ፍልስፍና

ከኢትዮጵያ ፍልስፍና ገጾች (የሐተታ ዘርዓ ያዕቆብ ፈትለ ነገር ትንታኔ)

እንደመግቢያ

 የዚህን ጽሑፍ ርእስ በመመልከት “የኢትዮጵያ ፍልስፍና የትኛው ነው? የኢትዮጵያ ፍልስፍና ሲባልስ የማን ፍልስፍና ነው?” የሚሉ ጥያቄዎችወደ አንባቢ አእምሮ ሊመጡ ይችላሉ። ርግጥ ነው ፍልስፍና ዜጋ የለውም። መገለጫ ባህርይውም በሰው ልጆች የአስተሳሰብ ታሪክ ውስጥ መሠረታዊ የነገረ ህልውና፣ የሥነ ምግባር፣ የሥነ እውቀት፣ የሥነ ውበት ባጠቃላይ ማኅበራዊና ተፈጥሯዊ ምስጢራትን መመርመር፣ በምክንያታዊነት መነጽር መተቸት፣ መሞገትና ማብራራት የፍልስፍና መንገድ ነው። ታዲያ የኢትዮጵያ፣ የእንግሊዝ፣ የጀርመን፣ የአሜሪካ ወይም የህንድ ፍልስፍና ስንል ምን ማለታችን ነው? አንድም በአንድ ዘመን በነበሩ ተጽእኖ ፈጣሪ ፈላስፎች አማካኝነት ለዚያ ልዩ አስተሳሰብ ስያሜ መስጠታችን ነው።

በሌላም በኩል አንድ ማኅበረሰብ በባህልና በታሪክ ጉዞው ውስጥ፣ ካለው ልዩ የተፈሮ ተግዳሮት፣ በይማኖታዊ አስተምህሮዎች ወይም ኬሌሎች ማኅበረሰቦች ጋር በሚያደርገው ግንኙነት ዓለምን የሚያይበት መነጽር በተወሰነ መልኩ ልዩነት ስለሚኖረው በፍልስፍናው ላይ የራሱን ጫና ስለሚፈጥር የዚያ አካባቢ ፍልስፍና የራሱ የሆኑ ውሱን መገለጫዎች ይኖሩታል። በዚያው ስያሜውን ይይዛል። በተለምዶ በአህጉር ወይም በአገር ሲጠራ በይዘቱ ደግሞ ተቀጽላ ተደርጎበት የፍልስፍናውን ይዘት ያንጸባርቃል። የአሜሪካ ፕራግማቲዝም፣ የብሪቲሽ እምፕሪሲዝም፣ የጀርመን አይድያሊዝም የሚሉት ተቀጽላዎች የዚህ ማሳያ ናቸው። በወቅቱ የነበረው የዘመን መንፈስ በቦታዎቹ የየበለጸገው ፍልስፍና መገለጫ ባህርያትን ያሳያል ማለት ነው።

 የኢትዮጵያ ፍልስስፍና እንደምን ያለ ነው? በዚህ ጉዳይ ላይ በአጥኝዎች ዘንድ ይህ ነው የሚል ስምምነት ያለ አይመስለኝም። ነገር ግን በባህልና፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋ፣ በፖለቲካዊና በማኅበራዊ እንዲሁም በኢኮኖሚያዊ ዘውጎች ልዩነት ያላቸው ኢትዮጵያውያን አንድ ዓይነት ፍልስፍና ይኖራቸዋል ማለት ይከብዳል። ምንም እንኳን አንዳንድ የታሪክና የባህል ተመራማሪዎች (ለምሳሌ ሌቪን፣ ተክለጻድቅ መኩሪያ) ሁሉንም ኢትዮጵያውያን አንድ የሚያደርጋቸው የጋራ የባህል ግንድ አለ የሚል ሙግት ቢያቀርቡም ሁሉም አንድ ዓይነት ፍልስፍና አላቸው ለማለት የሚያስደፍር አይደለም። የተለያዩ አካባቢያዊ ሁኔታዎች የእያንዳንዱን ማኅበረሰብ አስተሳሰብ ስለሚወስኑት ፍልስፍናውም የተወሰነ ልዩነት ይኖረዋል።

 “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” የሚለው ጥቅል መጠሪያ በኢትዮጵያ ምድር የሚገኝ ማንኛውም ፍልስፍናዊ አስተሳሰብ በሌላው ማኅበረሰብ የአስተሳሰብ ውህድ ውስጥ አሉታዊ ጫና የማያሳድር፣ የዚያን ማኅበረሰብ ፍልስፍናዊ ጥያቄዎች በተጠየቃዊ እና በሥነ አመክንዮአዊ ሙግት የሚመልስ ከሆነና ለዘመናችን አጣዳፊ የሕይወት ትርጉም፣ የህግ፣ የፖለቲካ፣ የሥነ ውበት፣ የሥነ ምግባር ወዘተ ጥያቄዎች ግብአት የሚሆን መላምታዊ አስተዋጽኦ ካለው ያን ማኅበረሰባዊ ጥበብ የኢትዮጵያ ፍልስፍና ልንለው እንችላለን።

 እነ ክላውድ ሳምነርና ቴዎድሮስ ኪሮስ የኢትዮጵያን ፍልስፍና ለመረዳት የሚጠቅሙን ዘዴዎች የቀጥታ ትርጓሜና የአንድምታ ትንታኔ በማለት በሁለት ይከፍሏቸዋል። ከትውልድ ወደ ትውልድ በቃል ወይም በተግባራዊ ክዋኔ ሲተላለፉ የመጡትንና በጽሑፍ ከሌላ ቋንቋ የተተረጎሙትን አስተሳሰቦች ፍልስፍናዊ መሠረት ለመፈለግ የአንድምታ ትርጓሜ መንገድን በመጠቀም መተንተን ይቻላል። ቀጥተኛ ትርጓሜ ደግሞ በግለሰቦች አስተሳሰብ የተጻፉ ወጥ የፍልስፍና ሥራዎችን ለመረዳት የምንጠቀምበት ዘዴ ነው። ከባህል የጋራ አስተሳሰብና የጠቢባንን ጥበብ ለመረዳት እነዚህና ተዛማጅ ዘዴዎችን በመጠቀም የኢትዮጵያን ፍልስፍና መመርመር ይቻላል።

በዚህም መንገድ የኢትዮጵያ ፍልስፍና ሦስት አቀራረቦች አሉት። አንደኛው በየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢ ያለ ከባህሉ ጋር የተቀየጠ አገረሰባዊ ጥበብ (Folk Wisdom) ነው። ይኸውም የጋዳ ሥርዓት፣ የሽምግልናና የህግ አስተምህሮዎች፣ የቅኔ ፍልስፍና፣ የነገረ መለኮት አስተምህሮዎች፣ የሕይወት ትርጉምና የኑሮ ዘዴዎች ውስጥ መሠረታዊ አስተሳሰቡን የሚወስነው ፍልስፍናዊ ሙግት ነው። ያንን ለመተንተን የምሁራኑ ሚና በዘልማድ ከሚታየውና ኋላ ቀር ነው ተብሎ ከተፈረጀው የላይ የላይ ኑሮ ባሻገር የአስተሳሰብ ምህዋሩን፣ ፍልስፍናዊ ፈትለ ነገሩን (Theme) ፈልፍለው ማውጣት እንደሆነ ሌቪን ይጠቁማል። ለምሳሌ ሳምነር ከኦሮሞ ቃላዊ ጽሑፎች ሦስት ያክል መጻሕፍትን ሲያሳትም፣ ሌቪን ሰምና ወርቅ ቅኔ ላይ የጻፈው መጽሐፉ ለአብነት የሚጠቀስ ይሆናል። ሁለተኛው ከጥንት ዘመን ጀምሮ 6ኛው እስከ 16ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ከውጭ ቋንቋ ተተርጉመው የቀረቡት የጽሑፍ ፍልስፍናዎች ናቸው። እነዚህ በሰሜን ኢትዮጵያ ሴማዊ ጫና ያላቸው ከዓረብ፣ ከግሪክ፣ ከሶሪያ፣ ከሩቅ ምሥራቅ ተተርጉመው የሚገኙት ናቸው። በእስልምናው የዓረብኛ ብራናዎች ውስጥ እንደዚህ ያሉ ድርሳናት ስለመኖራቸው እስካሁን አላረጋገጥኩም። በግእዝ ቋንቋ ተተርጉመው ከተገኙት ውስጥ ለምሳሌ የእስክንድስ ጠቢብ የሕይወት ታሪክና መርሆዎች፣ አንጋረ ፈላስፋ፣ እንዲሁም ፊሳልጎስ በመባል የሚታወቀው መጽሐፍ ይጠቀሳሉ።

 እነዚህ የትርጉም መጻሕፍት በምን ምክንያት የኢትዮጵያ ፍልስፍና ሊሆኑ ይችላሉ? መልሱ ግልጽ ነው። ኢትዮጵያውያን እንደወረደ አይተረጉሙም። የውጭውን አስተሳሰብ መሠረታዊ ይዘት ሳይለቅ ከኢትዮጵያ የባህል፣ የሃይማኖት፣ የፍልስፍና አስተሳሰቦች ጋር እንዲስማማና ዓውዱን እንዲጠብቅ አድርገው ይተረጉሙታል። ይህ የተጠና የትርጓሜ ዘዴያቸው አንዳንዴ ኦርጂናሌ እስኪመስል ድረስ ከኢትዮጵያ ጋር ያዋህዱታል በሚለው ሳምነርም ሌቪንም ይስማማሉ።

