በላ ልበልሃ

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሽግግር ባህል ክሽፈት ምንጭ ምን ይሆን?

የፖለቲካ ሽግግር ማለት ምን ማለት ነው? የመንግስት ለውጥ ነው? የሥርዓት ለውጥ ነው? የአመራሮች ለውጥ ነው? ወይንስ የሁሉም ለውጥ ድምር ውጤት ነው?

ሁሉም አይነት ለውጥ ቢሆን የራሱ መሰረትና የለውጥ ሥርዓት ካልተበጀለት በስተቀር አደገኛ ውጤት ሊያስከትል ይችላል። በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መንግስትና መሪ እንዴትና በምን መልኩ መለወጥ እንዳለበት ከመሰረቱ ተገቢውን ሥራ በመሥራት የተገበሩ ሀገራት በሂደቱ ተጠቃሚ ለመሆን ችለዋል። እነዚሁ ሀገራት የመንግስት ወይንም የአመራር ለውጥ በምን መልኩ መከናወን እንዳለበት ዲሞክራሲያዊ የሆነ አሰራር በማስቀመጣቸው የመንግስት ለውጥ በተደረገ ቁጥር የሚናጡበት የፖለቲካ ውጣ ውረድ አክትሟል።

 ዋነኛ ትኩረታቸውን ወደኢኮኖሚው መስክ በማድረጋቸውም በእድገት ለመስፈንጠር ችለዋል። በአንፃሩ ኢትዮጵያና መሰል ሀገራት ይህን አይነቱን የዲሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባት ባለመቻላቸው ሁልጊዜም የሥርዓት ለውጦችን በጦርነትና በአብዮት ለማምጣት ተገደዋል። በአብዮትና በጦርነት ወደ ሥልጣን የሚወጣውም ኃይል ከሥልጣን የሚወርደው በሌላ አብዮትና ህዝባዊ አመፅ ብቻ መሆኑ ደግሞ ነገሩን የማያቋርጥ አዙሪት ያደርገዋል። እናም በኢትዮጵያ እስከዛሬም ድረስ የፖለቲካ ሽግግር የሚደረገው በሥርዓት ለውጥ ብቻ ሆኖ እናገኘዋለን።

ከጥቂት አሰርት ያላለፈ እድሜ ያላቸው ሀገራት ከመሰል የሥርዓት ውጥንቅጥ ነፃ ወጥተው በዲሞክራሲ ሀዲድ ውስጥ በገቡበት ሂደት የቅድመ የሰው ልጅ መገኛና የስልጣኔ ቁንጮ እንደነበረች የሚነገርላት ኢትዮጵያ ግን ዛሬም የሀገር ግንባታ መሰረታውያን በሚባሉት ጉዳዮች ላይ እያጨቃጨቀች ትገኛለች። ኢትዮጵያ ትናንት እንደተፈጠሩት ደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያ፣ በቅርፀ መንግስት፣ ሕገ መንግስትና መሰረታዊ ሀገራዊ መገለጫዎች ዙሪያ ገና በርካታ ቁርጥ ያለ መፍትሄ ያላገኘች ሀገር ናት።

 ከሶስት መቶ ዓመታት ያላለፈ እድሜ እንደሌላት የሚነገርላት አሜሪካ በሀገር ምስረታ ሂደቷ በብዙ ፈተና ውስጥ በማለፍ ዛሬ በኢኮኖሚም ሆነ በስልጣኔ ጫፍ ላይ ትገኛለች። ከቅኝ አገዛዝ ሥርዓት ነፃ ወጥተው መንግስት ካቆሙ በኋላ የነፃ ሀገርነት እድሜያቸው ሲሰላ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ እድሜ እንኳን የሚበልጥ እድሜ የሌላቸው በርካታ የአፍሪካ ሀገራትም በብዙ መልኩ ኢትዮጵያን አልፈው ሲሄዱ ይታያሉ። በሰላም እጦትና በህልውና ሥጋት ውስጥ ወድቃ የነበረችውን ደቡብ ኮሪያ ኢትዮጵያውያን ምንጊዜም ታሪክ የማይረሳውን መስዋዕትነት በመክፈል ህልውናዋን ለማስጠበቅ ረድተዋል። ይህ የሆነው እ.ኤ.አ በ1953 የዛሬ 66 ዓመት አካባቢ ነበር። ደቡብና ሰሜን ኮሪያ ተለያይተው ደቡብ ኮሪያ እንደ ሀገር መኖር የጀመረችውም ከዚያ በኋላ ነበር። በዚህ አንድ መቶ ዓመት እንኳን ባልደፈነው የደቡብ ኮሪያ የሀገርነት ታሪክ ትላንት ኢትዮጵያውያን የተዋደቁላት ይህች ሀገር ዛሬ የት ደርሳለች?

