ከቀንዱም ከሸሆናውም

አስደማሚዎቹ የኪነ-ሕንጻ ጥበቦች በኢትዮጵያ

“በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ታሪክ ውስጥ ስማቸው በገናናነት ከሚጠቀሱ ሴቶች ለዛሬ ሦስቱን ላንሳ። ሦስቱ የኢትዮጵያ ሴቶቸ አለምን የሚያስደምሙ ስራዎችን አከናውነው ያለፉ ናቸው።”

ንግሥተ ሣባ

ገና የሰው ልጅ መንግሥት የሚባል ስርአት ሳይመሠርት አክሡም ውስጥ የዛሬ ሦስት ሺ አመታት ዘመናዊ መንግሥት መስርታ ውብ ኪነ-ሕንፃዎችን የገነባችው ንግሥተ ሣባን ማስታወስ እንችላለን። ሣባ / ማክዳ/ አክሡም ከተማ ውስጥ የዛሬ ሦስት ሺ አመታት ድንቅ የሚባሉ ግንባታዎችን አከናውናለች። ለምሣሌ ዛሬ ፍርስራሹ የሚገኘው ቤተ-መንግሥቷን ማስታወስ ይቻላል። ይህ ቤተመንግሥት የተሠራው እጅግ ማራኪ በሆነ ስፍራ ላይ ሲሆን ለበርካታ አገልግሎቶች የሚሆኑ አያሌ ክፍሎች አሉት። የሥነ-ቁፋሮ ሊቆች / አርኪዮሎጂስቶች/ ይህን ቤተመንግሥት የአክሡማውያን ድንቅ ችሎታ የታየበት ኪነ-ሕንፃ መሆኑን ይናገራሉ። የታሪክና የባሕል ሊቆች ደግሞ ንግሥተ ሣባ በዘመኗ ገናና መሪና ጥበብን የምትሻና የምታደንቅ ነበረች ይላሉ። ጥበብን በተመለከተም የተናገረችው ‘ክብረ ነገስት’ ተብሎ በሚታወቀው መጽሐፍ ውስጥ በሠፊው ሠፍሮ እንደሚገኝ ያብራራሉ።

“ንግሥተ ሣባ ለዚህ ሁሉ ዕውቅና ብሎም ታሪክ ዋነኛዋ ተጠቃሽ ነች። በኢትዮጵያ የሴቶች የኮንስትራክሽን ጥበብ ውስጥ የአንበሣዋን ድርሻ ትወስዳለች”

ከዚህ በተጨማሪም የንግሥተ ሣባ ታሪክ እንደሚያሣየው ጥበብን ፍለጋ ወደ ኢየሩሣሌም በመሄድ ከንጉስ ሰለሞን ዘንድ ደርሣ ጥበብን የተቀበለች፤ የተቀባች ሴት ከመሆን ባለፈ ከሰለሞን ጋርም በደም የተሣሠረ ወዳጅነት መስርታ ቀዳማዊ ምኒልክን ወልዳለች።

ይህች በጥበብ አለም ውስጥ ተጠቃሸ የሆነች ሴት በዘመነ አገዛዟ የተለያዩ ግንባታዎችን በአክሡም ከተማ ውስጥ በማከናወን ታሪካዊት ሴት ለመሆን በቅታለች። ዛሬ አክሡም ከተማ ውስጥ ተገማሽሮ የሚታየው የንግሥተ ሣባ የመዋኛ ገንዳ የተገነባው የዛሬ ሦስት ሺ አመት ነው። አሁንም ዘመናዊ ይመስላል።

 አክሡም ውስጥ በ1906 ዓ.ም መጥተው የአርኪዮሎጂ ጥናት ያደረጉት ጀርመናዊው ኢኖ ሊትማን በተከታታይ ባሣተሙት Expedition of Axume በተሠኘው መጽሐፋቸው ውስጥ እንዳስተዋወቁት ከሆነ አክሡም በምድሪቱ ላይ ካሉት የኮንስትራክሽን ጥበቦች መካከል አንዱ ነው። ለአክሡም ምስረታ እና ማበብ ከፊት ሆና የምትጠራው ደግሞ ንግሥተ ሣባ ነች። የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሣይንስ እና የባሕል ድርጅት ማለትም UNESCO አክሡም ከተማንና በውስጧ ያሉትን ኪነ-ሕንፃዎች የአለም ቅርስ ናቸው ብሎ ከመዘገባቸውም ቆይቷል። ታዲያ ንግሥተ ሣባ ለዚህ ሁሉ ዕውቅና ብሎም ታሪክ ዋነኛዋ ተጠቃሽ ነች። በኢትዮጵያ የሴቶች የኮንስትራክሽን ጥበብ ውስጥ የአንበሣዋን ድርሻ ትወስዳለች።

