ሌሎች አምዶች

ተውሳክ እና ታሪክ (በቁንጽል)

መግቢያ

የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማ ሳይንሳዊ አሰተሳሰብን ማኸዘብ ነው:: የሳይንስ ዕውቀት ሠፊና ዘርፈ ብዙ ጥናት ላይ ተመርኮዞ ከሚገኝ ውጤት የሚቃረም ሲሆን፣ በዚህ ፅሁፍ ውስጥ ለማስተዋወቅ የምሞክረው በታሪክ ሂደት ላይ “ተውሳክ” የነበረውን ተፅዕኖና ሚና በተመለከተ ነው::

 ለዚህ ጽሑፍ ማብራሪያ ሆኖ እንዲያገለግል፣ በመጀመሪያ ስለ ሳይንሳዊ ሙክረት (experiment) ብሎም ግኝተ በጥቂቱ ላውሳ:: ተክለሐዋርያት ተክለማርያም (ፊታውራሪ)«ትንሽ መፈተሸ ትምህርት» ብለው በ1922 ዓ/ም በደረሷት መጽሐፋቸው፣ ስለ ሳይንሳዊ የዕውቀት ማዳበሪያ ስልት ሲያወሱ የሚከተለውን አስፍረው ነበር፣ «በዙሪያችን ከቦን ሲኖር የምናየውን ፍጥረተ ዓለም ሁሉ እንደሚለዋወጥ እንደሚፈራረቅ እንደሚከናወንም እያስተዋልን ያንኑ ልብ አድርገን ጠባዩን ሁሉ መመርመር፣ የመረመርነውን መፈልሰፍ፣ የፈለሰፍነውን እንደገና በማንጠር በማሰተያየት በማመሳሰል በማመለካከት በማመዛዘን አስመስክሮ ማስረገጥ ኋላም ያንኑ እየተከተሉ በዘዴው መጠቀም በእንደዚህ ያለ አደራረግ ነው እውቀት የሚገኘው:: ከመመልከት እና ከመመርመር የተነሳ እንደዚህ ያለ የሚያስደንቅ የተፈጥሮ ምስጢረ ጥበብ ይገለጣል» ብለው ነበር::

 እንደብዙ ምሁራን እይታ የሳይንስ አስተሳሰብ በሦስት ወጋግራዎች ላይ ነው የተደገፈ (የተመሰረተ) ነው፤ እነሱም ተሞክሮ/ ማስተዋል (Observation/ Empiricism) ፣ ራሽናሊዝም/ሎጂካዊ አመክንዮ (Logical Reasoning) እና ነባር ዕውቀትን ሁሉ እንደወረደ አለመቀበል (መጠራጠር/ Skepticism) ናቸው (ዝርዝሩን «የሕያው ፈለግ» ውስጥ ያገኛሉ)::

ብዙ ጊዜ በጦርነት ተፋላሚዎች መካከል የጦርነቱን ውጤት የሚወስነው የጦር ኃይል ሚዛን፣ ብሎም የጦር ስልት እንደሆነ በታሪክ ይወሳል:: በጦርነት ወቅት የሚከሰተው ተውሳክ/ ወረርሽኝ የጦርነት ውጤት ላይ ያለው ሚና በታሪክ ዘጋቢዎች ብዙ ትኩረት ሲሰጠው አይሥተዋልም:: የታሪክ መዛግብት በጦርነት መንስዔ የሚጠፋው ሕይወት በጦር መሳሪያ ብቻ አለመሆኑን አስፍረዋል፣ እንዲያውም ተደጋግሞ እንደተከሰተው በጦር መሳሪያ ጉዳት ደርሶባቸው፤ሕይወታቸውን ከሚያጡ ተፋላሚዎች ቁጥር፣ በጦርነት ወቅት ወይም ከጦርነት ጋር ተያይዞ በበሽታ ተጠቅተው የሚሞቱት ግለሰቦች ቁጥር በጣም ይልቃል::

በአዉሮፓውያን መካከል ግዛትን ለማስፋፋት የጦፈ ፉክክር በነበረበት 19ኛው መቶ ዓመት፣ ግዛት ማስፋፋትን የወሰነው የባህር ኃይል ጥንካሬ (የመርከብ ቁጥር, ወዘተ.) ብቻ ሳይሆን፣ የመርከበኞች ጤና እንክብካቤ የጎላ ሚና እንደነበረው ተመዝግቧል::

 በዚህ ጽሑፍ ሁለት የተውሳክ መንስዔዎች ተወስተው፣ የችግሮችን መፍትሄ ማግኘት በግዛት መስፋፋት ታሪክ ላይ የቱን ያህል ተፅእኖ እንዳደረገ ይብራራል:: ሁለቱ የተውሳክ መንስዔዎች አመጣጣቸው በጣም የተለያየ ነው:: አንዱ «ስከርቪ» (scurvy) በምግ አለመመጣጠን መንስዔ ሲከሰት፣ ሁለተኛው ተስቦ «አቸንፋሪ» (ፓቶጂን/pathogenic) ሲሆን፣ የሚከሰትም ሰው በባክቴሪያ ሲወረር ነው:: በገላ ውስጥ የሚሰራጨውም በደም አማካይነት ነው:: ተስቦ (Epidemic louse-borne typhus)፣ «ሪኬትስያ ፕሮዋዛኪ» (Rickettsia prowazekii) ተብላ በምትታውቅ ባክቴሪያ ወረራ ምክንያት የሚያንሰራራ ወረርሽን ነው::

 እነኝህ ሁለት የተውሳክ መንስዔዎች፣ በጦርነት ጊዜ ለየትኛውም የተፋላሚ ወገን አድልኦ ሳያደርጉ፣ ማንንም ሳያግዙ፣ ሁለቱንም ተፋላሚ ወገኖች ያለርህራሄ ለማጥቃት ይችላሉ:: ሆኖም የችግሮችን መንስዔ የመከላከል መሰናዶ/ አቅም ያለው፣ ክፍልም ያው/ ከፉክክሩ በአሸናፊነት ይዘልቃል:: እነኝህን መሰል ተግዳሮቶች ጥሶ ለማለፍ የሳይንስ ሚና ምን ነበር? የሚለውን በማውሳት እና በመተንተን ነው ሳይንሳዊ አስተሳሰብን ለማኸዘብ የምሞክር::

