አድባራተ ጥበብ

የዶክተር እጓለ እሳቤዎች

ባለፈው ጽሑፍ የዶክተር እጓለን የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ ትንታኔ ጀምረን ነበር። የመጀመሪያዎቹ ሁለት ምዕራፎች የያዙትን ቁም ነገር አይተናል። የሐተታችን መጨረሻ ያደረግነውም የእውቀትና የሰናይት ተጻምሮ ወይም ውህደት የሚፈጥረውን የተስተካከለ ሰውነት ማሳየት ነው። ታላቁን የጀርመን ፈላስፋ ኢማኑኤል ካንትን የሥነ ምግባር እሳቤ በሁለተኛው መጽሐፍ በሰፊው የምናየው ቢሆንም እዚህኛው መጽሐፉ ሁለተኛው ምዕራፍ መዝጊያ ላይ “ያለ አንዳች ሕፀፅ ደግ ወይም ሠናይ ተብሎ ሊጠራ የሚችል ነገር አለ ተብሎ አይታሰብም ፤ ከአንድ ደግ ፍላጎት በስተቀር።” የሚለውን ሙግት ይጠቅሳል። ይህንም አንዳች ቁሳዊም ሆነ መንፈሳዊ ኃይል ሊገዛው አይችልም። ለሁሉም ሥነ ምግባራዊ በጎነት መሠረቱ ይኸው ደግ ፍላጎት (”Good Will”) ነው። ከእውቀት ጋር ምግባር ሲጻመር፣ ሁለቱ ሲተባበሩ ሰውን ወደ ከፍተኛ ማዕረግ ያደርሱታል። ለዚህም ነው የትምህርት ተቋሙ በር ሁለቱን ዓምዶች የግራውን አእምሮ፣ የቀኙን ሠናይት ብለነዋል የሚለን ሊቁ። (ገጽ፣ ፳፯/27) ለዛሬም ዳሰሳችንን ቀጥለን የመጽሐፉን ቀጣይ ምዕራፎች እንመልከት። የተመረጡት ርእሶች ሥልጣኔና የመንፈስ ትንሳኤ የሚሉት ናቸው። ለመሆኑ ሥልጣኔ ምንድን ነው? የሥልጣኔ ዘይቤስ ምንድን ነው? ሥልጣኔ ከመንፈስ ትንሣኤ ጋር ያለው ቁርኝት ምንድን ነው? የመንፈስ ትንሣኤ የሚባለውስ እንደምን ያለ ነው? የሚሉት ጥያቄዎች በዋናነት የቀጣዮቹ ምዕራፎች ዓምድና ካስማ ተደርገዋል። እነሆ ትንታኔው።

3. የሥልጣኔ ዘይቤ እና የመንፈስ

ትንሣኤ

በሦስተኛው ምዕራፍ ሊቁ የተከተለው አካሄድ የጥልቅ ትንታኔ ዘዴን በተቀራራቢ ትርጓሜው (Conceptual Analysis) መንገድን ነው። ሥልጣኔ የሚለውን ቃል ለማብራራት ከአገራችንም ከአውሮፓም ታሪክ እያጣቀሰ የቃሉን ታሪካዊ ዳራ እየፈተሸ ተግባራዊ ይዘቱን እየመረመረ ይቀጥላል። ይህ አካሄድ የነገሮችን ትክክለኛ ባህርይ ለመረዳት መጀመሪያ ጽንሰ ሐሳቦቹ የያዙትን ቁም ነገር መረዳት እንደሚቀድም ትምህርት ይሰጣል። የዘመናችን የትምህርትና የቋንቋ፣ የፖለቲካ ሰዎች ይህንን የቃላት ብዥታ ከመፍታት ቢጀምሩ ምናልባትም ለመግባባትና ለመከራከር ያመች ነበር። በህገ መንግስታችን ሳይቀር ያሉ ቃላት ካለ መብራራታቸው የተነሳ በተለምዶ እንጠቀምባቸዋለን እንጂ እኛን በቅጡ የሚገልጹ አይደሉም የሚሉ ትችቶች ሲሰነዘሩ ይስተዋላል። ለምሳሌ ብሔር፣ ብሔረሰብና ህዝብ የሚሉ ቃላት የዚሁ ትችት ሰለባዎች ናቸው። የሊቁ አካሔድ ግን ከዚህ ይለያል። ሌላው ደግሞ እድገትን የምንተረጉምበት መንገድ ነው። ከቁሳዊ ብልጽግና ጋር ብቻ በማያያዝ የሚታየው ነገር ላይ በማተኮር ምን ያክል እንዳደግን ሊያስረዱን የሚሞክሩ ጥቂት አይደሉም። በርግጥም ሊቁ ሥልጣኔን የተነተነበት መንገድ የዘመናችንን እድገት እንድናይበትም እግረ መንገዱን መነጽር ይሆነናል ብዬ አምናለሁ። ለዚህም ነው መጀመሪያ የቃሉን ትርጓሜ፣ የጽንሰ ሐሳቡን ይዘት መተንተንን የመረጠው። የተከተለውም አካሔድ “ቃል ይገድላል፣ ትርጓሜ ያድናል” የሚለውን የአበው መንገድ ነው።

