ስርሆተ ገፅ

አንድ አፍታ ከፕሮፌስር ታደለ ጋር

ፕሮፌሰር ታደለ ገብረሕይወት ይባላሉ:: ኢትዮጵያ ውስጥ እያሉ ጋዜጠኝነቱንም ደራሲነቱንም ሰርተውበታል፤ ኖረውበታል:: ሳይወዱ በግድ ከአገር እንዲወጡ የተደረጉት በደርግ ዘመን ነው:: አገር ውስጥ የጀመሩትን የከፍተኛ ትምህርት ገፍተውበት በተሰደዱበት ፖላንድ አገር የእንግሊዝኛ ስነ ጽሑፍን ተምረው የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ያዙ:: እዚያው ማስተማር ጀመሩ:: ከዚያም ወደ አሜሪካ ተሻግረው በርክሌይ፣ በሂዩስተን እና በአርካንሳ ዩኒቨርሲቲዎች በፕሮፌሰርነት ማዕረግ የአፍሪካ ስነ ጽሑፍን ለበርካታ ዓመታት አስተማሩ:: አሁን ጡረታ ላይ ቢሆኑም፤ ዛሬም ሂዩስተን ዩኒቨርሲቲ ተጋባዥ መምህር (Visiting professor) ሆነው ያስተምራሉ:: እንግዳችን ፕሮፌሰር ታደለ ከሰፊው የህይወት ልምዳቸውና ትዝታቸው ቆንጥረው እንዲህ አውግተውናል::

 ታዛ ፦ ከማይረሳዎት የቀደመ ትዝታዎ ወጋችንን እንጀምር ይሆን ፕሮፌሰር?

 ፕሮፌሰር ታደለ፦ ደስ ይለኛል:: ከኋላ ልምጣልሃ? አባቴ በአምስቱ ዓመት የጣሊያን ወረራ ወቅት አምርሮ የተፋለመ፣ በዚህም የተሸለመ ጦረኛ ነበር:: ከድሉ ስድስት ዓመት በኋላ በ1939 ዓ.ም ወሊሶ ውስጥ ተወለድኩ:: ዘመናዊ ትምህርት እንድማር ብሎ አዲስ አበባ የእናቴ ዘመዶች ዘንድ ላከኝ:: ኮከበ ጽባህ እስከ ስምንተኛ ክፍል ተማርኩ:: ስለራስ አይነገርም እንጂ ጎበዝ ተማሪም ነበርኩ:: ጥበቡ ተከፈተልኝ:: እናም The Merchant of Venice የተሰኘውን የዊሊያም ሼክስፒርን ድርሰት ወደ ቀላል እንግሊዝኛ ለውጬና የክፍል ልጆቼን አስጠኝቼ ኮሜርስ እንዲታይ አደረኩ:: ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን አየው:: ተደሰተ:: በጊዜው በብሔራዊ ቴያትር ምክትል ስራ አስኪያጅ ነበር:: እጄን ይዞ አሸለመኝ:: እስከመጨረሻው ጓደኛሞች እንደሆንን ቀጠልን:: አስተማሪዬ፣ መካሪዬ፣ አሳዳጊዬም ጭምር ሆኖ በጥሩ ወዳጅነት ኖርን:: የሚያሳዝነው ኒውዮርክ ልጠይቀው ሄጄ ያረፈ ዕለት የእሱ አልጋ ላይ ነው የተኛሁት:: ትኩሳቱ ይሰማኝ ነበር:: ይህ ነው ልጅነቴንና አዛውንትነቴን ያስተሳሰረው ከውስጤ የማይጠፋ ትዝታ::

ታዛ ፦ ከዚያስ የትምህርት ጉዞዎ እንዴት ቀጠለ?

ፕሮፌሰር ታደለ፦ ከኮሜርስ ንግድ ስራ ት/ቤት እንደጨረስኩ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፕሬዚዳንት ጸሐፊ ሆኜ ተቀጠርኩ:: ልዩ ረዳት እንደማለት ነው:: ለውጪ እና ለአገር ውስጥ የሚተላለፉ መልዕክቶችንና ንግግሮችን ማዘጋጀት ነወ:: ኑሮን በደመወዝ አንድ አልኩ:: እዚያው እያለሁ ፖለቲካል ሳይንስ ትምህርቴን ቀጠልኩ:: ከዚያም ሶሻል ወርክ ተማርኩ:: አንድ ዲፕሎም ሁለት ቢ.ኤ ያዝኩ:: ይህ የሆነው የደርግ አብዮት ከመምጣቱ በፊትና በኋላ ነው:: የንግድ ስራውን ትምህርት መቀጠል አልፈለኩም:: ነፍሴ ያለችው ጥበቡ ላይ ነበር:: ድርሰት ውስጤ ይንተገተግ ነበር:: እናም ባለቤቴ የመጀመሪያውን ልጅ ለመውለድ ስታምጥ እኔም «ማነው ኢትዮጵያዊ» የተሰኘውን መጽሐፌን አምጥ ነበር:: እሷ ቀድማ በወራት ልዩነት መጽሐፌ ተወለደ:: ብዙ ኮፒ ተሸጠ:: ጥሩ የገንዘብ አቅምም ፈጠርኩበት:: የኢትዮጵያ ሕዝብ የሳመልኝ ይህ ታሪክ ተኮር ልቦለድ መጽሐፍ ከድህነት አወጣኝ:: በሳምሶናይት ነበር ገንዘብ እሰበስብ የነበረው:: እንጦጦ ላይ መሬት ገዛሁ፣ ቤት ሰራሁ:: በቃ መንገዴ ይህ ነው ብዬ እርምጃዬን አፈጠንኩ::

ታዛ ፦ ቀጣዩ መጽሐፍዎ ምን ሆነ?

