ሌሎች አምዶች

ባህል፣ ብዝኀ-ባህል፣ ኅብረ-ባህል

ይህ ፅሑፍ ትኩረት ያደረገባቸው ባህል፣ ብዝኀ- ባህልና ኅብረ-ባህል በሚሉ ጥብቅ ትስስር ባላቸው ፅንሰ- ሀሳቦች ላይ ነው::

 ባህል፡- ‘ኅብረ-ባህል’ን በቀላሉ ለመረዳት ‘ባህል’ የሚለውን ሰፊና ጥልቅ ፅንሰ-ሀሳብ እንደ መነሻ መመልከት ያስፈልጋል:: ምክንያቱም ‘ኅብረ-ባህል’ ሁልጊዜ የሚገለፀው ከባህል ጋር ተዛምዶ ነው:: ጎርዶን (1964) ማንኛውም “ባህል ‘በልዩነትና በተመሳሳይነት’ የተቃርኖ ሕግ የሚገለፅ ሰፊ ሀሳብ ሲሆን የ’ኅብረ-ባህል’ን እና/ወይም የአንድን በሓውርታዊ ሀገር ‘ኅብረ- ማንነት’ የሚያጠቃልል ጥልቅ ፅንሰ-ሀሳብ ነው:: ይህ ብቻ አይደለም:: ባህል በየትኛውም የዓለማችን ክፍል የሚኖሩ የሰው ልጆች ሁሉ በወል

የሚጋሩት ሁለንተናዊ ባሕርይ ነው” ይላል:: ባህል በሰው ልጅ ረዥም የዕውቀት ታሪክ ውስጥ ቀዳሚ ሆነው ከሚጠቀሱት ፅንሰ-ሀሳች አንዱና ዋነኛው ነው:: ባህል የማይዳስሰው ወይም የማይነካው የሰው ልጅ የሕይወት ገጽታ የለም:: ከዚህ የተነሳም እስከ ዛሬ በየመስኩ የሚገኙ ምሁራን ከተቃኙበት የቲዮሪ መርህና የምርምር ትኩረት አኳያ ተግባራዊ ብያኔዎችን ሲሰጡ ቆይተዋል:: ለምሳሌ ፈላስፎች ከሥነ-ኅላዌ እውቀትና ጥበብ ፍለጋ አንፃር፣ ፎክሎሪስቶች ከአንድ ማህበራዊ ቡድን መንፈሳዊና ቁሳዊ ሕይዎት፣ ዕውቀት፣ ታሪክ፣ የአኗኗር ስልትና ብሂል፣ ጥበብ፣ ዘዴ፣ ሕግ፣ የእምነትና የእሴት ሥርዓትና ሥርዓተ-ክዋኔዎች፣ ወዘተ፣ በአጠቃላይም ከትውፊት አንፃር በመገንዘብ በየበኩላቸው ብያኔዎችን በየጊዜው ሲሰጡ ቆይተዋል::

ይሁንና በሁሉም የዕውቀት መስኮች የሚገኙ ምሁራንን ትኩረቶች ከሚያካትት ከአንድ የተጠቃለለ ንድፈ-ሀሳባዊ ብያኔ ላይ ለመድረስ አልቻሉም:: በመሆኑም እስከ ዛሬ ድረስ ከ230 የማያንሱ ተግባራዊ ብያኔዎችን እናገኛለን:: ይህ የሆነበት ዋና ምክንያትም ባህል ሲፊና ጥልቅ ፅንሰ-ሀሳብ ከመሆኑ የተነሳ ነው:: ስለዚህ ከተሰጡት በርካታ ተግባራዊ ብያኔዎች መካከል በጣም ጥቂቶችን ለአብነት ያህል በመጥቀስ እንደሚከተለው እንመለከታልን::

 በቅድሚያ በ1871 ታይለር በመዘርዝር መልክ የሰጠውንና እስካሁን በተደጋጋሚ በብዙዎች ዘንድ ሲጠቀስ የቆየውን ተግባራዊ ብያኔ ስንመለከት የሚከተለው ሁኔታ የተጠቀሰውን ይመስላል፡-

