በላ ልበልሃ

የአሜሪካ ሚዲያ፤ ዶናልድ ትራምፕ እና የውዝግባቸው አንድምታ

ብዙ ጊዜ መለስ ብለን ስለማናስተውለው እንጂ ጋዜጠኝነት ብዙዎች በጀግንነት የተሰውለት፤ የታሰሩለት እና የተሰደዱለት ሙያ ነው። በዓለማችን በአደገኛ ቦታዎችም ጭምር በመገኘት ህዝባቸው ማግኘት የሚገባውን ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኝ ጋዜጠኞች ብዙ መስዋእትነት ከፍለዋል። እንደ አሜሪካዊው ዳንኤል ፐርል ያሉት ደግሞ ለዚህ ሙያ ካላቸው ፍቅር የተነሳ የእውነትን ምንጭ በማሳደድ ሂደት ራሳቸውን ለአደጋ ከማጋለጥ አልፎ ህይወታቸውን እስከመሰዋት ደርሰዋል። በሃገራችንም ቢሆን ብዙዎች ከዚህ ያላነሰ መከራ ደርሶባቸዋል።

አሜሪካ ጋዜጠኝነት ቀድሞ ስራ ላይ ከዋለባቸው ሀገራት ተርታ እንደመሆኗ መጠን ብዙውን የጋዜጠኝነት አሰራርና ፍልስፍና ለዓለም ያበረከተች ሀገር ነች። በዚች ሃገር የሚተገበረው ጋዜጠኝነትም ለብዙ ሌሎች ሃገራት በተለይም በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት እንደተምሳሌት ሲወሰድ ቆይቷል። ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታየ ያለው በአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕና በአንዳንድ የዚያ ሃገር ሚዲያዎች መካከል የሚታየው ውዝግብ ይህን ለብዙ ዓመታት እንደ ተምሳሌት ሲወደስ የኖረ የሚዲያ ባህል ከጥያቄ ውስጥ ያስገባ ሆኗል።

 ዶናልድ ትራምፕ የማይወዱትን ዘገባ ሃሰተኛ ዜና (Fake News)፤ የማይመቻቸውን የሚዲያ ተቋም ደግሞ ተቃዋሚ ፓርቲ፤ ከዚያም አልፎ የመንግስት ጠላት (Enemy of the state)፤ ጋዜጠኞችን ደግሞ የህዝብ ጠላቶች (enemy of the people) ብለው ያለምንም ማንገራገር እስከመፈረጅ የደረሱ እና እንዲህም ሲሉ ምንም የማይሰቀጥጣቸው ሰው መሆናቸውን ብዙዎቻችን ታዝበናል። ከዚህም አልፎ ጫን ያለ ጥያቄ የጠየቀን ጋዜጠኛ ቀጣሪ ተቋማቱ ከስራ እንዲያባርሩ የሚጠይቁ ደፋር መሪ ናቸው። የስም ማጥፋትን (libel) የመሳሰሉ ህጎች ጋዜጠኛን ለመቅጣት በሚያመች መንገድ እንደገና ተሻሽለው እንዲቀረፁ ሲጠይቁም በጆሯችን ለማመን እየተቸገርን ሰምተናቸዋል።

ከዚህም ባለፈ ፕሬዚዳንቱ ኒውዮርክ ታይምስን፤ ዋሽንግተን ፖስትን፤ ሲ ኤን ኤንን እና ኤን ቢ ሲን የመሳሰሉ በሀገሪቱ ስመጥሩና ገናና የመገናኛ ብዙሃንን ሙሰኞችና የረከሱ እያሉ በማብጠልጠል በደጋፊዎቻቸው ዘንድ እንዲወገዙ የተሳካ ጥረት አድርገዋል። ይህም አንዳንድ ጸሐፍት እንደሚሉት ያልተጠበቀና እንዲያውም ከ1797 እስከ 1801 ከመሩት ከጆን አዳምስ የፕሬዚዳንትንት ዘመን ጀምሮ በአሜሪካ ምድር ያልታየ ተግባር ነው።

 የፕሬዚዳንቱን የመጀመሪያ ዱላ የቀመሰችው የፎክስ ዜና አንባቢ (anchor) ሚጊ ኬሊ ስትሆን ይህም በ2016 (እ.ኤ.አ) የምርጫ ዘመቻ ወቅት ነበር። ፕሬዚዳንቱ ይህችን ጋዜጠኛ “ከሚገባት በላይ የተራገበላት ሴት ናት” ከማለትም አልፈው ሰዎች የሷን ሾው እንዳይመለከቱ ለማሳደም ጥሪ አድርገዋል። የዋዛ ያልሆነችው ኬሊ ግን ፕሬዚዳንቱን “ከታዋቂ ጋዜጠኞች ጋር ጤናማ ያልሆነ ፆታዊ ስሜት የተጠናወታቸው” ስትል ወርፋቸዋለች። በርግጥ ኬሊ በዚህ ዙሪያ የጻፈችው መጽሐፍ በሚሊዮን ዶላሮች ተቸብችቦላታል።