 ደቡብ ኮሪያ በእነዚያ ዓመታት ባስመዘገበቻቸው ፈጣን የኢኮኖሚ ለውጦች በዓለማችን አሉ የሚባሉ ግዙፍ ኩባንያዎች ባለቤት ለመሆን ችላለች። ሌላውን እንተወውና ዛሬ በእያንዳንዳችን እጅ ያለው ሳምሰንግ ተንቀሳቃሽ ስልክ የደቡብ ኮሪያ ምርት እንደሆነ ስንቶቻችን እናውቃለን? የደቡብ ኮሪያው ሳምሰንግ ኩባንያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ባለው ከፍተኛ የገበያ ድርሻ እስከ ዛሬ ድረስ ለደቡብ ኮሪያ ኢኮኖሚ ምን ያህል አስተዋፅኦ እንዳበረከተ በሀገራችን ባለው የገበያ ድርሻ እንኳ መገመት ይቻላል።

በነገራችን ሳምሰንግ ኩባንያን በተንቀሳቃሽ ስልክ ምርቱና ቴክኖሎጂው በስፋት እንወቀው እንጂ ከቴሌቪዥን እስከ ማቀዝቀዣ፤ ብሎም ከዛ ያለፉ በርካታ የኤሌክትሮኒክስ ምርቶችን በስፋትና በገፍ የሚያመርት ግዙፍ ኩባንያ ነው። ዓመታዊ ገቢውም ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ከምታስገባው ሀገራዊ ገቢ በእጅጉ ልቆ እናገኘዋለን። እንደ ፎርቹን ግሎባል ዘገባ ከሆነ የሳምሰንግ ኩባንያ ዓመታዊ ገቢ ከ173 ቢሊዮን ዶላር በላይ ደርሷል። ዛሬ የኢትዮጵያን ዓመታዊ የኤክስፖርት ገቢ ስንመለከተው 3 ቢሊዮን ዶላር እንኳን መድረስ አልቻለም። ኢትዮጵያን ከደቡብ ኮሪያ ጋር ማነፃፀር ይቅርና ኢትዮጵያን ከአንዱ የደቡብ ኮሪያ ኩባንያ ጋር ማነፃፀር ራሱ የጥንቸልና የዝሆን ንፅፅር ያህል ሆኖ ይታያል። በዚህ አኳያ ሲታይ ትላንት ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ተዋድቀው የሀገርነትን ጎጆ ያዋጡላት ደቡብ ኮሪያ፤ ከኢትዮጵያ በብዙ እጥፍ በላቀ እድገት ውስጥ እንዳለች መገመቱ አያስቸግርም። ከሳምሰንግ ባሻገር ከተሽከርካሪ እስከ መርከብ የሚዘልቁ ግዙፍ ምርቶችን የሚያመርተው የደቡብ ኮርያው ዴው (Daewoo) ኩባንያ እንደሆነ ብዙዎቻችን የምናውቀው እውነታ ነው። በዓለማችን ቅንጡ ሞዴል አላቸው የሚባሉት እንደ ሀዩንዳይና ኪያን የመሳሰሉት ተሽከርካሪዎች ባለቤትነታቸው የደቡብ ኮሪያ ነው።

ደቡብ ኮሪያን በዚህ መልኩ እየበተንንና እየተነተንን በዝርዝር ብንመለከታት አንድ መቶ ዓመታትን ባልደፈነ የሀገርነት እድሜዋ በምን ያህል የእድገት መሰላል ውስጥ ወደላይ እንደተወነጨፈች መገመት ይከብዳል። በአንፃሩ የ3 ሺህ ዓመታት የመንግስትነት ታሪክ እንዳላት የሚነገርላት ኢትዮጵያ በፖለቲካውም ሆነ በኢኮኖሚው ከመንፏቀቅ ያለፈ ጉዞ መጓዝ አልቻለችም።

“ለሁሉም በሽታ አንድ አይነት መድሃኒት ስለሌለው ስለትክክለኛው መድሃኒታችን ለመነጋገር ስለትክክለኛው ሀገራዊ በሽታችን ሳንፈራና ሳናፍር መነጋገር መቻል አለብን”