 የተስቦ ወረርሸኝ (Epidemic louse-borne typhus እና ታሪክ በመሠረቱ ሁለት ዓይነት የተስቦ በሽታዎች አሉ፣ አንደኛው የአካባቢ ተስቦ (endemic typhus) በመባል የሚታወቀው፣ ለሞት የማይዳርገው ተስቦ ሲሆን፣ ያም በ«ሪኬትስያ ታይፊ» (Rickettsia typhi) በመወረር መንስዔ የሚከሰት ነው:: በሽታው ከበሽተኛ ወደ ጤነኛ ሰው የሚተላፈው በቁንጫ አቀባባይነት ነው:: ሁለተኛው እና በብዛት የሰውን ልጅ ለሕልፈት የሚዳርገው ከላይ ያወሳነው ተስቦ (Epidemic louse-borne typhus)፣ «ሪኬትስያ ፕሮዋዛኪ» (Rickettsia prowazekii) በመባል የሚታወቀው ወረርሽኝ (epidemic typhus) ነው:: ይህም ከአንድ ሰው ወደ ሌላ ሰው የሚተላለፍ በቅማል አስተናጋጅነት ነው:: በዚህ ጸሑፍ የሚወሳው ይህ ሁለተኛው ወረርሽኝ (ተውሳክ) ነው:: ታሪክ እና ወረርሽኝ የተስቦ ወረርሽኝ (epidemic typhus) በታሪክ የጎላ ሚና አለው:: የዓለም ሕዝቦች በወረርሽኝ በተደጋጋሚ ተጠቅተዋል:: በ«መካከለኛው ዘመን» (middle Ages) የተስቦ ወረርሽኝ ከ13 ሚሊዮን በላይ ለሆኑ ግለሰቦች ሕይወት መቀሰፍ ምክንያት ሆኖ ነበር:: በቅርብ ጊዜም፣ በ20ኛው መቶ ዓመት፣ በሌላ ዓይነት ወረርሽኝ.(በ«ኢንፍልዌንዛ»/ influenza) ከ20 ሚሊዮን በላይ ግለሰቦች ለሞት ተዳርገዋል:: በአገራችን ከፍተኛ ጉዳት አድርሶ ያለፈው ወረርሽኝ «የሕዳር በሽታ» በመባል ይታወቃል::

ተስቦ ወረርሽኝ ለመጀመሪያ ጊዜ በታሪክ የተመዘገበው በስፓኛ «የግራናዳ ጦርነት» (war of Granada) በተካሄደበት ዘመን (1482-1492) ነበር:: በዚህም ጦርነት ስፓኛ በጦር መሳሪያ መንስዔ ሦስት ሺ ገደማ ጦረኞች ሲሞቱባት፣ በተስቦ ወረርሽን ለሕልፈት የተዳረገው ተዋጊ ግን ከ17 ሺ በላይ ጦረኛ ነበር:: ይህም በጦርነት ካለቀው በብዙ የላቀ እንደሆነ አመልካች ነው::

 ተስቦ በብሪታንያ በጥንት እንግሊዝኛ «ጋል» ተውሳክ (Gaol Fever) በመባል ይታወቅ ነበር:: በዘመናችን እንግሊዝኛ «ጄይል» ተውሳክ (Jail Fever) ማለት ነው:: ይህን ዓይነት ስያሜ የተሰጠው ተውሳኩ በወህኒ ቤቶች አካባቢ የገነነ ስለነበረ ነው:: በዚህም የተነሳ በወህኒ ቤቶች ውስጥ የታሰረ ግለሰብ እስከሚቀጥለው የፍርድ ቤት ቀጠሮ ድረስ እስረኛው የሞት ፍርድ እንደተጣለበት ነበር የሚገመት::

እኔም ባደግኩበት አካባቢ፣ በፈለገ ብርሃን (ጎጃም) ወህኒ ቤት ስለ ተስቦ ወረርሽኝ ትዝታ አለኝ:: በዓመት ቢያንስ አንድ ጊዜ የተስቦ በሽታ ወህኒ ቤት እየገባ ብዙ እስረኞች ይጨርስ ነበር (1944-1947 ዓም):: አንድ ጊዜ ተስቦ ከገባ ከአምስት እስከ አሥር እስረኞች ይሞቱ ነበር:: ወህኒ ቤት ይፈራ የነበረው ነፃነት በማጣት፣ በመታጐር ሳይሆን፤ በተስቦ በሽታ የተነሳ የሚመጣ ሞት ነበር:: በሽታ ወህኒ ቤት ገባ ሲባል ወገን፣ ዘመድ፣ የታሰረበት ቤተሰብ ሁሉ እስረኛው የሞት ቅጣት የተፈረደበትን ያህል ነበር የሚያዝን፤ የሚጨነቅ (ዝርዝሩን ከጉሬዛም ማርያም እሰከ አዲስ አበባ ይመልከቱ)::

በ19ኛው መቶ ዓመት አውሮፓ ውስጥ በተካሄዱ ጦርነቶች ከሞቱት ተዋጊዎች፣ ዘጠና በመቶ የሚሆኑት በጦር መሳሪያ ሳይሆን በተስቦ ወረርሽን ነው ያለቁ:: «ናፖሊዮን ቦኖፓርቲ» (Napoleon Bonaparte) ወደ ሩስያ በዘመተ ጊዜ (1812) በጦርነት የወደቁት ከ100,000 ያነሱ ወታደሮች ሲሆኑ፣ በአንፃሩ በተስቦ መንስዔ ከ300,000 በላይ ግለሰቦች ተቀጥፈዋል:: በ20ኛው መቶ ዓመት በተቀሰቀሰው የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት (World War I) በመባል የሚታወቀው፣ በጦርነቱ የምሥራቅ ግንባር ላይ ተስቦ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል:: እንዲሁም በዚያው ዘመን በቀድሞው ዩጎዝላቭያ (Yugoslavia) ብቻ ከ150,000 በላይ ሰዎች በተስቦ ወረርሽኝ መንስዔ ለሕልፈት ተዳርገዋል::

በሶቭየት ዩኒዮን (Soviet Union) በ1922 ገደማ የተስቦ ወረርሽኝ በከፍተኛ ደረጃ ተንሰራፍቶ፣ ከ20-25 ሚሊዮን የሚሆኑ ግለሰቦች በበሽታው ተለክፈው ነበር:: ከነዚህም ወደ አራት ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑት ሕይወታቸውን ተነጥቀዋል:: እንዲሁም በሩስያ እርስ በእርስ ጦርነት (በቀይ እና በነጭ/ Red Army and White Army) ግጭት፣ ተስቦ ወገን ሳይለይ ከ3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ፈጅቷል::

በሽታው የሚያጠቃቸው ግለሰቦች በመጀመሪያ በተለያዩ ምክንያቶች ፅዳት የጎደላቸው ናቸው:: ፅዳት መጓደል ከተፋፍጎ መኖር (በማረፊያ ቤቶች፣ በጦር ግንባር ሰፈር፣ በረዥም የባህር ጉዞ፣ ወዘተ) ጋር የተቆራኘ ነው:: በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ (ጽዳት በጎደለበት) ቅማል (የራስ ፀጉር/ የገላ) በብዛት ለመራባት ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል::

