ፍልስፍና

ለመሆኑ “የአፍሪካ ፍልስፍና” ከወዴት ነው

(በባህሎች መካከል ተግባቦትን መፍጠር)

ባለፉት ክፍሎች የአፍሪካን ፍልስፍናጉዳይ በተቻለ መጠን ለማየት ሞክሬያለሁ።ይህ የመጨረሻ ክፍል ዘመናዊውን እውቀትከባህላዊ እውቀት ጋር እንዴት ማዋሃድይቻላል? ወይም የአፍሪካን ፍልስፍና ወይምአገር በቀል እውቀት ባጠቃላይ ለዘመናችንአንገብጋቢ ችግሮች መፍትሄነት እንዴትማዋል ይቻላል? የሚለውን መሠረታዊ ጥያቄመነሻ በማድረግ የማጠቃለያ ሐሳብ የያዘ ነው።በአገር በቀል እውቀት ጥናት ማዕከላት፣በቴክኖሎጂ ሥነ-ምግባር ጥናት (TechnologyEthics)፣ በትምህርቱና በፍልስፍናውዓለም ባህላዊ እና ዘመናዊ እውቀት እንዴትመዋሃድ ይችላል? የሚለው ጥያቄ ትኩረትየሚሰጠው ጥያቄ ነው። ይህም ሁለትመሠረታዊ ጽንሰ ሐሳቦችን ያቀፈ ነው። ባንድበኩል የጥንቱን አስተሳሰብ ለዘመናችን ችግሮችእንዴት ማዋል እንዳለብን የሚመለከት ሲሆንበሌላ በኩል የተለያዩ አስተሳሰባዊ መሠረትያላቸውን ጥንታዊ የህዝብ እውቀት (IndigenousFolk Wisdom) ከዘመናዊ የሳይንስ፣የቴክኖሎጅ እንዲሁም የፍልስፍና አስተሳሰብጋር እንዴት ማዋሃድ ይቻላል የሚል ነው። ባጠቃላይ በዘመን በተራራቁ ትውልዶችና በቦታና በአስተሳሰባዊ አውድና መሰረት በተለያዩ ባህሎች መካከል እንዴት ውህደት መፍጠር ይቻላል? የሚል ሰፊ ሐተታና ጥናት የሚያስፈልገው ጥያቄ የያዘ ነው።

 የተለያዩ የአገር በቀል እውቀት ላይ የተሰማሩ አጥኚዎች ስለ አፍሪካውያን አስተሳሰብ ባዶ እጃቸውን እንዳልተመለሱ ባለፈው በሰፊው አይተናል። የአፍሪካውያን የባህልና የአስተሳሰብ ካዝና በአገር በቀል ፍልስፍና የበለጸገ መሆኑ የማይካድ ሐቅ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በሰው ልጆች የሥልጣኔ ጉዞ ውስጥ ትልልቅ ፍልስፍናዊ አስተሳሰቦች፣ መላምቶች እንዲሁም የሕይወት ትርጓሜዎች ላይ ደርሰናል። ምንም እንኳ “እውቀት ለራሱ ፍላጎት ሲባል የሚጠና ጉዳይ ነው። (Knowledge for its own Sake” የሚል የመከራከሪያ ሐሳብ ያለ ቢሆንም ነባራዊ ሁኔታው የሚያሳየን ግን እውቀት ለተግባራዊ ፋይዳው ሲባል የሚጠና ትልቅ ማህበራዊ ፋይዳ ያለው የህዝብ ሃብት እንደሆነ ነው። እውቀትን ለተግባራዊ ፋይዳው ብቻ ሲባል ማከማቸት ደግሞ ሌላው ጽንፍ ሲሆን የራሱ የሆነ ተቃርኗዊ ችግር ያለው ነው። እንደ አድለር ያሉ ትምህርት ላይ ሐተታ ያቀረቡ ፈላስፎች እንደሚተቹት፣ ጥራት ላይና አስተሳሰባዊ ብልጽግና ላይ ከማተኮር ይልቅ ወደ አምራችነት፣ ሙያ ላይና ብዛት ላይ ያተኮረ የትምህርት ፖሊሲ ከባህርያዊ ቀናነት ይልቅ ሙያዊ እውቀት ያላቸው እንደ ማሽን የሚሰሩ ሰዎችን በማፍራት ላይ ስለሚጠመድ ሙያዊ ሥነ-ምግባርና ባህርያዊ ቀናነት እንዳይኖራቸው ያደርጋል። ይህ ዓይነት አስተሳሰብ ቁሳዊነት ላይ ያተኮረ ስለሚሆን መንፈሳዊ እድገትን ይዘነጋል።

