አድባራተ ጥበብ

«ቪላ አልፋ» ለምን ተዘጋ?

በዘመን ግስጋሴ ውስጥ ትውልድ ያልፋል፤ ትውልድ ይመጣል። የሚያልፈው ትውልድ በበጎም ሆነ በክፉ የሚታወስበት አሻራውን ትቶ ነው የሚሸጋገረው። ያ ደግሞ ታሪክ ይሆናል። በእንዲህ መልኩ በተለያዩ ዘመናት በትውልዱ ውስጥ ባከናወኗቸው ተግባራት ግለሰባዊ ማንነታቸው ገኖ የወጣ ኢትዮጵያውያን ጥቂት አይደሉም። አገረ ኢትዮጵያ አያሌ ጀግኖችን አፍርታለች፣ አምባገነኖችን አስተናግዳለች፣ የጥበብ ባለሟሎችን አውጥታለች።

 ዛሬ ላይ ከሃገር አልፎ ስማቸውና ክብራቸው በተለያዩ ሃገራት ከፍ ብሎ ከሚነገርላቸው የጥበብ ሰዎች መካከል እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ አንዱ ናቸው። በዓለም ዘንድ አንዱ የክብራችን መገለጫ እሳቸው ናቸው። በስራዎቻቸው ታውቀው ያሳወቁን ስለመሆናቸው መናገር ፈጽሞ እብለት አይሆንም። እኒህ ታላቅ ሰው ሲጠበቡ ኖረው ሲጠበቡ ያለፉ ናቸው። ያከማቿቸውን ስዕሎችና ሌሎች ንብረቶቻቸውን ለኢትዮጵያ ሕዝብ አውርሰው ካለፉ እነሆ ስምንት ዓመታት ተቆጠሩ። ጦር ኃይሎች ሆስፒታል አካባቢ የሚገኘው የስዕል መስሪያ ስቱዲዮና ቅርስ ማከማቻ ጋለሪ እንዲሁም መኖሪያ ቤታቸውን አጠቃሎ የያዘው ቪላ አልፋ ይህችን ዓለም በስጋ ሞት ከተሰናበቱበት ዕለት ጀምሮ እንደተዘጋ ቀርቷል። ለምን?

ለመሆኑ እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ማን ናቸው? ዓለም ያከበራቸውን እኚህ ታላቅ የፈጠራ ሰው ምን ያህል እናውቃቸው ይሆን? እስኪ ጥቂት ስለ ማንነታቸውና ሥራዎቻቸው እንጠቃቅስና ወደ ዋናው ጉዳያችን እናምራ። ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ከአባታቸው ከአቶ ተክሌ ማሞና ከእናታቸው ከወይዘሮ ፈለቀች የማታወርቅ ጥቅምት 22 ቀን 1932 ዓ.ም ሰሜን ሸዋ ውስጥ አንኮበር ነው የተወለዱት። ልጅነታቸውን በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት፣ ኋላ ላይ በሥራቸው ዝነኛ ከሆኑት እንደ አቶ ተስፋዬ ገሠሠ (ተባባሪ ፕሮፌሰር) እና ስብሐት ገብረእግዚአብሔርን ከመሳሰሉ ታዋቂ ከያኒያን ጋር እየተማሩ በጥሩ ውጤት ዘለቁ። በ1940 ዓ.ም በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ይሁንታ የውጪ ትምህርት ዕድል ተሰጥቷቸው ወደ እንግሊዝ ሃገር ተላኩ። ያኔ ገና አሥራ አምስት ዓመታቸው ነበር። አካሄዳቸው የምህንድስና ትምህርት ለመከታተል ቢሆንም ካላቸው ፍላጎትና ተሰጥኦ በመነሳት በለንደን ዩኒቨርሲቲ የስሌድ ሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት በቀለም ቅብና በቅርጻ ቅርጽ በኪነ ሕንጻ ዘርፍ ትምህርታቸውን በመከታተል በጥሩ ውጤት ተመረቁ። በውጤት ብቻ ሳይሆን በዚህ የትምህርት ዘርፍ የመጀመሪያው አፍሪካዊም ነበሩ።

 ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ጋር ለትምህርት ወደ እንግሊዝ ሲላኩ፤ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ « የፈረንጅ አገር ትምህርት ቀስማችሁ ስትመለሱ አገራችሁን እና ህዝባችሁን አገልግሉ፤ እውቀትን አስፋፉ… አደራ » ብለው ያሳሰቡትን በማስታወስ ልክ ከስድስት ዓመት በኋላ ትምህርታቸውን እንደጨረሱ ወደ ሃገራቸው ተመለሱ። የገበዩትን ዕውቀት «ሀ» ብለው ለሕዝባቸው ሲያሳዩ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የመጀመሪያ ኤግዚቢሽናቸውን አዘጋጁ፤ በዚህም ትልቅ አድናቆትና ከበሬታን አገኙ። ይህ ኤግዚቢሽን አቅም ስለፈጠረላቸውም ወደ አውሮፓ በመሻገር ተጨማሪ እውቀት ለመገብየትና ጥናት ለማድረግ ተነሱ። ለሁለት ዓመታት ያህልም በእንግሊዝ፣ ስፔን፣ ፖርቹጋል፣ ግሪክ፣ ፈረንሳይ ጣሊያንና በሌሎች ሃገራት በመዘዋወር የሥዕል ጥበባቸውን አሳደጉ። የሌሎች ሃገራት የጥበብ ደረጃና አቅም እስከምን ድረስ እንደሆነ ተገነዘቡ። በተለይ በስተኋላ ልዩ መታወቂያቸው የሆነውን የደመና ሥዕል (cloud formation) እና የመስታዎት ላይ የመስመር ቅጥልጣይ ሥዕል ወይም «ሞዛይክ» (Mosaic stainless glass) ተክነው ተመለሱ።

