አድባራተ ጥበብ

ባይተዋሩ የንጉሥ ልጅ መጨረሻ

ከለንደን ከተማ ሰላሳ ማይሎች ወጣ ብላ በተቆረቆረች ዊንድለር እየተባለች በምትጠራ ከተማ የሚገኘው ከጊዮርጊስ ቤተ-ክርስቲያን በስተጀርባ በርከት ያሉ የእንግሊዝ ነገሥታትና በብሪታንያ  ታላቅ ሚና ተጫውተው ያለፉ ሰዎች መቃብር ይገኛሉ፡፡ ይህች ቤተ-ክርስቲያን ማረፊያነቷ ለእነዚሁ ሰዎች ብቻ ሳይሆን ከእንግሊዝ ዘወድ ጋር አግባብ ያለቸውን የሌሎች አገሮችን ነገሥታት መሳፍንትን (በድን ሰውነታቸውን ይሁን እንጂ) እንዳላስተናገደች መቃብሮች ላይ ያሉት ጽሑፎች ራሳቸው ምሥክሮች ናቸው፡፡  በአንድ ትንሽ መቃብር ላይ የተፃፈው ፀሑፍ እንዲህ ይላል፡፡

ባይተዋር እንደነበር ባይተዋር ሆኖ ሞተ፡፡

መስፍኑ ዓለማየሁ ቴድሮስ፤ የንጉሥ ቴድሮስ ልጅ፤ ከታች ዝቅ ይልና #ንግስት ቪክቶሪያ; ይላል፡፡

      ዓለማየሁ ቴድሮስ እንግሊዝ አገር ለጥቂት አመታት ያህል ከኖረ በኋላ ቢሞትም፤ የእሱ ጉዳይ ግን በእንግሊዝ ፓርላማ በመንግሥቱና በእንግሊዝ ዘውድ መካከል ከፍተኛ ጭቅጭቅ የፈጠረና በተለይም በእንግሊዝ መንግሥትና በዘውዱ መካከል እስከመቼውም ጊዜ የማይጠፋ መቃቃር ያደረሰ መሆኑን በአሁኑ ጊዜ ማለትም ድርጊቱ ከተፈፀመ ከመቶ ዓመታት በኋላ ለህዝብ እንዲታዩ የተፈቀዱ ፋይሎችና ዶሴዎች ይጠቁማሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን ስነ-ልቦና ግን ዓለማየሁ እንግሊዝ አገር ከደረሰ በኋላ ብዙ ሳይቆይ መርዝ አቅምሰውት ሞተ ከሚል በማስረጃ ያልተደገፈ ጭምጭምታ በስተቀር ምንም የሚታወቅ ነገር እስካሁን የለም፡፡ የታሪክ ሙህራንም ቢሆኑ፤ የዓለማየሁን ጉዳይ በሚመለከት ለውይይት፣ ለጥናት በአጀንዳቸው ላይ ያቀረቡት ሃሳብ የለም፡፡ ዓለማየሁ ከኢትዮጵያ መቼና እንዴት ወጣ? ከእናቱ ከእቴጌ ጥሩነሽ ጋር እንዴት ተለያዩ? ከአገሩ ሲወጣ የስንት ዓመት ልጅ ነበር? እንግሊዝ አገር በነበረበት ወቅት በሞግዚትነት ያሳደጉት ማን ነበሩ? ውጭ አገር በነበረበት ጊዜ ከዘመዶቹ ጋር በደብዳቤ ይገናኝ ነበረ ወይ? የእንግሊዝ አገር አፈርን ከረገጠበት ጊዜ አንስቶ እስከ ዕለተ-ሞቱ ድረስ ምን ዓይነት አኗኗር ይኖር ነበር? የእንግሊዝ ዘውድ በተለይም ንግስት ቪክቶሪያ ስለ ዓለማየሁ የነበራቸው አመለካከት ምን ነበረ? የሚሉና ተመሳሳይ ጥያቄዎች በቡዙዎቻችን አእምሮ ውስጥ ይጉላላል፡፡

እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ያህል እንሞክራለን፡፡

       ታሪኩ በመቅደላ መወረር ይጀምራል፡፡ በጄኔራል ናፒዮር የሚመራው የእንግሊዝ ጦር መቅደላንና ምሽጎቿን ከወረረ በኋላ፤ በጄኔራል ናፒር የሚመራው የእግሊዝ ጦር አጼ ቴዎድሮስ ለብዙ ወራት እንዲያዋጋቸው ብለው ለሰራዊቱ ያዘጋጁትን ሥንቅ ተረባረበበት፡፡ በሴቶች ላይ ከፍተኛ ድፍረት ተፈፀመ፡፡ ይህ ግርግር ይካሄድ በነበረበት ወቅት ነበር፤ እቴጌ ጥሩነሽ ከዓለማዮሁ ጋር ተደብቀውበት ከነበሩ ምሽግ ወጣ ብለው፤ በአንክሮና በሀዘን ስሜት ሠለጠነ በተባለ የአውሮፓ ሰራዊት ይካሄድ የነበረውን ተራ ብልግናና ወራዳነት ይታዘቡ ነበር፡፡ እሳቸውም ቢሆን ማንነታቸውን እስኪታወቅ ድረስ ከመለስተኛ እንግልት አልዳኑም፡፡ በመጨረሻ ግን ታስረው ከነበሩት እንግሊዛውያን አንዱ ለጄነራል ናፒዮር የቴዎድሮስ ሚስት መሆናቸውን ገልፆ፤ ጄነራሉ በቀጥታ የግል ኃላፊነቱን ወስዶ ለአለማዮሁና ለእቴጌ ጥሩነሽ የሚያስፈልገውን እንክብካቤ አደረገላቸው፡፡ በጊዜው ወረራውን ከፈፀሙት የእንግሊዝ የጦር መኮንኖች አንዱ ለእቴጌ ጥሩነሽ እንዲህ ሲል ጽፏል፡፡

     ዕድሜዋ በግምት 25 ዓመት ይሆናታል፡፡ ጠይም ቆንጆ  ረጅም ፀጉርና ግሩም ተክለ ሰውነት ያላት ለጋ ወጣት ስትሆን የንጉሥ ሚስት ለመሆኗ፤ እሷ ወይም ደንገጥሯ ሳይሆኑ ልዕልታዊ ሰውነቷ ራሱ ይመሰክራል ” ይላል፡፡

       ዘ-ታይምስ እየተባለ የሚጠራው የታዋቂው ጋዜጣ ቃል አቀባይም የእቴጌ ጥሩነሽን ቁንጅና ካደነቀ በኋላ፤ ለአፍሪካና ለህዝቦቿ የተዛባ ዕውቀት የነበረው መሆኑን እንዲያምን ያደረገውን መሆኑን አትቶ ጽፏል፡፡