ባህል ምሉዕና ውስብስብ ነው፤ በውስጡም አስተሳሰብን፣ የዓለም አመለካከትን፣ ትውፊትን፣ ተቋማትን፣ ሕጎችን፣ ደንቦችን፣ መመሪያዎችን፣ እሴቶችን፣ ዕውቀትን፣ የሕይወት ስልትን፣ ልማዳዊ እምነቶችንና አሠራሮችን፣ ሥርዓተ- ክዋኔዎችን፣ ክብረ-በዐላትን፣ ሥነ-ጽሑፍን፣ ስነ-ጥባባትን፣ ቋንቋን፣ … ያካትታል:: ባህል አብሮ የሚወለድ ነገር አይደለም:: ሰዎች ከተወለዱ በኋላ የተወለዱበትን፣ የሚኖሩበትን፣ ህብረተሰብ ሆነው ለመኖር በሕይወት ዘመናቸው የሚያገኙት ወይም የሚማሩት፣ የሚቀረፁበት ነው እንጂ::

 ይህ ብያኔ ከመሰጠቱ በፊት ባህል አንድም እንደ ‘መለኮታዊ ስጦታ’ በቀርም አብሮ የሚወለድ፣ ወይም በደም በአጥንት – ‘በዘር የሚወረስ’ – ተደርጎ በብዙው ይታሰብና ይገለፅ ነበር:: እንደምናየው የታይለር ብያኔ የተሰጠው ከዚህ በተቃራኒ መሆኑ ነው:: ይህም የሰው ልጅ ባህልን ከመለኮታዊ ኃይል የሚያገኜው ወይም በተፈጥሮው ይዞት የሚወለድ ሳይሆን በሕይወት ዘመኑ ከተፈጠረበት ህብረተሰብ ውስጥ እየኖረ የሚማረው እና ከህብረተሰቡ አባለት ጋር በወል የሚጋራው መሆኑን፣ እንዲሁም፣ በየትኛውም የዓለማችን ክፍል የሚገኝ ማንኛውም ባህል በተፈጠረበት፣ ባደገበትና አገልግሎት በሚሰጥበት ማንኛውም ህብረተሰብ ውስጥ ብቁና ‘ምሉዕ’ መሆኑን መግለፁ ነው:: ‘ውስብስ’ ነው ያለውም የተለያዩ የባህል ገፅታዎች ተነጣጥለው የሚታዩ ሳይሆን በመካከላቸው እንደ ድር የተሳሰሩ መሆናቸውን ያስገነዘበት በመሆኑ በምሁራን ዘንድ ትልቅ የአስተሳሰብና የአመለካከት ለውጥ አስከትሏል::

 ቀጥሎ ደግሞ የጎርዶንን (1964) ብያኔ እንመልከት:: “ባህል ማንኛውም የምንማረውን፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፈውንና በወል የምንጋራውን የሰው ልጆች የሕይወት ስልት ሁሉ ያካትታል:: ባህል ዘመናትን የሚያቋርጥ ቢሆንም የማይለወጥ ቋሚ ነገር አይደለም:: ቋንቋ፣ እሴቶች፣ ሕጎች፣ እምነቶች እንዲሁም የሰው ልጅ የፈጠራቸው ቁሳዊ ሀብቶች ሁሉ የባህል ክፍሎች ናቸው:: ባህል በእኛ ላይ ያሚያሳድረው ተፅዕኖ ጥልቅ ነው:: ባህል በሕይወት ዘመናችን በውስጣችን እስከሠረፀ ድረስ ማንነታችንን፣ ሀሳባችንን፣ ድርጊታችንና ጠባያችንን፣ ስለምንኖርበት ከባቢ ዓለም የሚኖረንን አመለካከትና የምንሰጠውን ትርጉም ሁሉ ይገልፃል:: ለምሳሌ በመካከላችን እንዴት ግንኙነት ማድረግና እንዴት መቀጠል እንደሚኖርብን፣ ሥራችንን እንዴት ማከናወን እንደሚገባን፣ ግጭቶችንና ችግሮችን እንዴት መረዳትና መፍታት እንዳለብን፣ ወዘተ፣ የሚቀርፀን ባህል ነው::