 ከዚያ ሃገራዊ ሁነቶችን፣ ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸው መልዕክቶችን፣ ማህበራዊ ህይወት ገላጭ የሆኑ ጉዳዮችን በሰፊው መሳል የቀጠሉት ታላቅ ጠቢብ አፈወርቅ ተክሌ ውበትን፣ ጀግንነትን፣ ማዘን መከፋትን፣ መደሰት መዝናናትን የሚያመላክቱ አያሌ ሥዕሎችን በመሳል ከሃገር አልፎ ለዓለም አበረከቱ። ሁሌም ሲያስተውሏቸው ተመስጦ ውስጥ የሚከቱት ሥዕሎቻቸው ዋጋና ክብራቸው ከፍ እያለ መጣ።

 መረጃዎች እንደሚጠቁሙት እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ የመናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያንን ግድግዳ፣ ጣሪያና መስኮቶች በሃይማኖታዊ ምስሎች በቀለምና በመስታወት ሥዕሎች አስውበዋል። ይህንንም የሳሉት በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ትዕዛዝ ነው። ከዚህም ሌላ የድንግል ማርያም ንግስ፣ ኪዳነምሕረት እና የቀዳማዊ ኃይለሥላሴን የዘውድ ሥርዓት የሚያሳዩ ሥራዎችን ሰርተዋል። በሐረር ከተማ ቆሞ የሚታየውን የልዑል ራስ መኮንን ሀውልት የቀረጹትም እሳቸው ናቸው። በአብዛኛው ጥንታዊውን የኢትዮጵያውያን ባህላዊ የመስመር አሳሳል መሠረት አድርገው ነው የሚስሉት። ይህም በአሳሳል ዘይቤ ኢትዮጵያዊነትን ይገልጻል ባይ ናቸው።

በአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን አዳራሽ መግቢያ የሚታየውና በመቶ ሃምሳ ካሬ ሜትር ላይ የተሳለው ትልቅ የመስታወት ሥዕልም የእሳቸው ነው። ይህ ሥዕል የአፍሪካን ያለፈ የሰቆቃ ታሪክ፣ አልገዛም ባይነት፣ የተጋድሎ እንቅስቃሴና የወደፊቱን ተስፋ አመላካች ነው። በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የሚገኘው የመጀመሪያው የዳግም ምጽዓት ፍርድ ሥዕልና የአቡነ ተክለሃይማኖት ሥዕልም የእሳቸው በረከቶች ናቸው። ከዚህም ሌላ ሥዕሎቻቸው በበርካታ ታላላቅ የዓለም ሙዚየሞች ውስጥ በቋሚነት በመጎብኘት ላይ እንደሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ።

 በእንግሊዝ ሃገር በ‘ታወር ኦፍ ለንደን’ በቅዱስ ጊዮርጊስ ጸሎት ቤት ውስጥ ከብር እና ከእንጨት የሠሩት የመንበር መስቀል እንደሚገኝም ተመዝግቧል። በሩሲያ፣ በአሜሪካ እና በሴኔጋል ኤግዚቢሽን የቀረበው ‘የመስቀል አበባ’ ሥዕል፣ ‘እናት ኢትዮጵያ’ እና ‘ደመራ’ የተሰኙት ድንቅ ሥዕሎቻቸው ከበሬታን ካጎናጸፏቸውና እሳቸውም ከሚደሰቱባቸው ሥዕሎቻቸው ውስጥ ይጠቀሳሉ። ለቴምብር አገልግሎት የዋሉ ሥዕሎቻቸውም ጥቂት አይደሉም። ለመጫወቻ ለካርታና ለአደባባይ ፖስተር የሚሆኑ ሥዕሎችንም ሠርተዋል። በሥዕል ጥበብ እና በቅርስ ዙሪያ ያካሄዷቸውን ጥናትና ምርምሮቸ በተለያዩ አገራት በተዘጋጁ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች አቅርበዋል። የፈረንሳይ እና የሩሲያ አገራትን ጨምሮ የአራት ዓለም አቀፍ የስነ ጥበብ አካዳሚ አባልም ነበሩ ‐ ታላቁ ጠቢብ አፈወርቅ ተክሌ።

 በሥራቸው፣ በማህበራዊ ግንኙነታቸውና በንብረት አጠባበቃቸው እጅጉን ጠንቃቃ ናቸው። ብዙውን ጊዜ ሥዕሎቻቸውን ለማስጎብኘት ወደቪላ አልፋ የሚጋብዟቸውን ሰዎች፣ ለምሳሌም ከተለያዩ ሃገራት የሚመጡ ጋዜጠኞችን፣ ታዋቂ ሰዎችን፣ አምባሳደሮችንና ዲፕሎማቶችን የሚቀበሉት፣ ራሳቸው ዲዛይን ባደረጉት የሃገር ባህል ልብሳቸው አምረውና ደምቀው ነው። በተለያዩ ሃገራት የሥዕል ኤግዚቢሽኖች ለማዘጋጀትም ሆነ በክብር እንግድነት ተጋብዘው ሲሄዱ በባህል ልብሳችን ደምቀው መታየትን ይወዳሉ። «የማንነታችን አንዱ መገለጫና ክብራችን ነው» የሚባሉትም ከሥራዎቻቸው በዘለለ በእንዲህ ያለው የአለባበስ ሥርዓታቸውም ነው።

