ጥበብ በታሪክ ገፅ

የወገን ጦር

የመጽሓፉ ርእስ …………………………..… የወገን ጦር ትዝታዬ

ደራሲ …………………………………………….. ማሞ ለማ (ሻለቃ)

አሳታሚ ………………………….……. ሻማ ቡክስ፣ 2001 ዓ.ም.

አታሚ ……………………. የተባበሩት አታሚዎች አ.አ. ኢትዮጵያ

የገጹ ብዛት………………………………………………………..….497

ዋጋው ……………………………………..……………ያልተመለከተ

ሂሳዊ ንባብ …………………………………………..…. በአበራ ለማ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ በአገር ቤትም ሆነ በውጭ እየታተሙ የሚወጡ አንዳንድ መጻሕፍት የአንባቢያንን ቀልብ እየሳቡ ነው። ደህና የመወያያ ርእሶችም እየሆኑ ነው። እነዚህ የሕትመት ብርሃንን የታደጉ የቅርብ ጊዜ መጻሕፍት ኢ-ልቦለድና ልቦለዶች (Non fiction & fiction) ሲሆኑ፣ ዓይነተኝነታቸው በአራት ተከፍሎ ሊታይ ይችላል። ይህም ለዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ሂሳዊ ንባብ አቀራረብ ይመች ዘንድ የተመረጠና ሌሎች የሕትመት ሥራ ውጤቶችን (የትምህርት መርጃ መጻሕፍትን፣ ሙያ ቀመስ መጻህፍትን፥ ቃለ ተውኔቶችን ወዘተ…) ለጊዜው ያላካተተ መሆኑን ልብ ይሏል።

1. የሕይወት ታሪክ ማስታወሻ (Memoir)

2. ኔበንተኔና በንተሱ(እንደ ሰ.መ. አሰያየም)Autobiography & biography

3. የታሪክ መጻሕፍት (History)

4. የልቦለድና የግጥም ሥራዎች (Ficton and poetry) ናቸው። ከቁጥር አንድ አስከ ሦስት የተመለከቱት በኢ-ልቦለድና አራተኛው በፈጠራ ሥነ ጽሁፍ ሥራዎች ጎራ ውስጥ የሚካተቱ ናቸው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ታትመው ከወጡትና እጄ ከገቡት መካከል፣ ላሠራር ይመቸኝ ዘንድ ጥቂቱን ብቻ በየፈርጃቸው እዚህ ላይ ማመልከትን መርጫለሁ። የሕይወት ታሪክ ማስታወሻዎች ከሚባሉት ውስጥ …

ሀ. “አሞራው” ……………………………………..ግደይ ባህሪሹም

ለ. “የዘመን ታሪክ ትዝታዬ… ካየሁትና ከሰማሁት 1896 – 1922”” ………………………………………………… በብላታ መርሴዔ ሃዘን ወልደ ቂርቆስ

ሐ. “ካየሁት ከማስታውሰው”…………በልዑል ራስ እምሩ ኃይለ ሥላሴ

መ. “አይ ምጽዋ”………………………………….በታደሰ ቴሌ ሳልቫኖ

 ሠ. “መስዋእትነትና ጽናት”…………….. በሜ/ጄኔራል ሁሴን አህመድ

 ረ. “ነበር”(ክፍል አንድና ሁለት) ……………………….…… ዘነበ ፈለቀ

ሰ. “የጋዜጠኛው ማስታወሻ”…………………………በተስፋዬ ገብረ አብ

 ሸ. “የወገን ጦር ትዝታዬ” ………………………… በሻለቃ ማሞ ለማ

ቀ. “የፒያሳ ልጅ” …………………………በፍቅሩ ኪዳኔ

በ. በከፍተኛ የኢትዮጵያ ተራሮች ቆይታዬ……አርኖ ሚ. ዳባዲ (ትርጉም ገነት አየለ) ይጠቀሳሉ፡፡ በዚሁ የኢልቦለድ ሥነ ጽሁፍ ጎራ ውስጥ የሚመደብ “የገጠመኝ ጽሑፍ” የሚባለው ክፍል አንድ ሥራም፤ እጄ ገብቶ ተመልክቼዋለሁ። መሃል ሸገር ላይ በታዳጊ ሕጻናቶቻችንና ወጣቶቻችን የሕይወት ኪሳራ ላይ ምን እየተቆመረ እንዳለ ለማየት፣ ወኔውና ትእግስቱ ያለው ሰው፣ የጸሃፊ ደረጀ አያሌውን “መኃልየ መኃልየ ዘ ቺቺኒያ”ንና የተድባበ ጥላሁንን “መኃልየ መኃልየ ዘ ካዛንቺስ‹‹ን ማንበብ ይችላል። በደረጀ አያሌው የገጠመኝ ጽሑፍ ውስጥ የምትገኘውን፤ ላቅመ ሄዋን ያልደረሰችውን የሚጢጢን የመኖር ፍዳና አሳዛኝ ሕልፈት፣ በአንጻሩም ደግሞ የአንዳንድ የዘመኑን ባለ ገንዘብ ነውር እስኪያንገሸግሻችሁ ድረስ ትጋታላችሁ። ”ሦስት ባንድ ታውቃለህ?” እያለች ነበር የነዚህን የምድር ጉዶች የነውር ወሲብ ታሪክ ለደራሲ ደረጀ ያወሳችው።

 ሚጢጢ በአሥራ አንድ ዓመቷ እናት አልባ እራሷንና የሦስት ዓመት ሕጻን ታናሽ ወንድሟን ረሃብ ለማስታገስ ስትል ሥጋዋን መሸጥ ተገደደች። በጥቂት ዓመታት ውስጥ ለመኖር ስትል ስትውተረተር ካያ ሞት ጋር ተፈጣጠመች። “እውነት ይቺ አዲስ አበባ ያቺ እናውቃት የነበረች ከተማችን ናትን?” እያሉ በባይተዋርነት ውስጥን መናጥና የቺቺኒያን አምባ የመቅሰፍት ሠራዊት የሰፈረባት አድርጎ መራገም አይቀሬ ነው። ግን ግን ይህንን ህዝብ ከንዲህ ዓይነቱ የሥነ ልቦናና የተበላሸ ማህበራዊ ሕይወት ሰለባነት የሚታደገው ማን ነው? ባለቤቱ ማነው? መንግሥት? ፈጣሪ? ወይስ ማን? እያልን በውስጣችን መጨነቃችን የግድ ነው።“የጭን ቁስል‹‹ ዓይነቱ የተክሉ ጥላሁን ሥራም ለዘመናችን ጨካኝ ገዢዎች ያረመኔነት የሥነ ምግባር ጉድለት ማሳያ ነው፡፡

 ስለ አንድ የኢ-ልቦለድ ሥራ ከመነጋገራችን አስቀድመን ስለ ልዩ ጸባዩ ማወቅ ይኖርብናል። ኢ-ልቦለድ እውነትን እውነት ብሎ የሚያቀርብ የእውነታው ዓለም እማኝ ነው። የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚስማሙበት ሁሉ፣ ቢያንስ ቀጣዮቹ ሦስት ዐቢይ ነጥቦች ትኩረትን ይሻሉ።

