ጥበብ በታሪክ ገፅ

በምዕራብ የደመቀ ምሥራቃዊ ኮከብ

‹‹በአንድነት ቁሙ፤ ነገር ግን መተዛዘል እስኪሆን

ድረስ አትደራረቡ፤ የቤተ መቅደስ አእማድ ሲቆሙ ራቅ ራቅ ብለው ነው:: ዋርካ እና ዝግባም አንዱ በአንዱ ጥላ ሥር ሆኖ አይበቅልም››

የበረዶ ባርኔጣ ከደፋው የሊባኖስ ተራሮች ከፍታ፤ መአዛው ከሚያምረው የሊባኖስ ሸለቆ፤ ልምላሜ ውበታቸው ተደጋግሞ ከሚጠቀሰው የሊባኖስ ዝግባ ደኖች አቅራቢያ በምትገኝ እና ቢሻሪ የተባለች መንደር አንድ ሕጻን ተወለደ:: ይህ ሕጻን አስቀድሞ ትንቢት አልተነገረለትም:: ግና ትንቢት ቢነገርለት ኖሮ፤ ብዙ ‹‹ሰብአ ጥበቦች›› በሥነ ጥበብ ኮከብ እየተመሩ፤ የምስጋና መባ ቋጥረው፤ ከምሥራቅ ብቻ ሳይሆን ከምዕራብ ጭምር ‹‹እንኳን ተወለድክልን›› እያሉ ቢሻሪ ይገቡ ነበር:: ምክንያቱም፤ ይህ ሕጻን፤ ዕድሜ ልኩን ምሥራቅ እና ምዕራብን ለማስታረቅ የሚተጋ ሕጻን ነው::

ሰሎሞን በማህሌቱ፣ ዳዊት በመዝሙሩ፣ ኢሳያስ በትንቢቱ የሚያነሳሷት ሊባኖስ፤ ‹‹ተቃራኒዎችን ተመሳሳይ…›› የምታደርግ የትንግርት ምድር ነች:: በአንድ ቤተ መቅደስ አራት እምነቶችን የማስተናገድ ታሪክ አላት:: እንዲህ ያሉ የታሪክ ክስተቶች የሕጻኑን ህይወት በራሳቸው መንገድ አበጅተውታል:: ለምሳሌ፤ ቱርክ ሊባኖስን ባስተዳደረች ጊዜ፤ ቤተ ክርስቲያናትን መስጊድ ስታደርግ ነበር:: በሊባኖስ ምድር ታላላቅ የእስልምና መሪዎች እና የሐይማኖት ሰዎች ተመላልሰውባታል:: ከክርስቲያን ቤተሰብ የተወለደው ይህ ሕጻንም ከአረብ የኪነ ጥበብ እና የፍልስፍና ምንጭ የፈለቀን የአሊሞችን (የመምህራንን) ሐሳብ እንደ ዘምዘም ውሃ የመጠጣት ዕድል አግኝቷል:: ተረቶቻቸውን አንብቧል:: ይህም ሕጻን ጅብራን ካሃሊል ጅብራን ይባላል::

በበርካታ ድብልቅልቅ ዓለማዊ፣ ሐገራዊ እና ታሪካዊ ክስተቶች መሐል የተወለደው ጅብራን፤ ዕድሜ ዘመኑን ሙሉ ከዝብርቅርቁ ውስጥ አንድ ወጥ ድምጽ ለመፍጠር ጥረት የሚያደርግ የብዕር ሰው የሆነው፤ ምሥራቅን እና ምዕራብን ለማስታረቅ ሲተጋ የኖረው ለዚህ ሳይሆን አይቀርም:: ዓለምን በዐዲስ ዓይን የማየት ድፍረት እና ችሎታ ያለው ፈላስፋ እና ባለቅኔ የሆነውም ለዚህ ሳይሆን አይቀርም::

ቤተሰብ

ጅብራን ካሃሊል ጅብራን ሊባኖስ ውስጥ በሰሜን ምሥራቅ ቤሩት አካባቢ በምትገኝ ቢሻሪ የተባለች መንደር ጃንዋሪ 6 1883 ዓ.ም (እኤአ) ተወለደ:: በአረቦች ዘንድ የሚታወቀው ሥሙ፤ ‹‹ጅብራን ካሃሊል ጅብራን›› የሚል ነው:: መካከለኛው የአባቱ ሥም ነው:: አረቦች የእኛ ዓይነት የስም አጠራር ወግ አላቸው:: የአባት ሥም ተከታይ እንጂ ቀዳሚ አይደለም:: የጅብራን የአባቱ ሥም ‹‹ካሃሊል ጅብራን›› ነው:: ለእርሱ ‹‹ካሃሊል›› የመሐል ስሙ ነበር::

ጅብራን በአረብኛ በሚጽፋቸው ድርሰቶቹ ‹‹ጅብራን ካሃሊል ጅብራን›› የሚለውን ሙሉ ስሙን ሲጠቀም፤ በእንግሊዝኛ ድርሰቶቹ፤የመጀመሪያውን ‹‹ጅብራን›› የሚል ቃል ገድፎ ‹‹ካህሊል ጅብራን›› ይላል:: በአጻጻፉ ረገድም በስሙ ላይ ለውጥ አድርጓል:: በትክክለኛው አግባብ ‹‹KHALIL›› (ካሃሊል) የሚለውን የአጻጻፍ ስርዓት ወደ ‹‹KAHLIL›› (ካህሊል) ለውጦታል:: ወይም ለውጠውበታል:: በዚህ የተነሳ ‹‹ካሃሊል›› ይባል የነበረው ‹‹ካህሊል›› በሚል የሚጠራበት አጋጣሚ ተፈጥሯል:: እኛም ከእንግዲህ ‹‹ካህሊል›› እያልን እንቀጥላለን::