ሦስተኛዎቹ በኢትዮጵያውያን ግለሰቦች ተጽፈው የተገኙ ወጥ የፍልስፍና ድርሳናት ናቸው። ከነዚህ ውስጥ እስካሁን ለህትመት የበቁት በ17ኛው ክፍለ ዘመን የኖሩት ኢትዮጵያውያን የዘርዓ ያዕቆብና የርሱ ደቀ መዝሙር የነበረው የወልደ ሕይወት ሐተታዎች ብቻ ናቸው። በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የዘርዓ ያዕቆብን ሐተታ ፈትለ ነገር ወይም መሠረታዊ ይዘቱን በአጭሩ እዳስሳለሁ። በዋናነት የተጠቀምኩት አለቃ ያሬድ ፈንታ ወልደ ዮሐንስ በ2007 ዓ.ም ወደ አማርኛ የተረጎሙትን ነው። ከሐተታው ስጠቅስ የገጽ ቁጥሩ ይህንኑ እትም መሠረት ያደረገ ነው።

ዘርዓ ያዕቆብ ኢትዮጵያዊው ፈላስፋ

 አንዳንዶች ሐተታ ዘርዓ ያዕቆብና ወልደ ሕይወት በ17ኛው ክፍለ ዘመን የነበሩ

“ከሁለት ዓመት የብቸኝነት፣ የምርምርና የተመስጦ ዘመን በኋላ ማኅበረሰቡን ተቀላቀለ። ወደ ቀደመ መደበኛው መምህርነቱ እንዳይመለስ “ሐሰትን ማስተማር አልፈቅድም።” ይለናል”

ኢትዮጵያዊያን የጻፏቸው ሳይሆኑ በ19ኛው ክፍለ ዘመን የነበረ ጣልያናዊ ሚስዮን የጻፈው ልቦለድ ነው የሚል ክርክር ያነሳሉ። ከባህረ ሐሳብ ጋር በማጣቀስ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ የዘርዓ ያዕቆብን ኢትዮጵያዊነት ይሞግታሉ። የአክሱም ሰው ስለመሆኑና የሙግቶቹ ምንጭ ራሱ ስለመሆኑ ግን ጥርጣሬ እንዳላቸው ነግረውናል። በቅርቡ ደግሞ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት “የሌለውን ፈላስፋ ፍለጋ” የሚል የነ ሮሲኒን ሐሳብ የሚደግፍ የሚመስል ሙግት ይዞ ብቅ ብሏል።

 በዘርዓ ያዕቆብ ኢትዮጵያዊነት ላይ የነ ዓለማየሁ ሞገስን ሙግት በማካተት በርካታ ሙያዊ ትንታኔዎችን በማቅረብ ሁለቱ ሐተታዎች የአንድ ሰው ሥራ እንዳልሆኑ በማስረጃ በማስደገፍ እንዲሁም ዘርዓ ያዕቆብና ወልደ ሕይወት በ17ኛው ክፍለ ዘመን የነበሩ ኢትዮጵያውያን እንደሆኑ ሚዛን የሚደፋ ሙግትና ድምዳሜ ያቀረበልን ግን “በትውልድ ካናዳዊ፣ በምርጫ ኢትዮጵያዊ ነኝ” የሚለው ክላውድ ሳምነር ነው። እኔም ከሁለት ዓመታት በፊት በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ባቀረብሁት ጥናታዊ ጽሑፍ ከምሁራኖቹ ሙግት ባሻገር በወቅቱ ከተጻፉት የታሪክ ድርሳናት ውስጥ ዘርዓ ያዕቆብ የሚባል ፈላስፋ ስለመኖሩ ዳሰሳ አድርጌ ነበር። በርግጥም የተክለ ጻድቅ መኩሪያ፣ የአለቃ አጽሜ፣ የአጼ ሱሲንዮስ ዜና መዋዕል፣ ዓለማየሁ አበበ የተረጎመው ሁለት የውጭ ሰዎች የጻፉት የኢትዮጵያ ታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ፍንጭ የሚሰጡ ነገሮች አሉ። የሌለውን ወይም የነበረውን ፈላስፋ ፍለጋውን ለአንባቢ በመተው እኔ ስለነበረው ፈላስፋ ሕይወትና አስተሳሰቦች ትንሽ ለማለት ፈቀድሁ።

ዘርዓ ያዕቆብ ወይም ወርቄ ስለ ሐተታው ሲነግረን ምሥጢሩን ከሚያውቀውና የርሱው ፈለግ ተከታይ በነበረው ወልደ ሕይወት ብዙ ውትወታና ማግባባት በኋላ ከተደበቀው ምሥጢሩ ትንሹን ሊጽፍልን ችሏል።

