ጥበብ በታሪክ ገፅ

በዓሉ ግርማ፤ ወዴት አለህ? 35 ዓመት እንደዋዛ…

በኢትዮጵያ ዘመናዊ ልቦለድ እና ጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ የነበረው አበርክቶ ከፍተኛ ነው። ጋዜጠኝነትን በማስተርስ ደረጃ ተምሮ ሙያውን እየመራ በተጓዳኝ የፈጠራ ስራ ውስጥ እሱነቱን ከቶ ጥበብን በአግባቡ የዋጀ ነው‐ በዓሉ ግርማ። በህይወት ቢኖር ዘንድሮ 83 ዓመት ልደት በዓሉን ያከብር ነበር፡፡ ዛሬም በህይወት ይኑር አይኑር ባለየለት ሁኔታ ድንገት ከቤት ወጥቶ ደብዛው ከጠፋ እነሆ ዘንድሮ የካቲት 24/2011 ዓ.ም ልክ 35 ዓመትን ደፈነ። ባለቤቱ እትዬ አልማዝ ስለሱ ስታነባ፣ አቅማቸው ሳይጠና የተለያቸው ሦስት ልጆቹ እሱን ሲያልሙ ሦስት አሰርት ዓመታትን በጣር ዘለቁት።

 ከበዓሉ ደብዛ መጥፋት ጋር በተያያዘ ተጠያቂነት አለባቸው የሚባሉ የደርግ ባለስልጣናት በምህረትና በፍርድ ዛሬ ነጻ ወጥተዋል። እነዚህ ባለስልጣናት መጽሐፍ በጻፉ ቁጥር ምስጢሩን ይገልጻሉ ወይም አጠፋፉን ያመለክታሉ የሚል ጉጉት በህዝቡ ዘንድ ቢኖርም፤ ምንም ተጨባጭ ነገር ሳይሰጡን በተድበሰበሰ መረጃ ጉዳዩን እየዘለሉት ያልፋሉ። አንዳቸውም ተጠያቂነትን አልፈቀዱም። ውስጣዊ መቆርቆራቸውን እየነገሩን ራሳቸውን ከደሙ ነጻ ከማድረግ በዘለለ ትውልዱ እውነታውን እንዲያውቅ አላደረጉም።

ገነት አየለ «የሌተናል ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማሪያም ትዝታዎች» በሚል ርዕስ በ1994 ዓ.ም ባሳተመችው መጽሐፏ ኮሎኔል መንግስቱን ስለበአሉ አሟሟት ጠይቃቸው ስለ አሟማቱም ሆነ ስለ አጠፋፉ ምንም እንደማያውቁ፣ እርሳቸውም በእርሱ ደም እጃቸው እንዳልጎደፈ ተናግረዋል። በዚሁ መጽሐፍ በቁጥር 53 የኮድ ቁጥር የተሰጣቸው ግለሰብ ግን፤ በኮሎኔል መንግስቱ ትዕዛዝ የደህንነቱ ኃላፊ ጓድ ተስፋዬ ወልደስላሴ እንዳስገደሉት ነው የተናገሩት።

ኮሎኔል ፍስሐ ደስታም «አብዮቱና ትዝታዬ» በተሰኘ ግዙፍ መጽሐፋቸው ስለ በዓሉ በሰጡት ንዑስ ርዕስ ገነት አየለ ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማሪያምን አነጋግራ በመጽሐፏ ያሰፈረችውን መረጃ በምንጨነት ጠቅሰው ጥቂት ነገር ከማለታቸው ውጪ ሌላ መረጃ አልሰጡንም። ከደርግ ውድቀት በኋላ እስር ላይ እያሉ የደህንነቱን ኃላፊ ኮሎኔል ተስፋዬ ወልደስላሴን ስለ በዓሉ አጠፋፍ ጠይቀዋቸው «መጽሐፉ ከወጣ ጥቂት ወራት በኋላ ሻብያ በሬዲዮ ጣቢያው በማስተላለፉ በሰራዊቱ ላይ ለከፍተኛ ፕሮፓጋንዳና ቅስቀሳ ይጠቀምበት ጀመር። በዚህ ምክንያት የፖለቲካ፣ የደህንነት ሰራተኞችና አዛዦች ከፍተኛ ሮሮና ተቃውሞ ስላሰሙ፤ በተለይ በአመራሩ ላይ ቅሬታቸውን ስለገለጹ ነው»ማለታቸውን አስፍረዋል። በዚህም መገደሉን እንዳረጋገጡ ገልጸዋል።

