ጣዕሞት

ብሔራዊ ቴያትርን ከውድቀት ለመታደግ ጥሪ ቀረበ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴያትርን እያጋጠመው ካለው የውድቀት ጉዞ መታደግ ይቻል ዘንድ ለጥበብ ባለሙያዎችና አፍቃሪዎች ዳግም ጥሪ የቀረበው ባለፈው ሳምንት በተካሄደ ሁለተኛ ዙር የውይይት ፕሮግራም ነው።

ቴያትር ቤቱን እንዴት እናቃና የሚል ስሜት ያደረባቸውና የቴያትር ቤቱ ባለሙያዎች፣ ተዋንያን፣ አዘጋጆች፣ ተመልካቾችና ጋዜጠኞች በተገኙበት በተካሄደው ውይይት፤ ቴያትር ቤቱ በአስተዳደርም ሆነ ዋና ተልዕኮው በሆነው በኪነጥበብ አቅርቦቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከመ መምጣቱ ተደጋግሞ ተነስቷል። አዳዲስ ቴያትሮች አለመፈጠራቸው፣ ተዋንያንና ሙዚቀኞች በቴያትር ቤቱ አለመቆየታቸው፣ የቀደመ ስሙን የሚጠብቅ የሙዚቃ ሥራ አለመታየቱ የውድቀቱ ማሳያዎች መሆናቸው ተጠቁማል። ይህም የሆነው በቴያትር ቤቱ ኋላ ቀር አደረጃጀትና የአስተዳደር መዋቅር ልልነት መሆኑ በውይይቱ ወቅት ተወስቷል። አስተዳደሩ ለቴያትር ቤቱ ሰራተኞች ዕድገትም ሆነ ለቁጥጥር አመቺ ባለመሆኑ የቀድሞ ስሙንና ዝናውን እያጣ መምጣቱም ነው የተነገረው።

በዕለቱ አንጋፋዎቹ የመድረክ ባለሙያዎች አርቲስት ፍቅርተ ደሳለኝና አልጋነሽ ታሪኩ ያለፉበትን የኪነጥበብ ጉዞና መሰል ባለሙያዎች የከፈሉትን መስዋዕትነት አስመልክቶ ልምዳቸውን በስፋት አካፍለዋል። በአንድ ወቅት የቴያትር ቤቱ ስራ አስኪያጅ፣ ተዋናይ እና አዘጋጅ የነበሩት ተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሠሠ በበኩላቸው ቴያትር ቤቱን ለማዘመንና የተቋቋመበትን ዓላማ እንዲያሳካ ለማድረግ ከፍተኛ ትግል ሲያደርጉ እንደነበር አስታውሰው፤ በዚህ ዘመን መዳከሙ እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል። ቀደም ባለው ዘመን ወደ ጥበቡ ዓለም የሚገቡ ሁሉ ከገንዘብ ጥቅም ይልቅ ለስሜታቸው ሲሉ በፍቅር ይሰሩ እንደነበር አውስተው ይህንን ለማምጣትም መጀመሪያ የጥበብን ዋጋ መረዳት ይገባል ብለዋል።

 በዕለቱ የውይይት መነሻ ሃሳብ ካቀረቡት ባለሙያዎች አንዱ ዶ/ር ሱራፌል ወንድሙ፤ «ቴያትር ቤቱን ለመታደግ አንድ ዘመናዊ የሆነ አስተዳደራዊ ማዕቀፍ ያስፈልገዋል» ብለዋል። መንግስት ያስተዳድረው፣ በራሱ ገቢ ይተዳደር፣ በቦርድ ይመራ የሚሉ አማራጮችን በመያዝ አንድ የጥናት ሰነድ አዘጋጅቶ ለመንግስት በማቅረብ አጸድቆ ቴያትር ቤቱን ከውድቀት መታደግ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። በዚሁ የውይይት መድረክ ላይ በኪነጥበቡ መስክ ለዱክትርና ማዕረግ የሚያበቃቸውን ጥናት በደቡብ አፍሪቃ በማከናወን ላይ የሚገኙት አቶ ስሜነህ አያሌው የግል ተሞክሯቸውንና ተጨማሪ የመወያያ ሃሳቦችን አቅርበዋል። ከተሳታፊዎች በቀረቡ ጥያቄዎችና ሃሳቦች ላይም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በመጨረሻም የቴያትር ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ማንያዘዋል እንደሻው የመወያያ ሃሳብ ያቀረቡትን ባለሙያዎችና ተሳታፊዎችን አመስግነዋል። በዕለቱ የቀረቡ ምክረ ሃሳቦችን መነሻ በማድረግና ቴያትር ቤቱ በዕለት ተዕለት የሚገጥሙትን ተግዳሮቶች አስወግዶ ለስሙ የሚመጥን ሥራ ለመሥራት የሚችልበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ከመንግስት ጋር እንደሚሠሩ ተናግረዋል። ለዚህም ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ባለሙያዎችና ኃላፊዎች ጋር በመሆን ተገቢውን የውሳኔ ሃሳብ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመንግስት እንደሚያቀርቡ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የካቲቶችን የሚያስታውስ ዐውደ ርዕይ ተከፈተ