 ስለሆነም የቅማል መራባት በሽታ ከአንድ ሰው ወደ ሌላ ሰው እንዲተላለፍ ጥሩ አጋጣሚዎችን ይፈጥራል::

 ተስቦ እና ሳይንሳዊ ግንዛቤ

 የተስቦ ወረርሽኝ መንስዔ ምን እንደነበረ ከጠረጠሩት አንዱ «ጀምስ ሊንድ» (James Lind / 1716-1794) የብሪታንያ የጦር መርከብ ሐኪም የነበረ ግለሰብ ነበር:: በ«ጀምስ ሊንድ» ሃላፊነት ይተዳደር የነበረ የጦር መርከብ ሆስፒታል፣ የአካባቢው ፅዳት በጥሩ መልክ በሚስተናገድባቸው ክፍሎች (ታካሚዎችም ሆኑ ልብሶቻቸው በሚታጠቡበት/ በፅዳት በሚያዙበት) የሚታከሙ ህሙማን፣ የተስቦ ወረርሽኝ አያጠቃቸውም ነበር:: በተቃራኒው፣ አካባቢው ፅዱ ባልሆነ፣ በቆሻሻ በተበከለ ክፍሎች የተኙ ታካሚዎች (ገላቸውም ሆነ ልብሳቸው የማይታጠብ/ የማይፀዳ) ግን በተስቦ ወረርሽኝ ይጠቁ ነበር::

ስለሆነም «ጀምስ ሊንድ» ፅዳት ከበሽታ እንደሚታደግ፣ በተቃራኒው ፅዳት የጎደለበት አካባቢ ለበሽታ እንደሚዳርግ ጠረጠረ:: ስለሆነም የመርከበኞች ሁሉ ጽዳት እንዲጠበቅ (ገላ የልብስ)፣ ፀጉር እንዲላጭ ብሎም በፅዳት እንዲያዝ ቋሚ መመሪያ አወጣ:: የዚህም ውጤት ወረርሽኝ መቀነስ፣ አንዳንዴም ጨርሶ አለመከሰት ሆነ:: በዚህ ውጤት የብሪታኒያ መርከበኞች በተስቦ መጠቃት አከተመ:: የዚያ ዘመን ተፎካካሪዎቻቸው መርከበኞች ግን በተደጋጋሚ በተስቦ ወረርሽኝ ይጠቁ ነበር:: ስለሆነም የብሪታንያ መርከበኞች፣ ተፎካካሪዎቻቸው በነበሩ የፈረንሳይ መርከበኞች የበላይነትን ተቀዳጁ::

 የተስቦ ተውሳክ ከአንድ ሰው ወደ ሌላ ሰው እንዴት እንደሚተላለፍ የተረጋገጠ ከዘመናት በኋላ በ«ቻርልስ ሄንሪ ኒኮል» (Charles Henry Nicolle 1866-1936) ነበር::«ቻርልስ ሄንሪ ኒኮል» የተስቦ ወረርሽኝ ከአንድ ሰው ወደ ሌላ ሰው የሚተላለፈው በቅማል አስተናጋጅነት መሆኑን በሳይንሳዊ ምርምር አረጋገጠ:: የምርምሩ ሂደት፣ «ሙክረት» (experiment) እንደሚከተለው ነበር::

በተስቦ በሽታ ገላ ላይ ስትመገብ የነበረች ቅማል በአንድ ቺምፓንዚ (Chimpanzee) ገላ ላይ እንድትመገብ በማድረግ፣ ቅማል መጋቢዋን «ችምፓንዚ» ለተስቦ በሽታ ጥቃት አጋለጣት:: ቅማሏ በችምፓንዚ ገላ መመገብ በጀመረች በ10 ቀናት ውስጥ፤ ችምፓንዚዋ በተስቦ በሽታ የመጠቃት ምልክቶች አሳየች፤ አቶኮሳት፣ ታመመች፣ ችምፓንዚዋ የተስቦ በሽታ ሰለባ ሆነች::

 አንድ ቅማል በሕይወት ዘመኗ (ያም 35 ቀናት ገደማ)፣ 200 ያህል እንቁላሎችን ትጥላለች፣ የተጣሉትም እንቁላሎች በጥቂት ቀናት ውስጥ ወደ ቅማልነት ይቀየራሉ:: ስለሆነም፣ በአንድ ቅማል እድሜ ውስጥ ከሺ በላይ ልጆች፣ የልጅ ልጆች ወዘተ

ማፍራት ይቻላል:: አንድ ቅማል ሺዎችን ታፈራለች:: ቅማልበብዛት የምትራባ በቀላሉ ለዕይታ በማትጋለጥበት ሁኔታ ነው:: ለምሳሌ፣ ልብሶች ስፌት/ጠርዞች አካባቢ፣ በራስ ፀጉር ቆሻሻ ውስጥ፣ ወዘተ.. አንድ የ|| በዕውቀቱ ሥዩም || ግጥም ይህንን ሁኔታ በግርድፉ ታብራራለች::

… በፍራሻችን ሥር፤ ቃሬዛ ተጣብቆ በልብሳችን ገበር ፤ ከፈን ተደብቆ የእድሩ ጥሩንባ ፤ ከሙዚቃው ልቆ በዘንድሮ ጣቶች፤ ከርሞ ላይነካ “ደና ሰንብች” ማለት፤ ዘበት ኖሯል ለካ” ቅማል ምግብ የምታገኝ ደም በመምጠጥ ነው:: የወረርሽኝ ተስቦ መንስዔ የሆነው ባክቴሪያ፣ በበሽታው ከተለከፈ ግለሰብ ከደም ጋር ነው ቅማል ሆድእቃዋ የምታስገባ:: የተውሳኩም መንስዔ፣ ባክቴሪያው፣ ቅማል ሆድ እቃ ውስጥ ይራባል፣ ከዚያም ከቅማል ኩስ ጋር ወደ ውጭ ይከላል::ቅማል ደም በምትምግበት ጊዜ ኩሷን የመጣል ባህርይ አላት:: እንዲሁም ቅማል በምትመገብበት የገላ አካባቢ ያሳክካል፣ ማከክ ደግሞ ጥቃቅን ቁስሎች (የገላ ሽፋን/ቆዳ በመክላት) ይፈጠራሉ:: በነኝህ የቆዳ ቀዳዳዎች (በተጠቃው ቆዳ) ነው ከኩስ ጋር የወጣው ባክቴሪያ ወደ ሰው ገላ የሚገባ::