 ይህን የስም ለውጥ ያደረገው፤ ከ1895 እስከ 1897 ዓ.ም በቦስተን ከተማ ‹‹ኩዩንሲ ስኩል›› በተባለ ት/ቤት፤ እንግሊዝኛ ያስተምሩት በነበሩ መምህሩ ምክር ነው ይባላል:: ጅብራን የሚለው ስም ‹‹ጃበር›› ከሚለው የአረብኛ ቃል የወጣ ነው:: ትርጉሙ ‹‹ስምምነትን መልሶ ማስፈን›› ( to restore to harmony) ወይም ‹‹በአልጀብራዊ የሒሳብ ስሌት እንደሚደረገው አቻ ያልሆኑ ክፍሎችን አንድ ማድረግ›› (to bring unequal parts to unity as in Algebra) የሚል መሆኑን የአረብኛ ቋንቋ አዋቂዎች ይገልጻሉ::

 የጅብራን ካህሊል ጅብራን ቤተሰብ አምስት አባላት ያሉት ነው – አባቱ፣ እናቱ፣ ታላቅ ወንድሙ (የእናቱ ልጅ)፣ ሁለት ታናናሽ እህቶቹ:: የጅብራን አባት ሰውነተ ደንዳና እና ጠንካራ፤ ጠይም እና ሰማያዊ ዓይኖች ያሉት፤ በቢሻሪ ደኖች ውስጥ የሚጠመቀውን ወይን ጠጅ መጎንጨት የሚወድ፤ የመንደራቸው የቢሻሪ ግብር ሰብሳቢ ነበር:: የገበሬነት ህይወቱንም መቀየር የማይሻ ከብት እረኛም ነበር:: እርሱ አብዝቶ የሚጨነቀው ‹‹ትሪክ-ትራክ›› ለሚሉት የካርታ ጨዋታ እና ለሺሻው ነው:: በየጓደኞቹ ቤት እየዞረ ረብ የለሽ ወሬ ለማውራቱ ነው:: አልፎ አልፎ አረቄ ፉት ለማለቱ ነው::

 የጅብራን አባት መሽቀርቀር የሚወድ እና የደስደስ ያለው ሰው ነው:: በሊባኖስ አምባ ምድር ላይ ሜዳ ሜዳውን መዞር ይወዳል:: የበረታ የቁማር እና የአልኮል መጠጥ አመል ተጠናውቶታል:: ስለዚህ ለውዝ ከተከለባት ትንሽ ማሳው የሚያገኛትን መቅኑን የሆነች ገቢ በመጠጥ እና በቁማር ያባክናት ነበር:: አንዳንዶች አባቱን ‹‹በቢሻሪ መንደር ከሚገኙ አስቸጋሪ ዐመል ያላቸው ሞገደኛ ሰዎች›› እንደ አንዱ ይቆጥሩታል:: በሁሉም ረገድ ቢታይ የጅብራን አባት አብሮ ለሚኖረው ሰው የሚያስቸግር ነው:: ሚስቱም ሆነች ልጆቹ ይፈሩታል:: ከልጁ ካህሊል ጅብራን ጋር እንደ አባት አይቀራረቡም:: ስለዚህ በጅብራን የሥነ ልቡና ግንባታ ውስጥ አንዳች ተጽዕኖ የለውም::

“…እናቱን ያጣ ሰው፤ ያለማሰለስ የሚጠብቀውን እና የሚባርከውን አንድ ንፁህ ነፍስ አጥቷል›› በማለት ጽፏል”

አባቱ የኦርቶዶክስ ክርስትና ሐይማኖት ተከታይ ነው:: ጅብራን ሲወለድ አርባ ዓመቱ ነበር:: ካህሊል ጅብራን ለአባቱ ያለውን ስሜት ሲገልጽ፤ በመካከላቸው የነበረው አስቸጋሪ ግንኙነት የፈጠረውን አስቀያሚ እውነታ ለመሸፋፈን ጥረት እያደረገ መሆኑ በግልጽ ይታያል:: በአንድ አጋጣሚ ሲናገር፤ ‹‹የአባቴን ኃይል፣ ሐቀኝነት እና ግልጽነት አደንቃለሁ:: ራሱን ለመሆን ያለው ድፍረት፤ ሐሳቡን ያለ አንዳች ማመንታት ለመግለጽ መድፈሩ እና ለተጽዕኖ መንበርከክ የማይወድ ሰው መሆኑ፤ ውሎ ሲያድር ችግር ውስጥ እንዳስገባው አምናለሁ:: አባቴ፤ በዙሪያው መቶ ሰው ቢቆም፤ ሁሉንም በአንድ ቃል ይገዛቸዋል:: ሺህ ሰዎች ቢመጡ፤ ራሱን ሆኖ በመቆም ያሸንፋቸዋል›› ብሎ ነበር::

እንደ እውነቱ ከሆነ፤ ጅብራን ከአባቱ ጋር የነበረው ግንኙነት አስቸጋሪ እና ብዙ ጊዜ መሻከር የሚታይበት ግንኙነት ነበር:: ስለዚህ ጅብራን አምባገነን እና ብስጩ ጠባይ ካለው አባቱ ጋር የመቀራረብ ግንኙነት ኖሮት አያውቅም:: በአጭሩ የሚወደድ አባት አልነበረውም::

