ስርሆተ ገፅ

የወቅቱ የክራር እመቤት የትናየት

ለባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያችን ለክራር የከበረ ዋጋ ከሰጡ እንስት ከያንያን ውስጥ በቀዳሚነት የሚጠቀሱት ሜሪ አርምዴ እና አስናቀች ወርቁ ናቸው። እነዚሁ ከያንያን በአራቱም የሙዚቃ ስልቶች ህዝብን ሲያዝናኑ ኖረው አልፈዋል። እነሱን የሚተካ ሆኖ ሙያቸውን የተረከበ እስካሁን ባይፈጠርም በጥረት ላይ ያለችው የትናየት ይልማ ግን በብዙ ተስፋ የሚጣልባት ሆና ትገኛለች። በዚህ እትማችን ከስራዎቿ ጋር በተያያዘ ጥቂት አውግተናል። እነሆ።

ታዛ፡- ብዙ ጊዜ በክራር የሚጫወቱ ሴቶች ማግኝት በጣም ከባድ ነው። ቀደም ባሉት ጊዚያት የምትታወቀው ሜሪ አርሚዴ ነበረች። ከዚያ አስናቀች ወርቁ:: ከእነሱ ሌላ ማነው የሚታወቀው ባንቺ ግንዛቤ?

የትናየት ይልማ፡- እኔ ብዙ ማውቀው የለኝም። ግን የሆነች የትግርኛ ተጫዋች ነበረች ይባላል። ነብሷን ይማራትና አስናቀች ወርቁ መስክራልኛለች። “የምትተኪኝ አንቺ ነሽ” ብላለች እንግዲህ። ለወደፊት ሊኖር ይችላል አላውቅም። ምክንያቱም እኔም የጋን ውስጥ መብራት ሆኜ ነው ቀስ በቀስ እየወጣሁ ያለሁት። እንደኔ ሊኖሩ የሚችሉ ካሉ ራሳቸውን ያውጡ። በዚህ አጋጣሚ መልዕክቴን አስተላልፋለሁ። ግን እስካሁን ማንም የለም ብዬ ነው የማስበው።

 ታዛ፡- ከአስናቀች ወርቁ ጋር ሰርታችሁ ታውቃላችሁ? ትተዋወቃላችሁ በደምብ?

 የትናየት ይልማ፡- አልሰራንም። እሷ ግን ፈልጋኝ ነበር። አንድ ጊዜ ስሰራ አይታኝ አስፈልጋኝ ነበር። እኔን ለማግኝት ጥረት አድርጋ ነበረ፤ አርቲስት ወለላ አሰፋን ልካ በሷ በኩል ለማግኘት ሙከራ አድርጋ ነበረ። እኔ ግን ፈሪ ስለነበርኩ ራቅኳት። ይህን ማድረጌ ዛሬ ይቆጨኛል። ይመስለኛል እሷን ልተካት እንደምችል ስላሰበች ጥሩ ደረጃ ላይ እንድደርስላት ፈልጋ ነበረ። እግዚአብሔር አላለውም ያው ልትሞት አካባቢ ታማለች ሲባል በጣም በጣም አዝኜ አገኘኋት። “በጣም በጣም በርቺ” ነው ያለቺኝ። “እኔን የምትተኪኝ አንቺ ነሽ። አንቺ ካለሽ እኔ አልሞትኩም ማለት ነው። እና አትፍሪ፣ የሚፈራ ሰው ይህን ጊዜ መሻገር አይችልም” አለችኝ። ፈሪ እንደሆንኩኝ ስላወቀች ነው ይህን ያለችኝ። ያ የመከረችኝም ለኔ ትልቅ ብርታት ሆኖኛል። በዚህ አጋጣሚም በህይወት ባትኖርም አመሰግናታለሁ።

 ታዛ፡- ሙያውን ከየት አመጣሽው? እንዴት ጀመርሽው?