ስለ ግል ሕይወቱ ሲነግረን ምናልባትም በኢትዮጵያ የመጀመሪያው በሆነው ግለ- ታሪክ (Autobiography) መልክ በ1592 ዓ.ም በአክሱም አውራጃ ከአንድ ድሃ ገበሬ ተወለድሁ ይለናል። ከተወለደ በኋላ እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ወደ የኔታ ዘንድ ሄዶ ትምህርቱን ተከታተለ። በመምህሩ ምስክርነትና አስተያየት ልጁ ብሩህ አእምሮ ስላለው ወደ ቀጣይ ትምህርት ቢላክ ጥሩ መምህር እንደሚሆን ለአባቱ በተነገራቸው መሠረት ወደ ዜማ ቤት ይሔዳል። ድምጹ ጎርናና ከመሆኑ የተነሳ ጓደኞቹና ይስቁበት ስለነበር ከሦስት ወራት በኋላ ሐዘን በተሞላው ልቡናው ሰዋሰውና ቅኔ ወደሚያስተምሩ ሌላ መምህር ሄደ። ፈጥኖ ትምህርቱን በመያዙ የቀደመ ሐዘኑን የሚያስረሳ እርካታን አገኘ።

በዚያን ወራት ከልጆች ጋር ሲጫወት ገደል ገብቶ በተዓምር ተረፍኩ የሚለው ፈላስፋው ከዚህ ገደል መውደቅ በኋላ ያተረፈኝ ኃይል እንደምን ያለ ነው? የሚለው የግል ሕይወት ገጠመኝና አግራሞት የፍልስፍናው መነሻ እንደሆነው እንጠረጥራለን። ከዚያም በመቀጠል የቅዱሳትን መጻሕፍት ትርጓሜ ቀጠለ። የአገራችን መምህራንና የውጭ አገር መምህራን መጻሕፍትን እንዴት እንደሚተረጉሟቸው እየተመራመረ አስር አመታትን ቆየ።አሁንም የመጻሕፍቱ ትርጓሜ ነገር አብዝሃኛውን ጊዜ ከህሊናው ጋር ባለመስማማቱ የተጠራጣሪነት ዘር አቆጠቆጠ። “ነገር ግን ሐሳቤን ሁሉ በልቡናዬ ውስጥ ሸሽጌ ዝም አልሁ።” የሚለን ወርቄ፤ የተለያዩ መጻሕፍት ትርጓሜዎች ስለ አንድ እውነት እንዴት የሚቃረኑ እና የሚራራቁ እውነቶችን ሊይዙ ቻሉ? ለሚለው ጥያቄ በቂ መልስ ላለማግኘቱ ምስክር ነው። ከዚያ በኋላ በአክሱም አውራጃ ባለችው አገሩ ተቀምጦ መጻሕፍትን እያስተማረ ለ4 ዓመታት ተቀመጠ። ወቅቱ የሰው ፍቅር የጠፋበት፣ ንጉሡም የፈረንጅ ሃይማኖት የወደደበት ዘመን ነበርና በኢትዮጵያ ታላቅ ስደት ሆነ።

 በግል ሕይወቱ ደግሞ በሰው ፍቅር እና በትምህርት ከሁሉም እበልጥ ነበርና ባልንጀሮቼ ቀኑበኝ ይለናል። እዚህ ላይ በባልንጀሮቹ ለመጠላቱ አንዱ ምክንያት ይከተለው የነበረው የትምህርት ዘዴ ከተለመደው ባህል ያፈነገጠ፣ የእምነትና የሃይማኖት ጠበቃ ነን የሚሉትንም የሚያስቆጣ መሆኑ አልቀረም። “ፈረንጆች እንዲህ ና እንዲህ ይላሉ”፣ ግብጻውያንም “እንዲህ ና እንዲህ ይላሉ” “ይህ መልካም ነው፣ ይህ ክፉ ነው” አልልም። እዚህ ላይ አንድ ነገር ልብ ማለት ያስፈልጋል። የሌላውን ትምህርት ምንፍቅና፣ ክህደት ነው፤ የኛ ትምህርት ብቻ ነው ትክክለኛው ከሚለው ሃይማኖታዊ አስተምህሮ ባፈነገጠ መልኩ ተማሪዎቹን ራሳቸው አስበው፣ አሰላስለው፣ ትክክለኛውን እና ከልቡናቸው ጋር የተስማማውን እንዲይዙ ነጻነቱን ይሰጣቸው እንደነበር ያሳያል። ያ ደግሞ ተማሪው ሃሳብ እንዲወልድ እንጅ ሃሳብ እንዲሸከም ስለማያደርግ በመምህርነቱ የሶቅራጠስ አምሳያ ያደርገዋል።ይህ የማስተማር ዘዴው “ከከሃድያንና በመንግሥት ላይ ከሚያምጹት” አስቆጥሮት እንደነ ወልደ ዮሐንስ ዓይነቶቹን ከሳሾች አሰለፈበት። በዚህ ምክንያት ተረጋግቶ ማስተማር ያልቻለው ዘርዓ ያዕቆብ ሦስት ወቄት ወርቅና መዝሙረ ዳዊቱን ይዞ ወደ እንፍራንዝ እንደተሰደደ ራሱ ይነግረናል። በዚያም አራዊት እንዳይጣሉት በእሾህ አጥሮ ሰዎች ቢመጡበት ደግሞ ማምለጫ በር አበጅቶ ንጉሥ ሲስንዮስ እስኪሞቱ ድረስ ለሁለት ዓመታት በዋሻ ኖረ።