ፕሮፌሰር ታደለ፦ «ኢትዮጵያ ትቅደም» ነው:: በዚህ ደርጎች አሰቃዩኝ:: «ማን ፈቀደልህ?» እያሉ አራተኛ እያመላለሱ ትንሽ አንገላቱኝ:: ደጋግመው አነበቡት:: አብዮቱን የሚነካ አለመሆኑን ተረዱ:: ከዚያም «በቃ ጥሩ ነው፤ አንነካህም ቀጥል!» አሉኝ:: የሚገርመው ሁለቱም መጽሐፎቼ ሳንሱር ገብተው ተፈቅደው ነው የታተሙት:: ማውጣት የሚፈልጉትን ሁሉ አውጥተው ነው እንዲታተሙ የሆኑት:: ያም ሆኖ አላረፍኩም:: «ከርሞ ዘማች» የሚለውን መጽሐፌን አስከተልኩ:: ይህ ደግሞ በእድገት በህብረት ዘመቻ ወቅት የጻፍኩት ነው:: ዘማቹ ሁሉ የእኔን መጽሐፍ ይዞ ነበር የዘመተው:: ኢትዮጵያ ምን ያህል ድንግል እንደሆነች፣ ምን ያህል ቅድስት እንደሆነች ያሳየሁበት፣ በስራና በመተባበር መለወጥ እንደሚቻል የሰበኩበት ነው:: መጽሐፉን ከገጽ እስከ ገጽ ያረሙልኝ ሊቀ ስልጣናት አባ ሀብቴ (ዛሬ አቡነ መልከጸዴቅ) ናቸው:: በመቀጠል የኮሚኒስት ቻይናን The Red Book የተሰኘውን መጽሐፍ ነው የተረጎምኩት:: «ተራማጅ ጥቅሶች» በሚል ርዕስ:: የማኦ ፍልስፍና ነው:: ያኔ የሶሻሊስት አገር ርዕዮተ ዓለም ተከታዮች የመጽሐፍ ቅዱስ ያህል አክብረው፤ አክብደውም የሚያዩት መጽሐፍ ነበር:: እያንዳንዱ የደርግ አባል የእኔ መጽሐፍ ነበረው በኪሱ:: በየውይይት ክበባቸው ለንግግር ማሳመሪያ ጥቅስ ይመዘዝባት ነበር «ማኦ እንዳለው …» እየተባለ:: … ከዚያ ወደ ጀርመን ተላኩ::

ታዛ ፦ የመጽሐፍ ነገር አበቃ?

ፕሮፌሰር ታደለ፦ አላበቃም! ቆይ ልመጣ ነው:: እዚያ ያለፍላጎቴ ነው ደርግ የላከኝ:: የህብረት ማህበር እንዴት እንደሚሰራ ለመማር ነው አካሄዴ:: ከዩኒቨርሲቲ ለቅቄ ችርቻሮ ኮርፖሬሽን የሚባል ድርጅት እንደተቀጠርኩ ነው ይህ የሆነው:: እና እዚያ ሆኜ ፊት በጅምር ያቆየሁትን «የውሃ መንገድ» የሚል ርዕስ ያለው ሳይንሳዊ ልቦለድ መጽሐፍ ጽፌ ጨርሼ ተመለስኩ:: ለማሳተም ስሞክር ሳንሱር አደባየው:: እንደገና ጻፍኩት:: አልሆነም:: ስምጥ ሸለቆን፣ ዘጠኙን ሃይቆቻችንን፣ መሬታችንን፣ ማንነታችንን፣ ተፈጥሯዊ ሃብቶቻችንን በደንብ አጥንቼ የሰራሁት ነው:: በዋናነት ሃይቆቻችንን በቦይ በማገናኘት ምን ያህል ልንጠቀም እንደምንችል፤ የሚተነትን ከድህነት የመውጪያ አንዱ ጥሩ አማራጭ መሆኑን የሚያመላክት መጽሐፍ ነው:: የጀርመንና የሌሎች አገሮች ተሞክሮ ከአገራችን ነባራዊ ሁኔታ አንጻር እንዴት ሊተገበር እንደሚችልም በሳይንሳዊ መንገድ ጥቆማ የሚሰጥ ነው:: የሚያሳዝነው ግን አማረ ማሞ መጽሐፉን ስለወደደው ያኔ አንጀቱን እየታመመ ነው የአርትኦቱን ስራ የሰራልኝ:: ሦስት ጊዜ ሞከርኩ ሳንሱር ግን አላሳልፈው አለ:: በዚህ ምክንያት በጣም ተናደድኩ:: እብድ ሆንኩ ማለት ይቻላል:: በዚህ ሁኔታ ላይ እያለሁ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ገባሁ::

 ታዛ ፦ በጋዜጠኝነት?

