የታዛ ድምፆች

በጭብጨባ የተሸኘው አበው ከያኒ “ተንቀሳቃሹ ቤተ መዘክር”

ተዋናይም፣ የቴያትር አዘጋጅም፣ ደራሲም ነበር አንጋፋው ከያኒ ጌታቸው ደባልቄ። ለታዋቂ ድምጻውያን የዜማ ግጥሞችን አበርክቷል። “አደረች አራዳ” እና ግርማ ነጋሽ የተጫወታቸው “ምነው ተለየሽኝ”፣ “እንገናኛለን” እና “የኔ ሃሳብ” እዚህ ውስጥ አሉበት። ከድምጻዊቷ ከእትዬ ጠለላ ከበደ ጋር ለአራት ወራት እስር የተዳረጉበት “ሎሚ ተራ ተራም” የእሱ ድርሰት ነበር። የተለያዩ ሃገራት መሪዎች ወደኢትዮጵያ ሲመጡ የመቀበያ ዜማዎች ይዘጋጁ ነበር። ለዚህም ግጥሞች ቀድመው ይሰናዳሉ። አበው ከያኒ ጌታቸው በጭብጨባ የተሸኘው አበው ከያኒ “ተንቀሳቃሹ ቤተ መዘክር” ለእንደነዚህ አይነት አጋጣሚዎች ከሚፈለጉ ባለሙያዎች አንዱ ነበር። በአንድ ወቅትም “ኒሜሪ ኒሜሪ፣ የሱዳኑ መሪ” የሚል አዝማች ያለው ግጥም ጽፎ ነርሲስ ናልቫንዲያን ዜማ እንደሠሩለት ያስታውሳል። የብርቅዬዋን የመድረክ ኮከብ የእትዬ አስናቀች ወርቁን የሕይወት ታሪክ ጽፎም አሳትሟል። በዚህም ለኢትዮጵያ ኪነጥበብ ተጨማሪ ውለታ ውሏል።

 ባለፈው ሳምንት ከዚህ ዓለም በሞት የተለየን ጋሽ ጌታቸው በኪነጥበብ መስክ ጥናትና ምርምር ለሚያደርጉ ባለሙያዎች፣ ለጋዜጠኞችና ለታሪክ ተመራማሪዎች የማይነጥፍ ምንጭ ሆኖ ቆይቷል። ጋዜጦች፣ መጽሔቶች፣ የራዲዮና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የመረጃ ጥያቄ ሲኖራቸው ቀድሞ ወደሃሳባቸው የሚመጣው እሱው ነው። ጋሽ ጌታቸው የመረጃ ቋት ብቻ አልነበረም። ያለውን ለመስጠት ፍጹም ዝግጁ የነበረ ለጋስ ሰውም እንጂ። የሥራ ባልደረቦቹም ቢሆኑ፣ “ጋሽ ጌች፣ ምንትስ የተባለው ቴያትር መቼ ነበር በመድረክ የቀረበው? ወይንም እገሌ አባ ስበር መቼ ነበር ተሹመው የመጡት?” ወዘተ. አይነት ጥያቄዎችን ያቀርቡለታል። እሱም በተለመደ ፍጥነቱ መልሱን ይሰጣል። ለዚህም አይደል “ተንቀሳቃሹ ቤተመዘክር” የሚባለው! የዚህ ጽሑፍ አቅራቢም ከአንጋፋው ከያኒ የካበተ ልምድና እውቀት ከተጠቀሙ ሰዎች አንዱ ነው። በኅዳር ወር 2010 ዓ.ም ለታዛ መጽሔት አንባቢያን “አጼ ኃ/ ሥላሴና ቴያትር” በሚል ርዕስ ያቀረበው ጽሑፍም ከእሱው አንደበት የተገኘ ነው። ከሁለት ሳምንት በፊትም ስለአንድ ድንቅ ባለሙያ ሥራና ሕይወት ጠይቀነው ምስክርነቱን አግኝተናል። በዚህ ጽሑፍ የምናነሳሳቸው ነገሮችም በአብዛኛው በመሰል አጋጣሚዎች ካደረግናቸው ውይይቶችና አንጋፋው ከያኒ ደበበ እሸቱ በቀብሩ ሥነሥርዓት ላይ ካነበበው የሕይወት ታሪኩ የተወሰዱ ናቸው።

