ፍልስፍና

ኦርዮ እና ዳዊት

ወታደር ለሀገሩ፣ ንጉስ ለክብሩ ይጨነቃሉ!

በመፅሐፍ ቅዱስ ካሉ አስገራሚ ታሪኮች አንዱ የኦርዮ ታሪክ ነው። ኦርዮ በንጉስ ዳዊት ዘመን የነበረ የእስራል ጀግና ነው። ሀገሩን፣ ንጉሱንና ህዝቡን ከልቡ የሚወድ ጀግና ነበር። በዚህ ጀግንነቱ፣ በዚህ ቀናነቱ ምክንያትም ነው ህይወቱን ያጣው። ከዚህ አንፃር ካየነው፤ የኦርዮ አሳዛኝ ታሪክና ፍፃሜ ከብዙ የዓለማችን ጀግኖች ታሪክና ፍፃሜ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነው። የመጥፊያው ሰበብ ያገባት ሴት ነበረች። ቤርሳቤህ የምትባል እጅግ ውብ የሆነች ሚስት ነበረችው። የሀገሬ ጥቅስ ፀሐፊ “ቆንጆ እና ታክሲ ትርፍ መጫን ይወዳሉ!” እንዳለው ሆኖ በእርሷ ውበት ጦስ ነው ኦርዮ ህይወቱን እንዲያጣ የሆነው። ጀግኖች ብዙውን ጊዜ ቆንጆዎችን ያጠምዳሉ ወይም ቆንጆዎቹ ራሳቸው እያጠመዷቸው ሊሆን ይችላል፤ ብቻ ብዙ ጀግኖች ቆንጆ ሴት ያገባሉ።

 በዳርዊን ህግ መሰረት ተፈጥሮ ባደለቻቸው ብርታት የተሻሉ ሴቶች እንዲያገቡ አድርጓቸው ሊሆን ይችላል። ከዚያ አንድም በውርድት አንድም በብስጭት ነው የሚሞቱት። ምክንያቱም አንደኛ ጀግና ቢሆኑም ሴቶቹ አንዴ ሱሪያቸውን አስወልቀው ካዩዋቸው በኋላ እንደማንኛውም ወንድ ወይም ከዚያ ያነሰ ሆነው ሊያገኟቸው ይችላሉ። ሰው በእንጀራ ብቻ አይኖርም እንደተባለው ሴቶችም ቢሆኑ በስም እና በዝና ብቻ አይኖሩም፤ ፍቅርና የዘወትር እንክብካቤ ማግኘት አለባቸው፤ ሙቀት ማግኘት አለባቸው። ስለዚህ ወደሌላ ያማትራሉ፤ በዚህ ጊዜ ጀግናው መቅናት ይጀምራል። በዚህ ምክንያትም ወይ የሰው ህይወት ያጠፋል ወይ የራሱን ህይወት የሚያጣበት ሁኔታ ይፈጠራል። አንድም እንደ ኦርዮ ከኋላ በስውር በተሸረበ ሴራ ህይወቱን ሊያጣ ይችላል። ለማንኛውም የኦርዮ ታሪክ እንደሚከተለው ነው።

 የእስራኤል ሰራዊት ኢዮአብ በተባለ ጄኔራል እየተመራ ከሶርያውያን ጋር ከፍተኛ ጦርነት እያካሄደ ነው። በዚህ ወቅት ንጉስ ዳዊት በሚኖርበት የኢየሩሳሌም ቤተመንግስት ደግሞ እንዲህ ሆነ። አንድ ቀን ወደ አመሻሹ ገደማ ንጉስ ዳዊት ከምንጣፉ ተነሳ። በንጉሱም ቤት በሰገነቱ ላይ ተመላለሰ። የማታውን ንፁህ እና ነፋሻ አየር እየወሰደ፤ ጀምበሯም ስትጠልቅ የሚኖራትን ድንቅ ውበት እየተመለከተ ነበር ማለት ነው። በዚያን ወቅት፣ ሰገነት ላይ ሳለ አሻግሮ ሲያማትር አንዲት ገላዋ ሲያዩት የሚያማልል ሴት ከወንዙ ዳር እርቃኗን ሆና ስትታጠብ በርቀት ተመለከተ።