• የኢልቦለድ አንባቢያን ከማናቸውም በላይ ደራሲውን ማመን ይፈልጋሉ።

 • የኢልቦለድ ጹሑፍ እውነት የሆነውን ነገር ወክሎ መቅረብ ይኖርበታል።

• የኢልቦለድ ጽሑፍ አቀራረብ ተአማኒነትን ለማጎልበት ፋይዳው ማድረግ ይጠበቅበታል። በዚህ መመዘኛ ረገድ ሚዛን የሚደፉና ያንባቢን ቀልብ ከሚገዙ የቅርብ ዓመታት ሥራዎች መካከል ብዙዎቹን በናሙናነት ወስዶ መፈተሽ ይቻላል። ሆኖም የዚህ ጽሁፍ ዋና ትኩረት ይህ ባለመሆኑ፣ ጉዳዩን ብቻ ጠቁሞ፣ወደ አቢይ ፋይዳው ማለፍን ጸሃፊው መርጧል።

በኢልቦለድ ሥራዎች የትናንት ትናንትን ለዛና ጣእም ለማጣጣም፣ ዛሬን አድምቆ ለማየትና መጻኢ ወደፊትን ለማጮለቅ እኒህን ዓይነት ተጠቃሽ መጻህፍት ላይነ ንባብ ማብቃቱ ብርቱ ጠቀሜታ አለው። ለምሳሌ እንደ አንጋፋው ደራሲና ጋዜጠኛ እንደ ብላታ መርስዔ ሃዘን ሥራ የመሳሰለው ትናንትን እንደ ብሩህ መስታወት አጥርቶ የሚያሳይ ነው።

አንጋፋው የቋንቋና የሥነ ጽሁፍ ሰው ብላታ መርስዔ ሃዘን ወልደ ቂርቆስን የማያስታውስ የኛ ዘመንተኛ ይኖራል ብዬ አልገምትም። “የአማርኛ ሰዋሰው” በሚባለው ብቸኛ የቋንቋ ሥርዓትና አገባብ መማሪያ መጽሃፋቸው አሳምረን እናስታውሳቸዋለን። ብላታ አሥራ ሁለት ወጥ ጥናታዊና ትምህርታዊ መጻህፍትን ከመድረሳቸውም ባሻገር (የታተሙ)፣ ሰባት የትርጉም ሥራንም ላይነ ንባብ አብቅተዋል። ከሌሎች ምሁራን ጋርም ስምንት ሥራዎችን አበርክተዋል። ያልታተሙ ስድስት ወጥ ሥራዎችም እንዳሏቸው ልጃቸው አምሃ መርስዔ ሃዘን በቅርቡ ባሳተሙላቸው ያባታቸው መጽሃፍ መግቢያ ላይ አስታውሰውናል። ብላታ መርስዔ ሃዘን በ1964 ዓ.ም. የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሽልማት ድርጅት የአማርኛ ሥነጽሁፍ ተሸላሚም ነበሩ።

ብላታ መርስዔ ሃዘን የተዋጣላቸው የሕይወት ታሪክ ማስታወሻ ጸሃፊ እንደ ነበሩ፣ እነዚህ ሦስት ነጥቦች ከግንዛቤ ውስጥ ይዞ ሥራቸውን መፈተሽና እርካታን ማግኘት ይቻላል።

• የሕይወት ታሪክ ማስታወሻ ሌሎች እንዲያነቡት የሚጻፍ ነው።

• የሕይወት ታሪክ ማስታወሻ አንባቢውን ከግንዛቤው ውስጥ ከቶ የሚዘልቅ ነው።

 • የሕይወት ታሪክ ማስታወሻ ከተነባቢነት ፋይዳ ጋር ቁርኝት ያለው መሆን ይኖርበታል።

ይህ ልጃቸው አቶ አምሃ በቅርቡ ያሳተሙላቸው “የዘመን ታሪክ ትዝታዬ … ካየሁትና ከሰማሁት 1896 – 1922” መጽሃፋቸው ውስጥ አያሌ ድንቅ ትዝታዎቻቸውን ጥለውልን አልፈዋል። ውብ በሆነ የሥነ ጽሁፍ ቋንቋ አተራረክ፤ በዚያን ዘመን የነበረውን እውነተኛ ገጽታ እንደ ፎቶ ሽመልስ (እውቁን የ50ና የ60ዎቹን አሠርት ዝነኛ የሸገር ፎቶግራፍ አንሺ ሽመልስ ደስታን ያስታውሷል) የካሜራ ጥበብ ቁልጭ አድርገው አሳይተውናል። ስለ ብላታ ሥራዎች በጣም ብዙ ብዙ ሊባል ይቻላል።

 ኔበንተኔከሚባሉት ውስጥ …

ሀ. “ኦቶ ባዮግራፊ”……………..በፊታውራሪ ተክለ ሃዋሪያት ተክለ ማርያም

 ለ. “አንድ አፍታ ላውጋችሁ”….. በፕሮፌሰር ጌታቸው ሃይሌ

 ሐ. “የጦር ሜዳ ውሎ”…………በብ/ጄኔራል ተስፋዬ ሃብተ ማርያም

መ. “የጦር ሜዳ ውሎዎች፣ ከምሥራቅ እስከ ሰሜን (Autobiography)… በብ/ጄ. ካሣዬ ጨመዳ

 ሠ. የጨለማ ሌላኛው ገጽታ፥ የቄስ ጊዳዳ ሶለን ግለታሪክ…. በግርማዊ ቡሸን (ትርጉም)… ይካተታሉ። በዚህ ጎራ ውስጥ የተካተቱትን ዓይነት ኔበንተኔዎችን ማንበብም የጸሐፊዎቹን ተክለ ስብእና በጥልቀት ለማየት ያመቻል። ትውልዳቸውን፥ አስተዳደጋቸውን፥ ትምህርታቸውን፥ ሥራቸውን፥ ባገራቸው ውስጥ የነበራቸውን ሚናና ሰፊ ልምዳቸውን ለመቃኘት ያስችላል። ላይነት ያህል የፊታውራሪ ተክለ ኃዋርያትን ኦቶ ባዮግራፊ ያነበበ እንኳን ብዙ ጠቃሚ ነገርን ይገበይበታል።

 የፊታውራሪ ተክለ ሐዋሪያትን ዓይነት ሥራ ሁሌም ለቁም ነገሩና ለተክሌ ግለኛ ስብእና ስንል እየተመላለስን ብናነበው አንጠግበውም። ይህ ሥራቸው ከቋንቋ አጠቃቀማቸው፣ ከሃሳብ አሰዳደር ክሂላቸውና ካመለካከታቸው አንጻር የነዘመነ ቶልስቶይ መልካም ደቀ መዝሙር መሆናቸውን ይመሰክርላቸዋል። የኮንስቲትዩሽንን አስፈላጊነት የሚረዳላቸው ባለጊዜ ለማግኘት እንደዲዮጋን በቀተረ ተሲዓት ኩራዝ ለኩሰው ሲንከራተቱ ማስተዋል ውስጥን ይበላል። ከራሻዊቷ “አያታቸው” በተማሩትና ባስተዋሉት መሰረት የባለ ብዙ ጋሻ መሬት ባለእርስትና ባለጉልጥምት በመሆን፣ ሰፋፊ ሁዳዶቻቸውን እያሳረሱ የመኖር ሕልማቸውንና ስኬታቸውን ስናጤን፤ ዘመናቸው፥ ትምህርት ቤታቸውና ያደጉበት ሥርዓት የቀረጻቸው ሞዴል ለመሆናቸው እማኝ መቁጠር አያስፈልግም። ለራስ ተፈሪ መኮንን የተሰጠው ዓይነት አንድ ምላሽ ሁሌም አይረሴነት ያለው ነው። ምልልሱ እንዲህ ይመስላል….

