አድባራተ ጥበብ

ተአምረኛው ሌባ

መነሻ ከጋሼ ስብሃት ገ/እግዚአብሔር ጋር ከሶስት አመት በላይ በአንድ ቢሮ ውስጥ በተመሳሳይ ስራ አሳልፌያለሁ። በነዚህ አመታት ወንድሜ ዘነበ ወላ ያልሰማቸው፣ ሰምቶም ያልመዘገባቸው በርካታ ጨዋታዎች አብረውኝ አሉ። ከበርካታ የጋሼ ስብሃት ጨዋታዎች መካከል አንዱን ለዚህ አጭር ጽሑፍ እንደ መነሻ ተጠቀምኩበት። ይህ የጋሼ ስብሃት ጨዋታ ‹‹አምስት ስድስት ሰባት›› የተባለው መድበላቸው ታትሞ ከተሰራጨ በኋላ የሆነ ነው።

በመድበሉ ከተጠቃለሉ ታሪኮች መካከል የመድበሉ ርእስ የሆነው ‹‹አምስት ስድስት ሰባት›› ታሪኩ እጅግ መሳጭና ልብ የሚነካ ስለነበር፣ ለዚህ ያበቃውን ስነ ጥበባዊ ችሎታውን በእጅጉ ለማድነቅ ተገደድኩና ይህንኑ ስሜቴን ለጋሼ ስብሃት ነገርኩት።

‹‹ምኑ ሳበህ?›› ሲል በቁም ነገር ጠየቀኝ። ‹‹ታሪኩ ድህነት ከነነብሱ የቀረበበት፣ ገጸባህሪያቱ ማጣት የቱን ያህል አስቀያሚ እንደሆነ የገለጹበት፣ …›› እያልኩ ዘረዘርኩለት። መግለጫዬን ስጨርስ ጋሼ ስብሃት በሀዘን ውስጥ ሆኖ አገኘሁት።

 ‹‹ምን ሆኑ ጋሼ ስብሃት?›› የሚል ጥያቄ ወረወርኩ። ጋሼ ስብሃት ጥቂት ሲተክዝ ቆይቶ ‹‹እኔ ደግሞ ያልከኝ ታሪክ ታትሞ አንባቢ እጅ እንደመግባቱ አሳዝኖኝ የሚያውቅ አጋጣሚ የለም›› አለኝ።

 ‹‹እንዴት?›› አልኩት እየተገረምኩ። ‹‹አየህ፣ ህዝቡ በድህነት፣ በስራ ማጣት፣ በአስተዳደር በደል፣ በጦርነት … ሀዘን ላይ ነው። ይኸ ሳያንሰው እኔ ደግሞ ሌላ ሀዘን ጨመርኩበት። … ይኸ ጭካኔ ነው። ታሪኩ መታተም አልነበረበትም።››

 ‹‹እንዴ ጋሼ ስብሃት! እርስዎ ስለ ድሃና ድህነት ይጽፉ የለ እንዴ፣ ይኸን ታሪክ ምን አዲስ አደረገው?›› አልኩና አስረጂ ይሆኑኝ ዘንድ መድበሉ ውስጥ ያሉ ታሪኮችንና ገጸባህሪያቱን እየጠቀስኩ ለማስረዳት ሞከርኩ።

ጋሼ ስብሃት ግን ሞገተኝ። ‹‹ አየህ ልጄ! እኔ ስለ ድሃና ድህነት ጽፌ አላውቅም። … ሳጣራ ውስጥ፣ ቱቦ ውስጥ … የሚኖሩ የኔ ቢጤዎችን አስተውለህ ታውቃለህ! የቀን ፀሐይ፣ የማታ ብርድ ሳይበግራቸው ጧ ብለው ሲተኙ፣ አልጋ ሲጋሩ፣ አንሶላ ሲጋፈፉ፣ ልጅ ሲያሳድጉ፣ ከልብ ሲስቁ፣ … እስኪ ተመልከት! ከዚህ ምን ይታየኝ ይመስልሃል! ጥንካሬ! የከተማችን ሃብታምና ባለስልጣን ሞዝቮልድ አልጋ ላይ እንደነሱ ጧ ብሎ የሚተኛ፣ ሰውነቱ በስሜት ተወጥሮ ከሚስቱ ጋር ከልቡ የሚዝናና ይመስልሃል!? … ጥንካሬ የቱ ጋ ነው ያለው? አየህ እኔ ስለ ጥንካሬ እንጂ ስለ ድህነት ጽፌ አላውቅም፤…›› በሰፊው አስረዳኝ።

