ታሪክ እና ባሕል

ለውጥ፣ ባህል፣ ፖለቲካና ስምሙነት (አዳኘቴሽን)

የአዝጋሚ ለውጥ ንድፈ-ሃሳብ አባት ተብሎ የሚታወቀው ሊቅ ቻርልስ ዳርዊን፣ ‹‹ከፍጥረታት ሁሉ ዘሩን ከጥፋት ታድጐ በህይወት ለማቆየት የሚችለው ጠንካራው ሳይሆን ራሱን ከአካባቢውና ከሁኔታዎች ጋር አስማምቶ መኖር የቻለው ነው›› ብሏል ተብሎ ብዙ ጊዜ ይጠቀሳል:: ነገር ግን ዳርዊን ይህንን ሃሳብ በታወቀው መጽሃፉ (ዘ ኦሪጂን ኦፍ እስፒሽስ…) ውስጥ አስፍሮት አሊያም የሆነ ሌላ ስፍራ ተናግሮት እንደማይታወቅ በጥናት ተረጋግጧል:: ይልቁንም ከላይ በጥቅሱ የሰፈረውን ሃሳብ የተናገረው የሉዚያና ስቴት ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስ ኘሮፌሰር የሆነው ሊኦ ሜጊንሰን ነው:: ሜጊንሰን ይህን ሃሳብ የገለጸው በ1969/70 ዓ.ም በሳውዝዌስተርን የማህበራዊ ሳይንስ ማህበር ስብሰባ ላይ ነበር:: ከሜጊንሰን ንግግር ውስጥ የሚከተለው ይጠቀሳል፡-

እርግጥ ነው፤ ለውጥ የተፈጥሮ መሰረታዊ ህግ ነው:: ነገር ግን በጊዜ ሂደት የሚከሰተው ለውጥ በግለሰቦችም ይሁን በተቋማት ላይ ጫና የሚያሳርፈው በተለያየ መልክ ነው:: በዳርዊን ጥናት መሰረት ከፍጥረታት ሁሉ ህይወቱን ከጥፋት ታድጐ ከሞት የሚድነው አዋቂው ወይንም ጠንካራው ሳይሆን ራሱን ከአካባቢውና ከሁኔታዎች ጋር ማስማማት የቻለው ነው:: ይህንን ተፈጥሮአዊና ሳይንሳዊ ሃቅ ወደ እኛ ስንወስደው ከጥንት ዘመን ጀምሮ እስካሁን ድረስ ሳይከስሙ የዘለቁ የሰው ልጅ ስልጣኔ ውጤቶች የተፈጥሮ አካባቢን፣ የማህበራዊ፣ የፖለቲካ፣ የሞራልና መንፈሳዊ ለውጦችን ተቋቁመው፤ ራሳቸውንም ከለውጦቹ ጋር አዋህደው የተገኙት ብቻ ናቸው::

 ተፈጥሮ ውስጥ የምናየው ራስን ከለውጥ ጋር አስማምቶ የመዝለቅ ሁኔታ ረዥም/ቢሊዮን ዓመታትን የሚወስድና እጅግ አዝጋሚ፣ ሆን ተብሎ ታስቦበት በምርጫ የማይደረግ፣ የሞራል ግዴታም የሌለበት ነው:: በሰው ልጆች ህይወት የለውጥ ሂደት ውስጥ እነኚህ ሁኔታዎች የሉም:: ማህበረሰብ ራሱን ከለውጥ ጋር አስማምቶ ለመኖር የግድ ጭካኔ የተመላበትን መንገድ መምረጥ፣ ሞራላዊ ግዴታዎችን አሽቀንጥሮ መጣልና በረዥም የለውጥ ሂደት ውስጥ ማለፍ አይጠበቅበትም:: የሰው ልጅ በለውጥ ሂደት ውስጥ ዘልቆ ለመውጣት ከፈለገ ሆን ብሎ፣ በንቃት መክሮና ዘክሮ፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም በሁኔታው ላይ ተስማምቶ፤ እንዲሁም በፍጥነት ማድረግ ይኖርበታል::

እውቁ የኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ አምደኛና የበርካታ መጻህፍት ደራሲ የሆነው ቶማስ ፍሬይድማን፣ ‹‹ስላረፈድክ አመሰግናለሁ›› (Thank You for Being Late) በተሰኘው መጽሃፉ ማህበረሰብ በለውጥ ሂደት ውስጥ ራሱን አስማምቶ ለመዝለቅ እንዲረዳው የሚከተሉትን አምስት ስትራቴጂዎች የመጠቀም ችሎታ ሊኖረው ይገባል ይላል::