       ጄኔራል ናፒር የአጼ ቴዎድሮስን ሬሳ ከአስመረመረና፤ ራሳቸውን የገደሉ መሆናቸውን ከአረጋገጠ በኋላ ቤተ-ሰቦቻቸው በተገኙበት በመድኃኔዓለም ቤተ-ክርስቲያን እንዲቀበሩ የሚያስፈልገውን ዝግጅት ሁሉ አደረገ፡፡ የቀብሩ ሥነ-ሥርዓት ከተፈፀመ በኋላ ጄኔራሉ እቴጌ ጥሩነሽንና ልጃቸውን ልኡል ዓለማዮህን ወደ እንግሊዝ አገር ይዞ ለመመለስ የሚያስፈልገውን ሁሉ ማድረግ ጀመሩ፡፡ ዓለማየሁ ሌላ ሞግዚት ያስፈልገዋል ብሎ በማመኑም በጊዜው አማርኛ ይናገር የነበረው የሰራዊቱ አባል ሻለቃ እስፒዲ ይህንኑ ኃላፊነት እንዲወስድ አደረገ፡፡ በዓለማየሁ፣ በእናቱና በሻለቃ እስፒዲ መካከልም ጥሩ ወዳጅነት እየተፈጠረ መጣ፡፡ በተለይም በሻለቃ እስፒዲና በዓለማየሁ መካከል የነበረው መግባባት የአባትና የልጅ ስሜት ያስገረመው እናቱንና ጄኔራሉን ብቻ ሳይሆን መላውን የእንግሊዝ ወራሪ ጦር ነበር፡፡

       ጉዟቸውን ጀምረው አርማጭሆ እንደደረሱ፤ እቴጌ ጥሩነሽ በጠና ታመሙ፡፡ በእቴጌዋ መታመም ምክኒያት የእንግሊዝ ሰራዊት ለሁለት ሳምንታት ያህል የትም ቦታ መንቀሳቀስ አልቻለም ነበር፡፡ ከሁለት ሳምንት በኋላ እቴጌ ጥሩነሽ ታመው ባረፉበት ቦታ ሆነው ጄኔራል ናፔርን አስጠርተው እንዲህ አሉት፡፡

      እኔ ከእንግዲህ መሞቴ ነው፡፡ የዓለማየሁን ነገር አደራ፡፡ አባቱ ከመሞታቸው በፊት እንግሊዝ ሀገር ሄዶ እንዲማር ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበራቸው ደጃዝማች ዓለማየሁን ውሰዱና አስተምራችሁ ወደ አገሩ ላኩልን፡፡ ውለታችሁን ግን አምላክ በሰማይ ቤት ይክፈላችሁ ” ብለው ከተናዘዙ ከሁለት ቀናት በኋላ አረፉ፡፡

      ጄኔራል ናፒርም በጊዜው ለአንዲት ንግሥት የሚሰጠውን የክብር ቀብር ሥነ-ስርዓት ካስፈፀመ በኋላ፤ አለማየሁንና ሌሎችን ይዘው ጉዟቸው ወደ ፖርት ሱዳን ቀጠሉ፡፡ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ሰኔ 11 ቀን 1868 ዓ.ም ፌሮዝ እየተባለች በምትጠራ የእንግሊዝ የጦር መርከብ ወደ እንግሊዝ አገር ለመመለስ ከፖርት ሱዳን ለቀቁ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ዓለማየሁ ምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እንደነበር የሚገልፅ አንዳችም ነገር የለም፡፡ በጊዜው መርከቡ ላይ ከነበሩት ወታደሮች አንዱ ማስታወሻው ላይ በፃፈው ግን ስለ ዓለማየሁ እንዲህ ይላል፤

    ቁመቱ አራት ጫማ ከአራት ኢንች ይሆናል፡፡ ዕድሜው በግምት 9 ዓመት ሲሆነው፤ በዚህ ሁለትና ሦስት ወራት ያሳለፈውን አሰቃቂ ጊዜ፤ ማለትም የሀገሩን መወረር፣ የአባቱ ራሳቸውን መግደልና የእናቱ በድንገት በጉዞ ላይ እንዳሉ ጥለውት ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን የመቻሉ የመንፈስ ጥንካሬ ግን የወጣት ዕድሜውን የካደ ይመስላል ይላል፡፡

     ከአንድ ወር ጉዞ በኋላ ዓለማየሁ ከሻለቃ እስፒዲ ጋር ሆነው እንግሊዝ አገር ገቡ፡፡ የዓለማየሁ እንግሊዝ አገር መምጣት እንደተሰማ ንግሥት ቪክቶሪያ ቤተ-መንግሥታቸው እንዲመጣ አዘዙ፡፡ ሻለቃ እስፒዲ ዓለማየሁን ይዞ ወደ ዊንድለር ቤተ-መንግሥት ሄደ፡፡ ንግሥቲቱ ዓለማየሁን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያዩት የተሰማቸውን ስሜት እንዲህ ሲሉ ፃፉ፡፡

     እዚው በጋ ነበር፡፡ ውድ ዓለማየሁ፤ የአጼ ቴዎድሮስ ልጅ የሚያጌጡ የአቪሲኒያ ልብሶችን ለብሶ ከሻለቃ እስፒዲ ጋር ብቅ አሉ፡፡ ከፍ ያለ ደስታ ተሰማኝ፡፡ ቀረብ ብየ አቀፍኩት፡፡ ሁልጊዜ ስለ አባቱ የምንሰማው ቁጣ ግን ከፊቱ አይነበብም፡፡ በጣም አይነአፋር ሆኖ አገኘሁት፡፡ በእንግሊዝኛም ትንሽ አነጋገርኩት ” አሉ፡፡

     ንግሥት ቪክቶሪያ በጋውን ሙሉ ዓለማየሁንና ሻለቃ እስፒድን እያስጠኑ ያዩአቸው ነበር፡፡ ሻለቃ እስፒዲም ተመድቦ ይሰራ ወደነበረበት ህንድ አገር የሚገኘው የእንግሊዝ ሰራዊት ከመሄድ ይልቅ፤ ለአለማየሁ አንድ ስምምነት እስኪደርስ፤ ቀደም ሲል ይኖር በነበረበት ፍረሽ ወተር እየተባለች በምትጠራው ከተማ እየኖረ፤  በሞግዚትነት እንዲያሳድገውና እንዲያስተምረው ተወሰነ፡፡ ንግስት ቪክቶሪያም ዓለማየሁ በጊዜው ስለሚያደርገው መሻሻል ስለ ትምህርቱና ስለ ጤንነቱ ጉዳይ ማወቅ የሚፈልጉ መሆናቸውን ለሻለቃ እስፒዲ ገልፀውለት ሻለቃው በተሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ስለ አለማየሁ ጉዳይ ከቤተ-መንግሥቱ ጋር የሚያደርገውን የደብዳቤ ልውውጥ ጀመረ፡፡ ለምሳሌም በጥቅምት ወር 1868 ዓ.ም ሻለቃ እስፒዲ ዓለማየሁ ስለአደረገው መሻሻል ጠቅሶ ለንግስት ቪክቶሪያ እንዲህ ብሎ ፅፏል፡፡

    አስቀድሜ መልካም ሰላምታየን አቀርባለሁ፡፡ የዓለማየሁ ቴድሮስ ጤንነት በደንብ ይጠበቃል፡፡ ፍረሽ ወተር ከተማ የሚገኘው ቤቴ ባህርዳር ላይ በመሆኑ ዓለማየሁን ዋና የማስተማሩን ሥራዮን በጣም አቅልሎታል፡፡ አይን አፋርነቱ ወደ ድፍረት ተለውጧል፡፡ የእንግሊዝኛ ንግግር ችሎታው በጣም ተሻሽሏል፡፡ በዕውቀቱ በእሱ ዕድሜ ክልል ውስጥ ካሉት የእኛ ልጆች ከፍ እንጂ ዝቅ አይልም ” ይላል፡፡