የትናየት ይልማ፡- አባቴ በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ይሰራ ነበረ። ይልማ ደስታ ይባላል። ያኔ እዛ በሚሰራበት ሰዓት ብዙ ክፍያ የለውም። አስራ አምስት ብር ምናምን ነበር መሰለኝ የሚከፈለው። ያ ነገር ስላልተመቸው የግሉን ስራ መስራት ፈለገ። እንደ ናይት ክለብ የመሰለ ከፈተ። እየዞረ በየሆቴሉ ቤት መዝፈን ጀመረ። ክራር ይችላል፣ አኮርዲዮን ይችላል። ማሲንቆ ይችላል። ከዛ ያለውን ሙያ እያሰለጠነ መኖር ፈለገ። እንደዛ እያደረገ እያለ እኔ እንድማር ይፈልግ ነበረ። እኔ ግን የዛን ጊዜ ፍላጎቱ አልነበረኝም። የኔ ፍላጎት የተስተካከለ አልነበረም፤ ሯጭ መሆን እፈልጋለሁ። ሰዓሊ መሆን እፈልጋለሁ። የተዘበራረቀ ነበረ ፍላጎቴ። በዛን ሰዓት ትምህርቴ ላይ ትንሽ ደከም ስለምልበት አባቴ ወይም ማሲንቆ ወይንም ክራር እንድማር ይፈልጋል። እኔ ደግሞ ፍላጎት እንደሌለኝ ነው የምነግረው። “በዚህ ልትሾልኪ ትችያለሽ አይታወቅም፤ እና በሆነ ነገር ስኬታማ ባትሆኚ በዚህ ዘርፍ ልትወጪ ትችያለሽ ተማሪ” ሲለኝ “እሺ” አልለውም። አጋጣሚ ሆኖ አንድ ጊዜ ቤቴ ተኝቼ እሱ ሰው እያስተማረ ነበር። እኔ ደግሞ በሬዲዮ አስናቀች “እንደ ኢየሩሳሌምን” ስትዘፍን በሰመመን ሰማኋት። በጣም ተመሰጥኩኝ። እንዴት ብዬ እንደተነሳሁኝ አላውቀውም። በጣም ታግለህ ምትነሳው ዓይነት። ከእንቅልፍ ላይ ወዲያው ተነስቼ አባቴን “አስተምረኝ” ስለው በጣም ነው የሳቀው። “ቃኝተህ ስጠኝ” ስለው በጣም ነው የተገረመው። “መጀመሪያ እያንዳንዱን አዳምጠሸ ነው፤ ዝምብለሽ ዘው ብሎ አይገባም” ብሎ ቃኝቶ ሰጠኝ። መለማመድ ጀመርኩ።

ታዛ፡- አባትሽ ቴያትር ቤት ሲሰሩ ምንድን ነበር የሚጫወቱት?

የትናየት ይልማ፡- ክራር፣ ማሲንቆ ይጫወታል። በድምፅም ትንሽ ይሞክራል። ሴቶች ቴያትር በማይሰሩበት ዘመን ደግሞ ከነሙሉጌታ ኃይሌ፣ ከነዘለቀ ኃይሌና ከነሽሽግ ቸኮል ጋር ቀሚስ ምናምን እየለበሰ ነበር የሚሰራው። እኔ አልደረስኩም። ወዲያው ግን ወጣ። ምክንያቱም ብሩ አላኖር አለ።

ታዛ፡- ያቺን እንደ ኢየሩሳሌም መቼ ነው የሰማሻት? ትዝ ይልሻል?

 የትናየት ይልማ፡- .. አላስታውሰውም።

ታዛ፡- በወጣትነትሽ ነው በልጅነትሽ?

የትናየት ይልማ፡- በልጅነቴ።

 ታዛ፡- እሺ! አባትሽ አስለመዱሽ ቅኝቱን። ከዚያስ?

የትናየት ይልማ፡- አባቴ ፍንጩን ብቻ ነው የሰጠኝ። ከዚያ ብሔራዊ ቴአትር ይቀጥራሉ ሲባል ሰምቼ ቀጥ ብዬ ሄድኩኝ። እዛ ስሄድ አርቲስት ከተማ መኮንን “ምን ልትሰሪ ነው የመጣሽው?” አሉኝ። “ክራር ልጫወት” አልኳቸው። በጣም ነው ደስ ያላቸው። “እስኪ አሰሚኝ” ሲሉኝ፤ ሳሰማቸው ሳቃቸውን መቆጣጠር አልቻሉም። ምክንያቱም አልችልማ። ቅኝቱም አልተቃኘም። “ጎበዝ ጎበዝ” አሉኝ። ምክንያቱም ስሜቴ እንዳይጎዳ ብለው ነው። ፍላጎቴን አይተው ቃኙልኝና ሰጡኝ። ከዛ ወይ አልተመዘገብኩኝ ወይ ምን አላልኩኝ፤ ገባሁኝ ቀጥ ብዬ። የተቀጠርኩኝ መሰለኝ። በቃ።

 ታዛ፡- ከዚያስ?

 የትናየት ይልማ፡- ከዛ ለሻይ ሲወጡ እኔን “እዚያ ውስጥ ሁኚ ተለማመጂ” ብለውኝ ይወጣሉ። እና ከዛ ሲገቡ ተነጋግረውብኛል መሰለኝ፤ እነሱ ለመሳቅ ነው እንጂ ትችላለች ብለው ለማድነቅ አይደለም። እኔ ግን ሲስቁ “ጎበዝ ናት” የሚሉኝ ነው የመሰለኝ። እነሱ ሲጫወቱ ቅኝት በየደቂቃው ይቀያይራሉ፤ እኔ ዝም ብዬ ሳልቀይር ነው የምወዛወዘው። ከዛ ልክ እንደ ሰራተኛ ጠዋት ቁርሴን በልቼ ነው የምሄደው። በእግሬ። ከሰሜን ሆቴል አካባቢ ቀስተደመና ሆቴል ተነስቼ ማለት ነው። “እቺ ልጅ ክራር ትችላለች” እንዲሉኝ ነው የምፈልገውና ክራሬን አንግቤ በጎዳና እሄዳለሁኝ። እዛ ስደርስ ዘፈን ሳልዘፍን ክራሩን ስጫወት እነሱ ከልባቸው ይስቃሉ። ለኔ ግን ምንም ነገር አይሰማኝም። “ጎበዝ” ያሉኝ ያህል ነው የሚሰማኝ። በቃ ሰዓት እያከበርኩኝ ነው የምሄደው።

ታዛ፡- ትምህርትስ?

