አድባራተ ጥበብ

የግለሰብና የማህበረሰብ ችግሮች አፈራረጅ

የግል ችግር የሚባለው ምክንያቱና መፍትሄው በግለሰቡ ዘንድ ወይንም በግለሰቡ ከባቢ የሚገኝ ተግዳሮት ነው። አንድ ችግር ማህበራዊ ችግር ነው የሚባለው የችግሩ ምክንያትና መፍትሄ ከግለሰቡ ወይንም ከግለሰቡ የቅርብ ከባቢ ውጪ ሆኖ ሲገኝ ነው። ታዋቂው እንግሊዛዊ ሊቅ፣ ሲ. ራይት ሚልስ፣ ከፍ ሲል የተጠቀሰውን የአፈራረጅ ስልት በመጠቀም የግል ወይንም የግለሰብ ችግሮችን ‹‹የማህበራዊ ከባቢው የነፍስ ወከፍ ችግሮች›› (personal troubles of milieu) በማለት ሲገልጻቸው ማህበራዊ ችግሮችን ደግሞ ‹‹የማህበራዊ መዋቅሩ የወል ጉዳዮች›› (public issues of social structure) ይላቸዋል። ሚልስ ለእነኚህ ፈርጆች የተለያዩ የማብራሪያ ምሳሌዎችን ይጠቅሳል። ሚልስ የነበረበት ዘመን አውሮፓ በኢንዱስትሪና በከተማ መስፋፋት የተነሳ ከፍተኛ እመርታ ያሳየበትና ከዚያ በፊት ታይተው የማይታወቁ አዳዲስ ማህበራዊ ችግሮች ጐልተው የተስተዋሉበት ወቅት በመሆኑ ምሳሌዎቹ ኢኮኖሚያዊ ከሆኑ ጉዳዮች ጋር የተዛመዱ ነበሩ። ለምሳሌ አንድ ስራ አጥ ሰው ስራ ለማጣቱ የራሱ የሆኑ የግል ችግሮች ሊኖሩበት ይችላል። ይህ ሰው ሰነፍ፣ የሰብዕና ችግር ያለበት፣ ምንም ክህሎት የሌለው ወይንም ጊዜና ጉልበቱን በጽኑ የሚሻሙት ከባድ የቤተሰብ ችግሮች ያሉበት ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ በአንድ ሀገር ውስጥ 100 ሚሊዮን የስራ ዕድል ቢኖርና 150 ሚሊዮን ዜጎች ስራ ፈላጊ ቢሆኑ፣ ጉዳዩ የግለሰብ መሆኑ ይቀርና የማህበረሰብ ይሆናል።

እንዲህ ባለ ሀገር ውስጥ የግል ችግር በሌለበት ሁኔታ እንኳ ከህዝቡ ሲሶ የሚሆነው የስራ ዕድል ላያገኝ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ችግር የግለሰብ ችግሮችን በመፍታት ብቻ መፍትሄ የሚያገኝ አይሆንም።

በተመሳሳይ ሁኔታ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ባልና ሚስት በትዳራቸው መካከል የመግባባት ችግር ቢያጋጥማቸው፣ ችግራቸውን ሲያስታምሙ ከርመው በመጨረሻም መለያየት ዕጣቸው ሊሆን ይችላል። ባልና ሚስቱ በሚኖሩበት ህብረተሰብ ውስጥ ይህ ዓይነቱ ችግር የእነርሱ ቢጤዎች ሆኖ ከተገኘ ችግሩ የግለሰቦች ነው ብሎ መደምደም ይቻላል። ነገር ግን በዚያ ማህበረሰብ ውስጥ በሺህ ወይንም ከዚያ በላይ የሚቆጠሩ ጋብቻዎች ፈርሰው ቤተሰብ የሚበተን ከሆነ የችግሩ ምንጭ የተፋቺዎቹ የተዛባ ባህርይ ነው ለማለት አይቻልም። እንዲህ ባለው ሁኔታ መጠየቅ ያለበት ጥያቄ ‹‹እነኚህን ሰዎች ምን ነካቸው?›› ሳይሆን ‹‹በማህበረሰባችን የጋብቻና የቤተሰብ ተቋም ላይ ምን የከፋ ችግር ተፈጠረ?›› መሆን አለበት።