ጋሼ ስብሃት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የነገሮችን አፍአዊ ገጽታ ብቻ ሳይሆን ውስጣዊ ባህሪያቸውንም እንድመለከት ተጨማሪ አይን የከፈተልኝ ይመስለኛል።

ሰብስቤ፣ ሰርስር፣ ሸኽ ሁሴን

 ይህ የተጻፈ ታሪክ የሌባ ታሪክ እንዳይመስላችሁ። በእርግጥ ባለታሪኩ ይሰርቃል፤ በስርቆቱም በየጊዜው እየታሰረ፣ እየተገረፈ፣ እየተፈታ … ዘልቆበታል። እንዲያም ሆኖ የሚያውቁት አብዛኞቹ ሰዎች ሰብስቤን ሌባን በሚያዩበትና በሚረዱበት ስሜት አይገልጹትም። ከዚያ ይልቅ የሚያደንቁት፣ የሚፈሩት፣ የሚያስፈራሩበት ይበዛሉ። ልጆች ማታ ማታ ቤት እንዲዘጉ ታዘው ሲፎካከሩ ‹‹ዋ! ሰርስር እንዳይመጣ ዘግታችሁ ብትተኙ ይሻላችኋል›› እየተባሉ ይስፈራራሉ። ይህ ባለ ታሪክ ‹‹ሰብስቤ አስፋው›› ይባላል። ውልደቱ ደቡብ ወሎ፣ ወግዴ ወረዳ ነው። በ2002 ለመስክ ወደ አካባቢው በሄድኩ ጊዜ እድሜው ሰማኒያ ሁለት እንደነበር አጫውቶኛል። የሰውነቱን ቀልጣፋነት፣ የንግግሩን ፍጥነትና ጥፍጥና፣ የማስታዎስ ችሎታውን ለሚያይና ለሚረዳ ሰው ሰብስቤ የሰማኒያ ሁለት አመት አዛውንት ነው ብሎ ለመቀበል የሚከብደው ይመስለኛል።

‹‹ሰብስቤ›› ወላጆቹ ያወጡለት ስም ይሁን እንጂ አብዛኛው ሰው በዚህ ስሙ አያውቀውም። የሚያውቁትም ቢሆኑ ‹‹ሰብስቤ›› ብለው አይጠሩትም። የወረዳው ነዋሪ ‹‹ሰርስር›› እና ‹‹ሸኽ ሁሴን›› በሚል ስሙ ነው የሚያውቁትና የሚጠሩት። ‹‹ሰርስር›› የሚለውን ስያሜ ህብረተሰቡ ያወጣለት ሲሆን ‹‹ሸኽ ሁሴን›› የሚለው ስሙን እራሱ ሰብስቤ እንዳወጣው ይታመናል። ሰብስቤም በፋንታው ከልጅነት እስከ እውቀት የዘለቀበትን የ‹‹ስርቆት›› ህይወቱን እንደ ‹‹ሌብነት›› አይመለከተውም። ‹‹ኖርኩበት፣ ተዳደርኩበት፣ መከራም አሳለፍኩበት፣ ስምም ተከልኩበት›› ብሎ ያምናል።

ከላይ ለማስተዋወቅ እንደተሞከረው የወግዴ ሕዝብም ሰብስቤን እንደ ማንኛውም መደበኛ ሌባ፣ ድርጊቱን እንደማንኛውም ሌብነት አይመለከተውም። እንደ ጀግና፣ እንደ ተንኮለኛ፣ እንደ ብልሀተኛ፣ አንዳንዴም እንደ መተተኛ አድርገው ይገልጹታል። በአንድ ወይም በሌላ መንገድ የወግዴ ህዝብ የሚያውቃቸውና የሚተርካቸው የሰብስቤ የስርቆት ተረኮች ቀድሞ የተገለጸውን የሰብስቤ ገጽታ የሚገልጹ ናቸው ማለት የሚቻል ይመስለኛል።