ሀገራት በሀምሳና በመቶ ዓመታት ታሪካቸው ፍፁማዊ ለውጥ ውስጥ መግባት ከቻሉ ኢትዮጵያ ምን ችግር ገጥሟት ነው ጫጭታ የቀረችው? ከምንጊዜውም በላይ መፈተሽ ያለበት ችግራችን ምንድን ነው የሚለው ጉዳይ ነው። ፈረንጆቹ “A Problem clearly stated, is a problem half solved.“ ይላሉ። “ችግሩ በሚገባ የታወቀ አንድ ጉዳይ፤ መፍትሄው በግማሽ እንደተገኘ ይቆጠራል” እንደማለት ነው።

ስለዚህም ኢትዮጵያውያን ችግር ውስጥ እንዳለን ካወቅን የችግራችን ምንጭ ምንድነው ብለን መለየት መቻል አለብን። ችግር እንዳለብንማ ራሳችንን ከእኛ በእድሜ፣ በቆዳ ስፋት፣ በተፈጥሮ ሀብትና በመሳሰሉት የሚያንሱ ሀገራት በእጅጉ በእድገት ጎዳና ሲስፈነጠሩ ቀጭጨን እንደቀረን በጥቂት የንፅፅር ማሳያ ለመመልከት ችለናል። ሆኖም አሁን የሚያስፈልገው በሽታው መኖሩን ማወቅ ብቻ ሳይሆን የበሽታውንም አይነት ጭምር መለየት ነው። ለሁሉም በሽታ አንድ አይነት መድሃኒት ስለሌለው ስለትክክለኛው መድሃኒታችን ለመነጋገር ስለትክክለኛው ሀገራዊ በሽታችን ሳንፈራና ሳናፍር መነጋገር መቻል አለብን።

ኢትዮጵያውያን የውጪ ጠላቶችን በጋራ መመከት እንጂ የውስጥ ጉዳዮቻችንን በጋራና በመቻቻል መፍትሄ መስጠት እንደማንችል የቀደመ ታሪካችን መስታወት ሆኖ ያሳየናል። ኢትዮጵያውያን በመቆራቆስ፣ በመገፋፋት፣ ለስልጣንና ለግል ጥቅማችን ብቻ በመሯሯጥ ረዥም የታሪካችንን ክፍል በማሳለፋችን የታሪካችንን ረዥምነትና ቀደምትነት ያህል በእድገቱና በስልጣኔው ዘርፍ አልተገኘንም። እንደውም በመጨረሻው ረድፍ ላይ ነው የምንገኘው ማለት ይቻላል። ምሳሌዎችን እያነሳን ብንጨዋወት ይሄንን እውነታ ፍንትው አድርጎ ሊያሳይልን ይችል ይሆናል።

ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ በዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ በጉልህ ከሚታወሱት የኢትዮጵያ ነገስታት መካከል አንዱ ናቸው። ዓፄ ምኒልክ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለሀገራቸው በማስተዋወቁ ረገድ መሰረት የጣሉ ንጉስ ናቸው። ከዚህ ባለፈም ታሪካዊውን የአድዋ ጦርነት በድል በመወጣቱም ረገድ ዓፄ ምኒልክ የነበራቸው ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ሆኖም በስተመጨረሻ በገጠማቸው የጤንነት እክል ለዓመታት አልጋ ላይ መዋል ግድ ሆነባቸው። ይህ ሁኔታም ቀስ በቀስ በሀገሪቱ ከፍተኛ አመራሮች መካከል የሥልጣን ሽኩቻ እየተፈጠረ እንዲሄድ ማድረጉ አልቀረም።

ዓፄ ምኒልክ ከሳቸው ቀጥሎ ማን ዙፋኑን ወርሶ ሀገሪቱን ማስተዳደር አለበት? የሚለውን ጉዳይ ብዙም በማያሻማ መልኩ ምላሽ የሰጡበት ሁኔታ ነበር። በጊዜው በኢትዮጵያም ሆነ በቀረው ዓለም ወራሴ ዙፋን የሚመረጠው የዘር ሀረግን ተከትሎ ስለነበር ዳግማዊ ምኒልክም ከልጃቸው ከወይዘሮ ሸዋረጋ ምኒልክ እና ከራስ ሚካኤል የተወለደውን ልጅ ኢያሱን በመምረጥ የዙፋናቸው ወራሽ መሆኑን አስታወቁ።

