ጣዕሞት

መንታ መንገድ ቴአትር ተመረቀ

በግብፃዊ ደራሲ ተውፊቅ አል ሐኪም ተደርሶ በዓለማየሁ ገ/ሕይወት የተተረጎመው መንታ መንገድ ትያትር በርክት ያሉ የጥበቡ ቤተሰቦች እና አፍቃሪያን በተገኙበት መጋቢት 11፣ 2011 ዓ.ም በብሔራዊ ትያትር ተመርቆ ለዕይታ በቅቷል::

 ተክሌ ደስታ ባዘጋጀው በዚህ ቴአትር ከአስር አመት በኋላ ወደ መድረክ የተመለሰው ተስፋዬ ገበረሃና፣ ሺመልስ አበራ (ጀሮ)፣ እታፈራሁ መብራቱ፣ ሳሙኤል ተስፋዬ፣ ሚካኤል ታምሬ፣ ዳንኤል ተገኝ፣ ሕንፀተ ታደሰ፣ እዮብ ገረመው፣ ፋኡድ መሐመድ፣ ይትባረክ መሠረት፣ሰላማዊት በዛብህ እና ሌሎች ወጣት ተዋንያን ተሳትፈውበታል::

ቴአትሩን የመረቁት ተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሠሠ ለተዋናቹ አበባ ጉንጉን ከሰጡ በኋላ በሰጡት አስተያት፤ ተዋናዮቹ ቴአትሩን ጥሩ የተወኑት ከመሆኑ ባለፈ መልእክቱም ለትወልዱ አስተማሪ እንደሆነ ተናግረዋል::

 የቴአትሩ ተርጓሚ አቶ ዓለማየሁ ገ/ሕይወት በበኩላቸው፤ የአገር መሪን ጨምሮ ማንም ቢሆን በህግ የበላነት ስር እንደሆነ የሚያስገነዝበውን ይህን ቴአትር ከሁለት አመት በፊት ለማሳት ተሞሮ መታገዱን ገልፀው፤ አሁን በመፈቀዱ ለህዝብ ማድረስ ተችሏል ብለዋል::

6ኛው የጉማ የፊልም ሽልማት ተካሄደ

ሰሞኑን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር አዳራሽ በተካሄደው 6ተኛው ጉማ ፊልም ሽልማት የህይወት ዘመን ተሸላሚ ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ ሆነዋል:: በዚህ ኢትዮ ፊልም ባዘጋጀው አመታዊው ሽልማት መርሃግብር፤የክብር እንግዶች፣ የሙዚቃ ባለሙያዎች እና በርካታ ጥበብ አፍቃሪዎች ተገኝተዋል:: የውድድሩን ዘርፍ እና ተሸላሚዎቹ እነሆ ብለናል::

* የእድሜ ዘመን አሸናፊ ፕሮፌሰር ሀይሌ ገሪማ

* አጭር የተማሪዎች ፊልም አማኑኤል ዘሪሁን (ሙኑመ) እረከበ ፊልም

* ምርጥ አጭር ፊልም የአብስራ ዶጮ (በሌላው ጀግና)

* ምርጥ ድምጽ አናኒያ ሀይሉ (ድንግሉ)

* በምርጥ የፊልም መዚቃ (ድምፃዊ መሳይ ተፈራ፣ ዜማ አህመድ ተሾመ (ዲንቢ) እና ግጥም ወንደሰን – ሚስቴን ዳርኳት)

* ምርጥ የፊልም ስኮር ሱልጣን ኑሪ (በሲመት)

* ምርጥ የፊልም ሜክአፕ መሰረት መኮንን (በሲመት)

* ምርጥ የፊልም ስክሪፕት በሀይሉ ዋሴ (ዋጄ) በእናት መንገድ

* ምርጥ የፊልም ቅንብር (editing) ልኡል አባዲ (ወደ ኋላ)

* ምርጥ ፊልም ቀራጺ (Cinematography ) እውነት አሳሳኸኝ (ውሀ እና ወርቅ )

