አድባራተ ጥበብ

የዶክተር እጓለ እሳቤዎች

በባለፈው ክፍል እንደተገለጸው የዶ/ር እጓለ ገብረዮሐንስ ታትመው ገበያ ላይ የዋሉት መጻሕፍት ሁለት ብቻ ናቸው። ሌላ ስለመኖሩ እርግጠኛ አይደለሁም። ሁለቱ መጻሕፍት በዓላማ የተለያዩ ቢመስሉም በይዘታቸው ግን ተመሳሳይነት አላቸው። ይኸውም ሥነ-ምግባራዊ በጎነት ላይ ያተኮሩ መሆናቸው ነው። አንደኛው ሥነ ምግባራዊ በጎነትን ከትምህርት እና ከስልጣኔ ፍልስፍና ጋር አዋህዶ ሲያቀርብ ሌላኛው ደግሞ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባርን ከካንት ፍልስፍና ጋር አዋህዶ ያቀርብልናል። የሁለቱም መዳረሻ፣ እንዲሁም ማዕከላዊ ትኩረት ግን አንድ ነው። ማዕከላዊው ባለ ጉዳይ ሰውነት ነው፤ “ሰውን ወደ ሰውነት ክብሩ ከፍ ማድረግ” ሲሆን፣ መዳረሻቸው ደግሞ የሰለጠነ እና ምክንያታዊ ማኅበረሰብ ግንባታ ላይ ያተኩራል። የሊቁም ምኞት በጥበብና በሥነ ምግባር እንዲሁም በማኅበራዊ እሴቱ ያልተረበሸ፣ የተስተካከለ እና በምክንያታዊነት የሚያምን ማኅበረሰባዊ ውቅር መገንባት ነው። ይህንንም በሚወዳት አገሩ በኢትዮጵያ እውን ሆኖ ማየት ነው። ምናልባትም በበርካታ የአውሮፓ ስፍራዎች ተዟዙሮ ያየውን ማህበራዊ ምክንያታዊነት በፖለቲካዊ፣ ማህበረ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ እሴቶች እንዲሁም አስተሳሰባዊ ዝብርቅርቅ ውስጥ ለሚገኘው ኢትዮጵያዊ ህብረተሰብ የሚመራበትን የዘመናዊ አስተሳሰብ መንገድ ለመጠቆም በማሰብ ያዘጋጃቸው ይመስላሉ። እርሱ በነበረበት ዘመን የነበረው ስጋት እና ተምኔት የእኛንም ዘመን የሚመለከት በመሆኑ የሊቁን ሐሳቦች ማስታወሱ አስፈላጊ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። በሚቀጥሉት ክፍሎችም እንደ ታተሙበት ቅደም ተከተል መጽሐፎቹን ለመዳሰስ እሞክራለሁ።  

2. “የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ” (መጀመሪያ 1956/፲፱፻፶፮ ዓ.ም የታተመ)

  የመጽሐፉ ርእስ እንደሚያመለክተው የከፍተኛ ትምህርት ጉዳይ ሲሆን በንዑስ ርእስነት የቀረበው ማመልከቻ ደግሞ “የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ ሲመሠረት በትልቅ ግርማ ለተነሣው ኢትዮጵያዊ መንፈስ እጅ መንሻ ይሆን ዘንድ በአዲስ አበባ ራዲዮ የቀረቡ ንግግሮች” የሚለው ነው። በወቅቱ እንግዲህ በታላቅ ግርማ የተነሳ ኢትዮጵያዊ መንፈስ ነበረ ማለት ነው። ያ መንፈስ ደግሞ፣ መንፈስ እንደፈለገው ይነፍሳልና፣ አነፋፈሱ ትክክለኛ መንገዱን ይይዝ ዘንድ የልሂቃኑን፣ የታላላቆቹን ይሁንታ ይሻልና ለዚያው ይሆን ዘንድ በመጽሐፉ ውስጥ የምናገኛቸውን ምክረ ሐሳቦች ለእጅ መንሻነት አበርክቶልናል ማለት ነው። ገና የመጽሐፉን የውስጠኛውን የሽፋን ገጽ ሲገልጡት አንድ ጥቅስ ይገኛል። የዳንቴን ቅኔ በውብ ቃላት ተርጉሞልናል። ይህንን ”Epigraph” ለምን እንደመረጠ ለመረዳት መጽሐፉን መጨረስ ያስፈልጋል። ቅኔ አዋቂው የመጽሐፉ የመጀመሪያው ገጽ ላይ የሚከተሉትን የዳንቴን ቃላት ማስቀመጡ በርግጥም ተገቢ ነው።  ወጣቶች አነሱ ግምባራቸውን፤ ሊጠይቁ እኛን “ታውቁት እንደሆነ እስኪ ንገሩን ባቀበቱ ዙሪያ መንገድ ይኖርን፤ ቪርጂልዮ መለሰ እንዲህም አላቸው መስሏችሁ ይሆናል እኛ የምናውቀው መንገደኞች ነን እኛም እንደናንተው ትንሽ ቀደም አልንይ የደረስን አሁን ነው መንገዳችን ሌላ፤ የባሰ ከናንተው (ቀጥ ያለ አቀበት፣ እንቅፋት የሞላው) እንግዲህስ መውጣት ለኛ መቅለሉ ነው። እነዚህ ስንኞች ግዝፍ ነስተው የሚያስተጋቡትም የሰው ልጅ ትክክለኛውን መንገድ በመፈለግ የሚኳትነውን የሊቁ መጽሐፍ ሙሉ ይዘቱን ሲያነቡት ነው። ሕይወት ቀጣይ ነችና ትክክለኛው መንገድ በየት በኩል እንደሆነ በማስተዋል መፈለግ ይኖርበታል። ለዚህም ለኢትዮጵያውያን መልካም መንገድ ጠቋሚ ይሆን ዘንድ ይህንን ድንቅ መጽሐፍ እጅ መንሻ አድርጎ አበረከተልን። የመጽሐፉ ማውጫ 17 ንዑሳን ርእሶችን የያዘ ሲሆን ትምህርት እና ሥልጣኔ የሚሉ ቃላት በተደጋጋሚ የርእሶቹ አካላት ተደርገዋል።  መግቢያው ላይ በመጽሐፉ የቀረቡት ጽሑፎች የሁሉንም አድማጭ አቅም እንዲያገናዝቡ ተደርገው በሬድዮ ንግግር የቀረቡ እንዲሁም በአድማጮች ጥያቄ በጋዜጣ የታተሙ እንደነበሩና ኋላም ላይ ተበታትነው እንዳይቀሩና ባንድ ላይ ተጠርዘው ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆኑ በማሰብ በዚሁ በመጽሐፍ መልክ ቀረቡ። ይኸው እኛም ከዘመናት በኋላ ደርሶን እያነበብነው እንገኛለን።  ለመሆኑ ለምን የትምህርት ጉዳይ ላይ ለመጻፍ አስፈለገ? የዚህ ጥያቄ መልስ የሚገኘው በዚያው በመግቢያው ላይ ነው። “ትምህርት ቀላል ነገር አይደለም። ስለ ትምህርት ያለን አስተያየት ትክክለኛ ከሆነ ማናቸውም የሕይወት ችግሮች ሊፈታ ይችላል። ሰው ከሙሉ የሰውነት ደረጃ የሚደርሰው በትምህርት ነው” ይለንና ታላቁን የግሪክ ፈላስፋ ፕላቶን ጠቅሶ የሰው ልጅ ባህርይው በትምህርት፣ በሥርዓት ካልተገራ ከክፉ አራዊት የከፋው አውሬ እንደሚሆን ይነግረናል። በዚህ አነጋገር ሊቁ ሰውን ማዕከል ያደረገውን ሐተታውን በይፋ ይከፍታል። ይህ ትልቁ የመጽሐፉ ዓላማ መሆኑ ነው። የሰውን ልጅ ወደ ሰውነት ክብሩ የሚያደርሰው ርእሰ ጉዳይ ላይ ሐተታ ማቅረብ። ሁለተኛው ዓላማው ደግሞ “ለታላቁ ንጉሣዊ ቸርነት” (ቤተ መንግሥቱን የትምህርት አደባባይ እንዲሆን ላበረከቱበት) መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ነው።  