 1. ኃያል የኢኮኖሚና ወታደራዊ አቅም ካላቸው ባዕዳን ጋር በሚጋፈጡ ጊዜ በሽንፈት ወላልቆ ከመቅረት ይልቅ በጥበብ ራስን ከሁኔታው ጋር የማስማማት ችሎታ፣

 2. ብዝሃነትን አካትቶ የመያዝ አቅም፣

3. የራስን ችግር ለመፍታትም ሆነ መጪውን ዘመን ለመግራት ቅድሚያ ሃላፊነትን የመውሰድ ችሎታ፣

4. በሀገርና በመንደር መካከል ያለውን ሚዛን በትክክል የመጠበቅ ችሎታ፣

 5. በዚህ በተጣደፈው የቴክኖሎጂ ዘመን ፖለቲካንና ችግር የመፍታት ጥበብን በማይታክት፣ በተለያየ፣ በተዛነቀና ባልገረረ የአስተሳሰብ ዘይቤ (ማይንድ ሴት) የማስተናገድ ችሎታ

 አንድ ማህበረሰብ እነኚህን የለውጥ ሂደት የመግሪያ ጥበቦች ለመላበስ የሚወስድበት ጊዜ የሚወሰነው በሚያራምደው ፖለቲካ፣ በተዋቀረበት ባህልና ባዋቀረው የአመራር ጥበብ ነው:: ባህል ማህበረሰብ ፖለቲካዊ ለሆኑ ጉዳዮች የሚሰጠውን ምላሽ ይወስናል፤ አመራሩና ፖለቲካውም መልሶ ባህል ላይ ጉልህ ተጽዕኖ ይኖረዋል::

ቢዝነስዲክሽነሪ.ኮም የተሰኘ የድረገጽ መዝገበ ቃላት ባህልን እንደሚከተለው ይተረጉመዋል::

 ባህል በማህበረሰብ አባላት መካከል፤ እንዲሁም በማህበረሰብ አባላትና በተፈጥሮ ከባቢ መካከል በሚደረግ መስተጋብር ሳቢያ ለሚፈጠሩ ሁኔታዎችና ተግዳሮቶች ምላሽ የሚሰጥበት አግባብ (ፓተርን) የሚቀረጽበት፣ የሚጎለብትበትና እንደ አዲስ የሚፈጠርበት ሂደት ነው:: እነኚህ ምላሾች ለአስተሳሰብ፣ ለአመለካከት፣ ለስሜትና ለድርጊት ትክክለኛ ዘይቤዎች እንደሆኑ ስለሚታመንባቸው አዳዲስ የማህበረሰቡ አባላት እንዲያውቋቸውና ከትውልድ ትውልድ እንዲቀባበሏቸው ይደረጋል:: ባህል ቅቡሉንና ተቀባይነት የሌለውን፣ አስፈላጊውንና የማያስፈልገውን፣ ትክክለኛውንና ስህተቱን፣ የሚያገለግለውንና የማያገለግለውን ይወስናል::

 ይሁን እንጂ ባህል የማይቀየርና ሊቀየር የማይችል የተቸከለ ነገር አይደለም:: ባህል ሊቀየር ይችላል፤ ይህም ሲሆን ይስተዋላል:: የባህል ለውጥ በሁኔታዎች አስገዳጅነት፣ ለመኖር ባለ ጽኑ ፍላጎት፣ አንዳንድ ጊዜም በፖለቲካ መሪዎች የለውጥ መርሃ ግብር ሊመጣ ይችላል:: ሟቹ የአሜሪካ ምክር ቤት አባል ዳንዔል ፓትሪክ ሞይኒሃም እንዳሉት ወግአጥባቂ (ኮንሰርቫቲቭ) በሆነው አመለካከት የህብረተሰብን ስኬት የሚወስነው ፖለቲካ ሳይሆን ባህል ነው:: ለዘብተኛ (ሊብራል) በሆነው አስተሳሰብ ደግሞ ፖለቲካ ባህልን ሊቀይር ይችላል፤ ከመጥፋትም ያድነዋል::