 ባህል አንድን የማህበረሰብ ቡድን አእምሮ በጋራ ፕሮግራም ያደርጋል:: ይህም በትእምርቶች፣ በእሴቶች፣ በሥርዓተ- ክዋኔዎች፣ ወዘተ፣ አማካይነት ይገለፃል:: እኛም የሚፈጥረውን ተፅዕኖ አውቀን በትዕምርታዊ ምሳሌትነት በውስጣችን የምናሠርፀው ነገር ነው:: … ባህል ከአንድ የተወሰነ ህዝብ የሕይወት ወይም የአኗኗር ስልት ጋር የሚቆራኙ ገጽታዎችን፣ ሰዎች ሕይወታቸውን ከኅልውናቸው ጋር በማያያዝ አቀናጅተው ትርጉም የሚሰጡባቸውን ቋንቋዎች፣ ሃይማኖታዊ እምነቶች፣ ትውፊታዊ ልማዶችና ሕጎች፣ ድንቅ እሴቶችና ሀሳቦች፣ … ሁሉ የሚያካትት ሰፊ ቃል ነው” ሲል በሰፊው ይገልፃል::

 በመጨረሻ የዩኔስኮ (2001) የሰጠውን ተግባራዊ ብያኔ እንመልከት:: ይህም፡-

ባህል በዘመን እርቀትና በቦታ የተለያዩ ቅርፆችን ይይዛል:: ይህ ኅብረ-ባህል የሰው ልጆች በሚኖሩባቸው መልክዓ-ምድራዊ ወሰኖች የፈጠሯቸውን ቡድኖችና ህብረተሰቦች አንዱን ከሌላው ልዩ በሚያደርጉት ባሕርያትና የማንነት ኅብርነትን ያጠቃልላል:: ኅብረ(ብዝኀ)- ሕይወት ለተፈጥሮ አስፈላጊ የኾነውን ያህል ኅብረ-ባህልም ለሰው ልጆች አስፈላጊ የኾነ የልውውጥ፣ የፈጠራ፣ የአዲስ ግኝት ምንጭ ነው:: ይህ ብያኔም የሚያስገነዝበው ኅብረ-ባህል የሰው ልጆች ሁሉ የጋራ፣ ወይም ሁለንተናዊ ቅርስ መሆኑን ነው:: ስለሆነም ለዛሬውም ኾነ ለመጭው ትውልዶች ያለው ጥቅም ታውቆ በተግባር ሊረጋገጥ ይገባል::

የሚል ሆኖ ይገኛል::

 እነዚህ የተዘረዘሩት ብያኔዎችና የተለያዩ የባህል ገፅታዎች ሁሉ የአንድ ማህበረሰብ ወይም ማህበራዊ ቡድን ማንነቶች በሚገለፅባቸው አንፃራዊ ባሕርያት ሥር የሚመደቡ፣ የኅብረ- ባህል/ማንነት መገለጫዎችን የሚያካትቱ ብቻ ሳይሆኑ መሠረቶች መሆናቸውን መገንዘብ አስፈላጊ ይሆናል::

ኅብረ-ባህል፡- በሀገራችን ብዙ ሰዎች ‘ዳይቨርሲቲ’ (‘diversity’) የሚለውን የእንግሊዝኛውን ቃል ‘ኅብር’ በሚለው መንፈስ ሳይሆን ‘ብዝኀ’ በሚል ቅፅላዊ ሐረግ ወይም ‘ብዝኀነት’ በሚል ስም ተክተው ይጠቀሙበታል:: ይህ ትክክል አይደለም:: በእርግጥ ‘ብዝኀነት’ እና ‘ኅብር’ ወይም ‘ኅብርነት’ ቁርኝት አላቸው:: ምክንያቱም ያለ ብዝኀነት ኅብርነት አይኖርምና! በመሠረቱ በቃላቱ አጠቃቀሞች መካከል ምንም ልዩነት ባይኖር ወይም ሙሉ በሙሉ አንድ ዓይነት እሳቤ ቢወክሉ ኖሮ ከሁለቱ አንዱ በቋንቋዎች የቃላት ክምችቶች ውስጥ ሥፍራ ባልኖረውም ነበር:: በአጭሩ ቃላቱ ተያያዥነት ቢኖራቸውም በሚሰጡት ትርጉም ግን ያለያያሉ:: ስለዚህ ‘diversity’ የሚለውን የእንግዝኛውን ቃል ‘ኅብር’’ በሚል መጠቀም ለምን እንደሚያስፈልግ መጥቀስ አስፈላጊ ይሁናል::

