በላ ልበልሃ

የእኔ ሐተታ፣ በዕውቀቱ ሥዩም ጥቂት ስንኞች ላይ

ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ በቅፅ 2 ቁጥር 16 ታኀሣስ ጥር 2011 ዓ.ም. የታዛ መጽሔት ላይ በበዕውቀቱ ሥዩም ስንኞች ላይ ያቀረቡትን ሐተታ እና ትንታኔ ተመልክቼዋለሁ። በጽሑፋቸው ማጠቃለያም “… ይህች ጽሁፍ ተመሳሳይ ትንተና እንደምትጋብዝ እመኛለሁ …” ሲሉ ለሌላ ሐተታ ግብዣ ጥሪ አቅርበው መደምደማቸውን ካየሁ በኋላ እኔም ሐተታ በቀረቡባቸው ጥቂት ስንኞች ላይ የተሰማኝን ለማለት ይህንን ጽሑፍ አዘጋጅቻለሁ። ፕሮፌሰሩን ለግብዣቸው አመሰግናለሁ።

በማናቸው ቅርፅ ይዘቱን አካቶ ለሕዝብ የቀረበ የጥበብ ሥራ በተደራሲያኑ ዘንድ ሲደርስ ሁሉም እንደስሜቱ፣ እንደእውቀቱ፣ እንደሕይወት ልምዱ፣ የደራሲውን ሃሣብ እየተረጐመ ሊመለከተው መቻሉ እውነት ነው። እንደዚህ አይነት በብዙ ፈርጅና የእይታ አቅጣጫ እየተተረተሩና እየተከፋፈሉ የሚብጠረጠሩት የጥበብ ውጤቶች ውበታቸው ከዚሁ ባለብዙ ፈርጅነት እይታ እና አሟጋችነት ይመነጫል።

 ፕሮፌሰር ሽብሩ ሀተታ ካቀረቡበት የበዕውቀቱ ሥዩም ግጥም ውስጥ አንዱ “ሐተታ ቢራቢሮ” የሚለው ሲሆን ይህንን ግጥም ከፍልስፍና አንፃር ተመልክተውት በትንተናቸው ውስጥ እንዲህ ብለዋል።

 “ለማንኛውም ድርጊት አፃፋ እንዳለው ያመለክታል። ቁምነገሩ አድራጊውን አፃፋው እንዳያውከው ማድረግ ላይ ነው። በተጨማሪም አንድ ተግባር ከመፈፀሙ በፊት አፃፋው ምን ሊሆን እንደሚችል ማሰላሰል መጠንቀቅ እንደሚገባ ያመለክታል።“ ሲሉ የተሰማቸውን ጽፈዋል። እኔ ደግሞ ከዚህ ተቃራኒ በሆነ መልኩ የግጥሙ ስንኞች የፈጠሩብኝን ስሜት እገልጻለሁ። ወደ ትንታኔዬ ከመግባቴ በፊት ይህንኑ ግጥም እንዳለ ባስቀምጠው የቀደመውን መጽሔት አግኝተው ግጥሙን ላላነበቡ ሰዎች መነሻ መረጃ ስለሚሆናቸው ሐተታ ቢራቢሮን እዚህ አቅርቤዋለሁ።

