አጭር ልብወለድ

ዥዋዥዌ

ኮክ ስብሰባ ጠርቷል። ጋዜጠኞቹ አልወደዱትም¬ መሰብሰቡን። ያው የተለመደውን ማሳሰቢያ፣ ዘለፋ፣ ንዝንዝ መስማት አልፈለጉም።

 “አንዴ ባካችሁ ኤድቶሪያል እንጀምር” ሲል ኮክ አንካሳ እግሩን ጠረጴዛ ላይ አስደግፎ ተናገረ።

 የዜና ማዕከሉ ጋዜጠኞች የኮምፒውተሮቻቸውን ቁልፎች እየነካኩ ቀና ቀና አሉ።

 “ሁላቹሁም ተገኝታችኋል?” ጠየቀ ኮክ፤ በዓይኑ አስራ አምስት የማይሞሉ የክፍሉን ባልደረቦች እየቆጠረ።

 “ሁላችንም ተገኝተናል” ስትል የአማርኛ ዜና ዴስክ ኤዲተር ጐርፍነሽ መለሰች።

 “የጐደለ ሰው ይታየኛል” ሲል ኮክ ድምፁን ቆጣ አደረገው። ተያዩ ጋዜጠኞቹ።

 “ሌንዴቾ የታለ?”

 “አልመጣም እንዴ?” ሌላው ጋዜጠኛ የኮክን ጥያቄ አደመቀው።

 “አንድ ሰዓት ጠዋት ነው የገባው” ጐርፍነሽ ተናገረች። “ሰዓቱ ምን ያደርግልኛል? ካወቅሽ አሁን የት ነው ያለው?” “እሱ ሳይኖር መቀጠል አንችልም እኛ?” የእንግሊዘኛ ዜና ዴስክ ኤዲተሩ ሰለሞን ጠየቀ።

“መኖር አለበት” ኮክ ሰለሞን ላይ አፈጠጠበት። ጋዜጠኞቹ ተያዩ። “ይህቺ ሰውዬ ነገር ሸቷታል ማለት ነው” ዓይነት መናበብ።

 “ሌንዴቾ ሻይ ቤት ይመስለኛል” የአማርኛ ዜና ሪፖርተሩ ምስክር ተናገረ።

“አይተኸዋል?”

 “አላየሁትም”

 “ታድያ ጋዜጠኛ ሆነህ ይመስለኛል ብለህ ትናገራለህ?”

ኮክ ሁሉንም ቃኘት አደረገና

 “የይመስለኛል ጋዜጠኝነት አይደለም የምንሰራው። ጋዜጠኛ ይመስለኛል ብሎ መናገር ሲጀምር አብቅቶለታል”

 ጀመረው ደግሞ ንዝንዙ በሚል ስሜት ጋዜጠኞቹ ዕርስ በርስ ተያዩ። “ሌንዴቾ የት ቀረ?” ወደ ጸሐፊዋ አፍጦ ጠየቀ። ጥያቄዋ ለሷ የተሰነዘረ መሆኑ ቢገባትም አልመለሰችም።

“አልፈረመልሽም?”

 “ምኑን?” ሲል አንዱ ጋዜጠኛ ጠየቀ፤ ነገሩ ቢገባውም:: “ምኑን ልበልህ?” መለሰ ኮክ።

 “አይ ጥያቄህ ትዳር መስርታችሀል ዓይነት ስለመሰለኝ ነው” አለ ያ ጋዜጠኛ። ባልደረቦቹ በህብረት ሳቁ።

 “ፈርሟል” አለች ጸሐፊዋ።

 “ታዲያ የት ሄደ?”

ዝም አለች። ኮክ በስጨት አለ።

 “ጋዜጠኛ ስነ ምግባር ሲያጣ ያበቃለታል…” ንግግሩን ቀጠለ ኮክ። ጋዜጠኞቹ ኮምፒውተሮቻቸውን እየነካኩ ማዳመጥ ቀጠሉ።

* * *

ሌንዴቾ ከዜና ማዕከሉ ግቢ ትይዩ ከሚገኘው ካፍቴሪያ ጥግ ተቀምጧል። ጠዋት ወደ ቢሮ ሲገባ ቢሮ በር ላይ ያገኘውን እሽግ ፖስታ ከፍቶ ማንበብ ጀምሯል።

የእጅ ጽሑፉን አያውቀውም። የባልደረቦቹ እንዳልሆነ ርግጠኛ ሆኗል። በማዕከሉ የሚገኝ ስራ ክፍሎች ያሉ ሠራተኞች የእጅ ጽሑፍ በተለያየ አጋጣሚ አይቷል። ግን የማን እንደሆነ አልመጣለትም።

 ለ6ኛ ጊዜ ደግሞ ማንበብ ጀመረ።

…..