የሊቁ ትልቁ ስጋቱ እዚህ ላይ ይፋ ይወጣል። ምናልባትም እርሱ የነበረበትን ዘመን የሚወክል ነው። ወቅቱ የተለያዩ ኢትዮጵያውያን ወደ ውጭ እየሄዱ ወይም ከውጭ በመጡ መምህራን አማካኝነት ልዩ ልዩ እውቀት፣ ከልዩ ልዩ ባህልና ሃይማኖት እንዲሁም አስተሳሰብ ጋር ይተዋወቁ የነበረበት ነው። እውቀቶችን የማግበስበስ የሰው ልጅ ህሊና ጠባይ እና የእውቀቶችን መብዛት አደጋ፣ የኅሊና ዝብርቅርቅ አስተሳሰብ ፈተና በምን መልኩ ማስታረቅ ይቻላል? የሚለው ጉዳይ ትልቁ የዘመኑ ጥያቄ እንደሆነ እንገምታለን።  አንድ የቆሎ ተማሪ አኮፈዳን በምሳሌነት ያቀርባታል። አንድ የቆሎ ተማሪ ለእለት ጉርሱ የሚሆነውን ምግበ ሥጋ “በእንተ ስማ ለማርያም!” እያለ ይለምናል። በየቤቱ የተለያየ ምግብ ይሰጠዋል። ቆሎ፣ ንፍሮ፣ 

“ይህ አገላለጽ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ የነበረው የግሪኩ ፈላስፋ “የሰው ልጆች በተፈጥሮ አዲስ ነገር የማወቅ ጉጉት ያላቸው ፍጥረቶች ናቸው”

 ዳቦ፣ ሽሮ፣ የድግስ ትርፍራፊ መረቅ፣ ፍትፍት፣ በርበሬ ወዘተ የነካካ እንጀራ ይዞ ይሄዳል። ያች አኮፋዳ ምንድን ነው የያዘችው? ዝብርቅርቅ፣ ቅልቅል። ይህም የአንዳንድ ሰዎችን ህሊና የሚወክል ነው። የተለያየ እውቀት ዝብርቅርቅ ብሎ የሚገኝበት። ግንኮ ህሊና አኮፋዳ አይደለም፤ የሰጡትን ሁሉ ተቀብሎ የሚሰበስብ። “እውነተኛ ጠባዩ ባሕርዩ ሕግ ሥነ ሥርዓት ነው።” ይህም የሚሆነው በትክክለኛው ትምህርት ተኮትኩቶ ካደገ ነው።  ሊቁ ስለሐሳቦቹ ምንጮች ሲናገር ስለ ግል ህይወቱ ትንሽ ምስክር የሚሆን ፍንጭ ይሰጠናል። ይኸውም በአቴና እና በጀርመን በነበረበት ወቅት በርካታ የትምህርት አጋሮች ስለነበሩት ከነርሱ ጋር በመከራከር፣ በመወዳደርና በመወያየት እንዳበለጸገው ይነግረናል። እንዲያውም አብዝሃኛው ሐሳብ እራሱ እንዳልሆነ በኢትዮጵያዊ ትህትና ይነግረናል። (ገጽ 10)  ሁሉም ንግግሮች ባንድም በሌላም “ከትምህርት ፍልስፍና” ጋር ግንኙነት ያላቸው እንደሆኑ ይጠቁመናል። (ገጽ 11/፲፩) በዚሁ ፍልስፍናን ያብራራልናል። የሚታየውን እና የማይታየውን ዓለማት ለመረዳት የሚደረግ ዳሰሳ ወይም ነገረ ጥናት ቢያንስ ፍልስፍናዊ ባህርይ አለው። የሁለቱ ዓለማት መገናኛ ቦታ ደግሞ ሰው ነው። “ሰው በሁለት ዓለማት መካከል የሚገኝ አማካኝ ፍጥረት ነው። በአካሉ የጉልሁ ዓለም ተካፋይ ነው። በመንፈሱ የረ[ቂ]ቁ የዘላቂው ዓለም ተሳታፊ ነው። በሥነ ፍጥረት ላይ የሚጸናው የግዴታ ሕግ በእሱም ላይ ይጸናል። በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ የሚጸናው የነጻነት ሕግ በሱም ላይ ይጸናል።”