 ጋሽ ጌታቸው በቀድሞው የሸዋ ክፍለ ሃገር፣ በመናገሻ አውራጃ፣ በአዲስ ዓለም ከተማ ነው የተወለደው። ዘመኑም ሚያዝያ 1928 ነበር። እስከ ስድስተኛ ክፍል የተማረውም እዚያው ነው። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ አዲስ አበባ ውስጥ ይኖሩ ወደነበሩት አጎቱ መጥቶ በኮከበ ጽባህ መከታተል ጀመረ። ሆኖም በአንድ አጋጣሚ የማዘጋጃ ቤት ሙዚቀኞች በጊዮርጊስ አደባባይ የደንብ ልብሳቸውን ለብሰው ህብረ ዝማሬያቸውን ሲያቀርቡ ተመልክቶ ቀልቡ መሳቡን፣ መጋቢት 20 ቀን 1944 ዓ.ም የሙዚቃና ቴያትር ፈተና ወስዶ ጥሩ ውጤት በማምጣቱ ለመቀጠር መቻሉን፣ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ (ዛሬ ብሔራዊ) ቴያትር በ1948 ዓ.ም ሲቋቋም  ኦስትሪያዊው ዲሬክተር ፍራንሲስ ዘልቤከር በሙዚቃና ቴያትር መስክ ካሰለጠናቸውና አዲሱን ቴያትር ቤት ከተቀላቀሉት ባለሙያዎች አንዱ መሆኑን የሕይወት ታሪኩ ያስረዳል።

 አበው ከያኒ ጌታቸው “ዳዊትና ኦርዮን” በተባለው የቢትወደድ መኮንን እንዳልካቸው ድርሰት፣ በዘልቤከር አዘጋጅነት መድረኩን ከረገጠ በኋላ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴያትር ርቆ አያውቅም። አስከሬኑ ራሱም ወደዘላለም ማረፊያው የሄደው ከብሔራዊ ቴያትር መድረክ ተነስቶና በጭብጨባ ታጅቦ ነው። ከተወነባቸው ቴያትሮች መካከል ሥነ ሥቅለት፣ አኒባል፣ ቴዎድሮስ፣ ጎንደሬው ገ/ማርያም፣ የፌዝ ዶክተር፣ ዋናው ተቆጣጣሪ፣ ሻጥር በየፈርጁ፣ ርጉም ሐዋሪያ፣ የከርሞ ሰው፣ ድንገተኛ ጥሪ፣ ዕድሜ ልክ እሥራት፣ የፍቅር ጮራ የተሰኙትን ለአብነት ያህል መጥቀስ ይቻላል። ከጻፋቸው ተውኔቶች ደግሞ በድሉ ዘለቀ፣ ከተፎና መንጥር፣ ያስቀመጡት ወንደላጤ፣ ደህና ሁኚ አራዳና ሌሎችም ይገኙበታል። ጋሽ ጌታቸው 15 ያህል ቴያትሮችን ያዘጋጀ ሲሆን ዝርዝሩ የከተማው ባላገር፣ ደህና ሁኚ አራዳ፣ ለሰው ሞት አነሰው፣ ምኞቴ፣ ፍቅር መጨረሻ እና አሉላ አባ ነጋ የተሰኙትን ይጨምራል። ጋሽ ጌታቸው በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ተመድቦም አገልግሏል፡፡ የቴያትር ክፍልን፣ የሕዝብ ግንኙነት አገልግሎትንና የፕሮግራምና ፕሮዳክሽን ክፍልን በኃላፊነት መርቷል፡፡

 አበው ከያኒ ጌታቸው ቀደም ብለን ከጠቀስነው የሎሚ ተራ ተራ ጦስ በተጨማሪ ሁለቴ ታስሯል። የመጀመሪያው የኪነጥበብ ባለሙያዎች የመብት ጥያቄ ባነሱበት ወቅት ነበር። የሰልፉን መነሻና ዓላማውን እንዲህ ያስታውሳል።

