ጥበብ በታሪክ ገፅ

የወርቅ ጫማ ፍለጋ

በአርሲ ጠቅላይ ግዛት አቦምሳ በሚገኘው የእርሻ ጣቢያ የክብር ዘበኛ ወታደሮች መሳሪያቸውን አንግበው ክብ ሰርተው ቆመዋል። በክቡ ውስጥ አንድ ሰው ቆመው መግለጫቸውን እያዳመጡ ነው። ሰውየው የሀገሪቱ ንጉስ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ነበሩ። አርበኞች የነበሩና ጡረታ የወጡ ወታደሮች በአካባቢው ጃንሆይ መሬት ሰጥተዋቸው ቀሪ ህይወታቸውን እዚያው እንዲኖሩ ተደርጓል። ጡረተኞቹ ያለሙትን መሬት ጃንሆይ እንዲጎበኙላቸው ጠሯቸው። እርሳቸው ሲመጡ ግብር ተጥሎ መበላት አለበት ስለተባለ ድንኳን ተክለው ለአቀባበሉ ዝግጅት እያደረጉ ነው።

 በድንኳኑ ከነበሩት አስተናጋጆች አንዱ በቦታው ላይ ተገኝቶ ደፋ ቀና እያለ ነው። ወደ ቦታው የመጣው ብቻውን አልነበረም። ትንሽ ልጁ አብሮ ይገኛል። እንደ እናትም አባትም ሆኖ ያሳደገው በመሆኑ ትንሹ ልጅ አባቱ የትም ቢሄድ አብሮ ይከተላል። የትንሹ ልጅ አባት ስራቸውን ካገባደዱ በኋላ ምሽት ላይ ከጓደኛቸው ጋር ድንኳን ውስጥ ቁጭ ብለው ያወራሉ። ትንሹ ልጅ አባቱ ከጓደኛቸው ጋር የሚያወሩትን እያዳመጠ ነበር። በኪሱ የያዘውን የጨርቅ ኳስ አውጥቶ በምሽቱ ደብዘዝ ያለ ብርሀን እየተመራ ይጫወታል። አባትዬው አሁንም ከጓደኛቸው ጋር ያወራሉ። ንጉሡ ትምህርት እንደሚወዱ፣ ወጣቶችን እንደሚያስተምሩ ሲያወሩ ትንሹ ልጅ ኳስ መጫወቱን አቁሞ አዳመጠ። ከዚያ ጣልቃ ገባና አባቱን ፡-

‹‹ጃንሆይ ማስተማር ይወዳሉ?›› አላቸው።

‹‹አዎ››

‹‹ታዲያ እኔን ለምን አያስተምሩኝም?››

‹‹ጠይቃቸው››

‹‹እንዴት አገኛቸዋለሁ?››

‹‹ጥበቃ ስላለ ለማግኘት ያስቸግራል››

‹‹አንተ ለምን አታገናኘኝም?››

‹‹እርሳቸውን ማግኘት አስቸጋሪ ነው››

‹‹ለምን ?››

‹‹ወታደሮች አያስጠጉንም››

አባቱ ልጃቸው ንጉሡን ለማግኘት እንደማይችል ቢያውቁም ጥያቄውን ማፈን አልቻሉም። ሞራሉን ላለመንካት በማሰብ ጃንሆይን ሊያገኝ እንደሚችል እየደለሉት ነው። ትንሹ ልጅ አባቱ በሰጡት ተስፋ ተዘጋጅቶ ጠበቀ። ጃንሆይ እንደመጡ ወታደሮቹ ዘንድ ሄደ። አንደኛውን ወታደር ጠጋ ብሎም፤