 ሐተታ ቢራቢሮ

 ስንት ጊዜ ቀናኹኝ በዚያ ቢራቢሮ

 ከእግዜር መዳፍ ቀድሞ አበባይቱን ፈጥሮ

 እግሯን መንገድ ነስቶ መሬት ላይ ተከለው

 ከሣማት በኋላ እንዳትከተለው።

 በዚህ ስንኝ ውስጥ ግጥሙ ሲጀምር “ስንት ጊዜ ቀናሁ በዚያ ቢራቢሮ …” ብሎ ይነሣል። የገጣሚው መንፈስ ግጥሙን ከፀነሰባት መንፈስ ውስጥ አምጦ ሲወልደው በቢራቢሮ አድራጊነት በአበባዋ ተደራጊነት መቅናቱን ይናገራልና። አንዱ ልክ እንደ ቢራቢሮ አድራጊ  ሆኖ ለመሳም ተፈጥሯል። ሌላው ፍጡር ደግሞ ሁሌም ተደራጊ ሆኖ እንደ አበባዋ ተፈጥሯል። ያቺ እግር የተከለከላት ወይም ክንፍ አልባ የሆነች መሬት ላይ የተተከለች አበባ ሁሌም መሳም እንጂ የሳማትን ለመሳም ፍቃድና ነፃነት የተነፈገች ተደራጊ ፍጥረት ናት ይለናል። እንጂ አንዱ ለተደረገበት ድርጊት መልሶ የሚሰጠው አፃፋዊ ድርጊትም አለው። ስለዚህ ለተደረገብን ነገር ምላሽ ለመስጠት ማሰላሰልና መጠንቀቅ ይኖርብናል የሚለውን ትንታኔ የኔ ስሜት ሊጋራው አልቻለም። ከአድራጊው ቢራቢሮ በፊት ቀድሞ በእግዚአብሔር መዳፍ የተፈጠረው አበባ አለ። ይህ አበባ ሁሌም የሚስመውን ቢራቢሮ በተስፋ የሚጠብቅ ተደራጊ ፍጡር ነው። ውበቱም ሆነ መአዛው ለአድራጊው ቢራቢሮ ፍላጐትና ስሜት ብቻ የተፈጠረ ነው። ቢራቢሮው ወደ አበባ እንዲበር እንጂ አበባው ወደ ቢራቢሮ እንዲሄድ ተደርጐ አልተፈጠረም። አበባዋ እግር ቢኖራትም ከመሬት ላይ ስለተተከለች አትንቀሣቀስም። እንደ አድራጊው ቢራቢሮ አበባዋ ክንፍ የላትም።

 መሬቱን ለቃ ለመብረር እና የሣማትን ተከትላ መልሳ ለመሳም ነፃነትም ሆነ ፍቃድ የላትም። ገጣሚው በቢራቢሮው እና በአበባው መካከል ያለውን ተቃርኖ በስንኙ ውስጥ ሲገልፀው ለኔ የሚሰማኝ ሁሉም ነገር ወይም ሁሉም ድርጊት የራሱ አፀፋዊ ድርጊት አለው በሚል መልኩ አልመሰለኝም። እንዲያውም በተቃራኒው በመሳም የተደረገው አበባ በሳሚውና በአድራጊው ቢራቢሮ የተፈፀመበትን የመሳም ድርጊት ቢወደውም እንኳን ምላሹን ለመስጠት የማይችል ክንፍ አልባ ነፃነትና ፍቃድ የተነፈገው ለመንቀሣቀስ እንኳን እግር ተፈጥሮለት ግን መንገድ የሌለው መንገዱንም የማያውቅ አሳዛኝ ፍጡር ነው የሚል ይመስለኛል።

 የገጣሚው መንፈስ እራሱን እንደ አበባዋ መስሎ በማየት በባለክንፋሙ ቢራቢሮ የሚቀናውም ለዚህ ነው። መብረር ይፈልጋል ግን ክንፍ የለውም። መሄድ ይፈልጋል ግን መንገዱን አያውቀውም። ይህ እግዜር የሚሉት ነገር አንዱን ለአድራጊነት ሌላውን ለተደራጊነት አንዱን ለገዳይነት ሌላውን ለተገዳይነት አንዱን ለንግስና ሌላውን ለባርነት ፈጥሮታል። ከዚህ ሕግ ማንም አያመልጥም። በዚህ ምድር ላይ እንደ አበባይቱ ብታምርም ብትደምቅም ለአንተ ሣይሆን ለባለክንፋሙ ቢራቢሮ ጥቅም ሲባል ነው። አንተ ከተሣምክ በኋላ ጥቂት ቆይተህ ትረግፋለህ ትጠፋለህ የሚል ስሜት ተሰምቶኛል።

