ቀዳሚ ቃል

የአድዋ ድል የአንድነታችን እንጂ፤ የልዩነታችን ምክንያት ሊሆን አይችልም!

ራይሞንድ ጆናስ “The Battle of Adwa” በሚለው የመጽሐፉ መግቢያ ላይ እንዲህ ብሎ ጽፏል፡፡ “የአድዋ ድል በተፈጥሮ ነጮች አሸናፊዎች፣ ጥቁሮች ደግሞ ተሸናፊዎች የሚለውን ዓለም አቀፋዊ እምነት በአፍጢሙ የደፋ ክስተት ነው፡፡ አፍሪካውያንን ብቻ ሳይሆን መላው የዓለም ጥቁር ህዝቦች ያኮራ ታሪካዊ ድል ነው”

ይኸ አለምን ከጫፍ እስከ ጫፍ ያንቀጠቀጠው ድል በኢትዮጵያውያን የጋራ ተጋድሎ የተገኘ ድል ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ለአፍሪካ ብቻ ሳይሆን ለመላው የዓለም ጥቁር ህዝቦች ያበረከቱት ወደር የለሽ ስጦታ ነው፡፡

 ለኢትዮጵያውያን ደግሞ ከዚህ የበለጠ ትርም አለው፡፡ ከአድዋ ጦርነት ቀደም ብሎ የውጪ ወራሪዎች ኢትዮጵያን ለመውረርና ለማንበርከክ ብዙ ሙከራዎች አድርገው ከሽፎባቸዋል፡፡ ይኸንን ሽንፈት ለማካካስ ሲሉ ያለ የሌለውን ኃይላቸውን አሰባስበው ኢትዮጵያን ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማንበርከክ ተደራጅተው የመጡበት የአድዋ ጦርነት በተባበረው የኢትዮጵያውያን ክንድ ዳግም ተንኮታኩቷል፡፡

 የአድዋ ድል ኢትዮጵያ በመቶ ሃያ ዓመት ታሪኳ ካስመዘገበቻቸው ድሎች ትልቁ እና ዋነኛው በመሆኑ ኢትዮጵያውያንን የሚያኮራ፣ የሚያፋቅር እና የሚያስተሳስር እንጂ የሚያለያይ፣ የሚያናቁር ምክንያት ሊሆን አይችልም፡፡

 የታሪክ ምሁራን በአድዋ የብሔር ልዩነትን ከሚፈጥሩባቸው አስተምሮዎች ወጥተው፣ ፖለቲከኞች ታሪኩን የፖለቲካ መጠቀሚያነት ለማዋል ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ ታቅበው፤ አክቲቪስቶችም በአድዋ ሰበብ ልዩነትና ግጭቶችን ከሚፈጥሩበት እንቅስቃሴያቸው ወጥተው ድሉ አንድ ያደረገንን ታሪክ ሊያነሱ፣ ሊያድሱ ይገባል፡፡ ነገ ለሚፈጠረው ትውልድ ኃላፊነትን መውሰድና ለሀገሪቱ መልካም ማሰብ ይበጃል፡፡ የአድዋ ድል የአንድነታችን እንጂ የልዩነታችን ምክንያት በፍፁም ሊሆን አይችልም፡፡ የዘንድሮውን በዓል ስናከብር ይህን አስተሳሰብ በማራመድ ይሁን፡፡ መልካም በዓል!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top