ሀሳቡን ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ፣ ቀጥሎ ከበርካታ የሰብስቤ የስርቆት ተረኮች መካከል ጥቂቶቹ ይቀርባሉ። የተረኮቹ አቀራረብ ሁለት አይነት መንገድ የተከተለ ነው። በአንደኛው መንገድ ሰብስቤ የራሱን ተረክ እንደወረደ እንዲተርክ ተደርጓል። በሁለተኛው መንገድ፣ የሰብስቤን የስርቆት ተረክ የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ መረጃ አቀባዮች እንደተረኩለት እንዲቀርብ ሆኗል።

ተረክ አንድ፡- ሰብስቤ እንደተረከው ሌብነት የጀመርኩት በልጅነቴ ነው። አንድ ጊዜ ጡንጊ ላይ ከብት ነድቼ ስሄድ ድንገት እከበባለሁ። በዚህ ጊዜ ፈጥኜ መንደር ውስጥ ገብቼ እሰወራለሁ። ከዚህ አደጋ እንዴት መውጣት እንደምችል ሳሰላስል አንድ ሀሳብ መጣልኝ። እንደምታየኝ አሁን እንኳን አጭር ነኝ፤ በዚያን ጊዜ ደግሞ ካሁኑ በጣም አንሳለሁ። በዚያ ላይ ጺም የሚሉ ነገር አልነበረኝም። እና አንድ ቤት ገባሁና የሴት ቀሚስ ለብሼ፣ ልብሴንም ጓዝ አስመስዬ ተሸክሜ መንገደኛ መስዬ ከተሸሸግሁበት መንደር ወጣሁ። ማንም ከቁብ ሳይቆጥረኝ፣ በከበበኝ ሰው ትርምስ እየሳቅሁ ምሽት ላይ ወግዴ ከተማ ስደርስ ልብሴን ቀይሬ ገባሁ።

ረሃቡም ውሃ ጥሙም ውሎብኝ ስለነበር ወይዘሮ ደብሪቱ ጠጅ ቤት ገባሁ። አንድ ብርሌ ጠጄን ከጠጣሁ በኋላ ምግቤን እየበላሁ ‹‹ዛሬ ደግሞ ከተማው ጭር አለብኝሳ›› ስል ወይዘሮ ደብሪቱን አዋራኋት። ደብሪቱ በዚህ በወግዴ ከተማ የታወቀች ኮማሪ ነበረች። ሁል ጊዜ ልጅ መሆን የምትመኝ ጉደኛ የሴት ወይዘሮ ነበረች። በዚህ የተነሳ ‹‹ግድ እመቤት›› የሚል ስም ወጥቶላት ነበር። እርሷንም አፈር በላት።

 ‹‹ምን ሰላም አለ ብለህ ነው፤ ያቺ ሰርስር የሚሏት ጠንቀኛ ሌባ ተከባ ሰው ሁሉ ወደ ጡንጊ ሄዶ አልተመለሰም›› ስትል መለሰችልኝ። አነጋገሯ ደሜን አፈላው። የጀመርኩት ምግብ ተናነቀኝ። ብቻ ከጠጁ እየደጋገምኩ ጥቂት ቆየሁ። የወይዘሮ ደብሪቱን ግቢ ባለሁበት ሁኜ ሳስስ አንድ ፈረስ ግቢዋ ውስጥ ታስሮ ገለባ ሲበላ ተመለከትኩ። ‹‹ይችን ይወዳል ሰብስቤ›› አልኩና የታሰረውን ፈረስ ፈትቼ ይዠ ጠፋሁ።