ፕሮፌሰር ፍግ ላይ የበቀለች አበባ በሚለው ግጥምም ውስጥ የራሳቸውን ትንተና አቅርበዋል። አሁንም ግጥሟን ላስከትልና የራሴን አተያይ ልቀጥል።

 ፍግ ላይ የበቀለች አበባ

አበባይቱም አለች

ፍግላይ የበቀለች

ምንድነው ጥበቡ ?

ኔክታር ማጣፈጡ

አደይን ማስዋቡ

እኔም መለስኩላት

“ይብላኝ ለንብ እንጂ ዝንብማ ይተጋል

ከቆሻሻ አለም ውስጥ ጣምን ይፈልጋል።”

ፕሮፌሰሩ በትንታኔያቸው ውስጥ ንብ በፈጣሪ ቀድሞ የተዘጋጀውን ጥሬ እቃ ዘርፋ ማር ብትሰራም ብዙ ውጣ ውረድና ድካም በሌለበት ሲሆን ዝንብ ግን ከቆሻሻ ቦታ ተገኝታ በከፍተኛ ድካም ጣእም ያለውን ምግብ ሰብስባ በመመገብ ትኖራለች። የነገሩን ዙሪያ ጥምጥም ሣይመለከቱ መፍረድ አያስፈልግም የሚል መልክት ያስተላልፋል ቢሉም የኔ ስሜት ደግሞ ከዚህ በተቃራኒው መንገድ እንዲህ ይለኛል።

 ዝንብ ደክማ ጥራ ከቁሻሻው ውስጥ ያገኘችውን ለራሷ ትበላዋለች እንጂ ለሌላው አታበላውም። ለምን ቢሉ ከቆሻሻ ቦታ የተገኘ ምግብ ቆሻሻውን ለለመደው ፍጥረት እንጂ ከቆሻሻው ተለይቶ ንፅህናውን ጠብቆ ለሚኖር ፍጡር አይጠቅምም። ንብ ግን በጥበብ የሰራችውን ማር ለራሷ ብቻ ሣይሆን ለሌላውም ታበላለች። ለምን ቢሉ በጥበብ የተሰራ ነውና መድኃኒት ነው። በንብና በዝንብ መካከል ያለው ልዩነት ጠቢብ በመሆን እና ባለመሆን ሁኔታ ውስጥ የሚታይ እውነታ ነው። ንብ ቀድሞ በተዘጋጀ ጥሬ እቃ ቢሆንም ጥበቧን ተጠቅማ ማር ሰርታ ታበላለች፣ ትበላለች። ዝንብ ደግሞ ይህንን አለም በሞላው ቆሻሻ ውስጥ፣ ቆሻሻው ለሷ ጥሬ እቃ ከሆነ ማለት ነው፣ የምትሰራው የሚጣፍጥና ለሌላ የሚተርፍ ነገር የላትም።

 አለቃ ዘነብ በመጽሐፈ ጨዋታ መጽሐፋቸው ውስጥ “የዝንብ ብልሃት ምንድነው? ሌላው የሰራውን መብላት ነው። ሰነፍ ሰዎችም እንደዚሁ ናቸው። ሌላው የሰራውን መብላት ይወዳሉ ይላሉ። አስከትለውም በዚሁ መጽሐፍ ውስጥ ስለንብ ሲናገሩ “ማር ሁለት ጊዜ ያገለግላል አንድ ጊዜ ለመጠጥ አንድ ጊዜ መብራት ሆኖ። ምነው ቢሉ የብልሕ ስራ ነውና አሰርም /ገለባ/ የለውም” ይላሉ። ለሕይወት ጠቃሚ የሆነው ነገር የት ቦታ እንደሚገኝ ንቦች ያውቃሉ። ዝንቦች ግን የዚህ አይነቱ እውቀት የላቸውም። ሁሉም ከቆሻሻው ቦታ ተገኝተው ለሌላ ሰው የማይተርፍ ምግብ ለማግኘት ሲደክሙ ይኖራሉ።