 ‹‹ላናግርህ ፈልጌ ነው›› አለው።

‹‹ምን ፈለግክ?››

‹‹ጃንሆይን ላናግራቸው እፈልጋለሁ።››

‹‹ለኔ ንገረኝና ልንገርልህ››

‹‹ጉዳዩን ለእሳቸው ነው የምነግረው››

‹‹ይሄን ያህል ጥብቅ ጉዳይ ይዘህ?››

‹‹አዎ››

‹‹እንግዲያውስ በወረቀት ጽፈህ አምጣ››

‹‹በቃሌ ነው የምነገግራቸው››

ወታደሩ ትንሹን ልጅ ወደ ሌሎች ጓደኞቹ ወስዶ ቅድም ያልከውን

ንገራቸው አለው። እውነትም ንጉሡ ዘንድ የሚያቀርቡት መስሎት ነገራቸው። እነሱ ግን በድርጊቱ ተገርመው ይሳሳቁበት ያሾፉበት ጀመር። አባትዬው ንጉሡን ማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን ቀድመው ቢነግሩትም ተስፋ ሳይቆርጥ አንድ ዘዴ መፈለግ ጀመረ። ንጉሡ የጡረተኛ አራሽ ወታደሮችን መግለጫ በሚያዳምጡበት ሰዓት ወታደሮቹ ክብ ሰርተው እሳቸውን መሀል አስገብተው እየጠበቁ ነው። የክብር ዘበኛ ወታደሮች አቋቋማቸው በአሳርፍ መልክ በመሆኑ እግራቸውን ከፍተው ነው የቆሙት። ትንሹ ልጅ ኳሱን በኪሱ ከቶ ቁምጣውን እንዳደረገ በባዶ እግሩ ከወታደሮቹ ጀርባ ሆኖ እንዴት አድርጎ ንጉሡ ጋ መድረስ እንዳለበት እያሰላሰለ ነው። ወታደሮቹ ሰርክሉን እያጠበቡ መጡ።

ትንሹ ልጅ ከውጭ ሆኖ እግራቸውን በከፈቱት ወታደሮች ጀርባ መሬት ላይ ተኝቶ በእግራቸው ስር ንጉሡ ይታዩ አይታዩ እንደሆነ መመልከት ጀመረ። ሥራውን ሊጀምር ጥናት እያደረገ ነበር። ከዚያም በእግራቸው ስር መሹለክ ጀመረ። ከአንዱ ወታደር እግር ሌላው ወታደር እግር ሲሻገር በፍጥነት ነው። ወታደሮቹ በእግራቸው ስር ውልብ የሚል ነገር ያያሉ። ጎንበስ ሲሉ ግን ምንም የለም።

ትንሹ ልጅ በእግራቸው ስር እየሾለከ ንጉሡን መፈለግ ጀመረ። ግን እንዴት ያግኛቸው? ሰው የገጠመበት ቦታ ደረሰ። ንጉሡን ግን መለየት አልቻለም። ደግሞም በመልክ አያውቃቸውም። አባትየው ስለንጉሡ ሲያወሩ የወርቅ ጫማ እንደሚያደርጉ ሰምቷል። ትንሹ ልጅ ክቡ የገጠመበት ቦታ የወርቅ ጫማ ቢፈልግ አጣ። አሁንም ፍለጋውን ቀጠለ። ዛሬ የመጨረሻ ቀኑ ነው። እርሳቸውን ካላገኘ ያሰበውን ማሳካት አይችልም። ካላገኛቸው ህልሙና ፍላጎቱ እንደ ጉም በኖ ይጠፋል። ሌሊቱን ሙሉ ሲያስብ ያደረውን ስትራቴጂ ተግባራዊ ማድረግ አለበት። ዋናው ነገር እርሳቸውን ማግኘት ነው። ሆኖም ወርቅ ጫማ ያደረገ ሰው ቢፈልግ ሊያገኝ አልቻለም። ንጉሡ ካባ እንደሚያደርጉ አባትየው ሲያወሩ ሰምቷል። የወርቅ ጫማ ስላጣ ካባ መፈለግ ጀመረ። ቀና ሲል ካባ አየ። ካባ ያደረጉት ሰውዬ አጭር ናቸው። ቁመታቸው አልተነገረውም። ካባ ያደረጉት ሰውዬ እሳቸው ባይሆኑስ? ብሎ ጠረጠረ። ግን ደግሞ ሌላ ካባ ያደረገ ሰው የለም።