ፕሮፌሰር ታደለ፦ አዎ! የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ጋዜጠኛ ሆንኩ:: በሽቶው ከሚወለወል ቢሮ በአግባቡ ወደማይጠረግ ምቾት አልባ ቢሮ ነው እንግዲህ የተዘዋወርኩት:: ክፍለአገራትን በሙሉ እየተዟዟርኩ ያየሁበት፣ ባህልና ታሪክን በአግባቡ የተረዳሁበት ቤት ነው‐ የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ:: የወጣቶች ዓምድ ላይ ነበር ደግሞ አዘጋጅነቴ:: ደብዳቤ ይጎርፍልኝ ነበር:: ልክ እንደ ጳውሎስ ኞኞ ጥያቄዎች ሲላኩልኝ እመልስ ነበር:: በምክትል ዋና አዘጋጅ ደረጃ ደስ ብሎኝ ሰራሁ:: ሰርቶ የሚያሰራን አጥናፍ ሰገድ ይልማ ነበር ዋና አዘጋጁ:: ተራማጅ ነበር:: በፈታኝ ጊዜ ጋዜጣዋን ቀጥ አድርጎ የመራት ሰው ነው:: ያኔ ማዕረጉ በዛብህ፣ መርስኤሐዘን አበበ፣ መኮንን፣ እና ሌሎች ባልደረቦቼ ነበሩ:: ለአራት ዓመት ሰራሁና ለቀቅኩ::

 ታዛ ፦ መቼም ጋዜጠኝነት ፈታኝ ነገር አያጣውም፤ በዚህ ረገድ የገጠመዎት የተለየ ነገር አለ?

ፕሮፌሰር ታደለ፦ ምን የማይገጥመን አለ! አንዴ ከአንድ ተሳታፊ ግጥም መጣልኝ:: ሳነበው ሰውነትን ፍም የሚያደርግ በጣም የሚያስደስትና የአገር ፍቅርን የሚሰብክ ነው:: ቋንቋው የሚጣፍጥ:: ይታተም ብዬ ፈረምኩና ለአለቃዬ አጥናፍሰገድ መራሁት እሱም ወዶት ስለነበረ አሳለፈው:: በማግስቱ ታትሞ ሲወጣ ትልቅ ፈንጂ ይዟል ለካ:: የግጥሙ የመጀመሪያ ፊደሎች ቁልቁል ሲነበቡ «ኢሕአፓ ምንጊዜም ያሸንፋል! » ነው የሚለው:: በጠዋቱ አገር ታምሷል:: ያኔ ጋሽ በዓሉ ግርማ ነበር የማስታወቂያ ሚኒስቴር ቋሚ ተጠሪ:: ለካ «ታደለን ጋቢ ከቤትህ አስመጣ በሉት» ብሎ መልክት ልኮብኛል:: እሱ የራሱን ጋቢ አስመጥቷል:: መታሰር አይቀርማ! እንኳን ይህን የሚያክል ግዙፍ ስህተት አንዲቷም ቃል መንግስትን የምታሳጣ ከሆነች ወህኒ ነው:: ታዲያ ያን ዕለት አገር ሰላም ነው ብዬ ቢሮዬ አቅራቢያ ስደርስ አንድ መጥፎ ዜና የሚወድ ተላላኪያችን በሹክሹክታ «በል እንግዲህ የዛሬውን ቀን እግዚያብሔር ያውጣህ…» አለኝ:: «ምንድነው? ምን ተፈጠረ?» እያልኩ ብወተውተው አልነግር አለኝ:: ልቤ እየመታ ቢሮዬ ስገባ ባልደረቦቼ ጋዜጣዋን እያገላበጡ ይተክዛሉ:: አለቃዬ አጥናፍሰገድም አለ:: ምንም አልተባባልንም:: ሁላችንም ከመጠየቅ አናመልጥማ:: አለቀልን! ከዚያ ወደ ባለቤቴ ደወልኩና ሁኔታውን ነገርኳት:: «ምናልባት ወህኒ ቤት ሳይወስዱኝ አይቀሩም፤ ጋቢ ምናምን አዘጋጅልኝ» ብዬ የጋሽ በዓሉን መልዕክት ላሳካ መሆኑ ነው:: ባለቤቴ እዛው መታመም ጀመረች::

ታዛ ፦ መቼም መታሰርዎ አልቀረም?