ሰሞኑን ‹‹ሦስቱ የካቲቶች›› የተሰኘ የፎቶግራፍ ዐውደ ርዕይ በይፋ ተከፍቷል። ይኸው የካቲት 1888 ፣ የካቲት 1929 እና የካቲት 1966ትን የሚያስታውሰው ዐውደ ርዕይ ከየካቲት 1 – 30/2011 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ ነው።

 ዐውደ ርዕዩ በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ሥር በሚገኘው የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የሥነ ጥበባት ማዕከል የተዘጋጀ ነው። ከማዕከሉ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በመክፈቻው ሥነ ሥርዓት “የ1888 ወርሃ የካቲት የአድዋ ድልና ሥነ ጥበብ” የተሰኘ ጥናታዊ ጽሑፍ በአቶ ሰርፀ ፍሬስብሐት ቀርቧል። ሚስተር ኢያን ካምቤል እና ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ ስለ1929ኙ የየካቲት ጭፍጨፋ አስከፊነትና ስለተደረገው ተጋድሎ፤ አቶ አሰግደው ሽመልስ በበኩላቸው ስለ1966ቱ አብዮት ፍንዳታና ስለተከተለው የፖለቲካ ምስቅልቅል ጽሑፎችን አቅርበዋል፤ ውይይትም ተደርጎባቸዋል።

 ከውይይቱ ቀጥሎ በብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የሥነ ጥበባት ማዕከል የተሰናዳው ዐውደ ርዕይ በታዳሚዎች ተጎብኝቷል። ዐውደ ርዕዩ ዘወትር ከሰኞ እስከ ዓርብ ቀኑን ሙሉ ለህዝብ ክፍት እንደሚሆንም ማዕከሉ አስታውቋል።

«መጫሚያ አልባው ንጉሥ»

መጽሐፍ ተመረቀ

«መጫሚያ አልባው ንጉሥ» በሚል ርዕስ ስለ አጼ ቴዎድሮስ የተዘጋጀው የትርጉም መጽሐፍ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ በብሔራዊ ቤተ መጽሐፍትና ቤተ መዛግብት አዳራሽ ለምረቃ በቅቷል፡፡

በጀርመን ሬዲዮ (ዶቼ ዌሌ) የአማሪኛው ፕሮግራም ጋዜጠኛዋ ሸዋዬ ለገሠ ተተርጉሞ ለህትመት የበቃው ይህ መጽሐፍ፤ እንግሊዛዊው ፍሊፕ ማዝድን 10 ዓመት በፊት (The Barefoot Emperor) በሚል ርዕስ በእንግሊዝኛ ያሳተመው ነው፡ ፡ ፍሊፕ አጼ ቴዎድሮስን በቅርበት ያዩ፣ የተናገሩትን የሰሙ ሰዎች የተጻፉትን ማስታወሻ መሰረት አድርገው የጻፉት ስለሆነ ለመጀመሪያ ምንጭነት እንደሚያገለግል የታመነበት መሆኑን ታውቋል:: መጽሐፉ፤ ንጉሡን ከዚህ ቀደም ከጀግንነታቸው ባሻገር ይታወቁበት የነበረውን ቁጠኝነትና አምባገነንነት ባህሪ ሌላ ሰዋዊ ባህሪያቸውንና ስብዕናቸውን የሚያሳይ መሆኑ በምረቃው ወቅት ተገልጿል፡፡

በመጽሐፉ ውስጥ የተለያዩ ሰዎች እንደየስሜታቸው ንጉሡን ሲገልጿቸው ማወደስ፣ መሳደብ፣ መተቸትና ማመስገን እንዳለበት ተብራርቷል፡፡

«የተለያዩ መጻሕፍቶችን ባነብም አጼ ቴዎድሮስ ማንነታቸው በሌላ መልኩ መገለፁ ስላስገረመኝና የአጻጻፍ ስልቱም ስለማረከኝ ለመተርጎም ተነሳሳሁ» ስትል ለዝግጅት ክፍላችን የገለጸችው ጋዜጠኛ ሸዋዬ፤ መጽሐፉ የመጀመሪያ እማኞችን መሰረት አድርጎ የተጻፈ ስለሆነ ጠቀሜታው የጎላ እንደሚሆን ተናግራለች፡፡ ለማገናዘቢያ፣ ለጥናትና መርምር እንዲሁም ለታሪክ ጸሐፊዎች እንደሚጠቅም እምነቷን ገልጻለች፡፡ በቀጣይ ሌሎች ታሪክ ነክ መጻሕፍቶችን እያዘጋጀች መሆኑንም ተናግራለች:: 213 ገጾችና 81 ምዕራፎች ያለው ይህ መጽሓፍ በ100 ብር ዋጋ በመሸጥ ላይ ይገኛል፡፡

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top