አድባራተ ጥበብ

የበዕውቀቱ ሥዩም ስንኞች ሃተታ

መግቢያ

ግጥም እጥር ምጥን ባለ መንገድ መልዕክትን ማስተላለፍ የሚያስችል የድርሰት ስልት ነው። መልዕክቱ ውደሳ ወይም ወቀሳ፤ ምክር ወይም ማንገራገር፣ ዘፈን ወይም ሃዘን፣ ማባበል ወይም ማታለል፣ ወዘተ፣ ገላጭ ሊሆን ይችላል። የዚህ ጽሑፍ አንዱ ዓላማ በሙያው የተሰማሩ ደራሲያን እና ሃያሲዎች፣ ግጥሞችን እንዲተቹ እና እንዲተነትኑ ለመጎትጎት ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወጣቱ ትውልድ ለግጥም ከፍተኛ ፍቅር እንዳለው ፍንጮች እየታዩ ነው። «በጋለው ላይ ልጋግር» እንደሚባለው ሁሉ፣ ይህን ፍላጎት ወጣቱ፣ ያለውን የግጥም ፍቅር ደራሲያን እና ሃያሲዎች፣ በላቀ ደረጃ ሊያፋፉት ይችላሉ የሚል እምነት አለኝ። ወጣቶችንም የግጥም ደራሲዎች እንዲሆኑ ይገፋፋል። ግጥም መድረስ (መግጠም) ደግሞ መመራመርን ይቀሰቅሳል፣ የፈጠራ ችሎታን ያዳብራል፣ ያፋፋል ይባላል። እኔም ይህችን ጽሑፍ ሳዘጋጅ፣ ይህንኑ ግንዛቤ በተስፋ መልክ አንግቤ ነው።

 በመሠረቱ ግጥም በጥቂት ቃላት ብዙ ሁኔታዎችን መፈተሸ፣ መዳሰስ፣ መግለጥ፣ ማብራራት ሲሆን፣ ግጥሞች ለአንባብያን የመተርጎም ነፃነትን መድረክ ያበረክታሉ። ምንም መድረኩ የሥዕልን ያህል የሰፋ መፈንጫ ባይሆንም፣ መጠነኛ ልዩነት ላሏቸው አተረጓጎሞች መድረክ ሆኖ ያገለግላል። ስለሆነም እኔ ከታች የምሰጠው ትርጉም፣ የእኔን ዕይታ የሚያንፀባርቅ ነው፣ ሌሎችም የእኔኑ ዓይነት ዕይታ ቢኖራቸው አልደነቅም።

 ግጥም ማንበብ ብሎም ማነብነብ እወዳለሁ፤ በተገኘው መድረክ ሁሉ የግጥም ስንኝ መወርወር፣ ማስተጋባት ደስ ይለኛል። ያነበብኳቸው የአማርኛ ግጥሞች፣ ሁሉን ባላነብም ቅሉ፣ በብዛት በነባር ደራስያን (ነባር ያልኩት እኔ ተማሪ በነበርኩበት ወይም በወጣትነት ዘመኔ የተደረሱትን ነው) የተደረሱ ናቸው። በመሰለኝ እድሜ ቅደም ተከተል፣ ተሰማ እሸቴ (ነጋድራስ) ፣ ዮፍታሄ ንጉሤ (ቀኝ ጌታ)፣ ከበደ ሚካኤል፣ ሀዲስ ዓለማዬሁ፣ ተገኝ ተአምሩ ቢሻው፣ መንግሥቱ ለማ፣ ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው፣ ገብረ ክርስቶስ ደስታ፣ ፀጋዬ ገብረመድህን፣ ሰሎሞን ዴሬሳ፣ ተስፋዬ ገሠሠ፣ ዮሐንስ አድማሱ፣ ኃይሉ ገብረ ዮሐንስ፣ አያልነህ ሙላቱ፣ ፈቃደ አዘዘ እና ደበበ ሰይፉ፤ የሸረቧቸውን ስንኞች ብዙዎቹን አንብቢያለሁ፤ ብዙዎቹም መስጠውኛል።

እኔም ግጥም ለመጻፍ እሞክራለሁ።

  • የአዲሱ ትውልድ ደራስያን ግጥሞች፣ ምንም በየጊዜው የሚታተሙትን የግጥም መጻሕፍት ብሸምትም ብዙዎቹን የማንበብ እድል አላገኘሁም። ከዘመኑ ትውልድ (ወጣቶች) የግጥም ደራሲያን ስንኞች፣ ቀልቤን በጣም የሳቡት የበዕውቀቱ ሥዩም ግጥሞች ናቸው። የሱን ስንኞች ከነባር ደራስያን ድርሰቶች ጋር ላነፃፅራቸው እችላለሁ፤ የበዕውቀቱ ሥዩም ግጥሞች በአጭሩ ልዩ ናቸው፤ በራሳቸው ፈር ቀዳጅነት አዲስ መድረክ ላይ የሰፈሩ መስለው ነው የሚታዩኝ። ስለሆነም ጽሑፌ በዚህ ወጣት ደራሲ ግጥሞች ላይ ነው ያጠነጠነ።

 የበዕውቀቱ ሥዩም ጥቂት ግጥሞች ሃተታ

 ግጥም ምንም የስዕልን ያህል የዕይታን፣ የአተረጓጎምን አድማስ ባያሰፋም፣ በቂ መፈንጫ መስክ ያበረክታል። ስንኞች በሰም እና ወርቅ የተቀረጹ ከሆኑ፣ ስንኞቹ ስለተዛቁባቸው ቋቶች አንባብያን ሁሉ እኩል ግንዛቤ ስለማይኖራቸው፣ የዕይታዎች አድማስ የመለያየት አጋጣሚ ከፍ ያለ ይሆናል። ስለ አንድ የረቀቀ ግጥም አንባብያን ሁሉ አንድ ዓይነት ግንዛቤ ላይኖራቸው ይችላል፣ ስለሆነም በየግላቸው ስለ ግጥሙ የተለያዩ ግንዛቤዎችን ሊያነግቡ ይችላሉ። አንዳንድ ረቀቅ ያሉ በሰም እና ወርቅ የተዋቀሩ ግጥሞች ተደጋግመው ሲነበቡ፣ ከየአቅጣጫው እንደ ማለዳ (ጎህ) ብርሃን የሚፈልቀው ግንዛቤ እየዳበረ፣ የስንኞች ውበት እየፈካ አድማሶቻቸው እየሰፉ ይሄዳሉ።