የአንዳንዶቻችን ሕይወትና አኗኗር ልክ የዝንቡን ይመስላል። አንዳንድ ሰዎች ልክ እንደ ዝንቧ የት ቦታ ተገኝተው መስራትና መድከም እንዳለባቸው አያውቁም። መልካም ነገር በማይገኝበት አረቄ ቤት ተጐልተው ከአረቄው የሚጠቅም ነገር ለማግኘት ይደክማሉ። በሃሽሽ ደንዝዘው በሥራ ፈትነት ተጎልተው ይውላሉ።

“ገጣሚው በእኔ ውስጥ ይህ ዓለም እንደዚህ ነው። ሁለት የማይገናኙ የተቃርኖ ጫፎችን ያስተናግዳል። ሰውም ወይ በንብ ክንፍ ወደ አበባው ቦታ ይበራል አልያም በዝንብ ክንፍ ወደ ቆሻሻው ስፍራ ይበራል። ሰው የቅራኔ ባሪያ ነው። እግዜሩ እንዲህ አድርጐ ፈጥሮታል የሚል እይታ ይኖረኛል”

ከዚህ ቦታ ለሌላው የማይጠቅም ጣፋጭ ነገር የሚያገኙ ይመስል ሲጃጃሉ ይታያሉ።

ዝንብ ልክ እንደንብ መብረር ትችላለች። ግን ንቦች አበባ ወደሚገኝበት ሲበሩ ዝንቦች ደግሞ ወደ ቆሻሻው ቦታ ይበራሉ። ሰዎች ሁሉ እኩል የሆነ የአእምሮ ክንፍ ተሰጥቷቸዋል። ነገር ግን አንደኛው በቅን ሃሣቡ ማር ለመስራት ወደ አበባው ሥፍራ ይበራል። ሌላው በክፉ ሃሣቡ ከቆሻሻ ውስጥ ማር ለመፈለግ ሲደክም ይኖራል። ሁለቱም የሚሰጡት ነገር ይለያያል። ንብ ጣፋጭ ማር ትሰጣለች። ዝንብ ለጤና ጠንቅ የሆነ ቆሻሻ ትሰጠናለች። ልክ እንደዚሁ ሰዎች የአእምሮ ክንፍ ተሰጥቷቸው በግል መብረር ቢችሉም ሃሣባቸው የሚውልበትና የሚያርፍበት ቦታ የተለያየ ነው። አንደኛው ሰውን የሚገነባ ጥበብ ሲሰጥ ሌላው አፍራሽ የሆነ ነገር ይሰጣል። ይህም እንግዲህ ከቆሻሻ የተገኘ ጣፋጭ ነገር ነው ሊባል ነው። ገጣሚው በእኔ ውስጥ ይህ ዓለም እንደዚህ ነው። ሁለት የማይገናኙ የተቃርኖ ጫፎችን ያስተናግዳል። ሰውም ወይ በንብ ክንፍ ወደ አበባው ቦታ ይበራል አልያም በዝንብ ክንፍ ወደ ቆሻሻው ስፍራ ይበራል። ሰው የቅራኔ ባሪያ ነው። እግዜሩ እንዲህ አድርጐ ፈጥሮታል የሚል እይታ ይኖረኛል።