ይህም ብቻ አይደለም። እውቀትን ለመሳሪያነት የሚቆጥር የትምህርት ፖሊሲ አዳዲስ እሳቤ በመጣ ቁጥር ከነባሩ ጋር ከማዋሃድ ይልቅ “የተሻለ” መስሎ የታየውን በመያዝ ነባሩን አሽቀንጥሮ በመጣል በተማረውና ባልተማረው የህብረተሰብ ክፍል፣ በአባቶችና በልጆች መካከል ያለን ተግባቦት ቆርጦ በመጣል የባህልና የአስተሳሰብ ቀውስን ይፈጥራል። እንደዚህ ዓይነቱ የትምህርት ሥርዓት ላይ የተመሰረተው የልማት ፖሊሲ ምናልባትም በቁሳዊ እድገት በኩል የተሻለ መራመድ ይችል እንደሁ እንጅ ባጠቃላይ ሰውን መሰረት ያደረገ ቁሳዊና መንፈሳዊ ስልጣኔን ማረጋገጥ አይቻለውም።

በአፍሪካ ታሪክ፣ ትምህርት እንዲሁም ፍልስፍና ላይ ጥናት ያደረጉ አካላት (ለምሳሌ፣ በቀለ ጉተማ፣ ዳንኤል ስሚዝ፣ ሳንድራ ሃርዲንግ፣ ቻርለስ ቬርሃረን፣ ሰጣርገው ቀናው) እንደሚገልጹት ዘመናዊ ትምህርት በተለይም የከፍተኛ ትምህርት በአፍሪካ ኩረጃ ላይና የውጭውን ሃሳብ ብቻ ሽምደዳ ላይ ያተኮረ በመሆኑ ለአገር በቀል እውቀት ቦታ አይሰጥም። ቦታ አለመስጠት ብቻ ሳይሆን የአፍሪካውያን አስተሳሰብ ዘመን ያለፈበት እና ምክንያት ላይ ያልተመሰረተ ከሳይንስ በተቃራኒው ያለ እንደሆነ በመቁጠር ለአውሮፓዊው አስተሳሰብ ሙሉ ልብ የሰጠ ነው። ይህም በቅድመ ቅኝ ግዛት አፍሪካውያን ለውጭ ወረራ ተጋላጭ እንዲሆኑ መንገድ ከፍቷል። ድኅረ ቅኝ ግዛት ደግሞ የዩኒቨርሲቲዎቹ ህልውና በተለይም የገንዘብ ድጎማ በሚያደርጉላቸው የውጭ ድርጅቶችና የውስጥ የፖለቲካ መሪዎች ፍላጎት ላይ የተመሰረቱ ስለሆኑ በእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ሥር እንዲውሉ አድርጓቸዋል።