የበዕውቀቱ ሥዩም ጥቂት ስንኞችን መርጬ ሃታታ ሳቀርብ፣ ስለ ስንኞቹ ያለኝ የዕይታ አድማስ (አተረጓጎም)፣ ከደራሲው ዕይታ ጋር አንድ ዓይነት ባይሆንም ይመሳሰላል የሚል ግምት አለኝ። የተለያዩ ግለሰቦች በግጥሞቹ ላይ የሚሰጧቸው ትርጉሞች ቢፈለጉም ብዙ ሊለያዩ አይችሉም፣ ልዩነቶቹ እንዳይሰፉ ስንኞቹ የተቀዋቀሩባቸው ቃላት ይገቷቸዋል። አግባብ ባለው (ትክክለኛ) የስንኝ ትርጉም ሂደት፣ ስንኞች ከተዋቀሩባቸው ቃላት ትርጉም (ቃላቱ ከማይወክሏቸው አስተሳሰቦች) ማለፍ አይገባም። አስተሳሰብ በቃላት ስለሚገለጥ በተገቢ ትርጉም የግጥሙ ትርጉም ቃላት ካጎሩት በረት አጉራ ዘሎ

መውጣት የለበትም። ከሆነም ድርጊቱ እንደ «ላም ባልዋለበት ኩበት

ለቀማ» ይመሰላል። (2)

«ስብስብ ግጥሞች» ተብላ በተሰየመች የደራሲ በዕውቀቱ ሥዩም የግጥሞች መድበል ውስጥ ያሉ ስንኞች፣ ከሁሉም አንፃር (ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ወዘተ) የማያንኳኩት በር የማይፈትሹት ጓዳ ያለ አይመስልም። ለዚህ አስተያየቴ ማብራሪያ ይሆኑ ዘንድ በጣም ጥቂት ግጥሞችን መርጬ ሃተታ አቀርባለሁ።

 የበዕውቀቱ ስዩም ግጥሞች አጠር መጠን ብለው፣ በብዙ ገፅ ሊተነተን የሚችል መልዕክት የሚያስተላልፉ ናቸው። ስንኞቹ አቅማቸው ግዙፍ፣ አድማሳቸው ሰፊ፣ ጥልቀታቸው እና ትንተናቸው ባህር ነው፤ ከነባር አስተሳሰብም ወጣ ያለ መልዕክትን ያስተላልፋሉ። በቅርብ ጊዜ ባጋጠሙኝ መድረኮች ሁሉ የዚህን የወጣት ደራሲ ስንኞች አነበንባለሁ።

 በዚህች ጸሑፍ የዚህን ባለግዙፍ ስጦታ ደራሲ ግጥሞች ከሁለት አቅጣጫ እተነትናለሁ። (ሀ) አንደኛ አጠር መጠን ከመሆናቸው አቅጣጫ ነው። (ለ) ሁለተኛ ደግሞ በቋተ ብዙነት ይዘታቸው ነው። ግጥሞቹ የተወሰዱት ደራሲው «ስብስብ ግጥሞች» በሚል ርዕስ ካሳተማት የግጥሞች መድበል ነው። (3)

 (ሀ) እጥር ምጥን ያሉ ግጥሞች

 አንድ አጠር መጠን ያለች ግጥም፣ ለዛ ካላት፣ የአካባቢ ተወዳጅነትን ትጎናፀፋለች፣ ብዙ አንባብያንንም ታፈራለች፣ ከዘመናት በኋላ ዘመን ሳይሽራት የደራሲው ማንነት ባይታወቅም እንኳ የአካባቢ ባህል አካል ሆና፣ በተለያዩ ሁኔታዎች በተለያዩ ግለሰቦች እንደ አጋጣሚው ሁኔታ የዕይታ ማብራሪያ፣ ምሳሌያዊ መግለጫ ሆና ትዘልቃለች፣ እየተዘረፈች ትነበነባለች። ይህም በነባር ባህል ላይ የተመሰረተ ድምዳሜ ነው፣ እንዲህ ዓይነቱ ባህል በአገራችን የተለመደ ሆኖ ይታያል።

 በገጠር አንድን አጭር ግጥም በተለያዩ ጊዜያት ለተከሰቱ ተመሳሳይ ድርጊቶች፣ አዲስ ለሚከሰቱትም ድርጊቶች፣ እያመቻቹ መጠቀም የተለመደ ነው። ለምሳሌ የሚከተለው ግጥም እንደሚባለው በዓፄ ቴዎድሮስ ጊዜ የተገጠመ ቢሆንም፣ በተደጋጋሚ በተመሳሳይ ሁኔታዎች ለምሳሌ በደርግ ዘመነ መንግሥትም ኅብረተሰብ ተጠቅሞበታል።

 በቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት፡

 «አባ ታጠቅ ካሳ የእግዜር ታናሽ ወንድም፣

 ይህንን ተውልኝ ሁለተኛ አልወልድም።»

 በደርግ ዘመነ መንግሥት፡

«መላኩ ተፈራ የእግዜር ታናሽ ወንድም፣

 ይህንን ተውልኝ ሁለተኛ አልወልድም።»

በተጨማሪ የማን ድርሰት መሆናቸው የማይታወቅ፣ ዘመን ገላጭ የሆኑ የዘፈን ስንኞች ብዙ ናቸው፣ ለምሳሌ

«ደብረክ ደብረክ አለች በነማይ ደባይ

 ወገቧን በሽጉጥ ተመትታለች ወይ? (4)»

 «ደብረክ ደብረክ ነው ወትሮም አካሄዷ

 እንኳን አርግዛና ሽል ይዛ በሆዷ። (5)»

 ስንኞች የግል ባለቤት ላይኖራቸው ይችላል፤ በገጠር ብዙ አጫጭር ግጥሞች ወደ አካባቢ ኅብረተሰብ ስንኝነት ተመንዝረዋል – ተቀይረዋል። እነኝህን መሰል ግጥሞች ማሲንቆ ገራፊውም ሆነ በገና ደርዳሪው ዘማሪ ለዘመናት ያዜሟቸዋል።

የበዕውቀቱ ሥዩም ብዙ አጫጭር ግጥሞቹ መኸዘብ የባሕል አካል የመሆን እድል እንዲገጥማቸው ምክንያት ይሆናል ብዬ እገምታለሁ። ለዚህ እይታዬ እንደምሳሌነት እንዲያገለግሉ ስድስት አጫጭር ግጥሞችን መርጫለኹ።