 ይኸውም በእንግሊዝኛው እሳቤ የቃሉ አጠቃቀም የተወሰደው በቁሙ ‘ዥጉርጉር’ ፣ ‘እንደ አልጋ ልብስ’ ወይም ‘እንደ ወለል ምንጣፍ -ሥጋጃ – ያሸበረቀ’፣ ‘ቀስተ-ደመና’፣ ‘ከልዩ ልዩ ንጥረ-ነገሮች የተሠራ’፣ ‘ልብ የሚያማልል ዕይታ’ ወይም ‘ዓይን-አዋጅ’ … የሚሉትንና የመሳሰሉትን መስህብነትና ‘ኅብርነት’ ያላቸውን የዕይታ ሁኔታዎች የሚጠቅስ ነው:: በእንግሊዝኛው አጠቃቀም ‘ብዝኀነት’ ‘ፕሉራሊቲ’ ወይም ‘ሄትሮጀናይቲ’ የሚሉትን ተወራራሽ እሳቤዎች ይወክላል:: ይህን ካልኩ ለዚህ ፅሑፍ ዓላማ ‘ኅብረ- ባህል’ እያልኩ የገለፅኩት የእንግሊዝኛውን ‘cultural diversity’ የሚለውን ፍች በመውሰድ ነው:: ከዚህ አኳያ ‘ብዝኀ-ባህል’ የሚለው ‘cultural-plurality’ ወይም ‘heterogenity’ (በሓውርት) የሚለውን ነው:: ‘ብዝኀነት’ በአንድ ቦታና ጊዜ የሚኖርን ብዛት የሚያመለክት እሳቤ ነው:: ‘ኅብር’ ደግሞ የዚያን ብዛት መስተጋብራዊ ግንኙነት የርቀትና የቅርበት ደረጃና ዲግሪ ልዩነት የሚገልፅ እሳቤ ነው:: ለምሳሌ በአንድ አካባቢ የሚኖሩ የተለያዩ ባህላዊ ዳራዎችና ሃይማኖቶች ያላቸው ህዝቦች አንዱ ከሌላው ጋር የሚኖረው ቅርብና ፈጣን የግንኙነት መስተጋብር ካለው ወይም ከሌለው በዚያው መጠን የኅብረ- ባህልነቱን ደረጃና ዲግሪ የሚገለፅ ይሆናል::

 ይህ ሆኖ ‘ኅብረ-ባህል’ የሚለው በአንድ በተወሰነ አካባቢ በሚኖሩ በርካታ (በመርህ ደረጃ ሁሉንም) በባህላዊ ቡድኖች መካከል ያሉ መስተጋብራዊ ግንኙነቶችን የሚወክል ቃል ነው:: ኅብረ-ባህል ህዝቦች የሚለያዩባቸውን መገለጫዎች ወይም መንገዶች ሁሉ የሚያካትት ሰፊ ፅንሰ-ሀሳብ ነው:: በመሆኑም ግለሰቦችን፣ ማህበራዊ ቡድኖችንና የባህል ልዩነቶችን ሁሉ ያካትታል:: ብዙ ባህሎች ለዓለማችን የበለፀገ ኅብርን በማበርከት አስተዋፅኦ ያደርጋሉ:: እያንዳንዱ ባህል በረዥም ዘመናት ቅርሶቹን ልዩ የሚያደርጓቸው ክብር የተሰጣቸው ትውፊቶች እንዳሉት ሁሉ እያንዳንዱ ግለሰብም ከሌሎች ልዩ የሚያደርገው መለያ ባሕርያት አሉት:: በአሁኑ ጊዜ የፅንሰ-ሀሳቡ አጠቃቀም አንድ ባህል በተፈጥሮው ከሌላው ባህል የበላይነት አይኖረውም በሚለው መርህ ላይ በማተኮር በባህሎች መካከል ያሉ ልዩነቶችን መቀበልና አክብሮት መስጠት የሚለውን መሠረታዊ ሀሳብ የሚያንፀባርቅ ነው ልንል እንችላን:: ፈላስፋ ጆን ሂዩም፡- “ልዩነት ሰብአዊ ባሕርይ ነው:: … የልዩነት መፍትሔም ልዩነትን ማክበር ነው:: የሰላም መርህ የሚገኘውም ከዚህ ላይ ነው፤ እሱም ልዩነትን ማክበር!” ነው በማለት ገልፆታል:: ይህን ከዕለት ተዕለት የሕይወት ገጠመኝ መገንዘብ እንደምንችለው እያንዳንዳችን ከሌላው እንማራለን:: በመማማር እውቀት እናገኛለን:: ባወቅን ቁጥር እንከባበራን:: መከባበር ባለበት ቦታ ደግሞ እድገት ዕውን ይሆናል ማለት ነው::

