አድባራተ ጥበብ

የዶክተር እጓለ እሳቤዎች

4. የአውሮፓና የኢትዮጵያ መንፈስ

በቀደመው ክፍል የሥልጣኔን መንፈስ አይተናል። ቀጣዮቹ ተከታታይ አራት ምዕራፎች ስለ አውሮፓና ኢትዮጵያ የሥልጣኔ መንፈሶች ትንታኔ ያቀረበባቸው ናቸው። ሁለቱን ሥልጣኔዎች ለማዋሃድ ወይም “በተዋሕዶ ከበረ“ ወደሚለው ፍልስፍናው ከመሸጋገሩ በፊት የሁለቱን ሥልጣኔዎች ባህርያት ማሳየት ይፈልጋል። እኔም እንደሚከተለው ተመልክቸዋለሁ።

4.1. የአውሮፓ መንፈስ

 “የአውሮፓ መንፈስ” በተሰኘው ምዕራፍ የአውሮፓን ሥልጣኔ ፋውስታዊ ሥልጣኔ እንደሆነ ሽፔንግለር የተሰኘ ጀርመናዊ ደራሲን ጠቅሶ ይነግረናል። ፋውስታዊ ሥልጣኔ ምንድን ነው? ፋውስት በ15ኛው ክፍለ ዘመን የነበረ የእውቀት ሰው ነው። ዘመኑ ደግሞ አውሮፓውያን የሥልጣኔያቸውን መንገድ ለማበጀት ይጣጣሩበት የነበረው ዘመን ነው። ከመካከለኛው ዘመን የእምነት ሉዓላዊነት ወደ ምክንያታዊነት የተሸጋገሩበት ወቅት ነው። ሊቁ እጓለ ዶክተር ፋውስትን የአውሮፓ የሥልጣኔ መንፈስ ምስለኔ ያደረገበት ምክንያትም የሰውየው የግል ሕይወት የዘመኑን መንፈስ ስለሚወክል ነው። አዲስ ነገር ለማወቅ ካለው ከፍተኛ ጉጉት የተነሳ ያላንኳኳው የእውቀት በር የለም ይባላል። በመጨረሻም የጠንቋይ ቤት ድረስ እስከ መሄድ ደርሷል። የፋውስትን የመጣጣር ባህርይ የሚገልጸውን የጎቴን ግጥም ያቀርብልናል። የግጥሙ ጭብጥ ሰውን ለማሻሻልና ለመምራት፣ ለህሊና እርካታ የሚሆነውን እውቀት በመፈለግ በመኳተን አለሁ፤ ነገር ግን አልገለጥልህ ብሎኝ ይኸው ደስታን ሳይሆን ድካምን አተረፍሁ የሚል ተስፋ መቁረጥ ነው። (ገጽ ፵፯-፵፰/47-48)

ፋውስት እንዴት የአውሮፓን መንፈስ ይወክላል? የአውሮፓ መንፈስ የመጣጣር መንፈስ ነው። መጀመሪያ የሰው ልጅ በፈጣሪ ርዳታ የሚኖር ፍጡር ነው የሚለው የክርስቲያን ፈላስፎቹ እምነትንና ምክንያታዊነትን ለማስታረቅ ሞከሩ፤ በዚህ መሃል እነኮፐርኒከስ እነ ቤከን ከምድራዊ እስከ ሰማያዊ ያሉ ምስጢሮችን በሳይንስ መንገድ እንረዳለን የሚሉቱ ሳይንቲስቶቹ መጡ። በፍልስፍናው በኩል እነ ዴካርት የሰው ልጅ ከፍተኛ ምክንያታዊነት ተፈጥሮውን ተጠቅሞ እውነትን ማግኘት ይችላል የሚሉት ናቸው። በዚሁ በፍልስፍናው ትምህርት ቤት እውቀት በሥሜት ህዋሳት በሚገኝ መረጃ ላይ የተመሰረተ ነው የሚሉት እነ ሎክም አሉ። በመጨረሻም እነ ካንት መጥተው የሚታየው፣ የሚዳሰሰው ነገር ብቻውን የእውቀት ምንጭ መሆን ስለማይችል ህሊና በራሱ መንገድ አገናዝቦ የነገሮችን ምንነት ይነግረናል የሚለውን አስታራቂ ሃሳብ ይዘው መጡ። ባንድ በኩል ሳይንሳዊው መንገድ ሥጋዊ የሆነውን የሰው ልጆች ፍላጎት አቀርባለሁ ሲል ፊታውራሪው ቤከን ነበር። የሰው ልጅ እውቀት ትልቁ ጉልበቱ ተፈጥሮን ለሰዎች ፍላጎች ማስገበሩ ላይ ነው የሚለው አነጋገሩ ሲጠቀስለት ይኖራል። ይህም ዘመነ ተሃድሶ ይዞ መጣ። በሌላ በኩል ህሊና የማሰብና የመወሰን ክህሎቱን ተጠቅሞ ሰውን ከአስተሳሰባዊ ጭቆና ነጻ ያወጣዋል የሚለው በካንት ፊታውራሪነት የሚመራው ዘመነ አብርሆት ነው። በዚህ ዘመን ከተነሱት የሞራል እሳቤዎችም የነ ካንት በጎ ምግባር የምክንያታዊ በጎ እሳቤ መሠረት አለው የሚለው የካንት Categorical Imperative እና የነ ሚል የበጎ ምግባር መሠረቱ የሚያመጣው ውጤት ነው፣ ለብዙሃኑ ደስታ ምን ዓይነት አስተዋጽኦ ያደርጋል የሚል ጥቅመኝነት እሳቤዎች ተነሱ። በሃይማኖታዊ ረገድ የተነሳው የሉተር አስተሳሰብም የዚሁ መንፈስ አንዱ አካል ነው።