 ከስድስቱ ግጥሞች (ዝርዝርሩ ከታች ይቀርባል) ሁለቱን ከፍልስፍና አንፃር (ምንም እንኳን ሁሉንም ግጥሞች ከፍልስፍና አንፃር ለማየት ቢቻልም)፣ ሌሎች ሁለት ግጥሞችን ደግሞ ነባር ግንዛቤን ከመጠየቅ ከመፈተሸ አንፃር፣ ማለት ከለመድነው ዕይታ/እምነት በታቃራኒ መልክ የቀረቡ ናቸው። የቀሩት ሁለቱ ግጥሞች ደግሞ ፍፁም አዲስ ዕይታን የሚያንፀባርቁ በመሆናቸው፣ ዝርዝሩ እነሆ። ሆኖም የተመረጡት ግጥሞች ቦታ ሊቀያየሩ ይችላሉ፣ ለምሳሌ ነባር ግንዛቤን ከመጠየቅ ከመተፈሽ አንፃር የተመደቡት፣ አዲስ ዕይታን የሚያንፀባርቁ ተብለው ሊመደቡ ይችሉ ነበር፣ ወዘተ።

 ከፍልስፍና አንፃር

ሐተታ ቢራቢሮ

 ስንት ጊዜ ቀናኹኝ፣ በዚያ ቢራቢሮ

 ከእግዜር መዳፍ ቀድሞ፣ አበባይቱን ፈጥሮ

 እግሯን መንገድ ነስቶ፣ መሬት ላይ ተከለው

 ከሳማት በኋላ እንዳትከተለው።

ትንተና

 ለማነኛው ድርጊት አፃፋ እንዳለው ያመለክታል፣ ቁም ነገሩ አድራጊውን አፃፋው እንዳያውከው ማድረጉ ላይ ነው። በተጨማሪ አንድ ተግባር ከመፈጸሙ በፊት አፃፋው ምን ሊሆን እንደሚችል ማሰላሰል መጠንቀቅ እንደሚገባም ያመለክታል። ስለሆነም በሕይወት ሊገጥም የሚችል ተግዳሮት፣ በቅድሚያ አሰላስሎ፣ አስልቶ፣ ተግዳሮቱን የሚቋቋምበትን ወይም ከነአካቴው እንዳይከሰት የሚደረግበትን ስልት መተለም ያሻል።

ሌላ ህላዌ አለ

ጋን ከጀርባ ወድቆ ገል ሆኖ ቀጠለ

 ከመሰበር ወዲያም ሌላ ህላዌ አለ።

 ትንተና

በአገር ቤት ከሸክላ አፈር ከሚሰሩ የቤት እቃዎች ሁሉ ትልቁ ጋን ነው። ጋን የጠላ መጥመቂያ የጠጅ መጣያ የውሃ ማከማቻ ወዘተ ሆኖ ያገለግላል። መደበኛ አገልግሎቶቹ እነኝህን መሰል ሆነው ሳለ፣ ድንገት ከጀርባ ሲወድቅ ተሰባብሮ ወደ ገልነት ይቀየራል። ገል ሆኖም ግን ሌሎች አገልግሎቶችን ሊያበረክት ይችላል፣ ለምሳሌ እጣን ወይም መዓዛቸው ጥሩ ጥሩ የሆኑ እፅዋት ውጤቶችን (ለምሳሌ ጡንጅት፣ ወይራ) ማጤሻነት፣ እሳት ከጎረቤት መጫሪያ (አንድ ቤት ውስጥ የተዳፈነ እሳት ሲጠፋ፣ ከጎረቤት ረመጥ በገል አምጥቶ እሳት ማያያዝ የተለመደ የገጠር ተግባር ነው)።

 ይህ ምክር ማበረታቻ አዘል ግጥም፣ አንድ ግለሰብ ከቤት ከንብረት፣ ከሥራ ከሹመት፣ ተፈናቅሎ፣ ያልታሰበ ችግር ላይ ሲወድቅ፣ ተስፋ መቁረጥ እንደሌለበት ያበስራል። ለምሳሌ አንድ የቅርብ ወዳጁ፣ ጓደኛው መከፋቱን ሲያስተውል፣ የተከፋው ግለሰብም ቀን ጎደለብኝ ችግር የሰማይ ያህል በአናቴ ላይ ተደፋብኝ ብሎ ሲያመርር ሲሰማ፣ ለወዳጁ ጭንቀት ማስታገሻ ትሆን ዘንድ ይህችን ግጥም ለጓደኛው ሊያነበንብለት ይችላል።

ለዚህ ሁኔታ ገላጭ የሆነ በአገራችን የደርግ ዘመነ-መንግሥት አክትሞ፣ በኢሕአዴግ ሲተካ የተከሰተ በብዙ አካባቢ አነጋጋሪ የነበረ ጉዳይ አለ። የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት «የደርግ ወታደር» በመባል በጥቅሉ ተፈርጆ፣ እንዲበተን ሲደረግ፣ ብዙ ሰማይ የተደፋባቸው የቀድሞው የመከላከያ ሰራዊት አባላት፣ በቀደመው መንግሥት አገር ዕይታ ሕይወታቸውን እስከ መሰዋት ድረስ ቆርጠው ተሰማርተው የነበሩ በየጉራንጉሩ ወድቀው ይታዩ ነበር። ብዙዎች ከጀርባ (ከትክሻ ቢባል ይመረጣል፣ ወንድ ጋን የሚሸከም በትክሸው ነው) የወደቀ ጋን ሆነው በተለያዩ አገልግሎቶች ላይ ተሰማሩ፣ በጥበቃ ተቋማት ተቀጣሪነት ወይም በግል፣ በንግድ ድርጅቶች፣ በኩባንያዎች (በባንክ፣ በኢንሹራንስ ወዘተ) የሚያገለግሉ ብዙ ናቸው። ሌሎች ብዙዎች ለዘመናት ሥራ አጥ እንዲሆኑ ተደርገዋል። የሚገርመው ደግሞ፣ በጣም ጥቂቶች ይኹኑ እንጂ፣ በንግድ ስራ ተሰማርተው፣ የግል ችግሮቻቸውን አሽቀንጥረው ጥለው፣ ለሌሎች ብዙ ግለሰቦች ኑሮ አለኝታ ለመሆን የበቁ አሉ (ምሳሌ፤ የበላይነህ ክንዴ አስመጭና ላኪ ኩባንያ ዋና ተዋናይ)። ህይወት በተለየ ሁኔታ እና አጋጣሚ መቀጠሉን ለማብራራት ያስችላል።

ነባር ግንዛቤን ከማናጋት አንፃር

 በዕውቀቱ ሥዩም ነባር እምነት-አከል፣ እምነት-መሰል ጉዳዮችን አብዛኞቻችን ከምናውቀው ከተገነዘብነው ውጭ የመመልከት ችሎታው በጣም ከፍ ያለ እና ከብዙዎቻችን የላቀ ነው። አንድን ጉዳይ ከብዙ አቅጣጫ መመልከት ጠቀሜታ እንዳለውም ያስረዳናል።

 ፍግ ላይ የበቀለች አበባ

አበባይቱም አለች፣

ፍግ ላይ የበቀለች

«ምንድነው ጥበቡ?»