 ባክቴሪያ ወደ ሰው ገላ በገባ 5-6 ቀናት በኋላ፣ በበሽታው የተለከፈው ግለሰብ ገላ ላይ ጥቋቁር፣ ብጉር መሰል ነጠብጣቦች መታየት ይጀምራሉ:: ባክቴሪያው በበሽታው በተለከፈው ደም ውስጥ ይራባል:: በአጠቃላይ የበሽተኛው ደም በባክቴሪያ ይበረዛል:: በሽተኞች ሕክምና ካላገኙ በበሽታው ከተለከፉት አርባ በመቶው (40 %) ለሕልፈት ይዳረጋሉ:: በአጭሩ በወረርሽኙ ከተለከፈ የሰው ገላ ትመገብ የነበረች ቅማል፣ ሌላ ሰው ገላ ላይ ስትመገብ ነው፣ የተውሳኩን መንስዔ ባክቴሪያ ልታስተላልፍ የምትችል:: ተፋፍጎ መኖር ለዚህ ዓይነት የበሽታ መተላለፍ በጣም አመች ሁኔታን ይፈጥራል::

 ኒኮል በተስቦ በሽታ የተለከፉ ቅማሎችን በመደቆስ ክትባት ለማግኘት እንደሚቻል ደርሶበት ነበር:: ነገር ግን ተግባር ላይ የሚውል የክትባት መሰናዶ ለማዘጋጀት አልበቃም ነበር:: ለተስቦ ወረርሽኝ ወሳኝ በክትባት መልክ መፍትሄ የተገኘ ከአንድ ትውልድ በኋላ «በሩዶልፍ ቬጅል» (Rudolf Weigl) ነበር::

ክትባት እንዴት ነው የሚዘጋጅ?

 በመሠረቱ ክትባት የሕያው ከበሽታ የመከላከል ተግባር ነው:: ከበሽታ መከላከል የሚቻለውም፣ የበሽታ መንስዔ የሆኑ ወራሪ አካላትን የሚያጠቁ፣ በጥቅል «አንቲቦዲ» (antibody) በመባል የሚታወቁ፣ ግዙፍ ከፕሮቲን የተዋቀሩ አካላት ናቸው:: ይህ የመከላከል አቅም የተመሠረተው በነባር የአካል ተግባር ነው:: አንድ ሕያው አካል፣ የራሱ ገላ አባል/ አካል ያልሆነን ወራሪ፣ በራሱ አካል ከተደራጁ አካላት የመለየት (መሆን አለመሆንን) ክህሎት አለው:: ወራሪዎችን ከነባሮች (ከባለቤቶች) ይለያል::

 የወረርሽኝ በሽታ መንስዔ የሆኑ ሕዋሳት ለተወራሪው ገላ መጤዎች ናቸው:: ወራሪዎች «አንቲጂን» (antigen) በመባል ሲታወቁ፣ «አንቲቦዲዎች» የሚያጠቁ እነኝህ ወራሪዎችን ነው:: ጥቃቱ «አንቲጂኖችን» በማውደም ወይም ቆልፎ በማሰር፣ እንዳይሰራጩ፣ ብሎም ከተግባር ውጭ ማድረግ መቻል ነው::

 ለዚህ የመከላከል አቅም ግንባታ ሁለት መንገዶች አሉ:: አንዱ ሕያው አካል ራሱ (አካሉ) መከላከያውን ሲያዘጋጅ ነው፣ ይህም «አክቲቭ ኢሙኒቲ» (active immunity) በመባል ይታወቃል:: ሁለተኛው ደግሞ በሌላ ሕያው አካል የተዘጋጀን የመከላከያ መሰናዶ ወስዶ (በመድፊ ተወግቶ፣ ወዘተ) ወራሪን ለመከላከያነት ሲጠቀምበት ነው፣ ይህም «ፓሲቭ ኢሙኒቲ» (passive immunity) በመባል ይታወቃል::

በጦርነት ወቅት የሚከሰቱት ወረርሽኞች በተዋጊው ጦረኛ ላይ ከፍተኛ ጉዳትን ያደርሳሉ:: ከዚያም በውጊያው ያልተሳተፈው የአካባቢ ሲቭል ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል:: ከጠቡ (ከግጭቱ) ውጭ የሆኑ አገሮችን ሕዝቦች ወረርሽኙ ተሰራጭቶ ለከፍተኛ ችግር ያጋልጣል:: በጦርነት ጊዜ የሚከሰተው ወረርሽኝ ድንበር አይለይም:: እከሌ ጠብ አጫሪ ነው፣ እከሌ ሰላማዊ ነው ከሚል ስሌት ውስጥ አይገባም:: አንዱን ከሌላው ሳይለይ በጅምላ ያጠቃል:: ከጦረኞች እንቅስቃሴ ጋር ተቀናጅቶ በተደጋጋሚ ወረርሽኝ መስፋፋቱን የታሪክ ምሁራን መዝግበዋል:: የአሜሪካ የእርስ በርስ ጦርነት (American Civil War) የነበረበት ዘመን እና የነበረውን የወረርሽኝ ጉዳት እንደ ምሳሌ ልንወስድ እንችላለን::

በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ተስቦ ወረርሽኝ ከፍተኛ ጉዳት አድርሶ ስለነበረ፣ «ሩዶልፍ ቬጅል» (Rudolf Weigl) የሚባል የፖላንድ የተፈጥሮ ሳይንስ ምሁር፣ ለተስቦ በሽታ ክትባት በመፈለግ ሳይንሳዊ ምርምር ላይ ተሰማርቶ ነበር:: ይህንን የተገነዘቡ የጀርመን የጦር መኮንኖች፣ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት መባቻ፣ ግለሰቡን ለተስቦ ክትባት እንዲያዘጋጅላቸው ቀጥረውት ነበር:: የጀርመን ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ጦርነት እና ወረርሽኝ ቁርኝት እንዳላቸው የታሪክ ግንዛቤ ነበራቸው::

 በዚያን ወቅት እና ቀደም ብሎም (1933) «ሩዶልፍ ቬጅል» ከላይ እንደተጠቀሰው ተስቦ ክትባት ፍለጋ ትኩረት ሰጥቶ ሳይንሳዊ ሙክረት እያካሄደ ነበር፣ ሙክረቱም እንደሚከተለው ነበር:: በመጀመሪያ ገና ከእንቁላል እንደተፈለፈሉ (በበሽታ ያልተለከፉ ግልገል ቅማሎችን)፣ እየመገበ ያሳድጋል:: ምግብ (ደም) የሚያገኙ ከሰው ገላ ሲሆን፣ ደም የሚመገቡም ለሁለት ሳምንታት ያህል ነበር:: እያንዳንዷ ቅማል በየቀኑ ለግማሽ ሰዓት ያህል ነበር የሰው ደም የምትመገብ:: የአመጋገቡ ሥርዓት እንደሚከተለው ነበር:: ቅማሎችን በትናንሽ ቀፎ መሰል ከረጢቶች አጉሮ፣ ከረጢቱን ከሰው ገላ ጋር፣ በተለይ ባት አካባቢ፣ በማጣበቅ ነበር:: ከረጢቶች የሚዘጋጁ፣ በወንፊት መሰል ቁስ ሲሆን፣ የወንፊቱ ክፍተት ቅማልን ከመመገብ ባይገታም፣ ቅማል ከከረጢቱ ለመውጣት አያስችልም ነበር (በቂ ክፍተት አልነበረውም)::