የትናየት፡- የዛን ጊዜ ስድስተኛ ወይም አምስተኛ ክፍል ነበርኩኝ። ተውኩት። ጠዋት ግቢ ሳይከፈት ነው የምሄደው፤ ቀድሜያቸው። አንድ ቀን እነሱ ለካ የክፍለ ሀገር ጉዞ አላቸው፤ መኪና ውስጥ ገብተው ሲሄዱ እየወጡ እያሉ እኔ ክራሬን ይዤ ደረስኩባቸው። መኪና ውስጥ ልገባ ነው የፈለግኩት። ተቀጥሬያለሁ እኮ በኔ በኩል። “ነገ ነይ” ምናምን ሲሉኝ አለቀስኩኝ። እንዴት እኔ ተቀጥሬ እያለሁኝ ለምን አልሄድም ብየነው እኮ። ከዛ ወደ ቤቴ ቀጥ ብየ ተመለስኩኝ። እነሱ ሲሄዱ እኔ እያለቀስኩኝ፤ ሰዎች “ምን ሆነሻል እናት” ሲሉኝ ምንም መልስ ሳልሰጥ ቀጥ ብዬ ወደ ቤቴ ሄድኩኝ። ቤት ስደርስ “ምን ሆንሽ?” ሲለኝ አባቴ “ብሔራዊ ቲያትሮቹ እኔን ሸሽተው ክፍለ ሀገር ሄዱ” አልኩት። በጣም ነው የሳቀው። “ለምንድነው የሚሸሹሽ?” ሲለኝ እንባዬ ቀደመ፤ “መጀመሪያ ተማሪ፣ አዳምጪ ከተማርሽ እዛ ትደርሺያለሽ። እዛ ደረጃ ለመድረስ መማር፣ ማጥናት፣ ማየት ነው ያለብሽ። ጆሮሽን ጣል አርገሽ አዳምጪ” አለኝ።

ታዛ ፦ ከዚያ አገር ፍቅር ታየሽ አሉ?

 የትናየት ይልማ ፦ አዎ ቀጣይ ሙከራዬ እዚያ ነበር። ዘመናዊ ዘፋኝ ይቀጥራሉ ሲሉ ሰማሁና ሄድኩ። አበበ ካሳ እና መርዓዊ ዮሐንስ ናቸው ፈታኞቹ። ሲያዩኝ እድሜዬም ሆነ ችሎታዬ ለቴያትር ቤቱ የሚመጥን አልመሰላቸውም መሰለኝ ችላ አሉኝ። ገና ለፈተና ሳልቀርብ ማልቀስ ጀመርኩ። አባበሉኝና እስኪ የምትችይውን አሳይን አሉኝ። ያኔ የራሴን ግጥምና ዜማ መዝፈን ጀመርኩ። መርዓዊ ተደስቶ አጨበጨበ፤ አበበ ተቆጣው። ድምጼን ግን ወደውልኛል። ዓለም አቀፉን የድምጽ አወጣጥ እዚያው መድረክ ላይ አብሬያቸው እንድሞክር አደረጉ፤ ዓለም አቀፍ የሙዚቃ መሰረት ነው። አልቻልኩም። በቃ እንደተለመደው እያለቀስኩ ወደ ቤቴ ሄድኩ።

 ታዛ ፦ ከዚያ ወደ ማዘጋጃ አመራሽ ልበል?

የትናየት ይልማ ፦ ትክከል ነህ። ቴያትርና ባህል አዳራሽ ሁለት ወንድ ይቀጥራሉ ሲባል ሰማሁና አባቴ የሰጠኝን ክራር አንቄ ሄድኩ። ያኔ እንደምንም ብዬ አንድ ዜማ ተምሬያለሁ። ውጪ የተሰበሰቡት ገና ሲያዩኝ ምንድነው፤ ምንድነው? ብለው ጠየቁኝ። ልቀጠር ፈልጌ ነው አልኳቸው። ክራሬን እየነካኩ እስኪ ዝፈኚልኝ እያሉ መቀላለድ ጀመሩ። እኔ ለሚቀጥሩት ነው የማሳየው ብዬ ክራሬን እንዳይነኩብኝ እየተጠነቀቅኩ ቀጥታ አቶ ተፈራ አቡነወልድ ጋ ገባሁ። ለሰው ክብር ያላቸው ሰው ናቸው። እስኪ የምትችይውን አሳይኝ አሉ። አባቴ አሳይቶኝ በልምምድ ያዳበርኩትን ክራር እየከረከርኩ ዘፈንኩላቸው። ፀጉሬን እያሻሹ አበረታቱኝና እዚያው የቅጥር ደብዳቤ ጻፉልኝ። ወደፊት የምታድግ ልጅ ነች፣ ጥሩ ስሜት አላት፤ ብትቀጠር ተቃውሞ የለኝም ብለው። በዚህ ምክንያት ሁለት ወንድ የነበረውን ቅጥር አንድ ወንድ አንድ ሴት ተደርጎ ማስታወቂያ ወጣና ተወዳድሬ ገባሁ። ሁለገብ ችሎታ ነበር ፈተናው። ውዝዋዜ፣ ድምጽ እና ክራር አሳየሁ። በኮንትራት ተቀጠርኩ። ደስታዬ መጠን አጣ።

 ታዛ ፦ እና በሙዚቃው ቀጠልሽ?

