አድባራተ ጥበብ

ኖሊውድ – የአፍሪካ ኩራት

ዛሬ በየፊልም ቤቱና በየቴሌቪዥን መስኮቶቻችን እየቀያየርን የምንኮመኩማቸው የተለያዩ ፊሊሞች አብዛኞቹ በምእራባዊያን በተለይም አሜሪካኖች የሚሰሯቸው ናቸው::አሜሪካ በፊልም ኢንደስትሪው ልቃ ሄዳለች:: የምናያቸው ምእራባዊያኑ ፊልሞች የፍቅር ታሪክ ያላቸው(ሮማንቲክ) አልያም ጦርነት ወይም ድብድብ የሚበዙባቸው( አክሽን) ካልሆነም የሚያስፈሩ ዓይነት ይዘት ያላቸው (ሆረር) ሊሆኑ ይችላሉ:: ብቻ በየትኛውም መመዘኛ አሜሪካዊያኑ ፊልም ሲሰሩ የጦርነት ከሆነ ሀያልነታቸውንና አሸናፊነታቸውን የቴክኖሎጂና የሳይንስ ፊልምም ከሆነ የቴክኖሎጂው ምጥቀታቸውን ያሳዩናል::

 በዚህ ሁሉ አለምን ያጥለቀለቁት እነዚህ የአሜሪካ ፊልሞች መነሻቸውና መድረሻቸው “ሆሊዉድ” ተብሎ የሚጠራው የፊልም መንደር ነው:: እናም “ሆሊውድ” በአሜሪካ ሎስ አንጀለስ ካሊፎርኒያ ግዛት ውስጥ የሚገኝ ወረዳ ነው:: ሆሊውድ በአለማችን አንቱ የተሰኙና በየግድግዳችንና በየመኪኖቻችን መስታወት ላይ የምንለጥፋቸው የፊልም አክተሮች አብዛኞቹ አሜሪካዊያን የሆሊውድ ብቃዮች ናቸው:: ከእነዚህ የናጠጡ የሆሊውድ የፊልም አክተሮች ውስጥ በዋናነት ጄሪ ሰኒፊልድ ሻሩክ ካሃን፣ ቶም ክሩዝ፣ ቶም ሀንክስ፣ ጆኒ ዴፕ፣ ሜል ጊብሰን፣ ቲለር ፔሪ፣ ጃክ ኒኮልሰን ይገኙበታል:: ከሆሊውድ በመቀጠል በአለማችን ሁለተኛው የፊልም ኢንደስትሪ መገኛውን ሙምባይ ያደረገው የህንዱ “ቦሊውድ” ነው:: ዛሬ ላይ የአፍሪካ ኩራት በመሆን ብቅ ያለው የጥቁር ፈርጦቹ የፊልም አንደስትሪ ደግሞ “ኖሊውድ” ነው:: “ኖሊውድ” የሚገኘው በሌጎስ ሲሆን በአለማችን ሶስተኛው የፊልም ኢንደስትሪ ነው::

 በእርግጥ “ኖሊውድ” ትርጉሙ ምን ማለት እንደሆነ በእርግጠንነት ይሄ ነው ብሎ መናገር ባይቻልም ስያሜው “ኖ” ናይጄሪያን “ውድ” ደግሞ “ሆሊውድ“ ና “ቦሊውድ” ከሚለው አባባል የተወሰደ አፍሪካዊ የፊልም ኢንደስትሪ መሆኑን ለማመላከት የተሰየመ ይመስላል::

 ዛሬ ላይ በምእራቡ አለም ፊልም የአለማችን ትልቁ የገንዘብ ማስገኛ የጥበብ ዘርፍ እንደመሆኑ ሁሉ በናይጄሪያም የተለያዩ ጉዳዮችና መልእክቶችን ለማስተላለፍ ያገለግላል:: እንደሚታወቀው ናይጄሪያ የተለያዩ ጎሳዎች የሚኖሩባት ሀገር እንደመሆኗ የራስን ጎሳ ለማወደስና የበላይነቱን ለመስበክ ፊልም እንደ ዋና መሳሪያነት ያገለግላል:: ሀይማኖትን ለማስፋፋት ፊልም ከፍተኛ ሚና አለው::

