በላ ልበልሃ

ጋዜጠኛ ለመሆን ትምህርት ያስፈልጋልን

በዓለማችን እንደ ሚዲያ ተለዋዋጭነትን የሚያሳይና በቴክኖሎጂ ተደግፎ ፈጣን ለውጥ እያመጣ ያለ ዘርፍ አለ ለማለት ያዳግታል። የሰው ልጅ ከብዙሃን መገናኛ ጋር ያለው ቁርኝት ከምንጊዜውም በበለጠ ጠብቆ በሚገኝበት ዘመን ላይ እንደመገኘታችን ስለሚዲያ አሰራርና ነባራዊ ሁኔታ በተደጋጋሚ ቢወራ ክፋት ያለው አይሆንም። ሁላችንም እንደምናውቀው በሃገራችን የብዙሃን መገናኛ ፈቃድ አውጥቶ ለመስራት የተቀመጠውን የመመዝገቢያ ወጪ የከፈለ ሁሉ የሚሰማራበት የስራ ዘርፍ ሆኖ ይገኛል። ተሰጥኦ አለኝ ብሎ የሚያስብ ማንኛውም ሰው በዚህ ስራ ላይ ለመሰማራት በመቻሉ ምክንያትም አንዳንዶች ጋዜጠኛ ለመሆን የተለየ ትምህርት አያስፈልግም ብለው በአደባባይ እንዲሟገቱ የልብ ልብ እየሰጣቸው ነው።

 ለዚህም መከራከሪያ ይሆናቸው ዘንድ እነ እከሌ የትኛውን የጋዜጠኛነት ትምህርት ተምረው ነው እንደዚያ ጥሩ ጋዜጠኞች የነበሩት ብለው ያፋጥጧችኋል። ዋናው ጉዳይ እነዚህ ጥሩ ጋዜጠኛ ተብለው የተሞገሱት ቀደምት ጋዜጠኞችስ ምን ያህል በሳይንሳዊ መንገድ የተመዘነ ጋዜጠኛነትን ተግብረው ነበር የሚለው ነው። በጊዜያቸው ላለው ማህበረሰብ አቅማቸው በፈቀደ መጠን ያበረከቱት አስተዋጽኦ የማይካድ ቢሆንም ስራቸው ዘርፉ ሊከተል በሚገባው መርሆዎችና አተገባበሮች ሲመዘን ዛሬ ጋዜጠኝነት ብለን የምንጠራውን አሰራር የተከተሉ ነበሩ ለማለት ይቸግራል። በተለይም አሁን ባለንበት ዘመን በብዙሃን መገናኛ ዙሪያ ያለውን ውጥንቅጥ እያሰብን የምንከራከር ከሆነ ማንም ያለዘርፉ ትምህርት ጋዜጠኛ መሆን ይችላል የሚለው አካሄድ አጠያያቂና ብዙ ዋጋ እያስከፈለን ያለ ለመሆኑ ምስክር የሚያሻው ጉዳይ አይደለም።

ጋዜጠኛነት ሞያ ነው። ሙያ ነው ብለን ከተቀበልን ደግሞ የራሱ የሆኑ የእውቀት መሠረታዊያን አሉት ማለት ነው። ለምሳሌ አንድ ዶክተር ወይንም ጠበቃ የሙያውን መሰረታዊ እውቀቶች ሳይጨብጥ መስራት ይሳነዋል። የህክምና ሙያ የሌለው ሰው ቀዶ ጥገና ሊፈፅም ቢልና ቢፈቀድለት የሚያጋጥመውን ነገር መገመት አያዳግተንም።

አንድ ግለሰብም እንዲሁ ተነስቶ የጥብቅና ሙያ ያለእውቀቱ ቢፈቀድለት በወንጀል የተከሰሰን ንጹህ ሰው ነፃ ከማውጣት ይልቅ መጨረሻውን ከርቸሌ እንደሚያደርገው ጥርጥር የለውም። ይህ ከሆነ እንግዲህ ማንም ተነስቶ ዶክተር ወይንም ጠበቃ መሆን እንደማይችለው ሁሉ በጋዜጠኛነት ዘርፍም እነዚህን መሰረታዊ የሆኑ እውቀቶች ያልያዘ ሰው ጋዜጠኛ ነኝ ሲልና ገብቶ ሲፈተፍት ዶክተሩ ከሚያደርሰው በላይ አደጋ እንዳለው ግልፅ መሆን አለበት።