የሚያውቋቸው ሁሉ እንደሚናገሩት ትሁት ናቸው። ክብራቸውን እንደሚፈልጉ ሁሉ፤ የሌላውን ክብር ይጠብቃሉ። ሃገራቸውን ይወዳሉ። ባህልና ታሪካችንን ለሌላው ዓለም ለማስተዋወቅ ያገኙትን አጋጣሚ ሁሉ ይጠቀማሉ። ለቅርሶቻችን ይቆጫሉ። በጣሊያኖች ተዘርፎ በሮም አደባባይ ለበርካታ ዘመናት የቆየውን ሐውልት ለማስመለስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ባቀረቡት ጥናትም «እኛ ለታሪካችን እና ለቅርሶቻችን የምንሰጠው ዋጋ ዝቅተኛ ነው። ጠብቆ ለማቆየት የሚያስችለን የአሰራር ሥርዓትና ቴክኖሎጂ የለንም። ዘመነኛው ትውልድም ለአገሩ ቅርስና ታሪክ ያለው ቁጭትና የተቆርቋሪነት ስሜት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደበዘዘ ነው። … እኔ በግሌ በትምህርትና በሥራ በቆየሁባቸው በአውሮፓና አሜሪካ የሚገኙ ታላላቅ ዩኒቨርሲቲዎች ፣ ቤተ መጻሕፍት፣ ቤተ መዘክሮችና ጋለሪዎች በተለያዩ ጊዚያት ከአገራችን ተዘርፈው የተወሰዱ ቅርሶቻችንን በተለይም ደግሞ በርካታ ዕድሜ ያስቆጠሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የጥንት የብራና መጽሐፎቻችንን ለማየትና ለመመርመር ዕድሉን አግኝቻለሁ። በዚያ በሚደረግላቸው ልዩ እንክብካቤና ጥበቃም በእጅጉ ተደንቂያለሁ። በአንጻሩ ደግሞ መለስ ብዬ አገሬንና ህዝቤን ሳይ … በቀደሙ አባቶቻችን ብዙ ድካምና ልፋት የተዘጋጁና በብዙ ተጋድሎም ለትውልድ የተላለፉ ቅርሶቻችን እዚያው እንዳማረባቸው ተጠብቀው ቢቆዩና ባይመለሱስ ምን አለበት ስል እራሴን እጠይቃለሁ » ብለው ነበር። ከአያያዝና ከአጠባበቅ ልልነታችን አንጻር የሚመጣውን ጉዳት በማሰብ ነው ይህን ማለታቸው። ቅርስ ግን ከሃገር እንዲወጣ አይፈልጉም። እንዲያውም በተለያዩ መንገዶች ተዘርፈው ከአገር የወጡ ቅርሶቻችንን ሲያስቡ ይቆጫሉ።

 በርካታ ሥዕሎቻቸው ከሃገር እንዲወጡ አይፈልጉም ነበር። በዚህ ጉዳይ ላይ ለሐመር መጽሔት (ቅጽ 19፣ ቁጥር 3 ዕትም) በሰጡት ቃለ ምልልስ፤ ሥዕሎቻቸውን ለኢትዮጵያውያን የሚሸጡት ለውጪ አገር ሰዎች ከሚሸጡበት ዋጋ በግማሽ ቀንሰው ነው። «ሥዕሎቼን ለውጪ አገር ሰዎች ከሸጥኩ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ተመላሽ እንዲሆኑ ተዋውዬ ነው» ማለታቸውን መጽሔቱ ዘግቧል። በገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን በስተምስራቅ ደቡብ አቅጣጫ የሚገኙትን የግድግዳ ሥዕሎች በባለ ቀለም ጠጠሮች ክርክም መስታወትና በሞይዛክ የሰሩት ከሰዓሊ ብላታ ዕምአዕላፍ ህሩይ ጋር መሆኑን ተናግረዋል። ከአልማዝ፣ ከወርቅ፣ ከብር እና ከሐር የተሰሩ ልዩ ልዩ ኒሻኖች፣ ሜዳሊያዎች፣ አልባሳት፣ ዋንጫዎች፣ ሰርትፍኬቶችና ሽልማቶች ቤታቸው ውስጥ በአንድ ግዙፍ የመስታወት ሳጥን መቀመጣቸውን መጽሔቱ አስፍሯል።

ከሠሯቸው አጠቃላይ ሥዕሎች ውስጥ አሥር በመቶ የሚሆኑት የቤተክርስቲያን ስራዎች መሆናቸውንም ቃላቸውን ጠቅሶ አስፍሯል። እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ፤ በዕምነታቸው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ተከታይ ናቸው፤ በቪላ አልፋ ሰገነት ላይ ባሰሩት የጸሎት ቤት ለአምላካቸው ምስጋና ያቀርባሉ፣ ይጸልያሉ። የሳቸው ስራ የሆኑ የቅዱሳን ስዕሎችም በጸሎት ቤታቸው በክብር ይገኛሉ።