ሐሳቦች በህሊናችን ውስጥ የተሰናሰሉ እና ያንዱ ሐሳብ ድር ሲመዘዝ የሌላውን ማግ እየጎተተ ያስተሳሰራቸውን ፈትለ ነገር ለመፈተሽ ወደፊትም ወደ ኋላም መጓዝ ያስፈልጋል የሚለው ሊቁ የትምህርትን ዘይቤ ከመመልከታችን በፊት የሥልጣኔን ነገር መፈተሽ የግድ ይለናል ብሎ ቅድሚያውን ለሥልጣኔን ዘይቤ ሐተታ ይሰጣል። ይህንንም ያደረግነው “የትምህርትን ዘይቤ ከሥልጣኔ ዘይቤ ለማስገኘት ለማስረጽ ስለምንፈልግ ነው።” ይለናል። (ገጽ፣ 29/፳፱) ሥልጣኔ ምንድን ነው? ሥልጣኔ የሚለውን ቃል ለአውሮፓውያን ልናውሳቸው የሚገባ እንደሆነ በልበ ሙሉነት ይሞግታል። ምክንያቱም ምሉዕና የተዋጣለት ቃል ስለሆነ ነው። እንዴት?

የአውሮፓውያኑ ስልጣኔ የሚለው ቃል ካልቹራ ከሚለው የላቲን ቃል የመጣ ነው። አመጣጡም ከግብርና ሥራ ጋር የተያያዘ ነው። ይህንንም ከትምህርት ጋር ያያይዙታል። ቺቸሮ የሚባለው ሮማዊ ተናጋሪ “የገበሬውን ሥራ ምሳሌ በማድረግ፤ ትምህርት የሚባለውን የግሪክ ቃል Cultura animi ብሎ ሠይሞታል። የነፍስ የመንፈስ ወይም የሕሊና እርሻ ማለት ነው።” ይህም ሕሊናን ከለምለም፣ ከለዘበ መሬት ጋር በማመሳሰል የሥነ ጥበብ፣ የበጎ እሳቤ፣ ሩቁንና የቅርቡን ዓለማት በመመርመር ሰውን ከድንቁርና፣ ከባርነት ነጻ የሚያወጣውን አስተሳሰብ ያስገኛልና ከግብርና ሥራ ጋር ተመሳስሏል። ይህ የቺቸሮ አስተሳሰብ በሌሎቹም የአውሮፓ ቋንቋዎች ጥቅም ላይ ውሏል። (ገጽ 30-31/ ፴-፴፩) ሌላኛው ከሥልጣኔ ጋር የተገናኘው ቃል Civilization የሚለው ነው። ይህም ከከተማዊነት መስፋፋት ጋር የተገናኘ ነው። ይህም የከተማውን ኑሮ ከገጠሩ ኑሮ ጋር በማመዛዘን የተሻለ እንደሆነ የሚያሳይ ነው። የሁለቱ ቃላት ልዩነት ካልቸር የህሊና፣ ሲቪላይዜሽን ደግሞ የሥጋ ብልጽግናዎችን፣ ቁሳዊና መንፈሳዊ እድገቶችን የሚያሳዩ እንደሆኑ ያሳያል። ከፍተኛውን ቦታ ለህሊና ሥልጣኔ ይሰጡታል።

 የአማርኛው ትርጓሜስ ምን ይሆን? ዲልማንን ጠቅሶ ሰለጠ ከሚለው ግሥ የተገኘ እንደሆነና ሥልጣን ከሚለው ጋር የተያያዘ ነው ይለናል። ሥልጣን ማለት ደግሞ “ገዥነት፣ ማስገበር“ የሚል ዳራ አለው። ይህንን የቃሉን አመጣጥ ካሳየን በኋላ ከሰው ልጅ ታሪክና ነባራዊ ሁኔታ ጋር እንዴት እንደሚገናኝ ሲያስረዳ በሰው ልጅ ሁለት ጥንተ ነገሮች ላይ አጽንኦት ይሰጣል። “አንደኛው የሰው ልጅ መቅድማዊ ሁኔታ የባርነት ነው። ሁለተኛው ከዚህ ከባርነት ሁኔታው እንዲወጣ በገዛ ራሱ ውስጥ የሚገኘው የነጻነት ብርቱ ተምኔት ያስገድደዋል።” (ገጽ፣ 32 ፴፪) እነዚህን የሰው ልጅ መቅድማዊ ሁኔታዎች በቀጣዮቹ ገጾች ያብራራቸዋል። መቅድማዊ ባርነት ያለውም የሰው ልጅ በድንቁርና፣ በጨለማ ሕይወት ከእንስሳቱና ከአራዊቱ ጋር ሲታገል፣ በተፈጥሮ ክስተቶች ብርድና ሙቀት፣ ዝናብና ቸነፈር ሲንገላታ በርሃብ ሲሰቃይ ራሱን ነጻ ለማውጣት ሳይችል በተፈጥሮ ቁጥጥር ስር የነበረባቸው ዘመናት ናቸው። ስለዚህ በውስጣዊው የድንቁርና፣ ያለማወቅ ባርነት፤ በውጫዊ ደግሞ በተፈጥሮ ጉዳዮች ተግዳሮቶች ሲሰቃይ የኖረው የሰው ልጅ የባርነት ሕይወትን እንደኖረ ያሳያል። የገዛ ራሱ ስንፍናና በዙሪያው የተፈጥሮ ነገሮች መጫወቻ ኳስ ሆኖ የሥቃይ ኑሮን ይመራ ነበር። አሁንም በዚያ ሁኔታ የሚገኙ በርካቶች ናቸው።