ፕሮፌሰር ታደለ፦ ቆይ ልነግርህም አይደል:: በዚህ ጭንቅ ወስጥ ሆኜ ወደ ማስታወቂያ ሚኒስትሩ ሻለቃ ግርማ ይልማ ዘንድ ደወልኩ:: ላገኘው አልቻልኩም:: ዝምድና ስላለን ሁሌም ችግር ሲገጥመኝ እሱጋ ነው የምደውለው:: በእኛ ላይ ሲጠበቅ የነበረው እርምጃም አልፈጠነም:: በዚህ ጭንቅ ጥብ ውስጥ እያለን እሱ በእኛ ላይ ሊወስኑ ከተሰበሰቡት የደርግ ኮሚቴዎች ጋር ሙግት ገጥሟል ለካ:: አንድ ጥያቄ ነው የረታቸው:: «ከእኛ ውስጥ ጽሑፍ ስናነብ ማናችን ነን የመጀመሪያውን ፊደል ቁልቁል የምናነብ?» በሚለው:: መልስ የለም:: በዚህ አተረፈን:: ባለቤቴ ግን አዕምሮዋ ተናወጠ:: እንቅልፍ አጣች፣ መወራጨት አመጣች:: ይባስ ብሎ «ባለቤቴን ወሰዱት… አሰሩት… ገደሉት …» እያለች መለፍለፍ አመጣች:: ለአሥራ አምስት ቀን አማኑኤል ሆስፒታል ገብታ አገገመች:: ከዚህ በኋላ ጋዜጠኝነቱን ትቼ ወደ ድርሰት ስራዬ ማዘንበል እንዳለብኝ ተሰማኝ:: «የውሃ መንገድ»ን እንደምንም ተጨቃጭቄ ለማሳተም ተነሳሁ:: በዚያ ዘመን ፓርቲዎች ሲቋቋሙ ጋዜጣ ውስጥ ነበርኩ:: ሰዎች ወደ ፓርቲዎች ማዘንበል ጀመሩ:: እኔ ደግሞ እንዲህ አይነት ነገር ውስጥ መግባት አልፈለኩም:: ትግል ነው ያኔ:: የሆነ ፓርቲን መቀላቀል አለብህ፤ ግን አልሆንኩም:: ይቆሰቁሱኛል፤ ይወተውቱኛል፣ አልሆንኳቸውም:: በዚህ ምክንያት በፓርቲዎች ሁሉ የተጠላሁ ሆንኩ:: በተለይ ደርጎች ብዙ ታገሉኝ:: ለመተዳደሪያ ቢሆንም መጽሐፍ እጽፋለሁ:: የምጽፈው ደግሞ ደርጎችን የጠቀመ እንጂ የጎዳ አልነበረም:: ስለዚህ ተውኝ:: ቢሆንም አልተመቸኝም::

ታዛ፦ ምክንያቱ ምንድነው? ይህን ያህል ተደክሞበት ሳንሱርን ያለማለፉ?

ፕሮፌሰር ታደለ፦ ፖለቲካዊ ምክንያት ነው ነገሩ:: ይመስለኛል የሳንሱር ሰዎች አሳልፈውት የተያዘው በላይኞቹ ነው:: በኋላ ስሰማ የእኔ ውትወታ በላይኞቹ የፖለቲካ አመራሮች ተሰምቷል:: መጽሐፉም ተነቧል:: ግን እንዲወጣ አልተፈቀደም:: መጽሐፉ ላይ ያለው መረጃና ጥበብ በቀላሉ የሚሰራ ነው:: መንግስት ሊያደርገው ይችላል፤ ግን ገንዘብ የለውም:: ስለዚህ መጽሐፉ ወጥቶ ከሚያሳጣን ባይታተም ይሻላል ነው ውሳኔው:: ህዝቡ ዘንድ ከደረሰ ጥያቄው ይበረታብኛል፣ ያስወቅሰኛል ብሎ ነው ደርግ የሰጋው:: በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለሁ ጋዜጠኝነቱን ትቼ በችርቻሮ ኮርፖሬሽን ውስጥ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሆኜ ተቀጠርኩ:: ከዛሬዪቱ ጋዜጠኝነት የለቀቅኩት በዚያች ግጥም ሰበብ ሳይሆን በወቅቱ ፖለቲካ ነው:: ከዚያም ከዚህም አባል ሁን እያሉ ሲያዋክቡኝ ነው የለቀኩት:: በኮርፖሬሽኑ ውስጥ እያለሁም መጽሐፌ ለምን አይታተምም?! እያልኩ እጮህ ነበር:: በየቢሮው እያንኳኳሁ እናገር ነበር:: እናም የመጽሐፉ እጣ በደርግ ሲወሰን « መጽሐፉ አይታተምም፤ ደራሲው ግን ውጪ አገር ሄዶ ይማርና በሁለት ቋንቋ ደራሲነቱን ይቀጥል» ነው የተባለው:: ሳልጠይቅ፣ ሳላውቅ ወዲያው ለአምስት አገራት ኤምባሲዎች ደብዳቤ ተጻፈ:: ቀድማ ፖላንድ ፈቃዷን ገለፀች፤ ሳልወድ በግድ እያለቀስኩ በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1986 ሄድኩ::

እኔ አገሬን አጥብቄ የምወድ ሰው ነኝ:: የሆነ ሆኖ የሕይወት መስመሬ ተለወጠ:: ተማርኩ፤ አስተማርኩ:: «የውሃ መንገድ» ግን ዛሬም ውስጤ አለች::

ታዛ ፦ ፖላንድ ላይ ነን፤ እዚያ ምን ተማሩ?    