 የትናየት ይልማ ፦ አይደለም። ያን ሰሞን በዚያን ወቅት ቴዎድሮስ ቴያትር እየተዘጋጀ ነበር። ፍቃዱ ተክለማሪያም ነው መሪ ገጸ ባህሪውን የሚጫወተው። በአጋጣሚ አዘጋጁ አባተ መኩሪያ አየኝ። ስሜን ጠየቀኝና «ቴያትር ሰርተሽ ታውቂያለሽ?» አለኝ። «አዎ» አልኩት። ግን እንኳን ልሰራ ቴያትር ራሱ ምን ማለት እንደሆነ አላውቅም ነበር። ምንም ሳያወላዳ የተዋበችን ገጸ ባህሪ ሰጠኝ። ስክሪፕቱን በማግስቱ ሸምድጄው መጣሁ። በጣም ተደሰተ። አሁን ትልቁ ፈተና የመድረክ ላይ ስራው ነው። ብዙ ደከመብኝ። ስራዬ እያዝናናው እየሳቀ ግን ጥሩ አድርጎ አበቃኝ። አባተ ማለት በጣም ተቆጪ ሰው ነበር። በአጋጣሚ ደግሞ የተሳካ ስራ ሆነ። ጥሩ ተመልካች ያለው ቴአትር ነው። ከጅምሩ ከፍቃዱ ጋር መስራቴ እድለኛ ነኝ። ከእነ ጌታሁን ኃይሉ፣ ወለላ አሰፋ፣ ፍቅርተ ጌታሁንና አበበ ባልቻ ጋር መስራቴ ለእኔ ትልቅ ነገር ነው። ከዚያ በኋላ የጓጓሁለት የጥበብ በር ተከፈተልኝ። በተለይ ቴያትሩ የእኔ ሆነ። በመሪ እና ደጋፊ ተዋናይነት ብዙ ቴያትሮችን ሰራሁ።

ታዛ ፦ እሺ ቴያትሩን እስከየት ዘለቅሸው?

 የትናየት ይልማ ፦ ቴዎድሮስ ብቻ ወደ ሦስት አመት ሲታይ ተዋበችን እየተጫወትኩ ሁሌም መድረክ ላይ ነበርኩ። ከዚያ በኋላ ጤና ያጣ ፍቅር፣ ምርቅና መረቅ፣ የዲያብሎስ ደቀ መዝሙር፣ የከርቸሌው ዘፋኝ ወዘተ ቴያትሮች ላይ የተለያዩ ገጸ ባህሪያትን ወክዬ ተጫውቻለሁ። በጤና ያጣ ፍቅር ሙዚቃዊ ድራማ ላይም አለሁበት። በተጋባዥ ተዋናይነት ሌሎች ቴያትር ቤቶችም ሰርቻለሁ።

ታዛ ፦ ምን ያህል ዘመን ስንት ቴአትሮችን ሰራሽ ማለት ነው?

የትናየት ይልማ ፦ ብዙ ነው። እንግዲህ ከ1970 ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ማለት ነው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በዝውውር ወደ ራስ ቴያትር እስክሄድ ድረስ በቴያትር ቤቱ በሚታዩ ቴያትሮች ላይ ሁሉ እሳተፍ ነበር። ማስታወስ ይከብዳል በጣም ብዙ ነው። ሰዉ የሚያውቀኝ በቴያትሩ ነው።

ታዛ ፦ ከመድረክ ውጪ በፊልም ስራዎች ላይስ እንዴት ነሽ?

የትናየት ይልማ ፦ ብዙ ሰርቻለሁ። ሁሉንም ማስታወስ አይቻልም። 120 በሚለው ፕሮግራም ይተላለፍ የነበረ አንድ ተወዳጅ ፊልም ነበር። የካሳዬ ገበየሁ ድርሰት በሆነውና «ማረፊያ ያጣች ወፍ» በሚለው የቴሌቪዥን ተከታታይ ፊልም ላይ ነው ብዙ ሰው ያወቀኝ። ከነአለልኝ መኳንንትና ጥላሁን ዘውገም ጋር የሰራሁት አለ።

ታዛ ፦ በዝውውር ነው ወደ ራስ ቴያትር የሄድሽው?

 የትናየት ይልማ ፦ በመዋቅር ሽግሽግ ነው እንደሌሎች ተዋናዮች ወደዛ የተዘዋወርኩት። ራስ ቴያትር ደግሞ የፍቅር ቤት ነው። ማዘጋጃ ቤት በሙዚቃው ላይ ትንሽ ኩርኩም ነበረብኝ። እንድሰራ፣ እንዳድግ የሚፈልጉ ሰዎች አልነበሩም። ተዋናዮቹ ብቻ ናቸው በትወናዬ የሚያበረታቱኝ። እና ራስ ቴያትር ነው ክራሬን መልሼ ያነሳሁት። «አንቺ ብርቅዬ ነሽ፤ በርቺ» እያሉ መድረክ ሰጡኝ። በጥሩ ስሜት ሰራሁ።

 ታዛ ፦ ዛሬ ራስ ቴያትር የለም። ታዲያ የት ነው የምትጫወቺው?