በድሮ ጊዜ ሻወር ቤት ስላልነበረ ወይዛዝርቱ ሁሉ ወንዝ እየወረዱ ነበር የሚታጠቡት። ለነገሩ በእኛ ሀገርም እንደዚያው ነው። ወደ ገጠር ብንሄድ ሴቷ ሁሉ ወንዝ እየወረደች ነው የምትታጠበው። እንዲያውም ልጆች ሆነን ከብት ስንጠብቅ ከሚያስደስተን ነገር አንዱ ሴቶች ወንዝ ወርደው ሲታጠቡ ተደብቆ ማየት ነበር። እኛ ሰው እንዳያየን በቁጥቋጦ ስር ወይም በሆነ ቅጠል ውስጥ እንደበቅና በደንብ፣ በቅርበትና በትክክል በሚታየን ቦታ ላይ ሆነን “ፖርኖግራፊ”በነፃ እናይ ነበር። በዚያን ጊዜ የከተማ ልጆች “ፖርኖግራፊ” ይመለከቱ የነበረው በፊልም ቤት ለዚያውም ስሙኒ ከፍለው ነው። እኛ ግን እድለኞች ሆነን ኦርጅናሉን ነበር በቦታው፣ በተፈጥሮው በነፃ የምናየው።

       አምላክ መቼም ሴትን ሲፈጥራት ውብ እንድትሆን ያለውን ጥበብ ሁሉ አንጠፍጥፎ ሳይጠቀም አልቀረም፤ ይኸው ከዚያች ቀን ጀምሮ ምንም ነገር መፍጠር አቆመ። እንደኛ ነገስታት እርሱንም ፈጣሪው እጁን ቆርጦት ይሆን እንዴ! ድሮ ነው አሉ ነገስታቱ ጥሩ አናጢ ከሀገር ሁሉ አስፈልገው ቤተ መንግስታቸውን ያሰሩና ሌላ ተመሳሳይ ቤት እንዳይሰራ በማሰብ አናጢውን ይገድሉት ነበር ይባላል። ሀበሻ የእርሱን ከፍታ የሚለካው በሌላው ውድቀት ወይም ዝቅ ማለት ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። ብቻ እግዜር ሴት ከፈጠረ በኋላ ምንም ነገር አልፈጠረም። ሴቶቹ ግን እየተባዙ፣ እየተባዙ ሄደው ወንዱን ሁሉ ግራ አጋብተውታል። ምነው ዛሬ በሴቶች ላይ እንዲህ አመረርኩ? ቁርስ አልበላሁም እንዴ! ውዷ ባለቤቴ አትስማ! እስኪ ወደ ልጅነት ታሪኬ አንዴ ጎራ ብለን እንመለስ።

ከዕለታት በአንዱ ቀን እንዲህ ሆነ። ሶስት ኮረዶች ውሀ ሊቀዱ ወደ ወንዙ ወርደው ሳለ በዚያውም ልብሳቸውን አወላለቁና መዋኘት ይጀምራሉ። እኛ በጣም ትናንሽ ብንሆንም፤ ባላወቅነው ምክንያት ሴቶች ሲዋኙ ወይም ሲታጠቡ የማየት ሱስ እጅግ ተጠናውቶን ነበር። ያን ቀንም እንደዚሁ ተደብቀን እያየናቸው ነበርና አንዱ ጓደኛችን “ቀስ ብዬ ሄጄ ልብሳቸውን ሰርቄ ላምጣው ወይ?” ይለናል። እኛም በሀሳቡ ተስማምተን እንዲሄድ አበረታታነው። በደረቱ እየተሳበ ሄዶ እነርሱ ሳያዩት ልብሳቸውን ይዞ መጣ። እነርሱ እየዋኙ ስለነበር ፈፅመው አላዩትም። ከዚያ ልብሱን ወስደን በሆነ ሳር ውስጥ ደበቅነው። ኮረዶቹ ዋኝተው ከጨረሱ በኋላ ገላቸውንም በዚያው ታጥበው ወጡ። ልብሳቸውን ቢያዩ የለም! ቢፈልጉ ቢፈልጉ ሊያገኙት አልቻሉም። በመጨረሻ ማልቀስ ጀመሩ። እኛ ደግሞ ባለንበት ቦታ ተደብቀን መሳቃችን ቀጠልን።