 ከዚያም ሩዶልፍ ቬጅል የተስቦ መንስዔ የሆነውን ባክቴሪያ «ሪኬትሲያ ፕሮዋዛኪ» (Ricketssia prowazaki) ከፈሳሽ ጋር ቀላቅሎ በሰው ገላ ተመግበው የፋፉ ቅማሎች ሆድእቃ እንዲገባ አደረገ:: ከዚያም ለቀጣይ አምስት ቀናት የሰው ደም እየመገበ በሕይወት አቆያቸው (በበሽታው የተለከፉ ቅማሎችን ይመግቡ የነበሩ ግለሰቦች፣ ቅማሎች በሚመገቡበት ገላቸው አካባቢ ምንም ቢበላቸው እንዳያኩ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ይሰጣቸው ነበር)::

 በዚህን ወቅት ቅማሎች ወራሪውን ለመከላከል «አንቲቦዲ» (antibody) ያዘጋጃሉ:: ከዚያም «ሩዶልፍ ቬጅል» ቅማሎችን ገድሎ፣ አንጀታቸውን አውጥቶ፣ ለንቁጦ፣ የበሽታ መከላከያ ክትባት ለማዘጋጀት በቃ:: ቅማል ለበሽታ መከላከያነት ያዘጋጀችው መሰናዶ፣ የሰው ልጅም ከበሽታው እንዲከላከል የሚረዳ ነው::

በተስቦ የተለከፉ ቅማሎችን አንጀት አውጥቶ፣ አሰባስቦ፣ ሰልቆ (ደቁሶ) በቢልቃጥ መሰል ዕቃ ውስጥ አጠራቅሞ፣ እንዲሁም መሰናዶው እንዳይበላሽ አንባሪ (preservative) አክሎበት «ሩዶልፍ ቬጅል» ቋሚ የተስቦ ወረርሽን ክትባት ለማዘጋጀት በቃ:: በዚህ መንገድ የተዘጋጀውን ፈሳሽ የተወጉ ግለሰቦች ከበሽታው ራሳቸውን ለመከላከል በቁ:: በበሽታው የተለከፉ ስንኳን ቢሆኑ፣ በአጭር ጊዜ ከበሽታው ለማገገም ቻሉ:: ይህን ዓይነቱ ነው «ፓሲቭ ኢሙኒቲ» (passive immunity) በመባል የሚታወቀው::

 በአዲስ አበባ፣ ከቅማል አንጀት ክትባት

“የብርቱካን መሰል ፍራፍሬ የበሉት ከበሽታው ለመዳን መቻላቸው ግንዛቤ ቢገኝበትም፣ ብርቱካን ውስጥ ምን እንዳለ እና የሰውነት/ አካልም ከብርቱካን ምን እንደሚያገኝ (በሰውነት ውስጥ የሌለ) አይታወቅም ነበር”

የሚዘጋጀው ድሮ «ፓስተር ኢኒስቲትዩት» (Pasteur Institute) በመባል ይታወቅ በነበረው፣ በአሁን ወቅት «የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት» ተብሎ በሚታወቀው ተቋም ውስጥ ነበር:: የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሆኜ ቅማል መጋቢ ጥቂት የጉለሌ ነዋሪ ግለሰቦች ገንዘብ ይከፈላቸው እንደነበረ ስሰማ በወቅቱ በጣም ተገርሜ ነበር::

 «ሩዶልፍ ቬጅል» ቅማሎችን በብዛት ለማራባት የሚያስችል ዘዴ/ ቴክኒክቀይሶ ነበር:: በዚያን ወቅት ቅማል መጋቢ የነበሩ ብዙ ግለሰቦች ቀጥሮ ነበር:: በዚህ አገልግሎት የተሰማሩ (ቅማል መጋቢ ሆነው) ግለሰቦች፤ በብዛት የፖላንድ የውስጥ አርበኞች እና አይሁዶች ነበሩ::

በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወቅት አይሁዶች ተፋፍገው እንዲኖሩ የተገደዱባቸው«ጌቶ» (ghetto) በመባል የሚታወቁ አካባቢዎች፣ የተስቦ ወረርሽኝ አንሰራርቶ ነበር:: ብዙ አይሁዶችም በተስቦ ወረርሽኝ ለሞት ይዳረጉ ነበር:: እንዲሁም በጀርመን የምሥራቅ ጦር ግንባር ተስቦ አንሰራርቶ ነበር::«ሩዶልፍ ቬጅል» ወደ ምስራቅ ጦር ግንባር ክትባት እንዲልክ በቀጣሪዎቹ (በጀርመን የከፍተኛ የጦር መኮንኖች) ሲታዘዝ፣ የሚልከው ክትባት ደካማ፣ በሽታ የመከላከል አቅሙ ውስን የሆነ ነበር:: ይህንንም የሚያደርግ ጀርመኖችን በመቃወም (በተቃውሞ መልክ) ነበር:: በተቃራኒው በተስቦ ለተጠቁ/ ለሚጠቁ፣ በጌቶዎች ይኖሩ ለነበሩ አይሁዶች፣ በምስጢር ፍቱን የተስቦ ክትባት ይልክላቸው ነበር:: እስከ 30ሺ የሚገመቱ ግለሰቦችን የሚያገለግል ክትባት ለአይሁዶች እንደላከ ይታወቃል::

 እስከ ቅርብ ዘመን ድረስ ለየት ባለ መልኩ የተስቦ ክትባት ይዘጋጅ ነበር:: ዝግጅቱም የበሽታው መንስዔ የሆነውን ባክቴሪያ አቅም ለዘብ በማድረግ ሲሆን፣ የባክቴሪያው የማጥቃት አቅም ለዘብ የሚደረግ ወይም ፈጽሞ የሚኮላሽ «በፎርማልዴሃይድ» (formaldehyde) ነበር:: ባጭሩ የተውሳክ መንስዔነቱ የተኮላሸ፣ «ሪኬትስያ ፕሮዋዛኪ» (Rickettsia prowazekii)፣ ክትባት ሆኖ ያገለግላል:: ክትባቱም የሚስተናገድ በአራት ሳምንታት ልዩነት ለተከታቢው ግለሰብ በመርፌ (የመድሐኒት መስጫ መርፌ) በፈሳሽ መልክ ሲሰጥ ነው::