 ከጸሎት በኋላ ሥራ ሳይኖረው ስለ ሰዎች ክፋት፣ ስለ ፈጣሪ ትዕግስት፣ ስለ ሃይማኖቶች፣ ስለ ቅዱሳት መጻሕፍት፣ ስለ ሰዎች ህጎች ወዘተ. እየተመራመረ ኖረ። በመጨረሻም ከዋሻው ወጥቶ በእንፍራንዝ አንድ ሀብቱ ከሚባሉ ሰው ተጠግቶ መጽሐፍ በመጻፍ ይተዳደር፣ ልጆችን በማስተማር ይኖር ጀመር። ከሁለት ዓመት የብቸኝነት፣ የምርምርና የተመስጦ ዘመን በኋላ ማኅበረሰቡን ተቀላቀለ። ወደ ቀደመ መደበኛው መምህርነቱ እንዳይመለስ “ሐሰትን ማስተማር አልፈቅድም።” ይለናል። ነገር ግን የሀብቱን ልጆች እያስተማረ ወልደ ሕይወት የተባለውን ደቀ መዝሙር ማፍራት ሲችል፤ ሂሩት የተባለችውን የሃብቴን አገልጋይ ፈቃዷን ጠይቆ አግብቶ ልጅ ሳይወልዱ ለዓራት ዓመታት በደስታና በመተጋገዝ ከኖሩ በኋላ በዓራት ዓመታቸው ወንድ ልጅ እንደወለዱ ይተርክልናል። “ስሟ ኂሩት የምትባል የጌታዬ ቤተሰብ የነበረች አንዲት ሴት ልጅ ነበረች። እርሷም መልካም ምግባር ያላት አስተዋይና ትዕግሥተኛ እንጅ ውብ አልነበረችም። ለጌታ ሀብቱም ‘ይህች ልጅ ሚስት ትሆነኝ ዘንድ ስጠኝ’ አልሁት። ጌታ ሀብቱም እሺ በጄ ብሎ ‘ከዛሬ ዠምሮ የአንተ አገልጋይ እንጂ የእኔ አገልጋይ አትሆንም’ አለኝ። እኔም ‘ሚስቴ እንጂ አገልጋዬ አትሆንም ባልና ሚስት በጋብቻ እኩል ናቸውና። ጌታና አገልጋይ ልንላቸው አይገባም። አንድ ሥጋና አንድ የኑሮ ስልት ያላቸው ናቸውና፤’ አልሁት።” ከዚህ በኋላ የርሷ ፈቃድ ተጠይቆ መልካም ፈቃዷ ሆነ። በጋብቻም በፍቅርም ኖርን። ይለናል ፈላስፋው ስለ ሴቶች እኩልነት፣ ስለ ባልና ሚስት መፈቃቀድ፣ የነበረውን ይትበሃል በተግባር ሲተቸው የሚያሳየው ከዘመኑ የቀደመው የፍልስፍናው አንዱ መገለጫ ነው።

የዘርዓ ያዕቆብ ፍልስፍና መሠረታዊ ይዘቶች ትንታኔ

የዘርዓ ያዕቆብ ፍልስፍና በጣም እምቅ የሆነ፣ ጠንካራ ሙግቶች የያዘና ዘርፈ ብዙ ጉዳዮችን ስለሚዳስስ በዚህ አጭር ጽሑፍ ሙሉ ይዘቱን ማሳየት ከባድ ነው። አንባቢ ሙሉ ይዘቱን የግእዙን፣ የአማርኛውን፣ የእንግሊዝኛውን ቅጅዎች እንዲያነቡት አስተያየት በመስጠት ስለ ዋና ዋናዎቹ ጉዳዮች በአጭሩ ላስቀምጥ። የመጀመሪያው የነገረ ሕላዌ ጥያቄ(Metaphysical Question) ነው። እንግዲህ የሰው ልጅ መጀመሪያ ስለራሱ ምንነትና ባህርያት፣ ስለ አስገኝው ወይም ፈጣሪው ምንነት ጥያቄ ያነሳል። ዘርዓ ያዕቆብ ቀድሞ የተነገረው ሁሉን የፈጠረ አንድ አምላክ መኖሩን ነው።