 የጅብራን ህይወት መሠረት እና ዋልታ እናቱ ናት:: በአንድ ወቅት ራሱ ጅብራን፤ ‹‹እናታችን ሁሉ ነገራችን ናት:: በሐዘናችን ጊዜ መጽናኛ፤ በችግር ጊዜ ተስፋ፣ በድካም ጊዜ ብርታት ነበረች:: እርሷ የፍቅር፣ የምህረት፣ የርኅራኄ እና የይቅርታ ምንጭ ነች:: እናቱን ያጣ ሰው፤ ያለማሰለስ የሚጠብቀውን እና የሚባርከውን አንድ ንፁህ ነፍስ አጥቷል›› በማለት ጽፏል:: በርግጥ ጅብራን ከልጅነት እስከ ዕውቀት የ‹‹እኔ›› ብሎ ሊጠራው የሚችለውን ነገር ሁሉ ያገኘው ከሴቶች ነው:: ከእነዚህ ሴቶች ውስጥ በጅብራን ህይወት ልዩ ትርጉም ይዛ የምትገኘውም እናቱ ነች – የሴቶችን ነገር ዝቅ ብለን እያለን::

 እናቱ ካሚላ ራህማ ትባላለች:: እስጢፋኖስ ራህማ የተባሉ የአንድ ‹‹ማሮናዊ›› (Maronite – ካቶሊኮች) ቄስ የመጨረሻ ልጅ ነች:: እናቷ የወለዷት የ65 ዓመት አሮጊት ሆነው ነው:: የጅብራን እናት ካሚላ ራህማ፤ ነጣ ያሉ ጉንጮች፤ የሐዘን ጥላ ያረበበባቸው ዓይኖች ያሏት ደርባባ ሴት ናት:: በጅብራን ስሜት ውስጥ ጥልቅ የፍቅር እና የአድናቆት ስሜት መዝራት የቻለች ድንቅ ሴት ናት:: ካሚላ ራህማ መረዋ ድምጽ ያላት ነች:: ጽኑ ሐይማኖተኛ ሴት ናት::

የጅብራን አባት ሁለተኛ ባሏ ነው:: የመጀመሪያ ጋብቻዋን የፈፀመችው፤ የእርሷ ጎሣ አባል እና የአጎቷ ልጅ ከሆነው ከሐና አብዱልሰላም ራህማ ጋር ነበር:: ሆኖም፤ ብዙዎቹ የእርሱ ዘመን ሊባኖሳውያን እንደሚያደርጉት እርሱም የተሻለ ህይወት ፍለጋ ወደ ብራዚል ተሰዷል:: ግን አልቀናውም:: ጴጥሮስ የተባለ ልጅ ጥሎባት በስደት በሄደበት ሐገር ሞተ:: የህግ ባሏ ሲሞት ልጇን ይዛ ከአባቷ ቤት ገባች::

ታዲያ አንድ ቀን በአባቷ አፀድ ሆና ትዘምር ነበር:: የካህሊል አባት በመንገድ ያልፋል:: የካሚላ ራህማን መረዋ ድምጽ የሰማው የጅብራን አባት ቀልቡ ተሰረቀ:: ሳይውል ሳያድር የዚያን ድምጽ ባለቤት ማንነት ለማወቅ ተጣጣረ:: ብዙ አልቆየም ራህማን አያት:: የደስደስ ያላት ውብ ሴት ናት:: ራሱንም ሆነ ሌሎች ወዳጆቹን ሰላም ነስቶ እና አስቸግሮ አገባት::

 ከዚያም ጅብራን ተወለደ:: ቀጥሎ ለእናቱ የመጀመሪያ ሴት ልጅ፤ ለጅብራን ደግሞ የመጀመሪያ እህቱ የሆነችው ማሪያና ተወለደች:: በመቀጠል (በ1887 ዓ.ም) የመጨረሻ ሴት ልጇ የሆነችውን ሱልጣናን ወለደች:: ከባሏ ጋር ስትነጻጸር፤ ካሚላ ትዕግስተኛ ነች:: ልጆቿን አብዝታ የምትወድ እና ትልቅ ደረጃ እንዲደርሱ ትልቅ ምኞት ያላት ናት:: በርግጥ ካሚላ ራህማ ዘመናዊ ትምህርት አልተማረችም:: ሆኖም የተባ አዕምሮ እና ጥበብን (ዊዝደም) የታደለች ሴት ናት:: ምናልባት ብዙዎች ረብ የለሽ አድርገው ሊመለከቱት የሚችሉት ዕውቀቷ በታዳጊ ልጇ በጅብራን የወደፊት ህይወት ውስጥ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደር የቻለ ነው:: ጅብራንም፤ ‹‹የእኔ ውሳጣዊ ማንነት፤ በእናቴ ፍቅር እና እንክብካቤ የተቀረፀ ነው›› ይላል::

