ማዕደ ስንኝ

ሀገሬ!

…እንዲህ ቁጭ ብዬ

ትላንትን ሳስብ መለስ ብዬ

ትዝታሽ ውስጤን አመሰ፤

ጠረንሽ ሁለንተናዬን ዳሰሰ::

…አዝመራሽ አይነቱ፣

የጤፋ ማሳ፤ የስንዴ በቆሎ ’ሸቱ፣

የጋራ ፊፉ ሽቅበት፣

የጥሻ ጥሹ ቁልቁለት፣

ተስረቅራቂው የዋሽንት ዜማ፣

ለጥ ያለው ባድማ…

የጉብሎች አምባር፣ አልቦ፣ ዶቃ

የቡሬ፣ የዳለች፣ የመጋል ቡረቃ…

ታየኝ ተሰማኝ በሩቁ፤

ታወሰኝ ግዙፍ ከደቂቁ::

ሀገሬ!

የትውልድ መንደሬ

ተግ! ቢል ትዝታሽ ህሊናዬን ምሶ፣

የያኔ እኔነቴን ጠቅሶ፣

ጅራፍ ደበሎ ቁምጣዬ፣

የመደብ ድብዳብ ላይ መኝታዬ፣

ገሳ ጥላ ከለላዬ፣

የወንጭፍ ማጥቂያ መከታዬ፣

የባልንጀሮቼ ሩጫ፣

የቀበሮዎች ሩጫ፣

የገደል፣ ሸንተረር ዱሩ፣

የበዓላት ንግሠ ክብሩ…

ታየኝ፣ ተሰማኝ ከሩቁ፤

ታወሰኝ ግዙፍ ከደቂቁ::

ሀገሬ!

የትውልድ መንደሬ

ድንበርሽ ሳይሰፋ- ግዛትሽም ሳይጠብ፣

ጠረንሽ ሳይቀይር- ከለርሽም ሳይውብ፣

እንደነበርሽ ሆነሽ ላገኝሽ ተመኘው፤

ሳላይሽ እንዳላልፍ ዛሬን በጣም በጀሁ::

ምንጭ – ሳተናውና ልሎች…

(የአጫጭር ልቦለድና ግጥም መድብል)

ደረጀ ትዕዛዙ

ባሻ አሸብር ዳግመኛ በአሜሪካ

(የቅኔ ዘረፋ)

የሞጃው ባላባት ባሻ አሸብር ጉዱ

ጃንሆይ ልከዋቸው አሜሪካን ሄዱ::

ዋሽንግቶን ዲሲ ሽርሽር ሲሉ

የኬክ ቤት አዩና ሊቀምሱት ከጀሉ::

ከውስጥ ገቡና ጠረንጴዛ ይዘው

ነጩን ቦይ ጠቀሱት፣ “እስቲ ያንን አምጣው”

ቦዩም ተሸቆጥቁጦ፣ ፈራ ተባ እያለ

“ጌቶች ለእርስዎ የሚሆን እዚህ ምንም የለ”

“ኧረ!”

“ለነጮች ብቻ ነው ኬኩ የተጋገረ”

“ማን መሰልኩህ አንተ? የማነህ ጠምባራ?”

አሉና ዠለጡት በያዙት ከዘራ::

ባለ ቤቱ መጣ ወዲያው ፖሊስ ጠራ

ፖሊሱም ቀፍድዶ ወስዶ ከዘብጢያ

ገፍትሮ ጣላቸው እንደገዛው ባሪያ

“የሰለሞን ዘር ነኝ! የዛጉኤ የሳባ!”

ብለው ቢፎልሉም ኢምንትም አልገባ::

እምቦቲቶ ይዞ ዳቦ የሚገምጠው

በሙሉ ጥቁር ነው ወኽኒውን የሞላው::

“ብራዘር እንካ ሳንቲም!” ብለው ወረወሩላቸው::

“ጮማ እንዳልቆረጥሁኝ፣ እንዳልተጎነጨሁ ጠጅ

ራብ ይግደለኝ ያባ ቢላዋ ልጅ!

ከሻንቂላ ጋራ አልገምጥም ሀምበርገር!”

ብለው አድማ መቱ ጉደኛው አሸብር::

ማነታቸው ታውቆ ባለሟልነቱ

ተለቅቀው ተፈቱ አድረው በማግሥቱ::

ሆኖም “ፔርሶና ኖን ግራታ” ተብሎ ተፈርዶ

ዲፖርት ተደረጉ ወይ ነዶ ወይ ነዶ!

“እርም አሜሪካ እንግዲህ! ምድርሽን ብረግጠው

ዐይኔን ላፈር ያርገው!” ብለው ተገዝተው፣

የሞጃው ባላባት ገቡ ሀገራቸው::

ወዲያው እንደገቡ

ግቢ ተጠሩና፣ ጃንሆይ ፊት ቀረቡ::

“የተላክህበትን መከታተል ፈንታ

አያገባህ ገብተህ ሰው ሀገር ሁካታ?”

ንጉሡ ተቆጡ፤

ባሻ ደነገጡ::

መሬት እሲኪልሱ ለጥ ብለው ሲነሱ

“ቀልቀሎ ስልቻ!- ስልቻ ቀልቀሎ!”

ብለው ተወገዙ::

“ንሳ! ከከተማ ወጥተህ- ርስትህ ተቀመጥ!”

ተብለውም ተጋዙ::

ዘመን አለፈና የፍየል ወጠጤ

መኳንንቱን ሲያስር፣ ሚኒስትሩን ሲገል ሙልጭ ወጡ አጤ::

ሱካር በሽታና ግዞተኛነቱ፣

ባሻን ረዳቸው ካገር እንዲወጡ::

እርም ወዳሉበት አማሪካን አገር

ተመልሰው ሔዱ ጉደኛው አሸብር::

ሆኖም አልቀናቸው በዛባቸው ጣጣ

እግራቸውን ከልተው አረጉት ቆራጣ::

ኩላሊት ቀየሩ ቀጥሎም ጉበት፣

ዐይናቸውን አውልቀው ሌላ ተኩበት!

“ወይ ጦቢያ! ወይ ጦቢያ!

ወይ ጦቢያ! አገሬ- ወዲያ!

ምን ሕይወት አለና ከእንግዲህ ወዲያ!

“እዚህ ቅበሩኝ!” ብለው ተናዘዙ

አይጣል ነው አያድርስ የሰው ልጅ መዘዙ::

ልብ ብለህ ስማ ቆፍጣናው አበሻ

ካልተጠነቀቅህ ከሆንክ ሆደ ባሻ

ያሸብር ይሆናል ያንተም መጨረሻ::

ተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሠሠ

05፣11፣06

ስፕሪንግ ፊልድቪርጂኒያ

ዩ.ኤስ.ኤ

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top