 «በሪኬትስያ ፕሮዋዛኪ»፣ በቅማል እና በተስቦ ተጠቂ ግለሰብ መኻል ያለውን ግንኙነት ከተፈጥሮ ሳይንስ አንፃር እንመልከት:: አንዱ ግንኙነት በባክቴሪያዋ እና በቅማል መኻል ያለው ነው:: ሁለተኛው በሰው እና በባክቴሪያዋ መኻል ያለው ሲሆን፣ ሦስተኛው በቅማል እና በሰው መኻል ያለው ግንኙነት ነው:: ይህን ዓይነት ግንኙነቶች በጥቅሉ የጥገኞች/ቀላዋጮች (Parasites) እና የአስጠጊዎች (Host) ግንኙነት ይባላል:: ግንኙነቶች የሚጠቅሙ ለባክቴሪያዋ ብቻ ነው፣ ያም ባክቴሪያዋ በግንኙነቱ ተጠቅማ፣ ዘር በብዛት ለመተካት መቻሏ ነው:: ሌሎች የግንኙነቱ ተሳታፊዎች ቅማል እና ሰው፣ ተጎጅዎች ናቸው፤ ሁለቱም ለሞት ሊዳረጉ ይችላሉ:: ከተፈጥሮ ሳይንስ አንፃር ስንመለከተው፣ የምንረዳው/ የምንገነዘበው ሕያው በተገኙ አጋጣሚዎች ሁሉ ራሳቸውን ለመተካት የሚሄዱበትን አቅጣጫ፣ የሚቃኙበት ዘዴ፣ በጣም አስገራሚ መሆኑን ነው::

የተስቦ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ

በመጀመሪያ የተስቦ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ታሪክ የተወሳ (የተመዘገበ) በአፄ ቴወድሮስ ዘመነ መንግሥት በ1850ዎች መቋጫ አካባቢ ነበር:: የአፄ ቴወድሮስ አንድ የጦር ሰፈር በተስቦ ወረርሽኝ ተጠቅቶ ነበር:: በተለያዩ ዘመናት እና አካባቢዎች፣ የተስቦ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ደጋግሞ እንደተከሰተ ይወሳል:: ተስቦ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ በብዛት የሚከሰት በደጋው አካባቢ ሲሆን፣ ያም በደገኛ እና በቆለኛ አኗኗር ልዩነት ላይ የተመሰረተ ይመስላል:: ደገኛው ስለሚበርደው፣ ለቅማል መራቢያነት የሚያመች ዲሪቶውን ለብሶ ሲውል፣ ቆለኛው በሙቀት መንስዔ ብዙ ልብስ አይለብስም፣ እንዲሁም ደጋግሞ ገላውን ይታጠባል::

 በዘመናችን ይህ የተስቦ በሽታ ከብዙ አካባቢዎች ተወግዷል:: ሆኖም በ1960ዎች እና ከዚያ ወዲህ ስለ ተስቦ ወረርሽኝ የቀረቡ ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት፣ አሁንም በአፍሪካ በሽታው ያልተወገደባቸው አገሮች አሉ:: እነሱም ሩዋንዳ (Rwanda) ፣ ብሩንዲ (Burundi)፣ አልጀሪያ (Algeria) እና ኢትዮጵያ ሲሆኑ፣ ከበሽታው ያልተላቀቁ ጥቂት የደቡብ አሜሪካ እና የሩቅ ምሥራቅ አገሮች አሉ:: ኢትዮጵያ ውስጥ ደጋግሞ የተስቦ በሽታ የሚከሰት በትግራይ፣ በጎጃም፡ በጎንደር እና በሸዋ ጠቅላይ ግዛቶች (መረጃው የተቀናጀ ክልሎች ከመመስረታቸው በፊት ነበር) ነው::

«ስከርቪ» (scurvy) በምግብ አለመመጣጠን መንስዔ የሚከሰት ተውሳክ ለዘመናት ብዙ ርቀት የሚጓዙ መርከበኞች ከግማሽ በላይ ባልታወቀ ምክንያት ለሕልፈት ይዳረጉ ነበር:: የሞት መንስዔ፣ ነባር የአካባቢ ኗሪዎች በመጤዎች ላይ ባደረሱት ጥቃት ወይም የጠላት መርከብ ጦረኞች ያደረሱት ወይም የዘመድ ናፍቆት አልነበረም:: የሞት ምክንያት ስከርቪ (scurvy) በመባል የሚታወቅ ተውሳክ ነበር::

 መርከቦች ለወራት በባህር ጉዞ ከመጀመራቸው በፊት፣ የስከርቪ በሽታ አይታወቅም ነበር:: ሆኖም መርከቦች ወራት የሚፈጁ ጉዞዎችን እንደጀመሩ (ለወራት አንድም ወደብ ላይ መልህቅ ሳይጥሉ) ፣ ባልተመጣጠነ ምግብ ፍጆታ መንስዔ የሚከሰተውየ«ስከርቪ» በሽታ መርከበኞችን ማጥቃት ጀመረ:: ብሎም ለመርከበኞች ህለፈተ-ሕይወት ዋና መንስዔ ሆነ::

 ለምሳሌ «ቫስኮ ዳጋማ» (Vasco da Gama) ወደ ሕንድ በ1499 ዓ.ም. በተጓዘበት ጊዜ፣ ሁለት ሲሶ (66%) የሚሆኑት መርከበኞቹ በዚህ ተውሳክ ለሕልፈት ተዳርገዋል:: እንዲሁም በ1520 የብሪታንያው የመርከብ አዛዥ «ፈርዲናልድ ማጌላን» (Ferdinand Magellan 1840-1523) «ሰላማዊ ውቅያኖስን» (Pacific Ocean) ሲያቋርጥ፣ ሰማኒያ በመቶ (80%) የሚሆኑ መርከበኞችን በዚህ በሽታ መንስዔ አጥቷል:: ሌሎችም መርከበኞች ተመሳሳይ ችግር ደርሶባቸዋል:: በ«ሰላማዊ ውቅያኖስ» አካባቢ የነበሩትን የስፓኛ ግዛቶች ብሪታንያ በወረረችበት ጊዜ (በ1740 ዎቹ)፣ ከሁለት ሺ መርከበኞች አንድ ሺ ሦሰት መቶዎቹ በበሽታው መንስዔ ሕይወታቸውን አጥተዋል:: ስለሆነም የስከርቪ ተውሳክ መፍትሄ ረጅም የባህር ጉዞ ከተጀመረበት ዘመን ጀምሮ ሲፈለግ ነበር:: ስለሆነም ቅሰፈቱ «የባህር ወረርሽኝ» (the plague of the sea) የሚል ስያሜ ተሰጥቶት ነበር::