እዚያ ቁጭ ብለው እያለቀሱ ለብዙ ሰዓታት ከቆዩ በኋላ በአጋጣሚ ሌሎች ሰዎች መጥተው ለእነርሱ ነጠላቸውን ሰጥተው ገላቸውን እንዲሸፈኑ ካደረጉ በኋላ እኛን መፈለግ ያዙ። በዚህ ጊዜ እኛ ሮጠን አመለጥን። ልብሱን ግን አግኝተውት ወስደው ለልጃገረዶቹ ሰጧቸው። ሮጠን ማምለጥ ብንችልም ማንነታችን በመታወቁ ጉዳዩ ወላጆቻችን ዘንድ ደረሰ። በዚህ ምክንያትም ወደን እስከምንጠላ ድረስ ማታ ላይ ተገረፍን። ብቻ በልጅነቴ ከሚያስደስተኝ ነገር አንዱ ሴቶች ወንዝ ወርደው ሲታጠቡ ተደብቆ ማየት ነበር። ንጉስ ዳዊትንም አመሻሽ ላይ ወደ ቤተመንግስቱ ሰገነት የሚያወጣው ይሄ ነገር ሳይሆን አይቀርም። እስኪ ወደ ታሪኩ እንመለስ፤ አንዲት ሴት ከወንዙ ዳር እርቃኗን ሆኖ ስትታጠብ በርቀት ተመለከተ በሚለው ላይ ነበር ያቆምነው።

መልኳም በጣም ያማረ እንደ ነበር የምንረዳው መጽሐፉ “ሴቲቱ መልከ መልካም ነበረች” በማለት እንደገለፃት ስንመለከት ነው። በዚህ ጊዜ ዳዊት ከአሽከሮቹ አንዱን ልኮ ስለማንነቷ እንዲያጣራለት ነገረው። እንዲያጣራ የተላከው ሰውም ማን እንደሆነች ሄዶ ካጣራ በኋላ “የኤልያብ ልጅ የኬጢያዊው የኦርዮ ሚስት ቤርሳቤህ መሆኗን” ነገረው። በዚህ ሰዓት ዳዊት ጊዜ አላጠፋም፤ ሰው ልኮ ወደቤተመንግስቱ አስጠራት። ወደ ውስጥም አስገባት። ራሷ ፈቅዳም ይሁን አስገድዷት አብሯት ተኛ። መጽሐፉ “ከርኩሰትዋም ነፅታ ነበርና ተኛት” ይላል። ከዚህ

“ለሰባ ሺህ ወታደር ሞት ያላዘነ፤ ያላለቀሰ፤ ማቅ ያልለበሰ ህዝብ ንጉሱ ሞተ ሲባል በሚሊዮን ወጥቶ ቢያለቅስ አዘነ አይባልም”

አንፃር የእርሷም ፍቃድ ሊኖርበት እንደሚችል መገመት ይቻላል። ምክንያቱም በወር አበባ ላይ ነሽ ወይ ብሏት፤ አይደለሁም ብላው ሊሆን ይችላል። አለበዚያማ ከርኩሰትዋ መንፃትዋን እንዴት ሊያውቅ ይችላል?!

በዚህ ምክንያትም አረገዘች። ባሏ በአውደ ግንባር ሳለ ብታረግዝ እንዳመነዘረች ይታወቃልና ደነገጠች። በሙሴ ህግ መሰረት ማመንዘሯ የታወቀች ሴት በድንጋይ ነው ተወግራ የምትገደለው። (ይሄ የሙሴ ሕግ ዛሬም በአንዳንድ የዓረብ ሀገሮች ይተገበራል፤ ምን ያህል ወደኋላ ቢቀሩ ነው) በመሆኑም ቤርሳቤህ ወደ ንጉስ ዳዊት ትሄድና “ኧረ ጉድ ሆንኩልህ” ትለዋለች።

 “ምን ተፈጠረ?” ይላታል።

 “አረገዝኩ!”