ይህንን የሰውን ልጅ አማካኝ ስፍራውን እንዲይዝ በርካታ ጥያቄዎችና ማብራሪያዎች ያስፈልጉታል። የነዚህ ጥያቄዎች መልስ የሚገኘው በፍልስፍና ነው። (ገጽ. 12/፲፪) ይህንን የፍልስፍና መንገድ በመከተል የኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ ላይ ሐሳብ ይቀርባል።  በዚሁ ሦስተኛው የመጽሐፉ ዓላማ የዳንቴን ስንኞች ለምን መዋስ እንዳስፈለገው ይገለጥልናል። ከታሪክ መጨረሻ ላይ አይደለንም። ገና ወደፊት መጓዝ ይጠብቀናልና፤ መጀመሪያውም ላይ አይደለንም፤ ከኛ በፊት የቀደሙ ነበሩና። ይህን ወደፊት የሚደረግ ጉዞ የሚወስነው አንድ ማኅበረሰብ ለወጣቱ ትውልድ በሚያስተምረው ትምህርት ነው። ይህንንም ማድረግ የሚቻለው በፍልስፍና፣ በsociology፣ እና በሥነ ልቡና ላይ በሚደረግ ጥናት ላይ ነው። የዚህ መጽሐፍ ዓላማም ከትምህርት ጋር የተያያዘውን ፍልስፍና መፈተሽ ላይ ነው። “በዚህም ድርሰት አንድ ነገር ለማግኘት ብንፈልግ ይህ መሆን አለበት። አንድ ብርቱ ጥሪ ወይም ድምጽ እንዲሰማ ነው። ይህም ድምጽ ሌላ ምንም ሳይሆን የዘመናችን ትምህርት ዘይቤ ወይም ትርጓሜ እንዳለው በሁሉ ዘንድ የታወቀ ይሁን ፤ እንደሌለው ይፈለግለት የሚል ነው።” (ገጽ ፲፭እና ፲፮) የመጀመሪያው ምዕራፍ በዚህ ይደመደማል። እንግዲህ ሰውን ማዕከላዊ ያደረገው ሐተታ የትምህርት ፍልስፍና ላይ ትኩረቱን በማድረግ የሰውን ልጅ ወደ ሰውነት ክብሩ ከፍ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት በሐሳብ ለመደጎም የተጻፈ መጽሐፍ ነው።  “ምክንያታዊ መቅድም” የሚል ርእስ የተሰጠው ሁለተኛው ምዕራፍ የታላቁን የግሪኩን ፈላስፋ አርስጣጣሊስን ሐሳብ የሚያስተጋባውን እና ሐዋርያው ቅዱስ ሉቃስ አቴናውያንን የገለጸባቸውን ቃላት በመዋስ ይከፍተዋል። “ወሰብአ አቴንሰ ወእለ ይነግዱ ኲሎሙ ህየ ባዕድ ትካዝ አልቦሙ ዘእንበለ ዳዕሙ ለአጽምኦ ወነቢብ ዘሐዲስ።” (ገጽ ፲፯) እነዚህ የአቴን ሰዎች ሌላ የልብ ትካዜ የላቸውም። የሚያሳስባቸውና የሚናፍቃቸው ነገር ቢኖር አዲስ ነገር መስማትን እና አዲስ ነገር መናገርን ነው። ይህ አገላለጽ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ የነበረው የግሪኩ ፈላስፋ “የሰው ልጆች በተፈጥሮ አዲስ ነገር የማወቅ ጉጉት ያላቸው ፍጥረቶች ናቸው።” ካለው ጋር የሚስማማ ነው። ይህ የአቴናውያን የእውቀት ጉጉት በሁሉም ረገድ የአውሮፓን ስልጣኔ መሠረት እንዲጥሉ አስችሏቸዋል።  