 የ«ስከርቪ» በሽታ ልዩ ባህሪው በበሽታው የሚጠቁ መርከበኞች በመጀመሪያ ንዳድ መሰል ትኩሳት፣ ያጠቃቸዋል:: ገላቸው በቡግንጅ መሰል ቁስል ይወረራል፣ ከዚያም የበሽተኞች ድድ እንደ ስፖንጅ ይለሰልሳል፣ ጥንካሬ ያጣል፣ የጥርሶች መዋቅር ይዛባል፣ ጥርሶች ይናጋሉ፣ ይዋልላሉ፣ ብሎም ማኘክ ይሳናቸዋል:: የድድ ሥጋ እየተበጣጠሰ በበሽተኞች ይተፋል (እንደ አክታ ሁሉ)፣ አካባቢው በድድ ሥጋ ቁርጥራጭና/ በረገፉ ጥርሶች ይበከላል፣ ይከረፋል፣ ለማየትም ይዘገንናል:: ከዚያም የሚከተለው አካልን መቆጣጠር መሳት፣ በመጨረሻም ለሞት መዳረግ ነበር:: እንደሚገመተው ከ16ኛው እስከ በ18ኛው መቶ ዓመት፤ ከሁለት ሚሊዮን በላይ መርከበኞች በ«ስከርቪ» ለሞት ተዳርገዋል::

ብርቱካን መሰል ፍራፍሬዎች (citrus fruits) የስከርቪ በሽታ መከላከያ እንደሆኑ ለዘመናት በብዙ አካባቢዎች ቢታወቅም፣ እንዲሁም በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን «ጆን ውድላንድ» (John Woodall/ 1570–1643) የሚባል የብሪታንያ የምሥራቅ ሕንድ ኩባንያ (British East India Company) ተቀጣሪ ቢደርስበትም፣ ግኝቱ ወደ ተግባር የተመነዘረ በ18ኛው መቶ ዘመን ነበር::

ስለ ስከርቪ በሽታ «ጄምስ ሊንድ» (James Lind) የሚባል፣ የብሪታንያ የመርከበኞች ሐኪም በ 1747 ዓ.ም. አንድ ሳይንሳዊ ምርምር/ ጥናት በመርከበኞች ላይ አካሂዶ ነበር:: «ጄምስ ሊንድ» አስራ ሁለት በስከርቪ የተጠቁ መርከበኞችን፣ በጥንድ (ሁለት ሁለት እያደረገ) በስድስት ቡድኖች መደባቸው:: ሁሉም የቡድን አባላት የሚመገቡት ምግብ ተመሳሳይ ነበር:: «ጄምስ ሊንድ» ከመደበኛው ምግብ በተጨማሪ፣ ለያንዳንዱ ቡድን የተለያዩ፣ የበሽታው መፍትሄ ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ/ የተገመቱ ስድስት ዓይነት ኬሚካዊ ቅማመ-ቅመሞች በምግባቸው ላይ አከለበት::

በዚህ ሂደት «ጄምስ ሊንድ» ከመደበኛው ምግብ በተጨማሪ ለቡድን «አንድ»፣ አንድ ሊትር ገደማ ከአፕል (apple) የተጠመቀ መጠጥ «ሳይደር» (cider) በመባል የሚታወቅ ሰጠ:: ለቡድን «ሁለት» በ«ሰልፈሪክ አሲድ» (sulphuric acid) የተቀመመ ሃያ አምስት ጠብታ ተሰጠ:: ለቡድን «ሦስት» ስድስት ማንኪያ ቆምጣጤ (vinegar) ተሰጠ:: ለቡድን «አራት» አንድ ፓይንት (660 ሲሲ ገደማ) የባህር ውሃ (ጨዋማ ውሃ) ተሰጠ:: ለቡድን «አምስት» ሁለት ብርቱካን እና አንድ ሎሚ ተሰጠ (ሎሚ እና ብርቱካን ስለአለቀ፣ የቡድን አምስት ልዩ ምግብ ከስድስት ቀናት በኋላ ተቋረጠ):: ለቡድን «ስድስት» በቅመም የታጀለ የገብስ ጭማቂ ተሰጠ (በዘመናችን የሚካሄዱት ምርምሮች ከዚህ ረቀቅ ባለ መንገድ ነው)::

ውጤቱ እነሆ::የቡድን «አምስት» አባላት ከለከፋቸው «ስከርቪ» ተውሳክ ተፈወሱ:: እንዲያውም ከሁለቱ አንዱ በጥቂት ቀናት ውስጥ በመደበኛ የመርከበኛ ተግባሩ ተሠማራ:: ከሌሎች ቡድኖች ትንሽ ለውጥ ያሳየው ቡድን «አንድ» ብቻ ነበር:: ሌሎች አራት ቡድኖች (ማለት ቡድን «ሁለት» «ሦስት» «አራት» እና ቡድን «ስድስት» ምግባቸው ላይ የተጨመረው (የታከሉት) መፍትሄ ይሆናል ተብለው የተገመቱት ኬሚካዊ ቅማማ ቅመሞች ምንም መፍትሄ አላበረከቱም:: «ጄምስ ሊንድ» በዚህ ውጤት ላይ ተመስርቶ በ18ኛው መቶ ዓመት አጋማሽ አንድ ሳይንሳዊ ጽሑፍ አበርክቶ ነበር:: ሆኖም ሳይንሳዊ ግኝቱ ወደ ተግባር በወቅቱ አልተለወጠም (አልተመነዘረም):: የተለመደው የመርከበኞች ምግብ (ስንቅ) በብዛት ብስኩት እና ሥጋ ነበር:: ምንም የፍሬ ዓይነት አይሰነቅም ነበር::

ምንም ከነኝህ የጀምስ ሊንድ የምርምር ቡድኖች አንዱ የብርቱካን መሰል ፍራፍሬ የበሉት ከበሽታው ለመዳን መቻላቸው ግንዛቤ ቢገኝበትም፣ ብርቱካን ውስጥ ምን እንዳለ እና የሰውነት/ አካልም ከብርቱካን ምን እንደሚያገኝ (በሰውነት ውስጥ የሌለ) አይታወቅም ነበር:: በመሠረቱ ለስከርቪ መፍትሄ ሆኖ የተገኘው በብርቱካን መሰል ፍራፍሬዎች ያለ/ የሚገኝ ቫይታሚን (ቫይታሚን ሲ- vitamin C) ሲሆን፣ መፍትሄ አበርካቹ በቫይታሚን ሲ ውስጥ የሚገኘው ኬሚካዊ ውሁድ፣ «አስኮርቢክ አሲድ፣ ascorbic acid) ይባላል:: ከላይ እንደተገለጠው፣ የስከርቪ ተውሳክ መንሥዔ ገላ ውስጥ የሚገኝ አስኮርቢክ አሲድ መጠን ዝቅተኛ ሲሆን ወይም ጨርሶ ሲጠፋ ነው::

 ከዚያ በኋላ፣ መርከበኞች የሚያልፉባቸው አካባቢዎች ሁሉ ብርቱካን መሰል ፍራፍሬ «ሲትረስ» (citrus) አምራች እንዲሆኑ ተደረገ:: መርከቦች መልህቅ የሚጥሉባቸው ወደቦች ሁሉ መርከበኞች ሲያርፉ፣ ፍራፍሬ በብዛት እንዲመገቡ፣ ብሎም ለቀጣይ ጉዞ ፍራፍሬ በብዛት እንዲሰንቁ ይደረግ ጀመር::