መሪ ወይንም አመራር የለውጥ አማጭ ሊሆን እንደሚችል ብዙ ማብራሪያ የሚያስፈልገው ጉዳይ አይደለም:: የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የአመራር ጥበብ ሊቅ ኘሮፌሰር ራልፍ ሄይፌትዝ ‹‹የመሪ ሚና በሁኔታዎች መቀያየር የተነሳ የህብረተሰብ ሰላምና ብልጽግና አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ሰዎች እውነታን እንዲጋፈጡና ለውጥ እንዲያካሂዱ ማነሳሳት (ሞቢላይዝ ማድረግ) ነው›› ይላል:: የተፈጥሮ፣ የቴክኖሎጂና ማህበራዊ ለውጦች በፍጥነት እውን በሚሆኑበት በዚህ ዘመን የአመራር ሃላፊነት ትክክለኛውን ባህላዊ አመለካከትና የፖሊሲ አማራጮች ማቅረብ፣ መኮትኮትና ማስረጽ ነው:: የባለርዕይ መሪዎች ትልቁ ጉልበት ወይንም ስልጣን በምስቅልቅል ሁኔታ ውስጥ ህብረተሰብና ባህል ራሳቸውን ከተለወጠው ሁኔታ ጋር አጣጥመው ፈር ይዘው እንዲዘልቁ ማስቻል ነው:: ማንዴላ በደቡብ አፍሪካ ያደረጉት ይህን ነበር:: በእኛም ሀገር ጠ/ሚ አብይና ጓዶቻቸው የሚያደርጉት ጥረት ከዚህ የተለየ አይደለም:: ከግል ታሪክ፣ ከትውልድ አካባቢና ከፖለቲካ ደጋፊዎች ከፍ ብሎ ተቀናቃኞችንም ደጋፊዎችንም የሚያስደምም መሪ ከማግኘት በላይ የተሻለ ነው የሚባል የባህል ለውጥ የለም::

 የባለቤትነት ባህል ያስፈልገናል

 በማህበረሰብ ውስጥ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ የባለቤትነትን ስሜት ወይንም አመለካከትና አስተሳሰብን ማጎልበት ከቀውስ የማገገም አቅምን (ሪዚሊየንስ) ይፈጥራል ብሎም ያጠናክራል:: ስቴፋኒ ሳንፎርድ የተባለች የትምህርት ኤክስፐርት እንደምትለው የባለቤትነት አስተሳሰብ ብዙ ነገሮችን ለማስተካከል የሚረዳ አንድ ዘይቤ ሲሆን፣ እዚያው-ሳለም ሌሎች ብዙ ጉዳዮችን ለማስተካከል ሁኔታዎችን መልሶ ቀላል ያደርጋቸዋል:: ‹‹ዜጎች ስለሀገራቸው የባለቤትነት ስሜት ሲኖራቸው፣ መምህራን ስለሙያቸው የባለቤትነት ስሜት ሲኖራቸው፣ ተማሪዎችም ስለትምህርታቸው የባለቤትነት ስሜት ሲኖራቸው፤ ከመጥፎ ነገር ይልቅ ብዙ መልካም የሆኑ ነገሮች እውን ይሆናሉ::… በተገላቢጦሽ የባለቤትነት ስሜት በሌለበትና ዜጎች የተከራይነት ወይንም የአልፎ-ሂያጅነት አስተሳሰብ በተላበሱበት ጊዜ ከመልካም ነገሮች ይልቅ ብዙ መጥፎ ነገሮች ይከሰታሉ››::

አንድ ሰው በአንድ ጉዳይ ላይ የባለቤትነት ስሜት ካለው ከዚያ ሃላፊነት በላይ ከእርሱ ብዙ መጠበቅ ከባድ ነው:: ስለ አንድ ጉዳይ ባለቤት ስንሆን ሁኔታው ያሳስበናል፣ ትኩረት እንሰጠዋለን፣ የአደራ ተቀባይነት ስሜት ይሰማናል፤ ስለሆነም ስለወደፊቱ እንጨነቃለን:: ከአጭር ጊዜ ይልቅ ስለመጪው ረዥም ዘመን፣ ከታክቲክ ይልቅ ስለ ስትራቴጂ እንድናስብ የሚያደርገን በአንድ ጉዳይ ላይ ያለን የባለቤትነት ስሜት ነው:: ‹‹በዓለም ታሪክ የተከራየውን መኪና የሚያጥብ የለም›› የሚል አባባል አለ::

 ከፍ ሲል የጠቀስነው የኒው ዮርክ ታይምስ ታዋቂ ዓምደኛ፣ ቶማስ ፍሬይድማን፣ በየካቲት 2011 (እ.አ.አ) የካይሮውን የጣህሪር አደባባይ ህዝባዊ አመጽ ለመታዘብ/ለመዘገብ በቦታው ነበር:: የካይሮው አመጽ ዝንተ- ዓለም ለዴሞክራሲ ብቁ አይደላችሁም

“የሀገራችንን መልካም መጻዒ ዕድል የምንመኝ ሁሉ የለውጡን ሂደት ለመደገፍ ወደኋላ የምንል አይመስለኝም:: ለለውጡ የተስማማ የአስተሳሰብ ዘይቤ እንዲኖረን ያስፈልጋል”