በደርግ ባለስልጣናት ሁለተኛ ሰው የሚባሉት ኮሎኔል ፍቅረስላሴ ወግደረስ ድካም በፈጠረባቸው ቸልተኝነት ለህትመት የተዘጋጀውን የበዓሉ መጥፊያ ሰበብ የሆነውን «ኦሮማይ» መጽሐፍ ረቂቅ ሳያነቡት ከቁራጭ ማስታወሻ ጋር ኃላፊነቱን ለገምጋሚ ቦርድ በማስተላለፋቸው ሊታተም መቻሉን፤ በዚህም ከፍተኛ ቀውስ መፈጠሩን ኮሎኔል መንግስቱ ከገነት አየለ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል። ይሁንና እንዲህ የተባለላቸው የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ፍቅረሥላሴ ወግደረስ «እኛና አብዮቱ» በሚል ርዕስ ባሳተሙት ዳጎስ ያለ መጽሐፋቸው ውስጥ ስለ በዓሉ ምንም ምንም አላሉም። ለምን?

«የቀይ ኮኮብ ጥሪ» በተባለ ልቦለድ መጽሐፉ የሙያ ባልደረቦቹ በሆኑ ጋዜጠኞች ባህሪያትና ማንነት ላይ ተመስርቶ ስም እየቀያየረ እንደሰራ የሚነገርለት በዓሉ፤ «ኦሮማይ» በተባለ ረጅም ልቦለድ መጽሐፉ ደግሞ እንደ ቀይ ኮኮብ ጥሪ ሁሉ የደርግ ባለስልጣናትን ማንነትና ባህሪያት መሰረት አድርጎ ፖለቲካውን ተሳልቆበታል በሚል ደርግ እንዳጠፋው ነው ሲነገርና ሲጻፍ የቆየው።

 «ያለ ጥፋቱ፣ ያለ ፍርድ … ጠፋብኝ» የሚሉት ባለቤቱ ወ/ሮ አልማዝ አበራ፤ ሞቶም ከሆነ እንዲነግሯቸውና አጽሙ ያረፈበትን ስፈራ እንዲያሳይዋቸው ባለስልጣናትን ሲለማመኑ ኖረዋል። ቀደም ባሉት ጊዜ ከጋዜጠኞች ጋር ቃለ ምልልስ መስጠትን የሚፈቅዱት ወይዘሮ አልማዝ፤ ዛሬ ዛሬ ትዝታቸውን እየቀሰቀሱ ይበልጥ ኃዘን ላይ ስለሚጥላቸው፣ ጤናቸው ስለሚታወክ በጉዳዩ ላይ ማንንም ማናገር አይፈቅዱም። የእርሳቸው ህልምና ሃሳብ በዓሉን ማግኘት ነው። የእርሳቸው ቁዘማም ህመምም በዓሉን ማጣት ነው። በ1984 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሬዲዮ የኪነ ጥበብ ፕሮግራም ላይ ጋዜጠኛ ደጀኔ ጥላሁን ባደረገላቸው ቃለ መጠይቅ፤ ስለ በዓሉ በድንገት ወጥቶ መቅረት፣ ከማንነቱ እና ከመጽሐፎቹ አኳያ ላቀረበላቸው ጥያቄ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተው ነበር።

 በቃለ ምልልሱ ወ/ሮ አልማዝ እንዳሉት፤ በዓሉ አገሩን ይወዳል፤ ቤተሰቦቹን ይወዳል። በማህበራዊ ሕይወቱ ቁጥብ ነው። ብቸኝነትን ይወዳል። በብቸኝነቱ ውስጥ ሆኖ በሚወልዳቸው መጽሐፎቹ ይደሰታል። በመንግስት ስራ ውስጥ ሆኖ አንድም ጊዜ የአመት እረፍት ወስዶ አያውቅም፤ ያለ ደመወዝ ከስራ ከታገደ ወዲህ ለስድስት ወራት የነበረው ጊዜ ግን እረፍት ሳይሆን ጭንቅ ነበር። ቀን ከቤት ወጣ በማለት ምሳም ቁርስም ሳይበላ ውሎ ማምሻውን ወደ ቤት ብቅ ሲል አንድ ጓደኛው «የምናውቀው ቦታ እንገናኝ» ሲል በስልክ ያስቀመጠውን መልእክት እንዳደረሱት ወዲያው ወደዚያው ሄዶ በዚያው መቅረቱን የተናገሩት ወ/ሮ አልማዝ፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ጓደኞቹም ሆኑ የስራ ባልደረቦቹ ጠይቀዋቸው እንደማያውቁ ነው በቁጭት የተናገሩት።