 ታዲያ ከዚህ ባርነት እንዴት ነጻ መውጣት ቻለ? ወይም እንዴት መውጣት ይቻላል? ይህንን ጥያቄ መመለስ የሥልጣኔን ትርጓሜ ለመረዳት የተወሰነ ርቀት ይወስደናል። ሊቁም ከአውሮፓ ታሪክ አንድ ተረት ይዋስና ጉዳዩን እንዲህ ያብራራልናል። ይኸውም የፕሮሚሴቭስ ተረት ነው። (ገጽ 34-35/፴፬- ፴፭) የፕሮሚሴቭስ ግማሽ አምላክ ግማሽ ሰው የሆነ ነገር ነው። ከመላእክት ጋር ስለሰው ልጅ የሚመከረውን ይሰማ ነበር። መላእክትም የሰውን ልጅ ልዕልና ስለሚፈሩ ከመከራ ከጥንተ ባርነቱ የሚወጣበትን የእውቀት ብርሃን ጋርደውበት፣ አርቀው ደብቀውበት ነበር። ፕሮሚሴቭስ ግን ስለወገኖቹ ደህንነት በመቆርቆር የተደበቀውን ብርሃን ከመላእክት ሰርቆ ወገኖቹ ለሆኑት ለሰው ልጆች ሰጣቸው። የሰው ልጅም ነጻ መውጣት ጀመረ፣ መላእክቱም ይህንን ባዩ ጊዜ ፕሮሚሴቭስ እንዳደረገው አውቀው ተቆጥተው በገደል ላይ ጠፍረው አስረው አሞራ ለዘላለም እንዲበተብተው ፈረዱበት። ይህ እንግዲህ በአውሮፓ መንፈስ የሚገኝ ተረት ነው። ፕሮሚሴቭስ የመምህራን ምሳሌ ነው። የሶቅራጥስ በመርዝ መገደል፣ የጆርዳኖ ቡርኖ የጧፍ ቀሚስ ተጎናጽፎ በእሳት መቃጠል የዚህ ምሳሌ ነው።

 ሌላም ማስረጃ ያቀርብልናል። የሰው ልጅ ከቅድመ ባርነት ለመውጣት እውቀትን እንደሚሻ ማሳያው የእብራውያንና የአዳም ታሪክ ነው። በገነት፣ በተድላና በደስታ ከመኖር ይልቅ እውቀት የምትገልጠውን ፍሬ በልቶ ከገነት መኮብለልን መረጠ። “በኦሪት ዘፍጥረት እንደምናነበው የመጀመሪያው ሰው በገነት ሲኖር ማናቸውም ነገር ተፈቅዶለት “ከእውቀት ዛፍ” ብቻ አንዲት ፍሬ እንዳይቀምስ ተከልክሎ ነበር። ግን በልቶ ተገኘ። ይህንን ሐሳብ በነጻ ሕሊና ለመረዳት ብንፈልግ ሰው በስጦታ ወይም በችሮታ በሚገኘው ድሎት የማይደሰት መሆኑንና ከገነት ለመውጣት የደፈረው ከእውቀት በሚያገኘው ጉልበት ራሱን ለማስተዳደር የራሱ የሥልጣን ገዥ ለመሆን ነው እስከ ማለት እንደርሳለን።”

ይህን ሐሳብ ለማብራራት አንድ ግጥም ያስነብበናል። ምናልባትም የግጥሙ ባለቤት ራሱ ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም ያለ ወትሮው የግጥሙን ባለቤት ደብቆናል። “በዚህ ሐሳብ መሠረት ሰው የሚመኘው የሚጥረውም በገዛ ራሱና በዙሪያው ባሉት ነገሮች ላይ ሁሉ ሥልጣን እንዲኖረው ነው።” (ገጽ፣ ፴፮)