 መንፈስ ይሸበራል እንዲሉ የአውሮፓን መንፈስ እንደ ፋውስት ነፍስያ እያላጋው የፈረንሳይ አብዮት፣ የአሜሪካ አብዮት፣ የሶቭየት አብዮት፣ የካፒታሊዝምና የማርክሲዝም ሙግት፣ አንደኛውና ሁለተኛው የዓለም ጦርነቶች ወዘተ የሰውን ልጅ ሕይወት ተፈታትነውታል ማለት እንችላለን። የሰው ልጅ ምን ይፈልጋል? የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት ኤድዋርድ ሸፕራንገር የተባለን ምሁር ጠቅሶ ሰዎች እንደ ዝንባሌያቸው በአራት እንደሚከፈሉ ያስነብበናል። አንደኛው የኢኮኖሚ ሰው ነው። ገንዘብና ፍቅረ ነዋይ የዶክተር እጓለ ቀልቡን የነሳው የገንዘብ ሰው አለ። ፍላጎቱ በሃብት ላይ ሃብት መደረብ ነው። ሁለተኛው የፖለቲካ፣ የሥልጣን ሰው ነው። በማንኛውም መንገድ ሰዎችን መግዛት የሚፈልግ የሥልጣን ጥም የተጠናወተው። ሦስተኛው የእምነት ሰው ነው። ምድራዊውን ዓለም ሕደግዎ መንንዎ ብሎ ፈጣሪውን ፍለጋ ገዳም የሚገባው ዓይነት ሰው ነው። አራተኛው ደግሞ የእውቀት ሰው ነው። መመራመር፣ አዲስ ነገርን ማግኘት፣ የህሊናውን ጥያቄ ለመፍታት፣ የተፈጥሮን ምስጢር ለማወቅ ዘመኑን ለእውቀት የሰጠ ሰው ነው። “እዚህ የምንፈልገው የእውቀት ሰው የተባለውን ነው። … አየር አየራት ወጥቶ እመቀ እመቃት ወርዶ የዚህን ዓለም ጫፍና መሠረት ዳር ድንበር ለማወቅ ይፈልጋል። … ሌት ተቀን ታግሎ የሰውን የመንፈስ ግዛት ለማስፋት ያስባል፤ ይጣጣራል ይሳባል ይጎተታል፤ ወደፊት በመስገብገብ ይንጠራራይ። ከሰማይ ከዋክብት አንሥቶ እስከ ምድር ትሎች ድረስ ያሉት ሕይወቶች ምን የኑሮ ሕግጋት እንዳላቸው ለመረዳት ይጣጣራል።” (48-49/፵፰-፵፱)

 እንደ እጓለ እሳቤ የርሱ ፍለጋ ሰውን ትክክል ለመምራትና በገዛ ራሱ ለማሻሻል የሚሰራውን የእውቀት ሰው ነው። የሰዎችን ዝብርቅርቅ ሕይወት፣ የህሊና ቀውስ ሊፋቱ የሚችሉትን፣ አንድ ኢትዮጵያዊ ሊቅ (ከበደ ሚካኤል ?) እንዳሉት “የሐሳብ መሃንዲሶችን” ነው የሚፈልገው። እነዚህ የእውቀት ሰዎች የህሊናን አስተሳሰብ ወደ በጎው መስመር ለመቀየስ የሚጥሩት ናቸው። በባለፈው ክፍል የሰውን ልጅ በጭንቅ ጊዜ፣ ህሊና ሲታወክ ያንን ለመጠገን ሐሳብን አምጠው የሚወልዱት ሕመምተኞች ነው የሚፈልገው። “ፈላስፋው የሚፈልገው በሰውና በዓለማት ውስጥ ያለውን ሕግ ወይም ሎጎስ አግኝቶ በዚያ መሠረት ኑሮን ለማስተዳደር ነው። ፋውስት ጥረቱ ይህ ነበር። … የሰውን እግረ ሕሊና አንሻፎ የሚያሰነካክለውን ድንቁርና የሚባል ሞያሌ ከነሰንኮፉ ነቅሎ በቀጥታ እንደ ምኞቱ ሳይወድቅ ሳይነሳ የሚራመድበትን ዘዴ ለማስገኘት የሊቁ ተምኔት ነበር።” (ገጽ 49- 50/፵፱-፶)

 ይህ የፋውስት ተምሳሌታዊ መንፈሥ በአውሮፓ ሥልጣኔ እንዴት እንደተንጸባረቀ በቀጣዮቹ ገጾች ይገልጽልናል። ባጭሩ ከቁሳዊ እስከ መንፈሳዊ፣ ከሞራላዊ እስከ ማኅበራዊ ህግ ድረስ የሰዎችን ኑሮ የሚያሻሽለውን እድገት አበርክቷል፣ ትሩፋቱም ለሌላው ዓለም ተዳርሷል ሲል ይሞግታል።