ካሚላ ራህማ፤ ጥልቅ ‹‹ማኖራዊ ትውፊት›› ካለው ቤተሰብ የወጣች ሴት ናት:: የመጀመሪያ ባሏን ከማግባቷ በፊት፤ በሰሜናዊ ሊባኖስ ግዛት በሚገኘው የቅዱስ ስምዖን ማሳደጊያ፤ የህጻናት ትምህርት እና እንክብካቤ ሥራን ለመስራት ታስብ ነበር:: የእርሷ መንፈሳዊ ማንነት እና የማሮናውያን ሐይማኖታዊ ክንውኖች በጅብራን ህይወት ላይ የዕድሜ ዘመን ተጽዕኖ ነበራቸው::

 ካህሊል ጅብራን ስምንት ዓመቱን ሲደፍን፤ አባቱ ግብር በመሰወር ወንጀል ተከስሶ ዘብጥያ ወረደ:: በዚሁ የተነሳ የአባቱ ንብረት ተወርሶ፤ ቤተሰቡ ቤት አልባ ሆነ:: የጅብራን አባት በ1894 ዓ.ም (እኤአ) ከእስር ቢፈታም፤ የቤተሰብ ኃላፊነት የሚሰማው ሰው ባለመሆኑ፤ እንደ ሚስቱ ቁርጥ ሐሳብ አድርጎ የተሻለ ህይወት ፍለጋ ስደት መሄድ አልፈለገም:: ስለዚህ እርሱ እዚያው በሊባኖስ ሲቀር፤ መላ የቤተሰቡ አባላት ወደ አሜሪካ ተሰደዱ::

 ካህሊል ጅብራን፤ አባቱ የክስ መጥሪያ የተቀበለባትን ያችን ክፉ ማለዳ ከብዙ ዓመታት በኋላም ያስታውሳታል:: ፖሊሶቹ ወደ ግቢያቸው ግር ብለው ሲገቡ የነበረውን ሁኔታ አይዘነጋውም:: ቤተሰቡ ቤት አልባ ሆኖ የዘመድ ጥገኛ ሆኖ ለመኖር የተገደደበት አጋጣሚ ተፈጠረ:: በዚህ ጊዜ መንፈሰ ጠንካራይቱ እናቱ፤ የተሻለ ህይወት ፍለጋ ወንድሟ ቀደም ብሎ ወደ ሄደበት ምድረ አሜሪካ ለመሰደድ ወሰነች::

ሕጻንነት

 ካህሊል ጅብራን የመጀመሪያውን ትምህርት ያገኘው በቤት ውስጥ ነው:: የመጀመሪያ መምህሩም እናቱ ናት:: እናቱ አረብኛ፣ ፈረንሳይኛ እና እንግሊዝኛ ቋንቋን መናገር ትችላለች:: መገለጫ ያጣ እምቅ የሙዚቃ ችሎታም ነበራት:: ጅብራንን ከዝነኞቹ የ‹‹ሐሩን አል ረሽድ›› ጥንታዊ ተረቶች፤ ከ‹‹አረቢያን ናይት›› እና አቡ ኑዋስ ከደረሱት የአደን መዝሙሮች ጋር ያስተዋወቀችው እናቱ ናት:: ለስዕል ሥራ ኪነታዊ ዝንባሌ እንዲኖረው እና ዝንባሌውን እንዲያዳብር የሚያደርግ ዓይን ከፋች ትምህርት የሰጠችው ልበ ብርሃኒቱ እናቱ ካሚላ ራህማ ናት:: ጅብራን ከልጅነቱ ጀምሮ ልቡ ወደ ስዕል ይሳባል:: የብሩሽ አያያዝን እና የቀለም አጠቃቀምን ያስተማረችው እናቱ ናት:: በ6 ዓመቱ እናቱ፤ አንድ የሊዮናርዶ ዳቬንቺን የስዕል ሥራ ቅጅ ሰጥታው ነበር::

በድህነት ተቀይዶ ያደገው ጅብራን መደበኛ ትምህርት ለማግኘት የታደለ አልነበረም:: ነገር ግን ከመንደራቸው ይኖሩ የነበሩ አንድ ቄስ፤ የሐይማኖትን መሠረታዊ ነገሮች፤ መጽሐፍ ቅዱስን፤ የሶሪያ እና የአረብኛ ቋንቋን አስተማሩት:: ቄሱ የጅብራንን ቀለም ተቀባይ፣ ንቁ እና ጠያቂ አዕምሮ በማየት መሠረታዊ የፊደል እና የቋንቋ ትምህርት ሰጡት:: የታሪክን፣ የሳይንስ እና የቋንቋን ዓለም በርን ከፈቱለት:: ጅብራን ከህጻንነቱ ጀምሮ መንፈሱ ቀና ነበር:: የማይናወጥ ትኩረትን የታደለ ህሊናም ያለው ነው::

የሦስት ዓመት ህጻን ሳለ፤ የቢሻሪ ተራራዎችን የሚገርፍ ኃይለኛ ወጀብ ሲመጣ፤ እርሱ ልብሱን አወላልቆ ወደ ደጅ ይወጣ ነበር:: የልጇ ደህንነት የሚያሰጋት እናቱ፤ በተፈጥሮ ምስጢር የሚሸነፍ ልጇን (ecstatic boy) ተከትላ በመሮጥ፤ አፈፍ አድርጋ በማንሳት በክንዷ እቅፍ አድርጋ ወደ ቤት በመመለስ፤ እንደ በረዶ የቀዘቀዘ ሰውነቱን በአልኮል ትጠራርግለታለች:: ‹‹ሆኖም ህጻኑ በቀላሉ የሚታገድ አልነበረም:: ስለዚህ ደግሞ ደጋግሞ ከወጀቡ ይገባል:: ደመ ነፍሱ፤ በአስፈሪው የተፈጥሮ ግርማ ሞገስ ትሳብ ነበር›› ይላሉ የህይወት ታሪኩን ያጠኑ ፀሐፊዎች:: በመብረቅ እና በነጎድጓድ ትዕይንት የሚሸነፈው ያ ህጻን፤ ተፈጥሮ የሚያርድ ኃይሏን የምታሳይባቸውን ቅጽበቶች በአድናቆት የመመልከት ዝንባሌን ያዳበረው ከነዚህ አጋጣሚዎች ነው::