 በአሁኑ ጊዜ በሁሉም የማህበራዊ ሳይንስ የዕውቀት ዘርፎች ምሁራን ኅብረ-ባህል የዜጎችን ተሰጥኦ የሚያሰፋ፣ ለፈጠራና አዲስ ነገር ለማፍለቅ የሚያስችል አስተዋፅኦ የሚያበረክት ለጥንካሬና ለእድገት ምንጭ መሆኑን እያረጋገጡ ቢገኙም ሌሎች

“እግዚአብሔር ለአባታችን አብርሃም ሕይወትን በዓይነት ከጥፋት ውሀ ለማትረፍ በቀስተ- ዳመና ግላፄ ከገባለት መለኮታዊ ቃል-ኪዳን ጋር ተያይዞ ከትውልድ ወደ ትውልድ በትውፊት እየተላለፈ፣ ጥልቅ ሥርፀት እያገኜ፣ የብሔራዊ አንድነታችን መሠረት ሆኖ ይኖራልና ”

በተቃራኒው ያለውን ዳይናሚዝም ዝቅ አድርገው በማየት እንደ “እንከን”፣ እንደ “ጉድለት”፣ እንደ “ግጭት ምንጭ”፣ እንደ “ሸክም” በማየት አጥላልተው በስጋት ያቀርቡታል:: እነዚህ ኅብረ-ባህል የህዝቦችን አንድነት የሚያጠናከር ኃይል ሆኖ ሳለ ከልዩነቶች ለመማማርና ለመጠቀም ችለናል ወይ? ብለው ራሳቸውን በመጠየቅ መልስ ከመሻት ይልቅ ህብረተሰቦች ተከፋፍለው የሚገኙት በልዩነቶች ምክንያት ነው በሚል የፍራት ምንጭ አድርገው ይገልፁታል:: በህዝቦች መካከል ያለውን ተመሳሳይነት ወደ ጎን በመተው በልዩነቶች ላይ ብቻ በማተኮር በፍርሀት ይባንናሉ:: እንዲህ ያለው ፍርሀት ልዩነት በተመሳሳይነት ላይ የተመሠረተ መሆኑን ካለመረዳትና መፍትሔው ምን እንደሆነ ካለመገንዘብ የመነጨ ችግር ነው::

