በላ ልበልሃ

ፊደላት ለምን ይቀነሱ?

የግእዝ ሞክሼ ሆሄያት ይቀነሱ አይቀነሱ በሚል ሙግት ከተጀመረ አንድ ምእት አመት ሊሞላው ትንሽ ቀርቶታል። በየዘመኑ የእነዚህን ሞክሼ ሆሄያት /ሀ ፣ ሐ ፣ ኀ ፣ ሰ ፣ ሠ ፣ ዐ ፣ ፀ ፣ ጸ እና አ/ አስመልክቶ ከሚሰጡት የድምፅ ተመሳሳይነት የተነሣ አንድ ፊደል ለአንድ ድምፅ ውክልና ሊኖረው ይገባል በሚልና በአጻጻፍና ፊደሉን በማጥናት ጊዜ በሚኖረው የአገባብ ችግር የተነሣ ይቀነሱ አይቀነሱ ሲባል ሙግቱ መፍትሄ ሳያገኝ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተንከባለለ ዛሬ ላይ ደርሷል። ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው የቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ተቋም ባልተሰጠው ስልጣንና በሌለው ውክልና ውሣኔ ያሣረፈባቸው ይመስላል። ውሳኔዎቹም በዚህ ጽሑፍ መጨረሻ ላይ ተዘርዝረዋል።

ቀደምት የፊደል ተሟጋቾች በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ብለዋል ?

 ይህንኑ የፊደል ሙግት ከቃል አልፎ በጽሑፍ አስደግፈው ከሚከራከሩት ውስጥ የመጀመሪያው ሰው ኪዳነወልድ ክፍሌ ይመስሉኛል። በ1926 ዓ.ም ለንባብ ባበቁት መዝገበ ፊደል /የግእዝና የአማርኛ ቋንቋ መክፈቻ/ በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ እንዲህ ብለው ነበር። “በወዲያኛው በአስመራ ማኅተም በስዊድን ማኅበር በትግሬና በትግሪኛ መጽሐፍ ሦስቱን ፊደላት /ሠ ፣ ኀ ፣ ፀ/ እንዲወጡ የሆነ የጽሕፈት ሥርዓት ሊኖራቸው አይገባም፤ ከወዲሁ በአማርኛው መጽሐፍ በእኝህ በሦስቱ ላይ ሁለት ፊደላት /ዐ ሐ/ ተጨምረው አምስቱ እንደወጡ በብዙ ሰዎች ልብ ሃሣብና ምኞት ተነስቶ እንደ ጠኒ ይጉላላል። አንዳንድ ጊዜም እየፈላና እየገነፈለ በግድ ይነገራል። ሥራውንም እንኳን የጀመሩት ሰዎች አሉ” በማለት በፊደላቱ ላይ የተጀመረው ቅነሳ ከማተሚያ ቤት ደርሶ በሚታተሙት መጻሕፍት ላይ በስዊድን ሚሲዮናውያን አማካኝነት ሲተገበር የነበረ መሆኑን ገልፀው፤ ይኸው ድርጊት በሌሎች የሐገሬው ምሁራን ላይ ያሳደረውን ተፅእኖ በመቃወም አስተያየታቸውን በጽሑፍ አስፍረዋል።

 ሁለተኛው የፊደል ተሟጋች የነበሩት አስረስ የኔሰው በ1950 ዓ.ም ለኅትመት ብርሃን ባበቁት “የካም መታሰቢያ የኢትዮጵያ ፊደል መሠረትነት መታወቂያ” በሚለው ስራቸው ውስጥ የፊደልን ምንነት እንዲህ ብለው ዘርዝረውታል። “ቋንቋ መልክ ነው መልክም ቋንቋ ነው፣ ፊደል ሀውልት ነው፤ ሀውልትም ፊደል ነው፤ ፊደል አባት ነው፤ አባትም ፊደል ነው፤ ፊደል ልጅ ነው ልጅም ፊደል ነው፤ ፊደል ብሔራዊ አርማ ነው፤ ብሔራዊ አርማም ፊደል ነው። አላማ የኩራት ምልክት ነው ኩራትም ነፃነት ነው፣ ነፃነትም መንግስት ነው የማንኛውም ነገር መጠቅለያ ፊደል ነው፤ መንግስት ካለው ፊደል አለው፤ መንግስት ሲጠፋ ፊደልም አብሮ ይጠፋል። ሲሉ ስለ ግእዝ ፊደል አይቀነሴነት በአደባባይ ሽንጣቸውን ገትረው ተሟግተዋል።

