ጣዕሞት

«ኢትዮጵያዊው ሱራፌ» መጽሐፍ ተመረቀ

ስለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የሕይወት ታሪክና አስተዋጽኦ የሚተርከውና «ኢትዮጵያዊው ሱራፌ» በሚል ርዕስ በሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የተዘጋጀው መጽሐፍ ሰሞኑን ተመርቆ ገበያ ላይ ውሏል።

በኢንተር ኮንትኔንታል ሆቴል አዳራሽ በአራት ሊቃነ ጳጳሳት ቡራኬ የተመረቀው ይህ ባለ 1‚082 ገጽ መፅሐፍ፤ 4 ክፍሎች እና 27 ምዕራፎች ያሉት ሲሆን፤ በ 750 ብር እየተሸጠ ይገኛል።

ስለ መጽሐፉ አጠቃላይ ዳሰሳዊ ጥናት በዲያቆን ታደሰ ወርቁ፤ የቅዱሳን ገድላት ምንነት፣ መጽሐፍ ቅዱስና ታሪካዊ መሰረት ከ«ኢትዮጵያዊው ሱራፌ» መጽሐፍ አንጻር በዲያቆን ብርሃኑ አድማስ፣ እንዲሁም የጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሐዋሪያዊነት እና የሐዋሪያዊ አገልግሎት መስመሮች በአቶ ይኩኖ አምላክ ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል።

 መጽሐፉን ለማዘጋጀት ከአገሪቱ አልፎ በውጪ በሚገኙ ሙዚየሞችና ቤተ እምነቶች ጭምር መረጃ ማሰባሰቡን የተናገረው ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል፤ አጠናቆ ለህትመት ለማብቃት አሥር ዓመታት እንደፈጀበት ገልጿል።

የሀገር ፍቅር ቴያትር ለተሻለ ጥበባዊ ሥራ

እንዲተጋ ተጠየቀ

የሀገር ፍቅር ቴያትር ካሉበት ዘርፈ ብዙ ችግሮች ወጥቶ ጥበባዊ ድግሱን በተሻለ ሁኔታ ለማቅረብ የሚያስችለውን የአሰራር ስርዓት መዘርጋት እንዳለበት ተነገረ።

 ቴያትር ቤቱ ከ84 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ማግኘቱን አስመልክቶ፤ ሰሞኑን ባሰናዳው የ«እንኳን ደስ አላችሁ» መርሃግብር ላይ የታደሙ አርቲስቶች በሰጡት አስተያየት፤ ቴያትር ቤቱ እንደ አንጋፋነቱ ስሙንና ክብሩን ጠብቆ እንዲዘልቅ አስተዳደራዊ መመሪያዎችም ሆኑ የአሰራር ስርዓቶች ጥበብን ማእከል ያደረጉ መሆን ይገባቸዋል ብለዋል።

በተለያዩ ዘመናት ቴያትር ቤቱን ለማስተዳደር የተቀመጡ ሀላፊዎች የቴያትር ቤቱን የቀደመ ስምና ዝና እንዳላስጠበቁ፣ ሙያተኞችን በክብር እንዳልያዙ የጠቆሙት አስተያየት ሰጪዎቹ፤ በሙዚቃውም ሆነ በቴያትሩ ዘርፍ ደህና አቅም ያላቸው አርቲስቶች እየተገፉ ለመልቀቃቸው ምክንያቱ የአስተዳደር ብልሹነት የፈጠረው ችግር መሆኑን በቁጭት ተናግረዋል።

 በአንጻራዊነት በአሁኑ ወቅት የተቀመጠው አስተዳደር የተሻለ ስለመሆኑ ለቴያትር ቤቱ ህልውና መሰረት የሆነውን የይዞታ ካርታ ማስገኘቱ፣ እየራቁ ያሉ የጥበብ ሰዎችን እንዲቀርቡ መጥራቱና አዳዲስ የጥበብ ድግሶች እንዲፈጠሩ ማበረታታቱ መልካምነቱን እንደሚያሳይ ጠቅሰው፤ አሁንም አስተዳደሩ የአርቲስቱን ሁለንተናዊ ነጻነትና ክብር ጠብቆ ለመዝለቅ የሚጥር ከሆነ በሂደት ለሚያጋጥሙ ችግሮች ሁሉ አርቲስቱ ከጎኑ እንደሚቆም አረጋግጠዋል። አርቲስት ሳራ ተክሌ እንባ እየተናነቃት በታዳሚው ፊት ቆማ በሰጠችው ሃሳብ፤ ከልጅነቷ ጀምሮ ያደገችበትን የሃገር ፍቅር ቴያትር ቤት እንደምትሳሳለት ገልፃ፤ በሕይወት የሌሉትንም ሆነ ዛሬ በሕይወት ያሉትን የጥበብ እናትና አባቶቿ፣ ባልደረቦቿ እና የሀገር ፍቅር ማህበረሰብን በጠቅላላ ከልብ አመሰግናለች። ለዛሬው ቴያትር ቤት መቆም የደከሙ አንጋፋዎችን በማክበር፤ በመነጋገር፣ በመከባበርና ለአንድ ጥበባዊ አላማ በማበር ቴያትር ቤቱም ማሳደስ እንደሚቻልም ገልጻለች። እርሷም የበኩላን ሁሉ ለማድረግ መዘጋጀቷን ተናግራለች።