 ዛሬ ላይ እድሜ የተጫናቸው ወ/ሮ አልማዝ ውስጣቸው በነርቭና በሌላ ሌላ በሽታም ታምሷል። ለ35 ዓመታት በኃዘን ያነቡበት ዓይናቸው ተጎድቷል። የእንባ ምንጫቸው ደርቋል። በዓሉን የማግኘት ተስፋቸው ባይነጥፍም የመፋረጃ አቅማቸው ግን በብዙ ተጎድቷል። ስለ በዓሉ ፍርዱን እና ኃላፊነቱን ለህዝብ ሰጥተዋል። ቀደም ባሉት ጊዜ ስለ በዓሉ የተጻፉና የተነገሩ ሁሉ አያመልጧቸውም፤ ዛሬ ዛሬ ግን ስለ እሱ ምንም ነገር መስማትም ሆነ ማንበብም ሆነ መናገር አይፈቅዱም። ምክንያት አላቸው።

“እንባ እንባ ይለኛል ይተናነቀኛል… እንባ ግን የታባቱ ደርቋል ከረጢቱ ሳቅ ሳቅም ይለኛል ስቆ ላይስቅ ጥርሴ ስቃ እየነደደች መከረኛ ነፍሴ”

በመጽሐፍ መልክ የወጡ፣ በጋዜጣ፣ በመጽሔትም የተጻፉ፣ በአንዳንድ ድረ ገጾችና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች ስለበዓሉ የተነገሩት ሁሉ ስለአጠፋፉ እና አሟሟቱ የተለያዩ መላ ምቶችን አቀረቡ እንጂ የሆነውን በተጨባጭ የሚገልፁ ሆነው አልተገኙም። ቤርሙዳ በተባለ የደርግ ማሰቃያ እስር ቤት ከመታየቱና ጠፋ የተባለ ሰሞን ቮልስ ዋገን መኪናው ቃሊቲ መስመር አስፋልት ዳር ከመገኘቷ በቀር ህዝብ ስለ በዓሉ ተጨባጭነት ያለው ሌላ መረጃ አላገኘም።

ስለ በዓሉ ማንነትና ስራዎቹ መጽሐፍ ያዘጋጀው ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ፤ አንባቢ ከመጽሐፉ የሚፈልገው ዋና ጉዳይ ተንታኝ ምዕራፍ ላይ፤ አንድ የደህንነት አባል ለሚስቱ «ዛሬ በዓሉን ጨርሼው መጣሁ» ብሎ መናገሩን በሌላ ሰው ምንጭነት የሰሚ ሰሚ ነገረን እንጂ፤ መረጃው መጨረሻውን ደምድሞ ትውልዱን ከፍለጋ የሚገታው አልሆነም። ይህ የጥርጣሬው አንዱ አመላካች መንገድ ወይም ጥቁምታ እንጂ፤ ጥያቄውን የሚያቆም አይደለም። እንደሚታወቀው በደርግ ዘመነ መንግስት አያሌ ዜጎች በደህንነቶች ተጠልፈው የደረሱበት ደብዛ ጠፍቷል። በዓሉ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ነው። ትውልዱ በዓሉን በልዩ ሁኔታ የሚፈልገው ያለ ምክንያት አይደለም። በዓሉ የቤተሰቡ ወይንም የግለሰቦች ብቻ አይደለም።

 የህዝብ ኃብት ነው። በድርሰቱና በጋዜጠኝነቱ የሕዝብ አይን እና ጆሮ ሆኖ እንዳገለገለ ሁሉ፤ ማንነቱም የሕዝብ ነው። ለዚህ ነው የበዓሉ ጉዳይ መጨረሻው ምን እንደሆነ የሚጠይቀው። ጥያቄው ተጨባጭነት ያለው ምላሽ እስካልተገኘለት ድረስ በትውልድ ቅብበሎሽ ውስጥ የቤት ስራ እንደሆነ ይቀጥላል። ስለሱ ማንነትና ስራዎቹ፣ ስለ አጠፋፉ ምስጢር ጥያቄዎች ብዙ ብዙ ይጻፋል። ከመላምት የሚያወጣ እውነታ ግን ዛሬም በህይወት ያሉ የቀድሞ ባለስልጣናትና ደህንነቶች ዘንድ ይኖራል የሚል እምነት አለ። በንስሃ እድሜ ላይ ያላችሁ እናንት የበዓሉን መጨረሻ የምታውቁ ሰዎች ሆይ እባካችሁ ተንፍሱ። ታዛ መጽሔታችን ለእንዲህ አይነት ሰዎች ገጿን ክፍት አድርጋ እንደምትጠብቅ እንገልጻለን፤ ተጨባጭ ማስረጃና እውነታ ላላቸው ሁሉ ጥሪያችን እናቀርባለን። ቸር ያቆየን።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top