ስርሆተ ገፅ

የመረዋ አዲስ መንገድ

ሁሉም ወጣቶች ናቸው፤ የሙዚቃ ስሜት ያስተሳሰራቸው:: ያለ ምንም የሙዚቃ መሳሪያ በድምፅ እና በትንፋሽ ብቻ ሙዚቃን የተጠበቡ:: የኩኩ ሰብስቤን “እንዴት ነው ነገሩ” እና የግርማ በየነ “ፅጌሬዳ” ዘፈኖች በጥሩ መጫወታቸው የሙዚቃ አድናቂ እና አፍቃሪዎችን ቀልብ ስበዋል:: “መረዋ” ይባላል የስብስብ መጠሪያቸው:: የመረዋ ኣባል እና ማናጄር ወጣት አቤል ታምሩ ስለ ቡድኑ አጠቃላ እንቅስቃሴ እና መሰራረት የነገረንን እንዲህ አቅርበነዋል::

መረዋ ኳየር እንዴትና መቼ ተመሰረተ?

መረዋ “መረዋ” ከመባሉ በፊት፤ ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት በኢትዮጵያውያን ወጣት ድምፃውያን ነበር የተመሰረተው:: ከነዚህ ወጣት ዘፋኞች አንዳንዶቹ በያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት እንዲሁም ጃዝ አምባ ትምህርት ቤት የሚማሩ ተማሪዎችና አስተማሪዎች ሲሆኑ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምሩ የሙዚቃ መምህራን ናቸው:: ለአምስት ዓመታት ያህልም አብረው ሰርተዋል:: አሁን በዚህ አዲስ የሙዚቃ ስታይል የኢትዮጵያን ሚዲያዎችን ቀልብ ስበው ይገኛሉ::

ለለዛ የሙዚክ አዋርድ የሙዚቃ ኮንሰርት ከአብነት አጎናፈር ጋር የመጀመሪያው ስራቸውን አቀረቡ:: ይህ ሁሉ ሲሆን “መረዋ” ሚባለው ስም አልተሰጠውም ነበር:: የዛን ዕለት የነበረው አቀራረባቸው በጣም ቆንጆ ሆነ:: ከዛ በኋላ ይሄንን ነገር ለምን ስም አንሰጠዉም? የሚል ሃሳብ መጣ:: ሁለተኛው ስራ በኤግዝቢሽን ማዕከል በተዘጋጀው ትልቅ የቡክ ፌር ዝግጅት ላይ መረዋ የሚል ስም ወጣለት:: መረዋ ማለት የአንድ ድምፅ መለኪያ ነው::

 በአድማጭ ዘንድ ያለው ተቀባይነትስ እንዴት ይመስላል?

አዲስ ነገርን ማስተዋወቅ በጣም ከባድ ነገር ነው:: የዛሬ አርባ ዓመት ትንሽ ጭላንጭል የታየበት ይህንን ዓይነት የሙዚቃ አጨዋወት ለመሞከር ነበር:: እሱም ኢትዮጵያዊ አይደለም አርመናዊ ናቸው::

ግን አልተሳካም:: ስለዚህ ለመረዋ እንደ አዲስ ባለ ታሪክ እንደ አዲስ ኢትዮጵያዊ ጀማሪ ይህንን ነገር ሰው ይቀበለዋል ወይ ብሎ ማሰብ ለነሱ በጣም ከባድ ነበረ:: ግን ውጤቱ መጨረሻ ላይ የተገላቢጦሽ ነው:: አስራ አንድ ሰው እንደ አንድ ቡድን ሆነው በማቅረባቸው ትልቅ ስኬት ነው:: እያንዳንዳቸው ለድምፅ እንደ አንድ ሁነው እንደ አስራ አንድ የሚለውን ስሜት ይዘው በዛው ልክ አቅማቸውን አሳይተዋል::

በኮንሰርት ደረጃስ የት የት ተካሂዶ ነበር?

 ኳየር ሙዚቃ ስታይል ከአውሮፓ የመጣ ስለሆነ፤ ብዙዎቹ ኤምባሲ አከባቢ፣ ቆንስላ ፅህፈት ቤቶች ከዛም አልፎ በኢንተርናሽናል ሆቴሎች የውጪ ዜጎች ስለሚገኙ ለዚህ ሙዚቃም ቅርብ እንደመሆናቸው መጠን፤ ይህ ለሀገራችን አዲስ የሙዚቃ ስልት የሆነው ለነሱ እያቀረቡ ይገኛሉ:: እኛ ሀገር ላይ ስንመጣ ግን ስሜቱን ገና እንፍጠር ነው ቡድኑ የሚለው፤ እንጂ ገና ለህዝባችን ተደራሽ አልሆነም:: በሌላው ሀገር ለምሳሌ አፍሪካ ውስጥ ደቡብ አፍሪካ፣ ማዳጋስካር አካባቢ እንደ ባህል ነው ሚቆጠረው:: እነ ብላክ ሙባቤ የደቡብ አፍሪካ የባህል አምባሳደር ናቸው:: ምክንያቱም ደቡብ አፍሪካ የራሷ የሆነ የባህል ቡድን አምባሳደር የላትም:: አምባሳደሯ የኳየር ቡድን ነው:: ማንዴላ በሚዞሩበት ወቅት እነሱን ይዘው ነበር፤ ሀገሬን በዚህ ደረጃ ያሳያሉ ብለው ስለሚያስቡ ነው እና እዛ ደረጃ መድረስ እስከተቻለ ድረስ “እኛም የራሳችን ነገር ለሀገራችን በሙዚቃው ዘርፍ አምባሳደሮች ሆነን መገኘት ነው” የሚል እሳቤ አለው ቡድኑ:: ግን እሱን ለማድረግ መጀመርያ ኢምባሲዎች አካባቢ፣ ሆቴሎች የመሳሰሉ ቦታዎች ስራዎቻቸውን አቅርበዋል:: በተጨማሪም ቤተ-መንግሥት በመገኘት በክብርት ፕሬዝዳንት ጥያቄ መሰረት የኩኩ ሰብስቤን “እንዴት ነው ነገሩ” የተሰኘውን ተወዳጅ ዜማ አቅርቧል::