 እንዲህ ሲባል ይህ ሃሳብን በነጻነት መግለጽን እንደ መጋፋት ነው ብለው በተቃውሞ ሽንጣቸውን ገትረው የሚከራከሩ ብዙዎች ናቸው። በእርግጥ ጉዳዩ ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት ላይ እንደ ገደብ ሆኖ ምን ያህል ይታያል የሚለው ብዙ ትንተና ይፈልጋል። ነገር ግን ሃሳብን በነፃነት መግለጽ የሚደነገገው ሁሉም ዜጋ የሚሰማውን ሃሳብ ያለክልከላ መግለጽ እንዲችል ነው። ይህ ማለት ግን ሁሉም ሰው ብዙሃን መገናኛን በማቋቋም ሃሳቡን ይገልፃል ማለት አይደለም። ለግለሰብ የተሰጠን መብት ከብዙሃን መገናኛ ነፃነት መብት ጋር አለማጣረሱ ክርክሩን የሚያቀለው ይመስለኛል። አንድ ሰው በግሉ ሃሳቡን ሲገልፅና ያንን ሃሳቡን በራሱ ብዙሃን መገናኛ ተጠቅሞ ሲያሰራጭ ብዙ ልዩነት አለ። ለዚህም ነው በሀገራት ህገመንግስቶች ላይ የግለሰቦች ሃሳብን በነፃ የመግለጽ መብትና የብዙሃን መገናኛ ነጻነት በአንቀጽ ተለያይተው የተቀመጡት።

ስለዚህ በብዙሃን መገናኛ ነጻነትና በግለሰቦች ሃሳብን ያለ ገደብ የመግለጽ ነጻነት መካከል ሰፊ ልዩነት አለ። ብዙሃን መገናኛ ነጻነት ያስፈልገዋል የሚባለው ሙያውን በአግባቡ ተጠቅመው ህብረተሰቡን በእውቀት ላይ በተመሰረተ መልኩ እንዲያገለግሉ ነው። ይህ ያስፈለገበት ምክንያት ብዙሃን መገናኛ በህብረተሰቡ ዘንድ ካላቸው ቦታና በተለይም ቴክኖሎጂው ካጎናጸፋቸው ተደራሽነት በመነሳት ነው።

 እንግዲህ ግለሰቦች ሃሳባቸውን የሚገልጹባቸው ብዙ መንገዶች አሉ። በነዚህ ጊዜያት ሁሉ ነጻነታቸው መጠበቅ አለበት። ብዙሃን መገናኛ ዜጎች ሃሳባቸውን በነጻነት ከሚገልጹበት መንገድ አንዱ ቢሆንም ሁሉም ዜጎች ብዙሃን መገናኛን በባለቤትነት ይዘው ወይንም ጋዜጠኛ ሆነው ይጠቀማሉ ማለት አይደለም። ብዙሃን መገናኛን በማቋቋም የሚመሩ ባለሙያዎች (ጋዜጠኞች፣ አርታኢዎች፣ ወዘተ.) ታዲያ ከተራው ዜጋ ወጣ ያሉ ነጻነቶች የሚከበሩላቸው እና ለመረጃ ተደራሽ እንዲሆኑ የሚደረገው (ምንም እንኳ በተወሰነ ደረጃ ቢያደርጉትም) የግል ሃሳባቸውን በነጻነት ለመግለጽ እንዳልሆነ መገንዘብ ጥሩ ይሆናል።

 ለብዙሃን መገናኛ ባለሙያዎች እነዚህ ነጻነቶች የሚከበሩላቸው የሃሳብ መንሸራሸሪያ መድረክ በመሆን ህብረተሰቡን እንዲያገለግሉ ተብሎ ነው። ስለዚህ ብዙሃን መገናኛን የሚያቋቁም ሰው ማሰብ ያለበት የግል ሃሳቡን የመግለጽ ነጻነቱን እየተገበረ እንዳለ ሳይሆን ህብረተሰብ ለማገልገል የሚያስፈልጉት ነጻነቶች እንደተከበሩለት አድርጎ መሆን ይኖርበታል። ያኔ በግለሰብ ሃሳብን በነፃነት መግለጽና በብዙሃን መገናኛ ነጻነት መካከል ያለው ሰፊ ክፍት ቦታ ግልጽ ብሎ ይወጣል። ሆኖም ግን የንግግሩ አቅጣጫ መሆን ያለበት ሙያውን እውቀት ያለው ሰው ይስራው ቢባል ክፋቱ የቱ ላይ ነው በሚል መልኩ ቢሆን ተመራጭ ይመስላል።