 እዚህ ላይ ትልቅ እና አከራካሪ የፍልስፍና ሐሳብ ተነስቷል። ትንሽ ማብራሪያ ያስፈልገዋል። በርግጥም የሰው ልጅ ይህ የገዥነት ፍላጎቱ እስከ ምን ድረስ ነው? ከጥንቶቹ የግሪክ ፈላስፎች ሐተታ ብንጀምር የሰው ልጅ ሦስት ፍላጎቶች አሉት። አንደኛው የመብላት የመጠጣት ሥጋዊ ፍላጎቶች፣ ሁለተኛው የመግዛት፣ የማዘዝ የክብር፣ የኩራት ፍላጎቶች፣ ሦስተኛው ደግሞ የማወቅ፣ የመመራመር፣ ምክንያታዊ የመሆን ፍላጎቶች ያሉት ነው። ከሦስቱ አንዱን መምረጥ ሰውን ምሉዕ አያደርገውም። ከሁሉም ምጣኔ የምክንያታዊነት ፍላጎቱ ጎላ ቢልና በሌሎቹ ሁለት ፍላጎቶቹ መካከል ሚዛናዊነት እንዲኖር የዳኝነት ሚናውን በአግባቡ ቢወጣ የተስተካከለ ሰብዕናና ጠቢብ ይሆናል ይላሉ።

 በመካከለኛው ዘመን የፍልስፍና ታሪክ የተነሱት የሃይማኖት ፈላስፎች ደግሞ የፈጣሪም ድጋፍ የሰው ልጅም እምነት እና የማሰብ ክህሎት ታክለውበት ምድራዊውን ሕይወት የተሳካ ያደርጉታል ይላሉ። ከህገ እግዚአብሔር ወስደን ሕገ ልቡናን (የተፈጥሮን ህግ) ጨምረንበት ሕገ ሰብ (ሕገ መንግስት) ብናወጣ የሰውን ልጅ የጋራ ሕይወት የተሟላ ያደርገዋል የሚሉቱ ናቸው እነዚህኞቹ። ልዕለ ተፈጥሮ ረድኤት፣ የሕሊና የሐሳብ ውጤትና ማኅበራዊ ሕይወት ሰውን ወደ እግዚአብሔር መንግስት የተዘጋጀ ሕይወት እንዲኖረው ያደርገዋል። እናም ንጹሕ ህሊና ብቻዋን የሰውን ልጅ ሕይወት ምቹና የተሟላ አታደርገውም ባይ ናቸው።

እንዲህ ዓይነቶቹ መላ ምቶች የዘመናዊ የፖለቲካ ፍልስፍና ጠበብትንም አሳስበዋቸው የራሳቸውን ሙግት ይዘው ብቅ ብለዋል። የሰው ልጅ ማኅበራዊ ፍጡር ነው። ባንድም በሌላም ሕይወቱ የተሰናሰለ ስለሆነ አንዱ አንዱን ካልገዛሁ፣ ያንዱን ንብረት ካልነጠቅሁ ማለቱ አይቀሬ ነው። በዚህም የእያንዳንዳቸው ሕይወት አደጋ ላይ ትሆናለች። ፍጹም ራስ ወዳድ አራዊት የሆነው የሰው ልጅ በህግ ካልተገዛ የሰው ልጆች ሕይወት በስጋት የተሞላ የመከራ ሕይወት ነው። ስለዚህ ሰዎች ተሰብስበው አስፈርቶ የሚያስገብረው፣ ሥርዓት የሚያስዝ ኃይል ያስፈልጋል ወደሚል ስምምነት መጡ ይላል ቶማስ ሆብስ። የሱው ዘመን ጆን ሎክ የተሰኘው ፈላስፋ በበኩሉ የሰው ልጅ ለፍትህ የሚጓጓ ፍጡር ከመሆኑ የተነሳ ከፍጹማዊ የተፈጥሮ ነጻነቱ ቆርሶ በማዋጣት አንድ ሕግ አውጭና አስፈጻሚ መንግሥት መመስረት ፈለገ። ይኸው ነው የመንግሥታት ምሥረታ ታሪካዊ ዳራው ይላሉ።

 በርግጥም የሰው ልጅ ለነጻነት የተፈጠረ ነጻ ፍጡር ነው። የኤግዚስተንሻሊዝም ፍልስፍና አቀንቃኞች መሠረታዊ መነሻም ይኸው ነው። ሰዎች ስለሆንን የሰውን ልጆች ነጻነት ቅድምና የምንሰጥ ቢሆንም የተፈጥሮ ነገሮች በሙሉ ነጻነትን የሚሹ መሆናቸውን መካድ አይቻልም። ሕይወት ባለበት ሁሉ የነጻነት ፍላጎት እንዳለ እሙን ነው። በሽሙጥ ዘይቤ “እግዜር እንደሁ ሞቷል እርማችሁን አውጡ” የሚለው እና የሰውን ልጅ ፍጹም ነጻነት የሚሰብከው ኒችም እዚህ ላይ የሚጠቀስ ይሆናል። በፍልስፍና ታሪክ ውስጥ የሰው ልጆች ለባርነት የተፈጠሩ ናቸው የሚል አስተሳሰብ የያዘ ፈላስፋ አልገጠመኝም። በርግጥ ፍጹም ገደብ አልባ ነጻነት የተሰጣቸው ላለመሆኑ ማሳያ ለሌሎች ሰዎች ነጻነት መከበር ያላቸው ግዴታ እንዳለ የሚከራከሩትን እነ ካንትን መጥቀሱ ተገቢ ነው። ከዚህ የራስና የሌሎችን ነጻነት ከመፈለግ ነው የሰው ልጅ ሥነ ምግባራዊ በጎነትና የፖለቲካ ተቋማት ፍትሓዊነት የሚያስፈልገው ይለናል ካንት። በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት ከሰጡት ውስጥ የ20ኛው ክፍለ ዘመን አሜሪካዊ ፈላስፋ ጆን ራውልስ የሚጠቀስ ነው። ማንኛውም ማህበራዊ ተቋም የሰውን ልጆች የማይነቀነቅ የተፈጥሮ ነጻነት እና ክብር የሚጠብቅና የማኅበራዊ አባልነታቸውን ድርሻ በፍትሃዊነትና በእኩልነት የሚያካፍል መሆን አለበት ይለናል።