ኔክታር ማጣፈጡ

አደይን ማስዋቡ፣

እኔም መለስኩላት፣

«ይብላኝ ለንብ እንጂ ዝምብማ ይተጋል

ከቆሻሻ ዓለም ውስጥ ጣ’ምን ይፈልጋል።»

ትንተና

ነባር እምነት ንብን አሞጋሽ ዝንብን ወቃሽ ነው፣ ያም እምነት/ አስተያየት በአለቃ ተገኝ ተአምሩ እንደሚከተለው ቀርቧል። (6)

 ባለሙያ ንብ ነው ከጥበብ አበባ

ዘወትር ይቀስማል ሲወጣ ሲገባ።

ሰነፍ ግን ዝምብ ነው ለሰው ጤና ጠንቅ

ሌላ በሠራው ላይ ገብቶ እሚዘፈቅ።

ትንተና

ንብ ከአባባ የሚገኙ «ኔክታር» እና «ፅጌ ብናኝ» (pollen) ቀስማ ነው ማር የምትፈበርከው። ንብ ጎራ የምትልበት ለጣዕም የተዘጋጄ «ኔክታር» ያለበት አካባቢ በአበባ አሸብርቆ ደምቆ ነው የሚታይ፣ ስለሆነም ንብ የምትጎበኘውም የተዋበ አካባቢን ብቻ ነው። ከዚያም አካባቢ ኔክታር ፅጌ ብናኝ ሰብስባ ማርን ታዘጋጃለች። የማር መቀመሚያ መሰረታዊ ጥሬ ዕቃ (ኔክታር እና ፅጌ ብናኝ) በጣም ውስን በሆነ ርቀት፣ ከአንድ የሕያው አካል ክፍል (ከአበባ) ነው ጥሬ ዕቃ የምትዘርፍ። ያንንም ለመተግበር ንብ ብዙ ውጣ ውረድ አይገጥማትም። ዝምብ ግን ተስፋ ሳትቆርጥ ወጥታ ወርዳ ነው ከቆሻሻ መኻል፣ ከሚገማ፣ ከሚከረፋ አካባቢ፣ ብዙ ለፍታ፣ ታትራ፣ ማስና፣ ደክማ ነው ጣዕም ያለው ምግብ የምታዘጋጀው። ከቆሻሻ አካባቢ የምታዘጋጀው ምግብ ምንም ለሰው ልጅ ባይተርፍም ለዝምብ ምግብነት ይበቃል። ስለሆነም ለዝምብ ጣዕም ያለው ምግብ ለማዘጋጀት እንደ ንብ ተግባር አልጋ በአልጋ አይሆንም። ተግባሯም በወግ የታጠረ (ውብ አበባ፣ ጣፋጭ መዓዛ ወዘተ ተዘጋጅቶ እንዲጠብቅ ማስፈለግ) አይደለም። ዝምብ ካልባሌ ቦታ ጣዕም ያለው ምግብ ሰብስባ በመመገብ ትኖራለች። ስንኞቹ ዙሪያ ጥምጥሙን ሳይመለከቱ መፈረጅ አይበጅም የሚል መልእክት ያስተላልፋሉ።

ዳዊት እና ጎልያድ

እግዜርና ዳዊት፣ አብረው ተቧደኑ

ብቻውን ታጠቀ፣ ጎልያድ ምስኪኑ

አንዳንዱ ተገዶ፣ ለሽንፈት ሲፈጠር

በጥቅሻ ይወድቃል እንኳንስ በጠጠር።

ትንተና

የጦር ትጥቅ ሳይሆን፣ የእግዚአብሔር ድጋፍ፣ ረዳትነት ነበር የፍልሚያውን ውጤት ወሳኝ የሆነው። በእግዚአብሔር እርዳታ ምስኪኑ ዳዊት ትእቢተኛውን፣ ኃይለኛውን፣ ጎልያድን ድል ነሳው፣ ገነደሰው፣ ብሎም አረደው። የበግ እረኛ የነበረው ዳዊት፣ የእስራኤል ሠራዊት አባል ለነበረው ወንድሙ ስንቅ ለማቀበል ወደ ጦር ሜዳ አካባቢ እንደሄደ ነበር ከፍልስጤማውያን ወገን የተሰለፈ፣ ጎልያድ የሚባል ግዙፍ፣ አስፈሪ፣ ትእቢተኛ እና ትምክህተኛ ለውጊያ እንደተሰለፈ የሰማ። ጎልያድ ከራስ ጠጉሩ እስከ እግር ጥፍሩ ጡሩር የለበሰ፣ ሰይፍ የታጠቀ፣ ጦር የያዘ «እስኪ እኔ ነኝ ያለ ወንድ ከእስራኤል ጦር ይግጠመኝ» እያለ ተራራ ቁንጮ ላይ እየቆመ ለአርባ ቀናት ይፎክር እንደነበረ ይተረካል። የትጥቁን ጥራት እና የአካሉን ግዙፍነት ያስተዋሉ እስራኤላውያን ሲያዩት ብቻ ልባቸው እየራደ፣ እየተረበሸ፣ ሊፋለሙት ፈቃደኞች አልነበሩም።

በእግዚአብሔር እገዛ የሚተማመነው የእስራኤል ንጉሥ ሳዖል፣ ይህንን ጥጋበኛ ለሚያንበረክክ ግለሰብ ሽልማት እንደሚሰጥ ይፋ አደረገ። ይህን ዜና የሰማው ወጣቱ ዳዊት፣ ልቡን አደንድኖ ያንን ግዙፍ ፍጡር፣ ጎልያድን፣ ለመፋለም ወሰነ። ዳዊት አንድ ወንጭፍ እና አምስት ወፍ ማባረሪያ መሰል ጠጠሮች ብቻ ይዞ፣ ብረት ለበሱን ጎልያድን ለመፋለም ወደ ጎልያድ ተጠጋ።

 ጎልያድ ይህን ሊፋለመው የመጣውን ወጣት ሲመለከት፣ በወጣቱ ሳቀበት፣ አፌዘበት፣ «አንተ ነህ ወይ እኔን የምትፋለም»? በማለት። ዳዊትም መለሰለት «ዛሬ እግዚአብሔር በእኔ ክንድ ይጥልኻል፣ እገድልሃለሁ፣ የወገኖችህን የፍልስጤማውያንንም ሬሳ ያሞሮች ቀለብ፣ የዱር አራዊት ማዕድ አደርገዋለሁ» ብሎ መለሰለት። «እግዚአብሔር በሰይፍ በጎራዴ ሳይሆን የሚያሸንፍ በፈቃዱ ብቻ ነው፣ እኔ በእግዚአብሔር ፈቃድ ድል አደርግኻለሁ» አለው። ቀጠል አድርጎም ይህ ሲሆን አለ ዳዊት «ዓለም በሙሉ የእስራዔል አምላክ እንዳለ፣ ያውቃል፣ ይገነዘባል።»