 ቀጣዩ ምዕራፍ “የመንፈስ ትንሣኤ” የሚል ነው። ስለመንፈስ ትንሳኤ ባለፈው በሰፊው ተነጋግረንበታል። ባጭሩ ግን መንፈስ የሚነሳው ያለበትን መጠራጠር ሲጀምር ነው። መጠራጠር የፍልስፍና መቅድም ነውና ይህ መጠራጠር እንደ ግንደ ቆርቁር፣ ህሊናን ውስጥ ለውስጥ እየኮረኮረ ተረት የገነባውን ትልቅ የድንቁርና ህንጻ ይንደዋል። በዚያም መንፈስ ይነቃል። እንግዲህ ይህን የአውሮፓን የመንፈስ ትንሳኤ የተለሙት የጥንት ግሪካውያን ናቸው። “የሰማያቸው ንጹሕነት ሆነ ወይም የባሕራቸው ጽርየት፤ የምድራቸው የብስነት፤ የኑሯቸው ችግራማነት፤ ወይም ሁሉም ተባብረው፤ ምን እንደረዳቸው አይታወቅም፤ በዚያን ዘመን የነበሩ ግሪኮች ወይም በመጣፍ ስማቸው ጽርዐውያን ወደ ላይ ወደ አርያም የሚያወጣውን የሥልጣኔ መንገድ የተለሙ እነሱ ናቸው።” (ገጽ 53/፶፫) እነዚህ ግሪኮች የእውቀት ምንጭ የሆነችው በከተማቸው ስም የተሰየመችው አቴንስ የተባለችው አምላክ የልዕለ ኃያላን አምላክ ግንባር የፈለቀች ነች ብለው ያምኑ ነበር። የጥበብ ምንጯም አቴንስ ነች። በዚህ እሳቤያቸው የአውሮፓን አስተሳሰብ፣ የመንፈስ ትንሣኤ በፊታውራሪነት መሩት። ይህም የስልጣኔ ጉዞ ከአቴንስ ወደ ኢየሩሳሌም ተሸጋገረ፣ ከሎጎስ (ምርምር፣ ምክንያት፣ ህሊና) ወደ እምነት። ካለይ እንዳየነው እንደገና የሕሊና ትንሣኤው በዘመናዊ ፈላስፎችና ሳይንቲስቶች ጥረት ላይ

“ትምህርት ወይም እውቀት የሚባል ነገር ሕሊና በገዛ ራሱ ሕግጋት እየተመራ በመመራመር የሚገኝ መሆኑ ቀርቶ አንዲት መጣፍ በመተርጎም የሚገኝ ሆነ”

የተመሠረተ ሆነ።

ሌላው የአውሮፓ መንፈስ መገለጫው ውድድርን ፉክክርን ማበረታተቱ ነው። የአቴናውያንን የሶቅራጥሳዊ የክርክት መንገድን እዚህ ላይ ይጠቅሰዋል። ከዚህ የጥበብ መሻት፣ መወዳደርና ፉክክር የሚታወቀው የአውሮፓ መንፈስ ከአቴንስ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ መንፈስ ደክሞት ዝሎ ነበርና እመን የተባለውን ማመን ጀመረ። የክርስትና ትምህርት መጨረሻ መደምደሚያ ሆነ። “ትምህርት ወይም እውቀት የሚባል ነገር ሕሊና በገዛ ራሱ ሕግጋት እየተመራ በመመራመር የሚገኝ መሆኑ ቀርቶ አንዲት መጣፍ በመተርጎም የሚገኝ ሆነ።” ይህም በአውሮፓ መካከለኛው ዘመን የሚባለው ታሪክ ነው። ከዚያ በኋላ የተነሳው የሳይንቲስቶቹና የፈላስፋዎቹ መንፈስ የአውሮፓን ያንቀላፋ መንፈስ አነቃው። ሊቁ እጓለ ይህ የአውሮፓ ስልጣኔ በሁሉም ረገድ የተዋጣለት ነው የሚል እምነት አለው። ለዚህም በንጹህ ሕሊና የተገኘ የመጣጣር ውጤት ስለሆነ ትሩፋቱ በሌላውም ላይ እንዲሆን የራስ ማድረግ ያስፈልጋል ብሎ ይሞግታል። (ገጽ 58/፶፰)

እንዴት አድርጎ? ሁለት አማራጭ አለ። “አንደኛው ይህንን ብቻውን ተቀብሎ ያለፈውን ያረጀ ነገር ነው ብሎ ጨርሶ መተው ነው። ሁለተኛው ደግሞ ሰው ራሱን ፶ ለመካድ በላጲስ ለመፋቅ ስለማይችል የራሳችን ብለን የምንጠራውን ከአዲሱ ከምዕራባዊው ጋር በማጻመር በማዋሃድ ወደ ፊት አዲስ ህብር በመፍጠር እንሂድ የሚል ነው። ሁለተኛውን የምንከተል መሆናችን ግልጽ ነው። ስለዚህ እሊህ ሁለቱ የሚጻመሩበትን ዘዴ ከመተንተናችን በፊት ሁለተኛውን ተጻማሪ [ማግኘት ግድ ይለናል]።” (ገጽ 58/፶፰) በዚሁ ሁለት ምዕራፎች ወደ ሰጠው የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ያዘግማል።

 4.2. ያሬድ ወይም ስለ ኢትዮጵያ ሥልጣኔ (I እና II)

 የእጓለ ጉዳይ ከኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ፍልስፍና ጋር የተያያዘ ስለሆነ፣ ትምህርት ደግሞ ሰዎችን ወደ ሰውነት ክብር ከፍ የማድረግ ሥራ ስለሆነ ንቡርን ከመጤው፣ ዘመናዊውን ከባህላዊው ጋር ማዋሃድ አስፈላጊ ነው። ታዲያ ኢትዮጵያ አውሮፓዊን ስልጣኔ ለመቀበል እጇን በዘረጋችበት በዚህ ወቅት ማዕዱን ማቅረቢያና ማባያ የሚሆን ከጓዳዋ የተቀዳ አእምሯዊ ንብረት አላት ወይ? የሚለው ወሳኝ ጥያቄ ነው። የዚህን ምዕራፍ መክፈቻው ያደረገው የግእዝ ነው። የቃሉ ትርጓሜ አምላክን ሰማያውያን ኃያላን ሳይቀሩ ያመሰግኑታል፣ ቃሉ እውነት፣ ነገሩ ሁሉ የታመነ ለሆነ አምላክ፣ አመሰግነዋለህ፣ እገዛለታለሁ፣ ከፍ ከፍም አደርገዋለሁ፣ መንገዱ ሁሉ የቀና ነውና መንግሥቱም ዘለዓለማዊ ነው። የሚል ይዘት አለው። ምድራዊ ተገዥነትና ሰማያዊ ተስፋን ያዘለ ቃል ነው።

