ጣዕሞት

የሠዓሊ አወቀ ዓለሙ የሥዕል ኤግዚቪሽን ለሕዝብ እይታ ቀረበ

የሠዓሊ አወቀ ዓለሙን ሥዕሎች የያዘ ኤግዚቪሽን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴያትር የሥዕል ጋለሪ ከቅዳሜ ጥር 4 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ለሕዝብ እይታ ቀርቧል።

ከውልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በቴያትር ጥበብ የተመረቀው ሠዓሊ አወቀ ለሥዕል ጥበብ ባለው ልዩ ፍቅር የሠራቸውን የተለያዩ ሥዕሎች ያቀረበ ሲሆን ይህ ኤግዚቪሽንም የመጀመሪያው እንደሆነ ገልጿል።

በሥነሥርዓቱ ላይ የተገኙት እንግዶች በተለይም አንጋፋው ከያኒ ደበበ እሸቱ፣ የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ነቢዩ ባዬና ሠዓሊ በቀለ መኮንን የባለሙያው ሥራዎች ያስደመሟቸው መሆናቸውን ገልጸው ወጣቱን ሠዓሊ ይበልጥ ለማበረታታት በየፊናቸው የሚቻላቸውን ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።

 ሠዓሊ አወቀ በዚሁ ጊዜ ባደረገው ንግግር ለኤግዚቪሽኑ መሳካት ድጋፍ ያደረጉለትን ግለሰቦችና ተቋማት አመስግኗል። በዕለቱም በሠዓሊው ሥራዎች ከተዳሰሱ ታዋቂ ከያኒያን መካከል የባለቅኔዎቹ የጸጋዬ ገ/መድኅን፣ የገ/ክርስቶስ ደስታና የሙሉጌታ ተስፋዬ ግጥሞች ተነበዋል።

«ውሳኔ ቁጥር ሁለት» ፊልም ተመረቀ

ሴራው በተንኮል፣ በክፋት፣ በጭካኔና በወንጀል ላይ ያጠነጠነው «ውሳኔ ቁጥር 2» ፊልም ጥር 13/2011 ዓ.ም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ቤት ለምረቃ በቅቷል:: ሦስት ልጆቿን በትወና ያሳተፈችው ገነት ንጋቱ ፊልሙን ስታዘጋጀው፤ ዘላለም ይታገሱ ደግሞ በደራሲነት፣ በተዋናይነት እና በዳይሬክተርነት ተሳትፏል:: ከስድስት መቶ ሺ ብር በላይ ወጪ የሆነበት ይህ ፊልም፤ አንድ ሰዓት ከሰላሳ ዘጠኝ ደቂቃ ፈጅቷል::

 ካለፈው ገና ጀምሮ በሁሉም ቴአትር ቤቶች መታየት ቢጀምርም፤ በፊልሙ ስራ ላይ የተሳተፉትን ለማመስገን መርሃግብሩ መዘጋጀቱን የፊልሙ አዘጋጅ ገነት ንጋቱ ተናግራለች:: አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆና ፊልሙን ስታዘጋጅ ከጎኗ ሳይለዩ ያበረታቷትን፣ በተለያየ መልኩ ድጋፍ ያደረጉላትንና የተባበሯትን ሁሉ በመድረኩ ከልብ አመስግናለች::

በርካታ የፊልም አፍቃሪዎች፣ ታዋቂ የፊልምና የቴአትር ባለሞያዎች እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሰት ባለስልጣናት በተገኙበት በዚህ መርሃግብር ላይ ለፊልሙ አስተዋጽኦ ላደረጉ የምስጋና ምስክር ወረቀትና ሽልማቶች ተበርክተዋል::

ኢትዮጵያዊነት – የዜጎች መብት ማስከበሪያ ጉባኤ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጠ

ኢትዮጵያዊነት – የዜጎች መብት ማስከበሪያ ጉባኤ ጥር 14 ቀን 2011 ዓ.ም አዲስ አበባ ውስጥ በአዘማን ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። በዚሁም ወቅት የድርጅቱን መቋቋም አስፈላጊ ካደረጉት ምክንያቶች ዋናው የኢትዮጵያዊነት መሸርሸር መሆኑን አቶ ተስፋሚካኤል መኮንን የድርጅቱ የፕሬስ ኃላፊ አስታውቀዋል። ድርጅቱ እስካሁን በአሜሪካ ሲንቀሳቀስ መቆየቱን፣ በኢትዮጵያዊነት እሴቶች ላይ ጥናትና ምርምሮችን፣ አውደ ጥናቶችንና ጉባኤዎችን ማዘጋጀቱን፣ ኢትዮጵያውያንን በኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብ ዙሪ ሲያሰባስብና ከሌሎች መሰል የሲቪክ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ሲሠራ መቆየቱን፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በሃገራችን እየተካሄደ ባለው ለውጥ በመበረታታት የድርጅቱ መሪዎች ወደኢትዮጵያ መምጣታቸውን ሊቀመንበሩ ዶ/ር እርቁ ይመር አስታውቀዋል።

በሃገር ውስጥ ቆይታቸውም ከተለያዩ መንግስታዊና ህዝባዊ ተቋማት ጋር ለመመካከርና የድርጅቱን ዓላማና ተግባራት ለማስተዋወቅ መቻላቸውን፣ ወደክልሎችም በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸውን፣ እንዲሁም ድርጅቱ በሃገር ውስጥ የሚንቀሳቀስበትን ህጋዊ መሠረት በመፍጠር ላይ መሆናቸውን ዶ/ር እርቁ ጨምረው ተናግረዋል።

የአመራር አባላቱ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎችም ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፣ በዚህም ከብሔር ተኮር ድርጅቶችና ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር ለመስራት ማቀዳቸውን፣ እስካሁን ባደረጉት ውይይትም በዜጎች የመብት ጥያቄና ኢትዮጵያዊነትን በማራመድ ላይ ከበርካታ ወገኖች ድጋፍ ማግኘታቸውን አስረድተዋል።

“መንታ መንገድ” ቴያትር ለዕይታ በቃ

«ቴያትር ቤቶቻችን የጥበብ ምንጮቻቸው ነጥፈውባቸዋል፤ አዳዲስ ቴያትርና የትወና ጥበብን ማፍለቅ ተስኗቸዋል» እየተባሉ በሚወቀሱበት በአሁኑ ወቅት የሚወጣ አዲስ ቴያትር ያጓጓል:: ቴያትር አንዱ የማህበረሰባዊ ሂስ መድረክ ነው:: ከማዝናናት፣ ከማስተማርና ከማሳወቅ ባለፈ በማህበራዊ መስተጋብር ውስጥ ያሉ ህጸጾች እንዲታረሙ አይነተኛ ምክንያት ይሆናል:: ይህ በመሆኑም ቴያትር ቤቶች ሚናቸውን አውቀው ተልኳቸውን በአግባቡ ይፈጽሙ ዘንድ ሊወተወቱ ይገባል:: ከመድረክ የራቁ ይጠሩ፣ አዳዲሶችም ይፍለቁ ነው የጥበብ ቤተሰብ ጥሪ:: ሰሞኑን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴያትር መድረክ መታየት የተጀመረው ቴያትርም ጥበቡ ለናፈቀው አፍቃሪ ታላቅ የምሥራች እንደሆነ አያጠራጥርም::

 አዎ! በተውፊቅ አል ሃኪም ተደርሶ፣ በዓለማየሁ ገ/ሕይወት የተተረጎመውና በአርቲስት ተክሌ ደስታ የተዘጋጀው “መንታ መንገድ” ቴያትር እሁድ ጥር 5 ቀን 2011 ዓ.ም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ለዕይታ በቅቷል::

 ሳሙኤል ተስፋዬ በመሪ ተዋናይነትና በረዳት አዘጋጅነት፣ አርቲስት አልጋነሽ ታሪኩ ደግሞ በዝግጅት አስተባባሪነት ተሳትፈዋል::

አንጋፋና ታዋቂ ተዋንያን ተስፋዬ ገ/ሃና፣ ሺመልስ አበራ ጆሮ፣ እታፈራሁ መብራቱ፣ ሚካኤል ታምሬ፣ ዳንኤል ተገኝ፣ ካሌብ ዋለልኝ፣ ሕንፀተ ታደሰና ሌሎችም ተውነውታል።

ቴያትሩ የህግ የበላይነትን ዋና ርዕሰ ጉዳዩ አድርጎ የተነሳ ሲሆን ሃገራችን ላለችበት ሁኔታ ወቅታዊ ምላሽ ተደርጎ ሊታይ እንደሚችልም ይታመናል:: ቴያትሩ ከሁለት ዓመታት በፊት ተዘጋጅቶ ለተመልካች ከመቅረቡ በፊት መከልከሉና አዘጋጁም ተገዶ ከሃገር እንዲወጣ መደረጉ ይታወሳል::