ባዶ ድስት

ለሊቱ ይነጉዳል እሳቱ ይነዳል

 አልቦዘነም ጣቱ ጊዜና ጭራሮ አስሶ ይማግዳል

 ባዶ ድስቴን ልጣድ ባዶ ለማገንፈል

 ከንፍገት ይሻል እጦትን ማካፈል

 ፕሮፌሰር ለዚህ ግጥም የሰጡት ትንታኔ እንዲህ ይላል። “በእውቀቱ ሥዩም የለጋስ ስጦታን /ልግስናን/ ከቁስ አካል አምባ አውጥቶ ከፍ ባለ ደረጃ ገምቶ እምነት አካል ይዘት ያጐናፅፈዋል …. ለጋስነትን ቅን አስተሳሰብ ያደርገዋል” ብለውታል። ለእኔ ደግሞ ግጥሙ የሰጠኝ ስሜትና ትርጉም ይለያል።

የአገራችን ባለእጅ የሸክላ ድስት የሚሰራው ከአፈር ከውሃና ከእሳት ነው። በነዚህ ውስጥ አየር ይቀላቀልበታል። ሰው ይህን ይመስላል ይባላል። እንደ ገጣሚው አባባል ይህ ባዶ ድስት የሰውን ባህርይ እና ተፈጥሮ የሚወክል ይመስለኛል።

ይህ ባዶ ድስት የተባለ ሰው ኑሮ ከተባለ ምድጃ ላይ በዚህ ዓለም ተጥዶ ከኑሮው ጋር ተከትሎ በራሱ ጣት እየጐተተ በሚማግደው የመከራ ጭራሮ እራሱን እያነደደ ባዶ ማንነቱን ሲለበልብ ይኖራል። ሕይወት ባዶ ናት። ምንም ነገር የላትም። ሰው ሁሌም ፈላጊና ረሀብተኛ ነው። ከዚህ ከሸክላ አፈር ከተሰራ ማንነቱ ጋር በሚመሳሰል ባዶ ድስትነት ፈልጐ ያጣውን ለማግኘት በራሱ ጣት የመከራ ጭራሮውን እየማገደ ሲንተከተክ ይኖራል። እኔ የተረዳሁት ይህንኑ ባዶነቴን ነው። መስጠት መልካም ነው ያፀድቃል ካላችሁኝ የምሰጣችሁ ይህንኑ ባዶነቴን ነው። የእኔ ምፅዋት ለእናንተ ቀቢፀ ተስፋ ነው የሚል ይመስለኛል። የሚሰጥ ነገር በነፍስም ሆነ በስጋ አንድን ባዶ ቦታ ወይም ነገር የሚሸፍንና የሚሞላ መሆን አለበት። የሚሰጡት ልብስ ለተራቆተ ገላ መሸፈኛ ካልሆነ ወይም የሰጡት ሀሣብና እውቀት ለተራበው የሰው ልጅ መንፈስ ምግብ ካልሆነ ባዶ ነገር ማካፈል እንደ ስጦታ ሆኖ ሊቆጠር የሚችለው እንዴት ነው?

ፕሮፌሰር “….ለጋስነትን ቅን አስተሣሰብ ያደርገዋል” ቢሉም በእኔ እይታ ደግሞ ለጥቅም የማይሆን የባዶነት ልገሣ ወይም ምፅዋት ቢቀርብኝ ይሻላል። አለቃ ዘነብ እንዲህ ይላሉ። “ሸክላ ድስት እጅግ ክፉ ነው። ውሃ አርሶ አሰርቶት እሱ ግን ለእሳት መከታ እየሆነ ውሃውን ያንተከትከዋል።” ከበእውቀቱ ስዩም የባዶ ድስት ስንኝ ይልቅ የዘነብ ፍልስፍና የሕይወትን ትርጉም ይነግረኛል።