ዳዊት በመጀመሪያ በወነጨፋት ጠጠር፣ ጎልያድን መኻል ግንባሩ ላይ (ግንባሩ መስቀለኛው ላይ) መትቶ ጣለው፣ ከዚያም ግዙፉ ጦረኛ ከወደቀበት ቦታ ዳዊት ደርሶ፣ ጦረኛው ታጥቆት የነበረውን ሰይፍ ከአፎቱ መዝዞ አውጥቶ፣ የጎልያድን አንገት ቆረጠው፣ ከዚያም የጦረኛውን ግዙፍ ጭንቅላት በንጉሡ ፊት ግዳይ ጣለ።

በዳዩን ጎልያድ ተበዳዩን ዳዊት አድርገን እኛ የተገነዘብነውን፣ በዕውቀቱ ሥዩም በተገላቢጦሽ በደለኛው ጎልያድን ተበዳይ ያደርገዋል፣ ምርጫ የለሽ፣ ሲፈጠር ሊጠቃ እንደተወለደ አድርጎ ያቀርብልናል። አሸናፊው ሁልጊዜም ከእግዚአብሔር ጋር የቦደነው ነው፣ ከዚያ የላቀ ኃይል አለ ብሎ አይገመትም እና፣ መገመቱም ራሱ «ሃራም» ይሆናል። ከእግዚአብሔር ፈቃድ ደግሞ ዝንፍ ማለት የለም። ተበዳዩ ሳይፈልግ እና ለነባራዊ ሁኔታዎች ያለው ዝግጁነት ሳይጎለው፣ ለመሸነፍ የተፈጠረው ጎልያድ ነው ብሎ ያብራራልናል።

አዲስ እይታን የሚያንፀባርቁ ዘመን ሲታደስ

እኛ’ኮ ለዘመን ክንፎች አይደለንም ሰንኮፍ ነን ለገላው፣

 በታደሰ ቁጥር የምንቀር ከኋላው።

ትንተና እኛ በተለምዶ «ስንኳን ከዘመን ዘመን አሸጋገረን» እንላለን፣ በዕውቀቱ የሚያስረዳን ግን፣ የተሸጋገረው ዘመን እንጂ እኛማ እያረጀን ነው፣ እድሜ ጨመርን ደመርን እንጂ፣ እድሜያችንን እርጅናችንን አውልቀን ጥለን ወደፊት አልዘለቅንም። ዘመን ነው ጥሎን ያለፈ ይለናል። የዘመንን እንቅስቃሴ ሲያብራራ፣ ሲገልጥ፣ በእግሮች የሚጓዝ አላደረገውም፣ ከናፊ ነው ያደረገው፣ ጊዜ እየበረረ መሄዱን ነው የሚያሳየው። ጊዜ በረረ የምንል ደግሞ ሳንጠቀምበት ያለፈ ሲመስለን ነው።

 ዘመንን እንደ ሰይፍ ስንመስለው እኛ እንደ አፎት እንመሰላለን። ሰይፉ ሲመዘዝ (ጊዜ ሲተም) አፎቱ ወደ ኋላ ይቀራል። ዘመን እኛን ከገላው ከልቶን ነው የሚከንፍ። እባብ ስንኳን ሰንኮፉን ጥሎት ሲሄድ ስለጠበበው፣ ቀዶት፣ አሮጌውን ሰንኮፍ በአዲስ የገላ ሽፋን ተክቶ ነው የሚሄደው። ጊዜም አዲስ ዘመን (አዲስ የገላ ሽፋን) ያበጃል፣ ይብላኝ ሰንኮፍ ሆኖ ለሚጣለው ዘመን ላለፈበት ትውልድ እንጂ። ስለሆነም ከዘመን ዘመን መሸጋገር በበዕውቀቱ ሥዩም ዕይታ በአዲስ ገላ ተተክቶ ፋይዳ ቢስ ሆኖ መጣል፣ እንደ አሮጌ ዕቃ ጨርቅ መወርወር ነው።

ባዶ ድስት

ሌሊቱ ይነጉዳል!

እሳቱ ይነዳል

አልቦዘነም ጣቴ ጊዜ እና ጭራሮን አፍሶ ይማግዳል

ባዶ ድስቴን ልጣድ ባዶ ለማገንፈል

ከንፍገት ይሻላል ዕጦትን ማካፈል።

ትንተና

ተግባሩ የሚከናወነው ሌሊት ነው። ጭር ያለ ሌሊት ይመስላል። የሚሰማ ድምጽ ካለም፣ ጭራሮ ለማገዶነት ሲዘጋጅ፣ ሲሰበር ወይም በእሳት የተያያዘ የጭራሮ ትንታግ ሲፈነጠር፣ ሲወነጨፍ ነው። ጭራሮ የሚማግዱት ጣቶች ደግሞ አመድ ተላብሰው ወዝ አልባ ቆዳቸው ያለ ሥጋ ድልዳል ከመዳፍ አጥንቶች ላይ የተለጠፈ ይመስላል።

 በሌሊት ካለ እረፍት ምንም የሚበስል ምግብ የሌለበትን ዕቃ እሳት ላይ ጥዶ፣ እንቅልፍ-አልባ ሆኖ ጊዜ ማባከን የጭንቅ ኑሮ አንፀባራቂ እንደሆነ ይገመታል። ችግር ያንሰራፋባት ደሳሳ ጎጆ እንደሆነች ያመላክታል። እንደዚያም ሆኖ ግን ባለጉዳዩ ተስፋ አልቆረጠም። እንዲያውም ከራሱ ችግር አልፎ ለሌላ ችግረኛ ለመለገስ ያስባል።

 . በዕውቀቱ ሥዩም የለጋስ ስጦታን (ልግስናን) ከቁስ አካል አምባ አውጥቶ፣ ከፍ ባለ ደረጃ ገምቶ፣ እምነት አከል ይዘት ያጎናጽፈዋል። ወደ ማይታየው ወደ ማይዳሰሰው ዓለም ያሸጋግረዋል። ለጋስነትን ቅን አስተሳሰብ ያደርገዋል፣ ሃሳብ ብቻ ይበቃል እንደማለት። ለጋሱ ደሃ ወይም ባለሃብት ሊሆን ይችላል፣ ልግስና ቁስ-ነክ ስላልሆነ፣ በልግስና ዓለም በሁለቱ መኻል (ደሃ እና ባለሃብት) ልዩነት አይኖርም።

