ሌሎች አምዶች

“ታሪካችን ይጫነናልን” ባህልና ስለጊዜ ያለን አስተሳሰብ

ባህል ከግንዛቤ በታች ነው፤ ምክንያቱም ማንም እሱን ለማብራራት አይጨነቅም የሚባል አባባል አለ። አከራካሪ ሊሆን ይችላል። የማያከራክረው ግን ባህል የድርጊቶቻችንን ስረ-መሰረት የሚወስን መሆኑ ነው። ባህል ሰው ሰራሽ ነው፤ በመሆኑም በማህበረሰብ አባላቱ እውቅናና ተቀባይነትን አግኝቶ፣ ልማዳዊ በሆነ አግባብ መጪው ትውልድ ወይንም ከሌላ ስፍራ ማህበረሰቡን የተቀላቀሉ መጤዎች እንዲያውቁትና እንዲገነዘቡት ይተላለፋል። ባህል ሰዎች ስለራሳቸው ትርጉም ባለው መንገድ የሚያስቡበትንና የውጭውን ዓለም የሚጋፈጡበትን አውድ ይሰጣቸዋል። ክሊፎርድ ግሪትዝ የተባለ አንትሮፖሎጂስት እንደሚለው፣ ባህል “ሰዎች ስለ ህይወት ያላቸውን አመለካከትና እውቀት እርስ በርስ የሚረዳዱበት፣ የሚያበለጽጉበትና የሚያነብሩበት (ወይንም ዘላቂ የሚያደርጉበት) ዘዴ ነው። ሰዎች ልምዶቻቸውንና የድርጊቶቻቸውን መመሪያ የሚተረጉሙት በባህል ዘይቤ ነው።”

 በዚህ ጽሑፍ ሰዎች ለጊዜ ያላቸው አመለካከትና የሚሰጡት ትርጉም ከባህላቸው ጋር እንዴት የተሳሰረ እንደሆነ ለማመልከት እሞክራለሁ። ለጽሑፉ መነሻ የሆኑኝንና ሌሎች ዝርዝር ሃሳቦችን እንዲሁም አብነቶችን ያገኘሁት ትሮምፕናርስ እና ሃምፕደን-ተርነር የተባሉ ጸሐፊዎች በ1997 (እ.አ.አ) ባሳተሙት “ራይዲንግ ዘ ዌቭስ ኦፍ ካልቸር” ከተሰኘው መጽሐፍ ነው።

ከኑሮ ዘይቤ ወይንም ከባህል አኳያ ላለፈው፣ ላሁኑና ለመጪው ዘመን የሚሰጠው ግምት አንፃራዊ ልዩነት አለው። ለስኬት ላቅ ያለ ግምት ያላቸው ባህሎች (አቺቭመንት-ኦሪየንትድ የሚባሉቱ) መጪው ዘመን ካለፈውና ካሁኑ የተሻለ ይሆናል ብለው ያምናሉ፤ ምክንያቱም ትልም ወይንም ርዕይ እውን የሚሆነው ወደፊት በመሆኑ! በሌላ በኩል ለተወላጅነት ልዩ ትርጉም የሚሰጡ ባህሎች (ሪሌሽንሺፕ-ኦሪየንትድ የሚባሉቱ) መጪውን ዘመን የሚያዩት በስጋትና በጥርጣሬ ነው። በእንደዚህ ዓይነት ባህሎች አስተሳሰብ መጪው ዘመን አሁን ያለውን መዋደድና መተሳሰብ ከማጠናከር ይልቅ እያላላውና እያራከሰው ይሄዳል። እንደ ማህበረሰብ ለጊዜ የሚኖረን አመለካከት ወይ “የተራ በተራ” (ሲኴንሺያል) አሊያም “የጣምራ” (ሲንክሮኒክ) ሊሆን ይችላል።

በቀደመው አመለካከት ጊዜ ተከታትለው በሚያልፉ ሁነቶች ይገለጻል። በኋለኛው አመለካከት ደግሞ ጊዜ ያለፈው፣ የአሁኑና የወደፊቱ ተንሰላስለው የተያያዙበት በመሆኑ የወደፊት ሃሳቦችና ያለፉት ትውስታዎች የአሁኑን ድርጊት ይቀርጹታል ተብሎ ይታመናል። ይህን ዝቅ ብለን በተሻለ ዝርዝር እናያለን።