 ታላቁ ጠቢብ ከአገራችን አልፎ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ምስጋናና ሽልማቶችን ተቀብለዋል። በ1957 ዓ.ም የመጀመሪያውን የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ብሔራዊ የሥነ ጥበብ ሽልማት ተቀዳጅተዋል። ከመሞታቸው ጥቂት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እንግዳ ያደረገቻቸው ጋዜጠኛ የእናት ፋንታ ውቤ ከ97 በላይ ሽልማቶችን እንዳገኙ ዘግባለች። ለዓለም ባበረከቱት ጥበባዊ ስራ አማካይነት ስማቸውና የአገራቸው ባንዲራ ጨረቃ ላይ በክብር እንዲቀመጥ መደረጉንም ተርካለች።

«በኢትዮጵያ ላይ ክፉ አትይ፣ ክፉ አትስማ፣ ክፉ አትናገር» የሚል መሪ ቃል ያላቸው መሆኑንም አብራርታለች። አንጋፋው ጠቢብ በዚሁ ቃለ ምልልስ ወቅት እንደተናገሩት፤ ቪላ አልፋን የሠሩት ለመንደላቀቂያ ሳይሆን ለሥዕላቸው መስሪያና ማሳያ ብቻ ነው።

 እነሆ ያ ግርማ ሞገሳማ ግቢ ላለፉት ስምንት ዓመታት እንደተዘጋ ነው። በአካባቢው እግር የጣለውም ሆነ መንደርተኛው ሁሉ ቤቱን ሳይቃኝ፣ ስማቸውን ሳያነሳ፣ ስለ ቅርሶቻቸው ሳይቆጭ፣ ምነው መንግስት ዝም አለ? የሚል ጥያቄ ሳያነሳ አያልፍም። በራሳቸው ዲዛይን ሲያሰሩት በርካታ ዓመታትን የፈጀባቸው መሆኑ የሚነገርለት ቪላ አልፋ 22 የተለያዩ ክፍሎች እንዳሉት ይታወቃል። መኖሪያቸው ባለ አንድ ፎቅ ነው። ግቢው በተለያዩ ተክሎች የተዋበ ነው። የኢትዮጵያውያን የጥበብ አሻራ የሚታይበት ይህ ግቢ ባህላዊ፣ ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ በአጠቃላይ ሀገራዊ ዕሴቶችን አቀናጅቶ የያዘ ነው። እያንዳንዱ የቤቱ አቀማመጥና ፎርም ምክንያታዊ ነው። ለእርሳቸው ትርጉም አለው። ለምሳሌ የግቢው ዋና መግቢያ በር የሐረር ግምብ መግቢያ እና የፋሲል ግንብን አሰራር ጥበብ አዋህዶ የተሰራ ነው። ለዚህ ታላቅ የጥበብ ግቢ «አልፋ» የሚል ስያሜ የሰጡት በትምህርታቸው ጎበዝ ስለነበሩ መምህራኖቻቸው «አልፋ ፕላስ» እያሉ ይጠሯቸው ስለነበረ ያንን በማስታወስ መሆኑን ነው የተናገሩት። ህንጻዎቹን ሲያስገነቡም ከተለያዩ አቅጣጫዎች ትችት ተሰንዝሮባቸው ነበር። ይህንን መነሻ አድርጎ ስለ ቪላ አልፋ አጠቃላይ ሁኔታ ደራሲና ጋዜጠኛ በዓሉ ግርማ በግንባታው ማገባደጃ ላይ «የ‘ቪላ አልፋ’ አዲሱ መልክ» በሚል ርዕስ በ1961 ዓ.ም አንድ ዘገባ በመነን መጽሔት አቅርቦ ነበር።

እንደ በዓሉ ግርማ ሪፖርት፤ አንዳንዶች “ተርፎት፣ የሚሠራውን ቢያጣ ለመመጻደቅ ያደረገው ነገር ነው” ይላሉ። ሌሎች “አፈወርቅ ከአካባቢው ውጭ ወይም በላይ ሆኖ በራሱ የፈጠራ ዓለም ውስጥ ለመኖር የሚጥር ሰው በመሆኑ ነው እንዲህ ያለውን ቪላ የሠራው” በማለት ይናገራሉ። “ግላዊ ልዩነቱን ለመግለጽ ያደረገው ነገር ነው” የሚሉም አሉ። እርሳቸው ግን “ይህን የመሰለ ቤት የሠራሁበት ምክንያት አለኝ። የሠራኋቸው ሥዕሎች በተሠሩበት አካባቢ እንዲታዩ ለማድረግ ሲሆን፣ እንዲሁም እንግሊዝ ሀገር ተማሪ ሳለሁና በታላላቅ የአውሮፓ ከተማዎች እየተዘዋወርኩ ሥዕል በምሠራበት ወቅት፣ ብዙ ሠዓሊዎች ቤታቸው ይጋብዙኝ ነበር። አሁንም በተራዬ እዚህ በመጋበዝ አንድ ኢትዮጵያዊ ሠዓሊ እንዴት እንደሚኖር ለማሳየትና ከዚህም አልፎ ከሀገራችን የታሪክ ቅርስ ጋር ለማስተዋወቅ ነው። እንግዶቼ በውብ ነገር ተከበው ጊዜያቸውን እንዲያሳልፉ ከማድረግ ሌላ የዕለት ኑሮዬን እንዴት እንደማሳልፍ እንዲያውቁም ጭምር ነው” ሲሉ ነው የገለፁት።