 (ለ) ቋተ-ብዙ ግጥሞች

ቅኔ ቋተ-ብዙ ነው፣ ከብዙ ቋቶች የተሰነቀ ማዕድ ነው (ለምሳሌ እንደ እንጎቻ፣ ድፎ ዳቦ፣ ምጥን ሽሮ፣ ወዘተ.) ይባላል። ቋተ-ብዙ የሆኑ የአማርኛ ግጥሞችም አሉ፣ ግን ቋተ ብዙ መሆናቸው ብቻ በቅኔነት አያስመድባቸውም። ቅኔ ጠበቅ፣ ጠበቅ፣ ያሉ በሥርዓት የተዋቀሩ ይዘቶች አሉት። እነኝህ የቅኔ ባህሪዎች ናቸው የአማርኛ ግጥምን ከቅኔ መንደር እንዳይደመር የሚያስተጓጉሉ። በተጨማሪም ቅኔ በቃል የሚነበነብ እንጂ በጽሑፍ የሚመዘገብ አይደለም፣ ስለሆነም ነው «የቅኔ ቋንጣ የለውም» የሚባለው። (7) ሆኖም ምርጥ ምርጥ ቅኔዎች፣ እንዳይረሱ፣ በቅርስነት ለትውልድ ሊተላለፉ ይችሉ ዘንድ፣ በጽሑፍ የሰፈሩ በመድበል መልክ የተዘጋጁ አሉ። ከነኝህም መጻሕፍት ፈር ቀዳጆቹ፣ በሁለት ስመ-ጥር ሊቃውንት የተዘጋጁት ናቸው፣ በብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሤ እና በመልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ።

 በቋተ-ብዙነታቸው ከቅኔ ጋር የሚመሳሰሉ ሁለት ግጥሞች ከበዕውቀቱ ሥዩም መድበል አቀርባለሁ።

አልወጣም ተራራ

አልወጣም ተራራ ዳመና ልዳብስ

ቀስተ ደመናውን ሽቅብ ልቀለብስ

አልዋስም እኔ ካ’ቡነ ተክሌ ክንፍ ከያዕቆብ መሰላል

እኔ መውጣት ሳስብ ሰማዩ ዝቅ ይላል።

ትንተና

ተራኪው የተባዘተ የጥጥ ነዶ የመሰለውን ደመና ለመዳሰስ ወይም የቀስተ ደመናን ሕብረ-ቀለም በቅርበት ለማየት ቢመኝ አይፈረድበትም። ተራኪው የደመናን ውበት ብቻ ገልጦ አልቆመም። ቀስተ ደመናውን ሽቅብ ለመቀልበስ ወደ ሰማይ መውጣት ማስፈለጉን ከገለጠ በኋላ፣ ወደ ሰማይ ለመውጣት የማንንም እርዳታ እንደማይሻ ይገልጣል። ምንም በያዕቆብ መሰላል በመጠቀም ወይም ከአቡነ ተክለሃማኖት ክንፍ ተውሶ ወደ ሰማይ መውጣት ቢቻልም፣ ተራኪው ያን መሰል እርዳታ እንደማያስፈልገው ይገልጣል። ሁለቱም የትረካው ቋቶች በእምነት ዙሪያ ያጠነጥናሉ።

በብሉይ ኪዳን ዘፍጥረት ውስጥ እንደተገለጠው የይሁዳውያን የሃይማኖት አባት የነበረው ያዕቆብ አንድ ድንጋይ ተንተርሶ ሸለብ አድርጎት ሳለ፣ በህልሙ ሰማይን እና ምድርን የሚያገናኝ መሰላል አዬ። በመሰላሉም መላእክት ወደ ሰማይ ይወጡ ወደ መሬት ይወርዱበት ነበር። (8)

የአቡነ ተክሌ ክንፍ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ጋር የተገናኘ ነው። አባ ተክለሃይማኖት ደብረ ሊባኖስን የመሰረቱት መነኩሴ ሲሆኑ፣ ወደ እየሩሳሌም ሄደው የጎሎጎታን ተራራ የመጎብኘት ፍላጎት፣ ምኞት ነበራቸው። ሰይጣን ይህን ምኞት ለማጨናገፍ ፈልጎ፣ አባ ተክለሃይማኖት ከሚኖሩበት ቋጥኝ (የገደል አፋፍ) ወደ ታች የሚወርዱበትን ገመድ፣ እሳቸው ወደ ምድር በገመዱ ተንጠላጥለው በመውረድ ላይ እንዳሉ ገመዱን ቆረጠው (በጠሰው)።

 ገመዱ ሲቆረጥ ታላቁ መነኩሴ ከገደል አናት ወርደው አለት ላይ ተፈጠፈጡ። በዚያም መንስዔ እግራቸው ተሰብሮ መሄድ ተሳናቸው። ሆኖም እግዚአብሔር የሰይጣንን ተንኮል ተመልክቶ፣ ጎለጎታን የመጎብኘት ምኞታቸው እንዲሳካ ለተክለሃይማኖት ስድስት ክንፎች (በስዕሉ ሦስት የቀኝ ሦስት የግራ) ለገሳቸው። ከዚያም አባ ተክለሃይማኖት እየከነፉ ወደ እየሩሳሌም ይመላለሱ ነበር ይባላል።

እንግዲህ ተራኪው ወደ ሰማይ ለመውጣት ሲከጅል ሰማይ ይረግባል፣ ሸብረክ ይላል በዚያ ሂደት ተራኪው ደመና ለመዳበስ ይችላል። «ተራራው ወደ መሐመድ ካልሄደ፣ መሐመድ ወደ ተራራው ይሄዳል ነው»።

ይህም አባባል ከትረካ ቋቶች አንዱ ነው፣ ይህን የጻፈም «ፍራንሲስ ቤከን» የታወቀ ደራሲ በ1625 ገደማ ሲሆን፣ ተራራው ወደ መሐመድ የማይመጣ ከሆነ፣ መሐመድ ወደ ተራራው ይሄዳል ሲል፣ በመግባባት ጥረት፣ አንድ ግለሰብ ያሰበው፣ ምርጫው ካልተሳካለት፣ ሌላ አማራጭ መቀበል አለበት ነው፣ እርቅን፣ ሰላምን፣ መግባባትን የሚሻ፣ የግድ እኔ ያልኩት ይሁን አይልም ነው ትርጉሙ። በዕውቀቱ ሥዩም፣ በተገላቢጦሽ እኔ ወደ ላይ (ወደ ሰማይ) መውጣት ሳስብ (ስመኝ) ሰማዩ ዝቅ ይላል ነው የሚለው፣ መመኘት እንጂ መግባባት አያስፈልገኝም ነው የሚለው፣ ከ«ፍራንሲስ ቤከን» ተገላቢጦሽ። ይህን ዓይነት ድርጊት ብቻ ተራኪውን አላረካውም። ደመና-መሰል፣ ደመና-አከል፣ «ጉም» መሬት ለመሬት ስለሚንኳተት ያንን ለማድረግ አያዳግት ይሆናል፣ የግድ ወደ ሰማይ መውጣት አያስፈልግም። ሁለተኛው ምኞት ነው አስቸጋሪው፤ «የፊዝክስ ሕግ» ቀስተደመናን ሽቅብ ከመቀልበስ ያግዳል። ስንኞቹ የሚያብራሩልን ተራኪው በጣም በራሱ እንደሚተማመን ነው። ከዚያም አለፍ ይላል፣ አባባሉ እብሪተኛ ያስመስለዋል። ከፍ ባለ ድምጽ ወደ ትእቢተኝነት ያጋደለ፣ ከመተማመን የዘለለ፣ ብሎም የእብሪተኛ አዋጅ ያወጀ ያስመስለዋል። ቀስተ ደመናን ሽቅብ በመቀልበስ፣ ፍንክች የማይለውን የፊዝክስ ሕግ እጥሳለሁ ይላል።

