋላ የ57 ዓመት ሙሉ ሰው ሆኖ ተመለሰ። ጠጠውድም ገና አልሞተም ነበር። ይምርሃነክርስቶስ ለአንድ ዓመት ያህል ተደብቆ ቆይቶ በ58ኛው ዕድሜው ላይ ጠጠውድም አረፈና እሱ ነገሰ” ይላል።

ይህ ሰው በአሁኑ አጠራር ዲያስፖራ ቢባልም በስደት ዘመኑ ኪነ-ጥበብን የተማረ እና በዚህም የተዋጣለት ኪነ-ህንፃ አሰርቷል። ፣ አግብቶ ያልወለደ፣ በድንግልና የኖረ፣ የተዋጣለት ጥበበኛ ሆኖ የሳላቸው ወይም ያሳላቸው ስዕሎች ዛሬም ድረስ ድምቅምቅ ብለው ላለፉት 950 ዓመታት ስሙን ሲያስጠሩ ቆይተዋል። ዩኔስኰ እስካሁን ድረስ የዚህን ተአምረኛ ንጉስ ቅርሶች በዓለም የቅርስ መዝገብ ውስጥ አላኖራቸውም። ባህል ሚኒስቴር፣ ማኅበረቅዱሳን፣ ምሁራን፣ ባለስልጣናት እንዲሁም ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ስለዚህ ኪነ-ህንፃና ሥነ-ሥዕል ዩኔስኮን ለማሳመን መታገል አለበት።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top