 ይህ ከያሬዳዊ ስልጣኔ ጋር ምን ያገናኘዋል? የአውሮፓን መንፈስ በፋውስት ወካይነት እንዳብራራው ሁሉ የኢትዮጵያን መንፈስም በቅዱስ ያሬድ ይወክለዋል። ይህ አጠቃሏዊነት ኢትዮጵያዊውን መንፈስ እንደበደለው ይሰማኛል። በርግጥ እምነት፣ ተፈጥሮን ማድነቅ፣ ለልእለ ተፈጥሮ መገዛት ኢትዮጵያዊ መገለጫ ሊሆን ይችላል። የያሬድ መንገድ ምንድን ነው? የተፈጥሮን  ደንባዊነት፣ ሥርዓቱን በመገንዘብ አንድ ሰራኢ መጋቢ እንዳለ ማመን፣ ለሚያገኘው ረድኤት በማመስገን ለዚያ ሰራኢ መጋቢም መገዛት ነው። (ገጽ 59/፶፱) የዚህ ሥልጣኔ መሠረቱ እምነት ነው። እምነቱ ደግሞ ከሚታየው ነገር ጀርባ የማይታየውን ገፋኤ ኃይል እንዳለ ይነግረዋል። ለዚህ ኃይል መገዛት፣ ለህጉ ወይም ለደንባዊነቱ ተገዥ መሆን ደግሞ የሥነ ምግባር መሠረት ይሆናል። ስለዚህ አንክሮና ተደሞ እምነትን ወለዱ፣ እምነት ፈጣሪን ገለጠለት፣ ከዚህ በመነሳት ለዚያ ፈጣሪ ተስማሚ የሆነን ማንነት ለመያዝ ሥርዓት ወይም በጎ ምግባር አስፈላጊ ሆነ። ያሬዳዊ ሥልጣኔ ይህንን በእምነት የሚገለጥ አምላክ ማግኘትና ለሱ ተገዥ የሚሆኑበትን ህግ፣ ሥርዓት መፍጠር ላይ የተጠመደ መሆን አለበት።

 ያሬዳዊ ሥልጣኔ ለምን እምነትን መሠረት አደረገ? እዚህ ላይ ነው ሰው ምንድን ነው? የሚለው ጥያቄ የሚነሳው። እጓለ ስለዚህ ነገር ሲያብራራ ፈላስፎች ዓለምን ለሁለት ከፍለውታል። መንፈሳዊና ሥጋዊ (ቁሳዊና መንፈሳዊ) ብለው። “ስለ ሰውም ሲናገሩ አካላዊም መንፈሳዊም ነው በማለት የሁለት ነገሮች ተካፋይ፤ የሁለት ዓለማት ነዋሪ፤ ዜጋ፤ መገናኛ አድርገው ይመለከቱታል::” (ገጽ 61/፰፩) ሰው የሁለቱም ዓለማት አካል እንደመሆኑ የሚታየውና የማይታየውን ያስባል ማለት ነው። ስለ ሁለቱም ዓለማት ግድ ይለዋል። ስለ ሁለቱም ዓለማት እውቀት ሊኖረው ይችላል። ስለወዲያንዲያው መንፈሳዊ ዓለም የሚኖረን እውቀት ግን እምነት የታከለበት ነው። ከዚህ ጋር እጓለ በተደጋጋሚ የሚጠቅሰው ፈላስፋው ካንት ይስማማል። በክርስትናው የሥነ ፍጥረት አረዳድ ደግሞ ሰራኤ መጋቢ የሆነ ፍጹም አምላክ አለ የሚለው ላይ ይነሳና “ሥርዓተ ሰማያት ተሠርዓ በምድር” ሰማያዊ ሥርዓት በምድርም ተሰራ የሚል ትስስርን ለመፍጠር ችሏል።

 የአውሮፓውያንና የኢትዮጵያውያንን ሥልጣኔ የሚያለያየው ይኸው የሰማይና የምድር ትርክት ጉዳይ ነው። እንደ እጓለ አገላለጽ አውሮፓዊ ሥልጣኔ ማዕከል ያደረገው ሰውን ነው። Anthropocentric የሆነው እሳቤ ሰው ሁሉንም ነገር ማድረግ ይችላል ከሚለው እሳቤ ይመነጫል። ኢትዮጵያዊው ሥልጣኔ ደግሞ መለኮትን ማዕከል ያደረገ ነው። Theocentric የሆነው የሥልጣኔ አየር አላህ፣ እግዚአብሔር፣ ዋቃ፣ ረቢ የዓለም ሰራኢ መጋቢ ሲሆን ሰው ደግሞ በአምሳሉ ተፈጥሯልና በተሰጠው የአማላካዊነት ጸጋ ራሱን የሚያጸናበት፣ ህላዌውን የሚመራበት ህግ፣ ፍልስፍና፣ የኑሮ ዘዴ፣ ማኅበራዊ ሥርዓት ይሰራል ማለት ነው። የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ያሬዳዊ እሳቤው ይኸው ነው።