 ይህ ሐተታ እዚህ ላይ ያስፈለገው ከሊቁ ሐተታ ጋር ፍጹም የተቆራኘ ስለሆነ ነው። ለመሆኑ የእጓለ ሐሳብ ከየትኛው ወገን ነው? የሰውን ልጅ ነጻነትና ሥልጣኔ የሚመኝ መሆኑ እሙን ነው። ግን በየትኛው መንገድ ነው? እዚህ ላይ ቆመን ከተመለከትነው የአዳምን “ዓመጽ” የሚደግፍ የኒቼ ጓደኛ

“ሥልጣኔ ማለት መጀመሪያ ሰው በህሊናው ውስጥ ያሉትን ሃብታት መርምሮ ተረድቶ መሪነቱን ካወቀ በኋላ ዝቅተኛውን የሥሜት ወይም የፍትወት ዓለም አርቆ ገርቶ ለህሊናው ያስገበረ እንደሆን በራሱ ላይ ሥልጣን ያለው የሆነ እንደሆን የሚሰጠው ቅጽል ነው”

ሊመስለን ይችላል። ነገር ግን አንድ ሐዲስ ኪዳንን መሠረት በማድረግ በክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ላይ መጽሐፍ እስከ መጻፍ የደረሰን ፈላስፋ የአዳምን ታሪክ በንጹሕ ሕሊና ብቻ ተመልክቶ የአዳም ምግባር ተገቢና የሰው ልጆች ከፈጣሪ ትእዛዝ በመኮብለል ነጻነታቸውን ማወጅ አለባቸው የሚል ድምዳሜ ይይዛል ወደሚል መጠምዘዝ ግን ሰውዬውን በቅጡ አለመረዳት ወይም በቅንነት አለማንበብ ይመስለኛል። ለዚህም አሳማኝ ምክንያት አለን። ቀጣዮቹን ገጾች ብንገልጥ የሊቁ ሐሳብ ከነ ሙሉ ሥእሉ ይገለጥልናል። ሊቁን ለሙግት ለመጥቀስ ከፈለግንም ከነ ሙሉ ሐሳቡ እና ከነ ድምዳሜው ግርማ ሞገስ እንጅ አንዷን ሰበዝ ነቅሰን መሆን የለበትም። ያንን ካላደረግን ሃይማኖተኛውን ሊቅ “ለክህደት” ተባባሪ ልናደርገው እንደፍራለን። ለምሳሌ የልዕለ ተፈጥሮን ረድኤት ወይም መለኮታዊ ጉዳዮችን ለማስረዳት የያሬድን ጉዳይ ባተተበት የመጽሐፉ ክፍል ሰው ሕሊና ብቻ እንዳልሆነ፣ ንጹሕ ህሊና ብቻዋን እንደዚህ ዓይነቶቹን ጉዳዮች መረዳት እንደማትችል፣ እውነት በንጹሕ ሕሊና ብቻ እንደማትገለጥልን ካንትን መሠረት በማድረግ ፓስካልን ጠቅሶ ያስረግጥልናል። ይህንን ጉዳይ በሰፊው የምንመለስበት ቢሆንም ያሬድ የመንግስት እኩሌታ ቢሰጠውም ሌላኛውን መንገድ መርጦ ወደ ሰሜን ተራራ መኮብለሉን እስከ አሁንም የዝማሬ ድምጹን የሚሰሙ ሰዎች መኖራቸውን “የእምነት ጉዳይ ነው። ፍልስፍና ወይም ንጹሕ ሕሊና እንዲህ ያለውን ነገር አይረዳውም። ግን አንድ ነገር አለ። ይህም ልቡና የምንለው ነው።” በማለት ይሞግታል። (ገጽ 61-62/፷፩-፷፪)