መሰቀል ክብራ

 መስቀል ክብራ፤ በኢትዮጵያ የሴቶች አለም ውስጥ ድንቅ ጥበበኛ እንደሆነች ይነገራል። መስቀል ክብራ የታላቁ ጥበበኛ የቅዱስ ላሊበላ ባለቤት ነች። ቅዱስ ላሊበላ እነዚያን የፕላኔቷን አስደማሚ የኪነ-ሕንፃ ውጤቶች ሲሠራ ከጐኑ የነበረች፤ ከርሱ ጋር በጥበብ አለም ውስጥ ገብተው እስከ ዛሬ ድረስ የአሠራር ምስጢራቸው ያልታወቁትን አብያተ ክርስቲያናትን ከአለት ፈልፍለው አንፀዋል።

የዛሬ 800 አመታት ሰሜን ወሎ ውስጥ ላስታ ቡግና ወረዳ ውስጥ ሮሃ ከተባለች ቦታ ላይ የታነፁት እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት ምንም እንኳ መጠሪያቸው በቅዱሰ ላሊበላ ይሁን እንጂ የባለቤቱ የመስቀል ክብራ አስተዋፅኦ ከርሱ እንደማይተናነስ መገንዘብ እንችላለን። ግንዛቤያችንን የሚያሠፋው ደግሞ ስለ እሷ የተፃፈው ገድል ነው። ይህ የሕይወት ገድሏ ከላሊበላ ከተማ ወጣ ብላ በምትገኘው በገነተ ማርያም ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ ይገኛል።

እንደ መስቀል ክብራ ገድል አገላለፅ የቅዱሰ ላሊበላ ኪነ-ሕንፃዎች ሲሠሩ አምላካዊ ፀጋ እና ጥበብ ላስታ ላሊበላ ውስጥ እንዲሠፍን አምላኳን ሌት ተቀን የምትለምን የምትፀልይ ፍፁም ሐይማኖተኛ ነበረች።

 እናም ፈጣሪ ካለምንም ስሕተት ኪነ-ሕንፃዎቹ እንዲሠሩ በረከቱንና ፀጋውን ላሊበላ ላይ እንዲያወርድ ላሊበላን በጥበብ እንዲቀባው መስቀል ክብራ ትፀልይ ነበር። በፀሎቷ ውስጥ የሚታያትን ርዕስ በመናገር ቆማ የምታሠራ የ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መንፈሣዊ አርክቴክት ነበረች።

መስቀል ክብራ በገድለ ታሪኳ ውስጥ በግልፅ ሰፍሮ የሚገኘው ታሪክ እንደሚያስታውሰው በተለይ አባ ሊባኖስ የተሠኘው ቤተክርስቲያን ላሊበላ ውስጥ ከታነፁት ፍልፍል የኪነ-ሕንፃ ሥራዎች መካከል አንዱ ግማሽ አካሉ ሙሉ በሙሉ ከአለት ያልተላቀቀ ነው። የፊተኛው ገፅታው ከአለት ተላቆ የሚታይ ሲሆን ውበትና ትንግርትን ካጣመሩ የኘላኔቷ ሕንፃዎቸ መካከል አንዱ ለመሆን በቅቷል። መስቀል ክብራ ደግሞ ለዚህ ሕንፃ መታነፅ ዋነኛዋ አርክቴክት ነበረች።

 የዚህች ሴት የጥበብ አሻራ ያረፈባቸው የቅዱስ ላሊበላ ኪነ-ሕንፃ ሥራዎችን በተመለከተ በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ከጐበኘ በኋላ ግዙፍ መጽሐፍ ያሣተመው ፖርቱጋላዊ ፍራንሲስኮ አልቫሬዝ ሲጽፍ እንዲህ ብሏል።

 ‹‹ስለ ቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት አሠራር ምስጢራዊነት ይህን ይመስላሉ ብዬ ብጽፍ የሚያምነኝ የለም። ነገር ግን የምጽፈው ሁሉ እውነት መሆኑን በኃያሉ እግዚአብሔር ስም እምላለሁ።››

