ስርሆተ ገፅ

ፎቶ- የማታ የማታ … እንዲያው በዝምታ ይናገራል ታሪክ ፤ ያመጣል ትዝታ።

የግለሰቦች ታሪክ ተሰባስቦ ሲሰነድ ነው የአገር ታሪክ የሚሆነው። ይብዛም ይነስ እያንዳንዱ ሰው የራሱ ታሪክ አለው። ታሪኩ ከሀገርና ከህዝብ ጥቅም ጋር ያለው ቁርኝት ከፍ ሲል ደግሞ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገር ምክንያት ይሆናል። እናም የታሪክ አጥኚዎችና ጸሐፍት እንዲህ ያሉ ሰዎችን ታሪክ ዘመን ለማሻገር ያጓጓቸዋል። «የአዲስ አበባ ትዝታዎች» በሚል ርዕስ በአይነቱ ለየት ያለና አዲስ አቀራረብን ይዞ የመጣ አንድ መጽሐፍ ለህትመት በቅቷል። 235 ገጾች ያሉት ይኸው መጽሐፍ የግለሰቦችንና የተለያዩ ቤተሰቦችን ታሪክ በፎቶግራፎች አካቶ የያዘ ነው። ሰሞኑን በአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሴስ የፎቶግራፍ ዓውደ ርዕይ በተከፈተበት ዕለት ነው መጽሐፉ የተመረቀው። ለ3 ሳምንታት ከሌሎች የፎቶግራፍ አቅራቢ ተሳታፊዎች ጋር ለጉብኝትም በቅቷል። መጽሐፉን ያዘጋጁት ወንጌል አበበ፣ ናፍቆት ገበየሁ፣ ፍሊፕ ሹት ናቸው። ለመሆኑ የመጽሐፉ ይዘት ምን ይመስላል? በይዘትና አቀራረቡ ምን ልዩ ነገር ታየበት? ጠቀሜታውስ? እነዚህን ጥያቄዎች መነሻ አድርገን በእግረ መንገድ ግላዊ የሕይወት ጉዞዋን እንድታወጋን የ23 ዓመቷን ስኬታማ ወጣት ወንጌል አበበን ጋብዘናታል።

ታዛ፦ በእርግጥ መጽሐፉ በአቀራረቡ አዲስ ይመስላል። ለመሆኑ መጽሐፉን  ለማዘጋጀት ምን አነሳሳችሁ?

 ወንጌል፦ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ትምህርት ስንማር የክፍል ጓደኛችን… ኡጋንዳ ውስጥ አንድርያስ በተባለች ሴት ታሪክ ላይ የተመሰረተ “ታሪክ በሂደት ውስጥ” (History in progress) የሚል ርዕስ ያለው የመመረቂያ ፕሮጀከት የሆነ አንድ መጽሐፍ አምጥቶ አሳየን። ስራው የአንድ ሰው ታሪክ በፎቶ ብቻ የተገለጸበት ነው። የፎቶ መግለጫ (caption) የለውም። እዚያው ተወያየንበት። ሃሳቡን አዳብረን በአገራችን እንድንሰራ ተነጋገርን። ጉዳዩ ሰፊ ሆነብን። ኢትዮጵያን በፎቶ ሙሉ ለሙሉ መግለጽ ይከብዳል። ስለዚህ ለምን በአዲስ አበባ አንወሰንም ብለን ተነሳን። በሂደት አሳካነው። ከአራት ዓመት በኋላ ልክ 2009 ዓ.ም ትምህርታችንን እንደጨረስን ነው ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሰጥተን ከዋና ስራችን በተጓዳኝ በጋራ ሰርተን ያሳከነው።

ታዛ፦ ፎቶዎችን በምን መልክ ነው ያሰባሰባችኋቸው?