* ምርጥ ተስፋ የተጣለባት ተዋናይት ሕጻን ማክቤል (ሞኙ ያራዳ ልጅ ቁጥር 4 )

* ምርጥ ተስፋ የተጣለበት ተዋናይ በሀይሉ እንግዳ (ጃሎ)

* ምርጥ ሴት ረዳት ተዋናይት ዘነቡ ገሠሠ (ትህትና)

* ምርጥ ረዳት ተዋናይ ካሳሁን ፍስሀ ማንዴላ (ወደ ኋላ)

* ምርጥ መሪ ተዋናይት ሶኒያ ኖዌል (አንድ እኩል)

* ምርጥ መሪ ተዋናይ ኤርሚያስ ታደስ (አላበድኩም)

* በደሌ ስፔሻል የተመልካቾች ምርጫ ሚስቴን ዳርኳት

* ምርጥ የስራ መሪ (ዳይሬክተር) በሀይሉ ዋሴ (ዋጄ) በእናት መንገድ

* የአመቱ ምርጥ ፊልም በእናት መንገድ አሸናፊዎች ሆነዋል::

የተዉኔትና የሲኒማ መጻሕፍት በገበያ ላይ ዋሉ

በአቦነህ አሻግሬ (ተባባሪ ፕሮፌሰር) የተዘጋጀዉ“የዓለም ምርጥ ተዉኔቶች” እና ከሁለት የዉጭ አገር ምሁራን ጋር በመበተባበር ለህትመት ያበቋቸዉ ሌላኛው (CINE-ETHIOPIA: THE HISTORY AND POLITICS OF FILM IN THE HORN OF AFRICA ) ተሰኘው መጽሐፍ ለአንባቢ ቀረቡ::

የዓለም ምርጥ ተዉኔቶች፣ በአለም የታወቁ የስምንት ባለ አንድ ገቢርና የሦስት ባለ ሙሉ ጊዜ ተዉኔቶች በአጠቃላይ የአስራ አንድ ተዉኔቶች ትርጉም መድብል ነዉ::

 ተዉኔቶቹ ስመጥር ከሆኑ የአሜሪካ፣ የግብጽ፣ የራሺያ፣ የፈረንሳይ፣ የአርጀንቲና፣ የእስፔይን፣ የኢታሊያና የአየር ላንድ ደራሲያን ስራዎች ዉስጥ ተመርጠዉ ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ የተመለሱ ናቸዉ:: ስለ እያንዳንዱ ደራሲ የህይወት ታሪክና ሥራ፣ እንዲሁም ስለ የተዉኔቶቹ አጫጭር መግለጫም የተካተተበት ሲሆን በየማለቂያዉም የመለማመጃ ጥያቄዎች ታክለዉባቸዋል:: የገጹ ብዛት 583፣ ዋጋዉ ብር 230 ሲሆን፣ የታተመዉ በሜጋ አሳታሚና ማከፋፈያ ነዉ::

አቦነህ አሻግሬ፣ ከፕሮፌሰር አሌሳንድሮ ጀድሎዉስኪ (ሌጅ- ቤልጅየም ዩኒቨርሲቲ) እና የዶክትርና ተማሪ ከሆነዉ ማይክል ቶማስ (ለንደን ዩኒቨርሲቲ) ጋር በመሆን ፣ (CINE-ETHIOPIA: THE HISTORY AND POLITICS OF FILM IN THE HORN OF AFRICA ) በሚል ርእስ የአስራ ሁለት ምሁራንን ጥናቶች በተጓዳኝ- አርታኢነት ለህትመት አብቅቷል:: ይህ በአይነቱ የመጀመርያዉ የሆነ መጽሐፍ፣ በዋናነት የኢትዮጵያን እና የአፍሪካን ቀንድ ሲኒማ ጉዳይ የሚዳስሱ አስራ ሁለት ጥናታዊ ጽሑፎችንና የሦስት ታዋቂ ፊልም ሰሪዎችን ቃለ-መጠይቅ አካቷል:: የገጹ ብዛት 295፣ ዋጋዉ USA $ 40፣አሳታሚዉ ሚቺጋን እስቴት ዩኒቨርሲቲ ማተሚያ ነዉ::

ከየት ወዴት?