 “አዲስ ያቀናኸውን ከተማ ስም “አስበ ተፈሪ” ብለህ እንድትሰይመው…” ሲሉ ራስ ተፈሪ መኮንን ያዙዋቸዋል። “አልሰይምም። አንተ እራስህ ያቀናህውን ከተማ እንደሱ ብለህ ሰይመው” ፊታውራሪ ተክለ ሃዋሪያትይመልሳሉ።

 “እንድትሰይመው አዝዤሃለሁ!… ትእዛዝ ነው!…” ራስ ተፈሪ መኮንን።

እንዲህ መሰሉ እውነት፥ እልክና ሥልጣን የሰውን ልጅ ማንነት የሚፈርጁበትን አጋጣሚዎች ስናነብ የምጸት ፈገግታ ማሳየታችን አይቀርም። ተክሌ ላሻፈረኝ ባይነት ባህሪያቸው የእግረ ሙቅ ሰለባነት እዳ ከፍለውበታል።

 ተክሌ መጀመሪያ እግራቸውን ሂርና ላይ የተከሉበት እርስታቸው፣ ከራስ ተፈሪ መኮንን በስጦታ ያገኙት ሰላሳ ጋሻ መሬት ነበር። ይህ አልበቃቸውምና ካካባቢው ባለ እርስቶች በገፍ መግዛትን ተያያዙት። ተክሌ ያንን ሁሉ እርስት ከበር በመለስ የማግበስበስ ፍላጎታቸው ምን ጊዜም የማይበርድ በመሆኑ፣ በመጨረሻው በነገረ ሠሪዎች አቤቱታ ራስ ተፈሪ፣ “ከዛሬ ጀምሮ እኔን ሳታስፈቀድ ምንም ዓይነት እርስት እንዳትገዛ!…” ብለው ያስተላለፉባቸው መመሪያ አንባቢን ያስገርማል። እናም ሊዮ ቶልስቶይ ባንዲት የኖቭሌት ሥራው ላይ “ላንድ ሰው ምን ያህል መሬት ይበቃዋል?” ሲል በምጸት ያቀለመውን ታሪክ አባታችን አባ ተክሌ ያስታወሱት አይመስልም።

 እንግዲህ እንዲህ እንዲህ እያልን ብዙ ብዙ እንደሃረግ እየመዘዝን፣ የምናወሳው የዚህ ሸጋ ሥራ አንጓ ሞልቷል። ለምሳሌም ያህል ከግርጌ የተመለከተውን ከመጽሃፉ የቀነጠብኩትን ጥቅስ እንደምን እንመለከተዋለን? የሚል ጥያቄዬን ለትሁት አንባቢያን ማቅረብን እሻለሁ። እውን ያለመግባባት ፈሊጣችን መንስዔው ተክሌ እንዳሉት ሁሉ ቅይጥ መሆናችን ይሆን? እናም ይህ መቀየጣችን እስከመቼስ እንደባእድ የጎሪጥ እያስተያየን ይኖር ይሆን? ላለመስማማትስ እየተስማማን መኖር እስከመቼ፥ ምቾትና ውስጣዊ ሰላም ይሰጠን ይሆን? ያለዛስ የዘመናችንን አስተዋይ መሪ የዶከተር ዐቢይ አህመድን ያብሮነትና የመደመር ርዕዮት መቀጸል አይሻለንም ይሆን?

ፊታውራሪ ተክለ ሐዋሪያት እንዲህ ይሉናል…

“”ይልቅስ ሕዝቡ ስህተት የበዛበት ነው። እንደዚህም የሆነበት ምክንያት ታውቅዋል። ካንድ ጅንስ (ዘር) ያልመጣ ቅይጥ በመሆኑ ነው። ለዚህም ምክንያት የሆነው ያገራችን ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ ነው። የኢትዮጵያን ታሪክ ከስሩ አያይዘን ጠብቀን ስንመለከተው፤ በየጊዜው ጉዳት የሚደርስበት በጂኦግራፊያዊ አቀማመጧ መሆኑ በግልጽ ይታያል….” (ገጽ 158) ይላሉ፡፡ ይህን የጓዳ እኛነታችንን ይዘን እየተጓዝን ኑረን ነው፤ ከዛሬው የመቻቻልና የመደማመር ዘመን ላይ የደረስነው፡፡

 የታሪክ መጻህፍት ከሚባሉት ውስጥ…

 ሀ. “የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ከንግሥተ ሳባ እስከ ታላቁ የአድዋ ድል” … በብላቴን ጌታ ኅሩይ ወ/ ሥላሴ

ለ. “ክህደት በደም መሬት”……………… በሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ

ሐ. “የኢትዮጵያ ታሪክ (ከ1847- 1983)”……… ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ

 መ. “የአናብስት ምድር”……………………….…. በታደሰ ቴሌ ሳልቫኖ

 ሠ. “ የ1953ቱ የመንግሥት ግልበጣ መከራና ከ1908 -1966 የኢትዮጵያ ታሪካዊና ፖለቲካዊ ሂደት”…….……… በኮ/ል ቃለ ክርስቶስ አባይ

ረ. “ምስክርነት በባለሥልጣናቱ አንደበት” …… በሻምበል ተስፋዬ ርስቴ

ሰ. “ለኢትዮጵያ ታሪኳ ነው መልኳ”…………. በአፈሊቅ አክሊሉ ገብረ ኪሮስ… ይጠቀሳሉ።

 በዚህ ዘርፍ ውስጥ የተካተቱት ታሪክ ቀመስ ሥራዎች ሁለት ዓይነት ያጻጻፍ ገጽታ ያላቸው ናቸው። አንዳንዱ የታሪክ ጽሁፍን አጻጻፍ ወግ ተከትሎ በግርጌ ማስታወሻና በዋቢ መጻህፍት አጠቃቀስና አጠቃቀም ረገድ የተዋጣ አቀራረብን የተካነ ነው። አንዳንዱ ደሞ ካንጻር ምርጫው ጀምሮ የትኛውን ይዞ የትኛውን ትቶ የታሪክ ጽሑፉን ለገጸ ንባብ እንደሚያበቃ ግራ የገባው የሚመስል ነው። የግርጌ ማስታወሻ አጠቃቀሙም፥ የዋቤ መጻህፍት አጠቃቀሱም ሁሉ ውንግርግሩ የወጣበት ሆኖ ይስተዋላል። ከዚህ ከሁለተኛው ዓይነት የተበላሸ ያጻጻፍ ቴክኒክ የምናገኘውም አላባ እንደዚያው የተምታታና እናትዋን እንዳጣች ግልገል የሚዋልል ዓይነት ሆኖ እናገኘዋለን። ካነበብኳቸውና ካልተዋጣላቸው የታሪክ መጻህፍቱ ዝርዝር ውስጥ የሻምበል ተስፍዬ ርስቴን “ምስክርነት” ለአብነት መጥቀስ ይቻላል።

 የሻምበል ተስፋዬ ሥራ የባለ ሙያ እገዛ የተነፈገውና ወርቅ የሆነ ፍሬ ነገርን (material) በወጉ መጠቀም ያልቻለ መካን ሥራ ነው። በጭብጥ ደረጃ የሚያነሳቸውን ፍሬ ነገሮች፣ በታሪክ ጽሁፍ አጻጻፍ ቴክኒክና በታሪክ ቋንቋ አጠቃቀም ድክመት ምክንያት ሥራውን ሊዳጨው ችሏል። አንዳንድ ቦታ ላይ የሚያነሳቸውን ብርቱ ጉዳዮች መግለጽ ሲያቅተው፣ የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ ሊያደርሱ የሚችሉ ብይኖችን ሰጥቶ ሲያልፍ ይስተዋላል። ደርግን ከዚያ ሁሉ የሥልጣን ጥማትና አምባ ገነናዊ አመራር ነጻ ሊያዋጣ ሲፈልግ፣ ጦሱን ሁሉ ለነመኢሶንና ኢሕአፓ ሰጥቶ ቁጭ ይላል።