እየተባሉ በመሪዎቹ እየተነገራቸው ሲናቁና ሲዋረዱ ለኖሩት ግብጻውያን ፍርሃታቸውን አሽቀንጥረው ጥለው ሃይልና ስልጣንን ለራሳቸው-በራሳቸው የወሰዱበትና ነፃነታቸውን ዳግመኛ ላለመነጠቅ የወሰኑበት ነበር:: የጣህሪሩ አመጽ ውጪያዊ ምክንያቶች ያልገፉት ፍጹም ሀገር-በቀልና የማይሸነፍ ዓይነት እንደነበር ፍሬይድማን በአጽንዖት ይገልጻል:: ‹‹የካቲት 9 ዕለት ጠዋት ጣህሪር አደባባይ ነበርኩ:: በርካታ ወጣቶች የኘላስቲክ ጓንት አጥልቀው የአካባቢውን ቆሻሻ እየሰበሰቡ ጥቁር የላስቲክ ከረጢት ውስጥ እየከተቱ ነበር:: ለምዕተ ዓመታት ግብጻውያን ሀገራቸውን ከነገስታት፣ ከአምባገነኖችና ከቅኝ ገዢዎች የተከራይዋት በሚመስል መልክ ይኖሩባት ስለነበር ሊያጸዷት ፍላጐቱም የነበራቸው አይመስልም:: አሁን ግን ፍላጐት አላቸው:: በቅርብ እርቀት ‹ጣህሪር– በግብጽ ውስጥ ብቸኛው ነፃ ስፍራ› የሚል የቅስት ጽሁፍ ተሰቅሏል:: ቀስ ብዬ ቆሻሻ ከሚሰበስቡት ወጣቶች ወደ አንዱ ጠጋ አልኩና አንዳንድ ጥያቄዎችን መጠየቅ ጀመርኩ:: ወጣቱ ከሪም ቱርኪ ይባላል፤ በውበት ሳሎን ውስጥ የሚሰራ የ23 ዓመት ግብጻዊ ነው:: ‹ለምንድነው ለዚህ የበጎ ፈቃድ ስራ ፍቃደኛ ሆነህ ቆሻሻ የምትሰበስበው?› ብዬ ጠየቅሁት:: በተሰባበረ እንግሊዝኛ፣ ራሱን ለመግለጽ እየተጨነቀ ‹ይህ የእኔ መሬት፣ የእኔ ሀገር፣ የእኔ ቤት ነው:: ሙባረክ ከስልጣን ከተወገደ መላውን ግብጽ አጸዳለሁ› አለኝ››::

በእርግጥ የባለቤትነት ስሜት የራስ የሆነ ግብም አለው:: ከውድቀት አገግሞ ዳግም ለማንሰራራትና ጸንቶ ለመቆም ዋናው ምክንያት እሱው ነው:: ‹‹አንድን ትልቅ ጉዳይ/ ችግር ለመፍታት አስበህ ስራ ከጀመርክና ከተሳካልህ ዝናውን ለራስህ ብቻ ከመውሰድ ይልቅ መጋራት ብሎም ማብዛት ተገቢ ነው:: ውጤታማ የሆኑ አሰራሮች ሁሉ መልካም ስምንና ዝናን ጠቅልለው ለአንድ ሰው ብቻ የሚሰጡ ሳይሆን ከሌሎች ጋር የሚያጋሩና የሚያበዙ ናቸው››::

ሀገራችን በለውጥ ላይ ነች:: ከፍ ሲል ያነሳናቸው ሃሳቦች በሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ቀጥተኛ ትርጉም አላቸው:: የሀገራችንን መልካም መጻዒ ዕድል የምንመኝ ሁሉ የለውጡን ሂደት ለመደገፍ ወደኋላ የምንል አይመስለኝም:: ለለውጡ የተስማማ የአስተሳሰብ ዘይቤ እንዲኖረን ያስፈልጋል:: ከፖለቲካ መሪዎቻችንና ከለውጡ ግንባር ቀደም አራማጆች ለአርአያነት የሚበቁ ባህርያትን እንጠብቃለን:: ውስን ይሁኑ እንጂ በወጣቶቻችን ዘንድ የሚታዩት የባለቤትነትና የተነሳሽነት ስሜቶች ደስ የሚያሰኙ ናቸው:: አልፎ አልፎ በሚታዩት ያልተገሩ ስሜቶችና ተግባራት መልካም ባህርያቱና አበረታች እንቅስቃሴዎቹ ተደነቃቅፈው መቅረት የለባቸውም::

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top