     ታህሳስ ወር ላይ ሻለቃ እስፒዲ ወይዘሪት ኮታም የምትባል ሴት አገባ፡፡ ዓለማየሁ እንደ እናቱ የሚያያት ሴት በማግኝቱ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ደስ አለው፡፡ ባልና ሚስቱ በሚሄዱበት ቦታ ሁሉ ዓለማየሁን ከአጠገባቸው አይለዩትም ነበር፡፡ ሻለቃ እስፒዲ ካገባ በኋላም ዓለማየሁን ወደ ንግሥት ቪክቶሪያ እየወሰደ አብረው እጅ መንሳት ቀጠሉ፡፡

       የካቲት 15 ቀን 1869 ዓ.ም ዓለማየሁና ሻለቃ እስፒዲ ንግሥት ቪክቶሪያን ለማየት በሄዱበት ጊዜ ነበር በሻለቃ እስፒዲ ሚስት ማግባት የተደሰቱ መሆኑን፣ ዓለማየሁ ለንግሥቲቱ የገለፀላቸው ይህንን አስመልክተው ንግሥት ቪክቶሪያ በጻፉት ማስታወሻ፤

    “  ምሳ ከመብላታችን በፊት ነበር፤ ዓለማየሁና ሻለቃ እስፒዲ ብቅ ያሉት፡፡ ልጅ ዓለማየሁ ቆንጆ ልጅ ሆኗል፡፡ አድጓል፡፡ ጥሩ እናት ማግኝቱንና ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ደስተኛ መሆኑን ሻለቃ እስፒዲ እንዳይሰማ ብሎ ወደ ጆሮዬ ተጠግቶ ነገረኝ፡፡ እኔም በጣም ተደሰትኩ ” ብለዋል፡፡

      ባልና ሚስቱ ዓለማየሁን ይዘው በዚህ ዓይነት ሲኖሩ ከቆዩ በኋላ በሐምሌ ወር ሻለቃ እስፒዲ የሲታፑር ወረዳ ፖሊስ ኮሚሽን ሆኖ ተሽሞ ወደ ህንድ አገር በአስቸኳይ እንዲዳረስ የጥሪ ደብዳቤ ደረሰው፡፡ ለዓለማየሁ ማሳደጊያ ይከፍለው ከነበረው 7300 አበል ላይ ተጨማሪ 400 በየዓመቱ እያገኘና ዓለማየሁን በሞግዚትነት እንዲይዝ ተወስኖ ሐምሌ 14 ቀን 1869 ዓ.ም ሚስቱንና ዓለማየሁን ይዞ ወደ ህንድ አገር ሄደ፡፡ ሻለቃ እስፒዲ ህንድ አገር ሆኖ ከንግሥት ቪክቶሪያ ጋር ያደርግ የነበረውን የደብዳቤ ልውውጥ ቀጠለ፡፡ ከዘጠኝ ወራት በኋላ ለንግሥቲቱ የጻፈው ደብዳቤ፤

     #በመጀመሪያ መልካም ጤንነትዎን እየተመኘሁ በአሁኑ ጊዜ ዓለማየሁ ከበፊቱ በተሻለ የጤንነት ሁኔታ እንደሚገኝ ላበስርዎ እፈልጋለሁ፡፡ አገር ቤት በነበርንበት ጊዜ ካስተማርኩት ውሃ ዋና ሌላ ፈረስ መጋለብ ተምሯል፡፡ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታው ከምንጊዜውም የበለጠ ተሻሽሏል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጀምሮ ግን አንድ መጥፎ ጠባይ አይቼበታለሁ፡፡ ይሄውም እውነትን መደበቅ መጀመሩን ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከብዙ ማውጣጣት በኋላ ዕውነትን እንዲነግረኝ አደርገዋለሁ፡፡ በተረፈ ግን አጀማመሩ ተስፋ የሚሰጥ እንጂ የሚያስቆርጥ አይደለም; የሚል ነበር፡፡

       ዓለማየሁ ቴዎድሮስ ከሻለቃ እስፒዲ ጋር ህንድ አገር ይኖርበት በነበረበት ጊዜ፤ የእሱን የወደፊት ህይወት በሚመለከት ከቤተ-መንግሥትና ከከፍተኛ የመንግሥት ባለ ሥልጣናት የተለያዩ ሀሳቦች ይሰነዘሩ ነበር፡፡ ትምህርቱን ህንድ አገር ይቀጥል ወይንስ ወደ እንግሊዝ አገር ይመለስ? ከሻለቃ እስፒዲ ጋር ይቆይ ወይንስ ሌላ ሞግዚት ይፈለግለት? የሚሉት ጥያቄዎች የዓለማየሁ ጉዳይ ከሚመለከታቸው ግለ-ሰቦችና መስሪያቤቶች ይነሱ ጀመር፡፡ ንግሥት ቪክቶሪያ ግን የዓለማየሁ ህንድ ሀገር መቀመጥ ሳይሆን ከሻለቃ እስፒዲ በደስታ አብሮ መኖሩን ብቻ ነበር ትልቅ ቦታ የሰጡት፡፡

       የሻለቃ እስፒዲ ሞግዚትነት ከመጀመሪያ ጀምሮ ያልተቀበለው፤ በኋላም ዓለማየሁን ከሻለቃ እስፒዲ ጋር ህንድ አገር መላኩን የተቃወመው፤ በዚሁ በሥልጣን ላይ የነበረው የእንግሊዝ ሊብራል መንግሥት የገንዘብ ሚኒስቴር ሮበርት ላው ነበር፡፡ በመንግሥት በኩል ዓለማየሁን የሚመለከቱ ጉዳዮች ተጠያቂው እሱ ስለነበር፤ ከሻለቃ እስፒዲ ሆነ ከንግሥት ቪክቶሪያ ብዙ የደብዳቤ ልውውጦችን አድርጓል፡፡ የዓለማየሁን የወደፊት ህይወቱን አስመልክቶ ከሰነዘራቸው ሀሳቦች የመጀመሪያው ዓለማየሁን ወደ እንግሊዝ አገር መመለስ እንዳለበት ሁለተኛ ከዚያ እንደተመለሰ ሳንደርስት እየተባለ ወደ ሚጠራው የታወቀ የእንግሊዝ ጦር አካዳሚ እንዲገባ፤ አለበለዚያም ደባል ትምህርት ቤት ተፈልጎለት ትምህርቱን እንግሊዝ አገር እንዲቀጥል የሚሉ ነበሩ፡፡ ለምሳሌም ዓለማየሁን እንግሊዝ አገር የመመለስ አስፈላጊነት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ለግላድስተን፤ ታኅሳስ 18 ቀን፣ 1870 ዓ.ም ላይ በጻፈው ረጅም ደብዳቤ እንዲህ ይላል፤