 በተለምዶ ጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በሚል የወል ስም የምንገልጻቸውና ከማህበረሰባችን የኑሮ ዘይቤ ጋር ተለንቅጠው ለረዥም ዘመን የኖሩት የተለያዩ ተግባራት በተወሰነ አካባቢ፣ በተወሰኑ ሰዎች የሚፈጸሙ አይደሉም። እያንዳንዱ የማህበረሰብ አባል የልማትና የመሻሻል ዕድልን የሚያኮሰምኑ፣ የቁጠባ አቅምን የሚሰልቡ ተግባራትን ለመፈጸም የራሱ የሆኑ ምክንያቶች ቢኖሩትም፣ የእነኚህ ተግባራት መሰረታዊ ምክንያት ከእያንዳንዱ ግለሰብና የቅርብ ከባቢ ውጪ የሚገኝ ነው። ባህል የኑሮ ዘይቤ ነውና ባህልን የሚጋሩ የማህበረሰብ አባላት ተቀባይነትን ያገኙ ማህበራዊ ተግባራትን ያለ ብዙ ጥያቄና አቃቂር፣ በዘልማድ የመፈጸም ግዴታ አለባቸው፤ ምክንያቱም ህዝቡ ለብዙ ዘመናት የኖረበትና የሚኖርበት ነባር እምነትና አመለካከት (ጐጂም ሆነ ጠቃሚ) በቁሳዊ ኑሮው ላይ ተጽዕኖ ስላለው ነው።

በአንድ በኩል አንድን ችግር የግለሰብ ወይንም የማህበረሰብ ብሎ መክፈሉ ምንም ለውጥ አያመጣም የሚል አስተሳሰብ አለ። ምክንያቱ ስንፍና ይሁን አሊያም የኢኮኖሚ ቀውስ፣ ስራ ያጣ ሰው ያው ስራ አጥ ነው። የፍቺው ምክንያት የባልና ሚስቱ አለመግባባት ይሁን ወይንም በማህበረሰብ ዕድገት ሳቢያ በጋብቻና በቤተሰብ ላይ የመጣ ምስቅልቅል፣ የተፋቱ ባልና ሚስት ከመለያየት የሚመነጨውን ምሬትና ጸጸት ማምለጥ አይቻላቸውም። የልማት ጥረትን የሚያውኩ ጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ከግለሰብ የተዛባ አመለካከት ይመንጩ ወይንም የማህበረሰቡ ጫና ውጤት ይሁኑ፣ የኑሮ መሻሻል ህልም ሆኖ መቅረቱ አይቀርም። በሌላ በኩል ግን የችግሩን ፈርጅ ለይቶ ማወቁ ወሳኝነት አለው፤ ምክንያቱም የችግሩን ምክንያት፣ የሚያስከትላቸውን መዘዞችና ችግሩን እንዴት ማቃለል፣ ብሎም ማስወገድ፣ እንደሚቻል ፋና ስለሚወጋ ነው።

 ይሁን እንጂ ሁሉም ዓይነት ችግሮች ማህበራዊ ናቸው ማለት አይቻልም። የግለሰብ ችግሮችም ማህበራዊ ምክንያት አይኖራቸውም፤ ወይንም ደግሞ ማህበራዊ ችግሮች ግለሰባዊ ባህርይ ካላቸው አላባውያን ነፃ ናቸው ማለት አይቻልም። ለችግሮች ስነ ልቦናዊና አካላዊ የሆኑ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ስለዚህ ከእነኚህ ጉዳዮች ባሻገር ለመመልከት ካልተቻለ የችግሮችን መንስዔ በተመለከተ ሊኖረን የሚችለው እይታና ግንዛቤ የተውገረገረ ሊሆን ይችላል።

 ቀደም ሲል እንደተገለጸው ችግሮችን ግለሰባዊ ወይንም ማህበራዊ አድርጐ የመፈረጁ ጉዳይ የተለያዩ ምክንያቶችን ለመዳሰስ እንደሚረዳን ሁሉ የችግሮቹን የተለያዩ ውጤቶችም ለመመልከት ያግዘናል። ለምሳሌ የሚያርሰው በቂ መሬት የሌለው ገበሬና ቤተሰቡ ዘወትር በምግብ እጥረትና በችጋር እንደሚኖሩ የታወቀ ነው። ይህ ገበሬ የድህነቱ ምክንያት እሱው ራሱ (የ40 ቀን እድሉ) እንደሆነ አምኖ ከተቀበለ፣ ይህንኑ እድሉን እያማረረ፣ ራሱን እየረገመ ከድህነቱ ጋር ተመሳስሎና ተዋህዶ፣ ኑሮውን ኑሮዬ ብሎ መኖር ይቀጥላል። ይህ ሰው ድህነቱን የግለሰብ ችግር አድርጐ ፈርጆ ራሱንም ዋጋ እንደሌለው ፍጥረት (የማይረባ ሰው) አድርጐ ይመለከታል። እንዲህ ዓይነት የበታችነት ስሜት የማህበራዊ ችግር ሰለባ በሆኑ ግለሰቦች ዘንድ የተለመደ ነው። በስነልቦና ምሁራን አስተሳሰብ ድሃ ቤተሰብ ውስጥ የሚያድጉ ልጆችም ራሳቸውን የበታች አድርገው በመመልከት ድህነታቸውን