ከዚህ በተቃራኒ አንዳንዶች በተመሳሳይነት ባሕርይው ላይ ብቻ በማተኮር ልዩነት ያለውን ጠቀሜታ ገሸሽ አድረገው ይገለፁታል:: ለምሳሌ ይህን ጉንተር (2007) እንደገለፀው ‘ኅብረ-ባህል’ በቁጥር ከሁለት እና ከዚያ በላይ የሆኑ የተለያዩ ባህሎች ያሏቸው በአንድ አካባቢ የሚኖሩ የተለያዩ ህዝቦችን መስተጋብራዊ የግንኙነት ሁኔታዎችን የሚመለከት ነው:: ጉንተር እንደሚለው ኅብረ-ባህል፣ በአንድ በኩል፣ የባህሎቹን ወይም የማህበረሰቦቹን ልዩነት፣ በሌላ በኩል፣ በመካከላቸው ያለውን ተመሳሳይነት ይመለከታል:: የልዩነቶችና የተመሳሳይነቶች ርቀትና ቅርበት ደግሞ አንፃራዊ በሆኑ የማንነት መለያ ባሕርያት ተለይተው ይታወቃሉ:: ይገለፃሉ:: እነዚህ ሁሉ የ’ኅብረ-ባህል’ ውስጣዊ ባሕርያት ስለሆኑ ‘ብዝኀ- ባህልነት’ ወይም ‘በሓውርታዊነት’፣ እንዲሁም፣ ‘የማንነት መገለጫ ባሕርያት’፣ ወዘተ፣ የሚሉት ሀሳቦች ተጠቃለው ‘ኅብረ-ባህል’ ከሚለው ፅንሰ-ሀሳብ ጋር ተወራራሽ ናቸው፤ ሁሉም በማህበረሰቦች ወይም በሰው ልጆች ተመሳሳይነቶችና ልዩነቶች ‘መስተጋብራዊ ኅብር’ ዙሪያ ያጠነጥናሉ:: ስለዚህ በምሁራን መካከል የሚካሄዱት ክርክሮች እነዚህ ጉዳዮች ‘ኅብረ-ባህል’ በሚለው ፅንሰ-ሀሳብ ተጠቃለው ብያኔ ሊሰጣቸው በመቻል፣ ባለመቻሉ ላይ ያተኮረ ሆኖ ይገኛል::

ከዚሁ ጋር በተያያዘም የሕይወትና የከባቢ አየር ጠባይ ልየነቶችን፣ የነዋሪዎችንና የኤኮሎጂ-ሥርዓቶችን በሚመለከት ‘ብዝኀ-ሕይወት’ (‘biodiversity’) የሚለው ፅንሰ-ሀሳብ እያገለገለ እንደሚገኜው ሁሉ ‘ኅብረ-ባህል’ም በተመሳሳይ መልክ ከማህበራዊና ባህላዊ የልዩነት ባሕርያት ጋር ተዛምዶ ብያኔ የመሰጠቱና የማገልገሉ ሁኔታ በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱን ቫን ሎንደን እና ዴ ሩይተር (2003) ያስረዳሉ:: ቀጥለውም፡- “‘ኅብርነት’ አንዱ ከሌላው ተነጥሎ ሊታይ በማይችልበትና በመቀያየጥና በውህደት በሚቋጭበት በ’ሉላዊ’-ዓለም (“glocalized” world) አውድ ውስጥ የሕይወት-ዓለምና የአኗኗር ስልት ‘ኅብረ-ባህል/ማንነት’ የሚለው ፅንሰ-ሀሳብም እያካተተና በፍጥነት እየወከለ መጥቷል” ይላሉ:: ቫን ሎንደን እና ዴ ሩይተር ምሁራን በሰጧቸው ብያኔዎች የኅብርነት ገላጭ ባሕርያት መሠረቶች፣ ማለትም፡- ባህሎች፣ ቡድኖችና ማህበረሰቦች እንዴት ተዋቀሩ? በብሓውርታዊነት አውድ ውስጥ እንዴት ይኖራሉ? በሚሉትና እና በመሳሰሉት ጥያቄዎች ላይ ብቻ ሳይወሰኑ እነዚህ በውስጣቸውም ሆነ ከሌሌች ጋር ያላቸው ግንኙነት እንዴት እንደተፈጠረና ቀጣይነት ይዞ እንደሚገኝ ትኩረት ሰጥተውት እንደሚገኙ ያስረዳሉ::