 በቴያትሩ የመክፈቻ ዕለት የጥበብ አፍቃሪዎችና ቤተሰቦች የተገኙ ሲሆን በዝግጅቱ ለተሳተፉ ባለሙያዎችም የአበባ ስጦታ ተበርክቶላቸዋል:: ቴያትሩ ዘወትር እሑድ ከ8 ሰዓት ጀምሮ ለሕዝብ እንደሚቀርብም ቴያትር ቤቱ ገልጿል::

አዲስ የሙዚቃ ድግስ በኤሊያና

ሰሞኑን አንጋፋና ወጣት ሙዚቀኞች የተጣመሩበት የጃዝ እና የሶል ሙዚቃ ድግስ በኤሊያና ሆቴል መቅረብ ጀምሯል::

 ድምጻዊያን ግርማ ነጋሽ እና ባህታ ገብረሕይወት እንዲሁም ወጣቱ የፒያኖ ተጫዋች ሳሙኤል ይርጋ ዘወትር አርብ ምሽት የጥበብ አፍቃሪዎችን በሆቴሉ አዳራሽ እንደሚያዝናኑ ታውቋል:: ዛሬም ድረስ ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎችን ሲያቀርቡ እንደነበር የሚነገርላቸው ግርማ እና ባህታ፤ በተለይ በ1960ዎቹ ያቀርቧቸው የነበሩ ተወዳጅ ሥራዎቻቸው በሙዚቃ አፍቃሪዎቻቸው ዘንድ አይዘነጉም:: እነዚሁኑ ሥራዎቻቸውን በዘመናዊ መሳሪያ ታግዘው እንደሚያቀርቡም ነው የተነገረው::

 በተለያዩ አገራት ጭምር በመጓዝ የሙዚቃ ቅንብር ስራዎቹን በማቅረብ የሚታወቀው ሳሙኤል ይርጋም ተወዳጅ ሥራዎቹን እንደሚያቀርብ ታውቋል:: ዘካርያስ ጌታቸው በጊታር፣ ፍሬው መንግስቱ በቤዝ፣ ዮናስ ይማም በድራም፣ ጃን ኮንስታንቲኒስኮ በጊታር ምሽቱን እንደሚያደምቁት የዝግጅት ክፍሉ ገልጿል::

የአጼ ቴዎድሮስ ሁለት መቶኛ ዓመት ታስቦ ዋለ

ሰኞ ጥር 6፣ 2011 ዓ.ም በእምዬ ምኒልክ ወዳጆች ማህበር አዘጋጅነት ታላላቅ የኪነ ጥበብ ሰዎች በተገኙበት የዳግማዊ ንጉስ ቴዎድሮስ ሁለት መቶኛ ዓመት ማንነታቸውን በሚያስታውስ ዝግጅት በኢትዮጵያ ሆቴል ታስቦ ውሏል፡፡

በዕለቱ ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው የአጼ ቴዎድሮስን ህይወት ታሪክና ውጣ ውረድ፣ ትውልዳቸውን፣ ዕድገታቸውንና ባህሪያቸውን አስመልክቶ ለታዳሚው ንግግር አድርገዋል። የሙዚቃ ተመራማሪው ሰርፀ ፍሬስብሐት በበኩሉ፤ ከቋራ እስከ መቅደላ የአጼ ቴዎድሮስ ስም በኪ ነጥበብ ሥራዎች የገነነበትን ምክንያት በሰፊው አብራርቷል፡፡

ዶ/ር ዘሪሁን ሙላትም፤ የአጼ ቴዎድሮስን ጀግንነት፣ ጠንካራነትና፣ ዘመናዊት ኢትዮጵያን ለመፍጠር የተከተሉትን ስልትና አሟሟታቸውን በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

 በዕለቱም ታዳጊ ሚኪያስ ተስፋዬ የአጼ ቴዎድሮስን ገፀ-ባህርይ ተላብሶ መነባንብ ያቀረበ ሲሆን፤ በሌሎች ባለሙያዎች የቀረቡ ግጥሞችና ፉከራዎችም በዓሉን አድምቀውታል፡፡

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top