ወንጌል፦ ከቤተሰቦቻችን ጀመርን፣ ዘመዶቻችን ጋ ሄድን፣ ወደ ጎረቤት ከዚያም አካባቢያችንን እየቃኘን ከተማዋን አካለልን። ሰዎች ድሮ የተነሷቸውን ፎቶግራፎች ከተቻለም ከነ ታሪካቸው እንዲሰጡን ነው የምንጠይቃቸው። ፒያሳ፣ ካሳንቸስ፣ ቦሌ፣ መርካቶ፣ መገናኛ፣ የማንሄድበት የከተማ ከልል የለም። በየ መዝናኛ ስፍራዎች፣ በንግድ ሱቆች፣ ቡና ቤቶች ጭምር ገብተን እንጠይቃለን። መጀመሪያ ለመተባበር ያንገራግራሉ። ሌላ ጥቅም የምናገኝበት ይመስላቸዋል። እኛ ግን ሳንሰለች «ለቀጣዩ ትውልድ ታሪክ ለማስቀመጥ እንዲህ ያለ መንገድም አለ» እያልን እናስረዳለን። የገባው ይተባበረናል። እየጠየቅን መረጃ ማሰባሰብ፣ ፎቶግራፎቻቸውንም እየተዋስን በከፍተኛ የጥራት ደረጃ መገልበጥ (scan copy) ማድረግ ጀመርን። በስብስባችን ታዋቂ ሰዎች ላይ አላተኮርንም፤ ማንም ሰው ቢሆን የራሱ ታሪክ ስላለው ያንን ማወቅና ማሳወቅ ነው ፍላጎታችን። ማንነት፣ ባህል፣ እምነት፣ ጀግንነት፣ ጉስቁልና፣ ወዘተ በሁሉም ማህበረሰብ ዘንድም በብዙ አለ። ታዋቂ ሰዎች ያንን ሊወክሉ እይችሉም። እኛ ደግሞ እውነታን ነው ማሳየት የፈለግነው። ሰዎች በአስቸጋሪ ሕይወት ውስጥ እንዴት እንደሚኖሩና ያንን አልፈው ሲገኙ ምን ያህል ሌሎችን እንደሚያስተምሩም ነው በመጽሐፉ የሰበክነው። ስራው ትንሽ አስቸጋሪና ፈታኝ ቢሆንም፤ በማሰባሰቡ ሂደት ከትልልቅ ሰዎች ጋር ተዋውቀንበታል፣ ብዙ ነገርም ተምረንበታል። የሚያሳዝነው ግን አንዳንድ ትላልቅ ሆቴሎችና ሕዝባዊ ተቋማት ታሪክ የሚነግሩበትን ፎቶግራፎች በአግባቡ ሰንደው አለመያዛቸው ነው። አንዳንዶች ምንም የሌላቸው ሲሆን፤ አንዳንዶች ደግሞ በጊዜ ርዝማኔ እና በአያያዝ ወይም በጥንቃቄ ጉድለት ለብልሽት ተዳርገው ነው ያገኘናቸው። ይህ ያሳዝናል።

 ታዛ፦ ማሳተሚያ ገንዘብም ያስፈልጋል። ያስ እንዴት ታለፈ?

ወንጌል፦ መጀመሪያ ከአውሮፓ ህብረት የተወሰነ ብር አገኘን። ልክ እንዳገኘን ጉዳዩን ወደ ሶሻል ሚዲያ ወስደን ማስተዋወቅ ጀመርን። «Vintage Addis Ababa» የሚል ፌስ ቡክ ከፈትን። ስራውን በጥራት ለመስራት ስላሰብን፣ በገንዘብ ብቻ ሳይሆን በሃሳብና ፎቶግራፎችን ጭምር በመስጠት የሚተባበሩንን ለማግኘትና ሌሎች ድጋፎችም እንደሚያስፈልጉን ለማሳወቅ ነው ያንን ያደረግነው። በዚህም ተባባሪዎቻችን በዙ። ዓላማችንን የተረዱ ሁሉ ድጋፋቸው ጨመረ። በእኛ እቅድ ፕሮጀከቱን ለማጠናቀቅ አንድ ዓመት ከግማሽ ይበቃል ብለን ነበር፤ ነገር ግን ተጨማሪ አንድ ዓመት ወስዶብን ነው ያሳካነው። ባሰብነው ደረጃ ለማሳተም ገንዘቡ አልበቃንም ነበር። በአውሮፓ ደረጃ ጥራትን አስበን ስለተነሳን ሂደቱ ቀላል አልነበረም። በገንዘብ ድጋፉ የስዊዘርላንድ እና የፈረንሳይ ኤምባሲም የየራሳቸውን ትብብር አድርገው ነበር፤ ነገር ግን የምንፈልገውን የሚያሳካልን አልሆነም። እናም የገንዘብ እርዳታ ብቻ ከመጠየቅ መጽሐፉ በሕትመት ሂደት ላይ እያለ በኢንተርኔት አማካኝነት አስቀድሞ የመሸጥ ጥበብን ተጠቀምን። ቪዲዮ ሰርተን አሰራጭተን ስለነበር ፈረንጆች፣ ዳያስፖራዎች፣ ታሪክን የሚወዱ ሁሉ ገዙን። በመጨረሻም በጥሩ ጥራት ጀርመን አገር አሳተምነው።

ታዛ፦ መጽሐፉ ስለ ኢትዮጵያውያን ታሪክ ነው የሚነግረን፤ ታዲያ ስለምን በእንግሊዝኛ ቋንቋ ተጻፈ?