 ይህን ቃላቸውንም በአዋጅ በማስረገጥ በጃን ሜዳ ለተሰበሰበው ህዝብ ተናገሩ። ልጅ ኢያሱ በወቅቱ ገና በአስራዎቹ መጀመሪያ የልጅነት እድሜ ላይ በመሆናቸው ከምኒልክ ጤንነት ክፉኛ መዳከምና ከእሳቸውም ልጅነት ጋር በተያያዘ በርካቶች በሀገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ ላይ ከፍተኛ ስጋት እንዲያድርባቸው አደረገ። የሥልጣን ግብግቡ የተጀመረው ዓፄ ምኒልክ ገና በአልጋ ላይ እያሉ ነበር። ልጅ ኢያሱ የንግስና ስልጣኑን እንደሚረከቡ ያረጋገጡት የሸዋ መኳንንት በልጅ ኢያሱ ዙሪያ ተኮልኩለው የሴራ ጉንጎናውን ተያያዙት።

ልጅ ኢያሱ የንግስናውን ዙፋን ተረክበው ሀገር ማስተዳር ይችሉ ዘንድ ጥቂት ዓመታትን በእድሜ መግፋት ነበረባቸው። ሆኖም ሀገርን የማስተዳደሩ ሥራ መቀጠል ስለነበረበት በራስ ቢትወደድ ተሰማ እንደራሴነት የልጅ ኢያሱን የንግስና ዘመን ለማስቀጠል የተደረገው ጥረት ከባድ ፈተና ገጠመው። ሁኔታው ፈተና የሆነው ዓፄ ምኒልክ ገና አልጋ ላይ እያሉ መኳንንቱ እቴጌ ጣይቱን ወደጎን ብለው ሥልጣኑን ሙሉ በሙሉ ለመረከብ የተደራጀ እንቅስቃሴ በመጀመራቸው ነበር።

ባለቤታቸው በህይወት እያሉ ሥልጣኑ ከቤተመንግስቱ መውጣት እንደሌለበት ፅኑ አቋም በያዙት እቴጌ ጣይቱና ሌሎች የምኒልክ ከፍተኛ አመራሮችና መኳንንት መካከል ከፍተኛ ውጥረት ሰፈነ። የልጅ ኢያሱ ሞግዚትና እንደራሴ ራስ ቢትወደድ ተሰማ እንደዚሁም የጦር ሚኒስትሩ ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ ያሉበት ቡድን እቴጌይቱን በመቃወም አድማውን የተደራጀ አደረጉት። ከጳጳሱ አቡነ ማትያስ ጀምሮ አብዛኛው የኃይል ሚዛን ከእቴጌ ጣይቱ በተቃራኒ ቢቆምም እቴጌይቱ ጥቂት የቤተ መንግስት አንጋቾችን እና ባለሟሎችን ይዘው አሻፈረኝ አሉ።

እናም እቴጌይቱን ለማግባባት የወቅቱ ጳጳስ አቡነ ማትያስ ወደ ቤተመንግስት ቢላኩም አቡኑ በወቅቱ የገጠማቸው ምላሽ ፈፅሞ የማይጠበቅ ነበር። በጊዜው አቡኑ በቤተመንግስቱ ባለሟሎች ከተራ ስድብ እስከ ድንጋይ ውርዋሮ የደረሰ ከባድ ተቃውሞ የደረሰባቸው መሆኑን የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ።

 የአድዋን ጦርነት ከመሩት ጀግኖች ኢትዮጵያውያን መካከል አንዷ የነበሩት እቴጌ ጣይቱ ከባለቤታቸው በፀና መታመም ጋር በተያያዘ ክብርና ዝናቸው ዝቅ አለ። በተከበሩበትና በታፈሩበት ሀገር ክብራቸውን የማይመጥን የቃላት መወራወር ውስጥ ገቡ። በወቅቱ የነበረው የውስጥ ለውስጥ የሥልጣን ሽኩቻ በከፋ ደረጃ እየተቀጣጠለ በመሄዱ ወሬው ከሀገር ውስጥ አልፎ የአውሮፓ ታላላቅ መንግስታት ዘንድም ደረሰ። ለዚህም ዋነኛ ምክንያቱ ምኒልክን ከሞት ለመታደግ በቤተመንግስቱ አካባቢ የነበሩት የውጭ ሀኪሞችና አንዳንድ ፀጉረ ልውጦች በአዲስ አበባ ለሚገኙ የአውሮፓ ሀገራት ዲፕሎማቶች ወሬውን እያሾለኩ በማቀበላቸው ነበር።