 በአጠቃላይ ምሁራኑ በንድፈ-ሀሳብና በብያኔ ደረጃ ‘ኅብረ-ባህል’ ባህሎች፣ ቡድኖች እና ማህበረሰቦች በውስጣቸውም ሆነ ከሌሌች ጋር ያላቸው የግንኙነት ባሕርይና ስልት ግጭትን መቆጣጠር በመቻል ላይ ብቻ ሳይሆን በመካከላቸው መቻቻልን፣ ማለትም፡- መቀራረብን፣ መተዋወቅን፣ መማማርን፣ የጋራ መግባባትን፣ የጋራ ግንዛቤ መፍጠርንና ማስረፅን፣ መረዳዳትን፣ መተሳሰብን፣ አብሮነትን፣ አንድነትንና ሰላምን፣ ወዘተ፣ በሚያካትት ሁኔታ ብያኔ እየሰጡት እንደሚገኙ ያስረዳሉ:: ቫን ሎንደን እና ዴ ሩይተር በበኩላቸውም እንዲህ ሲሉ ገልፀውታል፡- “ኅብረ-ባህል ለዓለማችን ብልፅግና አስተዋፅኦ ያበረክታል:: እያንዳንዱ ባህል ልክ ቅርሶቹን ልዩ የሚያደረጋቸው ታሪክ ክብር ያጎናፀፈው ትውፊት እንዳለው ሁሉ እያንዳንዳችንም ልዩ የሚያደርገን ተሰጥኦና ባሕርይ አለን:: ኅብረ-ባህል የእውቀት ምንጭ ነው:: አንዱ ከሌላው ለመማማር እድል ይሰጣል፤ መማማር አለብን፤ እውቀት በመማማር ይገኛልና፤ በመማማር መከባበር ይገኛል፤ መከባበር በተረጋገጠበት ቦታ ደግሞ ዕድገት ይረጋገጣል::”

ከላይ ከተነሱት ነጥቦች መገንዘብ እንደሚቻለው የኅብረ-ባህል ዓይነተኛ ባሕርያት መቻቻል እና የዕድገት ምንጭነቱ መሆናቸውን ይሆናል:: በመሆኑም መቻቻል እንደ ኅብረ-ባህል መገለጫነቱ በባሕርይው በሰዎች ወይም በማህበራዊ ቡድኖች መከካከል አንዱ ለሌላው እውቅናና አክብሮት መስጠትን የሚያመለክት ፅንሰ-ሀሳብ ነው:: እያንዳንዱ ሰው ልዩ ነው ብሎ በመረዳት የእያንዳንዳችንን ልዩነት መቀበልና እውቅና መስጠትን የሚመለከት ነው:: ይህም ከዘር፣ ከህዝብ ቡድን የማንነት መገለጫዎች፣ ከፆታ፣ ከሀብት፣ ከሃይማኖትና ከፖሊቲካ እምነት፣ ወዘተ፣ አኳያ ሊታይ የሚችል ነው:: እንዲሁም በሰዎች መካከል አንዱ ከሌላው በመማማር የጋራ ግንዛቤ በመያዝ ከተራ መቻቻል አልፎ የበለፀገ ቀጣይ የልዩነት ገፅታዎችን በግለሰቦች ወይም በቡድኖች ውስጥ ማስረፅ ማለት ነው::

ይህንም በ2003 ዩኔስኮ በተጠናከረ ሁኔታ እንደሚከተለው ገልፆታል፡ –  

 ኅብረ-ባህል የሚወክለው የሰው ልጅ የተለያዩ ቡድኖችና የህብረተሰቦች አንዱን ከሌላው ልዩ የሚያደርጉ ባሕርያትና የተለያዩ የማንነት መገለጫዎች ኅብርን ነው:: … በዚህ ግንዛቤ መሠረት ኅብረ- ባህል የሰው ልጆች ሁሉ ቅርስ ነው:: ኅብረ-ባህል ሰብአዊነት ምን ማለት እንደኾነ የሚገልፅ ሁለንተናዊ ፅንሰ-ሀሳብ ነው:: እጅግ በጣም ጠቃሚው ጉዳይ ልክ ‘ኅብረ-ሕይወት ለተፈጥሮ አስፈላጊ የኾነውን ያህል፣ ኅብረ-ባህል ለሰው ልጆች በጣም አስፈላጊ የኾነ የልውውጥ፣ የፈጠራ፣ የአዲስ ግኝት ምንጭ፣ በእውቀት ላይ ለተመሠረተ የኢኮኖሚ ዕድገት ምንጭ ነው::’ በተጨማሪም በኅብረ-ባህል ላይ በቂ እውቀትና መረጃ ተመሥርቶ ‘ሁሉንም ዜጎች ያለ ልዩነት በእኩልነት ለማሳተፍ፣ የሰላም መሠረት የሆነ ማህበራዊ አንድነትንና የጥበቃ ዋስትናዎችን የሚያረጋገጥ ፖሊሲ በሥራ ላይ ለማዋል ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው::