የትናየት ይልማ ፦ መድረኩ ነው የሌለው እንጂ ራስ ቴያትር አለ። ተዋናዮቹም ሆኑ የሙዚቃ ሰዎቹ አለን። በውሰት በሌሎች ቴያትር ቤቶች መድረኮች ላይ ስራችንን እናሳያለን። የተለያዩ ኮንሰርቶች ላይ እና የጥበብ መድረኮች ላይ ስንጋበዝ ስራችንን እናሳያለን። ያኔ እኔም ክራሬን ይዤ እገኛለሁ። በነገራችን ላይ በኤምባሲዎችና በታላላቅ ሆቴሎች ስራዬን የማሳየት እድል ገጥሞኛል።

ታዛ ፦ ክራሩን ሙዚቃ ትምህርት ቤት ገብተሽ አዳበርሺው ወይስ በልምድ ዘለቅሽው?

 የትናየት ይልማ ፦ መሰረቱንም የያዝኩት፣ ልምምዱንም ያጎለበትኩት ከአባቴ ነው። ቅድም እንዳልኩህ የአስናቀቸ ወርቁን ዘፈን መስማቴ ደግሞ በጣም ጠቅሞኛል። ለዛሬ ማንነቴ የእነዚህ ሁሉ ውህደት በራሴ ላይ አርፏል።

ታዛ ፦ ምን ምን ቅኝቶችን ነው የምትጫወቺው?

 የትናየት ይልማ ፦ ሁሉንም እጫወታለሁ። ትዝታ፣ ባቲ፣ አንቺ ሆዬ፣ አምባሰል። ከዚያም በዘለለ ማይነር የሚባሉ አሉ እነሱንም እጫወታለሁ።

 ታዛ ፦ ግጥምና ዜማስ እንዴት ነው የምታደርጊው?

 የትናየት ይልማ ፦ የራሴ ናቸው። ግጥምም ዜማም የሰጠኝ የለም። ብዙ አሉኝ። ለመጀመሪያ ጊዜ ራስ ቴያትር ስገባ በመድረክ ላይ ተፈሪ ደጀኔ ግጥም፣ አንድ ስማቸውን የዘነጋሁት ሻለቃ ደግሞ ዜማ ሰጡኝ፣ በክራሬ ተጫወትኩ። ከዚያ ውጪ የኔ ስራዎችን ነው የማቀርበው።

ታዛ ፦ በቁጥር ደረጃ ማወቅ ይቻላል ግጥምና ዜማዎችሽን?

 የትናየት ይልማ ፦ ዉዉዉ…! ብዙ ናቸው።

 ታዛ ፦ የአስናቀች ወርቁን «እንደኢየሩሳሌም»ን መጫወት በጣም ትወጃለሽ አሉ፤

 የትናየት ይልማ ፦ አይይይ ወድጄ አይደለም። ራስ ቴያትር ስሰራ አንድ ስሙን መጥቀስ የማልፈልገው አለቃዬ መድረክ ላይ እንድሰራ አይፈልግም ነበር። በዚያው አንጻር ደግሞ ፋሲካ አከለ፣ ስንታየሁ፣ ቸርነት ገበየሁ ያበረታቱኝ ነበር። እና ያ ያልኩህ ሰው ሁልጊዜ እንደኢየሩሳሌም የሚለውን ዜማ ብቻ እንድሰራ ነበር የሚፈልገው። ኃላፊዬ ስለሆነ እታዘዛለሁ። በዚያን ወቅት የአምባሰል ሙዚቃ ቤት ባለቤት የነበረው አቶ ፍቃዱ ዋሬ የሆነ ዝግጅት ሲኖረው ራስ ቴያትሮችን ነው የሚያሰራው። ታዲያ አንድ ቀን ያንን ዘፈን ዘፍኜ ስጨርስ ወደ ውጪ ጠራኝና «ሙያተኛ ነሽ በሙያሽ አደንቅሻለሁ። ግን ሁሌ እንደኢየሩሳሌምን የምትሰሪ ከሆነ እኔ ስለማልፈልግ አንቺ እዚህ ውስጥ እንድትገቢ አልፈልግም፣ ይቅርታ አድርጊልኝ» አለኝ። በጣም አዘንኩ። ይህን ያህል ተሰልችቻለሁ በሚል ውስጤን አመመው። ግን ሁኔታውን ነገርኩትና ተረዳኝ። ከዚያ ጊዜ በኋላ መድረክ ላይ ስወጣ በጉልበቴ የራሴን ስራ ይዤ መቅረብን ደፈርኩ። የተመልካቾች አድናቆትና ሞራል ሲመጣ ያ አለቃዬ ምንም ሊል አልቻለም። በቃ በዚያው ቀጠልኩ።

 ታዛ ፦ በካሴት፣ አልበም ደረጃ የሞከርሽው ነገር የለም?