የራሳቸውን ምስል እንዲህ ስለዋል

“ማንኛውም ነገር ከተፈጥሮ ጋር በመዋሀድ በኅብረ ቀለሙና በአቀማመጥ አቅዱ ለአእምሮ ዕረፍትና ሰላምን ካልሰጠ አእምሯችን ወደ ከፍተኛ ደረጃ የሚመራ ነገር የመፍጠር ችሎታ ሊኖረው አይችልም። ከተፈጥሮ ኅብረት ጋር ሥራችንንና ኑሯችንን ለማስተባበር ካልሞከርን ውበትን ለመፍጠር አንችልም። ለኔ ከፍተኛው ምኞቴ ይህ ነው – ኅብረት ከተፈጥሮ ጋር። ይህንን ከፍተኛ ምኞት ለመግለፅ የምፈልገው በምሠራቸው ሥዕሎች ብቻ ሳይሆን በአኗኗሬም ጭምር ነው” ማለታቸውን ጋዜጠኛና ደራሲ በዓሉ ግርማ አስፍሯል።

 “ቪላ አልፋ” አንድ ሺ ሜትር ካሬ ላይ ነው የተሰራው። የተሰራውም በአሥር ዓመት ፕላን መሠረት ሲሆን፤ ቤቱን ለመሥራት ከሚሸጧቸው ሥዕሎች ዋጋ አንድ ሦስተኛውን ለዚህ ፕላን ቆጥበው ነበር። ሆኖም የቆጠቡት ገንዘብ ስላልበቃቸው ከአዲስ አበባ ባንክ ብድር መውሰዳቸውን አትቷል። ቤቱን የአፄ ፋሲልን ግንብ አስመስለው ለመስራት ያነሳሳቸውን ነገር ሲገልጹለትም፣ “ስለ አፄ ፋሲል ግንብ ያለኝን አድናቆት ለመግለጽና ይህ የጥንት ቅርሳችን ተሻሽሎ ለዘመናይ ኑሮ ለመዋል መቻሉን ለማሳወቅ ነው። አዎን የኮራና የከበረ ቅርስ እያለን የቤት ፕላን ከውጭ የምንቀዳበት ምክንያት አይታየኝም” ብለዋል። በዓሉ ስራዎቻቸውን በከፍተኛ አድናቆት ነው የተመለከታቸው። ለምሳሌ “የሰሜን ተራራ” ስለተባለው ሥዕላቸው ሲጽፍ፤ «ኅብረ ቀለሙ ልብ መስጦ፣ ዓይን ማርኮ፣ የአእምሮ ሰላም የሚፈጥር…» ማለት ያወድሰዋል።

የሚመለከታቸው አካላት ምላሽ

ከዚህም በላይ የሚነገርለት «ቪላ አልፋ» ዛሬ ምን ደረጃ ላይ ነው? ዕድሳቱ ለህዝብ ዕይታ የማይበቃው ስለምንድን ነው? ጥያቄያችን ሆነ። በየደረጃው ያሉ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላትን ለማነጋገር ስንነሳ በቅድሚያ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ቢሮን ነው ያንኳኳነው። በባለስልጣኑ የብሔራዊ ሙዚየም ዳይሬክተር አቶ ኤፍሬም አማረ እንዲህ ሲሉ መለሱልን። «መዘግየቱ የማይታበል ነው፤ እኛም ይሰማናል። ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚሰነዘርብንን ጥያቄ ይዘህ ነው የመጣኸው። እንዲያው ከቅድመ ሂደቱ ሁኔታውን ባብራራልህ ከቪላ አልፋ እድሳት ቀድሞ የነበረው ሁኔታ ጊዜ የሚወስድ ነበር። እንደሚታወቀው የዓለም ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ ሚያዚያ 2/2004 ዓ.ም ላይ በድንገት አረፉ። የእርሳቸው ማንነትና ስራዎቻቸው በዓለም ደረጃ የሚታወቅ ስለሆነ ወዲያው ህይወታቸው እንዳለፈ ቤታቸውና ንብረቶቻቸው ላይ ጥበቃ ማድረግ ነው የተጀመረው። ለዚህም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሰው መድቦ ንብረት ማስከበሩ ከተረጋገጠ በኋላ የህግ ሂደት ነው የቀጠለው። ምን አላቸው? ማን ነው ወራሽ? ምን፣ ለማን… የሚሉትን ጉዳዮች ማጣራት ተከተለ። ይህም ረጅም ጊዜ ወስዷል። የባንክ፣ የኢንሹራንስ፣ የአክሲዎኖችን ጉዳይም ማጣራት ሌላው ስራ ነበር። ከፌዴራል ፍርድ ቤት፣ ከቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን፣ ከብሔራዊ ሙዚየም፣ ከአርቲስቶች የተውጣጣ ኮሚቴ ነው ሥራውን የሰራው። ኮሚቴው ንብረቶቻቸው ተለይተው፣ ተቆጥረው በአግባቡ ተመዝግበው እንዲቀመጡ አድርጓል።»