 ኪነትን እኮ ሊገድሉ ሆነ። አምባገነን ሆኑ! እኛ በማኅበር እንደራጅ ብለን አመለከትን። ደብዳቤም ከሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ አመጣን። አቶ በቀለ የሚባሉ ከማኅበራዊ ጉዳይ የመጡ ሹም ሠራተኛውን ሰብስበው አወያዩን። ስምንት ሰዎች ብቻ ናቸው ከእኛ ጋር ያልነበሩት። ከዚያ አስፈቅደን ለሰላማዊ ሰልፍ ወጣን። ጉዛችንንም ወደ ደርግ ጽ/ቤት አደረግን። አንድ መቶ እንሆናለን። ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤትን አልፈን ወደ ቱሪስት ሆቴል ስንደርስ ወታደሮቹ መጡና እያንጠለጠሉ ካሚዎናቸው ላይ መጫን ጀመሩ። አስናቀች ወርቁን ከነያዘችው ባንዴራ ሲወረውራት አይቻለሁ። ጌታቸው ኩማ የሚባል የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ቴያትርና ባህል አዳራሽ ባልደረባ ነበር። እሱንም ይዞ ሊወረውረው ሲል ዘለለና በሁለት እግሩ መታው ፖሊሱን። ፖሊሱ ወደቀ። ሌላ ፖሊስ መጣና ደረቱን በሳንጃ ወጋው። በጥይትም መቱት፣ ሞተ። ሌላ ዓለማየሁ ዘለቀ የሚባል የብሔራዊ ቴያትር ባልደረባ ነበር። እሱም በሰደፍ ተመቶ ቆስሎ ኖሮ ኖሮ ሞተ። ሌሎችም እንዲሁ የተጎዱ ነበሩ። እኛ ትምህርት ሚኒስቴር ውስጥ ገባንና አመለጥን። ከዚያ ወጋየሁ ንጋቱ ቤት አብረን አደርን። ነገር ግን በማግስቱ ፖሊስ እንደሚፈልገኝ ስሰማ ወደቤተመንግስት ሄጄ እንድትመጣ ተብዬ ነው ብዬ ስጠይቃቸው ስምህ ዝርዝሩ ውስጥ የለም አሉኝ። እዚያው አካባቢ ስዝናና ኃ/ማርያም ሃሰን የሚባል ዋና ሰው ይመጣና ሲነግሩት በሉ ሂዱና ፈልጋችሁ አምጡት ይላል። መጡና አካልበው ይዘውኝ ሄዱ። ቤተመንግስት አንድ ቀን አሳደሩንና በሚቀጥለው ቀን ወደ አራተኛ ክፍለጦር ወሰዱን። እኔና ወጋየሁ አንድ ላይ ነበር የታሰርነው። ለአራት ወር! እነደበበ እሸቱ፣ ታደሰ መስፍንና መርዕድ ቅጣው አንድ ላይ፣ ሌሎችም እንዲሁ ተደለደሉ። በእውነቱ እዚያ ምንም አላደረጉንም። ከዚያ ከአራት ወራት በኋላ ሻለቃ ካሳዬ አራጋው መጣና እኔና ወጋየሁን አየን። ከስልሳ ሰዎች ጋር ነበር የታሰርነው። ብዙ ትላልቅ ሰዎች፣ ጄኔራሎችም ነበሩበት። “በቅርቡ ትፈታላችሁ፣ አታስቡ” ምናምን ብሎን ሄደ። ከዚያ ተጠራንና ወጣን። መንግስት ይቅርታ ጠይቋችኋል። ጉዳዩ ተጣርቷል። ከዛሬ ጀምሮ ወደሥራ ገበታችሁ መመለስ ትችላላችሁ። የት ነው መመደብ የምትፈልጉት? እያሉ እየጠየቁን ተፈሪ ብዙአየሁም፣ ደበበ እሸቱም፣ ሌሎችም ምርጫቸውን ተናገሩ። ከዚያ ወደየቤታችን ሄድን።

 ሁለተኛው ደግሞ የሆነ የፖለቲካ ድርጅት ልሳን አንብበሃል በሚል ነበር። በወቅቱ ዜናው በቴሌቪዥንና በራዲዮም ተላልፎ ነበር። ስለሁለተኛው አጋጣሚ ሲናገር እንዲህ ብሎ ነበር።