 ወንጌል፦ አዎ አማርኛ መሆን እንደነበረበት እናምናለን። መጽሐፉን ስንጀምር ግን አንባቢዎቻችንን (Target audience) ለይተን ነው። በዚህ የጥራት ደረጃ የተሰራን ስራ ለመሸጥም ሆነ ገዝቶ ለማንበብ አቅም የሚኖረው የውጪው ሰው ነው። እኛ የሰራነው የሚነበብ መጽሐፍ ሳይሆን፤ የፎቶ መጽሐፍ ነው። መግለጫ ያለው ፎቶ። ያ በአገራችን አልተለመደም፤ ሰርተን ተጠቃሚ ዘንድ ካልደረሰ ደግሞ ጉዳት አለው። ስለዚህ ነው በመጀመሪያ ዕትም እንግሊዝኛውን ያስቀደምነው። ይህ የእኛ አሰራር በውጪ አገራት የተለመደ ነው። የሆነው ሆኖ ይህንን የፎቶ መጽሐፋችንን ወደ አማርኛ እየመለስነው ነው። በቅርቡ ለማሳተም እቅድ ይዘናል። በየትምህርት ቤቱ መቀመጥ የሚችልበትን፣ በየቤተመጻሕፍቱ የሚገኝበትን ሁኔታ እንፈጥራለን። ደረጃውን ጠብቀን በሽያጭ ግን አቅምን ያገናዘበ እናደርገዋለን። ለዚህ ደግሞ አጋዥ ስለሚያስፈልገን እዚያ ላይ ነው እየሰራን ያለነው። ዋናው ጥረታችን ታሪክን ማስቀመጥ ነው። ዕይታችንን ብናሰፋው የአገር ታሪክ ከግለሰቦች ታሪክ ውስጥ አለ። በዚህ በኩል የበለጸጉ አገራት ተሞክሮን ጥቂቱን እንኳ ብንጠቀም እየጠፋ ያለ ታሪካችንን ለመታደግ ያስችለናል።

ታዛ፦ ለምሳሌ?

ወንጌል፦ ለምሳሌ እኔ እንግሊዝ አገር ሄጄ የግዙፉን የጋዜጠኝነት ተቋም ቢቢሲን የመጎብኘት እድል አግኝቼ ነበር። ያየሁትና የሰማሁት እጅግ የሚያስገርም ነው። እኛ የማናውቀው የራሳችን አገር ታሪክ እነሱ ዘንድ በክብር ተቀምጧል። በጣም ግዙፍ መጋዘን ውስጥ የምስልና የድምጽ ማከማቻ (Archive) አላቸው። የዓለም ታሪክ ነው እዚያ ያለው። ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት ያለ ቅርስ እዚያ አለ። በደረሱበት ቴክኖሎጂ ልክ የቀረጿቸውን በአግባቡ አስቀምጠውታል። አብዛኛው ማንዋል ነው። ወደ ዲጂታል እየቀየሩት ነው። ገና አልጨረሱትም። ለቢቢሲ ትልቁ የገንዘብ ምንጭ ይህ አርካይቭ ነው። ኮፒ ራይቱ የእነሱ ስለሆነ ያከራያሉ፤ ይሸጣሉ። በተለይ አፍሪካዊያን የምስልና የድምጽ ቴክኖሎጂው ዘንድ የደረሱት ዘግይተው ስለነበረ እነሱ በዜናና በፕሮግራም መልክ ቀርጸው የወሰዱት ታሪክ፤ የእነሱ ነው። መልሶ መግዛት ደግሞ የየአገራቱ ነው። እንዲህ ነው ቀድሞ መገኘት። ‘ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር መቁረጥ’ ነው የሚባለው?

ታዛ፦ እንዴት ቢቢሲን ልትጎበኚ ቻልሽ?