 አቶ ኤፍሬም አማረ ይህን እያሉ ባለ 421 ገጽ ዶሴ ፊቴ አቀረቡልኝ። በወፍ በረር ገለጥለጥ አድርጌ ቃኘሁት። ደቃቋ የቀለም ብልቃጥ ሳትቀር የተመዘገበበት ይህ ዶሴ፤ ብርቅና ድንቅ ስዕሎቻቸውን፣ አልባሳታቸውን፣ የስጦታ እቃዎቻቸውን፣ ሽልማቶቻቸውን፣ የምስክር ወረቀቶቻቸውን፣ መጽሐፎቻቸውንና ሌሎች ውድና በዋጋ የማይተመኑ ንብረቶቻቸውን ይዟል። እያንዳንዱ ገጽ በቁጥር ዝርዝር መረጃ የሰፈረበት ሰነድ ራሱ እንደ ቅርሶቹ ሁሉ ክብደት አለው። ሌላው የህግ ሂደቶችን ሰንዶ የያዘው ጥራዝም ብዙ ቁምነገሮችን ይዟል። ባለስልጣኑ እየተከተላቸው ያሉ አግባቦችንና ጥንቃቄዎችን ለመረዳት በቂ ሆነልኝ።

 ቤቱ እድሳት የሚያስፈልገው በመሆኑ መንግስት በመደበው ሁለት ሚሊዮን ያህል ብር ካለፈው ዓመት መጨረሻ ጀምሮ በተመረጠው ድርጅት አማካኝነት ሥራው እየተከናወነ መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ አማካሪው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምህንድስና ኮሌጅ መሆኑን ተናግረዋል። መኖሪያ ቤታቸውን፣ የሥዕል ስቱዲዮኣቸውን፣ ግቢያቸውን ሁሉ የማደስ ሥራ እየተሰራ ነው። በዚህ ሂደት ግን ከጅምሩ ቅርሶቹ እንዳይጉላሉ፣ ለብልሽትና ለጥፋት እንዳይዳረጉ ጥብቅ ጥንቃቄ ተደርጓል ብለዋል። ስዕሎቹ፣ ቅርሳ ቅርሶቻቸው፣ አልባሳታቸው፣ መገልገያ ቁሳቁሶቻቸው ሳይቀሩ ቀድሞ በነበሩበት ቦታና ሁኔታ እንዲቀመጡ የሚደረግ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ኤፍሬም፤ እርሳቸው ባስቀመጡት አግባብ መቀመጡ ትርጉም ይሰጣል ተብሎ በመታመኑ መሆኑን ነግረውናል። ይህን ለማድረግ ደግሞ ዕቃዎቹ ለእድሳት ከመነሳታቸው በፊት በቪዲዮና በፎቶግራፍ መቀረጻቸውን ተናግረዋል።

 ጥገናው ካለቀ በኋላ ቪላ አልፋ መቼ ለዕይታ እንዲበቃ ይደረጋል? እንዴት ይተዳደራል? የጉብኝቱ ሥርዓትስ በምን መልክ እንዲሆን ታስቧል? ለሚሉ ተከታይ ጥያቄዎቼ መልሳቸው አጭር ነው። «የህግ ማዕቀፍ ይኖራል። መንግስት ያስተዳድረው፣ በቦርድ ይመራ፣ ራሱን ችሎ ይንቀሳቀስ፣ ህዝባዊ ተቋም ይሁን ወዘተ የሚለውን ለይቶ ውሳኔ የሚሰጥበት ረቂቅ ጥናት እየተዘጋጀ ነው። ምን አይነት ባለሙያ እንደሚያስተዳድረውና እንዲሚሰራበት በዝርዝር ጥናቱ አካተናል። ይህ ሰነድ በመንግስት ከፀደቀ በኋላ ለህዝብ ይፋ ይሆናል። ጉብኝቱም ይጀመራል ማለት ነው። ይህን ለማድረግ ብዙ ጊዜ ላይወስድ ይችላል። ዞሮ ዞሮ ቅርስነቱን በሃላፊነት ተረክበን እያሳደስነው፣ እያደራጀነው ነው።»

በመጨረሻም «ኮንትራክተሩን ጫና የምናደርግበት በጥንቃቄ እንዲጠግን ነው። እናውቃለን መቆየቱ ህብረተሰቡን ውዥንብር ውስጥ ከቶታል፤ ጥቂት መታገስ ካለ ጥሩ ሙዚየም ይኖረናል ብሎ ማሰቡ ነው የሚጠቅመው። ከኮንትራክተሩ ጋር እስከ ግንቦት መጨረሻ ተጠናቆ እንደምንረከብ ተማምነናል። ባለ ስልጣኑ ትልቅ ሃላፊነት እንደተጣለበት፣ ተጠያቂነት እንዳለበትም እንረዳለን፤ ነገር ግን አንዳንዶች እንደሚያስቡት አልተኛንም።