 ለድስቱ መሰራት ውሃ አንደኛውን ስጦታ አበርክቷል። ነገር ግን ሸክላ ድስት በውሃ ምክንያት ያገኘውን ማንነቱን ረስቶ በተጣደበት ምድጃ ላይ መልሶ ሕይወት የሰጠውን ውሃ ጠላት ሆኖ ለእሣት ወግኖ ሰጪውን ውሃ ያንተከትከዋል ይለናል። ባዶ ነገር የለም አንዱ ለሌላው መገኘት ምክንያት ቢሆንም ሕይወት በቅራኔ ሕግ ውስጥ አሸናፊና ተሸናፊ እየሆነች ትቀጥላለች እንጂ በቀቢፀ ተስፋ ባዶ ድስት እንደሆነች አትቀርም። ሰው አካል ብቻ አይደለም ። በተገኘበት አካል ውስጥ ሌላ መንፈሳዊ አካልም አለው የሚል ይመስለኛል።

አልወጣም ተራራ

 አልወጣም ተራራ

አልወጣም ተራራ ደመናን ልዳብስ

 ቀስተደመናውን ሽቅብ ልቀለብስ

አልዋስም እኔ ካቡነተክሌ ክንፍ

            -ከያእቆብ መሰላል

 እኔ መውጣት ሣስብ ሰማዩ ዝቅ ይላል

 ፕሮፌሰር በትንተናቸው ውስጥ በጥቂቱ እንዲህ ይላሉ። አንድ ግለሰብ ያሰበው ምርጫ ካልተሣካለት ሌላ አማራጭ መቀበል አለበት። እርቅን ሰላምን መግባባትን የሚሻ የግድ እኔ ያልኩት ይሁን አይልም ነው ትርጉሙ ብለዋል። የኔ ትርጉም ደግሞ ከዚህ ይለያል።

የግጥሙ መሠረታዊ ትርጉም እና

“ባዶ ነገር የለም አንዱ ለሌላው መገኘት ምክንያት ቢሆንም ሕይወት በቅራኔ ሕግ ውስጥ አሸናፊና ተሸናፊ እየሆነች ትቀጥላለች እንጂ በቀቢፀ ተስፋ ባዶ ድስት እንደሆነች አትቀርም”

ምስጢር ያረፈው በመጨረሻው ስንኝ ላይ ነው። “…. እኔ መውጣት ሳስብ ሰማዩ ዝቅ ይላል” የሚለው ላይ ነው። ፈላስፋው ሶቅራጥስ ሣያስቡ ከመኖር እያሰቡ መሞት ይሻላል ይላል። ማሰብ ሰውን ከእንስሳት ብቻ ሣይሆን ሰውንም ከሰው ለይቶታል ይላል። የተጠራጣሪነት ፍልስፍና አራማጅ የሆነው ሬኒ ዴካርት መኖሬን በርግጥ የማውቀው በማሰቤ ብቻ ነው። ስለዚህ ስለማስብ አለሁ ይላል። ግጥሙ በገጣሚው መንፈስ ውስጥ የሃሣብን ታላቅነት እና ልእልናን አግዝፎ ያሳያል። የሶቅራጥስ ፍልስፍና ከተጠራጣሪው ዴካርት ጋር ተደምሮ በገጣሚው መንፈስ ውስጥ ትልቅ ተፅእኖ የፈጠረበት ይመስላል።

“እኔ መውጣት ሳስብ ሰማዩ ዝቅ ይላል“ የሚለው ሀረግ ለኔ የሚሰጠኝ ትርጉም አንድ ነገር ለማግኘት ወደ ተራራው ከፍታ መውጣት አያስፈልገኝም። እኔ ሳስብ በኔ ሀሣብ ውስጥ ሰማዩ በኔ እኩል ዝቅ ይላል። በከፍታውና በዝቅታው መካከል ያለውን ባዶ ቦታ የኔ ማሰብ ይሞላዋል። ገጣሚው እንደ አብርሃም ሃሣቤን ጥዬ እምነትን ተከትዬ ልጄን ለመሰዋት ወደሞርያም ተራራ መውጣት አያስፈልገኝም። ሰማይና ምድርን ያገናኘውም የያእቆብ መሰላል ከሰማይ ወርዶ እስኪዘረጋልኝ ድረስ በእምነት አልጠብቅም። እኔ ሳስብ ብቻ ሰማዩ ዝቅ ይላል። የኔ ሀሣብ የኔ ማንነትና ህልውና መሠረት ነው ይለናል።