 ተጠራጣሪዎች እያንዳንዱ የቴክኖሎጅ ውጤት የራሱ የሆነ ፖለቲካዊ ወይም ሌላ አጀንዳ ይዞ የሚመጣ ነው። በዚህም “Science and technology are not value free” የሚል ሙግት ይዘው ይከራከራሉ። ይህ ምናልባትም ወዳልተገባ ጽንፈኝነት የሚወስድ ሁሉም የውጭ የሆነ ነገር በአሻጥር የተሞላ ነው የሚል ጤናማ ያልሆነ መጠራጠር (Extreme Scepticism) ሊሆን ይችላል። በርግጥ መጠነኛ መጠራጠር አስፈላጊ ይሆናል። ይህም ባንድ በኩል በዘመናዊ ትምህርት ቤቶች የተማሩ ሰዎች አባቶቻቸው የኖሩበትን ባህል እንዳይዘነጉት ለራስም ዋጋ መስጠት እንዳለብን በማስገንዘብ የተጋነነ የውጭውን ማድነቅን መግታት ይቻላል። በሌላ በኩል ደግሞ በርግጥም እያንዳንዱ ባህል እራሱን ብቸኛው የእውነት ባለቤት አድርጎ ስለሚቆጥር የውጭው እሳቤ ያልተገደበ ተጽእኖ ፈጣሪና ብቸኛው አማራጭ ሆኖ እንዳይቀርብ ያደርገዋል።

የውጭው ሳይንስና ፍልስፍና የራሱን እሴቶች ወይም የባለቤቶቹን “values” ይዞ ሲመጣ በአገር በቀል እውቀት ላይ ከፍተኛ ጭቆና ያደርጋል። ነባሩ የህዝብ አስተሳሰብ እንደ ዋጋ ቢስ እንዲቆጠርና ለዘመናዊ ሳይንስ ሙሉ ትኩረት በመስጠት ለዘመናት የተከማቸው አገር በቀል ጥበብ ድባቅ እንዲመታ አድርጎታል። በእውቀት በኩል ያለው ጭቆና ይህ ብቻ አይደለም። ማኅበረሰቡ በለመደው መንገድ የለት ተዕለት ችግሩ እንዳይፈታ የዘመናዊ ህግና ሳይንሳዊ የችግር መፍትሄ የተሻለውና ብቸኛው መንገድ እንደሆነ በመቁጠር ለችግሮቻችን ሌላ ችግር ተጨምሮ ሕይወትንም ከባድ ያደርጋታል። ለምሳሌ ከህግ ጋር በተያያዘ ዘመናዊ የፍርድና የክርክር ሂደት ፍትህን በማረጋገጥ ረገድ ማንም ሊክደው የማይችል መፍትሄ ነው። በተለይም በሰለጠነው ዓለም ትክክለኛው ፍትህ በፍርድ ቤት የሚገኝ ነው። በተለያዩ

“በዘመናዊ ትምህርት ቤቶች የተማሩ ሰዎች አባቶቻቸው የኖሩበትን ባህል እንዳይዘነጉት ለራስም ዋጋ መስጠት እንዳለብን በማስገንዘብ የተጋነነ የውጭውን ማድነቅን መግታት ይቻላል” አገርበቀል እውቀት በበለጸጉ ህዝቦች ዘንድ ግን ከፍርድ ቤት ይልቅ በሽምግልና ዘላቂ ፍትህ ሊገኝ ይችላል። ለዚህም ነው አንድ ጊዜ ፍርድ ቤቶች በግለሰቦች መካከል የሚፈጠርን ቀለል ያለ ክርክር በሽምግልና እንዲፈቱት አስተያየት ሲሰጡ የሚስተዋለው። በርግጥም ህግን በተሳሳተ መልኩ ተርጉመው፣ በሙስና አጣመው ወይም በከፍተኛ ባለሥልጣናት ተገደው የአንድን ወገን ብቻ ፍላጎት የሚያሟሉ ነጻ ያልሆኑ ዳኞች ባሉባቸው የአፍሪካ አገራት ፍርድ ቤት ፍትህን ላያረጋገጥ ይችላል። እንደ ማሳያም በኢትዮጵያ ከመሬት ይዞታ ክርክርና ክፍፍል ጋር በተያያዘ ችግሮች የሚፈቱበት መንገድ ላይ ጥናት ያደረገው ደሳለኝ ራህመቶ የመሬት አስተዳደሩን ችግሮች የሚፈቱት ዳኞች ባንድ በኩል የህግ እውቀታቸው ውሱን ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የመንግሥትን ፍላጎት እንጅ የህዝቡን ፍላጎት የሚሰሙ እንዳልሆን ነግሮናል።