 ያሬዳዊ እሳቤ የነገረ ህልውና፣ የህግና የሞራሊቲ እሳቤው እንደምን ያለ ነው? የነገረ ሕልውና Metaphysics መሠረቱ የሥነ ፍጥረት ትርክት ነው። ይህ ትርክት ሁለት መሠረታዊ ነገሮችን የያዘ ነው። ፈጣሪና ፍጡርን። ፈጣሪ ሃያልነቱና ፍጹማዊ ጥበቡ ዓለምን ካለመኖር ወደ መኖር አመጣው። ያንን ሲያደርግ ደግሞ ዓለም የምትመራበትንም ህግ አብሮ ነው። ይህ ደንባዊነት ፈላስፋው ሌብኒዝ እንደሚለው pre-established harmony ነው። ይህ ህጋዊነትና ደንባዊነት በምድራዊው የማኅበራዊ ሕይወት ላይም የሚጸና ነው። ቅዱስ ያሬድ ዓለም በሙሉ በሥርዓቷ እንደ ተቀነባበረ ሙዚቃ እግዜርን ታመሰግናለች ይላል። የሞራል እሳቤው የሚመነጨው ከሁለት ነገሮች ነው። አንደኛው ማንጸሪያ ከሰዋዊ ምክንያታዊነቱ ይመነጫል። ይኸውም ነፍስ ለባዊ ስለሆነች በማገናዘብ በጎውን ከክፉ፣ እውነቱን ከሐሰት የመለየት ክህሎት አላት። የያሬዳዊ ስልጣኔ አንዱ መገለጫ ነፍስን አገናዛቢ (Rational)፣ ተናጋሪ ቋንቋን የምትጠቀም፣ እንዲሁም ዘለዓላማዊት ናት የሚለው እሳቤ ነው። ፈላስፋው ወልደ ሕይወት እንደሚለው፣ ዘለዓላማዊነቷ የሥነ ምግባር መሠረቷ ነው። በምድራዊም በሰማያዊም ሕይወት ዘለዓለማዊነቷን የምታረጋግጠው በምትኖረው በጎ ኑሮ ነው። ሁለተኛው ማንጸሪያው ሕገ እግዚአብሔር፣ ፈሪሃ እግዚአብሔርና ሕገ ሰብ (ሌሎች ሰዎች የሚፈልጉትን ማድረግ፣ የማይፈልጉትን አለማድረግ) ላይ የተመሠረተ ነው። “ሰው ሕሊና ልቡና ያለው በመሆኑ የማናቸውም ነገር መገኛ አስተናባሪ መለኮታዊ ሕሊና ባህርይ ተካፋይ ስለሆነ ይህን ዓለም የማስተናበር የመግዛት መብት ተሰጥቶታል።” (ገጽ 71/፸፩)

እነዚህ መስመሮች ሁለት መሰረታዊ ነገሮችን ይዘዋል። ባንድ በኩል ቀደም ብሎ ካየነው የሥልጣኔ ትርጉም አንጻር የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ጫና ነጻ ይወጣ ዘንድ ተፈጥሮ ላይ ጌትነት የተሰጠው መሆኑ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ተፈጥሮን በሚገዛበት ወቅት ሥርዓት ባለው መንገድ እንዲያደርገው ሕግን ከፈጣሪ ይዋሳል። ማስተናበር ማለት ነገሮችን እንደ ተፈጥሯዊ ፍላጎታቸው ማስተናገድ የሚል ትርጓሜ ከተሰጠው ሥርዓተ ሰማይ ተሠርዓ በምድር የሚል እንድምታ ይኖረዋል። በዚሁ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ጉዳዮችን የሚበይንበት ሕገ ሰብ ያወጣል ማለት ነው።

ይህንን የሚያደርገው ደግሞ ምክንያታዊ ፍጥረት በመሆኑ ነው። የሰው ልጅ አእምሮ ልሙጥ ወረቀት ነው የሚለውን የብሪቲሽ ኢምፕሪሲስቶችን ሙግት ሲያስተባብል ሊቁ እጓለ በማያወላዱ ቃላት እንዲህ ይለናል። “ሰው ልሙጥ ፍጥረት ያልተጻፈበት ብራና አይደለም። የለባዊነት፤ የማሰብ ፤ የሎጂክ ሕግጋት በሕሊናው ውስጥ በተፈጥሮ ተቀምጠው ይገኛሉ። የበጎ አድራጎት የሥነ ምግባር፤ የሞራል ሕግጋት በልቡናው ውስጥ በተፈጥሮ ተጽፈው ይገኛል። እሊህም ሕግጋት ከሰው ፍጥረታዊ ጠባይ ጋር ተስማሚነት ‘ሐዋዝነት’ ያላቸው ናቸው።” (ገጽ 71/፸፩) እነዚህ ቃላት የያዙት ጽንሰ ሐሳብ ሰፊ ነው። ነገር ግን ሰው ህሊናውን በመጠቀም ሰማየ ሰማያትን ወጥቶ እመቀ እመቃት ወርዶ ነገረ ሕላዌን ይመረምራል፣ ይገነዘባል፤ ልቡናውን ተጠቅሞ ደግሞ የህግን፣ የሥርዓትን፣ የበጎነትን ሕይወት ይኖራል። የሁለቱ ዓለማት መገናኛ የሆነው ሰው ሥርዓተ ሰማያትን በምድር ያበጃል። ይህ ነው የያሬዳዊ ሥልጣኔ ፈትለ ነገር። “ኢትዮጵያውያን በክርስትና ክንፍ ላይ ሆነው አየር አየራት ወጥተው እመቀ እመቃት ወርደው የነገሮችን ባህርይ ለመመርመርና ለመረዳት የህሊና ጥረት አድርገው ከብዙ የሃሳብ ትክክለኝነትና ጽርየት ደርሰዋል። (ገጽ፣፸፫/73)