ቴያትር ቤቱ ሲጀመር ጀምሮ የነበረው ታሪክ የሀገር ፍቅርን፣ መተባበርን፣ እርስ በርስ መተሳሰብንና መተዛዘንን የሰበከ፣ በተግባርም በጥበብ ሙያተኞቹ አማካኝነት ያሳየ መሆኑን ያመለከተችው አርቲስት አሰለፈች አሽኔ በበኩሏ፤ ቴያትር ቤቱን በግንባታ ደረጃ ለማሻሻል የሚደረገው ጥረት መልካም ቢሆንም፤ ታሪክ እንዳይጠፋ መጠንቅቅ እንደሚገባ በአጽንኦት ተናግራለች።

 ተመሳሳይ ሃሳብ የሰነዘረው አርቲስት ኪሮስ ኃይለሥላሴ በበኩሉ፤ ቴያትር ቤቱን አፍርሶ ሌላ ለመገንባት ሲሞከር ያለውንም እንዳናጣ መጠንቀቅ ያስፈልጋል ብሏል።

 በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሰጡት የቴያትር ቤቱ አስተዳደር ክፍል ሀላፊ መምህሩ ጫሞ፤ ቀደም ብለው የነበሩ አስተዳደሮች ለጥበባዊ ጉዳዮች እንጂ የይዞታ ጉዳይ የራስ ስለሆነ የማያሳስባቸው በመሆኑ ካርታ ሳያወጡለት መቅረታቸውን ጠቅሰው፤ አሁን ባለው ሁኔታ የቴያትር ቤቱ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ሊኖረው ግድ ስለሚል አስተዳደሩ ባደረገው ጥረት ሊሳካ ችሏል ብለዋል።

 6,856 ካሬ ሜትር ቦታ የቴያትር ቤቱ ይዞታ ሆኖ መረጋገጡን ጠቅሰው፤ ከዚህ ውስጥ ምንም ነገር ባላረፈባቸው ቦታዎች ላይ ለቴያትር ቤቱ ሙዚየምም ሆነ ለሌሎች አስፈላጊ ጉዳዮች የሚውሉ ግንባታዎችን ለማካሄድ መታቀዱን ተናግረዋል። በጀቱም በሕዝብና በመንግስት የሚሸፈን መሆኑን ገልጸዋል:: ለዚህም የፍላጎት መግለጫዎች፣ የአፈር ምርመራ እና የዲዛይን ስራ መጠናቀቁን አብራርተዋል። በማሻሻያ ግንባታ ውስጥ የቴያትር ማሳያ አዳራሹም ሆነ ሌሎች ለቢሮነት የሚያገለግሉ ታሪካዊ ቤቶች እንደማይፈርሱ ተናግረዋል። ለዚህም ኮሚቴ ተዋቅሮ እንደሚሰራ ገልጸዋል። ሐምሌ 11 ቀን «የሃገር ፍቅር ቀን» ሆኖ እንዲከበር ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ለመረዳት ተችሏል።

በዕለቱ የቴያትር ቤቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ዮሐንስ ስለሺ «አብረን እንስራ፣ አብረን እንደግ፣ አብረን ጥበብን እናሳድግ» የሚል መልዕክት ያለው ንግግር ያደረጉ ሲሆን፤ ስለ ቴያትር ቤቱ አመሰራረትና ታሪክ አጭር የዳሰሳ ጥናትም በአርቲስት ዮሐንስ አፈወርቅ ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል።

የዋሽንቱ ሊቅ አረፈ

ዓለምን ያስደመመው የሕዝብ ለህዝብ የኪነት ቡድን ውስጥ በዋሽንት አጨዋወቱ የተደነቀው፤ አርቲስት ወጋየሁ ንጋቱ በሬዲዮ የተረከውን የሀዲስ አለማየሁ ፍቅር እስከመቃብር ዘመናዊ ረጅም ልቦለድ መጽሓፍ በዋሽንቱ ያጀበው ዮሐንስ አፈወርቅ ሰሞኑን ማረፉ አስደንግጧል፤ አሳዝኗልም:: በቀድሞው ክፍለ አገር አገው ምድር አውራጃ ባንጃ ወረዳ የተወለደው ዮሐንስ፤ ከልጅነቱ ጀምሮ ዋሽንት ሲጫወት ነው ያደገው:: ዋሽንቱን ይዞ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በተለያዩ የምሽት ክበቦች በመጫወት ኑሮውን በማሸነፍ ላይ እያለ ችሎታውን ያዩ አንድ የፖሊስ ሰራዊት ባልደረባ ወደ ፖሊስ ሰራዊት ሙዚቃና ቴአትር ክፍል ይዘዉት በመሄድ እንዲቀጠር አደረጉ‐ በ1955 ዓ.ም:: ከዚያ በኋላ ከቦታ ቦታ እየቀያየረ ዋሽንትን ሲጫወት የኖረው ዮሐንስ፤ በኦርኬስትራ ኢትዮጵያ፣ በማዘጋጃ ቤት (ቴአትርና ባህል አዳራሽ) አገር ፍቅር ቴአትር እና በሌሎች ቴአትር ቤቶችም በመዘዋወር ዋሽንቱን ሲጫወት ኖሯል:: የተለያዩ ድምጻዊያንን በማጀብ በተለያዩ ቴአትር ቤት መድረኮች፣ ኮንሰርቶች ከመጫወቱ በዘለለ፤ በተለያዩ የውጪ አገራትም ከባንዶች ጋር በመጓጓዝ ሙያዊ ብቃቱን በማሳየት ተደናቂነትን አትርፏል::