ጠቅላይ ሚንስትር ግላድስተን

10 ዳውኒንግ መንገድ

ለንደን፤

      በመጀመሪያ የጠቅላይ ሚንስትሩን ጤንነት እየተመኘሁ ስለ ዓለማየሁ ጉዳይ ይህንን መጻፍ ተገድጃለሁ፡፡

      በአሁኑ ሰዓት ግልጽ ሊሆንልን የሚገባው ነገር ቢኖር ዓለማየሁን በሞግዚትነት የተረከቡትት ሻለቃ እስፒዲ እና ሚስቱ ሳይሆኑ መላው የእንግሊዝ ህዝብ ነው፡፡ ስለ ዓለማየሁ የወደፊት ህይወት እነ ሻለቃ እስፒዲ ከሚሰጡን ሃሳብ ወጣ ብለን መንግሥታችን ዘላቂ መፍትሄ ማግኝት ያለበት ይመስለኛል፡፡ በመጀመሪያ ዓለማየሁን ከህንድ አገር ማስመጣት ቅድሚያ መስጠት ይኖርብናል፡፡ ለወደፊት በአብሲኒያ ፖለቲካ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፤ የእኛ መንግሥት ጥሩ ጓደኛ እና ጥቅም አጥባቂ ይሆናል ብለን የምንጠብቀው ዙፋን ወራሽ ስለሆነ እንደ ህንድ በመሰለ በበሽታ፣ በድንቁርናና ኋላቀርነት የፍጥኝ ባሰረው ህብረተሰብ መካከል መቆየቱ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ አሁንም ቢሆን እስካሁን ድረስ እዛው እንዲቆይ በመደረጉ በጣም አዝናለሁ፡፡ በአስቸኳይ ወደ እንግሊዝ አገር እንዲመጣ ካልተደረገ ግን መጀመሪያውኑ ዓለማየሁን ለማሳደግና ለማስተማር ከአገሩ ማስወጣቱ ቁምነገር አልነበረውም ማለት ነው፡፡ ሻለቃ እስፒዲና ሚስቱ አንዳንዴ የሚናገሩትንና የሚያደርጉትን አያውቁትም፡፡ እኔ እርስዎን ቢሆን ባልና ሚስቱ የሚሉትን አልሰማም፡፡ የዓለማየሁ ከእነሱ ጋር መቆየት ከራሳቸው የኢኮኖሚ ጥቅም ጋር የተገናኘ በመሆኑ፤ መቼውንም ቢሆን ዕውቀትንና ለዓለማየሁ የሚበጀውን ነገር መናገር አይፈልጉም፡፡ ዓለማየሁ ከእንግሊዝ አገር እንደተመለሰ የሚገባበት ትምህርት ቤት አዘጋጅቼለታለሁ፡፡ ብራይተን የሚገኘው የቸልተናም ኮሌጅ ርዕሰ መምህር የሆነው ጃክስ ብሌክ በራሱ የግል ቤት አስቀምጦ እንዲያስተምረው ተስማምቶናል፡፡ ጂክስ ብሌክ ዘጠኝ ሴት ልጆች ስላሉት መቼውንም ቢሆን ዓለማየሁ ብቸኝነት አይሰማውም ብየ አምናለሁ፡፡ ዓለማየሁን ይሄንን የምንኮራበት የበለፀገ ባህላችንን የምናስተምርበት ከዚህ የበለጠ የሚያጋጥመን አይመስለኝም፡፡ ከዚህ በተረፈ ግን የርስዎን ትዕዛዝ ለመፈፀም ዝግጁ ነኝ፡፡

ታዛዥዎ

ሮበርት ላው

ግልባጭ

ንግሥት ቪክቶሪያ

ዊንድለር ቤተ-መንግሥት

ዊንድለር

     ንግሥት ቪክቶሪያ ይህ ደብዳቤ እንደደረሳቸው በጣም ተቆጡ፡፡ የገንዘብ ሚንስትሩ ያሳሰበው ለዓለማየሁ ማሳደጊያ ተብሎ የሚከፈለው ገንዘብ እንደሆነ እሳቸው ራሳቸው ገንዘቡን ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን፤ በተረፈ ግን ዓለማየሁ ወደ እንግሊዝ አገር መመለስ አለበት ተብሎ ከተወሰነ፤ የእንግሊዝ አገር የአየር ጠባይ የሚስማማው መሆኑንና አለመሆኑን የራሳቸው ዶክተር ዓለማየሁን መርምሮ ሪፖርት ማድረግ ይኖርበታል፤ የሚል ደብዳቤ አስፅፈው ለጠቅላይ ሚንስትሩ ላኩ፡፡

     በቤተ-መንግሥቱና በጠቅላይ ሚንስትር ጽህፈት ቤት መካከል ይህ ዓይነት ጭቅጭቅና አለመግባባት መኖሩን ያላወቀው ሻለቃ እስፒዲ ግን ስለ ዓለማየሁ የወደፊት ኑሮ ብዙ ነገሮችን ያወጣ እና ያወርድ ነበር፡፡ ለምሳሌ ለንግሥት ቪክቶሪያ በጻፈው ደብዳቤ የዓለማየሁን መልካም ጤንነት ጠቅሶ፤ ዓለማየሁን ለማስተማር ግን ጥሩ ትምህርት ቤት ለማግኝት አለመቻሉን፤ ምናልባምትም ንግሥቲቱ የሚችሉ ከሆነ፤ እሱ ወደ እንግሊዝ አገር ተመልሶ መጥቶ ዓለማየሁን እያስተማረ እንዲቀመጥ እንዲረዱት በመንግሥት ላይ የሚፈለገውን ያህል ተጽዕኖ እንዲያደርጉ ጽፎላቸዋል፡፡

     ይህ በእንዲህ ላይ እንዳለ በ1871 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ ሻለቃ እስፒዲ ህንድ አገር ይሰራበት የነበረበትን ቦታ ለቆ በጊዜው ሌላ የእንግሊዝ የቅኝ ግዛት ወደነበረችው #ፔናንግ; እየተባለች ወደምትጠራ የማሌዥያ ከተማ እንዲሄድ ደብዳቤ ደረሰው፡፡ ይህ ያልታሰበ ውሳኔ ለገንዘብ ሚንስትሩ ለሮበርት ላው፤ አለማየሁን ከሻለቃ እስፒዲ እጅ ለመንጠቅ ጥሩ አጋጣሚ ፈጠረለት፡፡ ሚንስትሩ ሻለቃ እስፒዲ ህንድ አገርን ለቆ ወደ ማሌዥያ እንዲሄድ መወሰኑን እንዲሰማ እንዲህ ብሎ ጻፈ፡፡

    #የዓለማየሁን የወደፊት ህይወት በሚመለከት ቋሚ መመሪያ ሊኖረን ይገባል፡፡ ይህ ሚስክን ልጅ አጋጣሚ ሆኖ መጀመሪያ በአንድ ወታደር እጅ በመውደቁ እሱ ዛሬ አፍሪካ፣ ነገ ህንድ አገር፣ ከነገ ወዲያ ቻይና ይሄድ ተብሎ በተወሰነ ቁጥር ልጁ አብሮ መንገላታት የለበትም፡፡ በአሁኑ ሰዓት ሻለቃ እስፒዲ ወደ ፒናንግ እንዲሄድ በመታዘዙ፤ ቀደም ሲል ዓለማየሁን እንዲያስተምር ያደረግነውን ስምምነት እዚህ ላይ ለማስቆም ወስኛለሁ፡፡ በተረፈ ግን ሻለቃ እስፒዲ በአስቸኳይ ዓለማየሁን ወደ እንግሊዝ አገር አምጥቶ ለርዕሰ መምህሩ ለጃክስ ብሌክ እንዲያስረክብ አስፈላጊውን ትዕዛዝ ሰጥቻለሁ; ይላል፡፡