በያእቆብ መሰላል /በእምነት/ ወደሰማይ ብወጣም የማገኘው ባዶ ደመና ነው። እሱን ለመጨበጥ በእምነት መድከም አያስፈልገኝም። እኔ ሳስብ ብቻ ደመናው ወደኔ መጥቶ በእጄ ይጨበጣል። ይህንን ለማድረግ የሀይማኖት ተራራ ወይም መሰላል መውጣት አያስፈልገኝም። ይህንን አለም ንቄ ሄጄም በተጋድሎ የሚሰጥ የአቡነ ተክለሃይማኖት ክንፍ አያስፈልገኝም። እኔ ሳስብ ብቻ ሰማዩ ዝቅ ይላል፣ ቀስተ ደመናው ይገለበጣል ይለናል።

 “የሰናፍጭ ቅንጣት ያክል እምነት ካላችሁ ይህንን ተራራ ከዚህ ሂድ ብትሉት ይሆንላችኋል“ የሚለውን የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት የገጣሚው መንፈስ አይቀበለውም። “በምንም ነገር አትጨነቁ እሱ ስለ እናንተ ያስብላችኋል“ የሚለውንም የጳውሎስ መልእክት የገጣሚው መንፈስ “ሞኝህን ብላ” እኔ ካላሰብኩ አልኖርም። ስለዚህ አስባለሁ። ስለዚህም አለሁ የሚል ይመስለኛል።

 “በእምነት ከሆነ የገዛ ልጅንም ቢሆን ማረድ ኀጢአት አይደለም” የሚለው የኪርጋርድ ፍልስፍና ለገጣሚው መንፈስ አይዋጥለትም። ኪርጋርድ እምነት የሚጀምረው አንድ ሰው ማሰብ ሲያቆምና በስሌት መራመድን ሲያበቃና ምክንያት መደርደር ሲተው ነው ይላል። የገጣሚው መንፈስ ግን ከዚህ ጋር አይስማማም። ጮክ ብሎ አልወጣም ተራራ እኔ መውጣት ሣስብ ሰማዩ ዝቅ ይላል እናም እባካችሁ አትሞኙ ከምታምኑ አስቡ …. አስቡ …. አስቡ የሚል ትርጉም ይሰጠኛል።

 ከጅምሬ እንዳልኩት ግጥሞቹ በብዙ አቅጣጫ ትርጉም ሊያሰጡ የሚችሉ ሆነው መጻፋቸው የስራውን ጥልቀትና ውበት ይናገራሉ። ይህም ስለሆነ ነበር ፕሮፌሰር ካዩበት አቅጣጫ ወጥቼ እኔ ደግሞ በዚህ አቅጣጫ እንደሚታየኝ ሀሣቤን በጽሑፍ ሳሰፍር እኔም እንደ ፕሮፌሰር ሽብሩ ሌላ አንባቢ የራሱ እይታና ትንታኔ ካለው በጉዳዩ ላይ እንዲሳተፍ ግብዣዬን አቀርባለሁ። ወይም የመጽሔቱ ዝግጅት ክፍል በእውቀቱ ስዩምን ፈልጐና አፈላልጐ ጠይቆና አጠያይቆ ሀሣቡን ከሀሣባችን ሚስጥሩን ከሚስጥራችን ትርጉሙን ከትርጉማችን ጋር ቢያስታርቅልን ጥሩ ይሆናል በማለት ቀሪውን ስራ ለአዘጋጁ በመተው ጽሑፌን አጠቃልላለሁ። አመሰግናለሁ።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top