በሌሎች መጽሐፎቻቸውም ሲከራከሩ ቆይተዋል። በተቃራኒው ደግሞ በይቀነሱ የክርክር ዘውግ ሽንጣቸውን ገትረው በመከራከር ጉባኤ አሰይመው በመሟገት እነ አቶ አበበ ረታን ተከትሎ ብላታ መርስዔ ሐዘን ወልደ ቂርቆስ፣ አቶ አዲስ አለማየሁ፣ ራስ እምሩ ኃይለሥላሴና መጨረሻም በዘመነ ኢሕአዴግ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው የቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ተቋም የተቃራኒው ዘውግ የክርክሩ ተዋንያን ነበሩ።

 ፊደላቱን መቀነስ በማንና መቼ ተጀመረ?

 ፊደላትን አስተካክሎ የመጻፍ ችግር የተከሰተው በቅርብ ጊዜ አለመሆኑን ካህሣይ ገ/እግዚአብሔር “ሚስጥረ ፊደል ወትርጓሜሁ” በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ ገልጸዋል። ለምሣሌ በዐፄ ገብረመስቀል ጊዜ የዚህ አይነት ችግር ተፈጥሮ በቅዱስ ያሬድ መሪነት እልባት ስለማግኘቱ ዶ/ር ፍሥሐጽዮንን ጠቅሰው እንዲህ ብለዋል።

 “በዚህ ሰአት የመጻሕፍት ፍቺና የደብዳቤዎች ትርጉም ተበላሸ፣ ተዘዋወረ፣ ስለዚህ አክሱም ውስጥ በቅዱስ ያሬድ መሪነት በዐፄ ገብረመስቀል ትእዛዝ ፊደል አሳስቶና አደባልቆ፣ አዘባርቆ፣ አንዱን በአንዱ ያለቦታው ተክቶ መጽሐፍ መጻፍ ክልክል መሆኑ በሕግ ታወጀ። አድርጐ የተገኘ ሰው ይከሰስ ይወቀስ ጀመር። እንደ አስፈላጊነቱም ከሥራው እንዲቀጣ ተብሎ ይዘዋወር ነበር ይባላል።” በዐፄ በካፋ ዘመነ መንግስት ደግሞ በፊደላት አጻጻፍና ትምህርት ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት ከፍተኛ የሆነ የሥነ ጽሑፍ እና የግእዝ ግስ አገባብ ትምህርት ቤት ተከፍቶ ነበር። ከዚህም አልፎ ይልቁንም “ሀ” ን ከሐመሩ ”ሐ” ሐመሩን ከብዙኀኑ “ኀ” አልፋውን “አ” ከዐይኑ “ዐ” ንጉሡን “ሠ” ከእሳቱ “ሰ” ጸሎቱን “ጸ” ከፀሐዩ “ፀ” ለይቶ በየስፍራቸው ያልፃፈ፣ ፊደል አዘዋውሮ የተገኘ ጸሐፊ እጁ ይቆረጥ የሚል አዋጅ አውጥተው እንደነበር የዶ/ር ፍሥሐፅዮንን ጥናት ጠቅሰው ካህሣይ ገ/ እግዚአብሔር ጽፈዋል።

እነዚህን ቀደምት ሕጐች ደፍረው በመጣስ ለመጀመሪያ ጊዜ ሞክሼ ሆሄያትን ያለቦታቸው እያስገቡና እያስወጡ መጽሐፍ በማሳተም ረገድ የስዊድን ሚሲዮናውያን የመጀመሪያዎቹ ሳይሆኑ አይቀሩም። በ1888 ዓ.ም. እነዚሁ ሚሲዮናውያን ወንጌል የመስበክ ዓላማ ይዘው ወደ አፍሪካ ሲመጡ ኢትዮጵያ ውስጥ የገጠማቸው ነገር ካሰቡት እና ከጠበቁት የተለየ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ሚስጥራትን በራሳቸው የግእዝ ፊደልና ቋንቋ ሲተነትኑና ሲያስተነትኑ የነበሩት ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ከእነሱ የላቀ እውቀት እንዳላቸው ሚሲዮናውያኑ ተረድተዋል።

ስለዚህም ከዚህ ፉክክር አዋቂ መስለው ለማምለጥ ሲሉ አብዛኛውን የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪ በስብከታቸው ለመያዝ ባመጡት የኅትመት መሣሪያ የፊደላትን አጻጻፍና አገባብ ሳይጠብቁ መጽሐፍ ቅዱስን አሳትመዋል።

