ከቀንዱም ከሸሆናውም

ሚሊየነሮቹ አክተሮች

መቼም እስከ ዛሬ የምናውቃቸው እነ ቦቢ፣ ውርዬና ኩኩ ቤት የሚያደምቁ፤ ግቢ የሚያሞቁና በተሰጣቸው የስራ ድርሻ ተሰማርተው ባለቤቶቻቸውን የምያገለግሉ መሆናቸውን ነው:: እነ ቦቢ አሁን አሁን ክብር አግኝተው ስለመብታቸውም መወራት ተጀመረ እንጂ ስማቸውን በራሱ እንደ ስድብ ስንገለገል ዘመናት ተቆጥሯል::

 በአገራችን “ውሻ” ማለት “ልክስክስ”, “የማይረባ”, “ወራዳ” አይነት ተደርጎ ሲቆጠር ኖሯል:: አሁንም ቢሆን ይሄ አስተሳሰብ ከበርካቶቻችን አዕምሮ አልተፋቀም:: እነ ኩኩንም ቢሆን እንቁላላቸውንና ስጋቸውን ቅርጥፍ አድርገን እየሰለቀጥን ነገር ግን “ዶሮ ብታልም ጥሬዋን” እያልን ስናፌዝባቸው ኖረናል:: እነውሮንም እንዲሁ “ ፀጉራቸው ይሰነፍገናል፣ አስም ያሲዘናል”፣ “አይነ ምድራቸው ይሸታል” ወዘተ እያልን ስናርቃቸው ኖረናል:: ባደጉ አገራት ግን ያላቸው ክብር እኛ ለልጆቻችን ከምንሰጠው ክብር በልጦ መገኘቱ ተስተውሏል። በፊልም ኢንደስትሪ ውስጥ ባላቸው ተሳትፎም ክብርን ብቻ ሳይሆን ቱጃርነትንም ተጎናጽፈውታል።

ጉንተር

ካርሎታ ሊበንስቲን የተባሉ ጀርመናዊት እመቤት እአአ በ1991 ከዚህ አለም በሞት ከተለዩ በኋላ ከሁሉ አስበልጠው ለሚወዱት ውሻቸው ጉንተር 106 ሚሊየን ዶላር አውርሰውታል::ጉንተር ሀብቱን በተለያዩ ኢንቨስትመንቶች ላይ በማዋል የናጠጠ ሀብታም ለመሆን በቅቷል:: በጣሊያንና በበሃማስ ደሴቶች ቅንጡ ቪላዎች አሉት::የሚገርም ጀት ባለቤትም ነው:: በቅርቡም በአሜሪካ ሚያሚ በ7.5 ሚሊዮን ዶላር በባህር ዳርቻ የሚገኝ መዝናኛ ስፍራን የግሉ አድርጓል:: ጉንተር በጣም የሚንከባከቡት የግሉ ሰራተኞችና አሽከሮች አሉት:: የጉንተር ሀብት አሁን ላይ 375 ሚሊዮን ዶላር ደርሷ::

ኦራንጂ

ኦራንጂ የሚገርም የትወና ብቃት ያላት አሜሪካዊት ድመት ስትሆን ስለችሎታዋ ብዙዎች ይመሰክራሉ:: በተለይም “Breakfast at Tiffany’s,” በተባለው ፊልም ላይ ብቁ ተዋናይነቷን አሳይታለች:: ይህቺ ድመት በወቅቱ ለኦስካር ሽልማት የታጨች ቢሆንም በፊልሙ አለም እንሰሳ የኦስካር ሽልማት አሸናፊ የሚሆንበት አሰራር ስሌለ ሽልማቱ አመለጣት እንጂ ለሽልማቱ ታስባ ነበር:: ይሁንና የአመቱ ምርት ተዋናይ ተሰኝታለች በወቅቱ::

ጎጊ

ጎጊ የተሰኘችው ዶሮ ከባለቤቶቿ ባገኘችው የ15 ሚሊዮን ዶላር ውርስ አንቱ የተሰኘች ቱጃር ሆናለች::

ግሩምፒ

ከወደ አሜሪካ የሆነችው ግሩምፒ የተሰኘችው ድመት ደግሞ በአንድ ወቅት ማስታወቂያ ከሰራች በኋላ ታዋቂና ዝነኛ ሆና አዱኛ በአዱኛ ሆናለች:: ዛሬ ላይ የ99.5 ሚሊዮን ዶላር ባለቤት ናት:: አብዛኛዉን ሀብቷን የፊልም ኢንዱስትሪ ላይ በማዋል የቀለጠች ነጋዴነቷን አስመስክራለች::