 ፕሮፌሰር ታደለ፦ ዋርሶ ዩኒቨርሲቲ ለአምስት ዓመት የእንግሊዝኛ ቋንቋ ስነ ጽሑፍን (English literature‐ comparative literature) ተማርኩ:: ደስ ብሎኝ ተማርኩ:: የዓለምን ሥነ ጽሑፍ ፈተፈትኩት:: ያልታዘዝኩትን ሁሉ አነብ ነበር:: በአገሬ ስነ ጽሑፍን ተጠምቼ ነበር:: ተወጣሁት:: የሚገርምህ በዩኒቨርሲቲው ቤተ መጻሕፍት ውስጥ አንድ እኔ የምቀመጥባት ልዩ ቦታ ነበረች:: ተደፍቼ የምውልባት::

ታዛ ፦ መመረቂያ ጽሑፎትን (Dissertation) ምን ላይ አደረጉ?

ፕሮፌሰር ታደለ፦ አዎ መጨረሻ የዶክትሬት (Ph.D) ትምህርቴን ማንጠፍጠፊያ ያደረኩት በኢትዮጵያ ማህበረሰባዊ ጽነ ጽሑፍ ላይ ነው:: (Elites Character in Ethiopian Novels) ይላል ርዕሱ:: በዩኒቨርሲቲው አዲስ ግኝት ነበር:: ከዚያ በፊት በዚህ ርዕስ አልተሰራም:: ልመረቅ ስል የመጨረሻ የጥናቴ ግምገማ ዕለት ከመላው አውሮፓ 100 ፕሮፌሰሮች እና ምሁራን ተገኝተው ነበር:: ሁኔታው ቢያስፈራኝም የምጠየቀውን ሁሉ እንደምመልስ እርግጠኛ ሆኜ ነው የተገኘሁት:: የሚገርመው አንድ ጥያቄ አልጠየቁኝም፤ አቀራረቤ ስቧቸው በሁኔታዬ ተገርመው ነበር ያዳመጡኝ፤ ዝም ብለው ማጨብጨብ ብቻ:: ቆመው ማጨብጨብ:: ለምንድነው ያ የሆነው እነሱም አያውቁትም:: እውቀት እነሱ ዘንድ ብቻ ያለ ይመስላቸዋል:: በዚህ አጋጣሚ አንድ ነገር ልንገርህ:: በዩኒቨርሲቲው ትምህርት ላይ እያለሁ ለሦስት ወር ጉብኝት ወደ አገሬ ስመጣ ኤርፖርት ላይ ልብሴንና ሁለመናዬን በደንብ ፈትሸው፣ ሻንጣዬን በርብረው ነው የላኩኝ:: ሌሎችንም አፍሪካውያን እንዲሁ ነው ያደረጉት:: ኋላ ላይ ምክንያታቸውን ስረዳ ትላልቅ የሳይንስና የትምህርት መጽሐፎችን ይዘን እንዳንወጣ ነው:: የዕውቀት ባለቤት እነሱ ብቻ እንዲሆኑ ነበር ፍላጎታቸው:: ወደ አፍሪካ የሳይንስ መጽሐፍ እንዳይገባ በብርቱ ይከላከሉ ነበር:: ጠፍረውን ነበር:: ዛሬ ያ የለም:: ዘመኑ ያፈራው ቴክኖሎጂ ሽሮታል:: ኢንተርኔት ሰንሰለታችንን ሰባበረልን:: አሁን ማንኛውም ጎጆ ውስጥ ያለ ኢትዮጵያዊ ኮንግረስ ላይብረሪ ገብቶ እንደልብ መዋኘት ይችላል:: በዚህ ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን አፍሪካዊያንም ነጻ ወጥተዋል:: አውሮፓውያን ምን ያህል ግፈኞች እንደሆኑ ያየሁበት አጋጣሚ ነው:: እንደደነቆርን፣ ሁሌም የእነሱ ጥገኛ ሆነን እንድንቀር፣ ጨለማ ውስጥ እንድንቀር ነበር ፍላጎታቸው፤ አልሆነም:: የሚያሳዝነው ወጣቱ ይህን መልካም ዕድል አልተጠቀመበትም:: ኢንተርኔትን ለቀልድና ለጨዋታ እንጂ ለዕውቀት ምንጭነት አላዋለውም:: ይህ ደግሞ ለእኔ አይነት ሰው ያስቆጫል:: ነጻነቱና በረከቱ ሲሰጠው ህዝባችን አንቀላፍቷል::

 ታዛ ፦ እሺ ከምረቃ በኋላ ወዴት ሄዱ?