     ሻለቃ እስፒዲ የዓለማየሁን የሞግዚትነት ጊዜ ቆጥሮ፤ ስለ ሁኔታው ለመነጋገር ከዓለማየሁና ከባለቤቱ ጋር እንግሊዝ አገር ገቡ፡፡  ንግሥት ቪክቶሪያ ስለ አዓለማየሁ ትምህርትና ሞግዚትነት ጉዳይ ምን እንደተወሰነና ለጂክስ ብሌክ ዓለማየሁን ከመስጠቱ በፊት ግን እንግሊዝ አገር እንደደረሱ እሳቸውን ለማየት ወደ ዊንድለር ቤተ-መንግሥት እንዲሄዱ የጋበዟቸው ደብዳቤ ለሻለቃ እስፒዲ ባለመድረሱ ሻለቃ እስፒዲ ቤተ-ሰባቸውን ይዘው ፍረሽ ወተር ወደ ምትባለው የመኖሪያ ከተማቸው ጉዟቸውን ቀጠሉ፡፡

     የሻለቃ እስፒዲ እና የአለማየሁ እንግሊዝ አገር መግባት እንደተሰማ ሮበርት ላው ዓለማየሁን በአስቸኳይ ለጂክስ ብሌክ እንዲያስረክብ ለሻለቃ እስፒዲ መልዕክተኛ ላከበት፡፡ ሻለቃ እስፒዲም፤ #እኔ እንግሊዝ አገር የመጣሁት ኮንትራቱን ለማደስ እንጂ፤ ለማላውቀው ሰው ያሳደግኩትን ልጄን ልሰጥ አይደለም; ብሎ እምቢ አለ፡፡ ሻለቃ እስፒዲ እሱ በሌለበት ሚኒስትሩ በሰራው ሥራ በማዘን በማስታወሻው ላይ የጻፈው፤

     ይሄን ያህል ጊዜ ከእኔ ጋር የኖረውን አንዱ ልጄ አድርጌ የማየውን ዓለማየሁን ከእኔ ነጥቃችሁ ለማላውቀውና ለማያውቀው ሰው ለመስጠት ስትወስኑ እንዴት እኔን አላማከራችሁኝም? ለመሆኑ ዓለማየሁ እዚች ምድር ላይ ከሚኖሩት ሰዎች ውስጥ እንደ እኔ የበለጠ የሚቀርበው ሰው ልትጠሩልኝ ትችላላችሁ? አሁንም ቢሆን የዓለማየሁ የመንፈሱ ሆነ የሰውነቱ ጥንካሬ ትልቅ ትምህርት ቤት ገብቶ ከማያውቃቸው ልጆችና አዲስ ሞግዚቶች ጋር ሆኖ እንዲማር ስለማይፈቅድለት ውሳኔያችሁን እንድትለውጡ  እማፀናችኋለው! ይላል፡፡

      የገንዘብ ሚንስትሩ ሮበርት ላው ለሻለቃ እስፒዲ ዓለማየሁን ለጂክስ ብሌክ እንዲሰጥ በተደጋጋሚ ቢጽፍለትና መልዕክተኛ ቢልክለት እምቢ ስላለው ግልባጩን ለንግሥት ቪክቶሪያ አድርጎ ከዚህ የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ ጻፈ፡፡

      መንግሥት ከህንድ አገር ወደዚህ እንድትመለስ ያደረገበት ምክኒያት ዓለማየሁን ይዘህ እንድትመጣና ወደ ብራይተን ሄደህ ለጂክስ ብሌክ ዓለማየሁን እንድትሰጥ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት በአዘዘህ መሠረት ዓለማየሁን የምታስረክብ እንደሆን አስረክብ፤ አላስረክብም የምትል ከሆነ ግን፤ ከእንግዲህ ወዲህ እኔም ሆነ በእኔ ሥር ያሉ ሠራተኞች ከአንተ ጋር ምንም ዓይነት የደብዳቤ ልውውጥ የማናደርግ መሆናችንን እያሳወቅንህ፤ ለዓለማየሁ ማሳደጊያና ማስተማሪያ ተብሎ ከመንግሥት ካዝና እየወጣ የሚሰጥህ አበል የሚቆም መሆኑን እንድታውቅ! ከዛሬ ጀምሮ ዓለማየሁን በሚመለከት ለሚፈጠረው ችግር ተጠያቂው ራስህ ነህ ” የሚል ዛቻ የተሞላበት ደብዳቤ ጻፈ፡፡

      የዚህ ደብዳቤ ግልባጭ ለንግስቲቱ እንደደረሳቸው፤ ጸሐፊያቸው በአስቸኳይ ለሻለቃ እስፒዲ ቴሌግራም ላከበት፡፡ ቴሌግራሙ የሚለው ሻለቃ እስፒዲ ዓለማየሁን ይዞ ወደ ብራይተን ሄዶ ጂክስ ብሌክ ጋር ጥሎት እንዳይመጣ ነው፡፡ ከመሄዳቸው በፊት ግን ሻለቃ እስፒዲ ዓለማየሁን ይዞ ወደ ዊንድለር ቤተ-መንግሥት እንዲመጣላቸው ጠየቁት፡፡ በተባለው ቀን ማለትም ጥር 23 ቀን፣ 1872 ዓ.ም ንግሥት ቪክቶሪያን ለማየት ሻለቃ እስፒዲ እና ዓለማየሁ ወደ ዊንድለር ቤተ-መንግሥት ሄዱ፡፡ ንግሥት ቪክቶሪያ ሁለቱን ካስተናገዱ በኋላ ዓለማየሁን በራሳቸው ዶክተር አስመረመሩ፡፡ ዶክተሩ ዓለማየሁን ከመረመረ በኋላ ለሁለት ዓመታት ያህል በሞቃት አገር ቢቆይ መልካም መሆኑን፤ ካልተቻለ ግን ባለው ሁኔታም ቢሆን ትምህርቱን በተጠቀሰው በብራይተን ከተማ መከታተል እንደሚችል ነገራቸው፡፡ ዶክተሩ ስለ ዓለማየሁ ባቀረበው ተጨማሪ ሪፖርት፤ ዓለማየሁ አሁን ባለው ሁኔታ ትልቅ ትምህርት ቤት ገብቶ ለመማር ዝግጁ ያለመሆኑን ጠቅሶ የሻለቃ እስፒዲ በአከባቢው መኖሩን አለበለዚያ የግል አስተማሪ ተቀጥሮለት፤ ግን የሻለቃ እስፒዲ እና ሚስቲቱ በየእረፍት ጊዚያቸው እየሄዱ እንዲጎበኙት መልካም መሆኑን ጠቁሟል፡፡