 በአብዛኛው በኖሊውድ ፊልም ከእንግሊዝኛው ባሻገር በዮሩባ ቋንቋም ይሰራል:: እነዚህ የዮሩባ ልጆች ድራማ በመስራት ልምድ ያካበቱ ሲሆኑ¿ ለኖሊውድ ፊልም ኢንደስትሪ መመስረትም የአንበሳውን ድርሻይ ይይዛሉ:: እናም የኖሊውድ ተዋናዮች በአብዛኛው ከምእራብ ናይጄርያ የበቀሉ ዮሩባዎች ናቸው:: በዮሩባዎች ከተሰሩ ፊልሞች “የኮነጂ መኸር” (kongi’s harvest)፣ “የፀሀዩ ውስጥ ጥጃ እንቁራሪት” (Bull Frog in The Sun )፣ “ቢሲ የወንዙ ሴት ልጅ” ( Bisi, Daughter of The River)፣ “ጃይስሚ” (Jaiyesimi)፣ “ የጩኸ ት ነፃነት” (Cry Freedom) ዋንኞቹ ናቸው:: እነዚህን ፊልሞች በመተወን ደግሞ ኦላ ባሎጉን ፣ ዱሮ ላዲፖ፣ አደይሚ አፎላያን(አዴ ላቭ) ግንባር ቀደሞቹ ናቸው::

 በሌላ በኩል በሰሜኑ የናይጄሪያ በሀውሳ ቋንቋም ፊልሞች ይሰራሉ:: ይህ የፊልም ማእከል ደግሞ “ካኒዉድ” በመባል ይታወቃል:: ይህም አንዱ የኖሊዉድ የፊልም ቅርንጫፍ ነው:: የዚህ ፊልም ኢንደስትሪ መቀመጫ የካኖ መንደር ነው:: በዚህ ፊልም ኢንደስትሪ ዋና ኮከቦች ዳልሃቱ ባዋ ና ካሲሙ ዬሮ ናቸው:: እነዚህ የፊልም አክተሮች በሰሜኑ የናይጄሪያ ክፍል በጣም ተወዳጅና ተደናቂ ናቸው::

ካኒውድ በተለይም በሰሜን ናይጄሪያ ዝናው የገነነ ሲሆን በዚህ የፊልም ማእከል በአብዛኛው የሃውሳና የህንድ ቅይጥ ባህላዊ ይዘት ያለው የፊልም ጥበቦች ተሰርተው ለእይታ ይቀርባሉ:: ከነዚህ ፊልሞች ውስጥ “ቱርሚን ዳኒያ” (Turmin Danya) በአማርኛ “አዘጋጁ” ማለት ነው¿ ይህ ፊልም በካኒዉድ የመጀመሪያው የተዋጣለትና ዳጎስ ያለ ገንዘብ ያስገኘ ፊልም ነው:: በመቀጠልም “ጊምቢያ ፋቲማ” (Gimbiya Fatima ) እና “ኪያርዳ ዳ ኒ” ( Kiyarda Da Ni) የተሰኙ ፊልሞች ገበያ ላይ ውለው አድናቆትን አትርፈዋል::

 በዚህ ሁሉ እንግዲህ እአአ በ1990ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ የናይጄሪያ ፊልም ኢንደስትሪ ኖሊውድ ብቅ ያለበትና የናጄሪያ ፊልም በርካታ  ታዳሚዎችን በማፍራት የኖሊውድ እርሾ የተጠነሰሰበት ነው:: የናይጄሪያው ኖሊውድ በአለም ላይ ፊልም በብዛት በማምረት ከቦሊውድ ቀጥሎ ሁለተኛው ነው:: ኖሊውድ በሚሰራቸው ፊልሞች ብዛት የታወቀ ቢሆንም በርካታ ችግሮችና እጥረቶች እንዳሉብት ይወሳል::