 ቴዎድሮስ ተክለአረጋይ ከአንድ የወሎ አበጋር ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ አበጋሩ የባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች ከዘመናዊው እንደሚሻሉ ይሞግታሉ። ሙግታቸው እውነት አለው። ከህክምና፣ ከአካባቢ ጥበቃ፣ ከሰላም፣ አጠቃላይ ከሰው ልጆች ደህንነት ጋር በተያያዘ ባህላዊ እውቀት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ባለፉት ክፍሎች አይተናል። ታዲያ የቱ ይሻላል? ከሁለቱ አንዱን የመምረጥ ጉዳይ አይደለም። ሁለቱም (ባህላዊና ዘመናዊ እውቀት) የራሳቸው የሆነ ደካማ እና ጠንካራ ጎን እንዳላቸው አይካድም። አንዱን ጥሎ አንዱን አንጠልጥሎ መሄድ አይቻልም። ያለው አማራጭ ሁለቱ የሚዋሃዱበትን መንገድ ማበጀት ነው። አወሳሰዱ ላይ ግን ከፍተኛ ጥንቃቄን ይጠይቃል። ሁለት ባህሎች በሚገናኙበት ጊዜ መንፈስ በምርጫ መሃል ይዋልላል።

 እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲፈጠር ለመወሰን ቢያንስ “ሁለት መንገዶች አሉ” ይሉናል እጓለ ገብረ ዮሐንስ። “አንደኛው ይህንን ብቻውን ተቀብሎ ያለፈውን ያረጀ ነገር ነው ብሎ ጨርሶ መተው ነው። ሁለተኛው ደግሞ ሰው ራሱን እኔነቱን ለመካድ በላጲስ ለመፋቅ ስለማይችል የራሳችን ብለን የምንጠራውን ከአዲሱ ከምዕራባዊው ጋር በማጣመርና በማዋሃድ ወደ ፊት አዲስ ህብር በመፍጠር እንሂድ የሚል ነው። ሁለተኛውን የምንከተል መሆናችን ግልጽ ነው።” እንዴት አድርጎ? የሚለውን ሊቁ “በተዋኅዶ ከበረ” ያሉት ነው። በሁለት ባህሎች መካከል የሚፈጸም ፍትሃዊ የአቻ ጋብቻ እንበለው። አንዱ ያለውን ይዞ ለሌላው በመለገስ የሌለውን የሚቀበልበት መንገድ ነው። የሊቁን ሙሉ ሐሳብ ለመረዳት የሚሻ አንባቢ “የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ” የተሰኘች መጽሐፋቸውን ማንበብ ይኖርበታል። አንዳንዶች በባህሎች መካከል የሚደረግ ውይይት ያስፈልጋል ይላሉ። ይህም “Intercultural Dialogue” የሚባለው ሲሆን አንድ ባህል ብቻውን ምሉዕ ስለማይሆን እና ህዝቦችም በዚህ በሉላዊነት ዘመን ብቻቸውን ተነጥለው ”መኖርና ማሰብ” ስለማይችሉ መነካካታቸው የማይቀር ነው። በሚነካኩበት ጊዜ መግባባት፣ መነጋገር ይኖርባቸዋል። ይህም መነጋገር በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ውህደት እንዲፈጠር እድሉን ማመቻቸት ያስፈልጋል። ያ ሳይሆን ሲቀር አንደኛው ክንደ ብርቱ ይሆንና የሌላውን ድምጽ ያፍነዋል። ይህም ብቻ ሳይሆን ሕይወትን ምስቅልቅል ያደርጋታል። ማርክሲዝምን እንደወረደ ለመተግበር የተነሱ አካላት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ምን ትርፍ እንዳመጡ ለተመራማሪዎች የሚተው ነው።