ልቡን ለሥነ ጥበብ ፍቅር ገና በማለዳ ዕድሜው የከፈተው ብላቴና፤ በቤት ወረቀት ቢጣፋ፤ ከደጅ ወጥቶ ከተከመረው በረዶ ላይ የተለያዩ ቅርፆችን እና ምስሎችን በጣቱ በመሳል ለሰዓታት ይቆይ ነበር:: የአራት ዓመት ልጅ ሳለ መሬት ቆፍሮ የወረቀት ቁርጥራጮችን ይተክል ነበር:: ይህን ሲያደርግ የመኸር ወቅት ሲመጣ ብዙ ወረቅት ማግኘት ይቻላል በሚል ተስፋ ነበር:: ደግሞ ጥንታዊ ተረቶችን በታላቅ የተመስጦ ስሜት ያዳምጥ ነበር:: ወደ ተራራውም በመሄድ ከአናት ሆኖ ፀጥታ የነገሰበትን ሸለቆ ቁልቁል መመልከት ይወዳል::

 አንድ ቀን ከጓደኛው ጋር በተራራው ሲጫወት (የበረዶ ሸርተቴ) ከሸለቆው ወድቆ ትከሻው ተሰብሮ ነበር:: በዚህ ጊዜ ለታዳጊ ቁመናው የሚመጥን መስቀል ነገር ተሰርቶ (አጥንቱ እንዲስተካከል መሰለኝ) ታስሮለት ነበር:: ይህንም ፀሐፊዎች ጅብራን አብዝቶ ከሚወደው ኢየሱስ ክርስቶስ ከተሰቀለበት መስቀል ጋር አገናዝበው ጽፈውታል::

ጅብራንም፤ ‹‹Sand and Foam›› በተሰኘ ድርሰቱ ራሱን እንደሚከተለው ከክርስቶስ ጋር ያነጻጽራል፤ ‹‹በመስቀል የተሰቀለከው ሆይ፤ አንተ በልቤ ላይ ተቸንክረሃል፤ የአንተን እጆች የወጉት ችንካሮች፤ የልቤን ግድግዳ በስተውታል:: እናም ነገ አንድ እንግዳ በዚህ ጎሎጎታ ሲያልፍ፤ በዚህ ስፍራ ደማቸው የፈሰሰው ሁለት ሰዎች መሆናቸውን አያስተውሉትም:: ደሙ የአንድ ሰው ደም ብቻ ይመስለዋል›› ብሏል::

 በአጭሩ፤ ጅብራን የህጻንነት ዘመኑን ያሳለፈባት የትውልድ አካባቢው ያሉት መልክዐ ምድር እና ሌሎች የተፈጥሮ ክስተቶች፤ ለጅብራን ጥበባዊ ህይወት የተለዩ ስንቆችን አስይዘውታል ማለት ይቻላል:: የስደት ህይወቱም ለሥራው ትልቅ ግብአት ሆኖታል::

ስደት

 በወቅቱ በኦቶማን ቱርክ አገዛዝ ይፈጸም የነበረው ጭፍጨፋ በሺዎች የሚቆጠሩ ሊባኖሳውያንን ለስደት ዳርጓቸዋል:: በርግጥ በ1860ዎቹ (እኤአ) በሊባኖስ የነበረው እና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታው ለስደት የሚገፋፋ ነበር:: ስለዚህ ሺዎች ወደ ግብጽ ተሰደዋል:: ይህ ጊዜ የግብፁ ‹‹ስዊዝ ካናል›› የተከፈተበት ጊዜ ነበር:: ይህ ካናል በ1869 ዓ.ም (እኤአ) ሲከፈት፤ የአካባቢው የንግድ እንቅስቃሴ ብቸኛ ማዕከል የነበሩት ሊባኖስ እና ሶርያ ሚናቸው ተዳከመ:: ከአውሮፓ ጋር የነበራቸው የጦፈ የሐር ንግድ፤ ከቻይና እና ከጃፓን የመጣ ከባድ ፉክክር ገጠመው:: በዚህ የተነሳ የሊባኖስ ኢኮኖሚ ይበልጥ አሽቆለቆለ:: የኦቶማን ቱርክ አገዛዝ የኢኮኖሚ ዕድገት ተስፋውን አጨለመው:: የመሬት ከበርቴዎቹ አገዛዝ የተራውን ሊባኖሳዊ ዜጋ ህይወት እጅግ አስቸጋሪ አደረገው:: ኢ-ፍትሓዊ የግብር ስርዓቱም ደካሞቹን እና ድሆቹን በተስፋ መቁረጥ አዙሪት ውስጥ እንዲወተፉ አደረጋቸው:: አስቸጋሪው ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ እና የነቀዘው ፊውዳላዊ አስተዳደር ተባብረው፤ በርካታ ሊባኖሳውያንን ለስደት አነሳሱአቸው:: የጅብራን ካሃሊል ጅብራን ቤተሰብም ተሰደደ::