ይህንን አስተያየት በመሃል ማስገባት የፈለግሁት ፍልስፍናዊ ጽሑፎችን የሚያነቡ ወጣቶች እንደፈላስፎቹ እንኖራለን እያሉ ወይም የፈላስፎችን ሐሳብ እየቆራረጡ ያልተረዱትን ለመኖር ሲሞክሩ መታዘብ የተለመደ በመሆኑ ነው። ለምሳሌ ከላይ የጠቀስነውን ጉዳይ በንጹሕ ህሊና ብቻ ለመረዳት ብንሞክር የመላምታችን ድምዳሜ፣ በርግጥም አዳም ነጻነትን በመሻት ከገነት መኮብለልን መርጧል ለማለት እንደፍር ይሆን? ሃይማኖታዊ ትርክቱን ከተከተልን በዚያው በእምነቱ ዓውድ ላሉ ሰዎች ወይም አማንያን የሚሆን በቂ እና የተሟላ ታሪክ አለው። ያንን ለእምነቱ ተከታዮች ትተን በፍልስፍና ወይም በሳይንስ በንጹሕ ህሊና ለመመርመር ብንሞክር ደግሞ ከዋናው ትርክቱ መውጣት ሊኖርብን ነው። መጀመሪያውን ፈጣሪ የሚባል ከልካይና ፈቃጅ፣ ገነት የምትባል ቦታ፣ መኖሯን በንጹሕ ሕሊና ማብራራት ይኖርብናል። ያንንም በተፈጥሮ ጉራንጉር ፈጣሪን መፈለግ (የእግዜርን ህልውና ማረጋገጥ)፣ የአዳምና የፈጣሪውን ውል፣ የውሉን መፍረስና የአዳምን ከገነት መውጣት ጉዞ መነሻውንና መዳረሻውን መተንተን ይኖርብናል። ያንን ለማድረግ “ገነት” የተሰኘች ስፍራን ፣ እጸ በለስ የምትባል  ፍሬን፣ አዳም የተሰኘን የመጀመሪያው ፍጡር የሚሉ ሃይማኖታዊ ጽንሰ ሐሳቦችን ታዛ ማድረግ ላይኖርብን ነው።

 ከዚህ በተጨማሪ በፍልስፍናዊ መንገድ የህዝባችንን የአስተሳሰብ ብልጽግና ለመደጎም የሚፈልግ ማንኛውም ጸሐፊ ከሃይማኖታዊ፣ ከፖለቲካዊ፣ ከባህላዊ አስተሳሰቦች ሐሳብን ሲወስድም ሆነ በተጠቀሱት የማኅበረሰባችን የሕይወት ዘይቤዎች ላይ ተቃርኖዎችን ለመተቸት፣ የአስተሳሰብ ዝንፈቶችን ለማረቅ ብዕራቸውን የሚያነሱትን የኔ ቢጤዎች ምሁራዊ ቀናነትን እንዲላበሱ አስተያየት ለመስጠት ነው። አንዳንዶቻችን ልንሳለቅበት፣ ልናጣጥለው፣ ልንተቸው የምንችለው ተረት፣ እምነት ወይም የሕይወት ዘይቤ በባለቤቶቹ ዘንድ የሕይወት ትርጉማቸው ዋልታና ማገር ስለሆነ ጥንቃቄ ያስፈልጋል። አውሮፓውያን አፍሪካውያንን በቅኝ ግዛት ሊወሩ በሚመጡበት ወቅት “በሃይማኖት ሐዋርያዎቻቸው” እና “በልማት ልዑኮቻቸው” አማካኝነት የአፍሪካውያን ነባር እምነትና ባህል ምክንያታዊ እንዳልሆነ ምድራዊ ጸጋንም ሆነ ሰማያዊ ጽድቅን እንደማያመጣላቸው በመስበክ ነው። ያም ራስን ከማንነት በመነጠል ለመግዛት የሚያመች ሥነ ልቡናዊ መልፈስፈስን የሚያመጣ መሣሪያ ነበር። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያውያን የተሻለ ጥንካሬ እንደነበራቸው ታሪካችን ያሳያል። ኋላ ላይ አድሃሪ፣ ግትር፣ የለውጥ ጸር እየተባለ በመሸርሸሩ ወጣቶቻችን ለማርክሲዝምና ሌኒንዝም ዘብ በመቆማቸው በትውልዶች መካከል የተፈጠረው ክፍተት ያስከፈለንን ዋጋ መረዳት አያዳግትም። የእኛ የሆነ ሁሉ እንደወረደ መወሰድ የለበትም፣ ዘመናዊ የሆነ ሁሉም እንደወረደ መዋጥ የለበትም። ትችቱም በዚያው ልክ መሆን አለበት። ይህንን ጉዳይ በሌላኛው የሊቁ ምዕራፍ በሰፊው እናገኘዋለን። እንመለስበታለን።

ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስ። በምዕራፍ ሦስት መዝጊያ የሥልጣኔን ሙሉ ትርጉም ያስነብበናል። “ሥልጣኔ ማለት መጀመሪያ ሰው በህሊናው ውስጥ ያሉትን ሃብታት መርምሮ ተረድቶ መሪነቱን ካወቀ በኋላ ዝቅተኛውን የሥሜት ወይም የፍትወት ዓለም አርቆ ገርቶ ለህሊናው ያስገበረ እንደሆን በራሱ ላይ ሥልጣን ያለው የሆነ እንደሆን የሚሰጠው ቅጽል ነው። ሁለተኛ በዙሪያው ያሉትን ሥነ ፍጥረቶች ለራሱ እንዲያገለግሉ ለማስገበር የሚያደርገው ጥረትና ከዚያም የሚያገኘው ውጤት ሥልጣኔ ይባላል። በመጀመሪያው በኩል ያደረገው እርምጃ ምንም እንኳ የሚያጠራጥር ቢሆን በሁለተኛው በኩል በጣም ርቆ ሄዷል። ” (ገጽ ፴፮-፴፯) “ለህሊናው ያስገበረ እንደሆነ” የሚለው ሐረግ የያዘው ቁም ነገር በጎ ምግባር ከእውቀት ጋር የተዋሃደው ሰብዕናን ለመግለጽ ነው። የስልጡን ሰው መገለጫም ይኸው ነው። ሁለተኛው ደግሞ በተፈጥሮ ላይ ገዥ መሆን ነው። ይህ አስተሳሰብ በነ ቤከን የታወጀው ተፈጥሮን በሳይንሳዊ መንገድ በመረዳት ለሰው ልጆች ተገዥ ማድረግ እና በቁጥጥር ስር ማዋል የሚል ሕጸጽ ያለው አመለካከት ነው። ምክንያቱም የሰውን ልጅ ከተፈጥሮ በላይ የማስገዛት አምባገነናዊነት ባህርይ ስለሚያላብስ ነው። የእጓለ ሐሳብ ግን ከዚህኛው የተለየ ይመስላል። ምክንያቱም የሰው ልጅ በበሽታ፣ በብርድ፣ በረሃብ፣ በሐሩር፣ በአራዊት መነደፍ ወዘተ የባርነት ኑሮ ሲመራ ስለነበር ከዚያ ነጻ ለመውጣት የተመጠነ የቁሳዊ ፍላጎቶቹ መሳካት ከተፈጥሮ የሚገባውን ያክል መውሰድ አለበት ወደሚለው ድምዳሜ ሚዛን ይደፋል። ቀጣዩ ምዕራፍ ከዚህኛው ምዕራፍ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው። የትምህርት ፍልስፍና ከሥልጣኔ ዘይቤ ጋር እንዴት የተሰናሰለ እንደሆነ ያሳየበት ምዕራፍ ነው።

ወደ ትክክለኛው ሥልጣኔ የሚወስዱን ትምህርቶችን በሁለት ዓበይት ክፍል ይከፍላቸዋል። አንደኛው መንፈሳዊ ሥልጣኔ የሚያስገኙትን የህግ፣ የታሪክ፣ የቁጠባ፣ የሥነ ጽሑፍ፣ የፍልስፍና፣ የቃለ እግዚአብሔር ትምህርቶችን የሚያካትት ነው። እነዚህም የጥንት ዘመን የሥነ ትምህርት ሰዎች Liberal Arts የሚሏቸውን የMoral Sciences የሚያጠቃልል ነው። ሰውን ከህሊናዊ የድንቁርና ባርነት ነጻ የሚያወጡት ናቸው። ሁለተኛው ደግሞ Natural Sciences የምንላቸው ሥነ ተፈጥሮን የሚያጠኑትን የሚያካትት ነው። ከግዑዛን የቅርቡ ዓለም አካላት እስከ ሥነ ከዋክብት ጥናት የተዘረጉ ናቸው። ከነዚህ ጋር የተያያዙ የተግባረ ዕድ Technical Sciences፣ ዘመናዊ የቴክኖሎጅ እውቀትን የሚያካትቱ ትምህርቶችም ይኖራሉ። ከነዚህ ውጭ የሆኑ በትምህርት የሚበለጽጉ ግን እውቀት ከሚለው ይልቅ ሃብታት ወይም ጸጋዎች የሚላቸውም አሉ። እንደ ዜማ፣ ሙዚቃ፣ ሥእል፣ ወይም Fine Arts የሚባሉት ናቸው። የነዚህ ሁሉ ጥምር ውጤት ሥልጣኔ ይሰኛል። “በዚህ አራት አንጻር ባለው መስክ የሰው ልጅ ጥሮ ግሮ ያስገኛቸው የመንፈሱ የክንዱ ፍሬዎች ሥልጣኔ ይባላሉ።” (ገጽ 40/፵) እዚህ ላይ ሁለት ተያያዥ ጥያቄዎችን ማንሳት ተገቢ ይመስለኛል። ለመሆኑ የኢትዮጵያ ባህላዊ የትምህርት ፍልስፍና ከዚህ አንጻር እንዴት ይመዘናል? ዘመናዊ የኢትዮጵያ ፍልስፍናስ በዚሁ ሚዛን ፊት ቢቀርብ ምን ይመስላል? የኔን አስተያየት ሌላ ጊዜ የምመለስበት ይሆናል። አንባቢም የራሱን አስተያየት እንዲሰጥ ነጻነቱ አለው።

