ቀዳሚ ቃል

ሽልማት እንዴትና በማን ?

ሽልማት ያተጋል። ቀደም ባሉት ዘመናት ለሽልማት ሳይሆን ለጥበብ ዕድገትና ለስሜታቸው ሲሉ ዕውቀታቸውን ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን ጭምር የሰዉ የጥበብ ሰዎች በርካታ ናቸው። እነ አውላቸው ደጀኔን፣ ኢዩኤል ዮሐንስን፣ ጥላሁን ገሠሠን፣ ወጋየሁ ንጋቱን፣ አስናቀች ወርቁን፣ ካሳ ተሰማን… ወዘተ መጥቀስ ይቻላል። የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የሽልማት ድርጅት የጥበብ ሰዎችን የሚያተጋ ሽልማት በመስጠት ጥበቡ እንዲያድግ የራሱ አበርክቶ ነበረው። ለተወሰኑ ዓመታት ቀጥሎ የቆመው ይህ የሽልማት ድርጅት ፍትሃዊነቱ ላይ ጥያቄዎች መነሳታቸው ባይቀርም (ለምሳሌ እንደ ሙዚቃና ትወና ያሉ የጥበብ ዘርፎችን በማግለሉ) በፈር ቀዳጅነቱ ሲወደስ ይኖራል።

 በዘመነ ደርግ የተዘለለው ሽልማት በኢሕአዴግ መራሹ መንግስት አንሰራርቶ ነበር። የኢትዮጵያ የሥነጥበባትና መገናኛ ብዙኃን የሽልማት ድርጅት በተወሰኑ በጎ አድራጊ ግለሰቦችና በድርጅቱ አመራሮች ጥረት ጥሩ መነቃቃትን ፈጥሮ ነበር። በ1980ዎቹ መጨረሻ እና ዘጠናዎቹ መጀመሪያ ባከናወነው የሽልማት ሥነሥርዓትም አንጋፋና ወጣት የጥበብ ሰዎችና የሚዲያ ባለሙያዎች ተሸልመዋል። ሆኖም ድርጅቱ አስተማማኝ የገቢ ምንጭ ስላልነበረውና በመንግስት በኩልም ለመነሻ የሚሆን በቂ ድጋፍ ስላላገኘ ተግባሩን ለመቀጠል ሳይችል ቀረ። ጅማሮው ግን ተስፋ ሰጪና ብዙዎችን ያነቃቃም ነበር።

 ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ ደግሞ በተለያዩ ተቋማት፣ ኮሚቴዎች እና ግለሰቦች ጭምር መሰል የዕውቅናና የሽልማት መርሐግብሮች እየተዘጋጁ ነው። በዲያቆን ዳንኤል ክብረት የሚመራው የበጎሰው ሽልማት፣ በብርሃኑ ድጋፌ የሚመራው የለዛ ሽልማት፣ አቢሲኒያ እና ሌሎችንም መጥቀስ ይቻላል። በቅርቡም ስንዱ ቢሰነብት የተባለች የጥበብ አፍቃሪ ለአንጋፋው ከያኒ ደበበ እሸቱ ደማቅ የምስጋና መርሀግብር በብሔራዊ ቴአትር መድረክ አዘጋጅታለች።

 ለመልካም ስራው መመስገንን፣ መሸለምንና መወደስን የማይሻ የለም። እነዚህን በረከቶች ለማግኘት ለሚታትሩ የጥበብ ሰዎች እውቅና መስጠት እና መሸለም መልካምነት ነው። የቀደሙትን የጥበብ ሰዎች ማሰብ፣ መዘከርና ማመስገንም ለቀጣዩ ትውልድ መልካም አርአያነትን ማሳየትና በአዲሱ ትውልድ ውስጥ አዳዲስ የጥበብ ሰዎች እንዲፈጠሩ የሚረዳም ነው። ይህ መልካም ሆኖ ሳለ፤ እውቅናውንም ሆነ ሽልማቱን፣ ምስጋናውንም ሆነ መዘክሩን የሚሰጠው ማነው? የሚል ጥያቄ መነሳቱ አልቀረም። ከአመራረጥ ጀምሮ በሽልማቱ ፍትሃዊነት ላይም ጥያቄ የሚያነሱ አሉ።

በእርግጥ በበጎነትና በቀናነት የሚዘጋጁ የሽልማት መርሃግብሮች መኖራቸው ባይታበልም፤ ስሜታዊ መሆናቸው ግን በብዙ መልኩ እየተስተዋለ ነው። ከእጩነት አመራረጥ ጀምሮ በጥናትና በበቂ መረጃ ላይ የተመሰረተ ተግባር የላቸውም፤ ቀጣይነት ያለው ስራ ለመስራት የኢኮኖሚ አቅማቸው አያራምዳቸውም፤ ምክንያቱም እንቅስቃሴዎቻቸው ሁሉ በጊዚያዊ ድጋፍ (ስፖንሰር) መሆኑ ነው የሚል ትችት ሲሰነዘርባቸው ይሰማል።

 ይህ የተበታተነ፣ ቀጣይነት የሌለው፣ በገንዘብ፣ በጥናትና በመረጃ እንዲሁም በሃላፊነት ያልተደገፈ የሽልማት አሰጣጥ ሥርዓት የጥበብን ዋጋና ክብርን ከፍ ሊያደርግ አይችልም። ሽልማት እንዴት? በማን? የሚሉ ጥያቄዎች መልስ ያሻቸዋል። በአደጉት አገራት ካለው ተሞክሮ በመነሳት ወጥነትና ቀጣይነት ያላቸው የሽልማት ድርጅቶች ሊቋቋሙ ይገባል። በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ከመቶ ዓመት በላይ ዕድሜ ያላቸው የሽልማት ድርጅቶች አሉ። እንዴት? የሚለውን በማንሳት ተሞክሮውን ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር በመቃኘት ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል። ለዚህ ደግሞ መንግስት በተለይም እንደ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ያሉት ክፍሎች፣ ባለሃብቶችና የጥበብ ቤተሰቦች በጋራ መምከር አለባቸው እንላለን። /

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top