እነዚህ ሰዎች የዐፄ በካፋን ሕግ የሚያስፈፅም ንጉስ በዘመናችን ቢኖር ኖሮ እጃቸውን ባጡ ነበር። ይህ ግን አልሆነም። የዘሩትም መርዝ እየተስፋፋ ኪዳነወልድ ክፍሌ በ1926 ዓ.ም እንዳሉት ሌሎች ደጋፊ ልጆች አፍርተው ሙግታቸውን እስከ አሁኑ ትውልድ ድረስ አዝልቀውታል። ዛሬም ፊደላችንን አስመልክቶ በይቀነሱ አይቀነሱ ክርክር እሰጥ አገባው ቀጥሎ ይገኛል።

የሙግት ዓይነቱ ዘውግ በስንት ተከፍሎ ነበር የቀጠለው ?

“ውሻ በቀደደው ጅብ ይሾልክበታል”

እንዲባል ሚሲዮናውያኑ የጀመሩትን ፊደል የመቀናነስና ያለቦታው የመጻፍ ነገር የሀገራችን ሰዎችም ተቀብለው የሙግታቸው መሠረት አድርገውት ሲከራከሩ ቆይተዋል። ምክንያታቸውን ሲያስቀምጡም፣

• ሕፃናትን ለማስተማርና ፊደላቱን በቶሎ ለመለየት ያስቸግራል።

 • አማርኛና ግእዝ የተለያዩ ቋንቋዎች ስለሆኑ አንድ ወጥ የሆነ የጽሕፈት ሥርአት ሊኖራቸው አይገባም።

• ሀ ፣ ሐ ፣ ኀ ፣ ሰ ፣ ሠ ፣ አ ፣ ዐ ፣ ጸ ፣ ፀ /ሞክሼ ሆሄያት/ የጥንት ድምፃቸው ስለጠፋና በአንድ ድምፅ ብቻ ተወክለው ስለሚገኙ ለአንድ ድምፅ አንድ ምልክት በሚለው የሥነ ልሳን መርህ መሠረት ሊቀነሱ ይገባል።

 • የቋንቋ ዋናው አገልግሎቱ መግባቢያነቱ ስለሆነ ሞክሼ ፊደላት ተቀንሰውም መግባባትና መጻፍ ስለምንችል ሊቀነሱ ይገባል፤ ሲሉ የአንዱ ወገን ጎራዎች መከራከሪያ ነጥባቸውን ያስቀምጣሉ። በተቃራኒው ወገን የሚሟገቱት ደግሞ ምክንያታቸውን እንደሚከተለው ይገልጻሉ።

 • ፊደሉ ታሪካዊ ቅርስ ነው፣ ከአባቶቻችን ተያይዞ የመጣና የተረከብነውም ስለሆነ ሊቀነስ አይገባም።

 • ፊደላቱ ቢቀነሱ እስከዛሬ በግእዝ ቋንቋ የተጻፈልንን ሚስጢር ለማንበብና ለመገልበጥ ይከብደናል።

 • አማርኛ ያለግእዝ ፊደል በተቀነሱት ሆሄያት ብቻ እራሱን ችሎ መቆም ስለማይችል እና ሙሉም ስላልሆነ ሊቀነሱ አይገባም።

 • ፊደላቱ ቢቀነሱ በሚወክሉት ሚስጥራዊ ቁጥር መዛባት የተነሣ የመለኮትን አላማና ሚስጥር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለመረዳት ስለሚያስቸግረን ሊቀነሱ አይገባም የሚል ነው።

ሙግትና የፊደላቱ የቁጥር ውክልና

አስረስ የኔሰው በካም መታሰቢያ መጽሐፋቸው ውስጥ አጠንክረው ከሚያቀርቡት ሙግት ዋናው ነገር የፊደላቱ የቁጥር ውክልና ነው። በሳቸው አገላለጽ የግእዝ ፊደላት ቁጥራቸው 26 ሲሆን እያንዳንዱ ግእዝ የሆነው ፊደል በሰባት ድምፅ እየተነበበ በጠቅላላው 26×7=182 ሆሄያት ሲኖሩት ሚስጥር የሚተነተንበት ጠቅላላ ቁጥሩ 800 ሆኖ 5,600 ደግሞ የጠቅላላው ፊደላት የቁጥር ውጤት ውክልና ተሰጥቶት ይገኛል።