ከጊዜ አንፃር የጥንታዊ ማህበረሰቦች አደረጃጀት ቀለል ባለ አስተሳሰብ ላይ የተመሰረተ ነው። ይህም በጨረቃ መውጣት መግባት፣ በፀሀይ መውጣት መጥለቅ፣ በክረምት መግባት መውጣት፣ ወዘተ ይገለጻል። በሰለጠኑ ማህበረሰቦች ዘንድ ግን ለጊዜ ያለው አስተሳሰብ በጣም ውስብስብ ሆኖ እናገኘዋለን። አስተሳሰቦቹ ሲፈተሹ በመሰረታዊነት ሁለት ተነፃፃሪ ግንዛቤዎች ጐልተው ይወጣሉ። አንደኛው ዓይነት ግንዛቤ ጊዜ ራሳቸውን በቻሉና በማይቋረጥ ሂደት ወደፊት የሚያልፉ ሁነቶች፣ ደቂቃዎች፣ ሰዓታት፣ ቀናት፣ ወራት፣ ዓመታት ክንውን ነው የሚለው ሲሆን፤ ሁለተኛው ግንዛቤ ደግሞ ጊዜን እንደ ቀለበት የሚመለከተውና በሰዓት ውስጥ ያሉት ደቂቃዎች፣ በቀናት ውስጥ ያሉት ሰዓታት፣ በሳምንቱ ውስጥ ያሉት ቀናት፣ ወዘተ እየዞሩ ራሳቸውን የሚደግሙበት ሂደት ነው።

 በግሪክ ሚቶሎጂ መልኳ የሴት፣ አካሏ የአንበሳ፣ እንደ ወፍ ክንፎች ያሏት ስፊንክስ የምትባል አስፈሪ ፍጥረት ነበረች ይባላል። ይህች ፍጥረት ወደ ቲቤስ የሚሄዱ መንገደኞችን “ጠዋት በአራት እግሩ፣ እኩለ ቀን ላይ በሁለት እግሩ፣ ምሽት ላይ ደግሞ በሦስት እግሩ የሚሄድ ፍጥረት ማን ነው?” እያለች ትጠይቅና መልሱን በትክክል መመለስ ያቃተውን ሰው ትበላው ነበር። አንድ ቀን ግን ኢዲፐስ የተባለ ሰው መልሱን በትክክል መለሰ። የኢዲፐስ መልስ “ሰው ነው” የሚል ነበር። ስፊንክስም ወዲያውኑ ራሷን አጠፋች። ኢዲፐስ የስፊክንስን የጊዜ እንቆቅልሽ የተረዳው በምሳሌ ነበር። በአራት እግሩ የሚሄደው የሚድህ ህፃን፣ በሁለት እግሩ የሚሄደው ጐልማሳ፣ በሦስት እግር የሚሄደው ደግሞ ከዘራውን የሚመረኮዘው አረጋዊ መሆኑ ነው። እንቆቅልሹ የተፈታው ስለጊዜ ዘለግ አድርጐ በማሰብ ነው።

 አንትሮፖሎጂስቶች አንድ ባህል ስለ ጊዜ ያለው አመለካከትና ጊዜን የሚያስተዳድርበት አግባብ የማህበረሰብ አባላት ለኑሮና ለሰው ልጅ ተፈጥሮ ስላላቸው ትርጓሜ ፍንጭ ይሰጣል የሚል ጠንካራ ሃሳብ አላቸው። ከዚህ አኳያ፣ ለምሳሌ ክሉኮንና ስትሮትቤክ የተባሉ አንትሮፖሎጂስቶች፣ ሦስት ዓይነት ባህሎች አሉ ይላሉ። አንደኛው ዘንድሮ-ተኮር (ፕረዘንት-ኦሪየንትድ) የሚባለው ሆኖ በአንፃራዊ መልኩ ዘመን አልባ፣ ባህል ልምድ ወግ የሌለውና የወደፊቱን የዘነጋ ነው። ሁለተኛው አምና-ተኮር (ፓስት-ኦሪየንትድ) ሆኖ ትኩረቱ ያለፈውን ባህል፣ ልምድና ወግ ጠብቆና አድሶ ማቆየት ነው። ሦስተኛው ደግሞ ከርሞ-ተኮር (ፊውቸር-ኦሪየንትድ) የሚባለውና ተፈላጊ የሆነውን መጪ ዘመን ያለመ፤ እርሱንም እውን ለማድረግ የቆረጠ ባህል ነው። እንደነ ክሉኮን አገላለጽ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማትን እውን ያደረጉት በአመዛኙ በሦስተኛው ጐራ የሚመደቡ ሀገራት ህዝቦች ናቸው።