“ታዲያ ምን ችግር አለው፤ ለዚህ የሚሆን መላ አይጠፋም። ባልሽን ከጦር ሜዳ አስጠራውና ካንቺ ጋር እንዲያድር አደርጋለሁ። ከዚያ ልጁ የእርሱ እንደሆነ አድርጎ እንዲያስብ ማድረግ እንችላለን” ይላታል። በዚህ ሀሳብ ተስማምተው ተለያዩ። በመጽሐፉ ላይ አልተገለፀም እንጂ በዚህ ጊዜም ቢሆን ወደ ንጉሱ እልፍኝ ጎራ ብለው አንድ ሁለት ተባብለው ሊሆን ይችላል።

ንጉስ ዳዊትም ወደ ጦር ጄኔራሉ ወደ ኢዮአብ “ኬጢያዊው ኦርዮንን ስደድልኝ” ብሎ መልዕክት ላከ። ኢዮአብም እንደተባለው ኦርዮን ወደ ዳዊት ላከው። ብዙ ቁልቁለት ወርዶ፣ ብዙ አቀበት ወጥቶ ኦርዮ ወደ ቤተ መንግስቱ መጣ። ወደ ንጉሱም እንዲገባ ተደረገ። ንጉሱም በክብር ከተቀበለው በኋላ ስለጦሩ አዛዥ ስለኢዮአብ፣ ስለሰራዊቱና ስለህዝቡ ደህንነት፣ ስለ ሰልፉ፣ ስለጦርነቱ ሁሉ ጠየቀው። ኦርዮም ሁሉም ደህና መሆናቸውን፤ ጦርነቱም ቢሆን በደህና ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን ነገረው። ከዚያ በኋላ ንጉስ ዳዊት ኦርዮን “በል ወደ ቤትህ ሂድ እግርህንም ታጠብ!” ብሎ አሰናበተው።

ኦርዮ ግን ከጌታው ባርያዎች ሁሉ ጋር በንጉሱ ቤት ደጅ ተኛ። ወደ ቤቱም አልወረደም። ይህን የታዘቡ የቤተ መንግስቱ ጠባቂዎች “ኦርዮ ወደ ቤቱ አልሄደም” ብለው ለንጉስ ዳዊት ነገሩት። ዳዊትም ኦርዮን “አንተ ከመንገድ የመጣህ አይደለምን? ስለምን ወደቤትህ አልወረድህም?” አለው።

ኦርዮም ዳዊትን እንዲህ በማለት መለሰለት፤ “ታቦቱ እና እስራኤል ይሁዳም በጎጆ ላይ ተቀምጠዋል፤ ጌታዬ ኢዮአብ እና የጌታዬም ሰራዊት በሰፊ ሜዳ ሰፍረዋል፤ እኔ ልበላና ልጠጣ ወይስ ከሚስቴ ጋር ልተኛ ወደ ቤቴ እሄዳለሁን? በህይወትህና በሕያው ነፍስህ እምላለሁ ይህን ነገር አላደርገውም!” አለው። ንጉስ ዳዊት በዚህ ጊዜ “ይሄን ጌጃ የሆነ ሰው ምን ባደርገው ይሻለኛል!” ብሎ ሳይናደድበት አልቀረም። ምክንያቱም ለነገስታትና ለባለፀጎች ሀገራቸው ክብራቸው እና ምቾታቸው እንጂ ሌላ ነገር አይደለምና ነው። ሀገር እና ህዝብ ትርጉም የሚኖረው ለድሀውና ለወታደሩ ብቻ ነው። ለዚህም ነው በማንኛውም ሰዓት ችግር ወይም ወረራ ባጋጠመ ጊዜ ውድ ህይወቱን የሚገብረው።