 ደብሬ ሆዬ ፈረሷን የወሰድኩት እኔ መሆኔ ገባት መሰል አንድ የሷ ወዳጅ የሆነ ሰው ሽምግልና ላከችብኝ። ለተላከብኝ ሽማግሌ ‹‹እኔ የሷን ፈረስ አልነካሁም። ያለ ስራዬ እንዲህ በማለቷ በስም አጥፊ ከስሸ ጉድ ነው የማደርጋት። … ሰረቀብኝ ብላ እንኳ ብታስብ ሰው ከምትልክ ለምን እራሷ አትጠይቀኝም›› ብዬ መለስኩት። ሌላ ጊዜ እራሷው ፈልጋ አገኘችኝ። እኔም ያን ቀን ያለችኝን ሁሉ እያነሳሁ ልክ ልኳን እስከ አፍ ጢሟ ነገርኳት። በመጨረሻ ሰማኒያ ጠገራ ብር ተቀብዬ ፈረሷን መለስኩላት።

ተረክ ሁለት፡- የመረጃ አቀባዮች እንደተረኩት

 በደርግ ዘመን ከአርሶ አደሩ የተሰበሰበ የግብር ብር ከገንዘብ ያዡ ቤት ይጠፋል። የገበሬ ማህበሩ አመራሮችና የወረዳው ባለ ስልጣኖች የተሰበሰበውን የግብር ብር ማን ሊሰርቀው እንደሚችል ውይይትና ምክክር ያደርጋሉ። በመጨረሻ በወረዳው የሚገኙ ‹‹ሌቦች›› ተይዘው ይመርመሩ የሚል ውሳኔ ያሳልፍና ሰብስቤ ከተጠርጣሪ ሌቦች የመጀመሪያው ሆኖ ይታሰራል።

ሰብስቤ በመንግስት የግብር ገንዘብ ስርቆት እንደታሰረ በዋዛ እንደማይለቀቅ፣ እንዲሁም የከፋ ምርመራ ሊደረግበት እንደሚችል ይረዳና ከዚህ እስርና ምርመራ ሊያመልጥ የሚችልበትን ዘዴ ይቀይሳል። የማምለጫ ስልቱንም በተለይ በወግዴ ከተማና አካባቢ በሚኖሩ ነጋዴዎችና የሀይማኖት መሪ እንዲሁም ፖሊስ ላይ ያደርጋል። ሰብስቤ እንደሚለው ነጋዴዎቹንና የሃይማኖት መሪውን ባለ ሀብት በመሆናቸው፣ ፖሊሱ ደግሞ የቆየ ቂም ስላላው ለመበቀል ያደረገው ነው።

 ሰብስቤ ለምርመራ ጣቢያ እንደቀረበ ‹‹ብሩ መዘረፉ እውነት ነው፣ ነገር ግን ብቻየን አልዘረፍኩም። ሀሳቡንም እኔ አላመጣሁትም፤ ይልቁንስ እኔ ብጠቁማችሁ ነው የሚሻለው›› በማለት ይጀምራል። ‹‹እሺ ካንተ ጋር እነማን አሉ?›› ይባላል። ከላይ የተዘረዘሩ የአካባቢው

“አንድ ቤት ገባሁና የሴት ቀሚስ ለብሼ፣ ልብሴንም ጓዝ አስመስዬ ተሸክሜ መንገደኛ መስዬ ከተሸሸግሁበት መንደር ወጣሁ። ማንም ከቁብ ሳይቆጥረኝ፣ በከበበኝ ሰው ትርምስ እየሳቅሁ ምሽት ላይ ወግዴ ከተማ ስደርስ ልብሴን ቀይሬ ገባሁ”

ነዋሪ ሰዎችን በስም እየጠቀሰ ይጠቁማል። ‹‹የተሰረቀው ብርስ ከማን ዘንድ ነው?›› ይሉታል። ሰብስቤ ቀድሞ ባዘጋጀው ስልት መሰረት፣ ተዘረፈ የተባለውን ብር ለዘረዘራቸው ሰዎች አከፋፍሎ በእነሱ እጅ እንደሚገኝ፣ ለእርሱ ግን ሳይሰጡት እንደተያዘ ያስረዳል።

 ሰብስቤ በሰጠው ጥቆማ መሰረት፣ ብሩን አብረው ሰርቀዋል፣ በእጃቸውም ይገኛል የተባሉ ሰዎች ከያሉበት መታደን፣ መታሰር ይጀምራሉ። የወግዴ ከተማ ነዋሪ በተለይም ባለ ሀብት ከፍተኛ ሽብር ውስጥ ይገባል። የከተማው ነዋሪ ‹‹ማነው ባለ ተራ›› እያለ የአዳዲስ እስረኞች ዜና መጠባበቅ ይጀምራል። በወቅቱ ያልተያዘው ነጋዴ ቤት ንብረቱን ትቶ ግማሹ ወደ ገጠር፣ የተቀረው ወደ ሩቅ አገር (ደሴ፣ አዲስ አበባ) ይሰደዳል።