 ከፍጥረታት ሁሉ ስለጊዜ ንቁ አስተሳሰብ ያለውና ሊቆጣጠረውም የሚጣጣር ሰው ብቻ ነው። የሰው ልጅ ጊዜን አምና፣ ዘንድሮና ከርሞ በማለት ከፋፍሎ የመመልከት የወል ባህርይ አለው፤ ነገር ግን ለእያንዳንዳቸው የሚሰጠው ትርጉምና ፋይዳ የተለያየ ነው። ጊዜ ሃሳብ እንጂ ቁስ ባለመሆኑ ለጊዜ የምንሰጠው ትርጉም በባህላችን ተጽዕኖ ስር የወደቀ ነው። ዕቅድ አወጣጣችን፣ ስትራቴጂ አቀራረጻችንና ተግባራትን ከሌሎች ጋር የምናስተባብርበት መንገድ ለጊዜ ካለን አስተሳሰብ ጋር የተጠላለፈ ነው።

 ታዋቂው የፈረንሳይ ሶሲዮሎጂስት ኤሚል ዱርክ፣ የጊዜ አተረጓጐም ግለሰባዊ ሳይሆን ማህበራዊ መሆኑን አጉልቶ ይገልጽና ትርጓሜው የማህበረሰቡ አባላት ስራዎቻቸውን አቀናጅተው እንዲመሩ ያስችላቸዋል ይላል። ይህም በማናቸውም ስራ ላይ ይገለጻል። ቀላል ምሳሌ ለመውሰድ፣ በቀጠሮ የተያዘ ስብሰባ የሚጀምረው የሆነ ሰዓት አካባቢ አሊያም በተባለው ሰዓት መሆን አለመሆኑ እንደየ ባህሉ የተለያየ ነው። አንድ ስራ ተጀምሮ የሚጠናቀቅበት ጊዜ ውልፍት ሳይል ይከበራል አሊያም ጊዜው የሚጠቅመው እንደ አጠቃላይ አመልካች ነው። የእኛን ሀገር የስብሰባ አጀማመርና የፕሮጀክት አፈጻጸም ከዚህ አንፃር መመልከት ይቻላል።

ላለፈው፣ ለአሁኑና ለመጪው ዘመን ያለን አስተሳሰብ

ያለፈው ጊዜ ላይመለስ በማለፉ፣ መጪው ጊዜም ገና እውን ባለመሆኑ በተጨባጭ የሚታወቀው የአሁኑ ጊዜ ነው። ነገር ግን ይህ አባባል በመጠኑም ቢሆን መስተካከል አለበት። ስላለፈውም ሆነ ስለመጪው ጊዜ የምናስበው ዛሬ ላይ ሆነን ነው። ስላለፈው ጊዜና ስለ መጪው ዘመን ያለን ሃሳብ የቱንም ያህል ያልተስተካከለና ያልተዋጣለት ቢሆንም፤ በአስተሳሰባችን ላይ ግን ከፍ ያለ ተጽዕኖ አለው። በሌላ አነጋገር እነኚህ ሦስቱ የጊዜ ክፍልፋዮች በዕለት ተለት ብያኔአችንና ውሳኔ አሰጣጣችን ውስጥ ይኖራሉ። በእርግጥ በየስራ መስካችን ህይወታችን የተቃኘው በወደፊቱ ስኬት ላይ ነው፤ ነገር ግን የአሁኑ ተለዋዋጭ ስሜታችንም ሆነ ያለፈው ተሞክሯችን ስለ መጪው ጊዜ ባለን ግንዛቤ ላይ ያለው ተጽዕኖ ቀላል አይደለም። በሦስቱ የጊዜ ፈርጆች መካከል ያለው ግንኙነት ውጥረት-አዘል ቢሆንም ውጤቱ ምርታማ ነው። ሦስቱም የጊዜ ፈርጆች በየድርጊቶቻችን ውስጥ አሉ። ስለ ከርሞ ያለን ተስፋ ዘንድሯችንን ይወስናል፤ የዘንድሮው ተግባራችንም መጪው ዘመን ላይ ተጽዕኖ አለው፤ ላለፈው ዘመን ያለን አተያይም በዘንድሮው ተሞክሯችን ይወሰናል፤ እኛነታችን የተቀረጸውም ባለፈው ተሞክሮ ላይ ነው። ይህ አገላለጽ የቃላት ጨዋታ ሳይሆን አስተሳሰባችን እንዴት እንደሆነ ለማመልከት እንዲረዳን ነው።