ፕሮፌሰር ታደለ፦ እዚያው ሆላንድ ዋርሶ ዩኒቨርሲቲ ልክ ልመረቅ ስል አንድ የአማርኛ ቋንቋና ስነ ጽሑፍ አስተማሪ ትቷቸው ሄደ:: እኔ ተቀጠርኩ:: ቋንቋችንን እንደ ቅንጦት ነበር የሚማሩት:: እዚያ እያስተማርኩ በግሌ መዝገበ ቃላት አዘጋጀሁ:: የፖላንድን ቋንቋ ወደ አማርኛ የሚመልስ:: በዚህም ዩኒቨርሲቲው ከመደሰቱ የተነሳ ቤተሰቦቼ በሙሉ እንዲመጡልኝ አደረገ:: አንለቅም ነው ነገሩ:: ለእነሱም ነጻ ስኮላርሺፕ ተሰጣቸው:: እዚያ በማስተማር ላይ እያለሁ አሜሪካን አገር የሚገኘው አርካንሳ ዩኒቨርሲቲ በተጋባዥ መምህርነት ጠራኝ:: ረዳት ፕሮፌሰር ሆኜ ነው የሄድኩት:: የአፍሪካ ሥነ ጽሑፍን ደስ እያለኝ ለሁለት ዓመት አስተማርኩ:: ከዚያ ደግሞ ዩ ሲ በርክሌይ ዩኒቨርሲቲ ቀጠረኝ:: የከበርቴዎች ትምህርት ቤት ነወ:: ይህንኑ ኮርስ ለሦስት አመት አስተማርኩ:: አፍሪካውያን በቀኝ ግዛት ውስጥ ከመውደቃቸው በፊት የነበራቸውን ስነ ጽሑፍ የሚያስስ (pre‐ colonial literature) ነው:: በጣም ተወደድኩ:: እንዲያውም የተፈጥሮ ፕሮፌሰር (Natural professor) የሚል ቅፅል ስም ሁሉ ሰጡኝ:: የማስተማር ጥበቤን ከመውደዳቸው ባለፈ በአዳራሽ ውስጥ ገኖ የሚወጣ ድምጽ ስላለኝ ነው እንደዚያ ያሉኝ:: ዝግጅቴ ጥብቅ ነው:: ሳስተምር ተመስጠው ነው የሚያዳምጡኝ:: ውጤት ዝም ብዬ አልሰጥም፤ ተማሪዎቼ ሰርተው ለፍተው፣ ቧጠው እንዲማሩ ነው የማደርጋቸው:: በዚያው ልክ ሁሉም ማለት በሚቻል መልኩ ውጤታማ ነበሩ::

ታዛ ፦ በማስተማር ተግባርዎ የኢትዮጵያውያን ተማሪዎችን አቅም ለመገምገም የሚያስችል ዕድል አለዎትና እንዴት ናቸው?

ፕሮፌሰር ታደለ፦ አዎ በተለይ በርክሌይ ዩኒቨርሲቲ ብዙ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ነበሩኝ:: ኢትዮጵያዊ በገባበት ዩኒቨርሲቲ አይወድቅም፤ እስከማውቀው የኛ ሰው በማንኛውም ዩኒቨርሲቲ ተሸንፎ አያውቅም:: ተፈጥሯዊ አቅም ያለው ይመስለኛል:: ይህን ስል አንዳንዶች ሊነቅፉኝ ይችላሉ ብዬ አስባለሁ፤ ግን እውነቱ ይህ ነው:: ድህነቷ እንጂ ኢትዮጵያ ምሁራንን አላጣችም:: አሁን እየታየ ካለው ፖለቲካዊ ለውጥ አኳያ የነገው ወጣት ትውልድ በዕውቀት ኢትዮጵያን ወደ ጥሩ ይለውጣታል ብዬ አምናለሁ::

ታዛ ፦ ከዚያስ ሕይወትዎ ወዴት አመራች ፕሮፌሰር?

ፕሮፌሰር ታደለ፦ በርክሌይ እያስተማርኩ እያለሁ እነዚያ መንትያ ህንጻዎች ወደሙ:: ያኔ ጥቁሩ መግቢያ አጣ:: ነጮች ጠሉት:: ስራ ጠፋ:: በዚያ ምክንያት ማህበረሰቡ «አንድ መረዳጃ ማህበር እናቋቁም» የሚል ጥያቄ አቀረቡልኝ:: ተስማማሁና የመረዳጃ ማህበሩን አቋቁመን ድጋፍ ማድረግ ጀመርን:: አንዳንድ አገልግሎቶች ከቀረጥ ነጻ እንዲሆኑ ማድረግ፣ የተቸገረን መደገፍ፣ ስራ ማስያዝ እና የመሳሰሉትን ተግባራት አከናወንን:: ዘረኝነቱንም ታግለን ወደ ቀደመ አስተሳሰብ ለመመለስ ያደረግነው ጥረት ተሳካ:: በዚህ ሂደት ገንዘብ ያላቸው የናይጄሪያና ጋና ዜጎችም ሊቀላቀሉን ፈለጉ፤ ይሄኔ እኔ እንዲህ አይነት ነገር አልፈልግም ብዬ ተውኩት:: ድርጅቱም ዓላማውን አሳክቷልና ወዲያው ተዘጋ:: ከዚያም ወደ ሂውስተን ተሻገርኩ:: በዚያው ዩኒቨርሲቲ ደግሞ ኮንትራቴን እያደስኩ የአፍሪካ ስነ ጽሑፍን ማስተማሬን ቀጠልኩ:: ጡረታ ወጥቼም ዛሬ ድረስ ሲጠሩኝ እየሄድኩ አስተምራለሁ:: ዛሬ በነጻነት አነባለሁ፣ እጽፋለሁ::