ሌሎች ደግሞ ዘመናዊው እውቀት አውዳዊ በሆነ መንገድ መተርጎም፣ መተንተን እንዳለበት ይመክራሉ። ይህም “Hermeneutics” የሚባለው ነው። ይህኛው ዘዴ ለሁለቱም የሚሰራ ይሆናል። ዘመናዊውን ከባህላዊው ጋር እንዲስማማ አድርጎ መተርጎም፣ መከለስ፤ እንዲሁም ባህላዊው እውቀት ከዘመናዊ ጋር እንዲስማማ አድርጎ መከለስ ይሆናል። በሁለቱም ባህሎች ላይ የሚደረገው ምክንያታዊ የሆነ ሙያዊና ሥርዓታዊ ጣልቃ ገብነት ሁለቱ ባህሎች እንዲግባቡ፣ እንዲዋሃዱ እና ሁለቱም በተናጠል ከሚሰጡት ጥቅም የተሻለ ተግባራዊ ፋይዳ እንዲኖራቸው ያደርጋል። በቁሳዊና መንፈሳዊ እድገት የሚደረገው ጉዞም ሚዛናዊ እንዲሆን ይረዳል።

በባህሎች መካከል የሚደረግ ተግባቦት፣ መዋሃድ፣ እንዲሁም መልካም መናበብ ባጠቃላዩ የዘመናዊና ባህላዊ እውቀቶች ላይ ብቻ የሚጠበቅ አይደለም። ልዩነትን መሠረት ያደረጉ የማንነት ፖለቲካ የሚዘውራቸውን መጋጨቶች በማስወገድ ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ባለ ብዝሃ ባህል፣ ቋንቋና ሃይማኖት ባለቤቶች በሆኑ ህዝቦች መካከል “Multiculturlism” ከሚለው ፖለቲካዊ ቅይጥ ጽንሰ ሐሳብ በተጨማሪ ሙያዊና ምሁራዊ በሆነ መንገድ የባህሎችን ተግባቦትና መሠረታዊ ውህደታቸውን ማረጋገጥ እንዲሁም ቅድምናዊ አንድነታቸውን ማግኘት ይበጃል። እንደ ሃንቲንግተን ያሉት ምሁራን የባህሎችን ስስ ብልት መሠረት ያደረጉ ግጭቶች ለወደፊቱ የዓለም ህዝቦች መልካም መግባባት ትልቅ ፈተና እንደሚሆኑ ይተነብያሉ። ለዚህ ዓይነተኛው መፍትሄ ለባህሎችና ለባለቤቶቻቸው እውቅና በመስጠት የጋራ መግባቢያ ድልድይ መሥራት ነው። ይህም የሚሳካው “Interculturalism” በሚለው የማዋሃድ ዘዴ ነው።

 ይህንን ማድረግ የማን ኃላፊነት ነው? ከሁሉም በፊት የሚሰለፉት ምሁራኑና ዘመናዊ ትምህርት ቤቶች ናቸው። በተለይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትልቁን ድርሻ ይይዛሉ። ዩኒቨርሲቲዎች ዓለም የደረሰበትን የስልጣኔ ደረጃና የአስተሳሰብ ልህቀት ወደ ትምህርት ገበታው በማምጣት የመማማሪያ፣ የመወያያ፣ የመከራከሪያ መስኮች ስለሆኑ ማንኛውም እውቀት ወደ ተግባራዊ ፋይዳው የሚመራባቸው የማዘዣ ጣቢያዎች ናቸው ማለት እንችላለን። በነዚህ ተቋማት የሚሰሩ መምህራን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የዘመናዊውን እውቀት ባለቤቶች ኑሮ ያውቁታል። አብዛኛዎቹ ደግሞ በማንነታቸው የማኅበረሰቡ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ትውፊቶች፣ አስተሳሰቦች ውጤቶች ናቸው። እነዚህ ምሁራን ራሳቸውን እንደ ብቸኛው የባህል ጠበቃ ወይም ብቸኛው የዘመናዊ ትምህርት አዋቂ በመቁጠር ከሁለቱ አንዱን ብቻ መምረጥ አይኖርባቸውም። ለባህሉ እና በውስጡ ላሉት ጠቃሚ እሴቶች ትልቅ ግምት የሚሰጥና የተማረው ዘመናዊ ትምህርት ለዚያ ባህል በሚመጥን መልኩ እንዴት መቅረብ እንደሚችል ዘዴውን በማጥናት በሁለቱ ባህሎች መካከል የመገናኛ ድልድይ ሆኖ ማገልገል ይኖርበታል።