 “የመሐንዲሶች ሁሉ አባት የሆነው እግዚአብሔር ዓለሙን ሲፈጥረው በቁጥር ልክ ስለፈጠረው ሁሉም ፍጥረት ልክ ሆኖ ተገኝቷል። ይህም የመለኮት ሚስጥር ተደብቆ የሚገኘው በግእዝ ፊደልና ቁጥር ውስጥ ነው” ይላሉ አስረስ የኔሰው።

በአዳምና በኢየሱስ መካከል ያለውን ሚስጥራዊ አንድነት በግእዝ ፊደል ቁጥር ሲያስረዱም “አዳም የሚለው ስም በሚስጥራዊ ቁጥር ሲሰላ 144 ቁጥር ይሰጠናል። አ 40 + ደ 100 + መ 4 = 144 ኢየሱስ የሚለውም በቁጥሩ ሲሰላ አ 40 + የ 90 + ሰ 7 + ሰ 7 = 144 ይሆናል። ይህ ቁጥር በሰው ልጆች እጅ ላይ ታትሞ ይገኛል። በኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ 17 ላይ የተጠቀሰውን የአብርሃምን እና የሣራን የስም ለውጥ አንስተው ስለሚስጥሩ ሲጽፉ እንዲህ ብለዋል።

 “እግዚአብሔር አብራምን ወደ አብርሃም ሦራ የሚለውን ወደ ሳራ ስም የቀየረበት ምክንያት ሚስጥር ስለነበረው ነው። የቀደመው አብራም የሚለው ስም በቁጥር ሲሰላ አ 40 + በ 9 + ረ 6 + መ 4 = 59 ነበር ይህ ቁጥር ለ60 አንድ ቁጥር የጐደለው ነበር። 60 ቁጥር መሠረት ስለሆነ ለ5 ሲካፈልም ውጤቱ 12 ስለሚሆን አብርሃም የ12ቱ ነገደ እስራኤል አባት ይሆን ዘንድ አስቀድሞ ሲጠራው ስሙን በመለወጥ “አብርሃም“ ብሎታል። ይህም አ 40 + በ 9 + ረ 6 + ሀ 1 + መ 4 = 60 ይሆናል። ይህ ስም ከዚህ ፊደል ጋር ተመሳጥሮ ተለውጧል እንጂ ዝም ብሎ አልተቀየረም። የሦራም ስም ወደ ሳራ ሲለወጥ ከቁጥሩ ጋር ግንኙነት አለው። በንጉሱ ሠ የተፃፈው በቁጥር ሲሰላ “ሠ“ 5 + ረ 6 = 11 ሲሆን ሳራ የሚለው ሲሰላ ሰ 7 + ረ 6 = 13 ቁጥር ይሰጠናል። ይህ ቁጥር የሰላም ቁጥር ነው። ሰላም የሚለውን በግእዝ ሚስጥራዊ ቁጥር ስናሰላው ሰ 7 + ለ 2 + መ 4 = 13 ይሆናል። በተጨማሪም የሰላም አምላክ የሆነው እየሱስ ክርስቶስ ከ12ቱ ሓዋርያት ጋር 13ኛ ሆኖ ወንጌልን አስተምሯል። የመጀመሪያዋ ሄዋንም ቁጥሯ 13 ነው። የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ “ለምን ይቀነሳሉ?” በሚለው መጽሐፍ ውስጥ ቁጥሮቹን አስመልክቶ ሰፊ ትንተና የሰጠበት ስለሆነ ለተጨማሪ ግንዛቤ መጽሐፉን ፈልጐ ማንበብ ይቻላል።

 በየዘመኑ የተነሱ መንግሥታትስ ምን አሉ ?

በአክሱም ስርወ መንግሥት ውስጥ የነበሩት ዐፄ ገብረመስቀል ከቅዱስ ያሬድ ጋር ተባብረው የፊደላቱ የአጻጻፍ ሥርአት በአግባቡ እንዲሆን አዋጅ አውጥተዋል። በ17ኛው ክፍለ ዘመን በሠለሞናዊው ስርወ መንግሥት የሚገኙት ዐፄ በካፋ ደግሞ እጅ እስከሚያስቆርጥ የሚደርስ ቅጣት ሊፈፅሙ እንደሚችሉ በአዋጅ አስነግረዋል። በኋላ ግን ሚስዮናውያኑ በ1889 ይህንን አዋጅ ጥሰው ፊደላቱን ያለአግባብ በመጠቀምና በመቀነስ መጽሐፍ ካሣተሙ በኋላ ጉዳዩ እየከረረ መጥቶ ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ላይ ደርሶ ነበር። በእርሳቸው ዘመን ሞክሼ ሆሄያት ፊደላትን አስመልክቶ ብርቱ ክርክር ተደርጓል። በአቶ አበበ ረታ “ይቀነሱ“ ባይነት እና በእነ መንግስቱ ለማ “አይቀነሱም“ ባይነት ጉባኤ ተሰይሞ ምሁራን ታድመው ክርክሩ በቃለጉባኤ እየተመዘገበ ሲደረግ ቆይቷል። ሆኖም አንዳች የፀና ውሳኔ ሳያገኝ ጉዳዩ ወደ ደርግ ዘመነ መንግስት ተሸጋግሯል። በዚህም ጊዜ ፊደላቱ የመቀነስ እጣ ፈንታቸው ላይ ጥያቄ ተነስቶ ነበር።