“በታሪክ ጽሑፍ አጻጻፍ ቴክኒክና በታሪክ ቋንቋ አጠቃቀም ድክመት ምክንያት ሥራውን ሊዳጨው ችሏል። አንዳንድ ቦታ ላይ የሚያነሳቸውን ብርቱ ጉዳዮች መግለጽ ሲያቅተው፣ የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ ሊያደርሱ የሚችሉ ብይኖችን ሰጥቶ ሲያልፍ ይስተዋላል”

የደርግ አስቀያሚው ገጽታ ባለቤቶች ሁሉ እነዚህን ድርጅቶች የመሳሰሉ እንደሆኑ ሰበብ እያፈላለጉ ሲዳርጉባቸው ይስተዋላሉ። “… የኢትዮጵያ ምሁራን… ሁሉን የሚጠሉ ናቸው። ባህላቸውን፣ ኢትዮጵያዊነትን ይጠላሉ፣ ይንቃሉ። ሁሉን ማፍረስ ይወዳሉ… እርስ በርስ መተማመን፥ መደጋገፍና መረዳዳት ሳይችሉ ቀርተዋል። (ኢሕአፓና መኢሶን በአብዮቱ ወቅት የሠሩትን ያጤነዋል) የጥቅም ስስታም ናቸው። የሥልጣን ስስታም ናቸው። ጨካኞች ናቸው…”” (ገጽ 115) እያሉ እንዲህ ያዘናጉናል። ደርግን ሳይሆን እኒህ የወደቀ ዛፍ ተምሳሌቶችን በሁሉም ረገድ እንድንረባረብባቸው ይወተውቱናል።

እኚህ ጸሃፊ አንድ ሌላ ነገርም ዘነጉ። እሳቸው እንደሚሉን በኢሕአፓና በመኢሶን ክፋትና ጨካኝነት አንጻር፣ እርሳቸውና እርሳቸው የሚያሽሞነሙኑት የወታደራዊው ደርግ አመራር የትኛውን የስልጣን ቸርነትና ርህራሄ እንዳደረጉ ሹክ ሳይሉን ማለፋቸው ነው። ወይም ባለፉት 27 ዓመታት የኖሩበትን የወያኔ/ኢሕአዴግ ሥርዓት የሥልጣን ቸርነትና ርህራሄ ላብነት ያህል ወዲህ ቢያቀብሉን መልካም በተደረስናቸው ነበር። ስለወያኔ/ኢሕአዴግማ አንዲት ዘለላ መስመርም ሳይጭሩ የብእር ቀለማቸው ነጥፏል። ምናልባት በቀጣዩ “የታሪክ” ጽሑፋቸው፣ ሊያስነብቡን የይደር ቀጠሮ ይዘውልን ይሆናል እንጠብቅ ይሆን

በአጠቃላይ ይህ ሥራቸው ሲመዘን፤ የመልካም ኢልቦለድ ጽሑፍን ደረጃ የማያሟላና ከማሳየት ይልቅ በመናገር ላይ ያተኮረ ረጋ ሠራሽ ሥራ ነው። ያማርኛ ቋንቋን የአጻጻፍ ሕግም በብርቱው የሚጻረሩ ችግሮችም ተስተውለዋል። ረዣዥም አረፍተ ነገሮችን መጠቀም፥ አንዳንድ ቃላትን ያለ ስፍራቸው መሰንቀር፥ አንቀጾችን አለመመጠን ይስተዋላል። ይህም ላንድ የኢልቦለድ ሥራ የተነባቢነቱን ፍጆታ በመቀነሱ ረገድ፣ አፍራሽ ሚናን እንደሚጫወት መጠቆምን እንወዳለን።

ከልቦለድና ከግጥም ሥራዎች ወስጥ…

 ሀ. “ቢስ ገላ”………………………….. በፀሐይ መልአኩ

ለ. “ዴርቶጋዳ”………………………………………በይስማዕከ ወርቁ

ሐ. ‹‹እንትን‹‹……………………………………….በተስፋዬ ብርሃኑ

መ. “ግራጫ ቃጭሎች”…………………………………..በአዳም ረታ

ሰ. ‹‹አፈር ያነሳ ሥጋ‹‹……………………………በሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው

ረ. “ኗሪ አልባ ጎጆዎች” እና ሌሎችም……………. በእውቀቱ ሥዩም

ሰ. ልጅነት…………በዘነበ ወላ የመሳሰሉት ላብነት ሊጠቀሱ ይችላሉ። በዚህ በልቦለዱ ዘርፍ አንድ አዲስ ያልተለመደ ዓይነተኛ ሥራ ሆኖ የብዙ አንባቢያንን ቀልብ በቅርቡ የሳበው፣ የይስማዕከ ወርቁ “ዳርቶጋዳ” ነው። ከሳይንስ ልቦለድ (Science fiction) አጻጻፍ ጎራ የሚመደብና ላይነትም በብርቱ የሚጠቀስ ነው። በጥሩ የሥነ ጽሁፍና የሥነ ሕይወት ሙያዊ ቃላት የሸገነ ሥራ ነው። አንባቢን ወጣሪና ከእውነታው ዓለም ጋር እያፋለመና እያዋዛ ጣናን የሚያስቀዝፍ ነው።

 እነዚህ ለዓይነት ያህል የተጠቀሱትም ሆኑ ሌሎቹ አዳዲስ የወጡ አብዛኞቹ መጻህፍት ብዙ ሊባልላቸውና ሂሳዊ ንባብም ሊካሄድባቸው የሚገቡ ናቸው። በዚህ ዓይነት አንድ አቢይ ጉዳይን ለማየት በተመረጠ ርእስ ስር ስለሁሉም ብዙ ለማለት ባይቻልም፣ በሌላ ጊዜ ተመልሶ በሌሎቹም ተጠቃሽ ሥራዎች ላይ ሊጻፍባቸው እንደሚችል የዚህ መጣጥፍ አቅራቢ ያምናል። እናም ለዛሬው ትኩረቴ ወደ መረጥኩት የሻለቃ ማሞ ለማ “የወገን ጦር ትዝታዬ” ሥራ ላቅና።

 “የወገን ጦር ትዝታዬ”

 “የወገን ጦር ትዝታዬ” ከላይ እንደተመለከተው ሁሉ፣ በኢልቦለድ የሥነ ጽሁፍ ጎራ፣ በሕይወት ታሪክ ማስታወሻ አጻጻፍ ክፍል ውስጥ የሚመደብ ነው። ከኔበንተኔ አጻጻፍ የሚለየው፣ ደራሲው የራሱን የትወልድም ሆነ የእድገት ወዘተ… ጉዳይ ፋይዳዬ ብሎ አንስቶ ከሀ እስከ ፐ ድረስ አለመተረኩ ነው። የ “ኔበንተኔ” ጸሃፊ ከልደት እስከ… ዓይነት ትረካን በራሱ የሕይወት ታሪክና ገጠመኝ ዙሪያ ያጠነጥናል። “የወገን ጦር ትዝታዬ” ዓይነቱ የሕይወት ታሪክ ማስታወሻ ጸሃፊ ግን፣ ከሕይወት ዘመኑ አንድ አንጓ እውነትና እውነት የሆነ ገጠመኝ በመነሳት፣ በዚያ መቼት ዙሪያ ያጠነጠነውን ማስታወሻውን ያስነብባል። እናም በዚህ አግባብና አንድምታም ነው የሻለቃ ማሞን ሥራ የምንቃኘው።