 መምህራኑ ተማሪዎቹን ከራሳቸው ባህል እያሸሹ ወደ ሌላ ባህል የሚያቀርቡ የውጭውን ብቻ የሚያስተጋቡ በቀቀን መሆን የለባቸውም። ይልቁንም ዘመናዊውን እውቀት ወደ ተማሪዎቹ ይዞ በመምጣት ከእነሱነታቸው ጋር እንዲዋሃድና ከወላጆቻቸው ከወረሱት የኑሮና የአስተሳሰብ ዘዴ ሌላ አማራጭ መኖሩን ማሳየት ይኖርባቸዋል። በዚህም ተማሪዎቹ ከሁለቱ አንዱን የመምረጥ ችግር ገጥሟቸው መንፈሳቸው እንዳይረበሽ ከሁለቱም የሚጠቅመውን እንዴት መውሰድ እንደሚችሉ ማሳየት መቻል ይኖርባቸዋል። አንድ በአፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ፍልስፍናን የሚያስተምር መምህር የፕሌቶ ወይም የዴካርት ወይም የካንት ፍልስፍና ምን እንደሆነ እና ያ ሐሳብም በፍልስፍና ታሪክ ምን ያክል ቦታ እንዳለው አሳይቶ መቆም የለበትም። ከቻለ በሚያስተምርበት ማኅበረሰብ አስተሳሰብ ውስጥ ሌላ እሱን የሚመስል ወይም የፈላስፋውን ሙግት የሚተካከል የህዝብ ጥበብ ካለ ፈልጎ ማሳየት ይኖርበታል። ካልቻለ ግን የካንት ወይም የፕሌቶ ሐሳብ ብቸኛው የሕይወት መርህ ነው ብሎ ማስተማር የለበትም። በአገር በቀሉ እና በውጭው ዘመን ተሻጋሪ ሐሳቦች መካከል ያለውን ወንድማማችነት በማሳየት ሁለቱን በማዋሃድ ለዘመናችን ችግሮች የተሻለ የመፍትሄ ሃሳብ ማፍለቅ ይቻላል ይላሉ ሊቁ እጓለ። በሳይንስ፣ በፖለቲካዊ አስተሳሰብ፣ በማኅበራዊ እሳቤዎችም ተመሳሳይ ውኅደት እንዲኖር መጣር አለባቸው። ካልሆነ ተቋሞቹ ከላይ የጠቀስነው ቬርሃረን እንዳለው “በማያውቁት ማኅበረሰብ መካከል ያሉ ደሴቶች” ከመሆን አይዘሉም።

 ከዚህ ወቀሳ ለመዳን ዩኒቨርሲቲዎች የተለያዩ የባሕል ጥናት ማዕከላትን በመክፈት በእያንዳንዱ ትምህርት ክፍል ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ተጓዳኝ አገር በቀል እውቀት መኖሩን የሚያጠና ተልዕኮ ሊኖራቸው ይገባል። አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ከአገር ሽማግሌዎችና ጠቢባን (ኦሩካ Sages የሚላቸውን) በመጋበዝ እንዲያስተምሩ፣ የማማከር አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ይቻላል። ይህ ዓይነቱ የማኅበረሰቡን ጠቢባን፣ የእውቀት ባለቤቶች ተሳታፊ ማድረጉ በተጓዳኝ ብቻ የሚደረግ ሳይሆን በመገናኛ ብዙሃን እንዲሁም በተለያዩ ቱባ ባህሎች ባሉባቸው አካባቢዎች ልክ የሃይማኖት ተቋማት እንደሚያደርጉት በመደበኛ መልኩ ለታዳጊዎች ማስተማርም ይቻላል። ምንም እንኳ ሐሳባዊ ቢመስልም፣ ሞዴል ትምህርት ቤቶችን በመክፈት ከመዋዕለ ህጻናት ጀምሮ እስከ ከፍተኛው ትምህርት ድረስ በአገር በቀል እውቀቶች ላይ የባህል ትምህርት እንዲሰጥ በማስቻል ዘመን ተሻጋሪ አስተሳሰቦቹ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፉ በማድረግ ለዘመናችን ችግሮች መፍትሄነት እንዴት መዋል እንዳለባቸው ዘመናዊ ዘዴን መቀየስ ይቻላል።