“በሩሲያ አብዮት ወቅት የፊደል ለውጥ ተደርጓል። እኛም እነሱን ተከትለን ወደ ሶሻሊዝም የምንጓዝ ስለሆነ እነዚህ አላራምድም እና አላሰራም ብለው ቀይደው በያዙን ፊደላት ላይ ቆራጥ ውሣኔ ማድረግ አለብን” ተብሎ ዕጣ ፈንታቸው “ለቆራጡ መሪ” ለጓድ መንግስቱ ኃ/ማሪያም ተላልፎ ነበር። እሳቸው ግን ጊዜ ስላላገኙ ጉባኤ ሰይመው አከራክረው የሰጡት ውሣኔ ሳይኖር በዘመነ ኢሕአዴግ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው የቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ተቋም ባልተሰጠው ስልጣን ፊደላቱ እንዲቀነሱ ውሣኔ አሳልፎባቸዋል።

 የተቋሙ ምክንያቶች

1. የአማርኛ ፊደል ለሥራ ምቹ ስላልሆነ በአሁኑ ፊደል በተቀላጠፈ መንገድ የአማርኛ መዝገበ ቃላትን ለመፃፍ የማይመች እና ለጽሕፈትም መኪና / ታይፕ ራይተር/ የማይመች፣ ተነባቢው ተለይቶ ባለመጻፉ እና በአማርኛ የሥነ ጽሑፍና የሥነ ልሳን ጥናት ሣይንሳዊ በሆነ መንገድ ለማካሄድ ስለሚያስቸግር፣

 2. አሁን የሚሰራበት ፊደል አማርኛን መደበኛ ለማድረግ አስቸጋሪ ስለሆነ፣

3. በአማርኛ አጻጻፍ ጊዜ በመኪና የሚጻፈው እና በእጅ የሚጻፈው ስለማይለይ፣

 4. ቋንቋው ካለው ድምፅ ጋር ሲመዘን ትርፍ ሆሄያት ስላሉበት፣

 5. ወደ አማርኛ ለሚገቡ ቃላት መቅጃ በቂ ሆሄያት ስለሌሉት፣

6. የሚጠብቁና የሚላሉ ድምፆች በአንድ ዓይነት ሆሄያት ስለሚጻፉ በሚል ምክንያት በአማርኛ ስም ግእዝ ከሆነው ፊደል ገበታ ላይ “ሐ” “ኀ” “ሠ” “ዐ” “ጸ” ተቀንሰው ወጥተዋል። ለብዙ ዘመናት የነበረው ክርክር ከሚሲዮናውያኑ ቀጥሎ የቋንቋ ተቋሙ በፊደላቱ ላይ ይህንን ውሣኔ ሰጥቷል።

በውሣኔው ላይ እነማን ምን አሉ?

በ1995 ዓ.ም. ይህ ውሣኔ እንደታወቀ ከየትኛውም በተለየ እና በተሻለ መልኩ የሐመር መጽሔት ብዙ ሰዎችን በማነጋገር ውሣኔው በሕዝቡ ዘንድ እንዲታወቅ ጥረት አድርጓል።

 በግንቦት/ሰኔ 1995 ዓ.ም. እትሙ መጽሔቱ ያነጋገራቸው ሊቀካህናት ክንፈገብርኤል አልታዬ ውሣኔው ያሳዘናቸውና ዩኒቨርሲቲውም ቋንቋውን የመቆነጻፀል እና በአማርኛም ሆነ በግእዝ ከፍተኛ አገልግሎት ያበረከቱትን ፊደላት ማውደም ስልጣኑ አለመሆኑን ጠቅሰው፤ “ይህ ድርጊት ብዙ ጥፋት የሚያመጣና የትርጉም መፋለስ የሚያስከትል፣ ትውልዱም አባቶቹ ጽፈውለት ያለፉትን መንፈሳዊም ሆነ ማኀበራዊ ይዘት ያላቸውን መዛግብት አንብቦ ሊረዳ አይችልም“ በማለት በሰፊው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