ከዚህ እጀምራለሁ፤ ስሜቴ ከሠከረበት። ባዶነት ምንድ ነው? ውሃው የተገለበጠ ጋን ማለት ይሆን? ወይስ የተዘጋ ባዶ ቤት? ወይስ የታሸገ ዋሻ?…

ጋኑ ውሃው የተገለበጠ ባዶነትን ያመላክታል ቢሉኝ አይገባኝም። ውሃውን ባይሸከምም አየሩን ይዟል። ህይወት አለው። ጋኑን በነኩት ጊዜ እንስራው የራሱ ድምፅ አለው። እንደ ዜማ ያለ ነገር። ወዳጄ እኔስ ህይወት ውስጤ ይመላለሳል ይላል። የተዘጋ ባዶ ቤት እንዲሁ ባዶ አይደለም። ውስጡ የታፈነ አየር አለ። አየር ውስጥ እንቅስቃሴ ይገኛል። እንቅስቃሴው ውስጥ የህይወት አንዲቷ ዘሃ አለች። እስትንፋስ። እዚያች ዘሃ ውስጥ ሽርፍራፊ ትዝታዎች ይመላለሳሉ። አሻራዎች ታትመው ከባዶ ቤትነት በፊት ያለውን ህይወት ይዘምራሉ። ዝማሬዎቹ የባለቤቶቹ ዱካዎች ናቸው። ዱካዎቹ የህይወት ፈለጐች ናቸው።

ባዶነት ግን እነዚህ ሁሉ የሉትም። የሚንጠፈጠፍ የስሜት ጠብታ ማግኘት ህልምን ማለም ፈልጐ የማጣት ያህል ይከብዳል።

እንጥፍጣፊ ስሜት የህይወት መቀጠያ አንዲት ቀጭን ክር ነች። ከሸረሪት ድር ሚሊዮን ጊዜ የቀጠነችውን ያቺን የእንጥፍጣፊ ስሜት ወካይ ክር ማጣት ህይወትን የማስቀጠል ስራ…

አንዳንድ ቀን እንዲህ ዓይነቶች ስሜቶች ውስጤ ይመላለሳሉ። ድንገት ደርሼ የምሄድበት ግራ ይገባኛል። የምሰራው ይጠፋኛል። የማየውን ነገር ማድነቅም መጥላትም ያቅተኛል። ሰዎች የተራቡ ውሻዎች ይመስሉኛል። በቃ ከመሬት ተነስተው የሚናከሱ። ይህም ስሜቴ ጥቂት ቆይቶ ከውስጤ ይወጣል።

 የምሄድበት አንድ ቦታ እፈልጋለሁ፤ የት እንደሆነ አላውቀውም። የምተኛበት አንድ አልጋ እፈልጋለሁ ፤የማን አልጋ እንደሆነ አላውቀውም። ፀጥታን እናፍቃለሁ ግን ሳገኘው ያገኘሁት አይመስለኝም። በቃ በዚያች ቅፅበት ባለሁበት ቆሜ መቅረት ብችል እመርጣለሁ፤ ግን አልችልም።

 እንጥፍጣፊ ስሜት የሌለው ባዶነት ይሰማኛል ልክ እንደ አሁኑ። ይህን ለምን እንደምፅፍ እንኳን ሳይገባኝ።

 ስለኪስ ባዶነት መናገር ቀላል ነው። ኪሴ ባዶ ሲሆን ምንም ማለት አይደለም። ሰዎች በኪሴ መጠን ሊሠፍሩኝ፣ ሊቆጥሩኝ፣ ሊመዝኑኝ ሲሞክሩ ያመኛል። እኔ ጤፍ አይደለሁም ለምን እመዘናለሁ? ዘይት አይደለሁም ለምን እሠፈራለሁ? ከበሬዎቻቸው አንዱ አይደለሁም ለምን ይቆጥሩኛል?