 በጊዜው የዲፕሎማቶቹ ዋነኛ ተግባራት ተደርገው ከሚጠቀሱት መካከል አንደኛው የአንድን ሀገር ውስጠ ምስጢር እያነፈነፉ ለሀገራቸው መንግስት ማቀበል ስለነበርም በኢትዮጵያውያን መኳንንቶች መካከል የነበረው የውስጥ የሥልጣን ይገባኛል ሴራና ትንቅንቅ ግልባጭ በነጮቹ እጅ ወደቀ። እናም ዲፕሎማቶቹ በበኩላቸው ምስጢሩን አስመራ በከተሙት የጣሊያን ጋዜጠኞች በኩል አሾልከው በአውሮፓ ጋዜጦች ላይ እንዲወጡ ያደርጉም ነበር።

 በዚህም የተነሳ በአድዋው ድል በአውሮፓ ምድር ጀግንነታቸው የናኘው ኢትዮጵያውያን ጤናማ የሥልጣን ሽግግር ማድረግ አቅቷቸው እርስ በርስ የመራኮታቸውና ጦር የመማዘዛቸው ጉዳይ ክብራቸውን ዝቅ አደረገው። በማክያቬላዊ የፖለቲካ ሴራ የቤተመንግስቱን ፖለቲካ የገለባበጠው የስልጣን ሽኩቻ እቴጌ ጣይቱን ከመገፍተር ባለፈ ልጅ ኢያሱንም ለግዞት ዳርጎ በስተመጨረሻ ዓፄ ኃይለ ሥላሴን ለረዥሙ የሥልጣን ዘመን አበቃቸው።

 ነገሩን ጠቅለል አድርገን ስንመለከተው ኢትዮጵያ አሁን ከተመለከትነው ከዳግማዊ ምኒልክ የሥልጣን ሽግግር መክሸፍ ቀደም ብሎም ሆነ በኋላ ኢትዮጵያን እየገጠማት ያለው ተመሳሳይ ታሪክ ነው። ከዚያ በኋላ በነበረው የሀገሪቱ የሥልጣን ሽግግር ታሪክ ዓፄ ኃይለ ሥላሴ በምን መልኩ ወደ ንግስናው ዙፋን ወጡ? በመሀልስ ምን ያህል ተግዳሮቶች ገጠሟቸው? በምንስ ሁኔታ ከዙፋናቸው ተወገዱ? ደርግስ እንዴት ወደ ሥልጣን መጣ? ኢሕአዴግስ በምን መልኩ የመንግስትነት ሥልጣን ሊጨብጥ ቻለ? በሚሉት ዙሪያ ብቻ በኢትዮጵያ ራሱን የቻለ የፖለቲካ ታሪክ ትንተና ሊካሄድ ይገባል።

 ይህም ኢትዮጵያን ከስልጣን ሽግግር ጋር በተያያዘ ለምን ችግር ይገጥማታል? ሁሌም የሚገጥማትን ይህን የችግር ምዕራፍ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ዘግታ በዲሞክራሲ የዳበረው ዓለም እንደሚያደርገው በሌሎች የእድገት ዘርፎች ላይ ትኩረት ማድረግ የምትችልበትን ሁኔታስ ለምን መፍጠር አልተቻለም? የሚሉትን ጉዳዮች በሚገባ ለመመለስ ያስችላል።

በእነዚህ ዙሪያ ተገቢውን ጥናት ማድረግ ማለት፤ በሌላ አነጋገር አሁን ስላለንበትና ወደፊትም ስለምንሄድበት አቅጣጫ ተገቢውን አመላካች ምላሽ መስጠት ማለት ነው። ይህንን ለማጥናት ደግሞ የኢትዮጵያውያን ባህል፣ አስተሳሰብ፣ የማህበረሰቡ ንቃተ ሕሊና፣ የእድገት ደረጃና የመሳሰሉት ጉዳዮች የጥናቱ ዋነኛ አካል መሆን ይኖርባቸዋል።