 መጽሔቱ በነሐሴ/መስከረም 1997 ዓ.ም. ዕትሙም የፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሀቅን አስተያየት ይዞ የወጣ ሲሆን፤ እሳቸውም በሰጡት አስተያየት “የእግዝ ፊደላት መቀነስ አለባቸው የሚሉ አስተማሪዎችን አንጐል መቀየር አለብን። ፊደላቱ በድምፅ አንድ ቢመስሉም የሚለያዩበት ሁኔታ አለ። ስለዚህ የቋንቋዎቹን ሁሉ ንግግር ለማዳመጥ ፊደላቱን መጠበቅ አለብን። መቀነሱ እና አንዱን ለሁሉ መጠቀሙ የትርጉም ፍልሰት ያመጣል“ ብለዋል።

 በዚሁ መጽሔት ላይ አስተያየት የሰጡት አቶ አስፋው ዳምጤም “ውሳኔ የሰጠው የቋንቋዎች አካዳሚ ውሣኔውን ለማስተላለፍ እና ፊደሉን ለመቀነስ ምንም የተሰጠው ሕጋዊ ስልጣን የለውም። ስለዚህ ሕጋዊ የሆነ ውሣኔም የለም“ ብለዋል።

መሪጌታ አእምሮ በሪሁን “የኢትዮጵያ ፊደል ታሪክና ክፍለ ዘመን“ በተሰኘ መጽሐፋቸው ውስጥ ውሳኔ የተላለፈባቸው ፊደላት እውነት ቢሆኑ በያሬዳዊው የዜማ ስልትና ምልክት ላይ የሚያደርሱት ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን በመግለፅ የችግሩን አይነት በሰንጠረዥ ዘርዝረው አቅርበዋል።

 የዚህም ጽሑፍ አዘጋጅ በ2009 ዓ.ም. ለህትመት ባበቃው “ለምን ይቀነሳሉ?“ በሚለው መጽሐፍ ውስጥ በተለይ ፊደላቱ የያዙትን የቁጥር ውክልና በሰፊው በማየትና የላሊበላንና የአክሱም ሀውልቶችን ምንነት ከቁጥሩ ጋር በማነፃፀር “ሊቀነሱ አይገባም“ በሚል ተሟግቷል።

 ካሕሣይ ገ/እግዚአብሔር “ምስጢረ ፊደል ወትርጓሜሁ“ በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ የፊደላቱን ምንነትና ትርጉም አስመልክተው በሰፊው አትተዋል። ለዘመናት ሲቀጥል በመጣው ሙግት ውስጥ የራሳቸውን ሚና አበርክተዋል።

በመሆኑም ፊደላችንን አስመልክቶ የተነሱ ክርክሮች እና የተሰጡ ውሣኔዎች በአብዛኛው ሕዝብ ዘንድ በግልፅ የማይታወቁና በአጻጻፍ ጊዜም ቢሆን ልዩነታቸው ተለይቶ ግልፅ በሆነ ሁኔታ ባለመለየቱ በከተማችን ውስጥ በሚሰቀሉ ማስታወቂያዎች ላይ ብዙ ስህተቶች ሲፈፀሙ ይታያል። ስህተቶቹን አውቆና ተረድቶ የሚያርም አካል ባለመኖሩና ትውልዱም ለፊደላቱ ያለው ግምት ዝቅ ያለ በመሆኑ ይባስ ብሎም “ትርፍ ናቸው፤ አያስፈልጉም“ በማለት እንዲቀነሱ በመሟገት ላይ ይገኛል።

 ዛሬ ፈር ያልያዘ ጉዳይ ለቀጣዩ ትውልድ ከባድ የቤት ስራ ይሆናል። ዋጋ ያስከፍላል። ለዚህ ጽሑፍ ይሰጣሉ ብዬ በማስባቸው ህብረ- መልሶች እልባት ላይ ሊያደርሱን የሚችሉና ምክንያታዊ የሆኑ ነጥቦች ይፈልቃሉ ብዬ እተማመናለሁ። ኃላፊነት አለብን የምትሉ ተቋማትና ግለሰቦች በሉ አንድ በሉ! 

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top