አጭር ልብወለድ

ጓ ደ ኛ ች ን ማ ን ነ ው? (ወ ስ ዋ ሴ ተ ረት _ Dilemma tale stor y )

አንድ ጊዜ አንበሳ፣ ነብር፣ ጅብ፣ እባብና “አጎት” እያሉ ትናንሽ አራዊት የሚያፌዙበት አንድ መሠሪ ጉሬዛና አንድ ደንቆሮ ውሻ የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ሲሉ፤ የትውልድ አገራቸውን ለቀው ወደ ሌላ ባእድ አገር ተሰደዱ አሉ። እዚያም አዲስ አገር እንደደረሱ አልቤርጎ ብጤ ያዙና፤ ታየሩም ተፍጥረተ ዓለሙም እየተለማመዱ ሰነባበቱ። የኋላ ኋላ ያልቤርጎው ወጪ እማይቀመስ ሆነባቸውና፤ ባንበሳ አሳሳቢነት ለየብቻቸው ቤት ለመከራየት ወሰኑ።

 ምንም እንኳን ይህ የመጡበት አገር ኑሮ በምግብ፣ በመጠጥ፣ በልብስና በትራንስፖርት ረገድ በሽ በሽ ቢሆንም፤ መጠለያ በማግኘት ረገድ ግን የዋዛ አልነበረም። ለብዙዎች ቤት መከራየትም መግዛትም አቅምን የሚፈታተን ሆነ። ለማንኛውም ስደተኞቹ ባዲሱ ያንበሳ ሃሳብ መሠረት የየግላቸውን ቤት ለመከራየት በየበኩላቸው ተሰማሩ። ሆኖም ትርፉ ድካም ብቻ ሆነ። የቤት እጥረት በእጅጉ ያየለበት አገር ነውና በየግላቸው በያቅማቸው የሚከራዩት ቤት አጡ። እናም አዲስ ሃሳብ መነጨ ካጎት ጉሬዛ!… ሁሌም ማንም ሳይቀድመው ኮሚቴ የማቋቋም ወይም የማፍረስ ሃሳብን በማመንጨት በሽታ የተለከፈ በመሆኑ፤ ይህንን ሃሳብም ማቅረቡ ለዘዴው ነው።

መሠሪው ጉሬዛ “በየግላችን ቤት ተከራይተን ለመኖር አቅማችን ካልፈቀደ፤ ለምን አንድ ትልቅ ቤት በጋራ ተከራይተን አንኖርም? ቢያንስ ቢያንስ ያገር ልጅነታችን እራሱ በራሱ፤ ባንድነት አስተሳስሮ ሊያኖረን የሚችል ነው…” ሲል አበክሮ አሳሰበ። እሱ የተነፈሳትን መልሶ በማስተጋባት ልክፍት ታመው የሚኖሩት አያ ጅቦና ደንቆሮው ውሻ “ድንቅ ሃሳብ ነው!… እጹብ ነው!… ” ሲሉ አሟሟቁት። ሌሎቹ ግን ጉዳዩን ባርምሞ በማየት፤ አንድም ሌላ አማራጭ በማጣት አንድም እስቲ ይሞከር… በሚል ዓይነት አንድምታ ጸጥ አሉ። እነ አያጅቦ ግን ከሰማይ መና የወረደ ያህል ጭራቸውን እየቆሉ ላራዊት ዝርያ ሁሉ ዜናውን አዳረሱት። ደንቆሮው ውሻማ  ያው እንደልማዱ ጉዳዩ ቢገባውም ባይገባውም፤ ያደንቋሪ ጋጋኖነቱን ግብር ላንቃው እስኪሰነጠቅ ድረስ በመጮህ አስተጋባው።

 አጎት ጉሬዛም፤ “ወደደዱም ጠሉም ሁሎቹም ተዳብለው በመኖር ሃሳብ ላይ ከተስማሙልኝ ባስቸኳይ አንድ ጉዳይ ማስፈጸም አለብኝ” አለና አዲስና ተጨማሪ ሃሳብ ሰነዘረ። ይሄውም “እያንዳንዳችን የሁለት ሁለት ዓመት የቤት ኪራይ በቅድሚያ መክፈል አለብን” አለና ወሰነ። ሳይወዱ የግድ ይህንንም መፈጸም ነበረባቸው… ተዳባዮቹ።