 በዚሁ የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ፕሬዚዳንቱ ጋዜጠኞችን ከአዳራሾች ሲያስባርሩና የካሜራ ሰዎችን በደጋፊዎቻቸው ካሜራቸውን ሲያስነጠቁ ነበር። ከተመረጡም በኋላ ብዙ የማይፈልጓቸውን ጋዜጠኞች ለይተው ወደ ዋይት ሃውስ እንዳይገቡ ክልከላ አድርገዋል። በቅርቡ በሲ ኤን ኤን የዋይት ሃውስ ዘጋቢ ጂም አኮስታ ላይ የደረሰውን ማስታወስ በቂ ይመስላል። በስደተኞች ጉዳይ ላይ በተነሳው የጋዜጠኛው ተደጋጋሚ ጥያቄ የተናደዱት ፕሬዚዳንቱ ድምጽ ማጉያውን በዋይት ሃውስ ተለማማጅ (intern) እንዲቀማ ሲያስደርጉ የተከሰተውን የስጠኝ አልሰጥም ልፊያ የብዙ ሚዲያ ቀልብ የሳበ እንደነበር እናስታውሳለን። የዋይት ሃውስ ሰዎች ቪዲዮው ኤዲት ተደርጎ ኮስታ በልጅቷ ላይ በክርኑ ጥቃት እንደፈጸመ ለማስመሰል ቢጥሩም ጉዳዩ በኋላ ላይ ተጋልጧል።

 የ2013 የፑሊዘር ሽልማት (Pulitzer Prize) አሸናፊው ብሬት ስቲቨንስ እንደሚለው የፕሬዚዳንቱን ተግባራት እንደሞኝነት ማየት ራሱ ጅልነት ነው። ይልቁንም በሚዲያ ላይ ፕሬዚዳንቱ የሚያደርጉት ነገር እንደብልጣብልጥነት ቢታይ እንደሚሻል ስቲቨንስ ይመክራል። እንደዚህ ሰው አባባል ትራምፕ በሚዲያ ላይ የሚጠቀሙት ዘዴ በፖለቲካ፤ በርዕዮት አለምና በፍልስፍና ዘዴ ከሚደረገው ይልቃል። በርዕዮተዓለሙ በኩል ሲታይ ካሉት ሚዲያዎች ትራምፕ ለሳቸው የሚመቹትን ለማስቀደም በዜና ፈንታ ፕሮፖጋንዳን ለማግነን ሲጥሩ ይታያል። በተጨማሪም በህዝቡ ዘንድ ተአማኒ ነገር እንዳይኖር አንድ እውነታ ብቻ ሳይሆን ብዙ የእውነታ አማራጮች (alternative facts) እንዳሉ ህዝቡ እንዲያስብ ያደረጉት ጥረት ተሳክቶላቸዋል።

 በእርግጥም አስተውሎ ላየው በትራምፕ ዘመን በሚዲያ ላይ የሚደረገው የጥቃት ዘመቻ የሚካሄደው በተለየ አሰላለፍ ነው። ያ ማለት በዚህ ተግባራቸው ፕሬዚዳንቱ ብቻቸውን እንዳይመስሏችሁ። ከታች በፕሬዚዳንቱ ላይ የተቃጣን ማንኛውንም አሉታዊ ዜና የሚያጣጥሉና የዜናዎቹን ዘጋቢ ጋዜጠኞችን የሚያብጠልጥሉ ቀኝ ዘመም የአክቲቪስት ሰራዊት አሉላቸው። ከላይ በፕሬዚዳንቱና በታችኛው ሰራዊት መሃከል ደግሞ በአማካይነት የፕሬዚዳንቱ ቀኝ እጅ የሆኑት የሚዲያ ተቋማት ተሰልፈዋል። እንደ ዘ ዴይሊ ኮለር፤ ብሬትባርት፤ ድሩጅ ሪፖርት እና በተለይም ፎክስ ኒውስ ያሉ የሚዲያ አውታራት ለፕሬዚዳንቱ ቀኝ እጅ ሆነው ፕሬዚዳንቱን ከታችኛው ደጋፊ ጋር የማገናኘቱን ሚና ይጫወታሉ።