አንዳንድ ግለሰቦችና ባህሎች ላለፈው ወይንም ለአሁኑ ወይንም ደግሞ ለመጪው ዘመን ያደሉ ይሆናል። አንዳንዶች ዛሬን (ማለትም ዘንድሮን) ብቻ ይኖራሉ ወይንም ለመኖር ይጥራሉ። ሌሎች ደግሞ ያለፈውን ዘመን በስስት ይናፍቃሉ፤ በአሁኑ ዘመን የሚሰራው ሁሉ ያለፈውን ዘመን እንዲመስልም ይፈልጋሉ።

የተግባራት አደረጃጀት ቅደም ተከተል” (ሲኴንሺያል) እና ጣምራ” (ሲንክሮኒክ) የጊዜ አስተሳሰብ

 ከፍ ሲል፣ ጊዜ በቅደም ተከተል ወይንም በየተራ በሚከናወኑ ሁነቶች ተከታታይነት በየተወሰነ ጊዜ እያለፈን የሚሄድ ተደርጐ እንደሚታሰብ ጠቁመናል። በሌላ በኩል ደግሞ ጊዜ ቀለበታዊ በሆነ ዑደት አምናን፣ ዘንድሮንና ከርሞን በጋራ ባህርያቸው መሰረት አጣምሮ ይዞ ሳያቋርጥ የሚመላለስ ሂደት ተደርጐም እንደሚወሰድ አመልክተናል። ጊዜን ተራ በተራ ወይንም በቅደም ተከተል በሚከናወኑ ተግባራት ሂደት ለሚገነዘብ ሰው እያንዳንዱ ነገር የራሱ ጊዜና ስፍራ አለው። ይህ ሁኔታ ከተዛባ ሰውየው ሰላም አያገኝም ወይንም ምቾት አይሰማውም። ለምሳሌ በእንግሊዝ ሀገር አገልግሎት ለማግኘት በሰልፍ ተራ ይዞ እየጠበቀ ያለ ሰው ተራውን አሳብሮ ወደፊት ለመሄድና ቀድሞ ለመስተናገድ ቢሞክር ማንም ዝም አይለውም። እያንዳንዱ ሰው ተራውን መጠበቅ አለበት። መጀመሪያ የመጣ መጀመሪያ ይስተናገዳል። አንድ ታዛቢ በለንደን ከተማ ያየውን እንደሚከተለው ገልጾት ነበር። “አንድ ቀን ከባድ ዝናብ እየዘነበ አውቶቡስ የሚጠብቁ ሰዎች በረዥሙ ተሰልፈው ቆመዋል። በአቅራቢያቸው መጠለያ ቢኖርም ሁሉም በዝናቡ ርሰዋል። ዝናቡ እስኪያልፍ በመጠለል ማንም ተራውን ማጣት አይፈልግም። መንገደኞቹ ትክክለኛውን ነገር ከመፈጸም ይልቅ ነገሮችን በትክክለኛው መንገድ መፈጸምን መርጠዋል።” በኔዘርላንድስም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ስጋ ለመግዛት ሉኳንዳ ቤት የገባችና 46 ቁጥር ንምራ የያዘች ሴት 12 ቁጥር ሲጠራ ለጠቅ ብላ ስጋ ለማስቆረጥ ብትሞክር፤ ንግስትም ብትሆን አሳር አይቀርላትም። ድንገተኛ አደጋ ቢያጋጥም እንኳ፣ ተራ ያው ተራ ነው። ለተለያዩ ጉዳዮች የእኛን ሀገር ተራ አጠባበቅ ልብ ብላችኋል? እንደ እኔ ትዝብት ብዙ ጊዜ እንደነገሩ በሰልፍ ይጀምርና፣ ትንሽ ቆይቶ ወልገድ ይልና በመጨረሻ ድብልቅልቁ ወጥቶ ሰልፉ ይፈርሳል። ጉዳዩ ከባህል አንፃር ለጊዜ ካለን አመለካከት ጋር የተያያዘ መሆኑን አስባችሁበት ታውቃላችሁ?