ሊቁ በዚህ መቅድም ውስጥ አንድ ትልቅ ፍልስፍናን ይዞልን መጥቷል። ይኸውም የመንፈስ ውይይት ነው። መንፈስ ወይም አስተሳሰብ ብቻውን አይገኝም። ቢገኝም ብቻውን ሊበለጽግ አይችልም። ከሌላው ከመሰሉ ጋር በመወያየት፣ ራሱን ለሌላው  በመግለጽ ነው። ይህ አስተሳሰቡ በመጽሐፉ ውስጥ ሙሉ ገዥ ሙግት ሆኖ የዘለቀ ነው። መንፈስን ከአስተሳሰብ ጋር ያመሳስለዋል። ይኸውም ማኅበረሰባዊ የአስተሳሰብ ክምችት፣ ማኅበረሰባዊ የጥበብ ውህድ ነው። እናም የመንፈስን ውይይት የጀርመኑን ፈላስፋ ሄግልን Dialectical Idealism ፍልስፍና በመዋስ ያብራራዋል። መጀመሪያ አንብሮ (Thesis) አለ። ይኸም እኔነት ወይም አወንታዊ አቋም ነው። በሌላ በኩል ተቃርኖ (Anti-thesis) ወይም አንጻራዊ መንፈስ፣ ሌላው መንፈስ ነው። ይኸኛው ነው ሲል ያኛው አይደለም የሚል ነው። በሁለቱ መካከል ያለው ቦታ ፍጹም ገደል ወይም የማይገናኙበት ሰፊ ወንዝ አይደለም። ይልቁን ሁለቱ በመወያየት በመግባባት ተጻምሮ (Synthesis) ይፈጥራሉ። በዚህ ተጻምሮ አማካኝነት ነው መንፈስ በውይይት ይዳብራል የሚለን። ለመሆኑ ይህ የመንፈስ መዋሐድ ጽንሰ ሐሳብ ፋይዳው ምንድን ነው? ከትምህርት ዘይቤ ጋርስ ምን ግንኙነት አለው?  እነዚህን ጥያቄዎች ከመመለሳችን በፊት በዚሁ መቅድም ላይ የሊቁን አንድ ወሳኝ ነጥብ እናንሳ። የሰው ልጅ ጉዞ ረጅም ነው ብለናል። ይህ የሰው ልጅ ጉዞም ከትምህርት ፍልስፍና ጋር የተቆራኘ ነው። በተለይ እጓለ የነበረበት ዘመን “ዘመነ ትምህርት ነው” ብሎ ያምናል።

“የዛሬው እኔነት መንፈስ በነገው የእኛነት መንፈስ ይፈተሻል፣ በትውልዶች መካከል የአንብሮ፣ ተቃርኖ፣ እንዲሁም አስተጻምሮ ሂደት ይፈጠራል”

እናም በዚህ ዘመን ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቤተ መንግሥታቸውን ለቤተ ትምህርትነት ይሆን ዘንድ ያበረከቱበትን ቅጽበት የዚሁ የዘመነ ትምህርት ከፍተኛው መገለጫ እንደሆነ ያሳያል። ስለሰጭው ታላቅነት፣ ስለስጦታው ግርማዊነት ካወደሰ በኋላ ስለ ተቀባዩ ትንሽ ነገር ማለት ይፈልጋል። ለመሆኑ የዚህ የትምህርት አደባባይ፣ መካነ አእምሮ ተቀባይ ማን ነው? “እንደ አስተያየቴ ተቀባይ አድርጌ የማስበው አንድ ጉልህና ግዙፍ የሆነ ነገር አይደለም። ረቂቅ ነው። ርኁቅ ነው። ግን ዓይንን ጨፍኖ ይታያል። ይህም የህዝባችን ተስፋ፣ ናፍቆት፣ ለወደፊት ዕድሉ ያለው መጓጓትና ተምኔት ፍትወት