ራሴን በስውር፣ በቁጥርና በልኬታ ተምኜውም አላውቅም። አልፈልግምም። እኔ የቁጥር ልጅ አይደለሁም። በርግጥ ቁጥሮች ያስደስቱኛል::

አንዱ ተነስቶ ማነህ? ሲለኝ ስንት አለህ ብሎ የጠየቀኝ ነው የሚመስለኝ። ያለኝን መንገር ያሳፍረኛል። በገንዘብ መጠን አይደለም የማፍረው። በጠያቂው ጥያቄ ነው። ለምን በገንዘብ እንዲሠፍረኝ ራሱን ያስገድዳል? እኔና ጠያቂው የምንጋራቸው ስንትና ስንት ነገሮች አሉን።

አንዱ ሰው የመሆናችን ጉዳይ ነው። ሌላው የህይወት እንቆቅልሽ ነው። ሦስተኛው በተፈጥሮ ላይ የሌለን ስልጣን ነው። እነዚህ ሦስቱ እንኳን ብንሸምናቸው እልፍ አእላፍ ድሮች አሏቸው። እልፍ አእላፍ እንቆቅልሾች አሏቸው። እነዚህን ለመመለስ የተሰጠን የዕድሜ በረከት መቶ እጥፍ ቢደገምልን አይበቃንም። ግን በቃ ውጪያዊ በሆነ ነገር ላይ ደርሶ መጠመድ ይመጣል።

• ስንት አለህ?

 “ይህንችክ ያለ የጋዜጠኝነት ዓለም ማምለጥ። የሰው ስም፣ አሃዝና ብሏልና ተብሏል ከሚባሉ ደረቅ እውነቶችና ለዛ ቢስ ቃላቶች መራቅ። ከችኮ አለቃና ከነተቡ ጋዜጠኞች በብዙ ሚሊዮን የምናብ ማይልስ መራቅ! አዎ! መራቅ! መራቅ!”

• ማነህ?

ጠያቂዬ ምላሼ ያረከዋል ወይም ያበሳጨዋል። የሚያረካው እኔን የሚሰፍርበት የገንዘብ መጠን ከሱ ያነሰ ሲሆን፤ ትልቅነቱ ያጐላል። ዋርካነቱን ያገዝፈዋል። ሥር የሌለው ዋርካ መሆኑን ግን ልብ ብሎት አያውቅም።

 ነፍሱን እንደምወድለት አይረዳኝም። ሰው የመሆናችን መሠረት እንዳስተሳሰረን አይገባውም። በማይሞላው ጐተራው ራሱን ይደልላል። በውራጅ ልብሱ ባዶ ለሆነች ነፍሱ የሚያልፍ ሽታ ያቀብላታል።

ለዛቢስ በሆነ ሳቁ ከንፈሩን ሊያወዛ ይሞክራል። የበላውን የምግብ አይነት ሲመዝን፣ የጠጣውን አረቄ ሲያሰፍር እድሜውን ይበላል።

 እናም ያኔ አንዳች ጥግ ተንጠልጥላ ለምትገኘው ነፍሴ ሹክ ስላት፣ ረመጥ ላይ እንደተጣለ ሥጋ እንጨረጨራለሁ። ማልቀስ እፈልግና እንባዬ አይታዘዝልኝም። ርቄ መብረር እሻና ሃሳባዊ ክንፎቼ አይዘረጉም።

 አለም ላይ ጢቅ ብዬ የቻልኩትን ያህል ልተፋ እሞክርና ትፋቴ መልሶ የግርሻ በሽታ እንደሚሆንብኝ ሳስበው እውጠዋለው።

 ሀሩሩ መሀል ተኝቼ መቅለጥ እመኝና ሩቅ ያሉት የምናቤ አለም አበቦች ያባብሉኛል። የምናቤ ማዕበል ውስጥ ገብቼ መጥፋት እፈልግና የምናቤ ወታደሮች ወደራሴው እስር ቤት ይከቱኛል።

በማለዳው ቅዝቃዜ ውስጥ የውርጭን ሃይል ለማግኘት እመኝና ሰው የመሆን ተፈጥሮዬ አስሮ ይይዘኛል። አስባለሁ።

 በጣም በረጅሙ እተነፍሳለሁ።

በከባዱ አጐነብሳለሁ። የውስጤ ሀዘን ያጐብጠኛል። አንዷ ቢራቢሮ ሌላዋን ቢራቢሮ በምንነቷ ነው የምትከተላት? ለምን ሲባል ነው ጐን ለጐን የሚበሩት? ለምን ሲባል ነው አበቦቹን የሚመርጧቸው? እንደገና ጠያቃለው:: እፅዋቱና ነፋሱ እጅ ለእጅ ተያይዘው መወዛወዝ ለምን

አስፈለጋቸው? ሙዚቃን ለመፍጠር? ተፈጥሮን ባለህብረ ብዙ ቀለማማ ለማድረግ?