 ከቪላ አልፋ እድሳት ጋር በተያያዘ አማካሪው፣ ኮንትራክተሩም ሆነ ባለስልጣኑ ያልተግባቡበት ጉዳይ የለም። እንደተረዳነው ስለመዘግየቱ አንዱ በአንደኛው ላይ ጣቱን የሚቀስርበት ሁኔታ የለም። እየተናበቡ መጓዛቸው መልካም ነገር ሆኖ፤ መዘግየቱ ግን በህዝቡ ዘንድ ቅሬታ ማሳደሩ አልቀረም። እነሱም ይህንን አምነዋል። ኮንትራክተሩስ በዚህ ላይ ምን ይል ይሆን? የቪላ አልፋን አጠቃላይ እድሳት በውል ተረክቦ ስራውን እያገባደደ ያለው ሻርፕ ራይዝ ኢንጂነሪንግ ሲስተምስ ሶልሽን ፒ.ል.ሲ ነው። የፕሮጀክቱ ማናጀር ደግሞ አቶ ሸምሰዲን ዳውድ ናቸው። የመጀመሪያ ጥያቂያችን ጥገናው ለምን ዘገየ? ነው። እንዲህ መለሱ፤

«ይህ የብዙዎች ጥያቄ ነው። ጋዜጠኞች፣ የአካባቢው ማህበረሰብ፣ የመንግስት አካላት፣ የጥበብ አድናቂዎች ደጋግመው ያነሱብናል። እኛም በውላችን መሰረት በመጪው ግንቦት ወር ጨርሰን ለማስረከብ ከፍተኛ ፍላጎት አለን። እድሳቱ እንደማንኛውም ቤት በቀላሉ የሚከናወን አይደለም። ይዞታውን ሳይቀይር ቀድሞ በተሰራበት ጥሬ እቃ ልክ እንደነበረ አድርገን ነው እያደስን ያለነው። ከጊዜ ይልቅ የእድሳቱ ጥንቃቄ ላይ ነው የበለጠ ትኩረታችን። የአገር ቅርስ ነው፣ የአገር ታሪክ ነው የሚቀመጥበት። ይህን ስል በጥገና ሂደቱ ላይ አንዳንድ መሰናክሎች እንዳሉም ልብ ማለት ይገባል። ለምሳሌ እያቆራረጠም ቢሆን ከመስከረም አስከ ህዳር ድረስ ዝናብ አላቋረጠም፤ በዚህም ምክንያት ዋናው ቤት ጣራውን ሸራ እያለበስን አንዳንዴም ዝናቡ አየል ሲል እያቋረጥን ነው የሰራነው። ቤቱ ካለው እድሜ አንጻር ቀደም ባለው ጊዜ መታደስ ይገባው ነበር፤ ያ ባለመሆኑ ተጎድቶ ነው ያገኘነው። ተጨማሪ ሥራና ትዕዛዝ ሲመጣ ደግሞ የእድሳቱን ጊዜ ወደፊት ሊገፋው የሚችል ይመስላል፤ እኛ ግን ባሰብነው ጊዜ ለመጨረስ እየጣርን ነው»

 አጠቃላይ የጥገና ሂደቱ ምን ላይ ደረሰ? ቀጣዩ ጥያቄያችን ሆነ። አቶ ሸምሰዲንም ሲመልሱ «በቪላ አልፋ ውስጥ የነበሩ አጠቃላይ ቅርሶች በግቢው ውስጥ በጊዚያዊነት በሰራነው ቤት በጥንቃቄ እንዲዛወሩ አድርገናል። ጊዚያዊ ቤቱም ለቅርሶቹ ጥንቃቄና ጥበቃ አመቺ ሆኖ የተሰራ ነው። የሰርቪስ ቤቱን እድሳት ጨርሰናል። የዋናው ቤት ጣራ በዝገትና በፍሳሽ የቤቱን ግርግዳ ጭምር በማበላሸት ላይ ነበር፤ እሱን ቀይረናል። የሚለወጡ እንጨቶችን እና ሌሎች የቤቱን የቀድሞ ሁለንተና የሚገልጹ ቁሶችን አሟልተን ነው እያደስን ያለነው። ወለሉንም ሰርተናል። በአሁኑ ወቅት ኮርኒስ እና ግርግዳዎችን በመስራት ላይ ነን። ዋና ዋና የሚባሉ ስራዎች አልቀዋል ማለት ይቻላል፤ ከአጠቃላይ ሥራው ከ70 እስከ 75 በመቶ ተጠናቋል። አሁን የያዝነው ሥራ ሲያልቅ ቅርሶቹን ወደነበሩበት ቤት በነበሩበት ሁኔታ ማስቀመጥ ነው። ሌላ ያልጠበቅነው እክል ካልገጠመን በስተቀር ይህ በአጭር ጊዜ ይሆናል ብለን እናስባለን» ብለዋል። አስፈላጊ ከሆነ የስራውን ሂደት መከታተልም ሆነ አሁን ያለበትን ሁኔታ መጎብኘት እንደሚቻልም ገለጹልን።