 የወረዳው የመንግስት ሀላፊዎችም በሰብስቤ ጥቆማ በቁጥጥር ስር ካዋላቸው ሰዎች፣ ሰብስቤ እነሱ ዘንድ አለ ብሎ በተመነባቸው ልክ የሰረቁትን ብር በአፋቸው አስነክሶ ‹‹እኔን ያዬ ይቀጣ›› እያስባለ ከተማ እንዲዞሩ ካደረገ በኋላ ወደ ግምጃ ቤት ገቢ ያደርጋል። ሰብስቤም ጠቋሚነቱ በመልካም ተግባር ተቆጥሮለት በነጻ ይለቀቃል።

 ተረክ ሦስት – ሰብስቤ እንደተረከው

 ደራ አንድ ሰው ነበረ። ባላባት ነው። ሲጠጣ ጠፍር አልጋ ላይ ተቀምጦ ነው። ይኸ ሰው ሰባት የገደለ ነው። የጥጋቡ ጥጋብ ገደሬ (ሰው የሚበዛበት የአካባቢ መንደር ስም ነው) ሲጠጣ ይውላል። ያያ (ይኸም ሰው የሚበዛበት አካባቢ መንደር ስም ነው) ሲጠጣ ይውላል። አይሸሸግም፣ አይፈራም። የቤቱ አጥር ተሰው ቁመት በላይ ነው። አምስት እሳት የላሱ ውሾች አሉት። ግቢው ተገብቶ፣ ቤቱ ተዘልቆ ጠመንጃውን ለመውሰድ አስቸጋሪ ነበር።

 ዘጠን ሽፍቶች ሆነን ይኸን ሰው ልንሰርቀው ተስማማን። ታዲያ የሰውየው ቤት በቀላሉ እንደማይበገር ስናውቅ ደራ ሄድንና መሰላል አሰራን። የበግና የፍየል ጭራ እየነጨን ከጭብጦ ጋር አስጋገርን። በዚያ ላይ ትንሽ አስማት አለችኝ፣ እሷን አደረኩና ሲመሽ ሰውየው ቤት ሄድን። ለውሾቹ ጭብጦውን ስንወረውርላቸው እየተነፋነፉ ወደ ጥግ ሄዱ። ተዛ አጥሩን በመሰላል ገባሁና ያጥሩን ሳንቃ ከፈትኩላቸው። ግቡ አልኳቸው። ገቡ።

 ቤቱን ብታየው አጠቃላይ ከደሬ እንጨት የተሰራ ነው። ዙሪያው ተውጭ ተግቢ የተዘጋ፣ የተመረገ ነው። የቤቱ ቁልፍ የሃምሳ ብር ነው። ብንዞር ብንዞር መግቢያ ከየት ይገኝ! ብቻ እንድህ በጓዳ በኩል ተዛነፏን አየሁ። “ተዛነፏ በባላ ቢነሳልኝ እገባ እንደነበር” ነገርኳቸው። ከጓሮ የነበረ ባላ አመጡና ተተዛነፏ አነሱልኝ። ገባሁ።

 ስገባ ባልና ሚስቱ እንርባ ይላሉ፣ ያንኳርፋሉ። ተዛ በልጅጉን፣ ሽጉጥን አነሳሁ። ሳጥኑን ብድግ አድርጌ ከውስጡ አምስት መቶ ጠገራ ብር አገኘሁ። ያንን ወስጀ ሰጠኋቸው። ከውጭ ያሉት ስምንቱ ጓደኞቼ “ጨረስክ፣ ምንም የቀረ እቃ የለም” አሉኝ። “ምንም የቀረ እቃ የለም” አልኳቸው። ለካ ሊከዱኝ አስበው ኖሯል የያዙልኝን ጋቢላ ደፍተውብኝ እልም አሉ። ማን ይቀራል እኔና አንድ ፍሻሌ ቦምብ ከአንድ ጩቤ ጋር። ጠመንጃየንም፣ ጀበርናየንም ፈትቸ ሰጥቻለሁ። እኔን እሽፍታው ቤት ውስጥ ብቻየን ጥለውኝ ንብረቴን ይዘውት ሄዱ።