 አዎ፤ ሊባኖስ የወለደችውን፤ የህይወት እና የጥበብ ፊደል በጥቂቱ ያስቆጠረችውን ውድ ልጇን፤ እንደ ነቢዩ ሙሴ እናት ‹ልጄ› ብላ ማሳደጉ አቃታት:: ሊባኖስ ጡት አጥብታ ያሳደችውን ይህን ጨቅላ፤ አስራ ሁለት ዓመት ሲሞላው ‹‹ጣለችው›› ነገር ግን እንደ ሕጻኑ ሙሴ በቅርጫት አኑራ ሳይሆን በመርከብ አሳፍራ፤ በእኛው የአባይ ወንዝ ላይ ሳይሆን፤ በአትላንቲክ ውቂያኖስ አንሳፍፋ፤ ከሊባኖስ ሰባት ሽህ አምስት መቶ ኪሎ ሜትር አርቃ ጣለችው:: በዚህ ጊዜ እንደ ፈርዖን ሴት ልጅ ሆና የተቀበለችው አሜሪካ ነበረች::

እንደ ፈርዖን አገዛዝ የኑሮ ቀንበር ሸክሙ የከበዳት እናቱ፤ የእግሯን ትቢያ አራግፋ ሊባኖስን ለቅቃ ለመሄድ ስትወስን፤ ባትመቸውም ‹‹ሞቴን ከሊባኖስ ጋር›› ያለው፤ ደግሞም ‹‹የቤተሰብ ኃላፊነት አይከብደውም›› በሚል የሚወቀሰው አባቱ ስደት አልገባም ብሎ በዚያው በሊባኖስ ቀረ:: እናቱ ግን አራት ልጆችዋን ይዛ የአትላንቲክ ውቂያኖስን አቋርጣ አሜሪካ ለመሄድ ወሰነች::

 ጁን 25 1895 ዓ.ም አምስት የቤተሰቡ አባላት ሰባት ሽህ አምስት መቶ ኪሎ ሜትር የሚያስጉዛቸውን ስደትን ጀመሩ:: ሰባት ሽህ አምስት መቶ ኪሎ ሜትር በባህር ተጉዘው በኤሊስ ደሴት ካለው የአሜሪካ ኑሮ ጋር ተጋፈጡ:: የፈተናው መልክ እና ይዘት ከመቀየሩ በቀር ህይወታቸው አሁንም ከመከራ አልራቀም:: ጅብራን ቦስተን ሲገባ የ12 ዓመት ልጅ ነበር:: እናቱ ሸቀጥ ነጋዴ ሆነች:: በወቅቱ በአሜሪካ ይኖሩ የነበሩ አረቦች፤ ከጎዳና ንግድ የተለየ የሚሰሩት ነገር አልነበራቸውም:: ስለዚህ ትጉኋ ካሚላ ራህማ፤ ቀን ቀን ሸቀጥ እያዞረች ትሸጣለች፤ ማታ ማታ ደግሞ ልብስ ሰፊ ትሆናለች::

በአሜሪካ የብዙ ስደተኞች ልጆችን ህይወት የሚያቃና በጎ ተግባር የሚሰሩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ነበሩ:: እነዚህ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች፤ ለብዙ ስደተኞች ልጆች በመንግስት ትምህርት ቤት ገብቶ የመማር ዕድል አመቻቹላቸው:: በጎዳና እየተንገላወዱ ዕድሜያቸውን ከማባከን አዳኗቸው:: ጅብራንም በዚህ አጋጣሚ የዕድል በር ተከፈተለት:: ከቤተሰቡ ውስጥ የአስኳላ ትምህርት ያገኘ ካህሊል ጅብራን ብቻ ነው:: ስለዚህ ‹‹ኩዩንሲ ስኩል›› (Quincy School) ከተባለ የወንዶች ት/ቤት ገባ:: ጅብራን ቀደም ብሎ መደበኛ ትምህርት ባለመማሩ የተነሳ፤ እንደ ማንኛውም ስደተኛ ልጅ፤ ደረጃ ባልተሰጠው ክፍል ተመድቦ፤ እንግሊዝኛን ‹‹ኤ›› ብሎ ከመማር ጀመረ:: እንዲሁም በመኖሪያ አካባቢው ከሚገኝ አንድ የስዕል ት/ቤት ተመዘገበ:: የስዕል እና ንድፍ ሥራ፤ ከዕድሜው ማለዳ ጀምሮ (ሊባኖስ እያለ)፤ የያዘው ጥበብ በመሆኑ፤ የአስተማሪዎቹን ትኩረት ለመሳብ ጊዜ አልፈጀበትም::

የአሜሪካን ምድር በረገጠ በሁለተኛው ወር (ሴፕቴምበር 30፣ 1895 ዓ.ም እኤአ) በመንግስት ት/ቤት ተመዝግቦ በጀመረው ትምህርት፤ ከክፍል ጓደኞቹ የላቀ ውጤት አስመዘገበ:: የጅብራን የሥዕል ሥራዎችን የተመለከቱት አስተማሪዎቹ፤ ተውህቦውን አይተው የወደፊት መንገዱን አቀኑለት:: ገና በ12 ዓመቱ፤ ከወደፊት ‹‹የጥበብ ሞግዚቱ›› ከፍሬድ ሆላንድ ደይ (Fred Holland Day) ጋር አስተዋወቁት:: ደይ፤ ተማሪዎቹ በዘመኑ ሰፊ ተቀባይነት ከነበረው የአሳሳል ፈለግ (አንዳንዶች ስዕላዊ ፎቶግራፍ የሚሉት) ጋር ብቻ ሳይሆን፤ ከእንግሊዝኛ ሥነ ጽሑፍም ጋር እንዲተዋወቁ ያደርጋቸው ነበር:: እከሌ ብለን መጥቀስ ባንችልም፤ ከጅብራን ጋር ይማሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች መኖራቸውን የሚጠቁሙ መረጃዎች አግኝቻለሁ::