ወንጌል፦ የአፍሪካ ወጣቶች እውቀት መካፈያ መድረክ (Young African Thinkers) አማካኝነት ነው። እንግሊዝ ውስጥ ለስብሰባ በኮሜን ዌልዝ አገራት ወጣቶች ኬንያና ዛምቢያን ጨምሮ ተጋበዙ። ኢትዮጵያ የለችበትም፤ ግን እኔ መስራች ስለነበርኩ አብሬ ተጓዝኩ። በእግረመንገድ እዚያ ላሉ ኢትዮጵያውያን በመጽሐፉ ዙሪያ ግንዛቤ ለመስጠት አሰብኩ። እናም እዚያ ከማውቃት መርሃግብር አመቻች (event organizer) ጋር ተነጋገርኩ። የተወሰኑ ሰዎችን አሰባሰበችልኝ። በዚያ ወቅት አንድ ቢቢሲ ውስጥ የሚሰራ ሰው አገኘሁ። በሱ አማካኝነት እንድጎበኝ ሆነ።

ታዛ፦ ሌላስ እቅድ አላችሁ?

ወንጌል፦ በተለያዩ ጉዳዮች ስልጠና መስጠት እንፈልጋለን። በተለይ ከዶከመንት አያያዝ ጋር በተገናኘ። ከአዲስ አበባ ውጪ ያሉ ወጣቶችን አሰልጥነን ይህን እኛ የምንሰራውን አይነት ስራ እንዲሰሩ እንፈልጋለን። ከዚያም ዘለን በአፍሪካ ደረጃም ይህንን ሃሳብ ማስፋት እንፈልጋለን። በቀጣይ ስራችን ፎቶግራፍ የሚሰጡንን እና ታሪካቸውን የሚነግሩንን በቪዲዮ በማስደገፍ የመስራት ዕቅድ አለን። እውነታውንና ፎቶ የተነሱበትን ዘመን ስሜት ለመረዳትም ያግዛል።

ታዛ፦ ይህ እንግዲህ የሦስታችሁ ስራ ነው፤ አሁንም አብራችሁ ለመስራት ዕቅድ አላችሁ? የራሳችሁ ድርጅትስ አላችሁ?

ወንጌል፦ የለንም። አንድ ዓላማና ስሜት ነው ያስተሳሰረን። ሁላችንም የየራሳችን የግል ስራ አለን። ይህንን በተጓዳኝ ነው የምንሰራው። በቀጣይ ግን አብሮነታችንን የሚያጠናክር አንድ ድርጅት እንከፍት ይሆናል።

ታዛ፦ አንቺ ምን ላይ ነው የምትሰሪው?

ወንጌል፦ በኮሙኒኬሽንና ማርኬቲንግ ላይ ነው የምሰራው። ቤተሰማይ ህትመትና ማስታወቂያ ድርጅት ነው ስሙ። ከሌሎች አጋሮችና ቤተሰቦቼ ጋር ነው የምሰራው። ሌላው የአፍሪካ ወጣቶች እውቀት መካፈያ መድረክ (Young African Thinkers) ውስጥ እሰራለሁ። እኔ ነኝ የምመራው። አዳዲስ አስተሳሰብ ማፍለቂያ ኢኒሺየቲቭ ነው። ለችግሮች እንዴት መፍትሄ ማፍለቅ እንደሚቻል ማነቃቂያና ግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክም ነው። ከዚህ በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት በአውሮፓ ህብረት ወጣቶች ላይ ያተኮረ ፖለቲካዊና ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ላይ እየሰራሁ ነኝ።

ታዛ፦ ስለዚህ ዕድሜሽንና ጊዜሽን በአግባቡ እየተጠቀምሸ ነው?

 ወንጌል፦ እየሞከርኩ ነው። (ሳቅ)

ታዛ፦ ለብርታትሽ መሰረት የሆነሽ ወይንም እገዛ የሚያደርግልሽ?

ወንጌል፦ ቤተሰቦቼ ናቸው። እናቴም አባቴም ወንድሞቼና እህቶቼ ከመሰረታችን በትምህርት እንድንበረታ አግዘውናል። አባቴ የፊዚክስ መምሀር ነበር። እናቴም መምህርት ነበረች። ብርታትን አውርሰውን አልፈዋል። አሁን በጋዜጠኝነት የመጀመሪያ ዲግሪዬን ይዣለሁ። በቀጣይ ለመማር የምፈልገውን ለመምረጥ የግል ንባብ ላይ ነኝ። ትምህርቴን ግን እቀጥላለሁ።

ታዛ፦ ሁሉም ሰው መሆን የሚፈልገውን ይመኛል። የበረታ ደግሞ እቅድ፣ ግብ ያስቀምጣል። አንቺስ?