 በልምድ ማነስና በበጀት እጥረት ሳቢያ ናይጄሪያውያን የሚሰሯቸው ፊልሞች እጅጉን ዘመናዊነት የሚጎላቸውና ቤት ወይም ሰፈር ሰራሽ መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ:: ይህ ችግር ደግሞ በሚሰሩት ፊልሞች ጥራት ላይ የራሱን አሉታዊ ተፅእኖ አሳድሯል:: ኖሊውድ እጥረቶች ያሉበትን ያህል ደግሞ የአፍሪካ የፊልም ኢንደስትሪ ኩራት ከመሆን ባሻገር በናይጄሪያ የስራ እድልን ከመፍጠር አኳያ ከግብርናው ቀጥሎ አንቱ ተሰኝቷል:: ኖሊዉድ ከዚህም ሌላ ናይጄሪያውያን ባህላቸውን፣ ማንነታቸውን፣ የጥበብ አሻራቸውን ለአለም እንዲያስተዋውቁ ረድቷቸዋል:: ፊልም መስራት እንደሚችሉም አሳይተውበታል:: በኖሊውድ በአብዛኛው አስቂኝና አዝናኝ (ኮሜዲ)፣ የድራማ፣ የሚያስፈሩ( ሆረር)፣ ሙዚቃዊ፣ አኒሜሽንና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው ፊልሞች በብዛት ይሰራሉ::

በኖሊውድ በቀን 6 ፊልሞች በወር ደግሞ ወደ 200 የሚሆኑ ፊልሞች ለእይታ ይበቃሉ:: ኖሊውድ በዚህ ሁኔታ በአለማችን ተወዳዳሪ ከምንላቸው ሆሊውድና ቦሊዉድ በመቀጠል ሶስተኝነቱን አስጠብቆ ይገኛል:: እናም በአፍሪካ ታላቁና ፈር ቀዳጁ የፊልም ኢንደስትሪ ተሰኝቷል :: በጣም አሪፍ ከሚባሉት የኖሊውድ ፊልሞች ውስጥ ጄብ ኢዚሮ ያዘጋጀው አኔ ኔጄማንዜ በዋናነት የተወነችበት “ዶሚቲላ” የተሰኘው ፊልም ተጠቃሽ ነው :: “የደም ገንዘብ” (blood money)፣ “ብቀላ” (scores to settl፣  “ኢጎዶ” (igodo)፣  “አኪ ና ኡኩዋ” (aki na ukwa)፣ “ኦሱኦፊአ በ ለንደን” (osuofia in London)፣  “ውቧና አጭበርባሪዋ” ኔካ (nneka the pretty serpent)፣ “በጣም ተፈላጊ” (most wanted)፣ “የባርነት ህይወት” (living in bondage) በጣም የታወቁና ዛሬም ድረስ ምርጥና ተወዳጅ የኖሊውድ ፊልሞች ናቸው:: በእነዚህ ፊልሞች የአዘጋጆቹንና የተዋናዮቹን ብቃትና ችሎታ የሚያሳዩ ናቸው::

እነዚህ የፊልም ስራዎች በአነስተኛ ገንዘብና አገር ባፈራው የቴክኖሎጂ ውጤት በመታገዝ የተሰሩ መሆናቸው የበለጠ እንድናደንቃቸው ያስገድዱናል:: ፊልሞቹ በአብዛኛው ከሁሉም የሰው ልጆች የህይወት ገጠመኝ ጋር ቁርኝት ያላቸውና የአብዛኛውን ሰው የህይወት ውጣ ውረድ የሚያሳዩ በመሆናቸው ይበልጥ ተወዳጅና አይረሴ ያደርጋቸዋል:: በተለይም ሸምገል ያሉትን ወዳሳለፉት የልጅነት ህይወት በማንደርደር በትዝታ ማእበል ውስጥ የመክተት ብርታት ያላቸው ሲሆን ወጣቶችን ደግሞ “ለካ ይሄም አለ እንዴ?” በማስባል በደስታ ህይወት የሚዘፍቁ አይነት ናቸው:: ፊልሞቹ ናይጄሪያውያንን ብቻም ሳይሆን የሌሎች ሀገራትን ዜጎች በተለይም አፍሪካውያንን የሚያዝናኑና ቁም ነገር የሚያስጨብጡ ናቸው:: ፊልሞቹ የናይጄሪያን በተለይም የሀውሳን ባህልና ቋንቋ የሚያስተምሩ እንደሆኑም ይነገርላቸዋል::