      ከብዙ ወራት ጭቅጭቅ በኋላ ዓለማየሁ ከጂክስ ብሌክ ጋር ሆኖ እንዲማር፤ የሻለቃ እስፒዲ ሚስትም በየጊዜው እየሄደች እንድትጠይቀው የዓለማየሁን የየዕለት ትምህርት መሻሻልና የጤና ሁኔታ ጂክስ ብሌክ ለንግሥት ቪክቶሪያ ሪፖርት እንዲያደርግ ስምምነት ተደረሰ፡፡ ሻለቃ እስፒዲም በስምምነቱ መሠረት መጋቢት 4 ቀን 1872 ዓ.ም ዓለማየሁን ለጂክስ ብሌክ አስረከበ፡፡ ንግሥት ቪክቶሪያ አማራጭ ስለሌላቸው ብቻ ሞግዚትነቱን መቀበላቸውን በደንብ ያላጤነው ጂክስ ብሌክ ስለ ዓለማየሁ የተሰማውን የመጀመሪያ ስሜት እንዲህ ሲል ለንግሥቲቱ ጻፈ፡፡

     በመጀመሪያ የንግሥትነትዎ ፈቃድ ዓለማየሁን እንደ አባትና አስተማሪው ሆኜ እንድይዘው አደራ ስለጣሉብኝ የተሰማኝን ክብር ከፍተኛ መሆኑን ልገልጽልዎ እወዳለሁ፡፡ ዓለማየሁ ከእኔ ጋር ባሳለፋቸው ጥቂት ሳምንታት ውስጥ በቅርብ መገንዘብ የቻልኩት ነገር ቢኖር፤ እንደዚያ ጨካኝና ቁጡ ነው እየተባለ ከምንሰማው አባቱ የወረሰው አንዳችም ጠባይ አለማየቴ ነው፡፡ ልኡላዊ አስተዳደጉ በጣም የሚያስገርም ነው፡፡ ለመጽሐፍት ያለው ክብር ይህን ያህል ባያስቀናም፤ የእግር ኳስና ፈረስ መጋለብ መውደዱ ጨርሶ ተስፋ የሚያስቆርጥ አይደለም፡፡ በመጨረሻ ግን ንግሥትነትዎን ላሳስብዎ የምፈልገው ይሄንን የተጣለብኝን ከባድ ኃላፊነት መወጣት የምችለው ሌሎች ሰዎች ማለትም ሻለቃ እስፒዲና ሚስቱ በእኔና በአለማየሁ መካከል ጣልቃ እስካልገቡ ድረስ ነው ” ይላል፡፡

     ጂክስ ብሌክ ከገንዘብ ሚኒስትሩ ጋር ባደረጋቸው የደብዳቤ ልውውጦችም ቢሆን፤ ከእስፒዲ ቤተ-ሰብ ጉብኝት አለመደሰቱን ገልጾአል፡፡ ለምሳሌም ሻለቃ እስፒዲ ወደ ማሌዥያ በተመለሰ በወሩ ሚስቱ ዓለማየሁን ልትጠይቀው በሄደች ጊዜ ዓለማየሁ የእሷን ጉብኝት የማይፈልግ መሆኑን ነግሯት ቤቱ ገብታ እንዳታየው ከልክሏታል፡፡

   ዓለማየሁ በአሁኑ ሰዓት የሚፈልገው ሰላምና ዕረፍት ነው፡፡ ለዘመዶቹ ሆነ ለሚያውቃቸው ሰዎች ደብዳቤ መጻፍ ከፈለገ ብዕርና ወረቀት አለለት፡፡ ነገር ግን የሚጽፍለት ዘመድ ስለሌለው ሁሉን ነገር እርግፍ አድርጎ ትቶ ከእኔ ልጆች ጋር ነው የሚጫወተው ” ብሎ ተናግሮ አሰናብቷታል፡፡

     ስለዚህ አለመግባባት ንግሥት ቪክቶሪያ ከሰሙ በኋላ ነበር እራሳቸው ጣልቃ ገብተው ሴትየዋ አለማየሁን እንድትጎበኝ የተፈቀደላት፡፡ አለማየሁም ይህንን ጉብኝት አጋጣሚመሆኑን ቢያስከፋውም ለጂክስ ብሌክ ቤተ-ሰብ ለእሱ ጥሩ መሆናቸውን፤ የወንድ ልጅ ጓደኛ ማግኝት ባለመቻሉ ግን ብቸኝነት እንደሚሰማው የነገራት መሆኑን ለንግሥት ቪክቶሪያ አሳውቃለች፡፡

     ጂክስ ብሌክ በዓለማየሁና በሻለቃ እስፒዲ ቤተ-ሰብ ይህን ዓይነት አቋም ለምን እንደወሰደ ግልጽ አይደለም፡፡ የሻለቃ እስፒዲ ሚስት ዓለማየሁን ለመጠየቅ እንዳይመጡ ብቻ ሳይሆን፤ ዓለማየሁ ከሴትዮዋጋ ንግሥት ቪክቶሪያን ለማየት እንዳይሄድ ከፍተኛ ጥረት ያደርግ ነበር፡፡ ለምሳሌም በጥር ወር 1873 ዓ.ም የ12 ዓመት ከስድስት ወር ልጅ ሆኖ ለንግሥት ቪክቶሪያ በጻፈው ደብዳቤ ውስጥ በአለማየሁ ላይ የነበረበትን ተጽዕኖ መረዳት እንችላለን፡፡

ይድረስ ለንግሥት ቪክቶሪያ፤

     ጤናዎ በደህና እንደሚጠበቅ ተስፋ አለኝ፡፡ ሚስተር ጂክስ ብሌክ ዊንድለር መጥቼ እንድጠይቅዎት ዕድል ስላልሰጠኝ በጣም አዝናለሁ፡፡ ሰሞኑን ከሻለቃ እስፒዲ ደብዳቤ ስለደረሰኝ በጣም ተደስቻለሁ፡፡ ለእርስዎ ይጻፍ አይጻፍ ግን አላወቅኩም፡፡ ሻለቃ እስፒዲ አንድ መቶ የሚሆኑ የህንድ ወታደሮችን ይዞ በማሌዥያዎች ላይ እንደዘመተና እንደተዋጋ ጽፎልኛል፡፡ ጦርነት ከመጀመራቸው በፊት ግን ሻለቃ እስፒዲ የሰላም ድርድር ጠይቋቸው ነበር፡፡ የሻለቃ እስፒዲን ጀግንነት ያላወቁት ማሌዥያውያን ግን ጠብ ፈለጉ፡፡ ሻለቃ እስፒዲ አንድ ሰዓት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ የማሌዥያውያን ምሽግ ከአንድ መቶ ወታደሮች ብቻ በመሆን ተቆጣጠረው፡፡ የተዋጉበት ቦታ ጭቃ የሞላበት በመሆኑ፤ የጭቃ ጫማ ያላደረጉ የጠላት ወታደሮች ማምለጥ አልቻሉም፡፡ ብዙዎቹ ሞቱ፡፡ ጥቂቶቹ ተማረኩ እልዎታለሁ፡፡ በጣም ጥሩ ዜና ነው፡፡ እኔ ትምህርቴን በመከታተል ላይ ነኝ፡፡ የዛሬ ሳምንት የትምህርት ቤታችን የሩጫ ውድድር ስለሚኖር ሽልማት እንደማገኝ ተስፋ አለኝ፡፡ ጂክስ ብሌክ ልቡን አራርቶ ቢፈቅድልኝ ዊንድለር ቤተ-መንግሥት መጥቼ እጅ እነሳለሁ፡፡ ”