 ፍሪንሲስኮ አልቫሬዝ በመሐላ ጭምር እየታገዘ የሚገልፃቸው እነዚህ የኪነ-ሕንፃ ሥራዎች እስከ ዛሬ ድረስ የአሠራራቸውን ምስጢር በተመለከተ የተረጋገጠ ጥናት አልተደረገም። እጅግ ብዙ የሚባሉ የሃገራችን እና የመላው አለም የኪነ-ሕንፃ ተመራማሪዎች ወደ ስፍራው እየመጡ ካጠኑ በኋላ የሚያወጧቸው ጽሑፎች እንደሚገልፁት የላሊበላ የኪነ-ሕንፃ ሥራዎች ምስጢራዊ ናቸው። አሠራራቸውን ለማብራራት ከባድ ነው ይላሉ። ሌሎች ተመራማሪዎች ደግሞ አሠራራቸው ላይ መንፈሣዊ ፀጋና በረከት አለ ይላሉ። ታዲያ ለዚህ ሁሉ ትንግርታዊ ጥበብ ከቅዱስ ላሊበላ ባልተናነሠ ብዙ አስተዋፅኦ ያደረገችው ባለቤቱ እቴጌ መስቀል ክብራ ነች።

የመስቀል ክብራ የጥበብ አሻራ ያረፈባቸውን እነዚሁኑ የቅዱስ ላሊበላ አብያተ-ክርስቲያናት በተመለከተ የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሣይንስ እና የባሕል ድርጅት (UNESCO) የምድሪቱ ትንግርት (Wonders of the World) በማለት የአለም ቅርስ መሆናቸውን መዝግቧል። የሰው ልጅም ወደ ላስታ ላሊበላ በመጓዝ እንዲመለከታቸው UNESCO ይጋብዛል። ስለዚህ በኢትዮጵያ የኪነ- ሕንፃ ታሪክ ውስጥ መስቀል ክብራ ከኢትዮጵያ ሴቶች ገናና ስም እና ዝና ያላት መሆኗን ያሣያል።

እቴጌ ምንትዋብ

ጐንደር ውስጥ በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ተነስተው ከነበሩት ገናና መሪዎች መካከል አንዷ ናቸው። በሕይወት ታሪካቸው ውስጥ እጅጉን ጐልቶ የተጻፈውና ዛሬም ድረስ እማኝ ሆኖ የሚጠራላቸው ጉዳይ ጥበበኝነታቸው ነው። ጥበብን በሁሉም ዘርፍ የታደሉ መሪ ነበሩ። አንደኛው በፖለቲካ አመራራቸው ለሀገራቸው ሕዝብ እድገትና ስልጣኔ ስላመጡት ለውጥ ጥበበኛ ይሏቸዋል።

ሁለተኛው ደግሞ በጐንደር እና አካባቢዋ የገነቧቸው ሕንፃዎች፣ የሰሯቸው አብያተ ክርስቲያናት ለኪነ ሕንፃ ጥበብ ያላቸውን ፍቅር በማየት ጸሐፊዎች ጥበበኛዋ ንግስት ይሏቸዋል። እቴጌ የቋራ ሴት ናቸው። ወደ ጐንደር ከተማ የመጡት በጋብቻ ነው። ኢትዮጵያን ከ1713-1723 ዓ.ም የመሩት አጼ በካፋ ወዳጅ ዘመዶቻቸውን አንድ ነገር አደራ ይላሉ። እኔ የማገባት ሴት በኢትዮጵያ ውስጥ ውብ እና ቆንጆ ከመሆኗ ባሻገር ጥበበኛ፣ አርቃ አሣቢ እና ብልህ ሴት ፈልጉልኝ ይላሉ። ሁሉም ይህችን ሴት ፍለጋ ውስጥ ገባ።

“እኔ የማገባት ሴት በኢትዮጵያ ውስጥ ውብ እና ቆንጆ ከመሆኗ ባሻገር ጥበበኛ፣ አርቃ አሣቢ እና ብልህ ሴት ፈልጉልኝ ይላሉ። ሁሉም ይህችን ሴት ፍለጋ ውስጥ ገባ። በመጨረሻም ምንትዋብ ተገኙ”

 በመጨረሻም ምንትዋብ ተገኙ። ወደ ጐንደርም መጡ። ከአጼ በካፋ ጋር ጋብቻ ፈፀሙ። ወደ ኢትዮጵያ የፖለቲካ እና የአስተዳደር ዘርፍ ውስጥ ውብ እና ጥበበኛ ሴት መጣች።

 እቴጌ ምንትዋብ ከባለቤታቸው ከአጼ በካፋ ጋር በመሆን በጐንደር ከተማ የሚገኘውንና ግብር ቤት ተብሎ የሚጠራውን ባለ ታላቅ ግርማ ሞገስ ሕንጻ አሠሩ። ከዚያም ባለቤታቸው አጼ በካፋ ከዚህ አለም በሞት ሲለዩ የ8 አመት ልጃቸው ኢያሱ እንዲነግስ ተደረገ። ነገር ግን ሀገሪቱን የማስተዳደር ስራው የተሠጠው ለእናቱ ለእቴጌ ምንትዋብ ነው። እቴጌ ምንትዋብ ከልጃቸው ጀርባ እና ጐን እንዲሁም ከፊት እየሆኑ ኢትዮጵያን መምራት ጀመሩ።