“የልማት ጥረትን የሚያውኩ ጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ከግለሰብ የተዛባ አመለካከት ይመንጩ ወይንም የማህበረሰቡ ጫና ውጤት ይሁኑ፣ የኑሮ መሻሻል ህልም ሆኖ መቅረቱ አይቀርም”

ከሁሉም ያነሱ ለመሆናቸው ማረጋገጫ አድርገው ይወስዱታል። በኢኮኖሚ ወዋዠቅ ምክንያት ስራ ያጡ ሰዎች የተፈጠረውን አጋጣሚ የሚቆጣጠሩበት አቅም እንደሌላቸው እያወቁ እንኳ ራሳቸውን እንደማይፈለጉ ሰራተኞች አድርገው መቁጠራቸው አይቀርም። ስለዚህ አንድ ችግር ግለሰባዊ ወይንም የግል ችግር ተደርጐ ከተፈረጀ ችግሩን ለማቃለል የሚወሰደው እርምጃ ባህርይ የግል ስትራቴጂ ይሆናል። ይህ ስትራቴጂ ወደ ራስ (ወደ ውስጥ) ‹‹መመልከት›› ሊሆን ይችላል። አንዳንዴ ከችግሩ የተገላገሉ ለመምሰል ስካር፣ በአደንዛዥ ሱስ መጠመድ፣ ራስን ማጥፋት፣ ወዘተ እንደ አማራጭ ይወሰዳሉ።

በግል ችግር የተያዙ ግለሰቦችን መርዳት አስፈላጊና ጠቃሚ ቢሆንም ከማህበራዊ ችግር አንፃር ይህ እርምጃ ጊዜያዊ መፍትሄ ነው። ችግሮችን ማህበራዊ አድርጐ መመልከት፣ በቅድሚያ ችግሮቹን በተለየ እይታ ለመመልከትና ከዚያም እጅግ ላቅ ወዳለ የተለየ መደምደሚያ፣ ብሎም የመፍትሄ እርምጃ ላይ ለመድረስ ያስችላል። ስለዚህ አንድ ሰው የድህነቱ ምክንያት የአርባ ቀን እድሉ ሳይሆን የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ሁኔታ ውጤት ነው ብሎ ካመነ ይህን የኢኮኖሚ ሁኔታ ለመለወጥ በታለሙ ማህበራዊ እንቅስቃሴዎችና የጋራ እርምጃዎች ውስጥ ተሳታፊ ለመሆን ይሞክራል። የፓኬጅ ፕሮግራሞች፣ የአነስተኛ ብድር አቅርቦቶች፣ ወዘተ ተጠቃሚ ለመሆን ጥረት ያደርጋል። ለድህነቱ ተጠያቂው ራሱ ብቻ እንደሆነ አድርጐ ባለመውሰድ ከራስ ጥላቻና እርግማን ነፃ ይሆናል። ምናልባት የሆነ ቁጭት፣ ንዴትና እልህ ሊሰማው ይችል ይሆናል፤ ነገር ግን ራሱን አይጠላም። ድህነቱ የራሱ የግል ችግር ሳይሆን የማህበረሰቡም መሆኑን በመረዳት እርሱ የድህነት ተጠቂ እንጂ የድህነት ፈጣሪ እንዳልሆነ በውል ይገነዘባል።

ለተጨማሪ ማብራሪያ አንድ ሌላ ምሳሌ እንውሰድ። ከዚህ ጽሑፍ ርዕሰ ጉዳይ ጋር ከሚያያዙ ችግሮች አንዱ የወሲብ ጥቃት ነው። የወሲብ ጥቃት ጉልህ ማህበራዊ ችግር እየሆነ ከመጣ ሰንበት ብሏል። የወሲብ ጥቃትን በአጥቂና በተጠቂ መካከል ያለ ችግር አድርጐ በመፈረጅና ችግሩን ማህበራዊ አድርጐ በመፈረጅ መካከል ያለውን ልዩነት እንዲሁም ይህ አፈራረጅ ወደ ምን ዓይነት የመፍትሄ ሃሳብ እንደሚወስድ በሚከተለው ምስል ለመመልከት እንሞክራለን።

ስለዚህ እንደማንኛውም ማህበራዊ ችግር የወሲብ ጥቃት በግል ጥረት ብቻ የሚፈታ የግል ችግር አይደለም። የተቀናጁና የጋራ የሆኑ የመፍትሄ እርምጃዎችን መውሰድ ይጠይቃል። ለረዥም ዘመን በህብረተሰቡ ውስጥ ሰርጸውና ስር ሰደው የሚገኙ የተዛቡ አስተሳሰቦችንና አመለካከቶችን ያላሰለሰ የመረጃ፣ የትምህርትና የኮሚኒኬሽን ዘዴዎችን በመጠቀም የባህርይ ለውጥ እንዲመጣ ማስቻልና የህግ ስርዓቱን ፍትሃዊ በማድረግ ችግሩን መጋፈጥ የግድ ነው።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top