 ከሁሉ በላይ ፕሬዚዳንቱ በሚዲያ መጠላታቸው በደጋፊዎቻቸው ዘንድ እንደ ብቸኛ ታጋይ እንዲታዩ ሲያደርጋቸው፤ በተቃራኒው ደግሞ ሚዲያዎች ይህን ታጋይ ለመጣል እንደሚንቀሳቀሱ ጠላቶች እንዲታዩ አድርጓቸዋል። እንደ ሮሰን ጄይ አገላለጽ ገለልተኛ ድምፆች በመጨረሻ እየተጣጣሉ ከጫወታ ይወጡና ትራምፕ በራሳቸው ጉዳይ ላይ ብቸኛ የመረጃ ምንጭ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል።

ትራምፕ ዜናውን ሁሉ ስለራሳቸው ማድረግ የሚችሉበትን ምስጢራዊ ዘዴ የተጎናጸፉ ሰው ናቸው። ብዙ ሰው ያልተገነዘበው ነገር ቢኖር በእኝህ ፕሬዚዳንትና በሚዲያ መካከል የተፈጠረው እሰጥ አገባ ሁለቱንም ወገኖች የጠቀመ መሆኑ ነው። በአንድ በኩል የሚዲያን ትኩረት አጥብቀው የሚሹት ፕሬዚዳንቱ ከተሰጣቸው ሰፊ ሽፋን ተጠቃሚ ሲሆኑ በሌላ በኩል በዚህ ዜና ሰበብ ከሚገኘው ብዙ አድማጭ/ተመልካች ብዙ የሚዲያ ተቋማትም አትራፊ ሆነው እናገኛቸዋለን። ለምሳሌ እንደ ጆን ሩተንበርግ ዘገባ በማርች 2016 የፎክስ ኒውስ የተመልካች የምልከታ መጠን (rating) ከቀደመው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ40 ፐርሰንት አድጓል። ከዚህም በበለጠ ሲ ኤን ኤን በትራምፕ ላይ በሚያደርገው ከፍተኛ ሽፋን ምክንያት የምልከታ መጠኑ 170 በመቶ አድጎ መገኘቱ የሚዲያ ተቋማቱ በፕሬዚዳንቱ ፈር የለቀቀ ባህሪ ላይ በመዘገባቸው እንዳተረፉ መገመት አያዳግትም።

 የፕሬዚዳንቱ አካሄድ ሚዲያ ያደረሰባቸውንና ያልተገባ ያሉትን ዘገባ በመተቸት ፈንታ እሳቸው ያተኮሩት በሚዲያ ላይ ጭፍን ጥላቻ እንዲፈጠር ወደማድረጉ ነው። የፕሬዚዳንቱ ዋና ጥል ከጋዜጠኝነት ዋና መርህ ከሆነው ገለልተኝነት ጋር የሆነ ይመስላል። ምክንያቱም እሳቸው የሚሹት ሁሉም ሚዲያ ወግኖላቸው እንዲሰራ ነውና። በዚህ የፕሬዚዳንቱ ተግባር ፕሬስ ከህዝቡ ጋር ያለውን ግንኙነት ሊያጣው ይችላል የሚለው የብዙኃን ፍራቻ ነው።

 ሚዲያውን በህዝብ ዘንድ የማስጠላት ሂደት አፍራሽ ስድቦችንም በመጠቀም የሚካሄድ ነው። “ፕሬሶች ቀጣፊዎች ናቸው፤ የማይታመኑ ሰዎች ናቸው፤ በጣም የማይረቡ ናቸው፤ ልክ እንደ ጥንብ አንሳ ናቸው” የሚሉት በፕሬዚዳንቱ በየመድረኩ የሚሰሙ ስድቦች ናቸው። የትዊተር አካውንታቸው እንደሚያሳየው ፕሬዚዳንቱ በመልእክቶቻቸው ውስጥ እስካሁን ሃሰተኛ ዜና የሚለውን ሀረግ 281 ጊዜ መጠቀማቸውን ያሳያል። ብዙዎችን ያስገረመው የሪፐብሊካኑ ፓርቲ ምሁራን ትራምፕ እንደ ሚዲያ ባሉ ጠቃሚ የዲሞክራሲ ተቋማት ላይ የሚያደርሱትን ቅጥ ያጣ ጫና መቃወም አለመቻላቸው ነው። እነዚሁ ምሁራን ግን በፕሬዚዳንቱ ኢላማ ስር የወደቁትን ስመ ጥሩዎቹን ኒውዮርክ ታይምስን፤ እና ዋሽንግተን ፖስትን፤ ጠዋት ጠዋት ሳያነቡ ከቤታቸው እንደማይወጡ ይነገራል።