 ቢሆንም ባይሆንም ትንሹ ልጅ ከወታደሮቹ እግር ስር ፈትለክ ብሎ ሄደና ካባ ያደረጉትን ሰው እንደ በረኛ እግራቸው ላይ ተጠመጠመባቸው። መጀመሪያ የያዘው አንድ እግራቸውን ነበር። በቂ ስላልመሰለው ሁለተኛ እግራቸውን ደገመና እንቅ አድርጎ ያዘ። ይሄን ጊዜ ንጉሡ ተንገዳገዱ። ወታደሮቹ ምን መጣ ብለው ደነገጡ። ተንደርድረው ሄደው ትንሹን ልጅ ከንጉሡ እግር ላይ መመንጨቅ ጀመሩ። ትንሹ ልጅ ግን እግራቸው ላይ እንደ መዥገር ተጣብቆ ‹‹አለቅም›› አለ።

ንጉሡም ወታደሮቹን ‹‹ቆይ ተውት›› አሉና ሊያናግሩት አንገቱን ቀና አደረጉት።

 ትንሹ ልጅ የተወለደው ጎንደር ውስጥ ደብረታቦር ነው። እናቱ በልጅነቱ ነው የሞቱት። አባቱ ወታደር ስለነበሩ አንድ ቦታ አልተቀመጡም። ጅማ፤ ሐረርና ሌላም ቦታ እየተዘዋወሩ በየስፍራው ሄደዋል።

 ልጁም አባቱን እየተከተለ ይጓዛል። አባቱ አንድ ቦታ ባለመቆየታቸው ትምህርት ቤት መግባት አልቻለም። ማንበብም ሆነ መጻፍ አይችልም። አሁን አባቱ ጡረታ ወጡና አንድ ቦታ ተቀመጡ። ነገር ግን እዚህ ቦታ ትምህርት ቤት የለም። ከዚህ በኋላ ትምህርት የማግኘት እድሉ የመነመነ ሆኖ ከአባቱ ጋር ጡረታ ለመውጣት ተገዷል። ትናንት ምሽት ግን ንጉሡ እንደሚያስተምሩ ከአባቱ በመስማቱ ፊደል የመቁጠር ተስፋው ለምልሟል። ከብዙ ጥረት በኋላ አግኝቷቸዋል። አሁን ደግሞ እግር ይዟል። የቀረው ድርድሩ ነው። ንጉሡ እግራቸውን የያዘውን ልጅ አስለቀቁትና ‹‹ማነው ስምህ?›› አሉት።