እነዚህ የሥልጣኔ እሳቤዎች በምን ተንጸባረቁ? በሥነ መንግሥት ረገድ አብርሃ ወ አጽብሐ የፈጣሪን ፈታሔ በጽድቅ የሚመስል ጥሩ ፍትሐዊ መንግሥት እንደመሰረቱ ታሪክ ይመሰክራል። (ገጽ፣፸፪/72) የገዳ ሥርዓት ባለቤቶች የዋቃን ሕግ ተመርኩዘው ፍጹም ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት አቋቁመው እንደነበረ ጥናቶች ያረጋግጣሉ። በፍልስፍናና ሥነ ጽሑፍ ረገድ ቅኔን ፈጥሯል፤ ሞንዙማን አስርጿል። በሥነ ሕንጻ ረገድ የየሐን፣ የአክሱምን፣ የላሊበላን፣ የጎንደርን፣ የጅማን፣ የሐረድን፣ ይምርሃነ ክርስቶስን፣ የትግራይ ውቅር አብያተ ክርስትያናትን የመሠሉ አብያተ መንግሥታትንና አብያተ እምነቶችን ከዓለት ፈልፍሏል፣ በውጥ ድንጋይ ላይ እስከ 33 ሜትር ርዝመት ያላቸው ሐወልቶችን በጽኑ መሠረት ላይ አኑሯል። ሥነ ጥበብ ረገድ የያሬድን የዜማ ፈጠራ ማስታወሱ በቂ ባይሆንም ታማኝ ምስክር ነው። የጽሑፉን ባህል፣ የግእዝ ድርሳናት የያዙትን ፍልስፍና፣ ታሪክ፣ ሥነ ተፈጥሮ፣ ሥነ መለኮትና ነገረ ከዋክብት፣ ባኅረ ሐሳቡ፣ በሙሉ ለጥናት የተተወ ነው። በባህል መድኃኒት ቅመማ፣ የሰው ልጆችን ከስንት ደዌ እንደታደገ መገመቱ አይከብድም፣ በህግ እና በሥሥርዓት፣ ማኅበራዊ መስተጋብር፣ ተፈጥሮን በመተንበይ፣ ለሕይወት የሚበጀውን ይሁንታ በማፍለቅ ረገድ ብዙ እሴት አለ።

 ፈጣሪን ማዕከል ያደረገው ያሬዳዊ ሥልጣኔ የጎደለው ምንድን ነው? ከአውሮፓዊው ሥልጣኔ ለማዋሃድ ያስፈለገውስ ምን ቢጎድለው ነው? ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠው መልስ ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ የሚያሸጋግረን ድልድይ ነው።

4.3. “በተዋኅዶ ከበረ”

 ይኸኛው ምዕራፍ ሁለቱን ሥልጣኔዎች ለማስታረቅ አንዱ ባንዱ ላይ እንዳይዘባበት ወይም አንዱ አንዱን እንዳይጫነው የታለመ ይሁንታ ነው። ሁለቱ መንፈሶች የሰው ልጆች ንብረት እንደመሆናቸው ወንድማማቾች ናቸው። ሊታረቁ፣ ሊግባቡ፣ ሊዋሃዱ ይገባል። የእጓለን ትንታኔ ረቂቅ ፍልስፍናዊ ሐተታ የሚያደርገው ዓላማው ቁሳዊ ሥልጣኔ ላይ ሳይሆን የመንፈስ ችግር መሆኑ ነው። ይህ ደግሞ የማኅበረሰቡ ጉዳይ ሳይሆን የተማረው አካል ላይ የሚስተዋለው ነው። በአውሮፓ ትምህርት የበለጸገው ኢትዮጵያዊ ባህል እና ኑሮ ጋር የሚጋፈጠው የተማረው አካል ላይ የሚስተዋለው የመንፈስ ችግር፣ የአስተሳሰብ ጣጣ ነው ትልቁ ርእሰ ጉዳዩ። ያሬዳዊ ስልጣኔ የጎደለው ነገር ከቴክኖሎጂ ጋር የተያያዘው ነውና ያንን ቴክኖሎጅ ወደ ኢትዮጵያ ለማስገባት ደግሞ የተሰለፉት ልሂቃን ከኢትዮጵያዊ ባህላዊ ሥልጣኔ ወይም Tradition ጋር ማስታረቅ እንዳለባቸው አበክሮ ይገልጻል። መንፈስ አንደኛውን ወርውሮ አዲሱን እስኪይዝ፤ ሁለቱን ዘመዳሞች መንፈሶች የሚያዋህዳቸው ሽማግሌ እስኪገኝ ድረስ ትውልድ ባዶ እጁን ይቀራልና ያ የባህል ህውከት የመከነ ትውልድ እንዳይፈጥር ማዋሃዱ ላይ ጥንቃቄ ያስፈልጋል። “በዘመናችን በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ምሁር ፊት የተደቀነው ሥራ ይህ ይመስለኛል። ሁለቱን ሥልጣኔዎች የኢትዮጵያንና የአውሮፓን በገዛ መንፈሳችን ድልድይነት ማገናኘት፣ በጥረታችን ግለትና ሙቀት እንዲዋሐዱ ለፍሬም እንዲበቁ ማድረስ።” (ገጽ፣፸፰-፸፱/78-9)