ከላይ ከተጠቀሱት ፍችዎች፣ ምሁራዊ ብያኔዎች፣ አስተያየቶችና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት ግንዛቤዎች አጠቃለን ስናይ የፅንሰ-ሀሳቡ አጠቃቀም በይበልጥ ‘ኅብር’ የሚለውን እሳቤ የሚጠቅስ ሆኖ እናገኛለን:: ይህን ለማጠናከር ያህል፣ ለምሳሌ፡- ጀሲ ጃክሰን፣ “ሠንደቅ ዓላማችን ቀይ፣ ነጭና ሰማያዊ፣ ሀገራችን ቀስተ-ዳመና፡- ቀይ- ብጫና ቡናማ፣ ጥቁርና ነጭ – እናም በእግዚአብሔር ዘንድ ሁላችንም ተወዳጅ ነን” (“Our flag is red, white and blue, but our nation is a rainbow- red, yellow, brown, black and white- and we’re all precious in God’s sight.”) ሲሉ አሜሪካን በኅብርነት ገልፀዋታል:: በቅርቡም ዴዝሞንድ ቱቱ አዲሲቱን ደቡብ አፍሪካ፡- “ዘ ሬንቦው ኔሽን” (“ብሔረ-ቀስተ- ዳመና”) በሚል የሀገራቸውን ብሔራዊ ማንነት መስለውታል:: የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ፡- ቀይ፣ አረንጓዴና ብጫ ኅብረ-ቀለማት ቀዳሚ ኩሉ አርአያ ምሳሌ መሆኑንም ከዚህ ላይ ልብ ማለት ይገባናል:: ትርጉሙ እግዚአብሔር ለአባታችን አብርሃም ሕይወትን በዓይነት ከጥፋት ውሀ ለማትረፍ በቀስተ-ዳመና ግላፄ ከገባለት መለኮታዊ ቃል-ኪዳን ጋር ተያይዞ ከትውልድ ወደ ትውልድ በትውፊት እየተላለፈ፣ ጥልቅ ሥርፀት እያገኜ፣ የብሔራዊ አንድነታችን መሠረት ሆኖ ይኖራልና! በአጭሩ ከእነዚህ ፍችዎችና አገላለፆች የምንረዳው ‘ኅብር’ የሚለው ቃል የሚሰጠው ትርጉም ‘ብዝኀነት’ ከሚለው መጠን፣ ብዛት፣ አመልካች ቃል የተለየ መሆኑን፣ እንዲሁም፣ የመቻቻል እሴቶች ምንጭነቱንና ከባህል ተነጥሎ የሚታይ፣ የሚተነተንና የሚተረጎም አለመሆኑን ነው::

ምሁራን በብያኔና በንድፈ-ሀሳብ ግንዛቤ ደረጃ በባህሎች ውስጥ፣ በባህሎች መካከል እና በተለያዩ ሀገሮች ባህሎች መካከል ዝምድናዎችን ለመለየት የሚደረጉ ንፅፅራዊ ጥናቶችን ለማጠናከር የ’ኅብረ- ባህል’ ገጽታዎችና ከዚሁ ጋር ተወራራሽነትና ጥብቅ ዝምድና ያላቸውን ቁልፍ ፅንሰ-ሀሳቦችን በመመርመርና በማብላለት አንድ አቃፊ ብያኔ መስጠት አስፈላጊ በመሆኑ ላይ ማተኮራቸውን አይተናል:: ከእነዚህ ቁልፍ ሀሳቦች መካከልም ‘ማንነት’ (identity)፣ ‘የማንነት መገለጫ ባሕርያት’ (ethnicity) የሚለው ይሆናል::

“ኅብረ-ባህል ለዓለማችን ብልፅግና አስተዋፅኦ ያበረክታል:: እያንዳንዱ ባህል ልክ ቅርሶቹን ልዩ የሚያደረጋቸው ታሪክ ክብር ያጎናፀፈው ትውፊት እንዳለው ሁሉ እያንዳንዳችንም ልዩ የሚያደርገን ተሰጥኦና ባሕርይ አለን”

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top