አንድ ጋደኛዬ መጽሔት ከደጃዝማች አሰጋኸኝ ጋር አምጥቶ ሰጠኝ። እንግዲህ የኛዎቹ ካድሬዎች እጄ ላይ አይተውታል መሰለኝ። ከዚያ ጥር 3 ቀን 1976 ዓ.ም ነው፣ መጡና ወደማዕከላዊ ወሰዱኝ። ስሄድ የማውቃቸውን ሰዎች አገኘሁ። ኮሎኔል በላይ ነጋ (የአቦይ ስብሃት ነጋ ወንድም) የህግ ባለሙያ ነው፣ ዶ/ር መንገሻ ገ/ ሕይወት ኋላ በዱላ ብዛት እግራቸው ተቆርጦ የነበርና የተገደሉ፣ ባላምባራስ ተፈራ ወ/ማርያም ወንድማቸው በመከላከያ ሚኒስቴር ሹም የነበር፣ የሆቴል ዲአፍሪክ ባለቤት ወንድም ስማቸውን ረሳሁት፣ እና ሌሎችም ነበሩበት። በአጠቃላይ በኅቡዕ የተቋቋመ የፖለቲካ ድርጅት አባል ናችሁ ተብለን የታሰርነው 115 ሰዎች ነበርን። ለአራት ዓመታት የቆየበትን እሥርቤት የሥራ ቦታው አድርጎት ነበር። እሥረኞቹን እያሰለጠነ ቴያትር አሠርቷቸዋል፤ ጭንቀታቸውን በጥበብ አስረስቷቸዋል፤ ተስፋቸውን አለምልሞላቸዋል። እሱም ራሱ የእሥር ቤት ትዝታውን “ደንቆሮ በር” በሚል መጽሐፉ ተርኮታል። ገና በልጅነቱ ከንጉሡ ፊት ግጥም በማንበቡ የሦስት ሺልንግ ሽልማት በመቀበል የጀመረው ጋሽ ጌታቸው በቴያትር ባለሙያነቱም የገንዘብና የወርቅ ሽልማት ተቀብሏል። በ1994 ዓ.ም ደግሞ የኢትዮጵያ የሥነጥበባትና መገናኛ ብዙኃን የሽልማት ድርጅት በቴያትር ዘርፍ የሕይወት ዘመን ተሸላሚ ሆኖ የወርቅ ሜዳሊያ፣ ዲፕሎማና የሃያ ሺ ብር ሽልማት ከሃገሪቱ ፕሬዚዳንት እጅ ተቀብላል። ጋሽ ጌታቸው የሁለት ሴትና የአንድ ወንድ ልጅ አባት ነበር። በብሔራዊ ቴያትር በተዘጋጀለት የሽኝት ፕሮግራም የሥጋ ልጁን መዓዛ ጌታቸውን ጨምሮ የሙያ አጋሮቹና ልጆቹ አንጋፋ ከያንያን መርዓዊ ስጦት፣ ደበበ እሸቱ፣ ፍቅርተ ደሳለኝ፣ አልጋነሽ ታሪኩ፣ የወይንሸት በላቸው፣ ጌትነት እንየው፣ ቴዎድሮስ ተስፋዬ፣ ተስፋዬ ገብረሃና፣ ሳሙኤል ተስፋዬና ደበሽ ተመስገን አክብሮታቸውንና አድናቆታቸውን ገልጸውለታል። በተለይ በመርሃ ግብሩ ማሳረጊያ የቀረበችው የደበሽ ግጥም ስሜት የምትነካ ነበረችና ለውድ አንባቢያን ልናጋራችሁ ወደድን።

 ጌታቸው ደባልቄ፣ ህያው ቤተመዝገብ

 ለጠየቀው ሁሉ፣ ተገልጦ የሚነበብ

እሱም ይብቃኝ አለ፣ አብሮ ሊሰበሰብ

 ከቀደሙት አበው፣ ከጥበብ ቤተሰብ

መጽሐፉም ተዘጋ፣ ድርሳን የሚያፈሰው

 ዛሬም በወር ተራ፣ ተለየን አንድ ሰው

 ምን እንበል ጎበዝ፣ አዬ ሰው አዬ ሰው!

 በመድረክ ላይ ገዝፎ፣ በሳጥን የሚያንሰው

 ይሁን እንጂ ባሻው፣

 ይሂድ እንጂ እንዳሻው፣

 ወትሮም ይታወቃል፣ የሰው መጨረሻው

 እንዲህ እንደሚሆን፣ ከጥንት ከመነሻው!

እሱማ ጠቢብ ነው፣ አያሻውም እንባ

 በክብሩ ቅበሩት፣ በምሱ ቅበሩት፣

 ሸኙት በጭብጨባ!

እናም በአዳራሹ የተገኘው የጥበብ ቤተሰብ አንጋፋውን ከያኒ በጭብጨባ ሸኘው፡፡ ቀብሩም የካቲት 24 ቀን 2011 ዓ.ም በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተፈጸመ።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top