 ‹‹ሸዋንግዛው›› ‹‹አባትህ ማን ነው?››

‹‹አጎናፍር››

‹‹ምን ፈልገህ ነው እግሬን የያዝከው?››

‹‹አስተምሩኝ››

‹‹እዚህ ትምህርት ቤት ልንከፍት ነው

የመጣነው››

‹‹እኔ እዚህ አልማርም››

‹‹የት መማር ነው የምትፈልገው?››

‹‹አዲስ አበባ››

‹‹በል እሺ አባትህ ይዞህ ይምጣ››

‹‹አልፈልግም እርሶ ይውሰዱኝ››

‹‹እንግዲያውስ ጎብኝቼ ልጨርስና

እወስድሀለሁ።››

ድርድሩ በዚህ ሁኔታ ወደስምምነት በመድረሱ ትንሹ ልጅ እግር ለቀቀና ቀጣዩን ነገር መጠበቅ ያዘ። ንጉሡ ጉብኝታቸውን እስኪጨርሱ ትንሹን ሸዋንግዛው መቶ አለቃ ጉደታ ለተባለ ሞተረኛ በአደራ ሰጡት። ከጉብኝታቸው ሲመለሱ ለጄኔራል መኮንን ደነቀ ቤተ መንግስት ድረስ እንዲያመጣላቸው ሰጡት። ጄኔራል መኮንን ደነቀ ደግሞ በማክ ለተጫኑት ወታደሮች ወደ አዲስ አበባ ይዘውት እንዲሄዱ በአደራ ሰጣቸውና ኳሱን በኪሱ እንደያዘ ትልቁ ማክ ላይ ተሳፈረ። አባትየው ጉዳዩን ሰምተው ወደ መኪናው መጡ። ሸዋንግዛው አባቱን ሲያይ ሆዱ ባባ። ማልቀስ ጀመረ። ለቅሶ ብቻ ሳይሆን አውርዱኝ ብሎ እሪታውን ለቀቀው። ለመውረድም ተንደረደረ። ወታደሮቹ ግን እጁን ጨምድደው ያዙት። አባትየው መኪናው ላይ ተንጠለጠሉና ‹‹ልጄን አምጡ›› አሉ።

 ‹‹ምንድን ነህ አንተ?››

‹‹የእኔ ልጅ ነው››

‹‹አናውቅህም አንተን››

‹‹ልጄ ነው ብያችኋለሁ ስጡኝ››

‹‹ የአደራ እቃ ነው አንሰጥም››

‹‹ልትወስዱብኝ አትችሉም። ልጄን ስጡኝ››

‹‹አንሰጥም››

‹‹ለምን?››

‹‹ጃንሆይ ተረክበውታል››

‹‹ልጠይቃቸው?››

‹‹ለእኛ ያስረከበን አለቃችን ነው። አትልፋ››

አባትዬው ከወታደሮቹ ጋር ሲከራከሩ ሸዋንግዛው አውርዱኝ ብሎ ሲጮህ ግብግብ ተፈጠረ። አባትየው መኪና ላይ ሲወጡ አስወረዷቸው። ወደ መኪናው እንዳይጠጉም አስጠነቀቋቸው። አባትዬው ‹‹ልጄን›› እያሉ ሲፍጨረጨሩ ትልቁ መኪና የሚያለቅሰውን ትንሽ ልጅ ይዞ እያጓራ አፈትልኮ ሄደ። ወታደሮቹ እየጨፈሩ ሸዋንግዛው እያለቀሰ አዲስ አበባ ገቡ። በነጋታው በአደራ የተረከቡት ጄነራል ወስደው ለንጉሡ አስረከቡት። ማደሪያውንም ቤተመንግስት አደረገ። ትምህርት ፈላጊው ታዳጊ አዲስ አበባ የደረሰው የትምህርት ጊዜ መገባደጃው ስለነበረ ትምህርት ቤት መግባት አልቻለም። ቀኑን ሙሉ እስኪደክመው ከአቦምሳ ይዞት የመጣውን ጨርቅ ኳስ ግቢው ውስጥ ሲያንቀረቅብ ይውላል። በአዲሱ ዓመት ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት አስገቡት። ትምህርት ቤቱ አዳሪ ስለነበር የሚውለውም የሚያድረውም እዚያው ሆነ። አልፎ አልፎ ወደ ቤተመንግስት እየሄደ ይጠይቃቸዋል።

 ታህሳስ 5 ቀን 1953 ዓ.ም ንጉሡ ለጉብኝት ወደ ብራዚል ሄዱ። ጄኔራል መንግስቱ ንዋይ የመራው መፈንቅለ መንግስት ተካሄደ። በዚያን እለት ግርግሩ እንደተነሳ ቤተሰቦች ወደ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት እየሄዱ ልጆቻቸውን መውሰድ ጀመሩ። ግቢው ውስጥ ከነበሩት 300 ተማሪዎች ሸዋንግዛውና አንድ ልጅ ብቻ ቀሩ።