 በቀደሙት ጊዜያት የጋዜጠኝነት ት/ቤቶች በሀገሪቱ ባለመስፋፋታቸው ምክንያት ተዋንያን፣ ገጣሚያን፣ የቋንቋ ሰዎች እና ሌሎች ቅርበቱ ያላቸው ሙያተኞች የጋዜጠኝነትን ስራ በመሰላቸው መንገድ እየመሩት ቆይተዋል። አሁን ግን ይህን አካሄድ መቀየር እንደሚያስፈልግ የሚጠቁሙ አስገዳጅ ሁኔታዎች ይታያሉ። የመጀመሪያው የብዙሃን መገናኛ ስራ በጣም ውስብስብና ያለሙያ እውቀት ሊተገበር የማይቻልበት ዘመን ላይ መሆናችን ነው። ሁለተኛው ደግሞ እንደቀደመው ዘመን ሳይሆን በሙያው የሰለጠኑ ባለሙያዎች በበቂ ሁኔታ ያሉበት ጊዜ ስለሆነ ያላዋቂዎች መፈንጫ ሲሆን በዝምታ መታየት ስለሌለበትም ነው።

ሌላው ደግሞ ሁሉም ተነስቶ ጋዜጠኛ ነኝ በማለቱ ምክንያት በህዝባችን ዘንድ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየደረሰ ያለው ችግር አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ከግንዛቤ ማስገባት ማስፈለጉ ነው። ሃሰተኛና ለአንድ ክፍል የወገኑ አስተሳሰቦችን በማራመድ ህዝብን ከህዝብ የሚያላትሙ መረጃዎችን ሃላፊነት በጎደለው መልኩ በማስተላለፍ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለዜጎች ህልፈት ምክንያት የሆኑ የማህበራዊ ሚዲያ አክቲቪስቶች እንዳሉ ሁሉ፤ ከዚህ ባላነሰ ሁኔታ በብዙሃን መገናኛው ዘርፍም ችግር እየፈጠሩ ያሉ እንዳሉ ግልፅ ነው። ከነዚህ መካከል በጋዜጠኝነት ትምህርት ውስጥ ያለፉም መኖራቸው የማይካድ ቢሆንም። በትምህርቱ ውስጥ አልፈው ተመሳሳይ ተግባር የሚፈፅሙትን ግን ባለማወቅ ነው ለማለት ባይደፈርም ትምህርት ሊለውጠው ያልቻለው ሰብእናቸው ግን ችግር እንዳለው መገመት ይቻላል። አሊያም የተሰጣቸው ትምህርት ጥራቱ ፍተሻ የሚያሻው ሆኖ ይሆናል።

“ብዙሃን መገናኛ ለህዝቡ በቂና ከአድልኦ ነጻ በሆነ መልኩ ሃሳባቸውን የሚገልጹበት መድረክ እንዲፈጠር መስራት ይጠበቅባቸዋል። እነዚህ ሃላፊነቶች በጋዜጠኛው ጫንቃ ላይ መኖራቸውን ለማወቅ የተቀናጀ የሙያ ትምህርት ያስፈልጋል”

በብዙሃን መገናኛ ትምህርት ቤቶች የሚሰጡ አስፈላጊ ትምህርቶች አንድን ጋዜጠኛ ምሉዕ የሚያደርጉት የሚዲያ ይዘቶች አሰባሰብና አዘገጃጀት ብቻ አይደለም። ከሁሉ አስቀድመው ትምህርቱን የሚማሩ ሰዎች ማወቅ ያለባቸው ብዙሃን መገናኛ በህብረተሰቡ ውስጥ ያላቸውን ቦታና በህብረተሰቡ ላይ ሊያደርሱ የሚችሉትን አሉታዊም ሆነ አወንታዊ ተጽእኖዎችና እንዲሁም የተጽዕኖዎቹን ደረጃ ነው። በተቋማቱ የሚሰጡቱ በርከት ያሉ የተግባቦትና የብዙሃን መገናኛ ቲዎሪዎች ስለነዚህ ተጽዕኖዎች ተማሪውን በስፋትና በጥልቀት ያስገነዝባሉ ተብሎ ይታመናል። በተጨማሪም ለብዙሃን መገናኛን ገዢ የሆኑ የስነምግባርና የህግ ማዕቀፎችም ከነጥቅማቸው በኮርሶች ደረጃ ይሰጣሉ። ሙያተኛው የትኞቹን የስነምግባር መርሆዎች ማክበር እንዳለበትና የትኞቹን የሀገሪቱን ህጎች አውቆ በተገዢነት መስራት እንዳለበት በተገቢው መንገድ ተጨባጭ እውቀት ያገኛል ማለት ነው። ከዚህም ባለፈ የተደራስያንን ባህርያት፤ የይዘት ምርጫ እና ሌሎች ይህን የተመለከቱ አያሌ እውቀቶችም በነዚሁ የመማሪያ ተቋማት ይሰጣሉ። ስለዚህ ነው እንግዲህ በነዚህ መሰረታዊ እውቀቶች ያልታገዘ የጋዜጠኛነት ስራ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል የሚባለው።