ከላይ እንደተጠቀሰው፣ ምንም የብርቱካን መሰል ፍራፍሬዎች የስከርቪ በሽታ መከላከል ጥቅም ቢታወቅም፣ ያ ዕውቀት ለጥቅም ከመዋል የዘገየበት ምክንያት ለሳይንስ እንግዳ አይደለም:: ታዋቂ የነበሩ ሰዎች ይሰነዝሯቸው የነበሩ እምነት አከል ግንዛቤዎችን ለመቀየር ዘመናት ይፈጃሉ (በግሪክ ፈላስፋዎች የተሰነዘሩ የተሳሳቱ አስተያየቶች ከሺ አመታት በኋላ ነበር ሊቀየሩ የቻሉት):: ቀደም ብሎ የነበረን የአዋቂዎችን አስተሳሰብ፣ በሌላ አስተሳሰብ መቀየር ማለት፣ ነባር ዕውቀትን አውልቆ ጥሎ አዲስ ዕውቀትን መላበስ የምሁራን አካባቢ አንድ አቢይ ተግዳሮት ነው:: የዝነኛ ግለሰቦችን አስተያየት፣ በቀላሉ መሰረዝ አይቻልም:: በአጭሩ የስከርቪ መፍትሄ በቀጥታ እንደተገኘ ያኔውኑ ወደ ተግባር ያልተመነዘረበት ዋና ምክንያት የዘመኑ የጤና ሙያ ጠበብት/ ሐኪሞች ስላላመኑበት ነበር::

 ምንም ይህን እውቀት ሊንድ ቢያመነጭ፣ የእንግሊዝ የባሕር ኃይል (the Royal Navy of UK) ግኝቱን ከጉዳይ አልጣፈውም/አልቆጠረውም ነበር:: ካፒቴን «ኩክ» (Captain Cook) ግን፣ የጀምስ ሊንድን አዲስ ግኝት እንደ ቁም ነገር ወስዶ ተግባር ላይ አዋለው:: የጀምስ ኩክ (James Cook) የመጀመሪያ ጉዞ (1768-71) እና በተደጋጋሚ ጉዞዎች ፤ (1772-75) እና (1776-79) መርከበኞቹም በተለያዩ ወደቦች ሲደርሱ፣ በብዛት ፍራፍሬ እንዲበሉ/እንዲመገቡ/፣ እንዲሁም የፍራፍሬ ስንቅ እንዲሰንቁ ትዕዛዝ ይሰጥ ነበር:: በተጨማሪ ቅጠላ ቅጠል በአንባሪ (Preservation) ውስጥ እየተደረገ በብዛት ይሰነቅ ጀመረ:: ካፕቴን ኩክ ይህን መሰናዶ ማድረግ ስለቻለ፣ በስከርቪ በሽታ መንስዔ አንድም መርከበኛ አልሞተበትም::

 በመጀመሪያ የስከርቪ መፍትሄ በማግኘት፣ ከዚያም ኢንዱስትሪ ባበረከተው ሞተር ታግዛ፣ ብሪታንያ የዓለም ውቅያኖሶችን ለመቆጣጠር በቃች፡ ብሎም የዓለምን ንግድ በጠቅላላ ተቆጣጠረች:: የብሪታንያ ፋብሪካዎች የሚያመርቱትን ቁሳቁስ የምታራግፍበትን ግዛቷን አስፋፋች:: ስለሆነም በሃያኛው መቶ ዓመት መባቻ፣ ሰፊው የዓለም አካባቢ በብሪታንያ ቁጥጥር ስር ነበር::

ከላይ በተብራሩት ሁለት የጤና ተግዳሮቶች ምክንያት፣ የዓለም ታሪክ ሂደት ተፅእኖ ደርሶበታል፤ የዘመኑ ድርጊቶች አቅጣጫዎችም በተውሳክ መንስዔ ተፅዕኖ ደርሶባቸዋል::

መደምደሚያ

 የገላን እና የልብስን ንፅሕና በመጠበቅ የብሪታንያ መርከበኞች በተስቦ ወረርሽኝ ከመተቃት ዳኑ:: ብርቱካን/ ሎሚ መሰል ፍራፍሬዎችን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ በመመገብ፣ ብሎም መርከቦች መልህቅ በሚጥሉበት አካባቢ ሁሉ «ሲትረስ» (citrus) ፍራፍሬ ዝርያ (ሎሚ/ ብርቱካን/ ወዘተ.) እንዲለማ በማድረግ እና ለምግብ ፍጆታ በማዋል፣ «ከስከርቪ» በሽታ ተላቀቁ::

 ይህም ተግባር ብሪታንያን ከተወዳዳሪዎቿ፣ ቀደም ሲል ስፓኛ (Spain) ከዚያም ፈረንሳይ (France) በባህር ጉዞ ልቃ ዘለቀች:: ብሪታንያ ለሁለት ሕይወት አጥፊ በሽታዎች መፍትሄ በማግኘት የዓለምን ውቅያኖሶች ተቆጣጠረች:: ይሀም ሁኔታ ግዛቷን ለማስፋፋት ከፍተኛ አስተዋፅዖ አደረገ:: ግዛቷም ከአጥናፍ አጥናፍ ተንሠራፋ:: ብሎም «በብሪታንያ ግዛት ፀሐይ መጥለቅ ተሳናት» ተባለ::

የብሪታንያ መርከበኞች ለስከርቪ መፍትሄ ባያገኙ ኖሮ (ተመጣጣኝ ምግብ ፍራፍሬ የታከለበት) ፣ እንዲሁም የተስቦን ወረርሽኝ የገላን እና የልብስን ንፅሕና በመቆጣጠር ለመቋቋም ባይችሉ ኖሮ፣ ብሎም ለሁለቱም ተግባራት ደምብ ባይዘጋጅ ለብሪታንያ መርከበኞች ሁሉ ባይሰራጭ ኖሮ፣ ብሪታንያ 19ኛው መቶ ዓመት እና የ20ኛው መቶ ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ታላቋ የዓለም መንግሥት (ታላቋ ብሪታንያ/ Great Britain) ለመባል አትበቃም ነበር ብሎ መገመት ይቻላል:: ስለሆነም የዚያን ዘመን የታሪክ ፍሰት የወሰነው ሳይንሳዊ አስተሳሰብን አንግቦ ለተውሳክ መፍትሄ ማግኘት ነበር ብሎ መደምደም ይቻላል:: ለዚህም ነው «ታሪክ እና ተውሳክ» ቁርኝነት አላቸው የሚባል::

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top