በጣሊያን ሀገር ደግሞ ሁኔታው የተለየ ነው። ከእኛም ጋር ይመሳሰላል። ታዛቢው የታዘበውን እንደሚከተለው ገልጾታል። በአንድ ሉኳንዳ ቤት አንዲት ደንበኛ የሾርባ ስጋ እየገዛች ነበር። ስጋ ቆራጩ የሾርባ ስጋውን እየጠቀለለ “ማነው ሌላ የሾርባ ስጋ የሚፈልግ?” በማለት ጮክ ብሎ ጠየቀ። የተራ ጉዳይ አልተዘነጋም፤ ሰዎች የሚፈልጉትን ስጋ ለመግዛት ተራቸውን እየጠበቁ፣ ከገዙም በኋላ ተራቸውን ጠብቀው እየከፈሉ ይሄዳሉ። ነገር ግን የሾርባ ስጋ ፈላጊ የሆነች ሌላ ደንበኛ ሌላ ዓይነት ተጨማሪ ስጋ ከሚጠብቁ ደንበኞች ቀድማ ሸምታ፤ ሂሳቧን ከፍላ፣ ለመሄድ ዕድል አላት። እንዲህ ዓይነቱ ዘዴ በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ደንበኞችን ለማስተናገድ ያስችላል።

 በሌላ በኩል ደግሞ በለንደን ወይንም በአምስተርዳም ሉኳንዳ ቤት ስጋ ቆራጩ ቁጥር ይጠራል፣ ስጋ ይቆርጣል፣ ይጠቀልላል፣ ለገዢው ያስረክብና ሌላ ቁጥር ይጠራል። አንድ ታዛቢ ሆን ብሎ ጣልቃ ገባና “የሾርባ ስጋውን እንደጀመርክ በነካ እጅህ ለእኔም አንድ ፓውንድ ቁረጥልኝ” አለ። ሌሎች ደንበኞች የሰሙትን ለማመን፤ ድንጋጤአቸውንም ለመደበቅ አልቻሉም። በሁለቱ ሀገሮች ባህል የታዛቢው ጥያቄ የማይታሰብ ነበር።

“ጊዜ ቀለበታዊ በሆነ ዑደት አምናን፣ ዘንድሮንና ከርሞን በጋራ ባህርያቸው መሰረት አጣምሮ ይዞ ሳያቋርጥ የሚመላለስ ሂደት ተደርጐም እንደሚወሰድ አመልክተናል”

ስለ ጊዜ የጣምራ አስተሳሰብ ያላቸው (ሲንክሮኒክ) ባህሎች ሰዎች የተለያዩ ተግባራትን (ልክ የተለያዩ ኳሶችን ሽቅብ እየወረወረ በስርዓትና በጥበብ መልሶ እንደሚቀልብ የሰርከስ ባለሙያ) በአንድ ጊዜ እንዲያከናውኑ ይጠብቃሉ። በጣምራ የጊዜ አስተሳሰብ ዋናው ትኩረት በአንድ ጊዜ ስለሚከናወኑት የተለያዩ ተግባራት ነው። ባህሉ በቅደም ተከተል የጊዜ አስተሳሰብ ለተቃኘ ሰው ይህ ተግባር ልዩና ያልተለመደ ነው። በአንድ ጊዜ ሁለት-ሦስት ነገሮችን የሚያከናውኑ ሰዎች ባህሉ በቅደም ተከተል የጊዜ አስተሳሰብ የተቃኘን ሰው ሊያስቀይሙ ይችላሉ። ይህን የሚያደርጉት ግን ሆን ብለው ላይሆን ይችላል። አንድ የደች ጸሐፊ እንደሚያስታውሰው፣ አንድ ቀን አርጀንቲና ውስጥ የአውሮፕላን ቲኬት ሲቆርጥ ሰራተኛዋ በስልክ ከባልንጀራዋ ጋር እያወራች ነበር። የምታወራው ደግሞ ስለ ባልንጀራዋ ልጅ ጉብዝና ነበር። በጸሐፊው ባህል የቲኬት ሰራተኛዋ እርሱን ብቻ ማስተናገድ ነበረባት።

 በሌላኛው ባህልም ቢሆን የቅያሜው ሁኔታ ተመሳሳይ ነው። ለምሳሌ አንድ የደቡብ ኮሪያ ማኔጀር ኔዘርላንዳዊ አለቃውን ለማነጋገር ወደ ኔዘርላንድስ ሄዶ ያጋጠመው ሁኔታ ጥሩ ምሳሌ ሊሆን ይችላል። “ወደ ቢሮው ስገባ ስልክ እያነጋገረ ነበር። እንደነገሩ የግራ እጁን ከፍ አድርጐ በሩቁ ሰላም አለኝና በስልክ ማውራቱን ቀጠለ። ቢሮው ውስጥ ሰው ያለ እንኳ አልመሰለውም። ከአምስት ደቂቃ በኋላ ስልኩን ሲጨርስ ከወንበሩ ብድግ ብሎ ሞቅ ያለ በሚመስል፣ ነገር ግን የለበጣ በሆነ ስሜት፣ እንኳን ደህና መጣህ ኪም፤ በመገናኘታችን በጣም ደስ ብሎኛል! አለኝ። ለማመን አልቻልኩም።”