 በአለም አቀፍ የሚዲያ አሰራር የጋዜጠኝነት ሙያ የሚከተላቸው መሰረታዊ መርሆዎች አሉ። ጋዜጠኛው ተአማኒነቱ ለሚያገለግለው ተደራሽ ወይም ለሚያገለግለው ህዝብ እንዲሆን፤ ለእውነት ታዛዥ እንዲሆን፤ ራሱን ችሎና ከሌሎች ጫና ነጻ ሆኖ ገዢዎችን የሚቆጣጠር አካል እንዲሆን እነዚህ መርሆዎች ይመክራሉ። ከዚህም ውጪ ብዙሃን መገናኛ ለህዝቡ በቂና ከአድልኦ ነጻ በሆነ መልኩ ሃሳባቸውን የሚገልጹበት መድረክ እንዲፈጠር መስራት ይጠበቅባቸዋል። እነዚህ ሃላፊነቶች በጋዜጠኛው ጫንቃ ላይ መኖራቸውን ለማወቅ የተቀናጀ የሙያ ትምህርት ያስፈልጋል።

 እዚህ ላይ ጋዜጠኛ ማነው የሚለውንና ይህን መመለስ ባለመቻሉ ከሚታየው ብዥታ ክርክሩን መጀመር ይቻላል። ምክንያቱም ይህ ከሁሉ ቀድሞ መጥራት ያለበት ጉዳይ ነውና። አንድ የሚዲያ ሰዓት ተከራይቶ የሙዚቃ ምርጫ ፕሮግራም የሚያስተላልፍ፣ ወይም የሳይበር ቴክኖሎጂ ላይ ያለውን እውቀቱን የሚያካፍል ሰው ወይንም የዳንስ ውድድር አዘጋጅቶ የሚያስተላልፍ ሰው ራሱን ጋዜጠኛ ነኝ ቢል (መዝናኛም ጋዜጠኝነት ነው በሚል እሳቤ ቢያደርገውም) በዜናና ዜና መሰል ዘርፎች ላይ ተመስርቶ መረጃን ለህዝብ ከሚያስተላለፈው ባለሙያ እኩል ስያሜው ይኖረው እንደሆነ መከራከር ይቻላል። የዚህ ጽሑፍ ዓላማም ዜናና ዜና ነክ ይዘቶችን በሚያዘጋጁና በሚያስተላልፉ ጋዜጠኞች ላይ ያተኮረ እንደሆነ መግለጽ እወዳለሁ።

አንዳንዴ ሙያው በባለሙያ ጋዜጠኛ መሰራቱ ብቻ በቂ ነው ማለትም አስቸጋሪ ይሆናል። ጋዜጠኛው ምንም ያህል የሙያ እውቀቱ ቢኖረው ሚዲያውን የሚመሩ አመራሮች ጋዜጠኛው በትምህርት ተቋማት ያገኘውን የሙያና የፍልስፍና ትምህርት ተከትሎ በነጻነት ስራውን እንዲተገብር የማይረዱት ከሆነ እና ስለሙያው በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በጋዜጠኛው እንቅስቃሴ ላይ እንቅፋት የሚፈጥሩ ከሆነ አሁንም ችግር መፈጠሩ አይቀርም። ይህ በተለይ በብዙ የመንግስት የመገኛኛ ብዙሃን ዘንድ የሚስተዋል ነገር ነው። እየተቀየረ ያለ ቢሆንም የመንግስትና የፓርቲ ሹማምንት የሆኑት አመራሮች ሚዲያውን በሳይንሳዊ መንገድ መምራት አለመቻላቸው ጋዜጠኛውን ሲያስወቅስ ቆይቷል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚታየው የጋዜጠኞች አወንታዊ እንቅስቃሴም በተወሰነ ደረጃ ከነዚህ አመራሮች ጫና በመላቀቁ ይመስላል። ስለዚህ ጋዜጠኞችን የሚመሩ ሰዎች እውቀቱ ቢኖራቸው የተሻለ ጋዜጠኝነት ልናይ እንችላለን ባይ ነኝ። በግሉ ዘርፍ ያሉትም ቢሆኑ በባለቤትነት የያዙትን ሚዲያ ተቋም ሙያውን የሚያውቅ ሰው ቀጥረው ቢያሰሩ ይበልጥ ውጤታማ ይሆናሉ። ሊሰመርበት የሚገባው ዋናው ነገር ችግሩ ሚዲያ ተቋም አቋቁሞ መስራት ላይ ሳይሆን በጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ ዘው ብሎ መግባቱ ላይ ነው።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top