ፖፕ ኮርን

ፖፕ ኮርን ዝነኛ አሜሪካዊ ፈረስ ነው:: በተወነባቸው ፊልሞች ላይ በአብዛኛው ተጋላቢ ሆኖ ነው የሰራው::ደንባራ ፈረስ ሆኖም ይተውናል:: በሀይለኛው እየደነበረ ከመኖሪያ ግቢው ሲወጣም ይታያል:: ፖፕ ኮርን በአሁኑ ወቅት በጡረታ ላይ ይገኛል::

ኡኖ

ኡ ኖ የተባለችው ውሻ በሆሊውድ የፊልም መንደር ታዋቂ ናት:: በተለይም “Harry Potter and the Half- Blood Prince” በተሰኘው ፊልም ላይ ባሳየችው ድንቅ የትወና ብቃቷ አድናቆትን አትርፋለች:: ኡኖ የፊልም ተዋናይ ከመሆኗ በፊት እጅግ አስቸጋሪ አመል የነበራት ውሻ እንደነበረች ባለቤቶቿ ይናገራሉ::ሆኖም የፊልም ተዋናይ ከሆነች በኋላ ግን አመለሸጋና ጨዋ ሆናለች ሲሉ ያሞግሷታል::

ማለትሰ ቴሪየር

አሜሪካዊቷ እመቤት ሊዮና ሄልምስሌይ እአአ በ2008 ከዚህ አለም በሞት ሲለዩ “ማለትሰ ቴሪየር” ለተባለች ታማኝ ውሻቸው 12 ሚሊዮን ዶላር አሸክመዋታል:: ግለሰቧ መቼም ወገን ዘመድ ወይም የቅርባቸው የሆነ ሰው አያጡም:: ነገር ግን እጅግ ለሚወዷትና ታማኛቸው ለሆነችው ውሻቸው ይህን ያህል ተዝቆ የማያልቅ ረብጣ ዶላር ተናዘውላት እየተንደላቀቀችበት ትገኛለች:: ይህ የወይዘሮዋ ድርጊት በብዙ ሰዎች ዘንድ አልተወደደም:: ተቃውሞም ገጥሞታል::ምነው የሰው ልጅ እያለ እንዴት ይህን ያህል ገንዘብ ለእንሰሳ? በማለት የሞገቱም አልጠፉም::

የኦስካር እጩዎቹ ጀግኖች

ኡጊ

በአሜሪካው ዝነኛ የፊልም መንደርና ኢንዱስትሪ ሆሊዉድ ውስጥ ትልልቅ ስም ያላቸው ፊልሞች ላይ በብቃትና በንቃት የተወኑ አንቱ የተባሉ እንስሳትን ላስተዋውቅዎት ነው:: እነኚህ እንስሳት ለኦስካር እስከመታጨት ደርሰዋል:: በፊልሙ ላይ የተሰጣቸውን ድርሻ በሚገባ የተወጡና የተወኑ ናቸው:: እንዴት አጠኑት ? እንዴትስ ሊገባቸው ቻለ? እንዴትስ ውጤታማ ሆኑ? የሚለው ጥያቄ ግን የሁላችንም ነው:: ኡጊ የተባለው ውሻ “Water for Elephants,” በተሰኘው ግሩም ፊልም ላይ ከነ ሮበርት ፓቲንሶን እና ሬሲዊተርስፑን ጋር ተውኗል:: በዚህ ፊልም ላይ ቀልጣፋ ሌባ በመሆን ሰርቷል:: በዚህ ውብ ትወናው ለኦስካር ሽልማት ታጭቶ ነበር::

ቶቶ

ባለቤትነቷ የአሜሪካዊው ካርል ስፒትዝ የሆነቺው ቶቶ የተባለችው ውሻ በሆሊውድ መንደር ዝነኛ ተዋናይ ናት:: ቶቶ በተለይም “The Wizard of Oz” በተባለው ፊልም ላይ በመተወን ድንቅ ብቃቷን አስመስክራለች:: በዚህ ፊልም ላይ ባሳየችው ብቃት ለኦስካር ሽልማት ታጭታ ነበር:: ቶቶ በእርግጥ 16 ፊሊሞች ላይ የተለያየ ገፀባህሪ ተላብሳ ተጫውታለች\::

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top