 ሻለቃ ማሞ የረዥም ጊዜ ልምዳቸው የዘመቻ መኮንንነት ባጠቃላይም ውትድርና እንጂ ጸሐፊነት አይደለም ብሎ እሰጥ አገባ የሚሄድ ሁሉ፣ ይህን ሥራቸውን ካነበበ በኋላ መረታቱ አይቀሬ ነው። ሰውዬው ባንድ እጃቸው ክላሽንኮቭ በሌላኛው እጃቸው ደግሞ ብእር ጨብጠው የኖሩ ዓይነት ሰው ናቸው… ሥራቸው የሚያስመስላቸው። ሃሳባቸውን በወጉ አፍታተው መግለጽ የሚያስችላቸው ሁለንተናዊ የቋንቋ ችሎታቸውና ጉልበታቸው የሚደነቅ ነው። የኢልቦለድ ሥራ ማቅረቢያ ቋንቋቸውና የወታደራዊ ሙያቸው ቋንቋ ብቃትና የሁለቱ ተጣጥሞሽ ለሥራቸው ስኬት ትልቁን አስተዋጽኦ እንዳደረገላቸው ማስተዋል አያዳግትም። በርግጥ አልፎ አልፎ በአርታዒ እጅ ሊቃኑ ይችሉ የነበሩ ያንቀጽ አቀማመጥ ስህተቶች ይስተዋላሉ። “አንድ አረፍተ ነገር አንድ አንቀጽ ሆኖ አይቀመጥም” የሚለውን ያማርኛ ቋንቋ ያጻጻፍ ሕግ ይጻረራልና ነው ይህን ማለታችን።

ሌሎቹም በጦር ግምባር ዙሪያ የተጻፉ አንዳንድ መጻህፍት የየበኩላቸውን ያተራረክና የመግለጽ ብቃት ማሳየታቸውን አለ ማለት አይቻልም። ታደሰ ቴሌ ሰልቫኖ፥ ብ/ጀኔራል ተስፋዬ ሃብተ ማርያምና ብ/ጄኔራል ካሳዬ ጨመዳ ብርቱ ሥራዎች ካቅረቡልን ጸሃፍት መካከል ናቸው። ያንን ዘግናኝ የምጽዋ እልቂት ታደሰ ቴሌ እንደ ካሜራ ቀርጸው አሳይተውናል። ጀነራል ተስፋዬ የናቅፋን አስደናቂ ግዳጅ አውጣጣቸውን፥ ጄኔራል ካሣዬ የጅጅጋውንና ባጠቃላይም ከወራሪው የዚያድ ባሬ ጦር ጋር የተደረገውን እልክ አስጨራሽ ፍልሚያ በየበኩላቸው እንደመስታወት አሳይተውናል። ይሁንና ሻለቃ ማሞ የጦር ግምባር ሁለንተናዊ ገጽታንና ሕይወትን በላቀ ደረጃ ባማርኛ ቋንቋ ፍንትው አድርገው ማሳዬት በመቻላቸው፣ ካድናቆቱ ያንበሳውን ድርሻ ሳይወስዱ አይቀሩም የሚል እምነት አለኝ። ይህ ሥራ እውነታን መደላድሉ አድርጎ፣ በሚዛናዊ አቀራረቡ ከበላይ አካል እስከ ተራ ወታደሩ ያለውን መዋቅር ሁሉ በወታደራዊ ሙያ ግብአት አኳያ የሚያሄስ ነው። ሻለቃ ማሞ ችግርን ብቻ የሚነግሩን ሳይሆኑ፣ የችግሩን አፈጣጠር መሠረት እየመረመሩ መፍትሄውንና አማራጩን ሁሉ እየጠቆሙ በማሳዬት ነው… ጠንከር የሚሉብን።

 ለኢልቦለድ ጸሐፍት አንድ ትሁት የባለሙያዎች ምክር አለ። ይሄውም…

• ያጻጻፍ ውበት ያለው የኢልቦለድ ሥራ ማቅረብ ከፈለክ፥ በልቦለድ አጻጻፍ ጥበብ ለመካን ተጣጣር።

• ኢልቦለዳዊ የፈጠራ ሥራ ምንጊዜም እውነትነቱን እንደጠበቀ መቆየት አለበት።

• በኢልቦለዳዊ የፈጠራ ሥራህ፥ አሳይ እንጂ እንዳትናገር፣…. የሚሉ ናቸው ይህን ምክር ሻለቃ ማሞ በወጉ የተጠቀሙበት ይመስላሉ። ጸሃፊው ጦር ሜዳን እንደ መልካም የእጅ መዳፍ አንባቢ ጠበብት አብጠርጥረው አንጠርጠረው ያስነብቡናል። ያሳዩናል። ወይንም በዘመቻ መኮንንነት ዘመናቸው ከጃቸው እንደማይለያቸው የጦር ሜዳ ካርታቸው ንባብ ሁሉ፣ የትናንት ውሏቸውን በቃላት እያሰሱ እኛን ያሰንብቡናል። ሰማዩ፥ ተራራው፥ ኮረብታው፥ ከተማው፥ መንደሩ፥ ሸለቆው፥ ሸንተረሩ፥ ጉራንጉሩ፥ ሰርጡ፥ ጉድባው፥ ወንዙ፥ ኩሬው፥ ምንጩ፥ አሸዋው፥ አለቱ…. መልክአ ምድሩ ሁሉ በያይነት በያይነቱ ሲገለጥልንና፣ የሰው ልጅ በነዚህ ሁሉ ውስጥ በእሳት እየተፈተነ ሲያልፍ ወይም ሲያሸልብ እንደሲኒማ ያሳዩናል።

ባኳያውም ጀቱ፥ ታንኩ፥ ብረት ለበሱ፥ መድፉ (120 ጀነራል መድፍ፥ ግራርፒ፥ 80፥ 70 ሚ.ሜ. ወዘተ…)፥ መትረየሱ፥ አር ፒ ጂው፥ ዶሽቃው፥ ዙ 23፥ ቦምቡ፥ በያይነት ጠመንጃው…. ይነገረናል ሳይሆን፣ ይስተዋለናል። በነዚህም አረርና የሳት ላንቃ እዚያም ቤት እዚህም ቤት ሕይወት ስትበላ፥ ሕይወት ስትጠጣ ሸጋው ብእረኛ ያሳዩናል። በሕይወት ታሪክ ማስታወሻ ጸሃፊነታቸውም ሻለቃ ማሞ በኤርትራ በረሃዎች ውስጥ እጅግ ፈታኝ በሆኑት ያልጌና፥ ያፋቤትና የሌሎችም ጦር ሜዳዎች ላይ ያሳለፏቸውን የጀግንነት፥ የሞትና የሽረት ወቅቶች (ክፉ ዓመታት፥ ወራት፥ ቀናት፥ ሰዓታት፥ ደቂቃዎችና ቅጽበታት…) ሁሉ እንደደህና ካሜራ ቀርጸው ለተደራሲያን አካፍለውናል።