……..

የካፊቴሪያ አስተናጋጇ የሚሰነፍጥ ፎጣ አምጥታ ጠረጴዛውን ስታሸው ከንባብ ባህር ወጣ – ሌንዴቾ።

 “ማነው? ምንድነው ለማለት የሚሞክረው?” በርካታ ጥያቄዎች ማንሳት ጀመረ።

***

 “እና እንዳልኳቹሁ በስነ-ምግባር የማይገዛ ጋዜጠኛ ሌባ ነው። የሚያመጣው ዜና አይታመንም።…” ኮክ ጉሮሮውን እንደመጠራረግ አድርጎ የላስቲክ ውሃውን ተጐነጨ።

ጋዜጠኞቹ በመሰልቸት መንፈስ ተያዩ።

 ነባሯ ጋዜጠኛ ሄለን እጇን አወጣች። “እሺ አስተያየት ልትሰጪ ነው?” ኮክ ፈገግ አለ። “ቃለ መጠይቅ አለኝ። ሰዓቱ ደርሷል እንድወጣ ይፈቀድልኝ ብዬ ነው” “እኔም ጋዜጣዊ መግለጫ አለብኝ” ብልጣብልጡ ተሾመ ተደረበ። “ረስተሀው ነው እንጂ እኔም እኮ ካስተዋወቅከኝ ኢንቨስተር ጋር ቀጠሮ አለኝ” ጐርፍነሽ ተናገረች::

***

ሌንዴቾ 3ኛ ቡናውን አዘዘ።

ንባቡን ካቆመበት ቀጠለ።

……………

ቀናት ቀለም አላቸው። አንዳንዶቹ ቀናት የዳመና ያህል ናቸው። ክብድ፣ ቅፍፍ ይላሉ። በነዚህ ቀናት ውስጣዊ ስሜቴ ጤና የለውም። ሰው ያስጠላኛል። ንግግር ያስጠላኛል። ዝምታም ያስጠላኛል። ሳቅም ይቸክብኛል። እንዲህ አይነት ቀለማት የምሰጣቸው ቀኖች ብዙውን ጊዜ ከእንቅልፌ ቃዥቼ ወይም ተደናብሬ ስነሳ ነው።

ለምሳሌ ዛሬ ቀኑን ቀለም ስጠው ብባል ከባዱ ደመናማ ቀን ነው። ሰማዩ እኮ ከብዷል። ሌሎች ሰዎች ቢጠየቁ ግን ዋ! ቀኑ ብርሃንማ፣ ፀሐይማ፣ ሀምራዊ ማለታቸው አይቀርም። ትክክልም ናቸው። የከበደ ሰማይን ማን ይፈልጋል!? ምድሩ ከብዶ፣ ሰማዩ ከብዶ ምን መላወሻ ይኖራል!?

የምሰራው የሂሳብ ስራ ነው። ቁጥሮች ያዝናኑኛል። ዳንሰኞች ናቸው። የማይደንስ ቁጥር የለም። ለምን ዳንሰኛ እንደሆኑ አስቤ አላውቅም። ለኔ ዳንሰኛ መሆናቸው ብቻ በቂ ነው። በከባዱ ምድር ውስጥ ዳንሰኛ ቁጥሮች ባይኖሩ የሰማዩን ክብደት ማን ይቋቋመዋል!?

 በሁለቱ ከባዶች መሀል የተረጋጋሁ ይመስለኛል። መስሎኝ ደግሞ ትክክለኝነቱን ሳጣራው ውስጤ ሃይለኛ አመፅ አለ። አሸባሪዎቹ እየተመላለሱ እንደሆነ ይሰማኛል። ደስተኛ የመሆን ስሜት ደግሞ በከፊል ይዳብሰኛል። በከፊሉ ደግሞ የዚሁ ተቃራኒው ያቅፈኛል።