ያኔ ከ23 ክንድ ገደል በተዓምር ያተረፈው ፈጣሪ ግን ምን ዓይነት ባህርያት እንዳሉት በፍልስፍናዊ መንገድ መመለስ ነበረበት። ክላውድ ሳምነር እንደሚለው ዘርዓ ያዕቆብ የሚያወራለት ፈጣሪ የክርስትናው እግዚአብሔር ወይም በሰው መልክ የተገለጠው ኢየሱስ ክርስቶስ አይደለም። ይልቁን ፈላስፎቹ እንደሚሉት ዓይነት በሥነ አመክንዮ የሚታወቅ ፈጣሪ ነው። ነገር ግን አንዳንድ ቦታ ላይ የሰዎችን እኩይ ባህርይ ሲተች በክርስቶስ የሚያምኑ ክርስቲያኖች እንዴት እንዲህ ያደርጋሉ? ሲል ይስተዋላል።

 የእግዚአብሔርን ህልውና ያረጋገጠው ዘርዓ ያዕቆብ የሰው ልጆች ተፈጥሮ ምን እንደሆነም በዚያው ያብራራልናል። ሁሉን የፈጠረ ለዘልዓለም የሚኖር ለባዊ የሆነ እግዚአብሔር ሰውን ከተረፈ ልቡናው ለባዌ አድርጎ ፈጥሮታል። ታዲያ ይህ ፈጣሪ በልቡና ቀናነት፣ በህሊና ልኅቀት የሚታወቅ ሲሆን ሰውንም ለባዌ ወይም አዋቂና ተመራማሪ አድርጎ ፈጥሮታል። “እኛ ስንኖር ፈጡሮች እንጅ ፈጣሪዎች አይደለንም። የፈጠረን ፈጣሪ አለ እንል ዘንድ ይገባል። ለባውያንና ነባብያን አድርጎ የፈጠረን ይህ ፈጣሪ ለባዊና ነባቢ ያልሆነ አይደለም። ከልቡናው ተረፍ ለባውያን አድርጎ ፈጥሮናልና።” ፈጣሪም ፈጥሮ የሰውን ልጅ እንዲሁ አልተወውም። ይልቁን ዘርዓ ያዕቆብ እንደገና “አስተዋዋይ ልቡና ስጠኝ” እያለ ፈጣሪን ሲለምን ይስተዋላል። ነገር ግን በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የሚያገናኙ መላዕክት መኖራቸውን የርሱ ደቀ መዝሙር ይጠራጠራል። ታዲያ ሰውና ፈጣሪ እንዴት ይገናኛሉ? “በጸሎት” እንደሚለን ግልጽ ነው። የሃይማኖት ፍልስፍናው እንደ ኤግዚስተንሺያሊስቱ ኬጋርድ ዓይነት ነው። የሰው ልጅ በመረጠው መንገድ ይሄድ ዘንድ ነጻ ፈቃድ የተሰጠው ፍጡር እንደሆነ ይሞግታል።

 ሁለተኛው የሥነ እውቀት ጥያቄ (Epistemological Question) ነው። ስለ ቅዱሳት መጻሕፍትና ስለ መምህራን አስተምሮ ተጠራጣሪ የሆነው ዘርዓ ያዕቆብ እውነትን ሁሉ መርምሩ የሚለውን በአጽንኦት ያሳስባል። የእውቀት ምንጩ ለባዌ የሆነው የሰው ልጅ ህሊና እንደሆነ፣ ከልቡናዬ ጋር የተስማማ ሁሉ እውነት ነው ብሎ ያምናል።ማንኛውንም እውነት ስንመረምር ልቡናችን ፍርድ ይሰጣል። ለምሳሌ ስለ እውቀት ባተተበት ምዕራፍ 8፣ ስለ አስርቱ ትዕዛዛት ሲያብራራ “ዐሠርቱ የኦሪት ቃላት የፈጣሪ ፈቃድ ናቸው። ሰንበትን  አክብር ከሚለው በቀር። ሰንበትን ስለማክበር ልቡናችን ዝም ጸጥ ይላልና።”

 በርግጥ በዘርዓ ያዕቆብ ፍልስፍና ላይ የልቡና እና የህሊና ልዩነት በግልጽ አይታይም። ልቡናን የመጨረሻው የእውነት ማረጋገጫ ምስክር አድርጎ ይወስደዋል። በተለምዶ ማስተዋልን “ልብ አድርግ” በማለት እንገልጸዋለን። የደም መርጫዋ ልብ የማሰቢያ ቦታ ማድረጋችን አይመስለኝም። ዘርዓ ያዕቆብም ልቡና የሚለው ልብ የተሰኘን አካላችንን ሳይሆን የምርምር ሂደቱን ይመስላል። ይህ ጉዳይ ለተመራማሪዎችና ለአንባቢዎች ፍርድ የተተወ ነው። ዘርዓ ያዕቆብ ግን ስለዚህ ነገር ልቡናዬ ዝም ብሏል፣ ከልቡናዬ ጋር አልተስማማም እያለ እውነትን ከልቡናው ምስክርነት ለማስረጽ (ለማስገኘት) ሲሞክር ይስተዋላል። ሌላ ጊዜ ደግሞ ኅሊናን ለምስክርነት ይጠራዋል። “ሰፊ በሆነው ልቡናዬ ሁልጊዜም የዳዊትን መዝሙር እጸልያለሁ። ይህ ጸሎት እጅግ ይጠቅመኛልና። ኅሊናዬም ወደ እግዚአብሔር ከፍ ከፍ ያደርገዋልና።