ንጉስ ዳዊትም በበነጋታው ኦርዮን ወደ ቤተ መንግስቱ አስጠራውና “ዛሬ ደግሞ በዚህ ተቀመጥ ነገም አሰናብትሃለሁ” አለው። ኦርዮም በዚያ ቀንና በነጋው በኢየሩሳሌም ተቀመጠ። ንጉሱ ዳዊት ኦርዮን ወደ እልፍኙ አስጠራውና በፊቱ አስቀምጦ እንዲበላና እንዲጠጣ አደረገው፣ አሰከረውም፤ ነገር ግን በመሸ ጊዜ ወጥቶ ከጌታው ባርያዎች ጋር በምንጣፍ ላይ ተኛ እንጂ ወደ ቤቱም አልወረደም።

ንጉስ ዳዊት በዚህ ጊዜ ከህሊናው ጋር መታረቅ ቢፈልግ ኖሮ ወይም እውነተኛ የፍትህ ንጉስ ቢሆን ኖሮ ከዛሬ ጀምሮ የእስራኤል ንጉስ አርዮ ነው ብሎ፣ አዋጅ አስነግሮ፣ ዘውዱንና ቤተ መንግስቱን አስረክቦ እርሱ ወደ ኦርዮ ቤት ወደ ቤርሳቤህ መሄድ የነበረበት። ለሁሉም የተሻለ አማራጭ ይሆን ነበር። እንደዚያ ቢያደርግ ደግሞ አሁን ካለው ታሪክ በተለየ ሁኔታ በጣም ገናና በሆነ ነበር። የፍቅር ተምሳሌት ተደርጎም በየዘመኑ በሚመጡ ትውልዶች በታሰበ! እርሱ ያደረገው ግን ተቃራኒውን ነው፤ ወደ መጽሐፉ እንመለስ፤

 “በነጋም ጊዜ ዳዊት ለኢዮአብ ደብዳቤ ፃፈ። በኦርዮም እጅ ላከው። በደብዳቤውም ኦርዮን ፅኑ ሰልፍ ባለበት በፊተኛው ስፍራ አቁሙት። ተመትቶም ይሞት ዘንድ ከኋላው ሽሹ ብሎ ፃፈ።” ታላቁ ንጉስ ዳዊት እግዚአብሔር እንደልቡ አለው የሚባልለት ዳዊት የራሱን ሀጢአትና እድፍ ለመደበቅ ሲል ይህን ያህል ርቀት መጓዙ እጅግ የሚገርም ነው! ከሁሉም በላይ ደግሞ በዚያን ጊዜ የነበሩ የእስራኤል ታሪክ ፀሐፊዎች እውነታውን እንዲህ አድርገው ሰንደው ማስቀመጣቸው ነው። እጅግ በጣም የሚያስመሰግናቸውን ተግባር ነው የሰሩት።

 የእኛ ሀገር የነገስታት ታሪክ ፀሐፊዎች ቢሆኑ ኖሮ ግን ኦርዮ እንዲገደል የተደረገበትን ምክንያት ትክክል መሆኑን ለማሳየትና የንጉሱን ገበና ለመደበቅ ሲሉ የሌለ ታሪክ ፈጥረው ኦርዮ ለጠላት ወገን መረጃ አሳልፎ ሲሰጥ ስለተገኘ ወይም ስለተደረሰበት ነው እንዲሞት የተፈረደበት ብለው ሌላ የታሪክ በደል ባደረሱበት ነበር። ለምን ይህን ያህል ውሸትና ማስመስል በታሪካችን ላይ ለዘመናት ነግሶ እንደዘለቀ ከምክንያቱ ጭምር የሚያስረዳን ፈላስፋ ይጥፋ!