አንዳንዴ በሚንተገተገው ነበልባልና እንደ ዶፍ በሚወርደው ዝናብ መሀል ራሴን አገኘዋለሁ። የዕሳቱም ልጅ አይደለሁም። የዝናቡም ጭምር። ነገር ግን የእሳቱ ነባልባልና የዶፉ ፍንጥቅጣቂ መሃላቸው አስገብተው፤ እጆቻቸውን በትክሻዬ ላይ አሻግረው ሲደንሱ ይታወቀኛል። ይሄኔ ውስጤ የሁለት ማዕበሎች /ዓለሞች/ መመላለሻ ሆኖ ያሰቃየኛል። ነበልባሉ በስሱ ሲያገኘኝ ሙቀቱ በምቾት ያንሳፍፈኝና ያስፈነጥዘኛል። የዶፉ አንድ ፍንጣሪ ሲያርፍብኝ አንገቴን መሸከም ያቅተኛል። አሁን በዚህ ስሜት ውስጥ ነኝ። ስሜት አልኩ እንዴ? ተሰስቼ ነው። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ነኝ ማለቴ ነው።

“ሂሳብ ትሰጠኝ?” የሚለው የአስተናጋጇ ድምፅ ከንባብ ባህር ውስጥ መንጭቆ አወጣው ሌንዴቾን።

***

“መች ኤድቶሪያሉን ጨረስንና ነው ሰዓት! ሰዓት የምትሉት?” ሲል ኮክ ቁጣ ያዘለ አስተያየቱን ሰነዘረ። “ለያዝነው ቀጠሮማ ታማኝ መሆን አለብን።” ጐርፍነሽ በስጨት አለች።

 “ለደንበኞቻችን በሰዓቱ አለመገኘት በራሱ እኮ የስነ-ምግባር ጉድለት ነው” ሲል ተሾመ ተደረበ።

“ኖ! ኖ!” አንገቱን ጭምር አነቃነቀ ኮክ።

 “የማያገናኘውን አታገናኙ!”

 “እንዴት?” ጐርፍነሽ አመረረች። ቀጥላም “ምኑ ነው የማይገናኘው? የትም ይሁን የት፤ ማንም ይሁን ማን በሰዓቱ ካልተገኘ ያው ጉድለት ነው” አለች ደልዳላ ሰውነቷን እየናጠች::

“ተጨማሪ ደግሞ” አለ ተሾመ ትንፋሹን አሰባስቦ “ለምን ጉዳይ እየሰበሰብከን እንደሆነም የረሳኸው ይመስለኛል!”

ጋዜጠኞቹ ተያዩ። አየሩ ውጥረት ሞላበት።

***

ሌንዴቾ ሂሳቡን ከፈለ። አራተኛ ቡናውን አዘዘ። ሰዓቱን ተመለከተ። የኤድቶሪያል ምድብ ሰዓት አልፏል። ኮክ ከነ ቁጣው ታየውና ፈገግ አለ። “ምስኪን ዘበኛ” አለ ለራሱ።

 ይህ ሰው ማነው? ለምን ይህን ማስታወሻ ፃፈ? ለምንስ እኛ ቢሮ በርላይ ማስቀመጥ አስፈለገው? በርካታ ተጨማሪ ጥያቄዎች ወደ ውስጡ መጡ።

 እስካሁን ያነበባቸው አራት ገፆችን አጣጥፎ ወደ ቦርሳው ከተተና ቀሪዎቹን ገፆች አያቸው። ከ10 ገፅ በላይ እጁ ላይ ይገኛል። ደጋግሞ ቢያነበውም መጨረስ እንዳለበት ይሰማዋል። ሰዓቱ ደግሞ አምልጧል።

 “ለምን ዛሬ ስራው አይቀርም?” ሲል ራሱን ጠየቀ።

 “ቀርቶስ?” እንደገና ጠየቀ። “ባልታወቀው ጸሐፊ ጫማ መራመድ። ከዚያም በሱ ዓይን ዓለምን ማየት” “እሺ ከዚያስ?” ራሱን መልሶ ጠየቀ:: “ከዚያማ” መለሰ ራሱ “ይህን ችክ ያለ የጋዜጠኝነት ዓለም ማምለጥ። የሰው ስም፣ አሃዝና ብሏልና ተብሏል ከሚባሉ ደረቅ እውነቶችና ለዛ ቢስ ቃላቶች መራቅ። ከችኮ አለቃና ከነተቡ ጋዜጠኞች በብዙ ሚሊዮን የምናብ ማይልስ መራቅ! አዎ! መራቅ! መራቅ!”