ይህንን ማህበራዊ የባህል መዋሃድ የሚያመሳስለው ከ’genetic engineeing’ ጋር ነው። የተሻለ ፍሬያማ ውጤት ለማግኘት የሁለቱ የሚዳቀሉት ዘሮች ተመጣጣኝ ቦታና ተገቢ ድርሻቸውን እንዲወጡ ማድረግ ያስፈልጋል። ባህሎችና ሥልጣኔዎችም ሲዋሃዱ የሁለቱ የተመጣጠነ ውህደት የተሻለ ውጤት ማስገኘት ይኖርበታል። እንዲህ ሲሆን ሄግል እንደሚለው የኔነት መንፈስና የእኛነት መንፈስ ሲዋሃዱ የተሻለ አማናዊ/አንጻራዊ መንፈስ ይፈጠራል። ያ አማናዊ መንፈስ ምንድን ነው? የኢትዮጵያውያን የራሳቸው እኔነት፣ ባህል፣ እምነት፣ የኑሮ ዘዴ ከአዲስ መጤው የሳይንስ፣ የፍልስፍና፣ የቴክኖሎጂ እድገት ጋር ሲዋሃድ የተሻለ እድገት፣ ሰውን ወደ ሰውነት ክብሩ ከፍ የሚያደርግ ማኅበረ ፖለቲካዊ መስተጋብር ይረጋገጣል ማለት ነው።

 ይህ የሚንጸባረቀው በምን ነው? ከፈሪሃ እግዚአብሔር ወይም ከፈሪሃ ፖሊስ በሚመነጭ በጎ ምግባር ነው። ከካፒታሊዝም የጥሎ ማለፍ ውድድር ወይም ጽንፍ ማኅበራዊነት የሚመጣ ሳይሆን ሁሉንም ሊያበቃ የሚችል ሥልጣኔ መሆን ይኖርበታል። የዘመኑ የልማት ወይም የትምህርት እቅዶች ከሁለቱም ባህል ግብአት ሲያመጡ ነው። ለምሳሌ ሃይማኖታዊ እሴቶች ላይ፣ የባህል የትምህርት ዘዴዎች፣ ባህላዊ የአስተዳደር ሥርዓቶች (ለምሳሌ ገዳ ሥርዓት)፣ እንዲሁም ከውጭው የፖለቲካ፣ የሳይንስ፣ የፍልስፍና፣ የቴክኖሎጂ አስተሳሰቦች ቀድቶ ቁሳዊና መንፈሳዊ ፍላጎቶች የሚስተናገዱበትን መንገድ መቀየስ ያስፈልጋል። የራስን ብቻ በመያዝ መጓዙ ከሌሎች የእውቀት ግኝቶች ትሩፋትና ጸጋ ለመካፈል በርን ስለሚዘጋ እድገትን ይበድለዋል። የውጭውን ብቻ በመያዝ መጓዝ ደግሞ የእጃዙር አእምሯዊ ቅኝ ግዛት በመሆን ህሊናን ይበድለዋል። ለዚህ ነው በተዋህዶ ማክበር አስፈላጊ ነው የሚሉት ሊቁ። ይህንን ማድረግ የማን ሚና ነው? የትምህርት ማኅበረሰቡ። 

4.4. ትምህርት

የመጽሐፉ ዋና ዓላማ የትምህርት ጉዳይ ላይ ሐተታ ማቅረብ ስለሆነ የመጨረሻዎቹ ምዕራፎች ትምህርት ላይ ትኩረት አድርገዋል። የታሪክ እድገት ወይም የዘመናት መለዋወጥ ከመንፈስ እድገት ጉዞ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው። መንፈስ ደግሞ በውይይት ነው የሚዳብረው። ባንድ በኩል እነ መሳይ ከበደ እንደሚሉት ከጥንታዊ እኔነት ጋር መታረቅ ያስፈልጋል። በሌላ በኩል ደግሞ እነ እጓለ እንደሚሉት ከመጤው ጋር መዋሃድ ያስፈልጋል። የጥንታዊ እኔነትንና የዘመናዊ መጤውን መንፈሶች የሚያዋህደው፣ የሚያነጋግረው ደግሞ አንደኛ ትምህርት ነው፣ ሁለተኛ ትምህርት ነው፤ ሦስተኛውም ትምህርት ነው። ትምህርት ሦስት ሚናዎች ይኖሩታል። አስታራቂ ሽማግሌ፣ አማካኝ ምስክር እንዲሁም ፈራጅ ዳኛ መሆን አለበት። እንደ ሽማግሌ የማይተዋወቁትን ዘመዳሞች ያስተዋውቃል፣ ያግባባል፤ እንደ ምስክር ያየውን፣ የሰማውን፣ የሚያውቀውን ሁሉ በደንብ ያስረዳል፤ እንደ ዳኛ ደግሞ ሁሉም የሚገባውን ቦታ ይይዝ ዘንድ ስለ እውነት፣ በእውነት ይፈርዳል።