ኢዮአብም እንደ ተባለው አደረገ። ከተማይቱን በከበበ ጊዜ የጠላት ወታደሮች በብዛት እንዳሉበት በሚያውቀው ስፍራ ኦርዮን አቆመው። የከተማይቱ ሰዎችም ወጥተው ከኢየአብ ጋር ተዋጉ። ከዳዊትም ባርያዎች፣ ከህዝቡም ብዙ ሰው ሞተ፤ የኬጢያዊው ኦርዮም ወደቀ። ኦርዮ ተመቶ ቆስሎ ሳለ ጓደኞቹ ለጠላት አጋፍጠውት መሄዳቸውን ባየ ጊዜ ከደረቱ ከሚፈሰው ደሙ በጣቱ ወስዶ መሬቱ ላይ እንዲህ ብሎ እንደፃፈ ፤

 “ጀግና ሰው ቢሞትም ታሪክ አይሞትም`

 ባገሩ መሬት ላይ ይጻፋል በደም።`”

ይሄን ክህደት በዓይኑ ካየ በኋላ ነፍሱ አለፈች። ምንም እንኳ በሚያምናቸውና በሚያከብራቸው መሪዎቹ ሴራ፤ በንጉሱ ክፋትና ራስ ወዳድነት ህይወቱ ቢያልፍም በክብር እና በጀግንነት፤ ህሊናውን ሳያሳድፍ፣ ለሀገሩ እና ለህዝቡ መስዋዕት ለመሆን በነበረው እምነት እንደፀና ለዘላለሙ አንቀላፋ። ክህደት ላይ ተንተርሶ እንደ አባቶቹ አሸለበ። ከዚህ ታሪክ በመነሳት ይመስላል በሀገራችንም፤ የጎጃሙ ደጃዝማች ጎሹ በራስ አሊ ታዝዘው፤ ከቋራው ካሳ ጋር ጦርነት ገጥመው ሲዋጉ በሞቱ ጊዜ አንድ አልቃሽ፤

 “ጎሹ እንደ አርዮ አሊ እንደ ዳዊት

ከጥንት አይደለም ወይ ተልኮ መሞት።”

 በማለት አልቅሳለች። አልቃሿ የረሳችው ወይም የዘነጋችው ነገር ደጃዝማች ጎሹ የሞቱት ለጌታቸው ሲዋጉ እንጂ በጌታቸው ሴራ አለመሆኑን ነው።

ፍልስፍናው የሚመጣው እዚህ ላይ ነው። ሀገርና ህዝብ ለአንድ ገናና ንጉስ የክብሩ እና የግርማ ሞጎሱ መገለጫ እንጂ ሌላ አይደሉም። ከዚህ ውጪ ያለው የሀገር እሳቤ የተረት ተረት ያህል ቀልድ እና ጨዋታ ነው። ለአንዳንድ መሪዎች ህዝብ ማለት ለንጉስ ሰራዊት የሚሆን ወይም ቀለብና ስንቅ የሚሰበሰብበት መስክ ነው። ሰራዊት ማለት ደግሞ በማገዶነት ለጦርነት የሚያገለግል እንጨት ነው። ህዝብና ወታደር ቁጥር እንጂ በራሱ ጊዜ ህይወት እና ዋጋ ያለው ነገር አይደለም። ይህን ያህል ወታደሮች ሞቱ ነው የሚባለው እንጂ የእያንዳንዱ ወታደር ሞት አይነገርም። ለምሳሌ በኢትዮ‐ ኤርትራ ጦርነት ጊዜ ከሰባ ሺህ የሚበልጥ ሰራዊት እንደሞተ ነው የሚነገረው፤ ሰባ ሺህ ምንድነው ቁጥር! በቃ ቁጥር ደግሞ ስሜት አይሰጥም። እያንዳንዱ ወታደር ስንት ልጅ እንዳለው፣ ምን ዓይነት ዓላማና ምን ዓይነት ታሪክ እንደነበረው አይነገርም፤ ለመስማት የሚፈልግ ሰውም የለም።

ንጉሱ ሲሞት ግን ሀገር ያለቅሳል ወይም እንዲያለቅስ ይደረጋል። እዚህ ላይ ለንጉስ የሚለቀሰው ንጉስ ሆኖ ሳለ በመሞቱ ነው እንጂ ሰው ሆኖ በመሞቱ አይደለም። ለሰባ ሺህ ወታደር ሞት ያላዘነ፤ ያላለቀሰ፤ ማቅ ያልለበሰ ህዝብ ንጉሱ ሞተ ሲባል በሚሊዮን ወጥቶ ቢያለቅስ አዘነ አይባልም። ለምን እንደሚያለቅስ ግን ግልፅ አይደለም፤ ምናልባት የሰው ከንቱነት እየታየው ሊሆን ይችላል። ብቻ የሰው ልጅ ከዚህ አንፃር አስመሳይ እና ሾካካ የሆነ ፍጥረት ነው።