 “ርቆ ርቆ መጨረሻው ምንድ ነው?”

***

 “እኔ መሄድ አለብኝ” ጐርፍነሽ ሳይፈቀድላት ውይይቱን ረግጣ ወጣች።

 “እኔም” ተሾመ ተከተላት።

 “ኧረባካችሁ አንዴ ታገሱ!” ኮክ ቁጣው እንዳላዋጣው ሲያውቅ መለመን ያዘ።

 “ምሳ ሰዓት ላይ ማድረግ እንችላለን። ወይም እነሱ ወጥተው እኛ እንቀጥል” ከነባሮቹ ጋዜጠኞች አንዱ ተናገረ።

 “አዎ ይቻላል” ሌሎቹም ድጋፋቸውን ገለፁ።

 “አይቻልም” ኮክ ድርቅ አለ።

ጸሐፊዋ ሳቋ አመለጣት። ወደሷ ዞሮ “ምንድነው የሚያስቅሽ?” ሲል አፈጠጠባት::

ደንግጣ ፀጥ አለች::

 “ምን አሳቀሽ?”

“ምንም”

“እንዴት ምንም?”

“በቃ ዝም ብዬ ነው”

“ዝም ብሎ ሳቅ አለ እንዴ?”

 “አዎ! ለምሳሌ እኔም አንድ አንድ ቀን ሳቅ ሳቅ ይለኛል” ሲል ነባሩ ጋዜጠኛ ጣልቃ ገብቶ መለሰ።

***

ሌንዴቾ አራተኛ ቡናውን ፉት እያለ አስተናጋጇን ጠርቶ ሚሪንዳ አዘዛት። በመገረም አየችው። ማንበቡን ቀጠለ።

…….

የቱ ስፍራ ነበር የቆምኩት መልሼ ማንበብ ይኖርብኝ ይሆን አያስፈልገኝም። ምክንያቱም ከዕድሜያችን ሦስት አራተኛውን ወደ ፊት በመሄድ ሳይሆን ወደ ኋላ ተመልሰን ጥናቶችን በማሰብ ነው የምናሳልፈው። ጨረቃን ከኮከብ፣ ጸሐይን ከደመና፣ ጨለማን ከንጋት ስናወዳድር:: አቧሯ የምንወድ ፍጥረቶች ! ያ የትናንት ታሪክ አቧራ መሆኑን አንቀበልም።

ትናንት ትዝታ ነው። ታሪክም ነው። ጨለማና ብርሃን ነው። በቃ። ይህን አቧራችን ዛሬ ውስጥ ለምን ጐትተን እንደምናወጣው ግራ ይገባል።

 ለደቂቃዎች ያህል ዓይኖቼን ከደንኳቸው። ቀድሞ ጨለማ መጣ። ቀጥሎ ጨለማው ላይ ጥርሱን ነክሶ፣ ዓይኑን ከድኖ የሚመለከተው እኔ መጣ:: ያ እኔ በተከደኑ አይኖቼ ስር፣ ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ሆኖ ጨለማውን እያየ አየሁት። ወይ ግሩም !! ድቅድቅ ፅልመት ውስጥ ያለው እኔ በምን የብርሃን አቅሙ ነው ጨለማውን ሊያይ የቻለው። አንዲት ዘሃ ብርሃን፣ አንዲት እንደ ሸረሪት ድር የቀጠነች የብርሃን ጨረር በሌለባት ፅልመት ውስጥ፣ ራሱን ፅልመቱን ማየት፣ እንደገናም ራስን ማየት። ምን ይሆን እንቆቅልሹ? ይህን ፅልመት ራሴ አንዲት ዘሃ ብርሃን ልለቅበት አይቻለኝ ይሆን? ቆይ እስቲ የዓይኖቼን ክዳኖች ልግለጣቸው።

 ኡ ! ያስፈራል! ጨለማና ብርሃን ለምን እኩል ያስፈራሉ?

…….