ከብዙ ብዙ ክፉ ገጠመኞቻቸውም መሃል እንዲህ እንዲህ ያለው ይጠቀሳል።

 “…አንድ ወታደር በዝግታ ወደሚሄደው ኦራል መኪና ሮጥ ሮጥ ብሎ ተጠጋና ከነጂው ጋር እንደመነጋገር ብሎ የመኪናውን መዝጊያ ይዞ በመንጠልጠል ከነጂው አንድ ነገር ይቀበላል። ያን መከረኛ ሲጋራ ይሆናል.. ምድር ያደበላለቀ ፍንዳታ ሰማሁ። ዓይኔን እዚያ አየው የነበረ መኪና ላይ ስወረውር መኪናው በጥቁር ጭስ ተሸፍኗል። ከጭሱ በላይ ወታደራዊ (ፊልድ) ጃኬት … ወደ ሰማይ ተወርውሮ እንደገና ይወርዳል… ወደ ተመታው መኪና ሮጬ ስሄድ… ነጂው አላንዳች ጉዳት አምልጧል።

 “ሌላስ ሰው ተርፏል?” ብዬ ጠየቅኩ።

ነጂው ራሱን ይዞ “እኔ ደህና ነኝ። ፈንጂው በሙሉ እሱ ላይ ነው ያረፈው” አለኝ።

“.. ያ ለካስ እንደቅጠልና እንደ ወረቀት ባየር ላይ ይንገዋለል የነበረው ጃኬት ቀደም ሲል የመኪናው በር ላይ ተንጠልትሎ የነበረ ወጣት ኖሯል። ዓይናችን እያየ አካሉ ተበጣጥሶ ባካባቢው ላይ ተዘራ። የሰው ልጅ ሕልውና እንዲህ በቅጽበት እንዳልነበረ ሆኖ ከትቢያ የሚደባለቅ ዘግናኝ ነገር ሆኖ ይቀራል።”” (ገጽ 206 – 207)

 ጸሐፊው የዚህ ዓይነቱን ቅጽበታዊ የሰው ልጅ ሕይወት ቅጥፈት በተለያዩ የጦር ሜዳዎች ላይ በተናጣልም በጅምላም አስተውለዋል። ይህ ከለጋ እድሜያቸው ጀምሮ አብሯቸው ያደገ እጣ ፈንታ ዛሬም ያ ክፉ ትዝታው ከውስጣቸው አልወጣ ብሎ እንደሚያሰቃያቸው በየምእራፎቹ ላይ እየተዘገነኑ ገልጸውታል።

በተለይም እጅግ በጀግንነቱ የሚያደንቁትና የሚወዱት ጓደኛቸው የመቶ አለቃ ተስፋዬ አያና፣ ሥርአት አልበኛና አምባገነን በሆኑ አዛዦች፥ ካድሬዎችና ተከታዮቻቸው ደባ እዚያው ጦር ግምባር ላይ እንዲረሸን መደረጉ እንደ እግር እሳት ሲያቃጥላቸው መኖሩን አምርረው ይገልጻሉ።

 “…ርሸናው በጠዋት መካሄዱንና ሃያ ሁለቱ ሰዎች መገደላቸውን ተስፋዬም… ከሌሎች የ324ኛ ሻለቃ አባላት ጋር መገደሉን ነገረኝ… በዚህ ዓይነት የገዛ ወገናችንን እያረድን በየሜዳው እየጣልን የትኛው ውጊያ ሊቀናን? … እግዚአብሄር የለም ማለት ነው እያልኩ ፈጣሪዬን የማማርርበት ደረጃ ደርስኩ… ሁላችንንም እንደኖህ ዘመን ያለ የጥፋት ውሃ አጥለቅልቆ እንዲጨርሰን ተመኘሁ። ባንድ ጊዜ ጠባዬ ሁሉ ተለውጦ ሌላ ሰው ሆንኩ። በረዥም የጦር ሜዳ አገልግሎቴ ብዙ የከፋ ውጊያ ስቃይና መከራ አሳልፌያለሁ። እንደዚያ ጊዜ ግን መንፈሴን የመረዘ ነገር አጋጥሞኝ አያውቅም።” (ገጽ 119/120) እያሉ በውስጣቸው የነበረውን ጽኑ መከፋት ገልጸውታል። በዚህ የራስን ወገን በራስ እጅ የመብላት ያልጌና ግምባሩ ክፉ ድርጊት፣ ከያንዳንዱ ብርጌድ ሃያ ሃያ ሰው፥ ከልዩ ልዩ ክፍሎች ደሞ ከመቶ ሰው በላይ ጭዳ እንደተደረገ ይተርካሉ ሻለቃ ማሞ። ይህ ሁሉ አሳዛኝ ድርጊት የተፈጸመው የበላዮች የሰጡትን የተሳሳተ የውጊያ አፈጻጸም ስልትና የተከተለውን ከፍተኛ ውድቀት፣ በምስኪን መስመራዊ መኮንኖች፥ የበታች ባለሌላ ማእርጎችና ተራ ወታደሮች ቅጣት ሸፋፍኖ ከተጠያቂነት እራስን ለማዳን ነበር።

በሌላም በኩል የኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ፈርጣማ የጭካኔ ክንድ እንደ ሜ/ጀኔራል ታሪኩ ዓይነቱን ምርጥ የዘመናችንን መኮንን ከማድቀቅ ያልታገተ ዓይኔ በወታደራዊ ሳይንስ በጦር አውድማዎች ውለው በእሳት የተፈተኑ ጀግና ነበሩ። ደራሲው የግፍ አገዳደላቸውን ምክንያት ልዩ በሆነ ገላጭ አነጋገር አስቀምጠውታል። “የጄኔራል ታሪኩ ዓይኔ መገደል የፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያምን የንዴት ግለት ለማብረድና የጭራቅነት ስሜታቸውን ለማርካት ካልሆነ በስተቀር ከጉዳት ሌላ ለሃገርም ሆነ ለሠራዊቱ የሰጠው አንዳች ጥቅም አልነበርም።” (ገጽ 282) አባባላቸው ትክክል ነው። ከዚያ በኋላ ጦሩ ከመሠረቱ እንደተናጋ ካብ ነበር የተናደው።

 ጸሃፊው ቀደም ብለውም ባወሱት አንድ አሳዛኝ ገጠመኝ ላይ እንዲህ የሚል ይነበባል። የመቶ አለቃ ጌታቸው ደምሴ የሚባል አንድ የመረጃ መኮንን ግዳጅ ላይ ፈጽሟል በተባለው የአፈጻጸም ስህተት በማርሻል ኮርት እንዲረሸን ይወሰንበታል። ውሳኔውን በበላይነት የሰጡት ጀኔራል አበራ አበበና ኮሚቴያቸው ነው። ሆኖም ከብርጌድ አዛዡ ከሻለቃ መረሳ የይሁንታ ምላሽ እስካልተሰጠ ድረስ ተፈጻሚ ሊሆን ስለማይችል ችኩሉና ጨካኙ ጀነራል አበራ ሻለቃ መረሳን ለስምምነቱ አጥብቀው ይጠይቋቸዋል። ቆራጡ ሻለቃ መልሳቸው አጭር ነበር። “ ጌታዬ፣ እንኳን እስረኛውን መኮንን እኔንም ቢሆን የማስገደልና የፈለጉትን ማድረግ የሚያስችል ሥልጣን ስላለዎት የፈለጉትን ማድረግ ይችላሉ እንጂ፤ ከማውቀውና ከማምንበት ውጭ በትእዛዝና በጫና ሰው ይገደል ብዬ አስተያየት አልሰጥም” ማለታቸውን በእማኝነታቸው የሰሙትንና ያሰተዋሉትን አስፍረዋል።