 ከተማው ውስጥ ያለው ተኩስ እየበረታ ሲሄድ ልጁና ሸዋንግዛው ግቢው ውስጥ ባለው ባንዲራ መስቀያ አጠገብ ተቃቅፈው ቁጭ አሉ። በኋላ ግን የልጁ ቤተሰቦች መጥተው ይዘውት ሄዱ። ሸዋንግዛው ‹‹እባካችሁ ቤተሰብ ስለሌለኝ እኔንም ውሰዱኝ›› ቢልም ሰሚ ባለማግኘቱ ግቢው ውስጥ ብቻውን ቀረ።

አሁን ሸዋንግዛው የሚገኘው ጦርነቱ የተፋፋመበት አካባቢ በመሆኑ ትልቅ ስጋት ላይ ወደቀ። አባቱ ትዝ አሉት። ለመማር ብሎ ትቷቸው መጥቶ እዚህ የጥይት እራት ሊሆን ተቃርቧል። ከተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ጎን የክብር ዘበኛ ግቢ አለ። ትምህርት ቤቱና ግቢውን የግንብ አጥር ነው የሚለያቸው።

በግንብ መሀል ደግሞ የእግር መንገድ አለ። መፈንቅለ መንግስቱን ያደረገው ክብር ዘበኛ ነው። ጦር ሠራዊት ደሞ መፈንቅለ መንግስቱን አክሻፊ ሆኖ ተሰልፏል። ጦር ሠራዊት ክብር ዘበኛን ለመግጠም ወደዚያ ያመራል። ሁለቱ የሚፋለሙት ትምህርት ቤቱን ማእከል አድርገው ነው። ትምህርት ቤት ውስጥ ያለው ሸዋንግዛው ነው። ክቡር ዘበኛና ጦሩ ሸዋንግዛውን መሀል ቤት ሳንዱች ሊያረጉት ነው።

አየር ሀይል የክብር ዘበኛ ግቢን እንዲመታ ስለታዘዘ እየተምዘገዘገ መጣ። ትምህርት ቤቱ ግቢ ውስጥ ገላጣ ሜዳ ላይ ሸዋንግዛው ቆሟል። ያንን ጄት የሚያበረው ደግሞ የቀድሞ የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ተማሪ ነው። አብራሪው የክብር ዘበኛን ካምፕ ለመምታት ዝቅ አለ። ቀደም ሲል ደጋግሞ መቶታል:: አውሮፕላኑ ዝቅ ሲል የክብር ዘበኛ ወታደሮቹ ወደ ፓይለቱ መተኮስ ጀመሩ። ይሄን ጊዜ አውሮኘላኑ ካምፑን ትቶ ትምህርት ቤቱ ላይ ቦንቡን ጣለው።

ቦምቡ ሰባተኛ ‹ሀ› ስምንተኛ ‹ለ› ምናምን ክፍሎችን አፈራረሳቸውና አንድ ክፍል ሆኑ። ትምህርት ቤቱ በቦምብ ሲመታ ሸዋንግዛው እግሬ አውጪኝ አለ። ነገር ግን የት እንደሚሄድ እንኳን አያውቅም። ግን ከግቢው ወጥቶ መሮጥ ጀመረ። አውሮፕላኑ ቦምቡን ሲያርከፈክፍ የክብር ዘበኛ ወታደሮች ድጋሚ አውሮኘላኑ እንደሚመጣ ስላወቁ ጠመንጃቸውን እየጣሉ ወደ እንጦጦ ተራራ መሮጥ ጀመሩ። ሸዋንግዛው መንገድ ላይ ጠመንጃ አገኘና አነሳው:: ግን ምንም ስለማያደርግለት መልሶ ጣለው።

