እነሆ እንደተለመደው ያስተምራሉ፣ ያዝናናሉ፣ ያሳውቃሉ የምንላቸውን ጉዳዮች ይዘን ብቅ ብለናል:: ታሪክ፣ ባህል፣ ኪነ ጥበብና ቅርስ ዋነኛ ትኩረቷን ያደረገችው መጽሔታችን፤ ሌሎች የፍልስፍናና ማህበራዊ ጉዳዮች እንዲሁም ግለ ታሪኮች ላይ የምታነሳቸው ቁምነገሮች ይኖራሉ:: ከአንባቢዎቻችን አስተያየት በመነሳት መጽሔታችን እየተወደደች መምጣቷን እየተረዳን ነው::
እኛም በተቻለ መጠን ደረጃዋን ጠብቃ እንድትዘልቅ ጥረታችንን በሃላፊነት መንፈስ እንቀጥላለን:: የእናንት የአንባቢዎች አስተያየትና ጥቆማ እንዲሁም ተሳትፎ እስካለ ድረስ አብሮነታችን ይዘልቃል::
ውድ አንባቢያን፤ በዚህ 16 ዕትማችን ከመጽሔታችን ባህሪ አንጻር ይመጥናሉ ብለን ያመንባቸውን የተለያዩ ጉዳዮች ይዘን ቀርበናል:: «የባይተዋሩ ልዑል መጨረሻ» በሚል ርዕስ የአጼ ቴዎድሮስ ልጅ ልዑል ዓለማየሁ እንግሊዝ አገር እንዴት ባለ ሁኔታ ኖሮ እንዳለፈ ከዚያው ከእንግሊዝ ነዋሪ የሆኑ ተሳታፊያችን የላኩልንን ታሪክ ይዘናል::
የበዕውቀቱ ስዩም ግጥሞች ባህሪ ላይ ጥልቅ ሃተታ የሚያቀርቡልን ምሁርም አሉ:: የዶክተር እጓለ ማንነት ቀጣይ ታሪክና የላሊበላ ህንጻ ወቅር የታሪክና የሃይማኖት ቅርስ ድንቅ ታሪክ በዚህ እትም ከተካተቱት ወስጥ ይገኛሉ::
በአጭር ልቦለድና ቀልዶችም ዘና ልናረጋችሁ ወደናል:: አስተያየትና ጥቆማችሁ ብርታታችን፣ ተሳፏችሁ አቅማችን ነው:: አብሮነታችን ይቀጥል፤ መልካም ንባብ!