የትናየት ይልማ ፦ ሞክሬያለሁ። አቶ ፍቃዱም በስራዬ ለውጥ ተደስቶ አልበም የሚሆን ዘፈን ባዘጋጅ እንደሚያሳትምልኝ ቃል ገባልኝ። ሦስት ስራ ሰራሁ ግን ከአቀናባሪው ጋር በትንሽ ነገር ስለተጋጨን አበላሸብኝ። ስራው በህብረት የተሰራ ነው። እኔ፣ ታመነ መኮንን እና አበባው የሚባል የክራር ተጨዋች ነን የሰራነው። ለልምምድ ያዘጋጀሁትን ስራ ነው ፈጥኖ ያወጣብኝ። እኔ አልተደሰትኩበትም ግን አንዳንድ አድማጮች ጥሩ መሆኑን ይነግሩኛል። የአልበሙ ስም። አቶ ፍቃዱም ሰው ሁሉ እየወደደው ነው ያለኝ። እኔ ግን ስህተቱ የቱጋ እንደሆነ ስለማውቀው ይቆጠቁጠኛል። ስሜቴ በጣም ነው የተጎዳው። ያም ሆኖ አሁን ሌሎች አዳዲስ ስራዎቼን ጨምሬ ራሴን ችዬ አልበም ለመስራት እየተዘጋጀሁ ነው።

 ታዛ ፦ ሴት ክራር ተጫዋች በአገራችን ብርቅ ነው፤ በአሁኑ ወቅት አንቺ ብቻ እንዳለሽ እረዳለሁ፤ ስለምን ይሆን ጎልተሽ ያልወጣሽው?

የትናየት ይልማ ፦ አሁንም እራሴ እየተጣጣርኩ ነው እንጂ በቴያትርና ባህል አዳራሽም በራስ ቴያትርም እንደፍላጎቴ ጎልቼ እንዳልወጣ እኔን የመጫን ነገር ነበር። እግዚአብሔር ያደለኝ ጥሩ ነገር ጉዳቴን ችዬ እንድኖር ማድረጉ ነው። አሁን አልቅሼ፣ ተከፍቼ በኋላ እረሳዋለሁ።

ታዛ ፦ የአስናቀች ወርቁጋ ደርሻለሁ ብለሽ ታስቢያለሽ? የእሷን ስራዎችስ ትችያቸዋለሽ፣ ትጫወቻቸዋለሽ?

የትናየት ይልማ ፦ አዎ እችላቸዋለሁ፣ እጫወታቸዋለሁ። ነገር ግን አንድ እምነት አለኝ። አስናቀች ወርቁ ራሷ አስናቀች ነች። የትናየት ደግሞ የትናየት ነች። እንደ እውነቱ ከሆነ አስናቀች ምርጥ ስራ ሰርታ ያለፈች ነች። ስራዎቿ ሁሉ ደስ ይሉኛል። ማንም ሊተካት እንደማይችል አስባለሁ። እኔ ተካኋት ቢባል እንኳ እኔ እኔ እንጂ አስናቀችን ከቶውንም ልሆን አልችልም። በእሷ የአጨዋወት ስልት ልታወቅባት አልፈልግም። ማንም ሰው በራሱ ራሱ ነው። አንዳንዶች ስጫወት አስናቀችን እንደምመስል ይነግሩኛል። በትክክሉ ግን ሁለታችንም በአንድ ጊዜና ቦታ ብንጫወት ፈጽሞ የተለያየን ነን። እኔ እሷን ልተካት አልችልም። በጣም ትልቅ ሙያተኛ ነች። የማከብራት ናት። እሷም ሙያውም እንዳይረሳ አድርጌ ይሆናል እንጂ አንደራረስም። እና የእሷን ስራዎች ከመጫወት ይልቅ የራሴን ስራዎች ብጫወት ነው የምመርጠው። በዛ እየሄድኩም ነው።

ታዛ ፦ ፈሪና አይናፋር እንደሆንሽ፣ የሙያ ባልደረቦችሽ ይናገራሉ፤ ያ ከምን የመጣ ነው? የመድረክ ሰው ካፈረ በስራው ከህዝብ ጋር ለመገናኘት አይከብደውም?

የትናየት ይልማ ፦ እንዳልከው ነው እኔ ፈሪ ነኝ። ፍርሃቱ የተፈጥሮ አይደለም። ያ ቢሆን በዚያ በልጅነቴ ወደ ሙያው ልገባ ባደረኩት ጥረት ክራሬን አንግቤ ቴያትር ቤቶችን ሳንኳኳ አልገኝም ነበር። ማዘጋጃ ቤት የደረሰብኝ ኩርኮማ ነው ያንን የፈጠረብኝ። እንደማልችል ሁሉ ተነግሮኝ ነበር። ስነ ልቦናዊ ጥቃት ነው እንድሸማቀቅ ያደረገኝ። እኔ ግን ውስጤን ስለማውቀው አቅሜን ስለምረዳ በትግል ነው የዘለቅኩት። አለመቻል የሚለው ነገር ፈሪ እንድሆን አድርጎኛል። እየሰራሁኝ ሁሉ የተሳሳትኩ እስኪመስለኝ እጨነቅ ነበር። ጥሩ ሰርቼ እንኳ ልክ አይደለሁም የሚለው ነገር ውስጤን ይረብሸው ነበር። ዛሬ ዛሬ ከሰው ጋር ስጫወት ስግባባ ነው ፍርሃቴ እንጂ መድረክ ላይ አልፈራም። ግን የሰው ልጅ ችሎታ እያለው በሌሎች ጫና እና ስነ ልቦናዊ ጥቃት ፈሪ እንደሚሆን እኔ ማሳያ ልሆን እችላለሁ።

ታዛ ፦ ግጥምና ዜማ እንደምትሰሪ ነግረሽኛል፤ ምን ጊዜ ነው የምትሰሪው?