እንደምንም ብዬ መውጫ ቀዳዳ ፈለኩ። የለም። የበሩን ቁልፍ እከፍታለሁ ብዬ ብሞክረው ምንና ምን፣ የሃምሳ ብር ቁልፍ። “እንድህ የቦረና እርግማን ደራ አምጥቶ ይግደለኝ! እዚያ እንኳ አገሬ ብሞት የገሌ አባበሉ ልጅ፣ የአስፋው አብቹ ልጅ ሞተ እባላለሁ። እዚህ ወገን እንደሌለው ሰው እንዳው አንድ ተሰው አገር የመጣ ሰው ተዚህ ሞተ ተብሎ ሊተረትብኝ ነው” አልኩና በጣም አዘንኩ። በዚሁ መካከል አንድ ሀሳብ መጣልኝ። በቀጥታ ወደ ቤቱ ባለቤት መኝታ ሄድኩና “ተነስ አንተ! ተነስ!” ብዬ ጮኽኩበት። ብድግ አለ በድንጋጤ። ወደሚስቱ ዞሬ ደሞ “እሳት አንድጂ አንቺ፣ ጭስ አጭሺ!” አልኳት። ልብሷን አስተካክላ ሳትለብስ ከሳቱ ጋር መጨናበስ ጀመረች። ከዚያ ወደ ሰውዬው ዞርኩና “ስማ እንጂ አንተ! ማን እንደሆንኩ፣ ከየት እንደመጣሁ አውቀሃል፣ እስቲ ቤትህን እየው” ብዬ ጮህኩበት።

ቤቱን ቢያዬው እንደተቆለፈ ነው። እንዲህ እንደኔ ያለ ቀላል ሰው አይነካውም። “እኔ የሸኽ ሁሴን ካዲም ነኝ። ከእሳቸው ተልኬ ነው የመጣሁ። ተሰማይ ልውረድ ተመሬት ልውጣ ታውቃለህ? አሁን ተነሳና እዛ ምሰሶው ስር አዱሩስ አጭስ! ለሸኽ ሁሴን አውሊያም ደጃፉን ክፈት!” ብዬ ለሌላ ወሬ ጊዜ ሳልሰጠው ማጓራት ጀመርኩ። ሰውዬው ደጃፉን ወለል አድርጎ ከፈተ። ሴትየዋ ጪሱን በላይ በላይ ታጫጭሰው ገባ። ምን እልሃለሁ ሀድራው ደመቀ።

ሳጎራ ከቤቱ ሳንቃ እስከ ቤቱ ምሰሶ እየተሸከረከርኩ ነበር። ወዲያ ወድህ ባልኩ ቁጥር ማምለጫዬን እያዬሁ ነበር። በመጨረሻ “አውልያው መጣ፣ ክንፉን ዘርግቶ ደረሰ። ተደፉ፣ ተደፉ፣ የሸኽ ሁሴን አውሊያ ገብቶ እስኪረጋጋና ተነሱ እስክላችሁ ባላችሁበት እርጉ” አልኳቸው። ባሉበት ተደፉ። እኔም እያጎራሁ፣ እያጎራሁ፣ በዚያው እልም! እንድህ አድርጌ አመለጥኩ።

 ከሽፍታው ቤት ማምለጤን ሳረጋግጥ ጊዜ የሆነ ነገር ሰውነቴን ወረረው። ጓደኞቼ መክዳታቸው ሳያንሳቸው ጠመንጃየንም ይዘው ጠፍተዋል። ባዶ እጄን ቀርቻለሁ። ልከተላቸው ወሰንኩና ሊሄዱበት ይችላሉ ብዬ በገመትኩት መንገድ ገሰገስኩ፣ እሮጥኩ ብለው ይሻላል።