 ደራሲው፣ ያንዳንድ ብርቱ ጀግኖቻችንንም ተጋድሎና ሕልፈት ለዓይነት ያህል አልፎ አልፎ በየምእራፎቻቸው ውስጥ እንደጌጥ ጣል ጣል እያደረጉ ያተራረክ ስልታቸውን አጓጊና ጣፋጭ አድርገውታል። የጀግናውን፥ ያስተዋዩንና የቆራጡን የሻለቃ መረሳን ድንቅ የጦር ሜዳ ውሎ ያነሱባቸው ገጾች ብዙ ናቸው። በአልጌና ግምባር ለአምስት ዓመታት በበረሃ ሲጠበስ በቆየው ሠራዊት ውስጥ፣ የብርጌድ አዛዥ ሆነው ብዙ የጀግነንት ተግባሮችን የፈጸሙት የሻለቃ መረሳ ፍጻሜ የብዙዎችን ልብ የሰበረና ቆራጥነትን ያስጠየቀ ነበር ሲሉ ጸሃፊው ያስታውሳሉ።

 ሻለቃ መረሳ ብዙ ግዳጆች ላይ ሲውሉ ብዙ ያሟሟት አይነቶችን ሁሉ እየናቁ፥ ሞትና እሳቸው ከቶም ሊተዋወቁ እንደማይችሉ በልበ ሙሉነት እየተናገሩ ለጦሩ ሁሉ በጀግንነታቸው አርአያ እንደነበሩ ይህ መጽሃፍ ያወሳል። በተለይም ፈንጂ የሚባል ነገር ከቶም ሊደፍረኝ አይችልም የሚሉና የፈንጂ አደጋ ደምበኞች የሆኑትን እነ ሻለቃ ማሞን ያሾፉባቸው እንደነበር ተተርኳል፡፡

ከ1971 እስከ 1976 ዓ.ም. ድረስ ፈታኝ ፍልሚያዎች ባአልጌና ግምባር ሲካሄድ ቆይቶ፣ በመጨረሻው ላይ የጦሩ አቅም እየሳሳ መሄዱን ያወቀው ሻቢያ መጠነ ሰፊ ማጥቃት ሲሰነዝር ጦሩ የመፈታት መጥፎ እጣ ፈንታ ገጠመው። በዚህ ውጊያ ላይ ጠላት እየገፋ መጥቶ የወገን ጦር እሩብ ያህሉ ብቻ ማፈግፈግ ሲችል፤ የቀረው በሞትና በምርኮ ከጥቅም ውጭ ይሆናል። መቀመጫውን አዲስ አበባ ላይ ያደረገው የበላይ አካል መጀመሪያውንም ለጦሩ የክፉ ጊዜ ጥንቃቄና ዝግጅት ባለማድረጉ የሚደርስለት አጥቶ እንደወጣ ቀረ።

ሩብ ያህሉ ጦር በማፈግፈጉ ሂደት ላይ እያለ ጠላት የወገንን ድርጅት ይከብና የጅ በጅ የጨበጣ ውጊያው ይፋፋማል። ወዲያውም ከታንክ ጋር ግብግብ ይገጠማል፡፡ ሻለቃ መረሳ አጠቃላይ የጦርነቱ አካሄድና የደረሰበት ደርጃ ክፉኛ ያበሳጫቸዋል። እናም እራሳቸውን ለማጥፋት ሲሞክሩ ተረባርበው ጓደኞቻቸው ያስጥሏቸዋል። ግና ውስጣቸው በጠላት እብሪትና በበላይ አካላት ደባ የነፈረው ቆራጡ መረሳ ከመጨረሻው ውሳኔያቸው የሚናጠቡ አልነበሩም። ዙሪያቸውን የከበቡዋቸውን ውድ የትግል ጓዶቻቸውን አዘናግተው አንድ ቅጽበታዊ እርምጃ በራሳቸው ላይ ይወስዳሉ፡፡ የማጥቂያ የእጅ ቦምባቸውን ከመቅጽበት ከመጠበቂያው ይነቅሉና እላዩ ላይ ተኝተው አሰቃቂ ሞት ይሞታሉ።

ጸሃፊው ሻለቃ ማሞ ስለ እኚህ አለቃቸው እንዲህ ይላሉ። “… እርሱ ግን በተመኘው ዓይነት ነው የመጨረሻ እንቅልፉን ያንቀላፋው። ሻለቃ መረሳ ሁልጊዜ የሚላትንና የሚመኛትን ነው ያደረገው። ሻለቃ መረሳ ልበ ሙሉ ጀግና ከመሆኑም በላይ በሃገሩና በወገኑ ላይ ጥቃት ሲደርስ ማየትና ለጠላት መሸሸን በፍጹም አይወድም ነበር። ከዚህ ሞትን ይመርጣል። ውርደትን እንጂ ሞትን አይፈራም ነበር….። (ገጽ 50)

ጸሃፊው አንድ የውጊያ ውሎ ለወገን ጦር ያልተመቸና ጠላት ከባድ ጉዳት ያደረሰበት ሁኔታ ከገጠመ፣ እንደ አልጌናው ግምባር ፍጻሜ ሁሉ ለጠላት እጅን ላለመስጠት ሲሉ እራሳቸውን በራሳቸው የሚያጠፉ ብዙ ጀግኖች እንደነበሩ አውስተዋል። ከብዙዎቹም መካከል አንድን ጀግና ወታደር ወስደው እንዲህ አስነብበውናል።

ወታደር ደረጀ ይባላል።አንድ ወሳኝ ግዳጅ ላይ እንዳለ ትከሻውን ይቆስላል። እነሻለቃ ማሞ (ያኔ መቶ አለቃ) እንዲገለል ያግባቡታል። አሻፈረኝ ይላል። እናም ወደ ምሽጉ ገብቶ ጠላትን መፋለም ይቀጥላል። ግን ይህም አልበቃው ኖሮ ከምሽጉ ዘሎ ወጥቶ ወደ ጠላት ወረዳ ይወረወራል። ጸሃፊው እንዲህ ይገልጡታል…

 “እግሩን አንፈራጦ ቆሞ ክላሺንኮቭ ጠመንጃውን ባንድ እጁ በሙሃይቱ ደግኖ ያለውን ጥይት በጠላት ላይ ያርከፈክፈው ጀመር። … እግሮቹን መሬት ላይ ቸክሎ እስከ መጨረሻው ሕቅታ መተኮሱን አላቋረጠም።.. ደረጀ እልሁንና ቁጭቱን እስከ መራራ ፍጻሜው ድረስ ለመወጣት ሲል ያደረገውን ለማመን የሚያዳግት ገድል ነበር። ጥይት ሰውነቱን እየበጣጠሰውና እየቦጫጨቀው ፍንክች ሳይል የመጨረሻውን ጥይት ተኩሶ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መሬት ላይ በጀርባው ተዘረረ።” (ገጽ 155)

ከበደ ይባል የነበረው ጎበዝ መትረየስ ተኳሽና ሌሎችም ጀግኖች በስህተት ከወገን በተሰነዘረ የመድፍና የታንክ ድብደባ ማለፋቸውንም ጸሐፊው አልሸሸጉንም። ታዲያ ከበደ ቆሰለ እንጂ አልሞተም ነበርና ረዳቱ ተክላይ አሟሟቱን ለሻለቃ ማሞ እንዲህ ይገልጸዋል። “… ቆስሎ ደግፈነው ስናመጣ እራሱን ይረዳ ነበር… የተራራው አናት ላይ ደርሰን ወደ እርሶ እየተቃረብን ሳለ፣ የታንኩ ድብደባ ጀመረ። ወዲያው በያገኘንበት ቋጥኝ ስር ሁላችንም ተሸሸግን። እሱ ከተከለለበት ቦታ “ዶፍ” የሚል ተኩስ ሰማን። አጠገቡ ሄጄ ሳይ የገዛ ሽጉጡን ጠጥቶ ራሱን በራሱ አጥፍቶ አገኘሁት… እኔ ጀግና ሰው ሲሞት ማየት አልፈልግም። በከበደ ፈንታ እኔው በሞትኩ!” (ገጽ 181) ሲል ለጀግና ጓደኛው ህልውና የራሱን ሕይወት ቢገብርለት እንደሚሻ ላዛዡ ገልጦላቸዋል። ድንቅ ፍቅር፥ ድንቅ የትግል ጓድነት ቋጠሮ!