ንጉስ ዳዊት የኦርዮን መሞት ከሰማ በኋላ ትንሽ ቆየት ብሎ ቤርሳቤህን በይፋ አገባት። ባሏ የሞተባት ሴት ሆናለች እና ህጉ የሚቃወመው አልነበረም። ካገባት በኋላ የተረገዘው ልጅ ተወለደ። በዚህ ጊዜ ነበር የእግዚአብሔር መልዕክተኛ ወደቤቱ የመጣው። እንዲህም አለው፣ “አንተ ንጉስ ነህ፣ እስኪ ፍረድ። አንድ ባለፀጋ ነበረ አንድ መቶ በጎች የነበሩት። ነገር ግን አንድ ቀን ወደ ቤቱ እንግዳ በመጣበት ሰዓት የራሱን በጎች ማረድ ሳስቶ የአንድ ድሃ ጎረቤቱን አንዲት በግ ወስዶ አረደበት” ይለዋል። ንጉስ ዳዊት በዚህ ጊዜ በጣም ተቆጣ “ይሄ ሰው ወንጀለኛ ነው አምጡልኝ መቀጣትም አለበት” አለ።

 በዚህ ጊዜ ናታን የተባለው ነብይ እንዲህ አለው “ያ ሰው አንተ ነህ። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በእስራኤል ላይ ንጉስ ልትሆን ቀባሁህ፣ ከሳኦልም እጅ አዳንሁህ፣ የጌታህንም ቤት ሰጠሁህ፣ የጌታህንም ሚስቶች በብብትህ ጣልሁልህ፣ የእስራኤልና የይሁዳን ቤት ሰጠሁህ፣ ይህም አንሶ ቢሆን ኖሮ ከዚህ የበለጠ እጨምርልህ ነበር። አሁንስ በፊቱ ክፉ ትሰራ ዘንድ የእግዚአብሔርን ነገር ለምን አቃለልህ? ኬጢያዊውን ኦርዮን በሰይፍ መትተሃል፣ ሚስቱንም ወስደሃል፣ እርሱንም በአሞን ልጆች ሰይፍ ገድለሃል። ስለዚህም አቃልለኸኛልና የኬጢያዊውን ኦርዮንም ሚስት በሰይፍ ወስደሃልና ለዘላለም ከቤትህ ሰይፍ አይርቅም።”

 ነብዩ ናታን በእግዚአብሔር ስም ከፍ ብሎ የተጠቀሰውን ወቀሳ ለንጉስ ዳዊት አሰምቷል። እንዲህ ያለ ነብይ ንጉስን በእግዚአብሔር ስም የሚገስፅ አባት ምነው በእኛ ሀገር ጠፋ እላለሁ አንዳንድ ቀን! እንደ ደቂቀ እስጢፋኖስ በአደባባይ እየተገረፉ ምላሳቸውም እየተቆረጠ ይሆናላ! ብዙውን ጊዜ ወደ ስራ ስሄድ በየግድግዳው የነብያትና የሐዋርያት ስም ተብሎ ተለጥፎ አያለሁ። ”ነብይ እገሌ ዛሬ ስብከት ያካሂዳልና እንድትገኙ” የሚል ሳነብ ይቺ ሀገር በኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን በውሸትና በነብያት ብዛትም እድገት እያሳየች ነው እላለሁ። ይልቅ በዚያ ዙርያ አንድ ሜክስኮ አካባቢ ያነበብኩትን ልንገራችሁ። “ነብይ እገሌ ነገ በእንትን ቤተክርስቲያን ከነሚስቱ ስለሚገኝ ሁላችሁም ተጋብዛችኋል” ይላል። እሰይ! ነብዮቻችን ባለሚስቶችም ናቸው ማለት ነው።