 ከግቢው ወጥቶ እንደሄደ አንድ ተማሪ አገኘ። አብረው ለመሆን ተነጋገሩ። መንገድ ላይ አንድ የወታደር መኪና አገኙ። መኪናው ውስጥ ገቡ። መንዳት ባይችሉም መኪና እንዴት እንደሚነዳ በወሬ ስለሰሙ ‹‹ይሄንን ንካ…. ያንን እንዲህ አድርግ›› እየተባባሉ ያገኙትን ቦታ መጎርጎር ጀመሩ።

 መኪናው ከተነሳ ከእዚህ አካባቢ ማምለጥ ይችላሉ። መኪናው ብቻ ይነሳ መሪ ይዞ መሄድ ነው። ምን ችግር አለው? ብለው አሰቡ። ሞተሩን ለማስነሳት ሲጐረጉሩ ከመኪናው ኋላ የሆነ ድምፅ ሰሙ። ዞር ሲሉ አንድ ወታደር ወድቋል። ደግሞም ያቃስታል። ሰውነቱ በደም ተጨማልቋል። ግን መሳሪያ ይዟል።

መሳሪያ መያዙን ሲያዩ ከመኪናው ዘለው ወረዱና አመለጡ። አሯሯጣቸው የድንጋጤ በመሆኑ ተበታተኑ። ራቅ ካሉ በኋላ ሲፈላለጉ ሊገናኙ አልቻሉም። በዚህ ቀውጢ ሰዓት አንዱ ለሌላው አስፈላጊ ነበሩ። ግን ተጠፋፉ። ሸዋንግዛው ልጁ ወዴት እንደሄደ ስላላወቀ ምናልባት ትምህርት ቤት ገብቷል ብሎ ስለገመተ እዚያም ሄዶ ፈለገው። ክፍሎቹን አሰሳቸው። ነገር ግን እዚያም የለም።

ከ30 አመት በኋላ ለተለያዩ ጉዳዮች ወደአሜሪካ ብዙ ጊዜ የተመላለሰው ሸዋንግዛው በአንድ እለት ሆቴል ውስጥ የሆነ ሰው ተመለከተ። የት ነው የማውቀው ብሎ ማሰብ ጀመረ። ነገሩ ግራ አጋባው።

 ተመሳስሎበት እንጂ የተሳሳተ ሰው እንዳየ ገመተ። ትቶት ሊሄድም ፈለገ። ሰውየውም ትኩር ብሎ ተመለከተው። ሁለቱም ተጠራጥረዋል። ሸዋንግዛው ወደ ሰውየው ሄዶ ‹‹እንተዋወቃለን አይደል?›› አለው።

‹‹መሰለኝ››

‹‹አዲስ አበባ ነው አይደል?››

‹‹አዎ››

‹‹ቦታውን ታስታውሳለህ?››

‹‹ንገረኛ››

‹‹ተፈሪ መኮንን››

‹‹አዎ እዛ እማር ነበር››

‹‹የመፈንቅለ መንግስቱ ቀን አብረን ነበር››

‹‹አሁን በደንብ አስታወስኩህ››

‹‹ለመሆኑ የዛን ቀን የት ሄድክ?››

‹‹እንደተበታተን ዘመዶቼን አገኘሁ››

‹‹ከዛስ?››

‹‹ትምህርቱ ቀረና እዚህ መጣሁ››

ሁለቱም ብዙ አወሩ። በ30 ዓመታት ውስጥ ብዙ ነገሮች ተቀያይረዋል። ሸዋንግዛው ለጊዮርጊስ ክለብ ገባና ዝነኛ ሆነ። ለብሔራዊ ቡድን ተመረጠ። በአራተኛው፤ በአምስተኛው፤ በስድስተኛውና በሰባተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለብሔራዊ ቡድን ተሰለፈ። ከተጫዋችነት አንስቶ በአሰልጣኝነት እንዲሁም በአመራር

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top