የሰው ልጅ የምኞቱ ብዛት ልክ በተሸነቆረ ማድጋ ውሃ እንደማመላለስ እንደሆነ የፕሌቶን ምሳሌ ጠቅሶ ካስረዳ በኋላ ወደ ሥልጣኔ ለመጓዝ ምኞቱን እያረካ መሄድ እንዳለበት፣ ወደኋላ መመለስ ወይም ቆሞ መቅረት እንደማይቻል ይሞግታል። ይህም ጉዞ በሰዎች ዘንድ የሥልጣኔ እድገት ነው። ሕይወት ያለው ነገር ሁሉ ዘመንና ቦታ በሚባል መስክ ላይ የተዘረጋ እንደመሆኑ ወደፊት መጓዙ አይቀርም። ሰው በጊዜ ሂደት ውስጥ ይወለዳል፣ ያድጋል፣ ያረጃል። ሥልጣኔም እንዲሁ ነው። በሰው የተፈጠረ እንደ መሆኑ ሊያረጅ ሊወድቅ ይችላል። “ወኩሉ ከመ ልብስ ይበሊ/ሁሉም እንደ ልብስ ያረጃል።“ ነገር ግን “ከወደቀም በኋላ ለመነሣት ይችላል። ሥልጣኔ ከመንፈስ የተገኘ እንደ መሆኑ የዘላቂነት የነዋሪነት ጠባይ አለው። ከሞተ በኋላ ለመነሣት ይችላል።” (ገጽ 42/፵፪) ይህ የሥልጣኔ የመወለድና የመውደቅ እንደ ገና የመነሳት ዲስኩር የሚያስተምረን ነገር አለ። ዘመን የራሷ ትውልዶች እንዳሏት በቀደመው ክፍል አይተናል። እነዚህ የዘመን ህመምተኞች ሥልጣኔ በተረበሸ ጊዜ የፈውስ ሓሳብ፣ የመንፈስ ትንሣኤ ለማምጣት የሚነሱት የልቡና ግለት ያላቸው ናቸው። “እሊህም ታሪክን ሥልጣኔን የሚያስገኙ ጀግኖች ብርቱ ሕመም እንደያዘው ሰው ፋታ የላቸውም። ዕረፍት የላቸውም። ሰላም ጸጥታ አያገኙም። ቀን ያቅዳሉ ይሠራሉ ያሠራሉ። ሌሊት ያስባሉ ያልባሉ ይባንናሉ። የብዙዎች ዕድል በእነሱ ትከሻ ያረፈ ይመስላቸዋል። በብዙዎች ፈንታ እነሱ መድከም እንደሚገባቸው ይሰማቸዋል። የራሳቸውን እኔነት ጨርሰው ክደው ከብዙዎች ሕላዌ ጋር ደባልቀውታል።” (ገጽ 42-43/፵፪-፵፫) የትምህርት ዓላማው እንደነዚህ ዓይነቶችን ከእኔነት የተፋቱትን ለሰው ልጆች ሁሉ በጎነት ራሳቸውን የሻማ ብርሃን የሚያደርጉትን ማፍራት ነው።

እጓለ እዚህ ላይ በግልጽ ባይነግረንም በዘመኑ የታዘበው ነገር ሳይኖር አይቀርም፣ ወይም ወደፊት የፈራው ሥጋት ሊኖር ይችላል። ሁሉም በእኔነት ቅርጫት ማሰብ ከጀመረ አደጋው የከፋ እንደሚሆን፣ የሥልጣኔ ጉዞ ከወደቀበት እንዳይነሳ በዚያው አፈር የሚጭነው የእንደዚህ ዓይነቶቹን ሕመምተኞች ማጣት እንደሚሆን ቢያንስ ማስጠንቀቂያውን ነግሮናል። ወደፊትም በመጽሐፉ ውስጥ የምናገኘው ፍንጭ ይኖራል። “ከተስፋው ምድር ሰውን በዓምደ ብርሃን ወበዓምደ ደመና መርተው የሚያደርሱ ሰዎች አሉ። እነዚህ ሰዎች እንደ ጸሐይ ማለት ናቸው።” እነዚህ ብርሃናት ለሰው ልጆች ሁሉ የሚበጀውን እውቀቶች የሚያፈልቁት “ነቅዓ ንጹሕ ጥሩ ምንጭ ማለት ናቸው። በገዛ ሕላዌያቸው ጥልቀት ሐሳቦችን ያመነጫሉ።”

 ከነዚህ በኋላ የሚመጡት ደግሞ የነርሱ ተከታዮች ናቸው። ”በከመ ይቤ“ እከሌ እያሉ እነርሱን የሚጠቅሱ። እንደገና ያለፉትን ብቻ ማስተጋባት ሲበዛ መንፈስ፣ ሥልጣኔ ድቀት ያጋጥመዋል። እንደገና የሚያነሱት የልቡና ግለት፣ የመንፈስ ልዕልና ያላቸው ጀግኖች ይወለዳሉ። የሥልጣኔ ቀጣይነት ማለትም ይኸው የዱላ ቅብብል ነው። የአራተኛው ምዕራፍ መዝጊያም ይኸው ነው። ለዚህ ረቂቅ ሐተታ (in abstracto) ማስረጃ ይሆን ዘንድ በቀጣዮቹ ምዕራፎች ሁለት ሥልጣኔዎችን ሊያሳየን ቃል ይገባልናል። እኛም ገጾቹን መግለጣችንን እንቀጥላለን። የወር ሰው ይበለን!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top