 ብዙ ነገሮችን በአጭር ጊዜ ለመማር በሚያስችለው ልዩ የአሜሪካ ስርዓተ ትምህርት ውስጥ ለሁለት ዓመት የተማረው ጅብራን፤ ይህን ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ ታላቅ ወንድሙን እና እናቱን ፈቃድ ጠይቆ እሺታቸውን በማግኘቱ ወደ ሊባኖስ ተመለሰ:: ጅብራን ካህሊል ጅብራን የተወለደባት እና የህይወት ጉዞን የጀመረባት ሊባኖስ ለሚሰራቸው ሥራዎች ነሻጣ እንደሆነች እስከመጨረሻው ዘልቃለች:: ጅብራን በስደት ወደ አሜሪካ ከመምጣቱ በፊት የህጻንነት ዘመኑን ያሳለፈባት ሊባኖስ፤ በህይወቱ ከፍተኛ አሻራ ያሳረፈች ናት:: ጅብራን ወደ ሊባኖስ የተመለሰው፤ የአፍ መፍቻ ቋንቋውን እና አረባዊ ባህሉን አደላድሎ የማወቅ ዕድል ለማግኘት ነበር:: እዚያም ሄዶ ከ1897 እስከ 1901 ዓ.ም (እኤአ) ድረስ በሊባኖስ መዲና ቤሩት በሚገኘው ‹‹መድረሳ አል ሂክማ›› ወይም ‹‹ደብረ ጥበብ›› (School of Wisdom) በተባለ አንድ ት/ቤት፤ ዓለም አቀፍ ህግ፣ ህክምና፣ ሙዚቃ እና ታሪከ-ሐይማኖት የተካተቱበትን ትምህርት (ኮርስ) ሲማር ቆየ:: በዚህ ጊዜ ‹‹ሃላ ዳኸር›› (Hala Daher) ከተባለች የ22 ዓመት ወጣት ጋር ፍቅር ጀማምሮት ነበር::

ጅብራን ብዙ ጓደኛ አልነበረውም:: ራሱን በትምህርት ብቁ ለማድረግ የሚተጋ ተማሪ ነበር:: ኮሌጁ በሚያካሄደው የግጥም ውድድር አሸናፊ ሆኖም ለመሸለም በቅቷል:: በዚህ የኮሌጅ ትምህርቱ ያጠናቸው የአረብ ፈላስፎች እና ገጣሚዎች ስሜቱን ገዝተውት ነበር:: አል ፋሪድ አቡ ዋስ እና አል ሙታናቢ የተባሉ ቀደምት ኢስላማዊ ገጣሚዎችን ተዋወቀ:: ኢብን ሲና እና ኢብን ካሀልዱን ከተባሉ ኢስላማዊ ፈላስፎች ሥራ ጋር ተገናኘ:: ካሃንሳ ከተባለች ድንቅ አረባዊት ሴት ገጣሚ ሥራ ጋር ተገናኝቷል:: በዚህ ኮሌጅ ያስተማሩት አቡነ የሱፍ ሐዳድ የተባሉ መምህሩ፤ የጅብራን ንቁ እና ለውጥ ፈላጊ (ዳይናሚክ) ነፍስ፤ እንዲሁም አመጸኛ እና ጥልቅ ህሊናው አስቀድሞ ታይቷቸው ነበር:: በ18 ዓመቱ ‹‹ደብረ ጥበብ›› በከፍተኛ ማዕረግ ተመርቆ ከወጣ በኋላ፤ በ1899 ዓ.ም አካባቢ ‹‹እውነቱ›› (‹‹Al- Hakikat›› –The Truth) የተባለ የፍልስፍና እና የሥነ ጽሑፍ መጽሔት አርታኢ ሆኖ ጥቂት ጊዜ ሰርቷል::

 የእስልምና ሐይማኖት ስዕል እና ቅርፃ ቅርፅን የሚያበረታታ ባለመሆኑ፤ ሊባኖስን በጦርነት የያዘው የኦቶማን ቱርክ ኢስላማዊ ኃይል፤ የክርስትና ሐይማኖት ተከታይ በነበሩ ሐገሮች የተገነቡ ቤተ ክርስቲያናትን መስጊድ ሲያደርግ፤ ስዕል እና ቅርፃ ቅርፆችን ያጠፋ ነበር:: ስለዚህ ስዕል እና የቅርፃ ቅርጽ ጥበብ በኢስላማዊ ሐገሮች ጨርሶ ጠፍቷል:: ነገር ግን የካህሊል ጅብራንን ህይወት አቅጣጫ አዲስ ጎዳና ያስያዘው የስዕል ሥራው ነበር::