ሲንክሮኒክ ባህሎች ለቀጠሮ አጥብቀው የሚጨነቁ አይደሉም። የመስኩ ተመራማሪዎች እንደሚሉት የቀጠሮውን ሰዓት ማክበር አስፈላጊ ሳይሆን ቀርቶ አይደለም፤ ነገር ግን ከባህል አንፃር ይህን የሚገዳደሩ አጋጣሚዎች መኖራቸው ነው። ዘመድ ወይ ጓደኛ ድንገት ሊያጋጥም ይችላል። ቀጠሮ አለብኝ በሚል ሰበብ እነርሱን ባግባቡ አለማስተናገድ ወይንም ቆም ብሎ፤ ጊዜ ሰጥቶ በተገቢው የዝምድና ወይንም የጓደኝነት ስሜት አለማናገር አይቻልም። በቀጠሮው ሰዓት ድንገት ብቅ ያለችው እናት ወይ እጮኛ ብትሆን ቅያሜው ምን ያህል ከባድ እንደሚሆን መገመት ይቻላል። ስለዚህ በሲንክሮኒክ ባህሎች የቀጠሮ ሰዓት ያ የተባለው ሰዓት ሳይሆን ከዚያ አለፍ ብሎ ሊሆን ይችላል። በላቲን አሜሪካ እስከ 15 ደቂቃ፤ በአፍሪካና በመካከለኛው ምስራቅ ከሰዓታት እስከ ግማሽ ቀን ሊወስድ ይችላል። ቀጠሮውን የሚጠባበቁት ሰዎችም በተጓዳኝ የሚያከናውነት ነገር አይጠፋም በሚል ግምት ማስጠበቁ እንደ አዋኪ ነገር አይወሰድም። እንዲያውም ትንሽ ረፈድ አድርጐ መምጣቱ ሌሎች ያልታሰቡ ስራዎችን ለመስራት ዕድል ይሰጣቸዋል።

ለጊዜ ያለን አመለካከት በምግብ አዘገጃጀታችን እንኳ ይንጸባረቃል። ቀጠሮን አጥብቀው በሚያከብሩትና ሲኴንሺያል በሆኑት ባህሎች ብዙውን ጊዜ የሚዘጋጀው ምግብ በተጠቃሚዎች ቁጥር ልክ ነው። ምግቡ እንዲቀዘቅዝ ወይንም ዳግም በቀላሉ ሊዘጋጅ ስለማይችል እንዲበላሽም አይፈለግም። በሲንክሮኒክ ባህሎች ግን አብዛኛውን ጊዜ ምግብ ሲዘጋጅ ተረፍ ተደርጐ ነው። ያልታሰቡ እንግዶች ድንገት ሊመጡ ይችላሉ ተብሎ ይታመናል። የሚዘጋጀውም ምግብ ቢቆይም የማይበላሽ፤ ወይንም እንደነገሩ በፍጥነት የሚዘጋጅ ሊሆን ይችላል።

 ጊዜን በጣምራ አስተሳሰብ የሚመለከቱ (ሲንክሮኒክ) ባህሎች አመለካከታቸው ማህበረሰባዊ (ኮሚዩኒቴሪያን) በመሆኑ “እኛ” ማለትን ያበዛሉ። በእነርሱ ዘንድ ወዳጅነትም ለዛሬ ብቻ አይደለም፤ የቆየና ወደፊትም የሚዘልቅ ነው። ዘንድሮን፣ አምናንና ከርሞን አጣምሮ ይዞ በፍቅርና በመልካም ትውስታ የተሞላ ነው። በሲኴንሺያል ባህል ግን ወዳጅነት በአመዛኙ ለጥቅም ወይንም ተጠቅሞ ለመጥቀም ነው።