ዓለማየሁ ቴድሮስ

ብራይተን

    ዓለማየሁ ኢትዮጵያ ከነበሩት አያቱ የእቴጌ ጥሩነሽ እናት ለወይዘሮ ላቂያዬ ደብዳቤ ይፃፍ አይፃፍ እስካሁን ግልፅ አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ ወይዘሮ ላቂያዬ ለዓለማየሁ የፃፉትን ደብዳቤ በቀጥታ ማግኝት ባንችልም ዓለማየሁን የአገሩ ህዝብ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ እንደሚፈልጉት እና፤ ትምህርቱን እንደጨረሰ ተሎ እንዲመለስ የጠየቁት መሆናቸውን የሚጠቅስ ደብዳቤ የደረሰው መሆኑን ለንግሥት ቪክቶሪያ ከጻፈላቸው የተለያዩ ደብዳቤዎች መረዳት ይቻላል፡፡

    ወይዘሮ ላቂያዬ ደብዳቤ የጻፉት ለዓለማየሁ ብቻ አልነበረም፡፡ ንግሥት ቪክቶሪያ ዓለማየሁን እንደልጃቸው አድርገው የሚያሳድጉት መሆናቸውን ስለሰሙ ሰኔ 15 ቀን፣ 1870 ዓ.ም እንዲህ ሲሉ ጽፈውላቸዋል፡፡

“ በስመአብ ወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ

ከወይዘሮ ላቂያዬ የእቴጌ ጥሩነሽ እናት የደጃዝማች አለማየሁ እሚታ የተላከ፤

ይድረስ ለንግሥት እንግሊዝ

(አንባቢው እጅ ይንሳልኝ)

መድኃኒዓለም ጤና ይስጥልኝ

መንግስትዎን ያስፋ

ጠላትዎን ያጥፋ

ሦስት ደጃዝማቾች፣ አራተኛ እቴጌ ሙተውብኝ የቀረኝ ደጃዝማች ዓለማየሁ ብቻ ነው፡፡

አደራዎን ይጠብቁልኝ፡፡

እግዚአብሔር አባቱንና እናቱን ቢነሳው እርስዎን ሰጥቶታል፡፡ እኔም ካላየሁት ከሞቱት ቁጥር ነኝ፡፡

እርስዎን እናቴ ይላል እንጂ እኔን እናቴ አይለኝም፡፡ አላሳደግሁትምና እርስዎ ያሳድጉት፡፡ ስለ እግዚአብሔር ብለው!

አሜን ”

ወይዘሮ ላቂያዬ የደጃዝማች ዓለማየሁ እሚታ

     ሰኔ 15 ቀን፣ 1870 እ.አ.አ፤ ዓለማየሁ ከጂክስ ብሌክ ጋር ከብራይተን ወደ ራግቢይ ሄደ፡፡ ነገር ግን ከጂክስ ብሌክ ጋር ተቀምጦ ከሚማር ይልቅ አዳሪ ትምህርት ቤት ቢገባ ይሻላል ተብሎ አዳሪ ትምህርት ቤት ገባ፡፡ ጂክስ ብሌክ ከዓለማየሁ ትምህርት ቤት አካባቢ ይኖር ስለነበር በየጊዜው እየሄደ ይጎበኘው ነበር፡፡ በ1876 ዓ.ም ግንቦት ወር ላይ ጂክስ ብሌክ ስለ ዓለማየሁ የወደፊት ኑሮ ለንግሥት ቪክቶሪያ እንዲህ የሚል ደብዳቤ ጻፈላቸው፡፡

     ዓለማየሁ በትምህርቱ በኩል የፈለግኩትን ያህል አልገፋበትም፡፡ ፍላጎትም የለውም፡፡ ትጉህ ቀልጣፋና በክፍል ጓደኞቹ በጣም ተወዳጅ በመሆኑ ወደ ውትድርና ዓለም ቢሰማራ የሚሻል ይመስለኛል፡፡ ትዕግስተኛና ስፖርት ነክ ነገሮችን ወዳድ በመሆኑ፤ ለሳንደርስት የጦር አካዳሚ ኮሌጅ ጥሩ ካዲት ያደርገዋል ብዬ አምናለሁ ” ይላል፡፡

      ይህ የጂክስ ብሌክን ሃሳብ በመጀመሪያ የደገፈው ማንም አልነበረም፡፡ የገንዘብ ሚንስትሩ ሮበርት ላው ቀደም ሲል የዓለማየሁን ወደ ውትድርና ዓለም መሰማራት ጠቁሞ የነበረው እንኳን ቢሆን፤ ሃሳቡን ለውጦ ለዓለማየሁ ጥሩ ቦታ እንደማይሆን ያለውን ጥርጣሬ ገልጾአል፡፡ ለዚህ የቀረቡት ምክንያቶች ግን የተለያዩ ነበሩ፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩና ንግሥት ቪክቶሪያ የዓለማየሁ የሰውነት ጥንካሬ እንደወታደርነት ላለ ከባድ ሥራ ብቁ አይደለም የሚል ሲሆን እነ ሮበርት ላው ግን የዓለማየሁ አፍሪካዊ (ጥቁር) መሆኑና ጥቁር በመሆኑ የእንግሊዝ ወታደሮችን የማዘዝ ችግር ያጋጥመዋል በሚል ነበር፡፡ ይህ ጉዳይ ተጠንቶ እስኪቀርብ ግን ለአንድ ዓመት ያህል የግል አስተማሪ ተቀጥሮለት በዚሁ በራግቢይ ከተማ ትምህርቱን ቀጠለ፡፡

      ከአንድ ዓመት በኋላ መስከረም ወር 1878 ዓ.ም ጀምሮ ዓለማየሁ ሳንደርስት ጦር አካዳሚ ያለምንም ፈተና እንዲገባ የተፈቀደለት መሆኑን የሚገልፅ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ቢሮ የተጻፈ ደብዳቤ ለጂክስ ብሌክ ደረሰው፡፡ ዓለማየሁ ሳንደርስት ጦር አካዳሚ ከመግባቱ በፊት ግን ቀደም ሲል ቤተ-መንግሥቱ ባወጣለት ፕሮግራም መሠረት ከንግሥቲቱ ዋና ጸሐፊ ከቢደልፍ ጋር ሆነው በጋውን የአውሮፓን ከተሞች በተለይም ፓሪስንና ፓሪስ ላይ በጊዜው ለህዝብ ይታይ የነበረውን ዓለም አቀፍ ኤግዚቪሽን ጎበኘ፡፡ በመስከረም ወር 1878 እ.አ.አ ሳንደርስት ጦር አካዳሚ ካዲት ሆኖ ገባ፡፡ ለስድስት ወራት ያህል ሳንደርስት ጦር አካዳሚ ሲማር በቆየባቸው ጊዚያት በየጊዜው ያመው ጀመር፡፡ ትምህርቱን በደምብ መከታተል አልቻለም፡፡ የሳንደርስት የጦር አካዳሚ አዛዥ የዓለማየሁን ደህና አለመሆንና በነበረበት ሁኔታ ሳንደርስት መቆየቱ ጊዜ ማጥፋት ስለመሆኑ ከጂክስ ብሌክ፣ ከሻለቃ እስፒዲ ሚስትና ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ተወያዩ፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ዓለማየሁን አነጋገረው፡፡ በመጨረሻም እንዲህ ሲል ለንግሥት ቪክቶሪያ ጻፈላቸው፡፡