 ለበርካታ ሃገራት የኢኮኖሚ ምንጭ ከቱሪዝም የሚገኝ ገቢ ነው። ለዚህ ደግሞ ቪላ አልፋ ታሳቢ ሊሆን እንደሚገባ የታመነ ነው። ሰርፀ ፍሬስብሐት የኢትዮጵያ ቱሪዝም ንግድ ሥራ ድርጅት ም /ዋና ዳይሬክተር ናቸው። ቪላ አልፋን በተመለከተ ድርጅታቸው ምን ሚና እንዳለው ላቀረብኩላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ «እንደሚታወቀው የዓለም ሎሬት ክብራችንን ከፍ ከሚያደርጉ ታላላቅ የጥበብ ሰዎች አንዱ ናቸው። ጥበብን ሲጠበቡ ኖረው አልፈዋል። እኛ ደግሞ ስራዎቻቸውን በአክብሮት ተንከባክበንና ጠብቀን በማቆየት ትውልዱ እንዲማርባቸው፣ እንዲያውቃቸውና ጥቅም እንዲያገኝባቸው ማድረግ ኃላፊነት አለብን። አዲስ አበባ ውስጥ ያሉንን የቱሪስት መስህቦች ለማወቅና ለመለየት የሚያስችል ጥናት ላይ ነን። ምን የቱጋ እንዳለ የሚያሳይ አመላካች ካርታ /resource mapping/ እያዘጋጀን ነው። በዚህ ሥራ ከለየናቸው ታሪካዊ ቅርሶችና የቱሪስት መስህቦች ውስጥ ቪላ አልፋ አንዱ ነው። ይህ ደግሞ ለቱሪስቶች የተመቸ ነው የሚሆነው። የማስተዋወቁም ስራ የኛ ነው» ብለዋል።

 «ተፈጥሯዊ ሁኔታን ለመጎብኘት፣ ባህልን ለማወቅ፣ የከተማ ግብይትን፣ ፋስቲቫሎችን፣ ኮንሰርቶች ላይ ለመታደም የሚገቡ ቱሪስቶች እንዳሉ ሁሉ፤ ጥበብን፣ አርትን ብለው የሚመጡም አሉ። ለቱሪስቶች በከፍተኛ ደረጃ ወደ አዲስ አበባ መምጣት ቪላ አልፋ ትልቅ ምክንያት እንደሚሆን እንገምታለን። ማንነታችንን እና ታሪካችንን በዓለም ሎሬት የጥበብ ስራዎች ውስጥ እናሳያለን ብለን እናምናለን» ያሉት አቶ ሰርፀ፤ «በስማቸው የገበያውና የፕሮሞሽኑ ስራ የእኛ ኃላፊነት ነው። ዘመኑን በዋጀ የቴክኖሎጂ ጥበብ በዓለም እንዲተዋወቅ እናደርጋለን። ስለ የዓለም ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ ዓለም ያውቃል። ሥራቸውና ማንነታቸው ለዓለሙ ማህበረሰብ አዲስ አይደለም፤ ከቪላ አልፋ ጋር በተገናኘ ግን ማስተዋወቁ ተገቢ ይሆናል። እርግጠኛ ነኝ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ተግባሩን እንደጨረሰ ከኢትዮጵያ ህዝብ አልፎ በተለያዩ አገራት የሚገኙ የአርት አፍቃሪዎችና የሎሬት አድናቂዎች ቪላ አልፋን ይዋጁታል» ሲሉ ሀሳባቸውን አጠቃለዋል።

 የጥበብ ሰዎቻቸው ካለፉ በኋላ ዓለም እንዲያስታውሳቸው የሚያደርጉ አገሮችም ጥቂት አይደሉም። በሙዚቃ፣ በቴያትር፣ በሲኒማ እና በሥዕል ሥራዎች የሚታወቁ ዜጎቻቸው ካለፉ በኋላ ሥራዎቻቸው ብቻ ሳይሆኑ ቤታቸውና መገልገያ ቁሳቁሳቸው ጭምር ለእይታ እየቀረበ ከፍተኛ የቱሪዝም ገቢ እያስገኘላቸው ነው። ለምሳሌ በአሜሪካን አገር የታዋቂው የሙዚቃ ሰው የኤልቪስ ፕሪስሊን መኖሪያ ቤት በዓመት 670 ሺ ያህል ህዝብ የሚጎበኘው ሲሆን፤ ከጉብኝቱም ከ270 ሚሊየን ዶላር በየዓመቱ እንደሚገኝ ተዘግቧል።  የ20ኛው ክፍለዘመን ምርጥ ሰው የሆኑት እጅግ የተከበሩ፣ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ሁለንተናዊ ማንነታቸውን የሚገልፀውን ቪላ አልፋ በገጸ በረከትነት ለኢትዮጵያ አውርሰዋል። ይህን ቅርስ አጭቆ የያዘ ህንጻ ጠብቆና ተንከባክቦ ለቀጣዩ ትውልድ የማስተላለፉ ተግባር የዚህ ትውልድ ኃላፊነት ነው። አጽማቸው ባረፈበት የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የተሰራላቸው ሐውልት ማንነታቸውን የሚያመላክት መታሰቢያ ቢሆንም፤ ከቪላ አልፋ ሌላ ስማቸውንና ክብራቸውን የሚመጥን መታሰቢያ ሊቆምላቸው እንደሚገባም ማሰቡ አይከፋም። በአጠቃላይ በመንግስት ስር ያሉ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ተቋማት የሚያከናውኑት ተግባር እንዳለ ሆኖ፤ በትውልድ ቅብብሎሽ ሂደት ውስጥ ከሚያጋጥሙ መልካም ታሪኮች አንዱ ይህ መሆኑን አስበን የጋራ ሃብትና ቅርሳችንን እንጠብቅ ነው መልዕክታችን።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top