ከዳዊት መዝሙር ውስጥ ከኅሊናዬ ጋር የማይስማማ ባገኝም እኔ እተረጉመዋለሁ።” ይኸ ነገር ኋላ ላይ ከመጡት እንደ እጓለ እና ፓስካል ሰውኮ ንጹህ ህሊና ብቻ አይደለም፣ ልቡናም ያለው ነው የሚለው ሐተታ እውቀትን በመፈለግ ውስጥ የኅሊናንና የልቡናን ኅብረት ያስረግጣሉ። ዘርዓ ያዕቆብ የነገረ ህልውናን፣ የፈጣሪን ምንነት፣ የሰውን ባህርያት፣ የሰው ልጆችን ዘልማዳዊ አስተምህሮ ባጠቃላይ ሕገ እግዚአብሔርና ሕገ ሰብን የሚመረምረው በልቡናና በኅሊና ምስክርነት ነው። ምናልባት የዘርዓ ያዕቆብ ልቡና የስሜት ቋት ትሆን፣ ወይስ የምርምር ሰንሰለት ድር? የእውቀት ሁሉ ማጠንጠኛ ግን ምርምር ነው። ሳይመረምሩ ማመን ሰዋዊ እንዳልሆነ፣ ሰዎች የነገሩንን እንደወረደ መቀበል ከለባዊት ነፍስ ጋር የማይስማማ የፈጣሪን ቁጣ የሚያመጣ ነው። ስለ ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ባተትሁበት በቀደሙት እትሞች የዘርዓ ያዕቆብ ፍልስፍና ለዘመናችን በስሜት ለሚነዳ የማኅበራዊ ብዙኃን መገናኛ ተጠቃሚ ምን ዓይነት ምክረ ሐሳብ እንዳለው አሳይቻለሁ።

 ሦስተኛው የሥነ ምግባር ጥያቄ ነው። እውነት ምንድን ነው? የሚለው የነገረ ኅልውናና የሥነ እውቀት ጥያቄ ከተመለሰ በኋላ በፍጥረታት መካከል ስለሚኖረው የጋራ ሕይወት የሚያትት ሌላ ጥያቄ አለ። እሱም በጎው የቱ ነው፣ መጥፎውስ? የሚለው የሥነ ምግባር ጥያቄ ነው። ዘርዓ ያዕቆብ የበጎነት ምንጭ ለሕገ እግዚአብሔር ተገዥ መሆን እንደሆነ ያምናል። በርግጥ ስለ በጎና መጥፎ ነገሮች በሐተታው ውስጥ ሰፊ ቦታ አልሰጣቸውም። ከአጠቃላይ ፍልስፍናው እንደምንረዳው ግን ሰዎችን ወይም ሌሎች ነገሮችን እግዚአብሔር መጥፎ አድርጎ እንዳልፈጠራቸው ያትታል። የሰው ልጆች ነጻ ፈቃድ የተሰጣቸው በመሆናቸው ለምግባራቸው ተጠያቂዎች ከመሆን አያመልጡም። ይኸው ተጠያቂነት የሥነ ምግባር መሠረት እንደሆነ መረዳት እንችላለን። “ዳግመኛም እግዚአብሔር ሰውን የምግባሩ ባለቤት አድርጎ ፈጠረው። እርሱ እንደወደደው ይሆን ዘንድ በጎንም ቢወድ፣ ክፉንም ቢወድ፣ ሰው ክፉና ሐሰተኛ ይሆን ዘንድቢመርጥ ይቻለዋል። ለክፋቱ የሚገባ ፍርድን እስኪያገኝ ድረስ።”የሰው ልጅ በጎነት ከእውቀት ጋር የተያያዘ ነው። የሰዎች ምግባር ግላዊ ሕይወታቸው ላይ ብቻ የተመሠረተ አይደለም። ለሌሎች ሰዎች በሚያደርጉት፣ በማኅበረሰቡ ዘንድ የሚያመጣውን እንድምታም መሠረት ያደረገ ነው።

