ቀዳሚ ቃል

ያለፉትን ስናከብር የወደፊቶችን ማፍራት ይቻለናል

በማንም ሊገታ የማይችል ተፈጥሯዊ ህግ ሞት ነው። ማናችንም ብንሆን በዚች ዓለም የምንኖረው እስከተፈቀደልን ዕድሜ ድረስ ነው። የልደታችንን መቼነት፣ የትነት እና እንዴትነት እንደማናውቅ ሁሉ፤ ህልፈታችንንም አናውቀውም። ዋናው ቁም ነገር ይድላንም አይድላን በኖርንበት ዘመን መልካም እያሰብን፣ መልካም እየሰራን ማለፍ ነው። ያኔ ቀሪው ትውልድ ያስበናል። ስራችንና ማንነታችን ለአርአያነት የሚበቃ ከሆነ ደግሞ ትርፋችን እጥፍ ድርብ ይሆናል። በእንዲህ አይነት ህይወት ውስጥ የሚያልፉ የጥበብ ሰዎች በበጎ መታወሳቸው አይቀርም። ህልፈታቸው ሲሰማ ግን ያስደነግጣል።

 ይህን መንደርደሪያ ያስቀደምነው ያለምክንያት አይደለም። ሰሞኑን ሦስት የኪነት ሰዎችን በተከታታይ ማጣታችን በጥበቡ ዘርፍ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት ለማመላከት እንጂ። በሁለገብ ከያኒነታቸው፣ ባላቸው እውቀትና በታሪክ ነጋሪነታቸው የሚታወቁት፤ በዚህም «ተንቀሳቃሽ ቤተ መዘክር» የሚል ቅጥያ የተሰጣቸው አበው ከያኒ ጌታቸው ደባልቄን አጥተናል። ከአገር አልፎ ዓለምን ያስደመመው ድንቅ የዋሽንት ተጫዋች ዮሐንስ አፈወርቅ ተለይቶናል። በትግርኛ ዘፈኖቹ የሚታወቀው ድምጻዊ አሚር ዳውድ ማረፉንም ሰምተናል።

የእነዚህ ከያንያን ህልፈት ጥበቡን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መጉዳቱ አይቀርም። ጥቂትም ቢሆን ወጣቱ ትውልድ ከእነዚህ የጥበብ ሰዎች የሚቀስመው እውቀት ጥበባዊ ዋጋውን ከፍ ያደርገው እንደነበር አይጠረጠርም። ሌላው ጉዳት የቤተሰባቸው፣ በተለይም የልጆቻቸው መሆኑ አያጠያይቅም። አብዛኞቹ የጥበብ ሰዎች ከራሳቸው አልፎ ለቤተሰቦቻቸው የሚተርፍ ጥሪት ሳያስቀምጡ፣ ቤት ሳይኖራቸው ነው የሚያልፉት። በተለይ ቀደም ባለው ዘመን ለስራቸው፣ ለላባቸው የሚደርሳቸው ክፍያ ሕይወታቸውን የሚለውጥ አልነበረም። ሌላው ቀርቶ ሲታመሙ መታከሚያ የሚሆናቸውን ገንዘብ ሳይቋጥሩ ድንገት ህልፈታቸው የሚሰማ ከያንያን ቁጥር ቀላል አይደለም። የምንወዳቸው፣ የምናከብራቸው እነዚህ የባህል አምባሳደሮች አሁንም ከኢኮኖሚ ጥገኝነት አልወጡም፡፡

አገራችን እንዲህ ያሉ ብርቆችን ከተመጽዋችነት የምታወጣበት መንገድ ካልፈጠረች ሌላ ብርቆችን የመፍጠሯን ነገር አጠያያቂ ያደርገዋል፡፡ በተለያዩ የኪነጥበብ መስኮች ሃገራቸውን ያገለገሉና ለጥበብ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ብዙ ከያንያን ዕድሜያቸው ከገፋ በኋላ የሚያስታውሳቸው አልተገኘም። ለእነዚህ አንጋፋ ባለሙያዎች ክብር አለመስጠታችን በመስኩ እየታየ ላለው ክፍተት አይነተኛ ምክንያት መሆኑም አይካድም።

የስነ ጥበብ ሞያተኞች ለዘመናት መብቶቻቸው እንዲከበርላቸው ደጋግመው ቢጮሁም መልስ ሳያገኙ የፈጠራቸውን ፍሬም ሳይበሉ በየተራ እየሸኘናቸው እንገኛለን፡፡ ዛሬም ያለፈ ስራቸውን እያሰቡ በየቤታቸው ሆነው በትዝታ የሚቆዝሙ አንጋፋ አርቲስቶች ጥቂት አይደሉም። ከፋም ለማም ዛሬ ላለው ጥበባዊ እድገት የከፈሉት ዋጋ ቀላል አይደለም። ቀደም ሲል በነበረው ኋላቀር አስተሳሰብ ምክንያት ሴቶች ወደ መድረክ ለመውጣት በማይችሉበት ዘመን የሴቶችን ሚና በመድረክ የተጫወቱ አበው ከያንያን ዛሬም እንዳሉ ማሰብ ይገባል።

መንግስት ለዚህ ችግር መፍትሄ በአጭር ጊዜ ካላበጀ በስተቀር ብርቆቻችንን ብቻ ሳይሆን፤ ባህላችንንም እንዲሁ ሸኝተን የሌሎችን ባህል ጠቅልለን የምንከናነብበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡ ስለዚህ ጠቢባንን ስናከብር፣ ስንደግፍ፣ ጥበብን እንደምናሳድግ ማመኑ እና ለተግባራዊነቱ መነሳቱ ነው የሚበጀው፡፡ ሰላም ለእናንተ ይሁን፡፡

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top