በ72 ዓመቱ ይህችን ዓለም በስጋ ሞት የተሰናበተው የዋሽንቱ ሊቅ አርቲስት ዮሐንስ፤ የካቲት 19 2011 ዓ.ም በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ስርአተ ቀብሩ ተፈጽሟል:: አርቲስቱ የአምስት ልጆች አባት እንደነበረ በስርአተ ቀብሩ በተነበበው ሕይወት ታሪኩ ለማወቅ ተችሏል::

የታዋቂው መሲንቆ ተጫዋች ለገሰ

አብዲ ሐውልት ተመረቀ

የጥበብ አፍቃሪዎች እና የአርቲስቱ አድናቂዎች በተገኙበት ሰሞኑን በተከናወነው በዚህ የምረቃ ሥነ ስርአት ላይ እንደተገለጸው፤ ለአርቲስቱ እንዲህ ያለ ክብር መስጠት ከትውልዱ የሚጠበቅ ነበር::

 በ1931 በሰላሌ ያያ ቀጨማ ከአባታቸው ከአቶ አብዲ ዳዲ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ፎሌ ጉደታ የተወለዱት አርቲስት ለገሰ አብዲ ከልጅነታቸው ጀምሮ ባላቸው ከፍተኛ ማስንቆ ፍቅር ሙያውን እስከ እድሜ ልካቸው ዘልቀውበታል::

አርቲስቱ አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ ሀገር ፍቅርን ጨምሮ በብሄራዊ ቴአትር፡ በአዲስ አበባ ቴአትር ማዕከል፤በፖሊስ ኦረኬስትራና በክቡር ዘበኛ የሙዚቃ ሥራቸውን ሲያቀርቡ ኖረዋል::

አርቲስት ለገሰ በአፋን ኦሮሞ በነፃነት መዝፈንም ሆነ ሃሳብን መግለፅ በማይቻልበት ወቅት፤ ችግሮችን በማለፍ በመዝፈን ለቋንቋው እድገትና ዕውቅና ታላቅ ተጋድሎን ካደረጉ አንጋፋ የመድረክ ፈርጦች መሃከል እንደሆኑም ይነገርላቸዋል::

ከህይወት ታሪካቸው መረዳት እንደተቻለው፤ ምንም አይነት ዘመናዊ የሙዚቃ ትምህርትን ሳይማሩ አራቱንም የሙዚቃ ቅኝቶች እንደሚጫወቱ የጫወቱ ነበር:: ከ 60 ዓመታት በላይ በሙዚቃው ህይወት ቆይተዋል:: በመድረክ በተለያየ ጊዜ ካቀረቧቸው ዘፈኖች በተጨማሪ 11 የዘፈን ሲዲዎችንና 1 ቪሲዲ አሳትመው ለገበያ አቅርበዋል።

 የሰባት ልጆች አባት ነበሩት አርቲስት ለገሰ፤ በተወለዱ በ80 ዓመታቸው በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ጥቅምት 12 ቀን 2011 ስርዓተ ቀብራቸው መፈጸሙ የታወሳል:: ሀውልቱም ተመረቀው እዚያው ነው::

የድምጻዊ አሚር ዳውድ ስርአተ ቀብር ተፈጸመ

በትግሪኛ ዘፈኑ የሚታወቀው አርቲስት አሚር ዳውድ በመቀሌ ዓይደር ሆስፒታል በህክምና ሲረዳ ቆይቶ ማረፉ ተሰምቷል:: በግጥምና ዜማ አፍላቂነቱ የሚታወቀው አሚር በተለይ «አልሞቱም ጀግኖቻችን» በሚለው ስራው ጎልቶ ይታወቃል::

 ይህ አርቲስት በቅርቡ 400ሺ ብር ያወጣበትን የሙዚቃ አልበም በትግራይ ክልል ለሚገኙና በተለያዩ ክልሎች ለተፈናቀሉ የክልሉ ተወላጆች እንዲውል ማበርከቱ ታውቋል:: አርቲስቱ የግጥምና የዜማ ደራሲ ም ነው፡፡ ባለ ትዳርና የሦስት ልጆች አባት የሆነው አሚር ሰሞኑን በመቀሌ ሙስሊም መቃብር ስርአተ ቀብሩ ተፈጽሟል::

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top