 ሌሎች ጉዳዮች:- ከተግባራዊነት አንጻር ስንመዝነው ከዘርዓ ያዕቆብ ረቂቅ ፍልስፍና ይልቅ የወልደ ሕይወት ተግባራዊ ፍልስፍና ስለ ግላዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች መሬት ድረስ ወርዶ ያብራራል። ነገር ግን የዘርዓ ያዕቆብ ትችትም ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ችላ ብሏል ማለት አይደለም። ለምሳሌ ከላይ እንዳየነው ስለ ጋብቻ ጉዳይ ሞግቷል። ጋብቻን ብቸኛው ተፈጥሯዊ የሰው ልጆች መንገድ አድርጎ በማስቀመጥ ምንኩስናን የተቸበት የሐተታው ክፍል ነው። ተፈጥሯዊ ባልሆነ መንገድ [ምናልባት ወንድ ከወንድ ወይም ሴት ከሴት] የሚደረግ ተራክቦን፣ ከአንድ በላይ የሆነ ጋብቻን፣ እንዲሁም ምንኩስናን ያወገዘው ከሕገ ተፈጥሮ ጋር ስለማይስማሙ ነው። ሴት ልጅ ከወለደች ወይም የወር አበባ ካየች በኋላ ለተወሰነ ጊዜ ለብቻዋ ትሁን የሚለውን የሙሴን ሕግ በተቸበት ብዕሩ አንድ ወንድ ከአንድ በላይ ሚስቶች ይኑሩት የሚለውን የመሐመድን ሕግ አልማረውም። ስለ ጾም የተቸበት ሌላው ክፍል ደግሞ እግዚአብሔው ወይም አላህ ይህን ብሉ፣ ይህን አትብሉ፣ በዚህ ሠዓት ብሉ፣ በዚህ ሠዓት ደግሞ አትብሉ የሚል ትዕዛዝ ሊያስተላልፍ አይችልም። ይልቁን ለጤና ተስማሚውን፣ ለቁመተ ሥጋ አስፈላጊውን ሁሉ በመጠን ብሉ የሚል ሙግት ይዞ ብቅ ብሏል።

 ከዚህ በተጨማሪ በዘልማድ ስለማመን፣ ከአባቶች ስለመጣ እምነት እና ሳይመረምሩ ስለመቀበል፣ ስለ ሃይማኖት ጉዳይ እርስ በርስ መጣላት፣ ከተመራማሪ ህሊና፣ ከለባዌው ሰውና ከእግዚአብሔር ሕግ እንዳልሆነ ይተቻል። በማህበር፣ በፍቅር በተራድኦ መኖርን የሚመክረው ፈላስፋው ስለ ፖለቲካ ጉዳዮች በግልጽ አልጻፈም ለማለትም አያስደፍርም። ባንድ በኩል በዘመኑ የነበረውን መሰደድና እልቂት የንጉሡ ተጠያቂነት እንዳለበት በግልጽ ሲተች በሌላ በኩል የፋሲልን ሕንጻ የሰሩትን ጠቢባን ንጉሡ ያለ አግባብ ማባረሩ መልካም ዲፕሎማሲ እንዳልሆነና ንጉሡ ለብልጽና የነበረውን የተሳሳተ አመለካከት ተችቷል። “ፋሲለደስ በመልካም ምክርና ጥበብ ይነግሥ ዘንድ ዠመረ። ነገር ግን በመልካም ነገር ጸንቶ አልኖረም። አመፀኛ ንጉሥ ሆነ እንጂ። በአመጽና ደምን በማፍሰስ ጸና። በጎ ነገር ላደረጉለት፣ ቤተ መንግሥትንና ያማሩ ቤቶችን ለሰሩለት፣ በጥበብ ነገር ሁሉም መንግሥቱን ላሳመሩለት ፈረንጆችንም ጠላቸው።” እያለ ሰዎችን ያለ ፍርድ ስለመግደሉ፣ ስለማሳደዱ፣ ሌላም ሌላም ነውሮቹን እየጠቀሰ ተችቷል።

 መውጫ

በርግጥም በገጽ ብዛቷ ትንሽ በቁም ነገሯ ሰፊ የሆነችውን የዘርዓ ያዕቆብን ሐተታ ነትንሽ ገጾች መተንተን ከባድ ነው። አንባቢ ሙሉ መጽሐፉን እንዲያነበውና በአገራችን የጥበብ፣ የምርምር፣ የፍልስፍና ገጾች ውስጥ የፈላስፋው ሐተታ ትልቅ ቦታ እንዳላት ለማሳየት ተሞክሯል።ለዘመናችን ተግባራዊና ጽንሰ ሐሳባዊ ርእሰ ጉዳዮችየሚኖረውን አስተዋጽኦ እንዲሁም በቀደምት የኢትዮጵያ ጥበብ ላይ ምርምር ለሚያደርጉ ጥቁምታ ለመስጠት ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ ከሐተታ ዘርዓ ያዕቆብ ጋር በአንድ ላይ መነበብ ስላለበት የወልደ ሕይወት ሐተታ በሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ። ሰላም ሁኑ!

“ሳይመረምሩ ማመን ሰዋዊ እንዳልሆነ፣ ሰዎች የነገሩንን እንደወረደ መቀበል ከለባዊት ነፍስ ጋር የማይስማማ የፈጣሪን ቁጣ የሚያመጣ ነው”

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top