 ወንጌል፦ ነገሮች በተለዋወጡና የአዕምሮ ብስለት በመጣ መጠን ፍላጎትም ሊለዋወጥ ይችላል። እኔ አሁን የምፈልገው ሚዲያን በመጠቀም በሰዎች ላይ መልካም ተጽዕኖን መፍጠር ነው። ግዙፍ ሚዲያ የመክፈት ዓላማ አለኝ። ከአገራችን አልፎ አፍሪካን የሚያካልል እንደ ቢቢሲ አይነት ሚዲያ።

ታዛ፦ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለሴቶች ከአሁን ቀደም ባልታየ ሁኔታ ልዩ ክብር እየተሰጠ ነው። በአገር ደረጃ ትልልቅ ስልጣን ላይ ሴቶች እየመጡልን ነው፤ ይህ ምን ስሜት ፈጠረብሽ?

ወንጌል፦ ይህ በእኔ ዘመን መሆኑ በጣም ገርሞኛል። ጊዜው ስለፈቀደ እግዚአብሔር አደረገው ነው የምለው። ኢትዮጵያ ውስጥ ለመቆየት፣ ለመስራት፣ ለውጥ ለማምጣት ተስፋ አለን ማለት ነው። ይህንን ዕድል ወጣት ሴቶች ሊጠቀሙበት ይገባል። ሁላችንም አስተሳሰባችንን በጥሩ በመለወጥ እገዛ ማድረግ አለብን።

ታዛ፦ በአንቺ ዕድሜ ላሉ ወጣቶች ምን የምትመክሪው ካለ?

ወንጌል፦ እኔ እንደምገነዘበው፤ በአሁኑ ጊዜ ወጣቱ ትኩረት የሚያደርገው በብር ማሳደድ ላይ ነው። ብሩ ሲገኝም የሚረካ አይደለም። የበለጠ ለማግኘት ሲል ይሄ ሙስና፣ ወንጀል የሚባሉ ነገሮች ውስጥ ይገባል። ይህ ለወጣቱ ጠቃሚ አይደለም። ከብሩ በፊት አላማ ይኑረን። ራዕይ ይኑረን። ራዕይ ለራስ አይደለም፤ ለትውልድ የሚጠቅም ነው። ያ ራዕይ እየተሳካ ሲሄድ ነው የሚጣፍጥ ገንዘብ የሚገኘው። አሁን በአመራሮች ላይ የምናይባቸው ነገሮች የመጡት ራዕይ ከማጣት ይመስለኛል። ለእኔ የሚባል ነገር ቀንሶ ለእኛ የሚለው ነገር የቀደመ። ዋጋ የምንከፍልባቸውን መንገዶችም እንለይ። በስሜት አንመራ። ቅን እንሁን ነው የምለው። ሌላው ፎቶ መስታወት ነው። አንድ ሰው የቀደመ ፎቶውን በተመለከተ ቅጽበት ብዙ የሚታወሱት ነገሮች ይኖራሉ። ፎቶ ታሪክ ነው፤ ታሪክን ደግሞ ለሌሎች ሲነግሩት ነው ቀጣይነት የሚኖረው። በየቤታችን የሚባክኑ ታሪኮቻችንን እኛ ባሰብነው መንገድም ባይሆን እናውጣቸው። ቅርስ ናቸው ብለን ብቻ ለብልሽትና ለብክነት አንዳርጋቸው። ለዚህ ደግሞ ወጣቶች የራሳችሁን ሚና ተጫወቱ ነው የምለው።

ታዛ፦ ስለ ፎቶ አንድ ግጥም ለአንባቢዎች ጋብዘሽ ብንሰነባበትስ?

ወንጌል፦ ልሞክር?…(ሳቅ) (ብዙ አሰበች አሰበች፤ እኔም ብዙ ታገስኩ። በመጨረሻም ይህን ገጠመች)

ፎቶ- የማታ የማታ …

 እንዲየው በዝምታ

ይናገራል ታሪክ፤

 ያመጣል ትዝታ።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top