ሌላው ተጠቃሽ የመትረየስ ተኳስ ወታደር ሽመልስ ነበር። ወደ ጠላት ወረዳ ገስግሶ ሄዶ ተአምራዊ ማጥቃት የፈጸመና ሊያጠቃ የመጣውን የሻቢያ ጦር ድምጥማጡን ለማጥፋት ሰበብ የሆነ ጀግና ነበር። ከጉድባ ጉድባ መትረየሱን ተሸክሞ እየተሯሯጠ በጠላት ላይ ድንገተኛ ድልን ለወገን አጎናጸፈ። የማታ ማታም ቅንድቡ ላይ ተመቶ ይወድቃል። በላቸው የተባለው ረዳቱም ቁስሉን ቢያስርለትም ሽመልስ የሚተነፍስ አልሆነም። ሞተበት። እናም በላቸው አቃባሪ ፍለጋ ወደ ወገን ጦር ይፈጥናል። የሸመልስ አስከሬን ከነበረበት በርከት ብለው ሲመለሱ፣ የጀግናው አስከሬን ከመቃብር በታች ውሎ ያገኙታል። በዚያ ፍጥነት በማንና እንዴት ሊቀበር እንደቻለ ግራ ገብቷቸው ይመለሳሉ። አመሻሹ ላይም የጀግና ወታደራዊ ያቀባበር ሥነ ስርዓትን ያከናውኑለታል።

 የሽመልስ የጀግንነት ገድል እየተወሳና እየታሰበ እያለ ከስድስት ወራት በኋላ፣ በጦር ሃይሎች ሆስፒታል ውስጥ ታዬ የሚል ዜና ይሰራጭ ጀመር። ለካስ ጓደኛው በላቸው አቃባሪ ፍለጋ ሲሄድ፣ አግላዮች ደርሰው አስከሬኑን ወደ ማግለያ ጣቢያ ወስደውት ኑሯል። ታዲያ ሌሊት ላይ ካስከሬኖቹ መሃል የኩርፊያ ድምጽ የሚያሰማ ሰው አለ የሚል ጥቆማ ከቁስለኞች ለሃኪሞች ይደርሳል። ሃኪሞቹ ሊያጣሩ ሲሄዱ እውነትም ሞተ ያሉትን ያልሞተውን ሽመልስን ያገኙታል። በማግስቱ ከሌሎች ቁስለኞች ጋር ወደ አሥመራ በሄሊኮፕተር ይላካል… ከዚያም ለከፍተኛ ሕክምና ወዳዲስ አበባ ይሸጋገራል… ከዚያም ለከፍተኛ የቀዶ ጥገና ሕክምና ወደ ምሥራቅ ጀርመን ይበራል። የሚቻለው ሁሉ ተደረገለት… ግን ተባህር ማዶ ሲመለስ፣ ያይምሮ መታወክ ሰለባ ሆኖ መቅረቱን ስንረዳ ውስጣችን በሃዘን ተረታ።

 ስለ ጀግኖች የበታች ሹማምንት፥ ተራ ወታደሮች፥ መስመራዊና ከፍተኛ መኮንኖች፥ ጸሃፊው የሚነግሩንን ያህል ስላንዳንድ ጀግኖች የጦር አዛዦችም ያወሱናል። የኮሎኔል ለሜሳና የመቶ አለቃ ወጋየሁ ደግነቱ (ድምጻዊው… አፈር ይቅለለውና) የጦር ግምባር የግዳጅ አፈጻጸም ፍጥጫም ፈገግ ከማሰኘቱም ባሻገር፣ ፍጻሜው ልብን ያረካል። ጎበዝ የበላይ አካልና የጦር አዛዥ አንድን ጀግና በጭንቅ ጊዜ መውለድ እንደሚችል የኮሎኔል ለሜሳ ቁርጠኛ ወሳኔና ትእዛዝ፣ የመቶ አለቃ ወጋየሁን እንደዘፈኑ ሁሉ ጠላትን ቆርጦ ቆርጦ ለመጣል አስችሎታል… በተግባር።

 የኮሎኔል ቢሹ ገብረ ተክሌ አስደናቂ የግዳጅ አፈጻጸምም በደራሲው መጽሃፍ ውስጥ ውል ያለው ተጠቃሽ ነው። እኚህ ጀግና በትውልድ ክፍለ ሃገራቸው በኤርትራ ሰላም ሳይሰፍን ጸጉራቸውን ላለመቆረጥ ለራሳቸው ቃል ገብተው ይኖሩ የነበሩ ቆራጥ ነበሩ። ኮሎኔል ቢሹ ጥይት አይመታቸውም እየተባሉ ይታመኑ የነበሩና 31ኛ ሻለቃን ከኮሎኔል ክፈተው መርኔ ጋር ነፍስ አድን ተወርዋሪ ጦር አድርገው የገነቡ ጀግና ነበሩ። ዝርዝር ገድላቸው ብዙ ብዙ ነው። የሕልፈታቸው አሳዛኝነትም ያጫረውን ቁጭት ደራሲው በዝርዝር አስቀምጠውታል። በሻቢያ የተገዛችው ፍቅረኛቸው ሕይወታቸውን አስገብራቸዋለች። ታሪካቸውና ስማቸው ግን ከመቃብር በላይ ሁሌም ገኖ ይኖራል።

የብ/ጄኔራል ሣምሶን ኃይሌ ታላቅ ትእግሥትና የጄኔራል ተስፋዬ ሃብተ ማርያም ያወቅሁሽ ናቅሁሽ እብሪት ልዩ ትኩረት ከተሰጣቸው የዚህ መጽሃፍ ደራሲ ነጥቦች አንዱ ነው። (ገጽ 240) በፓርቲ መዋቅር የበላይ የሆኑት ተስፋዬ በጦር አዛዥነታቸው የበላይ የሆኑትን ጄኔራል ሣምሶንን እንዴት ባንድ ቀውጢ የግዳጅ ሰዓት ላይ እንደተፈታተኗቸው በሰፊው ገልጸዋል። ይህም ለጦሩ የዘመቻ ስኬት ምን ዓይነት ዳፋ እንደነበር ገልጸው፤ በሌላ ጎኑ ደግሞ እንደ ሜ/ጄኔራል ሁሴን አህመድና ሜ/ጄኔራል ረጋሣ ጅማ ዓይነት በሳል የጦር መሪዎች እንዲህ ያለ አለመግባባት ባለበት ስፍራ ላይ የተጫወቷቸውን ገንቢ ሚናዎች አካፍለውናል። በቁምነገር መሃል ፈገግ የሚያሰኙ ቀልዶችን ጣል ማድረግ የሚወዱትን የጄኔራል ሣምሶንን ስሜት በሚገባቸው ቋንቋ እየኮረኮሩ መረጋጋትን በቀውጢው ሰዓት ላይ ለማስፈን ያደርጉ የነበረው ጥረት የሚደነቅ ነበር።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top