     ወጣቱ ዓለማየሁ ሳንደርስት ጦር አካዳሚ ውስጥ መቆየቱ ዋጋ ያለው አልመሰለኝም፡፡ ደስተኛም አይደለም፡፡ የመማር ፍላጎቱ ቀንሷል፡፡ ብዙ የሚያሳስቡት ነገሮች እንዳሉ ከፊቱ ማንበብ ይቻላል፡፡ በዚህ ላይ ጤናው ብዙም አልረዳውም፡፡ አልፎ አልፎም የመንፈስ መረበሽ ይታይበታል፡፡ አጋጣሚ ሆኖ ሻለቃ እስፒዲ ከማሌዢያ ተመልሶ ለዕረፍት ስለመጣ ከእሱ ጋር ቢቆይ ጥሩ መሰለኝ፡፡ ” ይላል፡፡

     ንግሥት ቪክቶሪያ በዓለማየሁ መታመም በመደንገጣቸው በአስቸኳይ ከሳንደርስት ጦር አካዳሚ ወጥቶ ከልዩ ጸሐፊያቸው ቤት ሆኖ ህክምናውን እንዲከታተል የዓለማየሁ ጉዳይ ለሚመለከታቸው ባለሥልጣኖች ቴሌግራም አደረጉ፡፡ ሳምንት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ዓለማየሁን ከነበረበት ኮሌጅ አውጥተው ወደ ንግሥቲቱ ልዩ ጸሐፊ ቤት ወሰዱት፡፡ ህመሙ እየጠናበት ሄደ፡፡ የዓለማየሁን የጤና ማጣት አስመልክታ የልዩ ጸሐፊው ሚስት ለንግሥት ቪክቶሪያ በጻፈችው ደብዳቤ እንዲህ ትላለች፡፡

   ውድ ዓለማየሁ በጣም ታምሟል፡፡ በመጨረሻ የተደረገው ምርመራ ትንሽ የተስፋ ፍንጭ የሚሰጥ ይመስላል፤ ነገር ግን ህይወቱን አደገኛ ጊዜ ላይ ነው ያለችው፡፡ በሳንባ በሽታ በጣም ይሰቃያል፡፡ ዓለማየሁ መርዙ አቅምሰውኛል ብሎ ስለሚጠረጥር ምግብ እና መድኃኒት የመውሰድ ፍላጎቱ ቀንሷል፡፡ በዚህ ምክኒያት በየዕለቱ ሰውነቱ እየደከመ በመሄድ ላይ ነው፡፡ ከቅርብ ቀናት ጀምሮ ግን ዶክተሩ ያዘዘለትን መድኃኒት መውሰድ ጀምሯል፡፡ መርዝ አብልተውኛል የሚለውን ቅዥቱንም ትቷል፡፡ በተረፈ ግን ለልጅ ዓለማየሁ እንፀልይለት ” ይላል፡፡

     የዓለማየሁ ዶክተር፣ የንግሥቲቱን የግል ሃኪምና ሌሎች የታወቁ የህክምና ሰዎችን አነጋገረ፡፡ ንግሥት ቪክቶሪያ የዓለማየሁን ህይወት ማዳን የማይቻል መሆኑን ኅዳር 11 ቀን፣ 1879 ዓ.ም ተነገራቸው፡፡ በጣም በማዘን አንድ የመጨረሻ ደብዳቤ ጻፉለት፡፡ ዓለማየሁ አልጋው ላይ ተኝቶ፤ እያቃሰተ የንግሥት ቪክቶሪያን ደብዳቤ ለማንበብ ጥረት አደረገ፡፡

የነበረውን ሁኔታ የንግሥቲቱ ልዩ ጸሐፊ ሚስት እንዲህ ብለው ይገልፁታል፡፡

  ዓለማየሁ ደብዳቤው ከማን እንደተጻፈለት ለማወቅ የደብዳቤውን አድራሻ መፈለግ ጀመረ፡፡ የንግሥት ቪክቶሪያን ስም እንዳዬ ፈገግ አለ፡፡ ፖስታውን ቀደደና ወረቀቱን ወጣ አድርጎ ትንሽ መስመሮችን እንዳነበበ በጣም ስለደከመው፤ ደብዳቤውን ሊያነብ በሚችልበት ቦታ ላይ እንዳስቀምጥለት ጠየቀኝ፡፡ አንገቱን ወረቀቱ ወደ ተቀመጠበት ዘወር አድርጎ የጀመረውን ለመጨረስ ታገለ፡፡ አልቻለም በመጨረሻ እጁን ይዞ ማቃሰት ጀመረ ” ይላል፡፡

     የሻለቃ እስፒዲንና የጂክስ ብሌክን ሚስት እጃቸውን እንደያዘ በ19 ዓመቱ፤ ኅዳር 14 ቀን 1879ዓም ከጥዋቱ ሦስት ሰዓት ላይ አረፈ፡፡

     በንግሥት ቪክቶሪያ ትዕዛዝ አለማየሁ ዊንድለር በሚገኘው የጊዮርጊስ ቤተ-ክርስቲያን እንዲቀበር ተደረገ፡፡ በሞተ በሦስተኛው ቀን ንጉሳዊ ቤተ-ሰቦችና ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣኖች በተገኙበት የቀብሩ ሥነ-ስርዓት ተፈጸመ፡፡

በመጨረሻም ንግሥት ቪክቶሪያ የሀዘን መግለጫቸውን እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፡፡

   የዓለማየሁን ዛሬ ጧት መሞት በቴሌግራም ሰማሁ፡፡ ጥልቅ ሀዘን ተሰማኝ፡፡ ባይተዋር እንደነበር ባይተዋር ሆኖ ሞተ፡፡ ከመጀመሪያ ጀምሮ ደስተኛ ልጅ አልነበረም፡፡ በወጣትነቱ ካሳደጉት ዘመዶቹና ወገኖቹ ርቆ መኖር ለወጣት ዓለማየሁ ከባድ ፈተና ነበር፡፡ ጥቁርና (አፍሪካዊ) ሆኖ መኖር በእኛ ህብረተ-ሰብ አስቸጋሪ መሆኑንም ተረድቶታል፡፡ አንድ ቀን ሊያየኝ የመጣ ቀን ለምን አንዳንድ ሰዎች ትኩር ብለው ያዩኛል? ብሎ የጠየቀኝ ትዝ ይለኛል፡፡ መልስ አልነበረኝም፡፡ ወጣት ዓለማየሁ ቆንጅዬና ተናፋቂ ወጣት እንደነበር፤ ቀንጅዬና ተናፋቂ ሆኖ ሞተ፡፡

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top