ይሄን የሙዚቃ ስታይል ያለ ሙዚቃ መሳርያ ለመስራት አይከብድም?

ፍቅሩ ልምምዱ ካለ አይከብድም:: እዚህ የኳየር የሙዚቃ ስታይል ስራ ላይ የሙዚቃ መሳሪያ የለም:: የኩኩም ሆነ የግርማ በየነ ስራዎች እንዳሉ በድምፅ እና በትንፋሽ ብቻ የተሰሩ ናቸው:: በቀጥታ ሲዘፈን ካልተሰማ በስተቀር ለማመንም ያስቸግራል:: ልዩ የሚያደርግበት አንዱ ምክንያትም የሙዚቃ መሳርያ አለመጠቀሙ ነው:: እያንዳንዳቸው በአፋቸው ድምፅ በመፍጠር የሙዚቃ መሳሪያ ዓይነቶችን ወክለው ይጫወታሉ:: ለምሳሌ፡- አንዱ ቤዝ ጊታር፣ አንዱ ድራም፣ ሌላው ትራምፔት ወዘተ በመተካት:: ይህን ለመስራት ግን ከባድ ልምምድ እና ደጋግሞ መስራት ይጠብቃል:: ከዚህ በኋላ መድረክ ላይ ስኬታማ መሆን ይቻላል::

 መረዋ በወደፊት ዕቅዱ ምን ይዟል?

 በኢትዮጵያ የኳየር የሙዚቃ ታሪክ ለወደፊት ሲነሳ ምናልባት “መረዋ” ኳየር የመጀመርያውን ደረጃ መረጋገጥ ነው:: ለዚህ ታሪክ ግብአት የሚሆነውም አልበም በመስራት ነው ሚሆነው:: የቡድኑ አባላት ባጭር ጊዜ ውስጥም አልበም ሰርተው ለአድናቂዎቻቸው ማቅረብ ይፈልጋሉ::

የቡድኑ አባልና ማናጄር አቤል እንዲህ ይላል…“የአንድ ሰው አልበም ለመስራት ምን ያህል ዓመታት እንደሚፈጅ ይታወቃል:: እኛጋ ወደ አስራአንድ ሰው ስንመጣ ደግሞ ባለን የተፈጥሮ ድምፅ እንደ ህልም ያህል የሚታሰብ ነገር እንደሰራን ከሚደርሰን ጥቆማና አስተያየት ተረድተናል:: የመጀመርያው ዕቅዳችን ለሚወደን ህብረተ-ሰብ ወደፊት መኖር እንፈልጋለን:: ወደፊት ለሚጠይቀን ህብረተ-ሰብ ሙዚቃ እንዴት አልተሰራም ብሎ ለሚጠይቀን ትውልድ ይህንን መልስ ሰጥተን ማለፍ እንፈልጋለን::

 ከቅርብ ጊዜ በኋላ በተለይ አዲሱን ትውልድ ወክለን ስለ እያንዳንዱን ሰው ሰላም፣ የእያንዳንዱን ሰው ማንነት፣ ፍቅር በሚመለከት ለሀገራችን እንሰራለን:: አቅማችንን አሳይተንም ለአፍሪካም ብሎም ለዓለምም መስራት እንፈልጋለን:: ይህ ደግሞ እንደ አዲሱ ትውልድ ማንነታችንም ግዴታችንም ነው ብለን እናስባለን:: የመጀመርያው ዕቅዳችን አልበም የመስራት ሆኖ፤ በቀጣይ ደግሞ ከሱ ጋር በተያያዘ ስለሰላም መስበክ በየቦታው መናገር፣ አንዱን ከአንዱ ጋር የማቀራረብ ስራ እንሰራለን ብለን ተነስተናል” ይላል::

 ሙዚቃ በኢትዮጵያ ረዥም ዘመን አለው:: ከቅዱስ ያሬድ ጀምሮ ማለት ነው:: ኳየር ሙዚቃ ግን በኢትዮጵያ ያን ያህል የታወቀ አይደለም:: የመረዋ ኳየር አባላት ሁሉም በተፈጥሮ የተሰጣቸውን የሙዚቃ ክህሎታቸውንና ድምፃቸውን ተጠቅመው ይህን ለሀገራችን አዲስ የሆነውን የሙዚቃ ስታይል እያስተዋወቁ ይገኛሉ::

 ወጣቶቹ በሙዚቃው ዘርፍ አዲስ ነገር ይዘው መምጣት ብቻ ሳይሆን፤ ለሰላምና ለፍቅር ሊሰብኩ መነሳታቸው ያስመሰግናቸዋል:: ድጋፍና ማበረታታትን ይሻሉ:: እኛ በርቱ ብለናል፤ በርቱ!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top