 የጊዜ ቅኝትና የስልጣን አተያይ

ለጊዜ ያለን አመለካከት ለስልጣን (ኦቶሪቲ በሚለው አገባቡ) ካለን አመለካከት ጋርም ሊያያዝ ይችላል። ታሪካቸው ይጫናቸዋል በሚባሉ ሀገራት ወይንም ላለፈው ዘመን ጠበቅ ያለ ግምት ይሰጣሉ በሚባሉ ህዝቦች ዘንድ የስልጣን መሰረት ተደርገው የሚወሰዱት ባህርያት ጠንከር ያሉና የቋሚነት ባህርይ ያላቸው (ለምሳሌ እንደ ዕድሜ፣ ጾታ፣ ጎሳ፣ የሙያ ብቃት/የትምህርት ደረጃ፣ ወዘተ) ናቸው። ዘመን ምስክር የቸረው የሙያ ብቃት ወይንም የአንድ ዝነኛ የትምህርት ተቋም ተመራቂ መሆን በጊዜው ላለ ታዋቂነትና ተስፋ ላለው መጪ ዘመን እንደ ጥሩ መገለጫ ሊወሰዱ ይችላሉ። አምናን፣ ዘንድሮንና ከርሞን አስተሳስረው ይገልጻሉ።

 በሲኴንሺያል ባህል ለስልጣን ያለው አመለካከት ከዚህ ለየት ያለ ነው። በአሜሪካ የሆሊዉድ የፊልም ኢንዱስትሪ የአንድ ተዋናይ ዝና እና ማንነት የሚወሰነው መጨረሻ ላይ በሰራው ስራ እንጂ ቀድሞ በነበረው ታዋቂነት ላይ ብቻ አይደለም። መጪው ጊዜ ስኬትንም ውድቀትንም የያዙ የተከታታይ ሁነቶች ቅጥልጥል ሊሆን ይችላል። በአንድ ወቅት ተሳክቶለት እላይ የወጣ፤ ሌላ ጊዜ ወርዶ እታች ዘጭ ሊል ይችላል። አሜሪካኖች ለሚቀጥለው የሙያ ዕድገትና የኑሮ ስኬት የማይረዳ ወዳጅነትንና ሽርክናን ተሸክመው መዝለቅ አይፈልጉም። በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከአውሮፓ ተሰደው አሜሪካ መስፈር የጀመሩት ስደተኞች ከአውሮፓ ጋር የነበራቸውን ትስስር ሁሉ እርግፍ አድርገው መተዋቸውን ልብ ይሏል!

የጊዜ ቅኝት ለውጥን የማስተናገድ ስሜት

 በአንድ ወቅት አንድ ሆላንዳዊ የስራ አመራር ባለሙያ (ማኔጀር) ከኢትዮጵያውያን አቻዎቹ ጋር ሆኖ የለውጥ ስራ አመራርን (ቼንጅ ማኔጅመንት) በተመለከተ ዐውደ- ጥናት ለማካሄድ ጥረት ያደርጋል። አብሮት አንድ እንግሊዛዊ ጸሐፊ (ደራሲ) ነበር። ኢትዮጵያውያኑ ስለ ወርቃማው የኢትዮጵያ ስልጣኔ ወደኋላ እየሄዱ በመጥቀስ አስቸገሩ። በዚህ ላይ ያልተመሰረተ ማናቸውንም የልማት አስተሳሰብ ለመቀበል ዝግጁ አልሆን አሉ። በዚህ የተነሳ ዐውደ-ጥናቱ በታለመው መንገድ አልካሄድ አለ። ሁኔታውን የተረዱት ሆላንዳዊውና እንግሊዛዊው ከጥቂት ኢትዮጵያውያን ረዳቶቻቸው ጋር ሆነው ተመካከሩና ጥቂት የኢትዮጵያ ታሪክ መጻሕፍትን ለመመልከት ወሰኑ። የታሪክ ንባባቸው አንዳንድ ነጥቦችን ከዘመናዊ የስራ አመራር መርህ አንፃር አገናዝቦ ለማየት ነበር። መሪ ሃሳባቸውን “በዚያ ጥንታዊ የስልጣኔ ዘመን ኢትዮጵያ ከተሞቿን ለማበልጸግና የንግድ ስራዋን ለማስፋፋት የወሰደቻቸው ትክክለኛ እርምጃዎች ምን ምን ነበሩ?” በሚለው ጥያቄ ዙሪያ እንዲያጠነጥን ተስማሙ። የሆላንዱ ኩባንያም በኢትዮጵያ ዘለግ ያለ ዕድሜና ታሪክ የነበረው በመሆኑ ይህንንም የጥናታቸው አካል አደረጉት። ከዚያም የሆላንዱ ማኔጀር ዋናውን ርዕሰ ጉዳይ ለዐውደ-ጥናቱ አቀረበ። መጪው የንግድ ስራ ዘመንም ያለፈውን ገናና ጊዜ ለማደስ የሚረዳ መልካም አጋጣሚ ተደርጐ ተቃኘ። ድንገት ዐውደ-ጥናቱ ነፍስ ዘራና የእያንዳንዱን ሀበሻ ሞቅ ያለ ተሳትፎ ማስተናገድ ተጀመረ።