አንድ ሰአት የሚሆን ጉዞ ካደረግኩ በኋላ፣ አንድ የእስላም መቃብር ቦታ ስደርስ መቃብሩ ግቢ የሰው ሹክሹክታ ሰማሁ። እነዚያ የከዱኝ ጓደኞቼ ከሽፍታው የወሰድነውን ንብረት እየተከፋፈሉ እንደሆነ ገባኝ። ወዲያውኑ በእጄ የቀረችውን ቦንብ ቀለበት ፈልቅቄ ወደ ጓደኞቼ አቅጣጫ ወረወርኳት። ቦንቧ እሳት እየተፋች የመቃብሩን ቦታ አተራመሰችው። ከቆይታ በኋላ ወደ መቃብሩ ስገባ አስር ጠመንጃና የሽፍታውን ንብረት ሁሉ እንዳለ አገኘሁ። … በመጨረሻ ከዚያ ሁሉ ጭንቀት ወጥቼ አስር ጠመንጃ እንደ እንጨት ተሸክሜ እኔም በፈንታዬ ለመሰወር በቃሁ። የከዱኝንም ጠመንጃ ሸጨ ብዙ ጊዜ ጠጣሁበት።

 ተረክ አራት – መረጃ አቀባዮች እንደተረኩት ሰብስቤ በአንድ ወቅት ከአንድ የበግ ነጋዴ ጋር ይጣላል። በወቅቱ በአካባቢያቸው የነበሩ ሰዎች በመካከላቸው ጣልቃ ይገባሉ። ሰውየውም ሃይለኛና ምንሽር የሚባል ጠመንጃ ያለው ሰው ስለነበር ሰብስቤ በጥሉ መግፋት አልፈለገም። ብቻ ‹‹በዚህ ሳምንት እኔ አንተን ባልሰራልህ እኔ ሰብስቤ አይደለሁም›› ብሎ ይዝትበትና ወደ ቤቱ ይመለሳል። ሰውየውም በንቀት ‹‹እናያለና›› ሲል ይቀልድበታል።

የሰውየው በጎች የሚያድሩት እቤት ውስጥ በተዘጋጀ ጋጥ ውስጥ ነበር። ሰብስቤ በዚያኑ እለት ምሽት የበግ ቆዳ እንደ ለምድ ለብሶና ከበጎቹ ጋር ተቀላቅሎ ጉሮኖ ውስጥ ይገባል። እዚያ ውስጥም አድፍጦ የሰውየውን አተኛኘት፣ ጠመንጃውን የሚያስቀምጥበትን ቦታ … ሁሉ ሲያጠና ያመሻል። በመጨረሻ ቤተሰቡ ሁሉ መተኛታቸውንና እንቅልፍ ውስጥ መውደቃቸውን ሲረዳ ከነበረበት ወጥቶ፣ የሰውየውን ምንሽር ጠመንጃ ይዞ ይሰወራል። ሲነጋ የቤቱ ባለቤት የጦር መሳሪያው እንደተወሰደ ሲያውቅ ወደ ሰብስቤ ሽማግሌ ይልካል። ከብዙ ሽምግልና በኋላ ሰብስቤ ካሳ ተቀብሎ ጠመንጃውን ይመልስለታል።

 መድረሻ

 በዚህ የመዳረሻ ክፍል እኔና እናንተ ሁላችን የጋሼ ስብሃትን ገጠመኝ አስታውሰን፣ የሰብስቤን ቃለ መጠይቅ ደጀን አድርገን እኔ የተመጠኑ ሀሳቦች ላንሳ። ጋሼ ስብሃት በድሆች ታሪክ ውስጥ ጥንካሬን ማየት እንደቻሉ ሁሉ በሰብስቤ የስርቆት ገጠመኞች ተረክ ውስጥ የፈጠራ፣ የልማድና የእምነት እውቀትና የፈጠራ ጥበብ ችሎታን እናገኝበታለን – በተለይ ለጥበብና ለፈጠራ ሰዎች።