 ምንም እንኳን እንደ አጎት ጉሬዛ ሃሳብ ሁሉ፤ ተዳብሎ መኖሩ ለሕብረት የሚረዳና ወጪንም በእጅጉ የሚቀንስ መሆኑ ቢታመንበትም፤ አንበሳን ግን የሆነ ጥርጣሬ ሰቅዞ ያዘው። ሦስት ጉዳዮችም ላይ አተኮረ። አንደኛው ስድስቱም የተለያዬ ጸባይ ያላቸውና በደካማ ጎናቸው ከመጡባቸው ሌላውን ከመተናኮል የማይመለሱ መሆናቸው ነው። ሁለተኛው ደግሞ “ለምን የሁለት ዓመት የቤት ኪራይ በቅድሚያ መክፈል አስፈለገ?” የሚለውና በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ “የመሠሪውን ጉሬዛ ሳጥናዔላዊ ዓይነት ተንኮል እንደምን መቋቋም ይቻል ይሆን?” የሚሉት ጥርጣሬዎቹ ናቸው። ሆኖም በነአያ ጅቦና በደንቆሮው ቦቢ አራጋቢነትና አጎብጓቢነት ምክንያት፤ ጌታ አንበሶ ያነሳቸው መሠረታዊ ጥያቄዎች ሳይመለሱ ተድበስብሰው ቀሩ።

 አጎት ጉሬዛ በነዚህ የስደት ጓደኛሞች ዘንድ የሚታወቅበት አስከፊ ጠባይ እንዳለው ሁሎቹም ያውቃሉ። መሠሪው ጉሬዛ ሲያዋሽክ፡ ሲያስተማማ፡ ሲያጎባድድና ሲያናክስ ውሎ እኩለ ሌሊት ላይ ብቻ ነው – በእንቅልፍ የሚሸነፈው። እርስ በርስ እያጋጨ መልሶ እሱ እራሱ አስታራቂ ሆኖ በሌሎች ድክመት መሳለቁም የሚጠቀስለት እኩይ ባህሪው ነው።

የአንበሳን ጥርጣሬና ፍርሃት ከፊሎቹ ቢቀበሉትም፤ በልባቸው “ከእንጨት ሽበቱ ጉሬዛ ሸርና ተንኮል አምላክ ይጠብቀኝ…” እያሉ አብሮ መኖርን ከመቀበል ሌላ አማራጭ አልነበራቸውም። የሆነው ሁኖ እያንዳንዳቸው የሚጠሉትን መጥፎ ጠባይ በዝርዝር አውጥተው እርስ በርስ በመነጋገር፤ ለወደፊቱ ተራርመው፡ ተጠባብቀውና ተከባብረው አብረው ሊኖሩ ከሚያስችላቸው የስምምነት አውድ ላይ እንዲደርሱ አያ ነብሮ በማሳሰቡ፤ ሁሉም በየበኩሉ የሚጠላውን ጠባይ ማስመዝገብ ቀጠለ።

 “እኔ በበኩሌ የጠዋት እንቅልፍ ስለምወድ ማለዳ የሚቀሰቅሰኝ አንዳችም ነገር አልፈልግም። ከዚህ ሌላ ግን ከናንተ ጋር ለመኖር የሚያዳግተኝ የተለዬ ጠባይ የለኝም” አለ አንበሳ።

 “እኔም ብሆን እፊት እግሮቼ ላይ አገጬን አስደግፌ ተኝቼ ባለሁበት ሰዓት፤ ማንም እንዲያናግረኝ አልፈልግም። በተረፈ ከዚህ የተለየ ክፉ ባህሪ የለኝምና ከሁላችሁም ጋር ተስማምቼ እኖራለሁ የሚል እምነት አለኝ” አለ ነብር።

 “እኔም በበኩሌ ክፉ አመል ቢኖርብኝ አንድ የሌሊት ጣጣ ብቻ ነው። ሌሊት ሌሊት ጥምብ ፍለጋ ሄጄ ንጋት ላይ ወደ ቤት ስመለስ፤ ማናችሁም ብትሆኑ ቀፈቴን አይታችሁ፤ ‘አቤት ሆድህ ምን ያህላል?’ ብላችሁ እንድትጠይቁኝ አልፈቅድም” አለ ጅብም በበኩሉ።

 እባብም “እኔም በበኩሌ ጭራዬን ማንም እንዲነካብኝ አልፈልግም። ተነካብኝ ግን አሱን አያድርገኝ” አለች ክፉ ጠባይዋን ሳትሸሽግ።

 አጎት ጉሬዛም በበኩሉ “ትናንት እንዲህ እንዲህ ነበርክ… እያለ አሮጌ መታወቂያዬን እያገላበጠ የሚያሳጣኝ አልወድም። እንዲህ ያለው ውስጥ አዋቂ ከምድረ ገጽ እስኪጠፋ ድረስ እንቅልፍ የለኝም” አለ።

 አስጠሊታውና ደንቆሮውም ውሻ በበኩሉ የሚጠላውን ጠባይ ተናገረ። “‘በምኒልክ ጊዜ የደነቆረ… ’ የሚባለውን ምሳሌ በምንም መልኩ ቢሆን በኔ ላይ ሊያውል የሞከረ ወዮለት!…” አለ።

 ስድስቱም በየግላቸው የተለዬ ባህሪያችን ነው የሚሉትን ከተገላለጡ በኋላ፤ አንዱ ያንዱን ፀባይ ችሎ በጋራ ለመኖር አማራጩ መንገድ ይህ ብቻ መሆኑን አመኑ። በስምምነታቸውም መሠረት የደባልነት ሕይወታቸውን ቀጠሉ።