ነው።” ይህም ተስፋና ተምኔት ቅጽበታዊ ወይም እለታዊ ሳይሆን የሩቅ ዘመን፣ ዘላቂና ዘለዓለማዊ ተምኔቱ ነው። (ገጽ 22/፳፪) ሊቁ ከላይ የመንፈስ መናበብ ያለው አንዱ መገለጫው ይኸው በትውልዶች መካከል ያለውን የተምኔት ቀጣይነት፣ የዓላማ ጠማሪነት ነው ማለት እንችላለን። የዛሬው እኔነት መንፈስ በነገው የእኛነት መንፈስ ይፈተሻል፣ በትውልዶች መካከል የአንብሮ፣ ተቃርኖ፣ እንዲሁም አስተጻምሮ ሂደት ይፈጠራል። ይህንንም የሐሳቡ ባለቤት ሄግል የታሪክ ጉዞ ብሎ ሰይሞታል።

 በዚህ የተምኔት ጉዞ ውስጥ ያለመውና የደረሰበት የማይታረቁ ከሆነ የመንፈስ መባተት፣ ኩፋሌ መንፈስ ያጋጥማል። ኩፋሌ መንፈስ እንዳያጋጥም፣ ተምኔቱ ግቡን እንዲመታ ደግሞ ታላቁ ሁነኛ ትምህርት ነው። “የኢትዮጵያም ሕዝብ ከታሪካዊ እድሉ ለመድረስ ከዛሬው የሚበልጠውን የነገውን ትልቅነት በእጁ ለማድረግ በተምኔት እየተመራ ወደ ፊት ይጓዛል። ከዚህ ዓላማ ከሚያደርሱት መሣሪያዎች አንደኛው ትምህርት ነው። ሁለተኛው ትምህርት ነው፣ ሦስተኛውም ትምህርት ነው።” (ገጽ፣ 25/፳፭) ተምኔት እውን የሚሆነው በትምህርት ነውና የመካነ አእምሮው ተቀባይ ይህንን ተምኔት የሚያስፈጽመው መጭው ትውልድ ነው። በርግጥም እኛ ሳንወለድ፣ ከሩቁ የገጠሪቱ ኢትዮጵያ የነበሩ ህዝቦች በአካል ሳይቀርቡ፣ አንዳንዶች ወላጆቻችን ሳይወለዱ፣ በመንፈስ፣ በተምኔት የተቀበሉት ግርማዊ ሥጦታ ይኸው ለእኛም ደርሶን ያንን ተምኔት ለማስፈጸም እውቀት ለመሸመት ደፋ ቀና እያልን እንገኛለን። የተሻለ ሆኖ ለልጅ ልጆቻችን እንዲደርስ የምንተጋ፣ የመንፈስ አንድነት፣ የጋራ ተምኔት ያለን ስንቶቻችን እንደሆንን ግን ለራሳችን የተተወ ጥያቄ ነው።

 ከዚህ ተምኔታዊ ህልሙ ለመድረስ ትምህርት ሦስት ጊዜ ተጠቅሷል። ለአጽንኦት ነው ወይስ ሌላ አንድምታዊ ትርጓሜ ይኖረዋል? ይህ ጉዳይ ”በተዋህዶ ከበረ“ የሚለውን ምዕራፍ እስክናነብ ድረስ ወይም መጽሐፉን ጨርሰን ስናሰላስል ይገለጥልን ይሆናል። አንባቢን ከመጽሐፉ ጋር እንዲያሰላስል በመጠየቅ ወደ ቀጣይ ዋና ነጥብ እንለፍ። የመጽሐፉ ከትምህርት ዘይቤ ጋር ማተኮር ሰውን ማዕከል ያደረገበት ነቁጠ ሐሳብ (thesis) የሆነውን እና የትምህርት ተቋሙ ደግሞ የዚህ የመንፈሳዊ የተምኔት ግዘፍ የነሳ ተምሳሌታዊ ውክልና መሆኑን ሥዕላዊ በሆኑ ቃላት ይገልጽልናል። የህንጻው መግቢያ ሁለት ቆመ ብእሲዎች ወይም አምዶች አሉ። ተምሳሌታቸው እስራኤላውያንን ከግብጽ ወደ ርስት ከንዓን የመራቸው መልዓክ፤ ቀን ከጸሐይ ሐሩር በሚከልል ዓምደ ደመና፣ ሌሊት ከጨለማ እንግልት በሚታደግ ዓምደ ብርሃን መርቷቸዋል ይባላል። እነዚህም ሁለቱን ዓምዶች