 ከዩኒቨርሲቲዎች በተጨማሪ የተለያዩ የባህል ጥናት፣ የቅርስ ጥበቃ፣ የሃይማኖት እና የማኅበረሰብ ጥናት ተቋማት ይህንን ግዴታ በመወጣት ረገድ ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ። የጥንታዊ አስተሳሰቦችና ባህሎችን ገለጻዊ ዳሰሳ በመሰነድ ሳይነኩ እንደነበሩ ወደፊት እንዴት መቀጠል አለባቸው የሚል ተግባር ላይ ብቻ መጠመድ የለባቸውም። መቀጠል ያለበትን በማስቀጠል መቆም ያለበትን በማቆም እነዚህን ጥንታዊ የቁሳዊና የመንፈሳዊ እሳቤዎች የበየነውን የህዝብ ጥበብ ለዚህ ዘመን ችግር መፍትሄነት እንዴት መዋል ይችላሉ፣ ከ“ባዕዱ” ከመጤው ባህል ጋርስ እንዴት መዋሃድ ይችላሉ? የሚል ሙያዊ አስተያየትም ይጠበቅባቸዋል።

ፖሊሲ አውጪዎች፣ የመንግስት አካላት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ በጥበብ ላይ የተሰማሩ አካላት፣ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች እንዲሁም አርቲስቶች በሙያቸው ይህንን መሠረታዊ የቤት ሥራ ታሳቢ በማድረግ የፈጠራዊ ሥራዎቻቸውና የህግ መመሪያዎች፣ የተግባራዊ ስትራተጂያቸው አካል ሊያደርጉት ይገባል። የፖለቲካ ሰዎችና የጥበብ ሰዎች ተግባር ውስጣዊ ብልጽግናን በማረጋገጥ፣ ባህልን ከባህል በማነጋገር፣ የአንድን አገር ህዝቦች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተገቢውን ቦታ እንዲያገኙ ማስቻል ነው። በዚህም የአገር የውስጥ ጥንካሬና ፖለቲካዊ ሉዓላዊነት ይረጋገጣል፣ የህዝቦቿም አስተሳሰብ በዓለም መድረክ ከፍ ብሎ ይሰማል። ይህ እውን የሚሆነው አገር በቀል እውቀት ከዘመናዊ እውቀት ጋር በሰላም መዋኃድ ሲችል፣ ይህም ውህደት የአካባቢያዊና ዓለማቀፋዊ አንገብጋቢ ችግሮችን ለመፍታት የተሻለ አማራጭ መንገድ ይዞ መምጣት ሲችል ነው። የዚህ የባህሎች መዋሃድ ትልቁ ስዕልም የሚታየው የተጨቆኑ፣ ያልተሰሙ፣ ችላ የተባሉ፣ ዘመን አይሽሬ አስተሳሰቦች ጎልተው ሲታዩና ከዘመናዊው አቻቸው ጋር ሲመክሩ፣ ለተሻለ አማራጭ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ ሲችሉ ነው። በአፍሪካ ፍልስፍና ዙሪያ ያደረግሁት ሐተታ እዚህ ይፈጸማል። በሌላ ርእሰ ጉዳይ እስክንገናኝ ሰላም!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top