 በአገዛዝ ዘመናቸውም ጐንደር ከተማ ውስጥ የሚገኘውን ቀጭን ፈታዮችና ወይዛዝርት ግንብ ተብሎ የሚጠራውን እጅግ ውብ ሕንፃ አሠሩ። ሕንፃው የተሠራው ሴቶችን ፈትል እና ሙያ ለማስተማር ነው። ከዚያም ባለ ሁለት ፎቅ የሆነ ይህም እጅግ በጣም ማራኪ እንደሆነ ዛሬም የሚመሰክረውን ቤተ-መንግሥታቸውን ጐንደር ላይ አገማሸሩት። እቴጌ ምንትዋብ መች በዚህ ብቻ አቆሙ። ከጐንደር ከተማ አፋፍ ላይ ቁስቋም ማርያም የተሠኘች ቤተ-ክርስቲያን አሣነፁ። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ውስጥ ትልቅ እመርታ ያመጡ ንግስት ናቸው። በዚህች ቁስቋም ማርያም ውስጥ መዘምራን፣ ቀሣውስት፣ የአብነት ተማሪዎች፤ ቅኔ ‘ወረቡ’ አቋቋሙ፣ ወዘተ ትምህርት ይሠጡበት ነበር። ጐንደር ዋነኛዋ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት መናኸሪያ እንድትሆን የዕውቀት እና የስልጣኔ ከተማ በማድረግ ረገድ እቴጌ ምንትዋብ ያበረከቱት አስተዋፅኦ እንዲህ በቀላሉ ተነግሮ የሚያልቅ አይደለም።

 ለምሣሌ እሳቸው ዘንድ ብቻ የነበሩ የምድሪቱን ሁለት ድንቅ ነገሮች ላውጋችሁ። አንደኛው የመጽሐፍ ቅዱስ አንድ ክፍል የሆነው መጽሐፈ ሄኖክ ነው። በግዕዝ ነው የተፃፈው /የተተረጐመው/። ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በአለም ላይ ጠፍቶ ነበር። እሳቸው ዘንድ ግን ተጠብቆ ቆይቶ ነበር። ሁለተኛው ‘ክብረ ነገስት’ የተባለው የነገስታትን ስርወ አወራረድ የያዘው መጽሐፍ ነው። ጀምስ ብሩስ የተባለው የስኮትላንድ ተጓዥ ወደ ጐንደር መጥቶ እነዚህን ሁለት ቅርሶች እና ሌሎችንም በመስረቅ ወደ አውሮፓ ወስዷቸዋል። በኋላም በተለይ መጽሐፈ ሄኖክ በግዕዝ ቋንቋ ተፅፎ በመገኘቱ አለም ተደነቀ፣ ተገረመ። ከዚያም የጐደለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ከግዕዝ ተተርጉሞ ለመላው ክርስቲያን ቀርቧል። አሁን የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሣይንስ እና የባህል ድርጅት እጅግ የተከበረ የምድሪቱ ቅርስ በማለት እነኚህን በእቴጌ ምንትዋብ አማካኝነት ተጠብቀው የቆዩትን ቅርሶች መዝግቧቸዋል።

 ከነዚህ በተጨማሪም እቴጌ ምንትዋብ ከቁስቋም ቤተክርስቲያን ጐን ቤተ-መንግሥታቸውን አንፀዋል። ይህ ቤተመንግሥት ትልቅ ግርማ ሞገስ ያውና ጣና ሃይቅን አሻግሮ ማየት የሚቻልበት ቁመና የነበረው ነው። ይህ ቤተመንግሥት የተሠራው በአንድ ሺ ሙያተኞች ነው ይባላል። 500 ሙያተኞች ሲሠሩ የቀሩት 500 ሙያተኞች ደግሞ ቁጭ ብለው በማየት ስህተቶችን ይጠቁሙ ነበር ተብሎ ተጽፏል። ለዚህም ነው እጅግ ውብ ኪነ-ሕንፃ መስራታቸው በስፋት የሚነገርላቸው። እቴጌ ምንትዋብ በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ጥበብ ውስጥ ውበት እና ግርማ ሞገስ የተላበሱ ታሪካዊ ሕንጻዎችን በማሠራት በታሪከ ውስጥ ስመ ገናና ናቸው።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top