 የትናየት ይልማ ፦ የሆነ ውስጤን የሚኮረኩረኝ ነገር ሲኖር ነው የምገጥመው። ሲከፋኝ ወይም ስደሰት ቶሎ ክራሬን ከመስቀያው አወርዳታለሁ። ሳንጎራጉር መንፈሴ ያርፋል። ደስ ይለኛል። ስሜቴን በግጥምና በዜማ እወጣዋለሁ። ለምሳሌ ፍቃዱ ተክለማሪያም በጠና መታመሙን ስሰማ ስልክ ደወልኩለትና አነጋገርኩት፤ ለመዳን ያለውን ተስፋ ነው የነገረኝ። ሁኔታው በጣም አሳዘነኝ። እኔም ተስፋ አድርጌ እያዘንኩ ስልኩን ዘጋሁ። ከቀናት በኋላ መሞቱ ተነገረ። ያ በስልክ ያወራነው ነገር መጣብኝ። ክፉኛ አዘንኩ። ያኔ ክራሬን አንስቼ እያለቀስኩ ሳላስበው ግጥምና ዜማዎች አንድ ላይ ፈሰሱልኝ። አጋጣሚ ሆኖ በሸገር ሬዲዮ በሌላ ጉዳይ ሊያናግሩኝ ሲጠይቁኝ ቀጥ ብዬ ሄድኩና ይህንን ለፍቃዱ ያንጎራጎርኩትን ለኢትዮጵያ ህዝብ አሰማሁ። ያኔ ባላቀርበው ጊዜ ያልፍበትና ለታሪክ አይቀመጥም ነበር። (በዜማ ካንጎራጎረችልኝ ውስጥ የሚከተለው ግጥም ይገኝበታል፡፡) ጉሮ ወሸባ ነው የደግ ሰው ሞቱ በክብር ተጠርቶ ሲሄድ ወደ አባቱ… ፈጣሪ እንደጠራው እንደምን አወቀ በጊዜ ተጣጥቦ ጸድቶ የጠበቀ… እሱም ፈጣሪውን መርጦ ነው መሄዱ… እንግዲህ እንዳሻው እሱ እንደፍቃዱ። እጅ አልሰጥም ብሎ እንደ ቴዎድሮስ በክብር ነው የሄደው ይቅር አናልቅስ።

 ታዛ ፦ ሙያሽ የሚሳሱለት ነውና ይበልጥ ወደ ህዝብ እንድትቀርቢ ምን ያስፈልግሻል?

የትናየት ይልማ ፦ አዎ እንዳልኩህ አንዳንድ ኤምባሲዎች፣ በበዓላት ጊዜና በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ወቅት የሚያውቁኝ ይጠሩኛል። ሆኖም እኔ የምፈልገውን ያህል ጎልቼ እንድወጣ የሚያደርገኝን መድረክ አላገኘሁም።  ምክንያቱን አላውቅም። እኔ ግን አቅም አለኝ፣ ፍላጎት አለኝ፤ ለሚፈልጉኝ ሙያዬን አሳያለሁ። ራሴን ችዬ መኖር፣ ራሴን ደብቄ መኖር ነው ጎልቼ እንድወጣ ያላስቻለኝ የሚመስለኝ። የሆነው ሆኖ ስሜቴን ተረድቶ በሙያዬ የሚረዳኝን ሰው እፈልጋለሁ። ታዛ ፦ በምን መልክ?

የትናየት ይልማ ፦ በተለያዩ ሆቴሎች ምሳ ላይ፣ እራት ላይ፣ በልዩ ዝግጅቶቻቸው ላይ ቀጥታ ክራሬን ብጫወት ደስ ይለኛል። በዚህ ስራ አይደለም አንድ አራት አምስት ሆቴሎች የመስራት አቅም አለኝ። በዚህ የሚረዳኝ ቢኖር በሙያዬ ይበልጥ ተጠቃሚ እሆን ነበር። በሙያዬ ብቻ የሚረዳኝን ሰው ነው የምፈልገው፤ ሰርቼ እንድኖር። የሚረዳኝ ሙያ ስላለ በገንዘብ ድጋፍ መኖርን አልሻም። በአሰብኩት መንገድ ብሰራ እያዘጋጀሁ ያለሁትን አልበም ለማውጣትም አቅም ይፈጥርልኝ ነበር። በዚህ አጋጣሚ እስከዛሬ ባሳለፍኩት ጉዞ ያበረታቱኝን የራስ ቴያትር ባልደረቦች ሁሉ፣ አርቲስት አሰፋ በየነን፣ ገለታ ተክለጻዲቅ፣የሀገር ፍቅር ስራ አስኪያጅ ዮሐንስ ስለሺ እንዲሁም የአምባሰል ሙዚቃ ቤት ባለቤት አቶ ፍቃዱ ዋሬን፣ የማራቶን ሙዚቃ ቤት ባለቤት አቶ ታምሩ ተክሌን፣ ሐኪም መሰረት ፋሲካን እና ሌሎችንም መልካም ሰዎቼን አመስግንልኝ።