 ታዲያን፤ ሰብስቤን ለመረዳት ወደዛሬ ሀምሳ አመት አካባቢ ስለነበረው ዘመን ባህልና አኗኗር እንዲሁም እምነት በአይነ ህሊና መመለስ ይጠይቃል። በዚያ ዘመን አውድ በዚህ ጽሁፍ የቀረቡ የስኬት ታሪኮች ሰብስቤን ‹‹ተአምረኛ›› ሰው የሚያስብሉት ይመስለኛል። ሰብስቤ በአካባቢው ሊደፈሩ፣ ከተደፈሩም የመጨረሻውን አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ ሁኔታዎች ውስጥ መግባትና ማለፍ ያዘወትራል። ከሰው እራስጌ ጠመንጃ መውሰድ፣ እሰው ግቢ ገብቶ ፈረስና በቅሎ መንዳት፣ የበግ ለምድ ለብሶ ከበጎች ጋር ተመሳስሎ ጉረኖ/ማደሪያ መደበቅ፣ አደጋው የከፋ እንደሆነ ሰብስቤም ያውቀዋል። ሰብስቤ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሲመላለስበት ኖሯል። ይህ ድፍረቱ፣ ‹‹አስማተኛ›› እስከ መባል አድርሶታል። ሰብስቤ እንደ ማንኛውም ‹‹ሌባ›› ሳይሆን በአካባቢው እንደ ‹‹ጀግና›› እንዲታይ አብቅቶታል።

 ሰብስቤ ደፋር ብቻ ሳይሆን ጥበበኛም ነበር። አደጋ ውስጥ ከወደቀ በኋላ እንዴት ከአደጋው ማምለጥ እንዳለበት የተውኔት ድርሰት ማዘጋጀትና መተወን ይችልበታል። ለዚህም እራሱንና አካባቢውን ጠንቅቆ የማወቅና የመረዳት ፍጥነቱ፣ እንዲሁም ወደ ጥበባዊ ድርጊት መለወጥ መቻሉ ያስደምማል። በንጉሱ ዘመን ልማድ መሰረት ወንድ ልጅ የሴትን ልጅ ቀሚስ መልበስ ያልተለመደና ነውርም እንደነበር በማወቁ የተውኔቱ አካል ማጠንጠኛ፣ ከገባበት ቅርቃር ማምለጫ አድርጎታል።

ሰብስቤ ደፋርና ጥበበኛ ብቻም አልነበረም። ሃይማኖት አካታች የሆነ እውቀትም ነበረው። ሰብስቤ ሃይማኖቱ ክርስትና ነበር። ነገር ግን የአካባቢው ሙስሊሞች ልማዳዊ ባህልና እምነት እውቀት ነበረው። በዚሁ እውቀቱ ‹‹እስላማዊ›› ተውኔት ሲያዘጋጅና ሲተውን፣ በተውኔቱ ከገባበት አጣብቂኝ በድል አድራጊነት እንዲወጣ አስችሎታል። ‹‹ሸኽ ሁሴን›› የሚል የማእረግ ስም እስከማግኘትም አድርሶታል።

መጨረሻ

ሰብስቤን ስላሳለፈው ዘመኑ ምን እንደሚሰማው ጠይቄው ነበር። ‹‹አይ አንተ! ልጅነት፣ በዚያ ላይ አለማወቅ ከንቱ ነው። አሁን አሁን ሳስበው የብዙ ሰው ህይወት እንደጎዳሁ ይገባኛል። ለነገሩ እኔም በእስራትም፣ በግርፋትም … ብዙ አይነት መከራ አሳልፌያለሁ። …..። ‹‹አሁን ኑሮህ እንዴት ነው?›› ‹‹አሁን እንደምታየኝ ያረጀሁ ይመስለኛል። ሰማኒያ ሁለት አመት የዋዛ አይደለም። … መንግስት የሰጠኝ መሬት አለኝ። እሱን እያሳረስኩ ይህችን ስልቻ እሞላታለሁ። አሁን ስራ አልሰራም። ፈጣሪ ይቅር ቢለኝ ጧት ማታ ከቤተክርስቲያን አልጠፋም። ቀሪውን ጊዜየን ደግሞ አረቂ እጠጣበታለሁ። …

 ይኸው ነው። በቃ።›› ሰብስቤን ለመጨረሻ ጊዜ ያገኘሁት በ2006 ነበር። በ2008 አካባቢ መሞቱን ተረዳሁ።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top