መጽሐፍ ገበያ ላይ ዋለ

የሰው ዘር ዝግመተ ለውጥና ማህበራዊ እድገት ያለማቋረጥ እንደሚጓዝ የሚያመለክተውና “ከየት ወደ የት?” በሚል ርዕስ በፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ የተዘጋጀው አዲስ መጽሐፍ ሰሞኑን ለንባብ በቅቷል:: ሳይንስና ሃይማኖት በዝግመተ ለውጥ ላይ የየራሳቸው አተያይና ፍልስፍና ቢኖራቸውም፣ መጽሐፉ አንዱ በልላው ላይ የሚጣረስ ሀሳብ እንደሌለበት ታውቋል:: 200 ገጽ ውስጥ 12 ምዕራፎች ያለው ይህ መጽሐፍ በ150 ብር በተለያዩ የመጽሐፍት መደብሮች በመሸጥ ላይ ይገኛል::

ኢትዮጵያ የአፄ ቴዎድሮስን ሹሩባ

ከእንግሊዝ ተረከበች

ዳግማዊ ቴዎድሮስ የአሥራ ሦስት ዓመት የንግሥና ዘመናቸው (1847-1860) ያበቃው በመቅደላ አምባ ከእንግሊዝ ሠራዊት ጋር በነበረው ጦርነት ፍጻሜ ላይ ‹‹እጄን አልሰጥም›› ብለው ራሳቸውን በጀግንነት ባጠፉበት ቅፅበት ነበር:: በጄኔራል ናፒር ይመራ የነበረው ጦር የመቅደላ አምባን ሲወር ከዘረፋቸው ቅርሶች በተጨማሪ ከንጉሠ ነገሥቱ አስክሬን ላይ ቁንዳላቸውን (ጉንጉን ፀጉራቸውን) ቆርጦ መውሰዱ ይታወቃል::

የታሪክ ሰነዶች እንደሚያሳዩት፣ ሁለት ቁንዳላን ቆርጦ የወሰደው መቶ አለቃ ፍራንክ ጀምስ ነው:: ጀምስ ሠዓሊም በመሆኑ በቃሬዛ ላይ የነበሩትን የአፄ ቴዎድሮስን ገጽታ በንድፍ በሚሥልበት ወቅት ነበር ቆርጦ የወሰደው:: የጀምስ ቤተሰብ ሁለቱን ቁንዳላዎች ከ100 ዓመት በኋላ እ.ኤ.አ. በ1959 ለብሔራዊ የጦር ሙዚየም ሰጥቷል:: በለንደን ከተማ ብሔራዊ ጦር ሙዚየም ለስድሳ ዓመታት የተቀመጠውን ሁለት ቁንዳላ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ ፈቃደኛነቱን ያሳየው ሙዚየሙ መጋቢት 11 ቀን 2011 ዓ.ም. ቁንዳላዎቹን ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ሒሩት ካሳው (ዶ/ር) አስረክቧል::

ሁለቱን ቁንዳላዎችን የያዘው ሳጥን ቅዳሜ መጋቢት 14 ቀን አዲስ አበባ ገብቷል:: በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም በጥብቅ ስፍራ እንደሚቆይ የሙዚየሙ ዳይሬክተር አቶ ኤፍሬም አማረ ገልጸዋል:: በብሔራዊ የጦር ሙዚየም በነበረው ሥነ ሥርዓት ላይ ዲስኩር ያሰሙት በለንደን የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍሥሐ ሻውል፣ በመቅደላ ጦርነት በእንግሊዝ ወታደሮች የተዘረፉት ቅርሶች እንዲመለሱም ጥሪ አቅርበዋል::

በርክክብ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ከተገኙት መካከል በለንደን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጎርጎርዮስ ይገኙበታል::

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top