በዓምደ ደመናና ዓምደ ብርሃን ልንመስላቸው እንችላለን፣ ካለን በኋላ ሌላ ተጨማሪ ታሪካዊ ማጣቀሻ ይሰጠናል። ታላቁ የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ አባል የሆነው ኮርፕስ ክሪስቲ ኮሌጅ መስራች ጳጳስ ኮሌጁን መርቀው ሲከፍቱ ኮሌጁን ወደ ዘለዓለማዊ መንግሥት የሚወስዳቸው መሰላል አድርገው የሳሉት ጳጳስ የቀኙን ዓምድ ሠናይት፣ የግራውን ደግሞ እውቀት ብለው ሰይመውታል። ሠናይት (Virtue) የልቡና ጠባይ ነው፤ እውቀት (Knowledge) ደግሞ የሕሊና ጠባይ ነው። ሰው ምክንያታዊ ብቻ አይደለም የልቡና ሠናይነት የተሰጠው ፍጡር ጭምር እንጂ። ሁለቱን አስተካክሎ የያዘ ደግሞ ጠቢብ ይባላል።

የትምህርት ቤቱን በር ሁለት ዓምዶች ዓምደ ሠናይትና ዓምደ ዕውቀት ብለናቸዋል። ለምን? ዓላማው ሁለቱን ነገሮች በምልዓትና በስፋት ማስፈጸም ነውና። የህሊናን እውቀት ማስገኘት፣ የልቡናን ሠናይነት ደግሞ መኮትኮት። ከዚያም አካባቢያቸውን ለበጎ የሚቀይሩ ጠቢባንን ማፍራት። “ሰውን ከሌላው ፍጥረት ከፍ ያደረገውና ከመለኮት ባሕርይ ተካፋይነት ያደረሰው ዕውቀቱ አእምሮው ሕሊናው ነው። ልቡና ደግሞ የምኞት የተምኔት የፍላጎት መደብር እንደመሆኑ ክፋትና ተንኮል የተመላውን በዙሪያችን ያለውን ዓለም በመካድ፤ ጨርሶ በመዘንጋት፤ ደጉን መልካሙን ሠናይ የሆነውን የፍላጎት መሠረት በማድረግ ሰላምና ኅብር ያለው ዓዲስ ዓለም በውስጡ ፈጥሮ በደስታ ይኖራል። ለመኖር ይመኛል። የሕሊና ርቀት ሳይንስን አስገኝቶአል። የልቡና ንጹሕነት የበጎ ምግባርን የሞራልን ከፍተኝነት አስገኝቶአል።” (ገጽ 26/፳፮) ይህንን ሐሳብ ለመደገፍ በጣም የሚወደውን የጀርመን ፈላስፋ ኢማኑኤል ካንትን በሰፊው ጠቅሶታል።

 እዚህ በረጅሙ የጠቀስኩት ጉዳይ በርካታ ሐሳቦችን ይዟል። የማንኛውም የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ዓላማ የህሊናን ልህቀትና የልቡናን ሠናይነት ሊያበለጽግ ይገባዋል ነው። ማንኛውም በከፍተኛ ትምህርት ላይ የተሰማራ መምህርም ሆነ ተማሪ ሁለቱን ነገሮች ታሳቢ በማድረግ በቁርጠኝነት ሊሰራ ይገባዋል። የሕሊናን የማሰብና የመፍጠር ከፍተኛ ክህሎት በማበልጸግ የልቡናን በጎነት እንዲሁም ሠናይነት በመኮትኮት የተሻለ አዲስ የጋራ ዓለም መፍጠር። የዘመናችን ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራንና ተማሪዎች ከዚህ አንጻር ራሳቸውን ቢገመግሙ የሚገኘው ምላሽ ምን እንደሆን ለመገመት አያዳግትም።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top