ሱዛን ክሬግ የተባለች የኒዮርክ ታይምስ የምርመራ ጋዜጠኛ እንደምትለው ፕሬዚዳንቱ ጋዜጠኞችንና የሚዲያ ተቋማትን ለመክሰስ መዛታቸው፤ የሚዲያ አባላትን በስድብ ማጥቃታቸው፤ የሚጠሏቸውን ጋዜጠኞች ከዋይት ሃውስ ገለፃ (Brief) ላይ ማባረራቸው እና ሌሎች በሚዲያ ላይ የሚደረጉ ጥቃቶች ሆን ተብለው የተፈጸሙና በብዙ መልኩ ሚዲያውን ለማሸማቀቅ የታቀዱ ተግባሮች ናቸው። “እንደኔ አስተሳሰብ“ ትላለች ሱዛን “ጋዜጠኝነትን በተመለከተ በጣም ወደሚያስፈራ ምዕራፍ እየገባን እንደሆነ ይሰማኛል።

“ ፕሬዚዳንት ትራምፕ በሚዲያ ላይ እያደረሱት ያለው ጥቃት የቆሰለ አውሬን ቁስሉ ላይ እንደመርገጥ ነው ይላሉ አንዳንድ ጸሐፊዎች። ምክንያቱም ምላሹ በጣም የሚከብደው ለፕሬዚዳንቱም ጭምር ስለሚሆን ነው። ለምሳሌ በነሃሴ ወር 2018 ቢቢሲ ባወጣው ዘገባ 300 የሚጠጉ የሚዲያ ተቋማት ፕሬዚዳንቱ በሚዲያ ላይ የሚያደርሱትን ጥቃት የሚቃወምና ነፃ ፕሬስን የሚያወድስ ዘመቻ በርዕሰ አንቀጾቻቸው በማውጣት ተቃውሟቸውን በይፋ ለማሳየት እርምጃ ጀምረዋል።

 ዘ ስታር ጋዜጣ በርዕሰ አንቀጹ እንዳስነበበው ትራምፕ ሁሉንም የሚዲያ መረጃ ሃሰተኛ ዜና ብለው መፈረጃቸው በውስጥ በሃገሪቱ ላለው የዲሞክራሲ መሰረት ትልቅ አደጋ ከመሆኑም በላይ በውጪም በአንዳንድ ሃገራት ላሉት አምባገነኖች በሃሳብ ነፃነት ላይ አፈና እንዲፈጽሙ ቀጥተኛ ያልሆነ ፈቃድ እንደመስጠት ይቆጠራል ብሎታል። የተባበሩት መንግስታት ኤክስፐርቶችም ትራምፕ በሚዲያ ላይ የሚያደርጉት የጥላቻ ቅስቀሳ በጋዜጠኞች ላይ ጥቃት እንዲደርስ የማድረግ አቅም እንዳለው በመግለጽ አስጠንቅቀዋል። በእርግጥም ደግሞ አንዳንድ ጋዜጠኞች ከትራምፕ ደጋፊዎች ዛቻና ማስፈራሪያ እንደሚደርሳቸው ይናገራሉ።

እንደ ታራ መክሌቪ ገለፃ በአሜሪካ ህዝቡ በሚዲያ ላይ ያለው እምነት ከምንጊዜውም በታች ሆኖ ያለ ሲሆን ፕሬዚዳንቱ ይህንን ይበልጥ በማባባሱ ስራ ላይ ተጠምደው ይገኛሉ። ኩኒንፕያክ ዩኒቨርሲቲ ባደረገው ዳሰሳ ጥናት ለምሳሌ 51 በመቶ ሪፐብሊካን ሚዲያ አስፈላጊ የዲሞክራሲ አካል ነው በማለት ፈንታ የህዝብ ጠላት ነው ብለው እንደሚያምኑ አሳይቷል። ከነዚሁ ደግሞ 23 በመቶዎቹ ትራምፕ እንደ ሲ ኤን ኤን እና ኒዮርክ ታይምስ ያሉ የሚዲያ ተቋማት እንዲዘጉ እንደሚፈልጉ ድምጽ ሰጥተዋል።

ስለዚህ በሚዲያ ላይ የሚደረገው ጥቃት በግፊት የሚፈለገውን ተመራጭ ለማስመረጥ የሚፈፀም ተግባር ብቻ ተደርጎ መወሰድ እንደሌለበት ብዙሃን ይመክራሉ። ይህ አካሄድ ህዝቦች በስርአቱ ላይና በስርአቱ ውስጥ የሚጠብቋቸውንና እያገለገሏቸው ባሉ ተቋማት ላይ ጭምር ያላቸውን ጭፍን ጥላቻ የሚያባብስ ነው። ለአሁኑ ግልጽ ሆኖ የሚታየው ነገር ፕሬዚዳንት ትራምፕ እስካሉና ሃይ የሚላቸው አካል እስካልመጣ ድረስ በሚዲያ ህልውናና በባለሙያዎቹ ላይ የሚያደርሱት ጉዳት የሚቀጥል ይመስላል። ምኞታችን ይህ ባህል ወደ ሌሎች ሃያላን ሃገራት እንደይዛመትና የዚህን ሙያ ግብአተ መሬት እንዳያፋጥነው ነው።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top