 ጅብራን ከሊባኖስ እንደ ተመለሰ በዕድሜ ዘመኑ ሁሉ ካልተለየችው ‹‹ጠባቂ መልዐኩ›› ከምትሰኘው ሜሪ ሐስኬል ጋር የመተዋወቅ ዕድል አገኘ:: ግን በጅብራን ህይወት ከባድ የሚባለው ዘመን የተከሰተው በዚሁ አካባቢ ነበር:: በ1903 ዓ.ም ሁለት ውዶቹን አጥቷል:: ጅብራንን በስድስት ዓመት የሚበልጠው፤ አሜሪካ ከሄዱ በኋላ ቤተሰቡን በብዙ መደጎም የጀመረው፤ የካህሊል ጅብራን ወንድም (የእናቱ ልጅ) ጴጥሮስ ሐና አብዱልሰላም ራህማ በ25 ዓመቱ (ማርች 12/1903 ዓ.ም) በመኖሪያ ቤቱ ህይወቱ አለፈ:: የቤተሰቡ ዋልታ እና ማገር እርሱ እና እናቱ ካሚላ ራህማ ነበሩ:: ጅብራን የመማር ዕድል ያገኘው በወንድሙ እገዛ ነው ማለት ይቻላል:: ጅብራን ትምህርት እንዲማር እርሱ በቦስተን ጎዳናዎች ቀን እና ሌሊት ይሰራ ነበር:: ጠቀም ያለ ገንዘብም ያገኝ ነበር:: የሥራ ጫናው እና የለከፈው ሳምባ በሽታ ዕድሜውን አሳጠሩት:: በወራት ልዩነት የጅብራን እናት ካሚላ ራህማ ተከተለችው:: አሜሪካ በሄደች በስምንተኛው ዓመት (ጁን 28/1903 ዓ.ም እኤአ) እርሷም በአንድ ሆስፒታል ተኝታ ህክምና በመከታተል ላይ ሳለች ህይወቷ አለፈ::

እነዚህ ሁለቱ የቤተሰቡ አለኝታዎች ሲሞቱ፤ ሸክሙ እና ኃላፊነቱ በማርያና ላይ ወደቀ:: እርሷ ከጅብራን በዕድሜ ሁለት ዓመት ታንሳለች:: ታናሽ እህቱ ማሪያና ልብስ እየሰፋች እና ጥልፍ እየጠለፈች ቤተሰቡ ጎዳና እንዳይወጣ አደረገች:: ዐውደ ርዕይ ለማዘጋጀት የሚሆን ገንዘብ ባይኖራትም፤ ጅብራን ለዐውደ ርዕይ የሚበቃ ስብስብ እስኪኖረው ድረስ ጠንክሮ የስዕል ሥራውን እንዲስል ታበረታታው ነበር:: እርሱም ‹‹ማርያና ለእኔ የነበራት ጥልቅ ፍቅር ባይገታኝ ኖሮ፤ እኔም ሟች ዘመዶቼን በፍጠነት እቀላቀል ነበር›› በማለት ውለታዋን ይዘክራል::

 ሆኖም ጅብራን ተስፋ የሚሆን ሰው አላጣም:: ‹‹ጠባቂ መልዐኩ›› ሜሪ ኤልዛቤት ሐስኬል (Mary Elizabeth Haskell 1873-1964) እና የጅብራን ‹‹ፋና ቤት›› የሚባለው ፍሬድ ሆላንድ ደይ አለኝታ እና ተስፋ ሆኑት:: ጅብራን ከተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ፈለጎች ጋር ባስተዋወቀው በፍሬድ ደይ እገዛ አድርጎለት፤ ጅብራን ስዕሎቹን በቦስተን አንድ ዐውደ ርዕይ (ኤግዚቢሽን) ለማቅረብ ቻለ:: ‹‹ስዕል ሸጬ ገንዘብ አገኛለሁ›› በሚል ተስፋ ጠንክሮ ይሰራ የነበረው ጅብራን፤ በመጀመሪያው ዐውደ ርዕይ ያቀረባቸው የስዕል ሥራዎቹ ተቃጠሉ:: ሆኖም በ1904 ዓ.ም (እኤአ) በፍሬድ ሆላንድ ደይ ስቱዲዮ ሌላ ዐውደ ርዕይ ባቀረበ ጊዜ፤ ከወደፊት ‹‹ጠባቂ መልዐኩ›› ከከሜሪ ኤልዛቤት ሐስኬል ጋር ተዋወቀ:: ጅብራን ፈረንሳይ ሄዶ ለሁለት ዓመት (ከ1908- 1910 ዓ.ም) ኪነ ጥበብን ለማጥናት፤ ቴክኒኩን ለማሳደግ እና ፍልስፍናውን ለማዳበር የሚችልበት ዕድል የተፈጠረለት በእርሷ እገዛ ነው::

አረባዊው (ምሥራቃዊው) ዓለም፤ በጠቅላላው ለዓለም፤ በተለይም ለአሜሪካ ያበረከተው የሊባኖሱ ሕጻን የጥበብ ጎዳናው ተመቻቸለት:: ስለዚህ ምሥራቅን ከምዕራብ የማስታረቅ ትግሉን ጀመረ:: በኪነ ጥበብ ሥራዎቹ ዓለም አቀፍ ዝናን ያተረፈው ጅብራን ካህሊል ጅብራን፤ ደራሲ፣ ፈላስፋ፣ ባለቅኔ፣ ሰዓሊ፣ የሙዚቃ ድርሰት ፀሐፊ፣ ሒዩማኒስት እና የሴቶች እኩልነት አቀንቃኝ ሆኖ በዓለም ታወቀ::

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top