 እንግዲህ የትምህርት ዓላማው ሰውን ወደ ሰውነት ክብሩ ከፍ ማድረግ ነው ብለናል። የዚህ ዓላማ ፊታውራሪው መምህሩ ነው። የመምህሩ መገለጫ ፍቅር ነው። “እውነተኛው መምህር በፍቅር ሥሜት የተጥለቀለቀ በመንፈሱም የሰከረ ነው።” (ገጽ 132/፻፴፪) ማንን ነው የሚያፈቅረው? አንደኛ ራሱን ያፈቅራል፤ ጧት ጧት መስታውት ፊት እየቆመች ራሷን እንደምታስውብ ኮረዳ መምህሩም ራሱን በእውቀት መሻሻል፣ የድንቁርናውን ጉድፍ የሚያስወግድባቸው መጻሕፍት፣ የእውቀት ምንጮችን በመፈተሽ ራሱን በመፈተሽ ራሱን ያፈቅራል። ሁለተኛ ተማሪውን ያፈቅራል። ተማሪውን የሚያከብረው እውቀትን ፈልጎ ወደሱ የመጣ ስለሆነ የእውቀቱን መሻት መንገድ ያሳየዋል። መንገድ ማሳየት፣ እውቀት በተማሪው ኅሊና ውስጥ ማስቀመጥ ሳይሆን የተማሪውን የማሰብ፣ የመጣጣር ሥራ የሚያግዝ ሩህሩህ ነው። ሦስተኛ ሰውነትን ያፈቅራል። የሰውነትን ክብር በእጁ ይዟልና ሰውነትን ያፈቅራል። ዶር እጓለ ገብረ ዮሐንስ ሺለር የተባለውን ጀርመናዊ ባለ ቅኔ ስለ ምሁራን፣ ስለ ጠቢባን የተቀኘውን ግጥም እንዲህ ተርጉሞልናል፡-

 የሰውነት ክብሩ እነሆ በጃችሁ

 ባላደራ ናችሁ ቢወድቅ ወድቃችሁ

 ቢነሳም አብራችሁ።

 (ብጹዓን ንጹሐነ ልብ፣

 1983፣ ገጽ 18)

 መምህሩ በእውቀቱ ከመላእክት ወገን፣ በሥጋው የሰዎች ወገን ነውና ሰዎችን የሚያፈቅር የእውቀት ባለቤት፣ እግረ ህሊና የሚመራበትን ብርሃን በፍቅር የሚለግስ ነው። ለዚህም ነው መምህሩ ቸር መሆን አለበት የሚለው። ግማሽ አካሉ ሃብታም፣ ግማሽ አካሉ ደግሞ ድሃ ነው የሚል ተረት ይጠቅሳል። ኤሮስ የመምህር ተምሳሌት ነው። ኤሮስ አባቱ ሃብታም እናቱ ደግሞ ድሃ ነች። በድህነት ችግር ይገባዋል፤ በሃብታምነቱ ደግሞ ለተቸገሩ ያካፍላል። ለዚህ ነው መምህር እውቀት ለተራቡ ሁሉ በቸርነት የሚያካፍለው። (ገጽ 131/፻፴፩)

 በፍቅረ ጥበብ እንዲሁም በፍቅረ ሰብ የተነደፉ ቸር መምህራን ሥራቸው ከጥንታዊ የእኔነት ባህል እንዲሁም ከዘመናዊው ሳይንስ ጨልፈው በማዋሃድ፤ ተማሪውም ያንን የማዋሃድ ስልት ተጠቅሞ፣ የራሱን የማሰብ ክህሎት አዳብሮ ለስጋዊና ለመንፈሳዊ ፍላጎት የሚሆን እውቀትን እንዲያመነጭ በቸርነት ይሰራሉ። መምህራን አዋላጅ ነርሶች ናቸው እንዳለ ሶቅራጥስ መምህራኑ በተማሪው ህሊና የተጸነሰን እውቀት ያዋልዳሉ እንጅ ራሳቸውን ብቸኛው የእውቀት ባለቤት እንደሆኑ በመቁጠር በአምባገነናዊነት በተማሪዎች ህሊና ላይ ባዕድ እውቀትን አይጭኑም።

 5. ማጠቃለያ

 በገጽ ብዛቱ አነስተኛ፣ በሐሳብ ብዛቱ ግዙፍ የሆነውን የዶክተር እጓለን መጽሐፍ ትንታኔ ከብዙ በጥቂቱ ከላይ የቀረበው ነው። ዋናው የሐሳብ ማጠንጠኛው ሥነ እውቀትና የሰው ልጆች የአስተሳሰብ ብልጽግና ነው። በዘመኑ የነበረውን ኢትዮጵያዊ ምሁር እንዲሁም በአገሪቱ የነበረውን ከፍተኛ የትምህርት መነሳሳት እንዲሁም የሥነ አእምሮ ቅኝ ግዛት አደጋ ያሳሰበው ሊቁ ይህንን የይሁንታ ሐሳብ አካፍሎናል። በርሱ ዘመን የነበረው ችግር በኛም ዘመን ያለ ስለመሰለኝ ትኩረት እንዲሰጠው በማሰብ ነው ትንታኔውን ያቀረብሁት። ትንታኔው ሰፊና በርካታ ጉዳዮችን ያካተተ ሲሆን ለመጽሔት አንባቢዎች እንዳያሰለች ለማሳጠር ተሞክሯል። ይኸውም ሆኖ በጣም እንደረዘመ ይሰማኛል። እኔ ካቀረብሁት ዳሰሳ በላይ መጽሐፉ በርካታ የሥነ ሰብ፣ የሥልጣኔ፣ የሥነ እውቀት፣ የነገረ ህልውና፣ የግብረ ገብ፣ የትምህርት ፍልስፍና የታጨቁበት ስለሆነ የሊቁን ሌሎች ሥራዎቹንም ደጋግመው እንዲያነቡ እጋብዛለሁ። በሌላ ርእሰ ጉዳይ እስክንገናኝ ቸር ይግጠመን!!

“ወለእመ ተሰብሩ አዕጹቂሃ ኪያከ አውልዓ

 ገዳም ተከሉ መካኖሙ

ወኀበርከ ሥርዎ ምስሌሆሙ

 ወኮንከ ዘይተ ከማሆሙ።

 ፍሩሃከ ንበር

ወኢትዜሃር ላእለ አእጹቅ

 እስመ አኮ አንተ ዘትፀውሮ ለሥርው

 አለ ሥርው ይፀውረከ” ( ገጽ 75/፸፭)

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top