 ታዛ ፦ ከማስተማሩ ባለፈ በውጪ አገር ቆይታዎ ምን መልካም ነገር ሰራሁ ብለው ያስባሉ?

ፕሮፌሰር ታደለ፦ ሂውስተን እያለሁ ውስጤ ብዙ ጊዜ ሲብላላ የነበረን አንድ ታሪክ ሰርቻለሁ:: የመድሃኔዓለም አገልጋይ ዘማሪያንን አስተባብሬ፣ ዶክተር ማሞ ወልዴ የሚባል አንድ አገር ወዳድ ሰው ይዤ የአድዋ ታሪክን የሚያስታውስ ቴያትር አስጠንቼ አሳየሁ:: በህመም ሆስፒታል ውስጥ የገቡ አንዳንዶች ይህን ቴአትር ለማየት የወጡበት ሁኔታ ነበር:: ኢትዮጵያውያን ጀግኖቻችን በማይታወቁበትና ስማቸው በማይጠራበት አገር ይህን ቴያትር መስራት ፈታኝ ነበር፤ ግን ሆነ:: ኢትዮጵያውያን የተደሰቱበት ጊዜ ያ ነበር:: ወጣት ኢትዮጵያውያን እንዲህ አይነት ጀግንነት አለን ለካ የሚል ቁጭትና ወኔ በውስጣቸው እንዲፈጠር ነው ያደረኩት:: ከሌሎች ነገስታት በተሻለ አጼ ምኒልክን በደንብ አውቃቸዋለሁ:: ስለ እሳቸው ብዙ አንብቢያለሁ:: የሚገርምህ ፈረንጆች በተለያዩ ቋንቋዎች የጻፏቸው ወደ 30 መጽሐፎች አሉ:: ስለ ምኒልክ በማንኛውም ነገር ልጽፍ እችላለሁ:: በደግነት፣ አገርን በማስተዳደር፣ ስልጣኔን ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ረገድ እንደ ምኒልክ ማንም የለም:: ይህ ነው ለእኔ ትልቅ ነገር የሰራሁት ሂውስተን ውስጥ:: በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታዩ ሁለት ታሪክ ላይ ያተኮሩ ቴያትሮችን ጽፊያለሁ፤ ከቴያትር ቤቶች እየተነጋገርኩ ነው:: ከተሳካ ሕዝብ ይደሰትባቸዋል ብዬ አስባለሁ::

 ታዛ ፦ ወደ ኢትዮጵያ እንዴት መጡ? ጠቅልለው አገር ቤት የመግባት ዕቅድ የለዎትም?

ፕሮፌሰር ታደለ፦ ቤተሰቦቼን፣ ጓደኞቼን፣ ዘመዶቼን ለመጠየቅ ነው በዋናነት የመጣሁት:: ሌላው ለዘመናት ውስጤ ሲብላላ የኖረውን የውሃ መንገድ አንድ እልባት ላይ ለማድረስ::

ታዛ ፦ በምን መልክ?

ፕሮፌሰር ታደለ፦ ለማሳተም! ዛሬ ሳንሱር የለ…:: ስምጥ ሸለቆንም እንደገና መጎብኘት እፈልጋለሁ:: ከዚህ ስመለስ መጽሐፉን ለመጨረስ ጉልበት አያበጀሁ ነው የምሄደው:: በሚመጣው ዓመት ለማሳተም እመለሳለሁ ብዬ ተነስቻለሁ::

 ታዛ ፦ ግን ይህን መጽሐፍ ለመጻፍ ያነሳሳዎትን ምክንያት እኮ አልነገሩኝም?

ፕሮፌሰር ታደለ፦ «ሪፍት ቫሊ» በሚል ርዕስ አንድ እስራኤላዊ የጻፈው መጽሐፍ ነው:: 39 ገጽ ነች መጽሐፏ:: የኢትዮጵያን ሃይቆችና ስምጥ ሸለቆዎች አካባቢ አጥንቶ የሰራው ድንቅ መጽሐፍ ነው:: በሚሊዮን የሚቆጠር አሳ አርጅቶ እንደሚሞት ይነግረናል:: ያንን ይዘን መራባችንን በቁጭት ይነግረናል:: ኢትዮጵያ ጥሩ የኢኮኖሚ መሰረትና የገበያ ማዕከል ልትሆን እንደምትችልም ያትታል:: ሲሳይ ያላት አገር ይላታል:: ዛሬም ድረስ ያልተለየኝ መጽሐፍ ነው:: 50 ዓመት ሊባል ይቻላል::

ታዛ ፦ ከዚያ የሳንሱር አፈና በኋላ ለማሳተም ደግመው አልሞከሩም? … ዛሬስ እንዳለ ቢታተም ይሆናል ብለው ያስባሉ?