በእርግጥ እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ በኢትዮጵያ ብቻ የሚሆን እንግዳ ነገር አይደለም። ማንኛውም የለውጥ ሂደት የነበረውን ሁሉ ሽሮ፣ ማንነትንም አሽቀንጥሮ ጥሎ ተግባራዊ እንዲሆን አይፈለግም። ማንነትን ጠብቆ ለማቆየት በተወሰነ መልኩ የቀድሞን መስሎ መቀጠል ተገቢ ነው። ይህን ሳያረጋግጡ በባዕድ ምክርና ጉትጐታ ለውጥን ለማስተናገድ ማንም ማህበረሰብ አይፈልግም። ስለዚህ ቀደም ሲል እንዳመለከትነው ሲንክሮኒክ ባህሎች አምናን በዛሬና በነገ ውስጥ ይዘው ስለሚኖሩ ነባሩ ቅርስና ውርስ ተጠብቆ መቆየቱን ሳያረጋግጡ ለውጥን በፀጋ አይቀበሉም።

 ጊዜን በቅደም ተከተል የሁነቶች ሂደት በሚገነዘብ ማህበረሰብ ዘንድ ዕቅድ በአመዛኙ ትንበያ ነው። ዘንድሮ ያሉ ዝንባሌዎች ወደፊትም ብዙ ለውጥ ሳያሳዩ ይቀጥላሉ ተብለው ይገመታሉ። በዕቅድ አዘገጃጀት ዓላማን ለማሳካት ይረዳሉ ተብለው የሚታሰቡ ዘዴዎችና የአፈጻጸም ደረጃዎች በሚገባ እንዲታወቁና ስራዎቹም በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ እንዲጠናቀቁ ይጠበቃል። በአንድ ወቅት እንግሊዝ ሀገር የነበረች አንዲት ጣሊያናዊት የጥናትና ምርምር ባለሙያ እንዳለችው፡- “እንግሊዝ ውስጥ ሁሉም ነገር ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ መታቀድ አለበት። የአየር ንብረቱ ሲቀየር ሁሉም ነገር እንደገና ይከለሳል።” እንዲህ ዓይነቱ ዕቅድ አጣጣል ያልተረጋጋ ሁኔታ ባለበት እምብዛም ውጤታማ ሊሆን እንደማይችል ብዙ ጸሐፍት ይስማማሉ። ሲኴንሺያል ዕቅድ ባልታሰቡ ሁኔታዎች የተነሳ በቀላሉ ይደነቃቀፋል። ትኩረቱ ሁሉ ግቡ ላይ በመሆኑ የሁኔታዎችን ረዥም ክትልትሎሽ ከግምት አያስገባም። በሲንክሮኒክ ባህሎች ግን የተቀመጠው ግብ ከሚታዩ አዝማሚያዎችና ከድንገተኛ አጋጣሚዎች ጋር ተገናዝቦ ይታያል።

 የሆነው ሆኖ ባህላዊ አመለካከቶች ግርር ያሉ አማራጮች አይደሉም። ሁለቱም በጣምራ ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ። የተለያዩ ሀገራት ዜጎች ሰራተኞችን አስተባብሮ የሚመራ ማኔጀር በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ በተሻለ መንገድ ውጤታማ ይሆናል ብሎ ያሰበውን ዘይቤ ሊጠቀም ይችላል። በሀገራችን ለጊዜ ያለን አመለካከት ብዙ ጊዜ ሲንክሮኒክ፤ አንዳንድ ጊዜ ግን ሲኴንሺያል ይመስላል። በቀጠሮ ቀልድ የማያውቁ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ፣ ደንታ የሌላቸውም ብዙ ናቸው። ዋናው ቁምነገር ከባህል አንፃር ለጊዜ ያለውን አስተሳሰብና አመለካከት ማወቅ ለሰብዓዊ ወዳጅነት፣ ለንግድና ለዲፕሎማሲ ግንኙነታችን እጅግ ጠቃሚ መሆኑን መረዳት ነው።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top