ኀሠሣ ሰላም

ማጭድ ይኾነን ዘንድ፣ ምንሽር ቀለጠ

ዳሩ ብረት እንጂ ልብ አልተለወጠ

ለሣር ያልነው ስለት፣ እልፍ አንገት ቆረጠ።

ትንተና

ማረሻ እንደ የልማት መሳሪያነት ሲታይ፣ ሰይፍ ደግሞ እንደ የጥፋት መሳሪያነት ነው የሚታየው። ምኞቱ የጦር መሳሪያን ወደ ሰላማዊ ተግባር መሳሪያነት መቀየር፣ ሰይፍን ወደ ማረሻነት መቀየር (swords to ploughshares) አባባል መሰረቱ ብሉይ ኪዳን ነው። ይህ አባባል ለዘመናት ለተለያዩ ግን ተመሳሳይ ለሆኑ ሁኔታዎች መግለጫ ሲደረግ ዘመናት አስቆጥሯል።

 ለምሳሌ በዘመናችን ለጥፋት ታስቦ የዳበረውን የኒውክልየር ቴክኖሎጂ (ሂሮሽማ እና ናጋሳኪ ላይ አሰቃቂ ውድመትን ያስከተለው የአቶሚክ ኃይል) ለበጎ ተግባር ለማዋል ተችሏል (ለምሳሌ ለኤለክትሪክ ኃይል ማመንጫነት)። ከአውዳሚነት ወደ ልማት ማለት ከሜጋቶን (megaton) ወደ ሜጋ ዋት (megawatt) ተመንዝሯል። እንዲሁም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማግሥት ይህንኑ ምኞት ገላጭ የሆኑ የጦር መሳሪያዎች ወደ ልማት መሳሪያነት ተቀይረዋል።

 በነብያት መጻሕፍት ትንቢተ ኢሳይያስ፣ ምዕራፍ ፪ አንቀጽ ፫ እና ፬«፫ ሕግ ከጽዮን የእግዚአብሔርም ቃል ከኢየሩሳሌም ይወጣልና ብዙዎች አሕዛብ ሄደው። ኑ፣ ወደ እግዚአብሔር ተራራ፣ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፣ እርሱም መንገዱን ያስተምረናል፣ በጎዳናውም እንሄዳለን ይላሉ።

 ፬ በአሕዛብም መካከል ይፈርዳል፤ በብዙ አሕዛብም ላይ ይበይናል፤ ሰይፋቸውንም ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ……»

 ከሌላ አንፃር ዕይታው ተገልብጦ፣ በትንቢተ ኢዩኤል ምዕራፍ ፫ አንቀጽ ፲ ይገኛል።

 « ማረሻችሁን ሰይፍ፣ ማጭዳችሁንም ጦር ለማድረግ ቀጥቅጡ። ደካማውም እኔ ብርቱ ነኝ ይበል።»

የዚህ አስተሳሰብ ገላጭ የሆነ ከነሃስ የተሠራ ሃውልት የሶቭየት ሕብረት መንግሥት ለተባበሩት መንግሥታት ማህበር አበርክታለች፣ ሃውልቱም በመንግሥታቱ ዋና ቢሮ ፊት ለፊት ካለች አንዲት ትንሽ አደባባይ ውስጥ ይገኛል።

በተጨማሪ ይህን አባባል መሰረት አድርገው የተደረሱ መዝሙሮች አሉ፣ ሁለቱን እነሆ። በብዙ አካባቢ የሚታወቀው ዝነኛው «የጦርነት ተቃውሞ» መግለጫ መዝሙር «የወይን ሐረግ እና የበለስ ዛፍ» (The Vine and Fig Tree) ነው።

«And everyone neath their vine and fig tree shall live in peace and unafraid,

————-.

And into ploughshares beat their swords Nations shall learn war no more.»

ይህ መዝሙር ተተርጉሞ በበገና ሊደረደር ይችላል፣ ትርጉሙ እነሆ።

 «ሰይፍ ተቀጥቅጦ፣ ወደ ማረሻነት ሲቀየር፣

 እንኖራለን በሰላም፣ በክብር፣

 በፍቅር በወይን ሐረግ፣ በበለስ ዛፍ (ጠለላ) ስር።»

በተመሳሳይ መንገድ ዝነኛው ዘፋኝ ሚካኤል ጃክሰን፣ «ዓለምን መፈወስ» ብሎ በሰየመው ሙዚቃው (Heal the World” by Michael Jackson (1991)

 : Create a world with no fear

 Together we’ll cry happy tears

See the nations turn

Their swords into plowshares

ይህም ሙዚቃ ተተርጉሞ በበገና ሊደረደር ይችላል፣ ትርጉሙም እነሆ።

«እንመስርት በሕብረት፣ በትብብር፣

 ሰላማዊ አገር፣ ሰላማዊ ምድር።

 በሕብረት እንፈንጥዝ፣ እናንባ፣

እንራጭ፣ በደስታ እንባ።

እናስተውል፣ ሰይፍ ሲቀልጥ ሲሰባበር፣

 ወደ ማረሻነት ሲቀየር።»

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የወጣትነት እድሜውን ያሳለፈው ሮን ፖል (Ron Paul) የሚባል አሜሪካዊ በዚሁ ጉዳይ ላይ መጽሐፍ ጽፏል (Swords into Plowshares: A Life in Wartime and a Future of Peace and Prosperity)። በተመሳሳይ መንገድ ብዙ ታዋቂ ግለሰቦች በዚህ ምኞት አዘል አባባል ተጠቅመውበታል።