 እኔ የምለው ነብዩ ናታን እግዚአብሔር “የጌታህንም ሚስቶች በብብትህ ጣልሁልህ” ብሎሃል የሚለው እንዴት ነው! አንድ ለአንድ የሚለው ሕግ የዚያን ጊዜ አልወጣም ነበር እንዴ። ረስቼው ለካ አንድ ላንድ ያለው የግሪክ ፍልስፍናን ያጠናው ሐዋሪያው ጳውሎስ ነበር። መቼም ጳውሎስ እንዲያ ሊል የቻለው አንዷም መከራ ነች ብሎ መሆን አለበት። እንዴት ነው እኔም ይሄ ፀረ ሴት የሆነው አመለካከት ሳላስበው እየተጋባብኝ ነው እንዴ! ውጭ ስውል ነው እንደዚያ የማስበው። ከወንዙ ወዲያ ባለው ዓለም ስውል እንዲህ ነው የሚያደርገኝ። ወደቤታችን የሚወስደውን መንገድ ከተሻገርኩ በኋላ ሴት መላዕክት ናቸውና የሚቀበሉኝ ስለሴት ጥሩ ጥሩ ነገር ነው የሚያናግረኝ። በዚያን ጊዜ ሁሉም ነገር ብሩህ ሁሉም ነገር ደስታ ብቻ ይሆናል።

 ወደ ንጉስ ዳዊት ጉዳይ እንመለስና ናታን ለዳዊት የሚለውን እንስማ፤ ዳዊት እግዚአብሔርን እንደበደለ ተናገረ። በዚህ ጊዜ ነብዩ ናታን “እግዚአብሔር ኃጢአትህን አርቆልሃል፣ አትሞትም ነገር ግን በዚህ ነገር ለእግዚአብሔር ጠላቶች ታላቅ የስድብ ምክንያት አድርገሃልና ስለዚህ ደግሞ የተወለደልህ ልጅ ፈፅሞ ይሞታል” አለው።

በዚህ ታሪክ ላይ እንዴት ዓይነት ፍርድ ነው የምናየው! አባትየው ባጠፋው ጥፋት ልጅየውን መቅሰፍን ምን አመጣው፤ አበሻ ሲተርት አህያውን ፈርቶ ዳውላውን የሚለው እንዲህ ዓይነቱ ነገር ሲገጥመው ነው። እግዚአብሔር በዳዊት መጨከን አልቻለም፤ እንዲያውም በዚህ ምክንያት ዳዊት በማዘኑ የተነሳ አይዞህ ከእርሷ ሌላ ልጅ እሰጥሃለሁ ብሎ ካባበለው በኋላ ነው ሴት አውል የነበረውና በዚህ ሴት አውልነቱም ጥበበኛው ንጉስ በመባል የሚጠራው ሰሎሞን የተወለደለት። ከሁለት በውስልትና ከተጋቡ ሰዎች ተወልዷልና ሰባት መቶ እቁባቶች የማይበቁት ሞገደኛ ንጉስ ሆነ። እውቀትን በመሻት ሀገር አቆራርጣ የሄደችውን የእኛ ልጅም እንደ ንጉስ ሳይሆን እንደመርካቶ ዱርዬ አታልሎ በእፍኝ ውሃ ክብረ ንፅህናዋን ወስዷል። በዚህ ጊዜ ንግስት ሳባ “ለዚህ ለዚህማ ሀገሬስ ነበር አይደል!” ብላለች አሉ። አንድ ያልታወቀ ታሪክ ዘጋቢ እንዳለው። ይልቅ ነብዩ ናታን “በቤትህ ሰይፍ አይጠፋም” ያለው ትንቢት ዛሬም ድረስ በእስራኤል ምድር ሰይፍ እንደተመዘዘ ነውና ያስገርማል! እነርሱም በሰይፍ ፍልስጥኤማውያንን ያጠፋሉ፤ እርግማኑ እየሠራ ነው ማለት ነው።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top