ታዛ ፦ በግምት ከአንድ ዓመት በፊት ያለፈው የባህል ዘፈን ድምጻዊ ሀብተሚካኤል ደምሴ የቅርብ ቤተሰብሽ እንደሆነ አውቃለሁ፤ እሱም በሙያሽ ውስጥ አበርክቶ እንደነበረው ነግረሽኛል፤

የትናየት ይልማ ፦ በጣም፤ በጣም!  ሀብተሚካኤል የታላቅ እህቴ ባለቤት ነው። ብዙ ሰው ያስተዋወቀኝ፣ በሙያዬ እንድገፋ ያበረታታኝ ሰው ነው። አጋጣሚው ፈቅዶ አብሬው አለመስራቴ ይቆጨኛል። ሃሳብ ነበረኝ፣ ግን እግዚአብሔር አልፈቀደም። ልጁ ኤፍሬም ጥሩ ዜማ ሰጥቶኛል ይመስገንልኝ፡፡

ታዛ ፦ እስከመጨረሻው ከእናትሽ ጋር እንደኖርሽ አውቃለሁ፤ ሌላ ቤተሰባዊ ህይወት አልመሰረትሽም?

የትናየት ይልማ ፦ አዎ እናቴ ለእኔ ብዙ ነበረች። ጓደኛዬም፣ ምስጢረኛዬም፣ አፅናኜም፣ የደስታዬም ተካፋይ… ምን ልበልህ?… ማታ ስራ አምሽቼ ወደ ቤት ስሄድ በመንደራችን መዳረሻ የመንገድ መብራት በሌለበት ቦታ ሻማ ይዛ የምትጠብቀኝ ነበረች። ሻማው ሲያልቅ ኩራዝ ትለኩሳለች። እዚያ ቦታ ሁሌ በእንዲህ ሁኔታ ስትጠብቀኝ የሚያያት አንድ ሰው ፓውዛ ገዝቶ ሰጥቷት ነበር። አንድ ነበር አብሮነታችን። ሌላ ህይወት ሳልመሰርት እስከመጨረሻው ኖረን እሷ አለፈች። ከዚያ በኋላ የስሜት መጎዳቱ አየለብኝ። ቢሆንም አለሁ።

ታዛ ፦ ለእሳቸው መታሰቢያ ያንጎራጎርሽውን በመድረክ እንዳቀረብሽው ከሙያ አጋሮችሽ ሰማሁ፤

የትናየት ይልማ ፦ ትክክል ነህ። የራስ ቴያትር መድረክ ሳይፈርስ ነው ነገሩ የሆነው። «ማረፊያዬ የት ይሆን… » ብዬ ያዘጋጀሁትን ስሜት የሚነካ ግጥም ልብ በሚሰብር ዜማ መድረክ ላይ አቀረብኩት። እያለቀስኩ ነው የተጫወትኩት። ህዝቡም የኔ ስሜት ተጋርቶበት ያለቅስ ነበር። በዚያን ጊዜ የባንድ መሪው «ይህን ነገር ቀይሪው፤ መድረክ ማዝናኛ እንጂ ማዘኛ መሆን አይገባውም» ብሎ ሲገስጸኝ ተውኩት። በቃ ረሳሁት። ግጥሙን ከዚያ በኋላ ማስታወስ አልፈለኩም። ዜማውን ግን የፍቅር ዘፈን ሰራሁበት። እኔ አዝኜ ሰውን ማሳዘን አልፈለኩም። የሚገርመው እናቴ ከሞተች በኋላ ቢያንስ ለሦስት ዓመት ራሴን አለማወቅ ደረጃ ደርሼ ነበር። የራስ ቴያትር ባልደረቦቼ ናቸው አጽናንተው የመለሱኝ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሳለቅስ ወይም ሳዝን በጣም ሃይለኛ ራስ ምታት አለብኝ።

ታዛ ፦ ወደፊት ጡረታ ስትወጪ ምን ሃሳብ አለሽ?

የትናየት ይልማ ፦ ክራሬን አንግቤ ማንጎራጎሬን እቀጥላለሁ። እኔ ብሶተኛ ነኝ። አጫዋቼ ክራሬ ነው። ከዚያ በፊት ግን ፊልሞች ላይ የሚያሰራኝ ቢኖር ደስ ይለኛል። ብዙ ቴያትሮችን በመስራቴ ፊልም መስራቱ ይከብደኛል ብዬ አላስብም። ሰካራሙ ፖስታ እና ጥቁር እንግዳ የተሰኙ ፊልሞች ላይ መስራቴም ይታወቅልኝ።

ታዛ ፦ በጣም አመሰግናለሁ መልክትሽን አደርሳለሁ።

የትናየት ፦ እኔም አመሰግናለሁ፤ እግዚአብሔር ይስጥልኝ።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top