በዕውቀቱ ሥዩም ቅን አስተሳሰብ እንጂ የጦር መሳሪያ ችግር አይደለም ጠብን የሚገታ ይላል። ጥፋቱ ከመሳሪያ ማንገቡ አይደለም የሚመነጭ፣ በመሳሪያው ከተጠቀመበት ግለሰብ አስተሳሰብ እንጂ ይለናል። ይህን ሁኔታ ለማብራራት ይረዳ ዘንድ አንድ አፈ ታሪክ አቀርባለሁ።

የልጅ እያሱ ምኒልክ የቅርብ ወዳጅ እና አማካሪ የነበሩት ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ አንጎላቸው ውስጥ ደም ፈሶ ባልቻ ሆስፒታል ተኝተው ሳለ፣ እሳቸውን ለመጠየቅ አፄ ኃይለ ሥላሤ ሄደው በነበረ ጊዜ የተከሰተ ነው ይባላል። ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ጭንቅላታቸው ውስጥ ደም ፈሶ፣ አንደበታቸው ተዘግቶ ነበር። ንጉሠ ነገሥቱ ሊጠይቋቸው ወደ ሆስፒታል ያመሩ በነበረ ጊዜ ነው። ንጉሠ ነሥቱም የተሰማ እሸቴን ልሣን መዘጋት አጢነው፣ «እንግዲህ አንደበትህ ተዘጋ፣ እንዴት ትሳደብ?» አሏቸው። (9) በዚህን ጊዜ ነጋድራስ በንጉሠ ነገሥቱ ላይ ምላሳቸውን አወጡባቸው ይባላል። ነጋድራስ በቃላት መወረፍ ቢሳናቸው፣ ተመሳሳይ መልዕክት ምላስ በማውጣት አስተላለፉ። ስለሆነም ቁም ነገሩ አንደበቱ አይደለም፣ የግለሰቡ አስተሳሰብ እንጂ፤ አንደበት ቢዘጋ በምግብ ማብላሊያ፣ ማማሳያ ምላስ አማኻኝነት፣ መሳደብ ይቻላል። የአንደበታቸው መታሰር ነጋድራስን ከመሳደብ አላገዳቸውም።

 ለዘመናት ብዙ የታወቁ ግለሰቦች (የፖለቲካ መሪዎች፣ ደራስያን፣ ሙዚቀኞች፣ ወዘተ) ያመኑበትን ሁኔታ፣ የሰበኩትን እምነት፣ ይህ ወጣት ደራሲ በዕውቀቱ ሥዩም ፉርሽ ያደርገዋል። «እባካችሁ አትቀልዱ፣ የጦር መሳሪያን ወደ ሰላማዊ መሳሪያነት በመቀየር አይደለም ሰላም በዓለም ላይ እንዲሰፍን መደረግ ያለበት፣ ቁም ነገሩ የሰውን ልጅ አስተሳሰብ መቀየር ነው» መሰል ምክር አበረከተ።

 ባጭሩ የበዕውቀቱ ሥዩም ግጥም ሰላምን ለማስፈን ቁም ነገሩ የጦር መሳሪያን ወደ ልማት መሳሪያነት መቀየር ሳይሆን፣ አስተሳሰብን መቀየር ነው የሚያሻ የሚል መልዕክት ነው ያስተላለፈችልን።

 ጽሑፉ ጠሎ ሲቀርብ፣ ከላይ የቀረቡት ትችቶች የሚያመለክቱን በአጫጭር ግጥሞች፣ ሰፋፊ ይዘት ያላቸው መልእክቶችን፣ እንዲሁም ጥልቅ አስተሳሰቦችን፣ ለአድማጮች/ለአንባብያን ለማበርከት እንደሚቻል ነው። የግጥም ውበቱም ይህ አጠር መጠን ብሎ ብዙ መልእክት ማስተላለፍ መቻሉ ነው።

ይህች ጽሑም ተመሳሳይ ትንተና እንደምትጋብዝ እየተመኜሁ፣ በቅርብ ጊዜ ጎልቶ የመጣውን የወጣቱ ትውልድ ግጥም ወዳድነት ትደጉማለች የሚል እምነት፣ ተስፋ ሰንቂያለኹ። ካለ ተስፋ ወደፊት መራመድ አይቻልም።

 ተስፋ ከከሰመ፣ ምኞት ከገረጣ፤

 አለመኖር እንጂ፣ መኖር ትርጉም አጣ።

ማስታወሻዎች፣

 1. ሽብሩ ተድላ 2008. የስንኝ ማሰሮ ከ1955 እስከ 2008 ዓም፣ ማስተር ፕሪንተርስ አ.አ.

2. «ላም» የነጠላ እንስት መግለጫ፣ ከብት የሚለውን ቃል ተክቶ ለከብት መንጋ መግለጫነትም ያገለግላል።

3. በዕውቀቱ ስዩም 2001 ዓም. ስብስብ ግጥሞች። ህትመት ፋርኢስት ትሬዲንግ ኃላ .የተ.የግ.ማህበር።

 4. እነማይ በምሥራቅ ጎጃም ውስጥ በብቸና አውራጃ የሚገኝ ወረዳ (የበፊት የመንግሥት መዋቅር) ነው።

 5. ሁለቱም ግጥሞች አንድ መልዕክት ነው የሚያስተላልፉ፣ የወይዛዝርት «ደብረክ» «ደብረክ» እያሉ መራመድ፣ ግጥሞች በተደረሱበት ዘመን ተወዳጅ እንደነበረ ነው የሚያመለክቱ። የዚያን ዓይነት አረማመድ መወደድ፣ መደነቅ፣ ዘመን የሻረው ይመስላል።

6. ተገኝ ተአምሩ ቢሻው (አለቃ) 1967 ዓም። የኢትዮጵያ ፋናዎች (ማተሚያ ቤት አልተገለጠም)።

7. በ«ኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር» የተዘጋጀው የአማርኛ መዝገበ ቃላት፣ « ቅኔ»ን ትርጉም «እንደ ግጥም ቤት የሚመታ» ብሎት ያልፋል። ይህም ትርጉም የአማርኛ ግጥም ቅኔ እንዳልሆነ ያስረዳናል።በ«ኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር» የተዘጋጀው የአማርኛ መዝገበ ቃላት፣ « ቅኔ»ን ትርጉም «እንደ ግጥም ቤት የሚመታ» ብሎት ያልፋል። ይህም ትርጉም የአማርኛ ግጥም ቅኔ እንዳልሆነ ያስረዳናል።

 8. መሰላሉ ራሱ ክርስቶስ ነው፣ ምድርና ሰማይን ያገናኘው መሰላል እርሱ ስለሆነ ተብሎ ህልሙ ተተረጎመ። 9. ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ በግጥም ሰውን መወረፍ ይቀናቸው እንደነበረ ይወሳል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top