 ከእለታት አንድ ቀን ማለዳ ላይ፣ ጅብ የወደቀ ጥምብ ሲሰለቅጥ አድሮ፣ ሆዱ ድብኝት አክሎ ወደ ቤት ተመለሰ። ገና ከደጃፍ ሲደርስ፤ የኮቴውን ድምጽ አጥፍቶ በሩን በቀስታ ከፍቶ ገባ። ይሄኔ መሰሪው ጉሬዛ አየውና፤ “ዛሬ እርስ በርስ አባልቼ ይቺን ቤት ብቻዬን ካልተቆጣጠርኳት እናቴ አልወለደችኝም” አለና በልቡ ማለ። ወዲያው ወደ ነብር ጆሮ ተለጠፈና የሆነ ነገር አንሾካሾከለት እንደልማዱ። ይህኔ፤ አያ ነብሮ የፊት  እግሮቹ ላይ አገጩን አንተርሶ ካደፈጠበት ቀና ሲል፤ የጅቡ ሆድ መሬት ሊነካ ተንጠልጥሎ ሲመለከት፣ ጅብን አናገረው።

 “አቤት!… አቤት!… ሆድህ ምን ያህላል?” አለው ባድናቆት… አያ ነብሮ። ይሄኔ አጎት ጉሬዛ እንጣጥ አለና እበሩ ላይ ተቀምጦ መሳቅ ጀመረ። ነገር ከከረረ እግሬ አውጪኝ ለማለት ነው… በሩን መያዙ።

 “ ‘ሆድህ ምን ያህላል?’ እንዳትሉኝ ብዬም አልነበር?” አለና በቁጣ አንድ ጊዜ ጩኸቱን ለቀቀው… አያ ጅቦ። በጅቡ ጩኸት ከእንቅልፉ የተቀሰቀሰው አንበሳ፤ “ማለዳ ላይ አትጩሁብኝ ብዬም አልነበር እንዴ?” አለና ከተኛበት ተወርውሮ፤ በቀኝና በግራ እጁ ጅብንና ነብርን ይዞ እርስ በርስ ግምባር ለግምባር ክፉኛ አላትሞ ወደማይመለሱበት ዓለም አሰናበታቸው። ሆኖም በንዴት እንደጦፈ እያጉረመረመ ወደ ኋላው ሲመለስ፤ የእባብን ጅራት ሳያውቀው ረገጠው።

 እባብም “ጭራዬን ብቻ እንዳትነኩብኝ አላልኩም ነበር?” ብላ ግምኛ ተቆጥታ፤ አፈር እየላሰች ከተኛችበት ቀና ብላ፤ አንበሳን በመርዟ ጠቅ አደረገችው። አንበሳ እንደማዞር፡ እንደማጥወልወል አደረገውና ተሽከርክሮ ደንቆሮው ውሻ ላይ ድብ ሲልበት፤ የሆነውን ሁሉ ሳይሰማ በቅዥት ዓለም ሲዋልል የነበረው ደንቆሮው ውሻ “ህቅ…” አለና ትንፋሹን ውጦ ቀረ።

 አጎት ጉሬዛ ሉሲፈራዊ አንጀቱ እስኪቆስል በደስታ ሲንከተከት ቆይቶ፤ እሱ በጫረው እሳት እርስ በርሳቸው ተባልተው ያለቁትን “ጓደኞቹን” አስከሬን በድል አድራጊነት እያስተዋለ፤ “ወንዳታ አንከረባበትኳቸው!… ዋው ይህን የመሰለ ቪላ በነጻ ለሁለት ዓመት… አይ ዘዴ አይ ጥበብ!… ቅቅቅቅቅቅ!….. ያውም ብቻዬን!…. ዋው!….“ ብሎ ጉራውን አወራርዶ ሳይጨርስ፤ እባብን ከማዶ ተገሥላ በማየቱ እግሬ አውጪኝ ብሎ ፈረጠጠ።

 “አጎት ጉሬዛ ተነቃቅተናል!… ሁለተኛ ተዚህች ቤት ድርሽ አትላትም!… ቀንህን ጠብቅ! ላንተም የጓደኞችህ ቀን ይቆረጥልሃል… አንተ የሞቀበት አጨብጫቢ… የበላህበትን ድስት ሰባሪ… ገጸ ጻዲቅ ግብረ ምርቅ… ቀላል… የቀትር ጋኔል!…” ወረደችበት። ግና ነፍሱን ሊያድን ፈጥኖ በመራቁ… ልበ ሳጥናዔሉ ከፊሉን አልሰማትም።

 እባብ የትናንት ወዳጆቿን የሚያቃብራት አጣች እንጂ፤ ቤቱንስ በሰፊው ለብቻዋ ይዛው ቀረች ይባላል። ያልታደለች…

 (በጥንታዊው አገርኛ የምድጃ ዳር ተረት ላይ የተመሠረተ

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top