የሞባይሉ ንዝረት ከንባቡ መለሰው። ሞባይሉን አውጥቶ አየው፤ የቢሮ ስልክ ነው። ጸሐፊዋ ነች። አመነታ።

ጠረጴዛው ላይ አስቀመጠው።

የካፊቴሪያው ተስተናጋጆች የመገላመጥ ያህል አዩት።

***

“ስልኩን አያነሳም” አለች ጸሐፊዋ፤ ኮክን የጐንዮሽ እያየች። የዜና ማዕከሉ ኤድቶሪያል ያለ ውጤት ተበትኗል።

 የጠረጴዛ መሳቢያዎቹን እየከፋፈተ “ደግመሽ ደውይለት” አላት። ጠረጴዛው ላይ የሚገኙ ወረቀቶች ተበታትነዋል።

“ምነው የጠፋብህ ነገር አለ?” በሚስቅ ዓይኗ እየጐበኘችው

“ላግዝህ እንዴ?”

“ምንም አልጠፋኝም። ሂጂና ስልኩን ደውዪ” ቀና ብሎ የመገላመጥ ያህል አያት።

 ጸሐፊዋ እንደወጣች “ኤጭ” አለ::

 “የትገባ ደግሞ?” ራሱን ጠየቀ።

***

ሌዴንቾ ንባቡን ቀጠለ።

……

ዓለም ጥፍራም ነች። ሰዎቿም የሚሰለቹ ናቸው። እኔ ደግሞ የጥፍሯ ቆሻሻ። ወዳጄ ኮክ ይህን ማስታወሻ ለምን እንደፃፍኩልህ ታውቃለህ ?አታውቀውም። የሚገርመው ደግሞ እኔም አላውቀውም። በልጅነታችን አስተማሪዬ አድርጌ አስብህ ነበር። አንካሳነትህ የተፈጠረው የዓለምን ክፍተት የሚሞላ አድርጌ እገምት ነበር። ነፍስ ባወቅኩ ጊዜ አንተ ራስህ የዓለም አራሙቻ መሆንህን አወኩ። ጐዶሎነቷን ከሚያከፉ ሰዎች አንዱ አንተ መሆንህ ገባኝ። አስተማሪነትህ በህያውነት ሰሌዳ ላይ ያልተቀለመ መሆኑን ተረዳሁ። ታላቅነትህ ወረደብኝ። ቀለማማ ድምፅህ ኳኳታ ብቻ መሆኑን ተገነዘብኩ።

ተፀየፍኩህ። አንተን ስፀየፍ ራሴን ተፀየፍኩ። ራሴን ስፀየፍ ዓለምን ተፋታኋት። ዓለምን ስፋታ ጨረቃና ኮከብ ተሳፈጡኝ። ብርሃንና ፅልመት ደነሱልኝ። ወደ ምንምነት ለሚደረገው ጉዞ መንኮራኩራቸውን አቀረቡልኝ።

 የማዝነው ያንተ አራሙቻነት ሳይበቃ ለዚህች ጥፍራም ዓለም ተጨማሪ አራሙቻዎች መዝራትህ ነው።

……

የስልኩ ንዝረት በጠበጠው።

 ጸሐፊዋ ነች።

ተበሰጫጨ። “ምናባቷ ትነዘንዘኛለች?” አለ ሌንዴቾ ከተመስጥኦ ንባቡ መውጣቱ እያነጫነጨው።

 “ጥፍራም!”ያመለጠው ቃል አስደነገጠው።

***

“ስልኩን አላነሳ አለኝ” አለች የቢሮው ምስቅልቅል መውጣት የበለጠ ግራ ያጋባት ጸሐፊው።

 “በቃ ያለበት ቦታ ድረስ ሄደሽ አምጪው!” ተቆጣ:: ስለተናገረው ነገር ሳያስብ። ግራ ተጋባች። የታመመም መሰላት።

 “የት እንዳለ እኔ በምን አውቃለሁ?” “እንጃልሽ! በቃ ፈልጊው አልኩ ፈልጊው!” አምቧረቀ። ደንግጣ ወደ ቢሮዋ ተመለሰች:: ኮምፒውተሯ ስር ተሸጉጣ ሳይታወቃት በሳቅ ተንከተከተች።

“ምነው?” ስትል በሁኔታዋ የተገረመች ወጣቷ ጋዜጠኛ ጠየቀቻት። “ለብቻ የሚያስቅ ነገር ምን ተፈጠረ?” “አንዳንድ ቀን እኮ ዝም ብሎ ያስቃል ሲባል ቅድም ኤድቶሪያል ላይ አልሰማሽም?!”

“ነው እንዴ?” ወጣቷ ጋዜጠኛ እንደማሽሟጠጥ ቃጣት።

 “እናስ?” ጸሐፊዋ እንደመቆጣት አደረጋት

“ገባኝ!!”  

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top