“…በዚህም የተነሳ በአድዋው ድል በአውሮፓ ምድር ጀግንነታቸው የናኘው ኢትዮጵያውያን ጤናማ የሥልጣን ሽግግር ማድረግ አቅቷቸው እርስ በርስ የመራኮታቸውና ጦር የመማዘዛቸው ጉዳይ ክብራቸውን ዝቅ አደረገው”

በየትኛውም ሁኔታ ኢትዮጵያ ላይ የነገሱ ነገስታትም ሆኑ ስልጣን ይዘው የነበሩ ኃይሎች ከኢትዮጵያውያን የወጡ ናቸው። ኢትዮጵያውያን መሪዎችና አመራሮች ወይንም እነዚህ አካላት የሚዘረጉት መንግስታዊ ሥርዓት በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ የኢትዮጵያውያን ባህል፣ አመለካከትና አስተሳሰብ ነፀብራቅ መሆኑ መዘንጋት የለበትም።

 በመሆኑም “የኢትዮጵያ መንግስታት ዲሞክራሲን ማስፈን አልቻሉም” ሲባል ጥያቄው ተመልሶ መወርወር ያለበት ወደራሱ ወደህብረተሰቡም ጭምር ነው። በማህበረሰቡ ቤተሰባዊ መዋቅር ውስጥ፣ በተለይም በዕድር፣ በዕቁብና በባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓቶች ውስጥ ዲሞክራሲን መትከል፣ መኮትኮትና ማሳደግ ካልተቻለ፤ ዲሞክራሲ ከአራት ኪሎ ቤተ መንግስት ሊዘንብ አይችልም። በርካቶች በቤተሰባቸው ውስጥ፣ ከፍ ሲልም በማህበረሰባቸው ውስጥ ሊያመጡት ወይንም ሊያሰፍኑት ያልቻሉትን ዲሞክራሲ መንግስት ከሚባል አንድ ግዙፍ ሀገራዊ ተቋም ሊያገኙት ይፈልጋሉ። እነዚህ ሰዎች የረሱት ቁም ነገር ቢኖር መንግስት ማለት የግለሰቡና የማህበረሰቡ ትንንሽ መዋቅሮች ድምር ውጤት መሆኑን ነው።

 የዲሞክራሲ ባህልን ባዳበረ ህብተረሰብ ውስጥ ኢዲሞክራሲያዊ መንግስት ሊፈጠር አይችልም። ቢፈጠርም እንኳን ነባራዊ ሁኔታው የተመቻቸ ስለማይሆንለት ውሃ እንዳጣ ችግኝ ደርቆ ከመሞት የሚያልፍ እድሜ ሊኖረው አይችልም። አምባገነኖች በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ በቀላሉ የሚበቅሉ፣ የሚያድጉ፣ የሚፋፉና ከዚያም አልፎ ለቀጣይ አምባገነኖች ሁኔታዎችን የሚያመቻቹ ከሆነ ጥናቶች ሊደረጉ የሚገባው የእነዚያ አምባገነን መንግስታትና ነገስታት ምንጭ በሆነው ህብረተሰብ ላይ ነው። ስለዚህም ኢትዮጵያውያን በዚህ ዙሪያ ላለው ችግር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍትሄ መስጠት ካለባቸው በህብረተሰብ ትንተና ላይ ትኩረት ያደረጉ ጥናቶችን ማካሄድ ይጠበቅባቸዋል።

የማርክሲስት ሌኒኒስት ሳይንሳዊ የማህበረሰብ ጥናት ፍልስፍናም፤ መንግስታት ወይንም መሪዎች የአንድ ማህበረሰብ ነፀብራቅ መሆናቸውን በመግለፅ፤ በመንግስታት የሚታዩ ማናቸውንም ችግሮች ለመቅረፍ በመጀመሪያ የዚያን ህብረተሰብ ታሪክና ነባራዊ ሁኔታ በሚገባ ማጥናት እንደሚያስፈልግ ይገልጻል። በመሆኑም የህብረተሰባችንን ባህል፣ አመለካከት፣ አተያይ፣ የንቃተ ሕሊና ደረጃ፣ ፍልስፍና፣ አገር በቀል እውቀት፣ ለውጪው የህብረተሰብ ክፍል ያለውን ተጋላጭነት፣ ማህበረሰባዊ ትስስርና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በየዘርፉ በጥልቀት ማጥናቱ እስከዛሬም ድረስ እየመላለስን እየወደቅንበት ካለው የፖለቲካ አዘቅት ሊታደገን ይችላል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top