 እነዚህ የኖሊውድ ፊልሞች ዘመኑ ባፈራቸው የረቀቁ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ያልታገዙና ከፍተኛ የጥራት ጉድለት ቢታይባቸውም ገቢ በማስገኘት ረገድ ሚናቸው የጎላ ነው::እናም ናይጄሪያ ከገቢዋ 11 በመቶ የሚሆነውን

“በአገራችን ያሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለዘርፉ ትኩረት ያልሰጡና መሆናቸውና በቂ የማሰልጠኛ ተቋማት አለመኖራቸው ችግሩን አባብሶታል”

ከፊልም ኢንደስትሪ ታገኛለች:: ኢንዱስትሪው በአሁኑ ሰአት መሻሻል እየሳየና እያደገ ነውም ተብሏል::

 ናይጄሪያ ባለፈው ወር ታዋቂው ፊልም አዘጋጅ ና ዳይሬክተሯን ፓወል ኢሜማን አጥታለች:: በኖሊውድ የታወቀው ፓወል ኢሜማ እአአ መጋቢት 2019 በ52 አመቱ ከዚህ አለም በሞት ተለይቷል::

ስለ ኖሊውድ ይህን ያህል ካልን ወደ አገራችን የፊልም ኢንደስትሪ ስንመጣ በአገራችን የፊልም ስራ ከተጀመረ 117 ዓመታትን እንዳስቆጠረ ይነገራል:: እንደሚታወቀው ሃገራችን ባለብዙ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦችእናት ስትሆን አለምን ያስደመሙና ተዝቀው የማያልቁ ባህል፣ ወግ፣ ታሪክና እሴት ባለቤት ናት:: ይህ ሁሉ ሀብቷ ለፊልም ስራ መዋል የሚችል ነው:: ነገር ግን ይሄ ሁሉ በእጃችን እያለ የናይጄሪያን ያህል እንኳን ልንሰራ አልቻልንም:: በእርግጥ አርኪ ናቸው ባይባሉም የሚሞካከሩ ፊልሞች አሉ:: እነርሱም ቢሆን በርካታ ችግሮች ያሉባቸው መሆኑን ዘርፉን የሚያውቁ ይናገራሉ:: በዋናነት ለኢንደስትሪው ድክመት የባለሙያ እጥረት፣ የገንዘብ ችግርና የገበያ ማጣት እንደችግር ይነሳሉ::

 በአገራችን ያሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለዘርፉ ትኩረት ያልሰጡና መሆናቸውና በቂ የማሰልጠኛ ተቋማት አለመኖራቸው ችግሩን አባብሶታል:: ፊልም በአገራችን አዋጪና አትራፊ ኢንቨስትመንት እንዳልሆነ የሚናገሩም አሉ:: በተለይም ከኮፒራይት ጋር ተያይዞ የሚሰሩ የጥበብ ውጤቶች ከአትራፊነታቸውና አዋጪነታቸው ይልቅ አክሳሪነታቸው ማየሉ ዘርፉ እንዲቀጭጭ አድርጎታል:: ለማንኛው ለኢንደስትሪው ትንሳኤ መንግስት፣ ባለሃብቱና የትምህርት ተቋማት እንዲሁም ሙያተኛው እጅ ለእጅ ተያይዘው ሊሰሩ ይገባል እንላለን::  

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top