 ፕሮፌሰር ታደለ፦ ከዚያ በኋላ አልሞከርኩም:: ተስፋ ግን አልቆረጥኩም፤ አንድ ቀን እንደማሳትመው እርግጠኛ ነኝ:: ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይጠቅማል ብዬ የማስበውና በዜግነቴ ማበርከት ያለብኝ አንድ ነገር እሱ ነው ብዬ አስባለሁ:: አሁንም ከዘመኑ ሁኔታ፣ ከተፈጥሯዊ ሃብት መቀያየር፣ ከአገራዊ አጠቃላይ ሁኔታዎች አንጻር የሚሻሻሉ ነገሮች እንዳሉ ይታሰበኛል:: ለዚህ ነው ዳግም ጥናት ያስፈለገኝ:: ደግሞም ሳልሞት አሳካዋለሁ::

 ታዛ ፦ መነሻችን ላይ ከሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን ጋር ወዳጅ እንደነበሩ ጠቁመውኛል፤ እስኪ ስለ ማንነታቸውና የስደት ህይወታቸው ይንገሩን? በመጨረሻ ዘመናቸው ላይ ምን ያስቡ፣ ምን ይመኙ እንደነበር የሚያውቁት ካለ ቢያጫውቱን?

ፕሮፌሰር ታደለ፦ ጋሽ ፀጋዬ ገበያ ነው:: ከወደደህም ወደደህ፤ ከጠላህም ጠላህ ነው:: የሚጽፍን ያበረታታል:: ሲናደድ ለሌሎች የምትከብድ አንድ የተለመደች ስድብ አለችው:: አንዳንዴም ቁጡ ነው:: በራሱ የሚተማመን፤ ግን ሰርቶ ያልረካ፣ ጽፎ ያልጠገበ አገር ወዳድ ሰው ነው:: የአፍሪካ ትልልቅ ጸሐፊዎችን ያወቅኩት በእሱ ነው:: ጋሽ ፀጋዬ በስራዎቹ ግዙፍ ነው:: በእኔ እምነት ማንም የሱን ጫማ ማጥለቅ አይቻለውም:: በመጨረሻው ዘመን ላይ እሱ ኒዮርክ እኔ ቴክሳስ ነው የኖርነው:: ማታ ማታ ብዙውን ጊዜ ይደውልልኝ ነበር:: «አንተ እንደኔው ተኝተሃል?! በሰበስን እኮ… እንደው ምኑን ኖርን ይባላል? … የሆነ ነገር እንኳ ጻፍ እስኪ፣ አትተኛ ባክህ» ይለኝ ነበር:: ይህን ሲለኝ እየጻፈ መሆኑ ይሰማኛል:: ምናልባት ወደፊት የሚወጡ ድንቅ ስራዎች ይኖሩት ይሆናል ብዬ አስባለሁ:: መጨረሻ ላይ ወደ ማርጀት መሄዱ እንደሆነ ተሰምቶታል:: በምርኩዝ ነው የሚሄደው፣ ህመሙ አለ፣ ጥበብን ተጠቦ አልጠገበም፣ ከአገሩና ከወገኖቹ ርቆ መኖሩ አልተመቸውም፣ ብቻ ያሳዝን ነበር:: ያንን የመሰለ ግዙፍ የጥበብ አባት በእንዲያ ሁኔታ ማጣታችን ያሳዝናል::

 ታዛ ፦ ወደ አገርዎ የመመለስ እቅድ አለዎት ወይስ…?

 ፕሮፌሰር ታደለ፦ በሦስት ዓመት ውስጥ የመመለስ እቅድ አለኝ:: እዚያ እኮ አይመችም:: ብቸኝነቱ፣ ዘረኝነቱ፣ ባህሉ ለኢትዮጵያውያን የሚመች አልሆነም:: መኖር በሚገባኝ ዘመን ኖሪያለሁ፤ አሁን ያለኝን ሸክፌ ወደ አገሬ ማቅናት ነው:: ልጆቼም አድገው፣ ተምረው ጥሩ ጥሩ ስራ ይዘው መልካም ቦታ ላይ ደርሰውልኛል:: ቀሪ እድሜዬን በነጻነት ማንበብ፣ መጻፍ ላይ ነው ትኩረቴን የማደርገው:: በሕይወቴ ውጤታማ ነኝ ብዬ አስባለሁ::

ታዛ ፦ ቀሪ ዘመንዎ የሰላምና የጤና እንዲሆን፣ በሚወዷት አገርዎ እንዲኖሩም እመኛለሁ::

ፕሮፌሰር ታደለ፦ አመሰግናለሁ፤ እግዚአብሔር ይስጥልኝ::

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top